ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ

መግቢያ!

አብዮቱ ከፈነዳ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ ህዝባችን ሰላምና እረፍት ማግኘት አልቻለም። አብዮቱ ሲፈነዳ፣ የንጉሳዊ አገዛዝ ሲፈርስ፣ የሱ መሰረት የሆነው የፊዩዳሉ ስርዓት ሲደመሰስ ሰፊው ህዝብ የነፃነት ብርሃንን የማየት ዕድል አጋጥሞት ነበር። እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ ነፃነትን በመጎናጸፍ እንደቆመበት የህብረተሰብ ክፍል የየራሱን ማህበራዊ ተቋም መመስረት ችሎ ነበር። ይሁንና ግን ይህ የተጎናጸፈው ድልና የተስፋ ብርሃንን ማየት ከውስጥ ከዚህና ከዚያ ብቅ ባሉ ድርጅቶች፣ ግን ደግሞ ዕውነተኛ ዓላማቸው በማይታወቅ ኃይሎች በመወጠርና ጦርነት ውስጥ እንዲገባ በመገደዱ አገሪቱ እስካሁን ድረስ ጋብ ሊል ያልቻለ ትርምስ ውስጥ እንድትወድቅ ተገደደች።

በመሰረቱ አብዮቱ ሲፈነዳ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችና፣ እንዲሁም ደግሞ በብሔረሰብ ነፃነት ስም የሚታገሉ ድርጅቶችን ጥያቄዎች መመለስና ማስተናገድ የሚችል ነበር። እንደሚታወቀው በአገራችን ምድር የዲሞክራሲ መብትና የመሬት ለአራሹ ጥያቄዎች ሲነሱና እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ መልስ ሊሰጣቸው ሙከራ ሲደረግ፣ የጥያቄዎቹ አነሳሰም ሆነ ተግባራዊ የማድረጉ ጉዳይ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነውን ህዝባችንና ልዩ ልዩ ድርጅቶችንም የሚያካትትና በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለመተርጎምና ቀስ በቀስ ነፃነትን ለመቀዳጀት የሚያስችል ሂደት ነበር። ይሁንና ግን የአብዮቱ መፈንዳት፣ የንጉሳዊው አገዛዝና የሱ መሰረት የሆነው የፊዩዳል ስርዓት መገርሰስና ልዩ ልዩ የጥገና ለውጦች ቀስ በቀስ ተግባራዊ መሆን ከረጅም ጊዜ አንፃር ሲታይ ዕድገትንና ነፃነትን ሊያመጣ የሚችለውን አካሄድ ያልተገነዝቡ ኃይሎች በመሰረቱ በወታደራዊ አገዛዙ ላይ ሳይሆን በህዝባችን ላይ በመዝመት አገራችንን ትርምስ ውስጥ ለመክተት ችለዋል። ከሰላሳ ዓመታት በላይ በየቦታው የተካሄደው ጦርነት አገሪቱን ውጥረት ውስጥ መክተቱ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሰውና የሀብት ውድመት እንዲፈስ አድርጓል። ካለማወቅና በሰፊው ካለማሰብ የተነሳ ከዚህ ብሔረሰብ ነው የመጣሁት፣ ስጨቆን ነበር ፣ ስለዚህም የምፈለገው ሌላ ነገር ሳይሆን „ነፃነቴን“ ብቻ ነው በማለት የተካሄደው እልክ አሰጨራሽና የወንድማማቾች ርስ በርስ መተላለቅ አገራችን ዛሬ ላለችበት አስከፊና እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ከፍተኛውን አስተዋፅዖ አድርጓል ማለት ይቻላል።

በአገራችን ምድር ከሃያ አምስት ዓመታት ጀምሮ ስልጣን ላይ ቁጥጥ ያለውና፣ የአገራችንና የህዝባችንን የመኖርና ያለመኖር ዕድል የሚወሰነው የወያኔ አገዛዝ በቡሃ ላይ ጆሮ ደግፍ ተጨምሮበት እንደሚባለው አነጋገር አገራችንን በብሔረሰብ በመከለልና የክልል ፖለቲካ ተግባራዊ በማድረግ ህዝባችን በአንድነት ተነሳስቶ በጋራ አገሩን እንዳይገነባ አድርጎታል። የሚሆነውን የማይሆነውና፣ ከታሪክ ጋር ግኑኘት የሌላቸውን ነገሮች በማውራትና የጥላቻ መርዙን በመርጨት ምስኪኑ ህዝብ ርስ በርሱ እንዳይተማመን አድርጓል። በተለይም ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮና ይህን ዐይነቱን የከፋፍለህ ግዛና የጥላቻ ፖሊሲ ሲያዳምጥ ያደገ ወጣት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ላይሰማው ይችል ይሆናል። ስለሆነም ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ብሔረሰብ ነው የመጣሁት በማለት ርስ በርሱ እንዳይግባባና በጎሪጥ እንዲተያይ ለማድረግ ተችሏል። በመሆኑም አብዛኛው ወጣት የመለያ ቀውስ(Identity Crisi)እንዳለበት ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በእርግጥም ወያኔ ስልጣን ከጨበጠ ጀምሮ ለተወለደ ልጅና በወያኔ የትርምስ ፖለቲካ ውስጥ ላለፈና ጭንቅላቱ ውስጥ ካካተተ ወጣት የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ሊምታታበት ይችላል። በተለይም ደግሞ በምድር ላይ የሚታየው የኢኮኖሚና የማህበረዊ ጉዳይና የተወሰነውም የህብረተሰብ ክፍል በገንዘብ መናርና መባለግ አዲስ ታዳጊ ወጣት ስለህብረተሰብና ስለኢትዮጵያዊነት ምንነት ሊምታታበት ይችላል። በዚህም የተነሳ በብዙዎቻን ዘንድ የሚነሳው ጥያቄ የአገራችንና የህዝባችን የወደፊት እጣ ምን ይሆናል? ኢትዮጵያስ ባለችበት መልኳ ልትቀጥል ትችላለች ወይ? ወይስ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እንደሚታየው በአገራችንም ምድር የእርስ በርስ መተላለቅ በመከሰት አገራችን አሁን ባለችበት መልኳ ልትቀጥል ትችላለች ወይ? የሚለው ነገር እያሳሰበን መጥቷል። የነገሩን አሳሳቢነት ለመረዳት አንዳንድ የተሳሳቱና ከታሪክና ከህብረተሰብ ግንባታ ጋር ሊያያዙ የማይችሉ ነገሮችን በማንሳት ዛሬ አገራችን ለምን ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ላይ ለመድረስ እንደቻለች ለመወያየት እንሞክር።

የህብረ-ብሔር ምስረታ አስፈላጊነትና የብሔረሰብ ጥያቄ ጉዳይ በአጠቃላይ!

እንደሚታወቀው በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ብሔረሰቦች የሌሉበት አገርና የተለያዩ ብሔረሰቦች ሳይጋቡና ሳይዋሃዱ እያንዳንዱ ብሔረሰብ በራሱ ክልል ብቻ ተወስኖ የኖረበት ማህበረሰብ በፍጹም የለም። የሰው ልጅ ውስጣዊ ኃይል(Dynamism) ስላለው በአንድ ቦታ ረግቶ ሊኖር በፍጹም አይችልም። በተለይም በአንድ አካባቢ የስራ-ክፍፍልና ገበያ የሚባሉት ነገሮች ሲዳብሩ፣ የዚህ ወይም የዚያ ጎሳ ተወላጆች ከሌላ አካባቢ በመምጣት የተቀረው እዚያ በመጋባትና በመዋለድ፣ እንዲሁም አዲስ የስራ ባህል ሲለምድና ገቢ ሲያገኝ ድሮ ከነበረበት የጎሳ ወይም የብሔረሰብ ስንሰለት በመላቀቅ የአስተሳሰብ አድማሱ ይሰፋል። እንደዚህ ዐይነቱ የህዝብና ወይም የግለሰቦች እንቅስቃሴ የማይታየው ወይም በጥቂት ብቻ የሚካሄደው በከብት አርቢነት ሙያ በሚተዳደሩና፣ ዘላን እየተባሉ በሚጠሩ ጎሳዎች ዘንድ ነው። የእንደነዚህ ዐይነት ጎሳዎች እጣ ደግሞ እግዚአብሔር የሰጣቸውን የመፍጠር ኃይል ለመጠቀም አለመቻል ብቻ ሳይሆን፣ በተለያየ ጊዜ ከተፈጥሮ በኩል የሚመጣባቸውን አደጋ መቋቋም አይችሉም። ህይወታቸውም ተደጋጋሚና አሰልቺ ሰለሚሆን የመፍጠር ኃይላቸው ውስን በመሆን አዳዲስ መሳሪያዎችን በመስራት ኑሮአቸውን መልክ ሊሰጡትና ወደ ተሻለ የአኗናር ስልትና ዕድገት ደረጃ ላይ ሊሸጋገሩ በፍጹም አይችሉም።

በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ሆኖ በአንድ ክልል ውስጥ ከሚኖሩት ውስጥ፣ እስከዚህም ድረስ በአንድ ቋንቋም ሆነ በባህል ካልተሳሰሩት ውስጥ አንደኛው የህብረተሰብ ክፍል ወይም ጎሳ በባህል፣ ቋንቋን በማዳበርና የአገዛዝ መዋቅርን በመዘርጋትና፣ በመጀመሪያ ደረጃ በአካባቢው ያለውን የጥሬ-ሀብትንና መሬትንም ጭምር በመቆጣጠር ከራሱ የተውጣጡ ብሔረሰቦችንም ወደ መበዝበዝ ያመራል። ግብር(tribute) እንዲከፍሉ ያስገድዳል። የተወሰነውንም ለጦር በመመልመል ከውጭ የሚመጣበትን ወራሪ ኃይል መክቶ በመመለስ የበላይነትን ይቀዳጃል። በአካባቢው ሌላ አገዛዘ እንደዚህ ካለ በጉልበት ለማስገበር ይሞክራል፤ ወይም በመጋባትና ርስ በርስ በመተሳሰር አገዛዙን ያስፋፋል። በህብረተሰብ ውስጥ በሚደረግ ማህበራዊ እንቅስቃሴ(Social Mobility) በተለይም በንጉስ መልክ በተዋቀረ አገዛዝ ከአንድ ጎሳ ብቻ በመውጣጣት የበላይነቱን ይዞ ሊቆይ አይችልም። ከአንድ ጎሳ የተውጣጣ አገዛዝ ወይንም ኤሊት በጎሳው ላይ የበላይነቱን ይዞ ሊቆይ የሚችለው በክላን በሚተዳደርና ገና ባልተሰበጣጠረና(Undifferenciated or non-segmented) በስራ-ክፍፍል ባልዳበረ ማህበረሰብ ውስጥ ብቻ ነው። ስለሆነም በንጉስ መልክና በፊዩዳላዊ ስርዓት ስር በተዋቀረ አገዛዝ ውስጥ ባለው ቅራኔና ሬሶርስን ለመቆጣጠር በመፈለግ የተነሳ በተለያየ አካባቢ የሚገኙ ከተለያዩ ንዑስ-ጎሳዎች የተውጣጡ የገዢ መደቦች ርስ በርስ በመጋባት የጎሳ ውስንነት ቀስ በቀስ ይደመሰሳል።

ይህ ዐይነቱ ከተለያየ አካባቢ የተውጣጡ የገዢ መደቦች ርስ በርስ መጋባትና የአገዛዝ መዋቅርን ማስፋፋት በአውሮፓ ምድር የተሰፋፋና የተለመደ ነበር። በተለይም በእንግሊዞችና በፈረንሳዮች የገዢ መደቦች መሀከል መተሳሰርና መጋባት ነበር። በሌላ ወገን ደግሞ በዕድገትና በአስተዳደር ቀድመው የሄዱ ግን ደግሞ ገና ወደ ህብረ-ብሔር(Nation-State) ደረጃ ላይ ያልደረሱ አገሮች፣ ሌሎች በዕድገት እስከዚህም ያልገፉ አገሮችን በመውረር ህልውናቸውን ለመደንገግ በቅተዋል። ጀርመን እ.አ በ1871 ዓ.ም በአንድ ግዛት ውስጥ ከመጠቃለሏ በፊት በስዊደን፣ በዴንማርክ፣ በአውስትሪያና በፈረንሳይ ተደጋጋሚ ጦርነት ተከፍቶባትና እስከተወሰነ ጊዜያትም ድረስ በተለይም የተወሰነው የጀርመን ክፍል በፈረንሳይ አገዛዝ ቁጥጥር ስር ነበር። እንደዚሁም እንግሊዝ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ የሆነውን የሰሜኑን አየርላንድ ህዝብ በማስገደድ የተወሰነው አልቀበልም ሲል ደግሞ ከመሬቱ በማፈናቀልና ተከታይ የሆናቸውን የስኮቲሽንና እንግሊዛዊያንን በማስፈር የኋላ ኋላ አየርላንድ የካቶሊክንና የፕርቴስታንት ሃይማኖት ዕምነትን በሚከተሉ በመከፋፈል አንድ ጎሳ በሃይማኖት የተነሳ ሊለያይ በቅቷል። በጊዜው የእንግሊዝ ዋና ዓላማ የስራ ኃይል ለመፈለግና የአየርላንድንም ሪሶርስን ለመቆጣጠር ስለነበር የተከተለው ዘዴ አንድን ህዝብ በሃማኖት መከፋፈልና እንዲጠላሉ ማድረግ ነበር። የኋላ ኋላ ልዩነቱ እየከፋ በመሄድ አንድ ወንድማማች ህዝብ ርስበርሱ ለረጅም ዓመታት እንዲጨራረስ ተደረገ። የአውስትሪያው የሀብስበርግ ሞናርክያዊ አገዛዝም የተለያዩ ጎሳዎችን በጉልበት በማጠቃለል ነበር በአንድ በኩል አገዛዙን ለማሰፈን የቻለው። በሌላው ወገን ደግሞ ከረጅም ጊዜ አንፃር ሲታዩ ለህብረ-ብሔር ምስረታ ሊሆን የሚችል መስረት በወረረባቸው አገሮች ውስጥ በመጣል እንደ ሀንጋሪ የመሳሰሉ አገሮች ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የበቃው። የሀብስበርግ ሞናርኪያዊ አገዛዝ ከተደመሰሰ በኋላ አውስትሪያ ወደ ሪፑብሊክነት በመሸጋገርና አገዛዟን ውስን በማድረግ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሰፈነባት አገር ለመሆን በቃች። ዛሬ የምናየውንም የዕድገት ደረጃ ላይም ለመድረስ በቃች። በዚህ ዐይነቱ ተሻልን የሚሉ አገዛዞች ባደረጉት ጦርነትና መስፋፋት የግዴታ በህዝቦች ዘንድ መቀላቀልንና መዋለድን አስከትሏል።

በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የህብረ-ብሔርን ወይም በአንድ አገዛዝ መጠቃለልንና የሪፑብሊክን መመስረት ልዩ የሚያደርገው፣ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በተለያዩ ኤፖኮች ጭንቅላትን የሚያድስ ምሁራዊ እንቅስቃሴዎች መካሄዳቸው ነው። በተለይም በጣሊያን ምድር ሬናሳንስ የሚባለው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ከመከሰቱ በፊት የኢጣሊያን ህዝብ አንድ የሚግባባበት ቋንቋ ስላልነበረውና፣ ለዕድገት አስቸጋሪም ስለነበር ዳንቴ የሚባለው ፈላስፋ ህዝቡ የሚግባባበትን አንድ ቋንቋ በመፍጠርና ተግባራዊ በማድረግ ለሬናሳንስ እንቅስቃሴ ተቀዳሚ ስራ በማዳበር እምርታ ሊሰጠው ችሏል። ሬናስንስ የሚባለው እንቅስቃሴ ሲጀምር፣ ሲስፋፋና ሲዳብር የዕደ-ጥበብ ስራ፣ ንግድና የከተማ ግንባታዎች በመስፋፋት ህዝባዊ እንቅስቃሴ በመዳበር ተሰበጣጥሮና በተለያየ ጎሳ ተከፋፍሎ ይኖር የነበረው የኢጣሊያን ህዝብ በመሰባሰብ የስልጣኔ ባለቤት ሊሆን ችሏል። ይሁንና ግን ከካቶሊክ እምነት ለመላቀቅ ያልቻለው የኢጣሊያን ህዝብ በካቶሊክ የገዢ መደቦችና በቀሳውስት በመሰቃየት እንደ እንግሊዝና፣ ሆላንድ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ እንደ ፈረንሳይና ጀርመን ሙሉ በሙሉ ሪፑብሊክን በመመስረት አንድ ህዝብ ሊሆን አልቻለም። ከውስጥ በነበረው የገዢ መደቦች ሽኩቻ የተነሳ ጣሊያን በወጭ ኃይሎች ልትወረርና በሪናሳንስ አማካይነት የተቀዳጀችውን ስልጣኔ በጠቅላላው በጣሊያን ምድር ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አልቻለችም። ይህ ዐይነቱ ልዩነት እስከዛሬም ድረስ በተለይም በሰሜኑና በደቡቡ ኢጣሊያን ክፍል መሀከል ጎልቶ የሚታይ ሀቅ ነው።

ወደ ሌሎች አገሮች ስንመጣ የህብረ-ብሔር ምስረታ የተለያየ መልክ የያዘ መሆኑ እንረዳለን። የእንግሊዚን የህብረ-ብሔረሰብ አመሰረራት ለየት የሚያደርገው፣ የህብረ-ብሔረሰብ ምስረታው ሳይንስና ቴክኖሎጂን የዕድገት መሰረት ለማድረግ በሚፈልጉት የፕሮቴስታንት መሪዎችና፣ ሳይንስንና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም አጠቃላይ ዕድገት እንዳይኖር በሚቃወሙት በካቶሊክ እምነት ተከታዮች መሀከል የተካሄደ የጦፈ ትግል ሲሆን፣ በተጨማሪም በመሬት ከበርቴው፣ በአሪስቶክራሲውና በሌላ ወገን ደግሞ እያደገ በመጣው የኢንዱስትሪና የንግድ ከበርቴ መሀከል ነበር። የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮችና ቄሶች፣ የመሬት ከበርቴዎችና አሪስቶክራሲው የነበራቸውን ስታተስ ላለማጣት ሲሉ ለውጥ እንዳይመጣ አግደው ይዘው ነበር። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንግሊዝን አንድ ወጥና ጠንካራ መንግስት ሆና እንዳትወጣ አግዶ ሲይዛት፣ እንግሊዝ ሀብቷን ወደ ሮም ላለው የካቶሊክ አገዛዝና ስፔይን የምታስተላልፍ ነበርች። ይህ ሁኔታ በዚህ መቀጠል እንደሌለበት የተረዱት የቱዶር ሞናርኪዎች ሃይንሪሽ ሰባተኛውና ስምንተኛው፣ በተለይም በሬናሳንስ ዕውቀት የሰለጠነው ሃይንሪሽ ስምንተኛው የእንግሊዝ ንጉስ በሮሙ የካቶሊክ ሃይማኖት ህግ የሚገዛ ሳይሆን በራሱ እንደሚገዛና ነፃም እንደሆነ በማወጅ የመጀመሪያውን የካቶሊክን ሃይማኖት የበላይነት ዕምነት ይሰብራል። ይሁንና ግን አብዮቱ እስከፈነዳበት እስከ 1642-1651 ዓመት ድረስ የፊዩዳሉና የአሪስቶክራሲው መደብ የበላይነት ያያለበትና ለዕድገትም እንቅፋት በመሆኑ የጥገና ለውጥ በሚፈልጉት ፓርሊያሜንታሪያንና በንጉሳዊ አገዛዝ ተከታዮች ዘንድ የጦፈ ጦርነት በመካሄድ ለመጨረሻ ጊዜ የካቶሊክ ሃይማኖት የበላይነት በመሰበር የከበርቴውን መደበ የበላይነት ይረጋገጣል። ለማኑፋክቱር አብዮት እንዲያም ሲል ለካፒታሊዝም ዕድገት የሚያመች ሁኔታ ይፈጠራል። ይህ የጥገና ለውጥና ከዚያ በኋላ የማኑፋክቱር አብዮት መካሄድና የገበሬው መደብ ከመሬት እየተፈናቀለ መምጣትና ወዝአደር መሆን የእንግሊዝ ህዝብ እንዲሰበጣጠርና በአንድ አገዛዝ መዋቅር ስር እንዲጠቃለል አድርጎታል። በሌላ አነጋገር ለአንድ ህብረ-ብሔር ምስረታና ለካፒታሊም ዕድገት እንቅፋት የነበረው የካቶሊክ ሃይማኖትና የመሬት ከበርቴውና አሪስቶክራሲው፣ እንዲሁም የበላይ ጠባቂያቸው የሆነው ንጉሳዊ አገዛዝ ከተደመሰሰ በኋላ ነው እንግሊዝ ቀስ በቀስ ወደ ኢንዱስትሪ አብዮትና ወደ ካፒታሊዝም ዕድገት ለመሸጋገር የቻለቸው። በዚህም አማካይነት ነው ወደ ህብረተሰብ ምስረታ ልታመራ የቻለችው።

ወደ ጀርመን ስንመጣ ጀርመንም እስክ 1871 ዓ.ም ደረስ ከሶስመቶ በላይ በሚቆጠሩ መሳፍንት የምትተዳደርና በውጭ ወራሪ ኃይሎች የምትሰቃይ ነበረች። ይህ በዚህ መቀጠል እንደሌለበት የተረዳው የፕረሺያ የንጉሳዊያን አገዛዝ አልገዛ ያሉትን በኃይል በመውረር፣ ሌሎችን ደግሞ በጥቅም በመግዛት የመጨረሻ መጨረሻ ወደ አንድ ግዛትነት ልታመራ ችላለች። ማርቲን ሉተር መጽሀፍ ቅዱስን እስካተመበትና የፕሮቴስታንትን ሃይማኖት እስካወጀና የህዝቡ የማሰብ ኃይል በትምህርት አማከይነት መዳበር አለበት ብሎ መስበክ እስከጀመረበት ድረስ ጀርመንም በጎሳና በሃይማኖት የተከፋፈለች ነበረች። መጽሀፍ ቅዱስ ወደ ጀርመንኛ ቋንቋ ሲተረጎምና አድባራት የሃይማኖት መማሪያ ተቋሟት መሆናቸው ቀርቶ ወደ ህዝብ መማሪያነት ሲለወጡ የህዝቡ ኃይል መሰብሰብና የማሰብ ኃይሉም መዳበር ይጀምራል። የመፍጠር ችሎታውም ያድጋል። በዚህ አማካይነት የፕሮቴስታንት ሃይማኖት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የንግድ እንቅስቃሴና የዕደ-ጥበብ ሙያዎች ይዳብራሉ፤ ይስፋፋሉም። በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ ቀደም ብሎ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት የተስፋፋባቸው አካባቢዎች የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ከሆኑት አካባቢዎች ጋር ሲወዳደሩ በዕውቀትም ሆነ በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በንግድ እንቅስቃሴና ከተማዎችን በመገንባት በብዙ እጅ ቀድመው እንደሄዱ ነው። ይሁንና ግን አገሮች በአንድ ግዛት ውስጥ ሲጠቃለሉ ሁሉም አካባቢዎች ወይንም ክፍላተ-ግዛቶች የግዴታ አንድ ወጥ ትምህርትንና ተመሳሳይ የሆኑ ለቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያመቹ ሙያዎች ዕውቀቶችን በመቀበል ዕድገታቸው ተመጣጣኝ እየሆነ ሊመጣ ችሏል።

በአጠቃላይ ሲታይ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የህብረ-ብሔረስ ምስረታ፣ በአንድ በኩል በተለያየ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ሲደደገፍና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ በኢንዱስትሪ አብዮትና በንግድ አማካይነት መልክ ሲይዝ፣ አስቸጋሪ በሆነባቸው ቦታዎች ኃይል ወሳኝ ሚናን መጫወት ችሏል። በተለይም ከሰላሳኛው ዓ.ም ጦርነት የካቶሊክና የፕሮቴስታንቶች ሃይማኖት ጦርነት በኋላ እ.አ በ1648 ዓ.ም የህብረ-ብሔር ምስረታ ተቀባይነት በማግኘት አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮች ብሔራዊ ነፃነታቸውን ለማስከበርና ወደውስጥ ደግሞ መረጋጋትን ለማስፈንና ህዝቡን በአንድ ባንዲራ ስር ለማጠቃለልና የዜጋዊ ስሜትነት እንዲሰማው ለማድረግ ወደ ውስጥ ያተኮረ የተቀነባበረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ግንባታ ማካሄድ ጀመሩ። በየአገሮች ውስጥ የናሺናሊዝም ስሜት በመዳበር ሁሉም አገዛዝ መጀመሪያ አገሬን ታላቅ አገር ማድረግ አለብኝ ብሎ በመነሳት ጥገናዊ ለውጥ ማካሄድ ጀመረ። በዚህም መሰረት ለነጋዴውና በማደግ ላይ ላለው የኢንዱስትሪ ከበርቴ እንክብካቤ በማድረግ የውስጥ ገበያ(Home Market) እንዲስፋፋ ለማድረግ በቃ። ከእንግዲህ ወዲያ ካፒታሊዝምና የህብረ-ብሔረሰብ ግንባታ የማይነጣጠሉ መሰረተ-ሃሳቦች ሆኑ። ከዚህ ዐይነቱ አጠር መጠን ያለ ትንተና በመነሳት ነው ዛሬ በአገራችን ምድር የተንሰራፋውን አገዛዝና የብሔረሰብ ጥያቄ ጉዳይ መረዳት የምንችለው።

የህብረ-ብሔር ምስረታ ሙከራና የብሔረሰብ ጥያቄ በኢትዮጵያ!

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ግዛት መሰረት የተጣለው ከአክሱም አገዛዝ በፊትና ከአክሱም አገዛዝ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል። ሁላችንም እንድምናውቀው የህብረተሰብ ታሪክ ተከታታይነት ያለውና፣(Evolutionary Process) ከአንድ ቦታ ጀምሮ ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች የሚስፋፋ ነው። የአክሱም ስልጣኔን ልዩ የሚያደርገው ከውጭ በመጣ ባህልና አስተሳሰብ ውስጠ-ኃይል ማግኘት መቻሉ ነው። በመጀመሪያ ግን የግዕዝ ቋንቋን አመሰራረት ስንመለከት፣ ቋንቋው እንደ ፊደል ከመቀረጹና ከማደጉ በፊት የገበሬው የመነጋገሪያ ቋንቋ ነበር። በጊዜው በነበረው ምናልባትም ዳማት በሚባለው ንጉሳዊ አገዛዝ ፊደል ሲቀረጽለት፣ የመጀመሪያዎቹ ፊደሎች ኮንሶናንት ነበሩ። እንደዛሬው የተራቡና በሁለት መቶዎች የሚቆጠሩ አልነበሩም። በአራተኛው ክፍለ-ዘመን የክርስትና ኃይማኖት ሲገባና በንጉስ ኢዛና የሚመራው ንጉሳዊ ቤተሰብ የክርስትናን ሃይማኖት ሲቀበል፣ በዚያው መጠንም የመጀመሪያው የግዕዝ ፊደል ቫውል ተጨምሮለትና ተስፋፍቶ በመነበብ ለቋንቋውና ለባህል ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት ቻለ። ከዚያ በኋላ የያሬድ ሙዚቃና የቤተክርስቲያን የሙዚቃ መሳሪያዎች በመፈጠርና በመዳበር ለባህላዊ ዕድገት ዕምርታ ሊሰጡት ችለዋል። ይሁንና ግን የአክሱም ስልጣኔ በዘጠነኛ ዓ.ም ንግስት ዮዲት ተብላ በምትጠራው የአገው ተወላጅ ሴት ሲደመሰስ የተቀረው ወደ ደቡቡ ክፍል በመሸጋገር እንደገና በአስራሁለተኛው ክፍለ-ዘመን በዛግዌ ዲናስቲ አማካይነት እምርታን በማግኘት ሊያብብ ችሏል። የሰሎሞናዊ ዲናስቲ በመባል የሚታወቀው እስከ አስራአራተኛው ከፍለ-ዘመን ድረስ ስልጣን ከመያዙና ከያዘም በኋላ ግዕዝ የአገዛዞችና የቤተክርስቲያን ቋንቋ ነበር። በሌላ በኩል አማራ እየተባለ የሚጠራው አብዛኛው ህዝብ ደግሞ የሚግባባበት ወይም የመነጋገሪያው ቋንቋው አማርኛ ስለነበር ግራ የተጋባው የንጉሳዊው አገዛዝ የግዕዝን ፊደል በመውሰድና በማሻሻል የአማርኛ ቋንቋ መጻፊያም በማድረግ፣ የንጉሱም ሆነ የተቀረው ህዝብ የመነጋገሪያ ቋንቋ እንዲሆን ያደርጋል። ጨ፣ ሸ፣ ኘ የሚባሉት ፊደሎች በመፈጠርና ከነበረው ፊደል ጋር በመዋሃድ ለአማርኛ ቋንቋ ማደግ እምርታን ይሰጡታል።

ይህ በእደዚህ እንዳለ የሰለሞናዊት አገዛዝ ፊዩዳላዊ የመሬት ስሪትን በማስፋፋት በገባርና በአስገባሪዎች መሀከል ያለውን ግኑኝነት ያጠነክራል። የክርስቲያኑ ገበሬ ርስት የሚባል የመሬት ይዞታ ቢያገኝም ለፊዩዳሉ መደብ፣ ለንጉሳዊ ቤተሰቦችና ለቤተክርስቲያን ግብር በመክፈል የሚበዘበዝ ነበር። ከዚህም በላይ የአብዛኛው ህዝብ ሙያ ግብርና ስለነበርና፣ በዕደ-ጥበብ ሙያ ከተሰማራው ጥቂቱ የህብረተሰብ ክፍል ጋር የመገናኘትና የመገበያየት ዕድል ስላልነበረው ምርታማነትን በማሻሻልና የተወሰነውን ምርቱን ገበያ አውጥቶ በመሸጥ ኑሮውን ማሻሻል አልቻለም። ከሰለሞናዊ አገዛዝ በኩል የአስተዳደር ጥገናዊ ለውጥና ከውጭ የመጣ ሃይማኖትን ለመቀበል የተደረገው ሙከራ በመክሸፉ የፊዩዳሉ ስርዓት ለብዙ መቶ ዓመታ እንዲቆይ አድርጎታል። ይሁንና ግን ንጉሳዊው አገዛዝ ሌሎች ከሱ ክልል ውጭ ያሉትን በማስገበር ተገዢ ለማድረግ ችሏል። በአንድ ግዛት ስር ባልተጠቃለሉ፣ ይሁንና ግን ግብር እንዲከፍሉ በተደረጉ የደቡብ ግዛትም ዘንድ የሰራ-ክፍፍልና የንግድ እንቅስቃሴ ለመዳበር ባለመቻላቸው እነሱም በዕድገት ወደ ኋላ የቀሩና የኋላ ኋላ በመጀመሪያ በክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት ወደ አንድ ግዛት ለመጠቃለል ያመሩ ክፍሎች ነበሩ ማለት ይቻላል። የማዕከላዊ ግዛት መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች በጣም በውስን ደረጃ የተጣሉት በአፄ ቴዎድሮስ አማካይነት ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያን ዘመናዊና የኢንዱስትሪ አብዮት ዕድል እንዲያጋጥማት ለማድረግ ያላቸው ህልም፣ ከውስጥ በፊዩዳሉ የገዢ መደቦችና መሳፍንቶች፣ እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች፣ ከውጭ ደግሞ በተለይም በእንግሊዞች ተንኮል ይጨናገፋል። አፄ ቴዎድሮስ እንግሊዞችን ኢንጂነሮችንና በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠኑ ሰዎችን እንዲልኩላቸው ደብዳቤ ሲጽፉ፣ እንግሊዞች የላኩላቸው ግን የሃይማኖት ሰባኪ ቄሶችን ነው። የዚህ ውጤት ምን እንደሆነ ይታወቃል። ያም ሆነ ይህ አፄ ቴዎድሮስ ካለጥገናዊ ለውጥና ካለ ኢንዱስትሪ ወይም ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀት ህብረ-ብሔር እንደማይመሰረት ገብቷቸው ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ህልማቸው ግን የኋላ ኋላ በአፄ ምኒልክ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ተግባራዊ ሊሆን በቅቷል።

አንዳንድ የአሮሞ ምሁራን የአፄ ምኒልክን ወደ ደቡቡ ክፍል መስፋፋትንና ሌሎችን አካባቢዎች በአንድ አገዛዝ ስር ማጠቃለል ልዩ አድርገው ይመለከቱታል። በሌላ አነጋገር በነሱ ግምት እንደዚህ ዐይነቱ የተቀረውን አካባቢ በአንድ አገዛዝ ስር በኃይል ማጠቃለል በኢትዮጵያ ምድር ብቻ እንደተካሄደ አድረገው ነው የሚያቀርቡት፤ ወይም ሰውን ለማሳመን የሚሞክሩት። ይህ ግምታቸው ወይም ታሪክን በዚህ መልክ መተርጎማቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ህብረ-ብሔረን ለመመስረት ከተደረገው ሙከራና ከተሳካው ጋር በፍጹም የሚጣጥም አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ በአፄ ምኒልክ የአገዛዝ መዋቅር ውስጥ አማራዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ራሳቸው የኦሮሞ የገዢ መደቦችም ተሳትፈውበታል። በሌላ አነጋገር የተገለጸላቸው የኦሮሞ የገዢ መደቦች የህብረ-ብሔርን ምሰረታ የደገፉና የጦር አዝማቾችም ነበሩ። በእርግጥ የአፄ ምኒልክ ወታደሮች አልገበር ያሏቸውን ባላባቶች አንዳንድ አላስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎች ወስደውባቸዋል። እንደዚሁም የኦርሞ ተዋጊዎች በአፄ ምኒልክ ወታደሮች ላይ ከፍተኛ እልቂት አስከትለዋል። የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ በሁለቱም በኩል ብዙ ሰው ህይወቱን አጥቷል።፡

በአብዛኛዎቹ የኦሮሞ ኤሊቶች የታሪክ አተረጋጎምና ግንዛቤ መሰረት ኦሮሞዎች በአንድ አገዛዝ ስር የሚታደደር ማህበረሰብ እንደነበራቸው ሆኖ ነው የሚቀርበው። እንደሚታወቀው ኦሮሞዎች ዛሬ ኦሮሚያ የሚባለውን ግዛት ከመቆጣጠራቸው በፊት ግዛቶቹ በአምስት የተለያዩ ብሔረሰቦች ቁጥጥር ስር የነበሩና ነገስታትም የሚተዳደሩ ነበሩ። እነዚህ ነገስታትና ብሔረሶቦቻቸው በእርሻ ሙያና በሌሎች ነገሮች የሚተዳደሩ ነበሩ። ከአስራስድሰተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ኦሮሞዎች ወደ ተለያየው የኢትዮጵያ ክፍላተ-ግዛት ሲስፋፉ እነዚህን ነገስታት በመደምሰስ ነው ብዙ ቦታዎችን መቆጣጠር የቻሉት። ወደ አማራው ክፍላተ-ግዛትም በመስፋፋትና ከህዝቡ ጋር በመጋባትና በመዋለድ በዚያ አካባቢ በልዩ ልዩ መልክ ለሚገለጸው የባህል ዕድገት አስተዋፅዖ አበርክተዋል። የኦሮሞ ኤሊቶችን ታሪክ ለመቀበል የሚያስቸግረው ሌላው ምክንያት አቀራረባበቸው ከህብረተሰብና ከህብር-ብሔር አገነባብ ታሪክና ሂደት ጋር በፍጹም ስለማይጣጣም ነው። በሌላ አነጋገር፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ እንደ አንድ ህብረ-ብሔር በአንድ ማዕከላዊ አገዛዝ ጥላ ስር ተደራጅቶ የነበረ አይደለም። ለአንድ ማዕከላዊ አገዛዝና ህብረ-ብሔር የሚያስፈልጉ ቅድመ-ሁኔታዎች የኦሮሞ ኤሊቶች ኦሮሚያ ብለው በሚጠሩት አካባቢና ማህበረሰብ ውስጥ አልነበረም። በቋሚ ወታደር፣ ፖሊስና በሲቪል ቢሮክራሲ የተደገፈ የአስተዳደር መዋቅር በየቦታው አልነበራቸውም። እንደዚሁም ህዝቡን ለማስተዳደር የሚያስችል በየቦታው የተዘረጋ ኢንስቲቱሽን አልነበራቸውም። ከዚህም በላይ ለአንድ ህብረ-ብሔር እንደ መሰረታዊ ቅድመ-ሁኔታ የሚያስፈልግ በማኑፋክቱር ላይ የተገነባ ኢንዱስትሪና ሰፋ ያለና የዳበረ የስራ ክፍፍል አልነበራቸውም። በተጨማሪም ሰፋ ያለ የገበያ ኢኮኖሚ አልነበራቸውም። ከዚህና ከሌሎች ለአንድ ህብረ-ብሔር ከሚያስፈለጉ መሰረታዊ ጉዳዮች ስንነሳ ኦሮሞን እንደ ብሔር ወይንም እንደ ህብረ-ብሔር የሚያስጠራው ምንም ዐይነት ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም። ስለሆነም በሌለ ነገር ላይ መነታረኩ ጊዜ ማጥፋት ነው የሚሆነው። የጋራ ችግርንም በአንድነት ተሰማምቶና ተባብሮ እንዳንሰራ እንቅፋት ይሆናል። ለሁለመንታዊ ዕድገት በሆኑ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፍልስፍና ጉዳዮች ላይ እንዳንረባረቡ መንገዱን ይዘጋብናል።

ያም ሆነ ይህ የአፄ ምኒልክ አገዛዝ ወደ ደቡቡ ክፍል መስፋፋትና፣ እዚያ አዳዲስ የአስተዳደር መዋቅሮችን መዘርጋት አዲስ የህብረተሰብ ግኑኝነት(Social and political relationship) እንደፈጠረ መገንዘብ ይቻላል። በማዋቅም ሆነ ባለማወቅ በባላባትና በጭሰኞች መሀከል የሚገለጽ ግኑኝነት ሊፈጠር ተችሏል። በዚህ ዐይነቱ አዲስ የህብረተሰብ ግኑኝነት የአፄ ምኒልክን አገዛዝ የተቀበሉ የየአካባቢው ባላባቶችም ተጠቃሚ ሆነዋል። ይህም ማለት የባላባትና የጭሰኝነት ግኑኝነት በመጤው አማራና በኗሪው ህዝብ ብቻ የሚገለጽ አልነበረም። የዚህ ዐይነቱን አጠቃላይ የፊዩዳል ስልተ-ምርት ግኑኝነት መረዳት የሚቻለው በዘመኑ የነበረውን የፖለቲካ፣ የህብረተሰብ፣ የባህልና የኢኮኖሚ ንቃታ-ህሊና መዳበርና አለመዳበር ጋር ያገናኘን እንደሆን ብቻ ነው። እንደሚታወቀው አፄ ምኒልክ የተገለጸለት አዲስ ቢሮክራሲያዊና ምሁራዊ መሰረት አልነበራቸውም። የአስተዳደራቸው መሰረት የፊዩዳል ኢንስቲቱሽንና ቤተክርስቲያን ነበሩ። እሳቸው በአስተሳሰብ በብዙ እጅ ቀድመው የሄዱ ቢሆንም የሳቸውን የዘመናዊነት ፍላጎትና ህልም በምሁራዊ ዘዴ እየተነተነ ተግባራዊ የሚያደርግ ኃይል ባለመኖሩ የዘመናዊነቱ ሂደት ውስንና ውስጠ-ኃይሉም በጣም ደካማ ነበር። ይሁንና ግን አንድ ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚያስችልና፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ብለን ለምንጠራትና የራሳችንም መለያ ለመሆን የበቃች እገር መሰረት ጥለው አልፈዋል ማለት ይቻላላል።

በአጠቃላይ ሲታይ የኢትዮጵያን ወደ ህብረ-ብሔር መሽጋገርና በጠንካራ መሰረት ላይ እንድተገነባ አስቸጋሪ የሚያደርገው ነገር የተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶችች፣ ከተማዎችና መንደሮች በስነ-ስርዓት አለመገንባታቸው፣ የዕደጥበብ ሙያና የንግድ እንቅስቃሴ አለማደጋቸው፣ በዚህም አማካይነት ከክልላዊ አስተሳሰብ ተላቆ በሰፊ ሜዳ ላይ ለመዋኘት የሚፈልግ የከበርቴ መደብ መፍለቅ አለመቻሉ ነው። ይህ ዐይነቱ የተጨናገፈ አካሄድ የኋላ ኋላ በብሔረሰብ ደረጃ ለሚንቀሳቀሱ፣ የታሪክን ሂደትና የህብረተሰብ ግንባታን ለመረዳት ለማይፈልጉ ኃይሎች መንገዱን አመቻችቷል ማለት ይቻላል።

ያልተስተካከለ ዕድገት፣ (Unequal Development) የብሔረሰብ ጥያቄ አነሳስና ጎልቶ መታየት!

አፄ ምኒልክ ከሞቱ በኋላ አፄ ኃይለስላሴ ከስደት እስኪመለሱ ድረስ ያለውን ጊዜ በመተው፣ ንጉሱ እንደገና የስልጣን ወንበራቸው ላይ ከተቀመጡ በኋላ የተከተሉትን ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጠጋን ብለን እንመልከት። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የማዕከላዊ አገዛዝ ሂደት እንደተጠናቀቀ ይታወቃል። ይሁንና ግን አፄ ኃይለስላሴ እንደገና ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ የሰሩት ትልቅ ስህተት የጣሊያን ወራሪ ኃይል የደመሰሰውን የፊዩዳል ስርዓት እንደገና መመለሳቸውና ማጠናከራቸው ነው። በተጨማሪም ጣሊያን ያቋቋማቸውን አዳዲስ ኢንስቲቱሽኖችና የገነባቸውን ከተማዎች በዚያው በመቀጠል ከማስፋፋትና ከማዳበር ይልቅ እንዲፈራርሱ ማድረጋቸው ነው። በእሳቸው ዘመን አዲስ አበባ ውስጥ አዲስ ቢሮክራሲያዊ ኃይል ቢቋቋምም ወደ ክፍለ-ሀገር ከተማዎችና ወረዳዎች፣ እንዲሁም ምክትል ወረዳዎች ስንሄድ አፄ ኃይለስላሴ የዘረጉት የተገለጸለት ዘመናዊ ኢንስቲቱሽን አልነበረም። በመሆኑም የአገሪቱን የሰውና የማቴሪያል ሀብት ሊያንቀሳቅስና ህዝባዊ ሀብት ሊያዳብር የሚችል ዘመናዊ እንስቲቱሽን አልነበረም። ስለሆነም ግራ የተጋባውና ያልተማረው ህዝብ የተሰማራው እስከዚህም ድረስ ሀብረተሰብአዊና ብሔራዊ ሀብት(National and Social Wealth) ሊፈጥሩ በማይችሉ ጥቃቅን የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ነው። በመሰረቱ እነዚህ ከእጅ ወደ አፍ የማያልፉ የገቢ ምንጮች በመሆናቸው በየሎካሉ ላሉ ኋላ-ቀር አስተደዳሮች የገቢ ቀረጥ ምንጮች ሊሆኑ የቻሉ አልነበሩም። በዚህም ምክንያት የተነሳ የየሎካሉ አስተዳደሮች በቂ የገቢ ምንጭ ስላለነበራቸው ለህዝቡ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችንና የስራ መስኮችን ሊያቋቋሙም ሆነ ሊከፍቱ አልቻሉም። በጊዜው የነበሩትም የሎካል የአስተዳደር መዋቅሮች እጅግ ወደ ኋላ የቀሩ በመሆናቸው እንዴት አድርገው አካባቢያቸውን ማልማት እንደነበረባቸው እስከዚህም ድረስ የሚያውቁት ነገር የለም። አብዛኛው ስራ የሚሰራው በዘፈቀደ ነበር ማለት ይቻላል።

ወደ አጠቃላዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው ስንመጣ ደግሞ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አፄ ኃይለስላሴ የተከተሉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በዘመኑ በሌሎችም የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተካሄደውን ዐይነት የምትክ የኢንዱስትሪ ተከላ( Import Substitution Industrialization) እየተባለ የሚጠራውን ነው። እንደሚታወቀው ጣሊያን ጠቅላላ አገሪቱን ሲገዛ ለራሱ ፍጆታ የሚጠቅም ኢንዱስትሪዎች አስፋፍቶ ነበር። እንዲሁም የሬዲዮ ጣቢያ ዘርግት ነበር። አፄ ኃይለስላሴ እንደገና ስልጣናቸውን ሲረከቡ በሞግዚትነት ተከትላቸው የመጣችው እንግሊዝ ጣሊያን ያቋቋመውን ኢንዱስትሪና የሬድዮ ጣቢያ ነቃቅላ በመወሰድ አገዛዙ ሀ ብሎ እንዲጀምርና ሁኔታውን እንዲያዘበራርቅ አድርጋለች። ያም ሆነ ይህ አፄ ኃይለስላሴ ስልጣን ከተረከቡ በኋላ በአዲስ አበባና በአካባቢው፣ እንዲሁም በአንዳንድ የክፍለ-ሀገር ከተማዎች ያቋቋሟቸው ኢንዱስትሪዎች ለአጠቃላይ የሀብት ክምችት( Capital Accumulation) የሚያገለግሉና በየአቅጣጫው ሊስፋፉ የሚችሉ አልነበሩም። ሰፋ ያለ በሁሉም መልክ ሊገለጽ የሚችል ለስራ-ክፍፍል መዳበር የሚያመች የኢንዱስትሪ ፖሊሲ አይደለም አፄውና አገዛዛቸው የተከተሉት። እነዚህም የስኳር፣ የብስኩት፣ የመጠጥ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የሲጋራና፣ እነዚህን የመሳሰሉትን የኢንዱስትሪ ተከላዎችን ነው የአፄው አገዛዝ ተግባራዊ ያደረገው። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በአዲስ አበባና በአካባቢው በመቋቋመቸው፣ 1ኛ) የሰው ኃይል ፍልሰት ከገጠር ወደ አዲስ አበባ እንዲያመራና ከተማዋን እንዲያጣብብ አድርጎታል። 2ኛ) የአዲስ አበባ ከተማ ራሱ በእቅድ የተሰራ ስላልነበር አዳዲስ የሰው ኃይል ከገጠር ሲመጣ ይህን አዲስ የህብረተሰብ ክፍል ሊያስተናግድና መጠለያ ሊሰጥ የሚችል ኢንስቲቱሽን አልነበረም። በመሆኑም ህዝቡ ራሱ በዘፈቀደ እዚህና እዚያ አልባሌ መኖሪያቤቶችን በመስራትም ሆነ በመከራየት አዲስ አበባ በዕቅድና ስርዓት ባለው መልክ እንዳትገነባ ለመሆን በቃች። 3ኛ) ከገጠር ወደ አዲስ አበባ የዘመተው አዲስ የሰው ኃይል ዘመናዊ በሚባሉ የኢኮኖሚ መስኮች ውስጥ የስራ ዕድል ለማግኘት ባለመቻሉ ባልባሌና ሀብትን ሊፈጥሩ በማይችሉ የስራ መስኮች እንዲሰማራ ተገደደ። ሴቱ፣ ሴተኛ አዳሪ፣ እንጀራ ጋጋሪና በችርቻሮ የሚተዳደር ሲሆን፣ ወንዱ ደግሞ በሊስትሮነት፣ በሱቅ ነጋዴነትና፣ በአናጢነትና በልብስ ስፌትነትና እነዚህን በመሳሰሉት፣ ኢንፎርማል ሴክተር በመባል በሚታወቁት እንዲተዳደር ተገደደ። 4ኛ) ይህ ዐይነቱ ኢንፎርማል ሴክትር ዘመናዊ ከሚባለው የኢኮኖሚ መስክ ጋር ግኑኝነት ስላልነበረው፣(Linkages) ህብረተሰብአዊና ብሔራዊ ሀብት ለመፍጠር የሚያስችል አልነበረም። በዚህ መስክ ተሰማርቶ የሚተዳደረው የህብረተሰብ ክፍል ገቢው በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ከዘመናዊ መስክ የሚመረቱትን ምርቶች ገዝቶ ለመጠቀም አይችልም ነበር። 5ኛ) ይህ ዐይነቱ ግኑኝነት አለመኖርና የሰፊውም ህዝብ የመግዛት ኃይል መዳከም፣ በአንድ በኩል የገንዘብን በፍጥነት መሽከርከር ሲያግደው፣ በሌላው ወገን ደግሞ ለአገዛዙ ሰፊ የገቢ ቀረጥ መሰረት ሊጥልለት አልቻለም። በዚህም ምክንያትና አገዛዙ በተከተለው የተበላሽና የህብረተሰቡን ፍላጎት ያላካተተና ቀስ በቀስ ከታች ወደ ላይ ሊያድግ የሚችል የኢንዱስትሪ ተከላና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት( Systematic Industrialization and Organic Growth) ባለመከተሉ በአገሪቱ ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገት(Unequal Development) ሊስፋፋ ችሏላ። ይህ ዐይነቱ የተበላሸ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትንሽ ገንዘብ ያለውን ባለሀብት ወደ ነጋዴነት እንዲያመራና እንዲያተኩር በማድረግ በአገሪቱ ምድር በኢንዱስትሪ ተከላ ላይ ሊያተኩርና ቀስ በቀስ እያለ ሊያድግ የሚችል የኢንዱስትሪ ከበርቴ እንዳያድግ አደረገ። በተጨማሪም ይህ ዐይነቱ የተዘበራረቀና ዓላማው ምን እንደሆን የማይታወቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አስተሳሰቡ የተዘበራረቀበት የህብረተሰብ ክፍል እንደአሸን እንዲፈልቅ አደረገ። ከኢትጵያዊነት ይልቅ አሜሪካንን የሚናፍቅ ኃይልና፣ ከዘጠና በመቶ በላይ ከሚሆነው ህዝብ የተገለለና በራሱ ዓለም ውስጥ የሚኖር የህብረተሰብ ክፍል ብቅ በማለት ባህላዊና ማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር ተደረገ። በዚህም መሰረት የኢኮኖሚው ፖሊሲ በአገሪቱ ውስጥ ሰፋ ያለና ዘመናዊ ገበያ እንዲዳብርና እንዲስፋፋ የማያመች በመሆኑ ህብረተሰቡን ሊያስተሳስር፣ የማሰብ ኃይሉን ሊያዳባር የሚያስችለው፣ የፈጠራ ችሎታውን ሊያሳድግና አዳዲስ መሳሪያዎችንና ምርቶችን በማምረት ማንነቱን ሊገልጽ የሚችል የህብረተሰብ ክፍል ብቅ ሊል አልቻለም። በአፄው ዘመን ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ነፃ ዜጋ የሚታይና መብትና ክብር ያለው መሆኑ የሚቆጠርና የሚከበር አልነበረም። ዘመናዊ የሚባለው አዲስ አበባ የተዘረጋው ቢሮክራሲ ይህንን ክፍተትና ኋላ-ቀርነት ለማረም የሚችል ባለመሆኑ፣ በአገሪቱ ውስጥ እዚያው በዚያው ዘመናዊና ፊዩዳላዊ የአስተዳደር መዋቅሮች በመዘርጋት ለአጠቃላይ ዕድገት ጠንቅ መሆን ችለዋል ማለት ይቻላል። በመሆኑም የአፄው አገዛዝ ፖለቲካዊ፣ ህብረተሰብአዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ንቃተ-ህሊና የጎደለው ብቻ ሳይሆን፣ ስትራቴጂካሊ ለማሰብ የሚችል አልነበረም። በአገሪቱ ውስጥ ሰላም እንዲስፈንና አገሪቱም በውጭ ኃይሎች እንዳትጠቃ በኢኮኖሚ መስክ መካሄድና መወሰድ ያለበትን ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ባለመቻሉ ለሰላም ጠንቅ የሆኑ ነገሮችን ዘርግቶ አለፈ።

ወደ መንግስት መኪናው አውቃቀር ስንመጣ፣ መንግስታዊው አወቃቀር ከታች ወደላይ ከህብረተሰቡ የማቴሪያል ዕድገት ጋር እየተቀናጀ ያደገ መንግስታዊ አወቃቀር አይደለም የተዘረጋው። የወታደሩ፣ የፀጥታው ኃይል፣ ፖሊስና ሌሎች አውታሮችም በውጭ ኃይሎች የሰለጠኑ በመሆናቸው ለውጭ የስለላ ኃይል ሰርጎ መግባት የሚያመቹ ነበሩ። ይህ ዐይነቱ ስርጎ መግባት በተለይም አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ተግባራዊ የሆነና፣ በወታደሩና በፀጥታው ኃይል መተማመን እንዳይፈጠር ያደረገ ነው። አሜሪካንን በሚደግፍና መረጃዎችን የሚያቀብል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ቀስ በቀስ እያለ ለሶቭየቶች ታማኝ ሊሆን የሚችል ኃይል የሚመለመልበት ነው። ይሁንና ግን የኢትዮጵያ መንግስት መኪና አወቃቀር ለብዙ ዐመታት ከአሜሪካኖች ጋር የተያያዘ ስለነበርና፣ የአሜሪካን የኑሮ ፍልስፍና ከደሙ ጋር የተዋሃደ ስለነበር፣ በተለይም ኮሙኒዝምን ወይም ሶሻሊዝምን የሚጠላው ኃይል ለአሜሪካ ያደላና በአብዮቱ ዘመን ህብረተሰብአዊ ለውጥ እንዳይኖር ያገደ ነው። ይህ ኃይል ደርግ ሊወድቅ ሲልና በኋላ የአሜሪካን ፓስፖርት እየተሰጠው አሜሪካን ገብቶ ኑሮውን እንዲመሰርትና ተደላድሎ እንዲኖር የተደረገ ነው።

ያም ሆነ በታሪክ ውስጥ የመንግስትን አመሰራረትና ለዕድገት አመቺ መሆን አለመሆን ስንመለከት በራሳቸው ጥረት የመንግስታቸውን መኪና ያላዋቀሩ አገሮችና የራሳቸው ፍልስፍናዊ መመሪያ የሌላቸው አገሮች ለዕድገት ጠንቅ እንደሚሆኑ ነው። የሶቭየቱና የቻይናው አብዮት ከሞላ ጎደል ሊሳካና እነዚህ አገሮች ኃያልና የሚፈሩ መንግስታት ሆነው ብቅ ማለት የቻሉት የራሳቸውን የመንግስት መኪና በራሳቸው ጥረት በመገንባታቸው ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ በራስ ጥረት የመንግስት መኪናን ማዋቀርና አገርን መገንባት አገር ወዳድነትንና ብሔራዊ ስሜትን ያዳብራል።ለዕድገት ያመቻል። መተማመንን ይፈጥራል። በህዝብና በአገዛዝ መሀከል ሊኖር የሚገባውን መደጋገፍና መተሳሰብ ያጠናክራል። ዛሬ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለውን ጭቆና፣ የሀብት ዘረፋና ሙስና ስንመለከት ዋናው ምክንያት መንግስታትና አገዛዞች ከታች ወደ ላይ በአንዳች ፍልስፍናና ሳይንስ ያልተገነቡ መሆናቸውን ናቸው። አብዛኛዎቹ መንግስታት በውጭ ኃይሎች በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚጠመዘዙና የእሱንም ጥቅም የሚያስጠብቁ ናቸው። ስለሆነም በአንዳች ፍልስፋና የማይመሩና የህዝቦቻቸው ተጠሪ ያልሆኑ አገዛዞችና መንግስታት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ላይ ስቃይን ያደርሳሉ፤ አንድ አገር በዘለዓለማዊ ትርምስ ውስጥ እንዲኖር ያደርጋሉ። ችግሩ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ እንዲሸጋገር በማድረግ ህዝቦች በዘለዓለማዊ ድህነት ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋሉ። ህዝባቸው በራሱ ላይ እንዳይተማመንና ቢያንስ እንኳ መሰረታዊ ነገሮችን እንዳያሟላ እንቅፋቶችን ይፈጥራሉ። ስለዚህም ለአገር ወዳድነትና ብሔራዊ ስሜት መዳበር በአዲስ ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ የመንግስት መኪና አወቃቀር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። አዲሱ የመንግስት መኪናና ልዩ ልዩ ኢንስቲቱሽኖችም ከማኝኛውም የውጭ ኃይል ተፅዕኖ የተላቀቁ መሆን አለባቸው። ከላይ እስከታች ያሉ ባለስልጣናትም ሆነ አዳዲስ የሚቀጠሩ ወይም የሚሾሙ የህይወት ታሪካቸው መጠናት አለበት። ቀደም ብሎ ሆነ አሁንም ከማንኛውም የውጭ ኃይል ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግኑኝነት የነበረውና የውጭ ኃይሎችን የሚያመልክ ግለሰበም ሆን ቡድን ለስልጣን እንዲበቃ መደረግ የለበትም፤ ወይም በአማካሪነትም ቢሆን እንኳ በስልጣን አካባቢ መድረስ የለበትም። ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንድ አገር በሁሉም አቅጣጫ ለማደግና ህዝቦቿም ዕውነተኛ ነፃነትን ሊቀዳጁ የሚችሉት። ይህንን የተቀደሰ ዓላማ በሆነው ባልሆነው ለማሰናከል መሞከርና የማይሆን ዘመቻ እያካሄዱ እንቅፋት መፍጠር የኢዮጵያዊነትን ስሜት ማኮላሸቱ ብቻ ሳይሆን ህዝባችን ዘለዓለሙን ደሀ ሆኖ እንዲቆይ ሁኔታውን ማመቻቸት ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አገር እንዳይገነባ እንደማሰናከል ይቆጠራል። ዛሬ በአብዛኛው ተማርኩ በሚለውና ውጭ አገር በሚኖረው ምሁር ዘንድ ያለው ትልቁ ችግርና የአስተሳሰብ ክፍተት ይህንን ሁኔታ በቅጡ ለመረዳት አለመቻል ነው። በተጨማሪም ለውይይትና ለክርክር ዝግጁ ባለመሆን ሽምጥጥ በማለት ወደ ስልጣን ለማምራት ከፍተኛ ሩጫ ማድረግ የትኛው አገር ወዳድ እንድሆነ የትኛው ደግሞ የአገር ጠላት እንደሆነ ለማወቅ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የብሔረሰቦች እንቅስቃሴ መጠንሰስና መስፋፋት፣ እንዲሁም ብሔራዊ ስሜት ያለመዳበር ጉዳይ!

የኤርትራን የነፃ አውጭ ድርጅቶች መጠንሰስ ስንመለከት በመሰረቱ የኢጣሊያን የቅኝ አገዛዝ ያሰፈነው ልዩ ዐይነት ስርዓት በተወሰነው የኤርትራ የህብረተሰብ ክፍል ላይ የህሊና ጫና ወይንም ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዳይዳብር አድርጎታል። በተጨማሪም የአረቦች ተፅዕኖ ቀስ በቀስ ነፃ አውጭ ነኝ የሚሉትን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ዘመቻ እንዲያካሂዱ አግዞአቸዋል። በተለይም አፄው ኤርትራን ለጊዜው በፌዴሬሽን መተዳደርና፣ ጊዜው ከማለቁ በፊት በኃይል ማጠቃለል ኤርትራው ውስጥ የነበረውን ሁኔታ የባሰውን አባብሶታል። አፄው ስትራቴጂካል በሆነ መልክ ማሰብ የማይችሉ በመሆናቸውና የሪፐብሊክ አሰተሳሰብ የተዋሃዳቸው ስላልነበሩ በኤርትራም ሆነ በጠቅላላው የአገሪቱ ግዛት ፓርሊሜንተሪ ዲሞክራሲ እንዲዳብር ለመፍቀድና ሁኔታውን ለተረጋጋና ለዕድገት ለማመቻቸት ዝግጁ አልነበሩም። የመሰላቸው በሽወዳና በተንኮል እንዲሁም በኃይል ሁኔታውን መቆጣጠር የሚችሉ ሆኖ ነው የተሰማቸው። የዲስፖቲክ አገዛዝ ዋናው ችግር ኃይል አለኝ ብሎ ስለሚገምትና ሁሉንም ለመቆጣጠር የሚችል ስለሚመስለው አንድን የፖለቲካ ክስተት ከሁሉም አቅጣጫ ለማየት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ አማካሪው የሚለውን ባለመስማትና በጥርጣሬ ዐይን በመመልከት ያለውን ሁኔታ የባሰውን ማባባስ ነው። ስለሆነም አፄ ኃይለስላሴ የተከተሉት ስታሬቴጂክና ፖለቲካ አልባ አካሄድ የኤርትራን ነፃ አውጭ ድርጅቶች እልክ ውስጥ ከተታቸው። አብዮቱ ከፈነዳም በኋላና እስከመጨረሻው ድረስ የተካሄደው በእልክ ላይ የተመሰረተ የጭፍጨፋ ፖለቲካ ሁኔታው የባሰውን አበላሸው እንጂ ለችግሩ መፍትሄ ሊሆን በፍጹም ሊሆን አልቻለም። በሰፊው ሳይታሰብበትና ከሁሉም አቅጣጫ ውይይት ሳይካሄድበት ዝም ብሎ በፊዩዳል ግብዝነት „ሁሉንም ነገር ወደ ጦር ግንባር“ በሚለው መፈክር የተደረገው ዘመቻና ጦርነት የሰውና የማቴሪያል ኃይል የፈሰሰበት፣ የአገሪቱን ሁለ-ገብ ዕደገትና የኢትዮጵያዊነትን ስሜት እንዲቦረቦር ያደረገ ነው። ማንም ኃይል አንድን የህብረተሰብ ክፍልም ሆነ የብሔረሰብ እንቅስቃሴን በጉልበት ሊያሸንፈው አይችልም። ውስጥ ካለው የተዛባ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር ተያይዞ የሚያድግ እንቅስቃሴ በመሆኑ፣ እንደዚህ ዐይነቱን የውስጥ ችግር በፖለቲካ ሪፎርምና ሁለ-ገብ በሆነ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ግንባታ ፖሊሲ ብቻ ነው ማረምና ብሔራዊ ወይም የአገር ወዳድ ስሜትነት ማዳበር የሚቻለው።

በሌላ ወግን ግን የኤርትራው የነፃ መውጣት እንቅስቃሴ ብሶት የወለደውና የቅኝ አገዛዝ የህሊና ተጽዕኖ ውጤት ቢሆንም፣ እንቅስቃሴው የተጀመረውና የተካሄደው በተገለጸላቸውና የዲሞክራሲን ትርጉም በተረዱና ከጭንቅላታቸው ወይም ከሰውነታቸው ጋር ባዋሃዱ ኃይሎች አይደለም። እንቅስቃሴው እየጎለመሰ ሲሄድ ወደ ዘረኝነትና ወደ ማንአለኝበት ያመራና፣ በእንቅስቃሴው ውስጥም የትግሉን ዓላማ ለመወያየት ለዲሞክራሲያዊ ውይይት የሚያመች ሁኔታ የሌለበት ወደ አምባገነንነት ያመራ ነው። ስለሆነም ወጣቱ ክፉውን ከደጉ እንዳይለይ በጥላቻና በንቀት መንፈስ እንደሚረዝ በማድረግ፣ ከምሁራዊ እንቅስቃሴ ይልቅ ይበልጥ ወደ ጦርነት ስልትና ትግል በማምራት ጭካኔነትን ከደሙ ጋር እንዲያዋህድ ለማድረግ በቃ። በጦርነቱ ውስጥ የተሳተፉትና ከሞት የተረፉት የኢትዮጵያ ወታደሮች እንደመዘገቡት ከሆነ በተማረኩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ይደርስ የነበረው ስቃይ እጅግ ዘግናኝ እንደነበር ነው። ይህ ብቻ አይደለም። አቶ ኢሳያስና ግብረ አበሮቹ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠልና ነፃ ለመውጣት ሲሉ አዲስ አበባና አንዳንድ የአገሪቱ የክፍለሀገር ከተማዎች በንግድና በስራ ዓለም ተሰማርተውና ተደላድለው፣ እንዲሁም ሀብት አፍርተው የሚኖሩ ኤርትራውያንን ሁሉ በጥላቻ መንፈስ በመመረዝና ማፊያዊ በሆነ መልክ በማደራጀት አገራችንን ውስጥ ለውስጥ ሲቦረቡሩና ሀብቷን ሲዘርፉ ነበር። አብዮቱ ከፈነዳም በኋላ ነፃ እንወጣለን በማለት ትግል የጀመሩ እንደወያኔ የመሳሰሉ ቡድኖችን በማስታጠቅና በማደራጀት አገራችን ዛሬ ላለችበት አስከፊ ሁኔታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። አገሪቱ በሁሉም አቅጣጭ በጦርነት እንድትወጠርና ማዕከላዊው መንግስት እንዲዳከም ያላደረገው ጥረት ይህ ነው አይባልም። ከዚህ ስንነሳ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ነን በሚሉና ዛሬ በአሜሪካን ምድር ተደላድለው በሚኖሩ አንዳንድ የድሮ ባለስልጣኖች የሚነገረው አባባል፣ የእነ ኢሳያስ ቡድን „ኢትዮጵያ እንድትገነጣጠል አይፈልግም“ የሚለው አባባል ከተጨባጩ የኢትዮጵያ ሁኔታና ከኮመን ሴንስም ሆነ ከሎጂካዊ አቀራረብ ጋር በፍጹም የሚጣጣም አይደለም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ „የኢትዮጵያ ተቆርቋሪዎች“ በእዚህ ዐይነት አቀራረባቸው የሚያረጋግጥሉን ስለዲሞክራሲና ስለ ነፃነት ያላቸውን እጅግ የተዛባ አመለካከት ነው። ለመሆኑ የእነ አቶ ኢሳያስ ቡድን ኢትዮጵያ እንዳትበታተን የሚፈልግ ከሆነ ለምን ወያኔንና የኦሮሞ ነፃ አውጭ ድርጅቶችን አስታጠቀ ? እነዚህ ትላልቅ ስዎች ያልገባቸው ነገር የእነ ኢሳያስ ዋናው ዓላማ ኢትዮጵያን ከውስጥ መቦርቦርና ማዳከም ብቻ ሳይሆን፣ የወታደሩ አገዛዝ አትክሮው ሁሉ ወደ ጦር ሲያመራና ኃይሉንና ሀብቱን በጦርነት ላይ ሲያውል መዳከም ይጀምራል፤ እኛም በቀላሉ ልናሸንፈው እንችላለን ከሚለው ስሌት በመነሳት ደርግን የሚቃወሙ ኃይሎችን ሁሉ ማስታጠቅና ማደራጀት እንደነበር በፍጹም የተረዱ አይመስልም። ስለሆነም የእነ ኢሳያስ ድርጊት በቀጥታ ኢትዮጵያ እንድትበታተን ከመደገፍ ውጭ ሊታሰብ አይችልም። እነ አቶ ኢሳያስ በሁሉም አቅጣጫ ጦርነት እንዲከፈት ሁኔታውን ሲያመቻቹና እንገነጠላለን ያሉ ኃይሎችን ሁሉ ሲደግፉ ማዕከላዊው አገዛዝ የግዴታ ለኢኮኖሚ ግንባታና ለሌሎች ስራዎች ሊጠቅምበት ወይም ሊያውል የሚችለውን ሀብት ጦርነት ላይ እንዲያውል ተገደደ። ከውስጥ የሰው ኃይልም ሆነ ሀብት እንዲወድም ተደረገ። በሌላ ወገን ግን በዚህ ዐይነቱ እርኩስ ተግባርና ተንኮል የኤርትራ ተገንጣይ ቡድኖችና ሰፊው የኤርትራ ህዝብም በምንም ዐይነት ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም። በከፍተኛ ምሁራዊና በሳይንሳዊ አስተሳሰብ ላይ ተደግፎ የተካሄደ እንቅስቃሴና ጦርነት ባለመሆኑ የመጨረሻ መጨረሻ የጨለማ ኑሮ ውስጥ ሊወድቁ ቻሉ። እንደገና ሊያገግሙ የማይችሉበት ሁነታ ውስጥ ወደቁ። አገዛዙ ብቻ ሳይሆን ሰፊው የኤርትራ ህዝብና በተለይም ወጣቱ በቀላሉ መፍትሄ የማይገኝለት የሳይኮሎጂካል ቀውስ ውስጥ ነው የወደቁት። በቀላሉ ራሳቸውን በራሳቸውን ማግኘት እንዳይችሉና እየባነኑ እንዲኖሩ ነው የተደረጉት። ከዚህ ስንነሳ ኤርትራ ያለቀላት አገር ነች። በምንም ዐይነት እንድገና በራሷ ጥረት አገግማ ካለበት ሁለመንታዊ በሽታ ድና ልትነሳ አትችልም። ህዝቡ፣ በተለይም ወጣቱ ከፍተኛ የሆነ የህሊና ጥገና ድጋፍ የሚያስፈክልገው ነው። ራሱን በራሱ ለማወቅ የብዙ መቶ ዐመታት ጉዞና ህክምና ያስፈልገዋል። አገዛዙም በዲሞክራሲያዊ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ በሚያስብ ኃይል እስካልተለወጠ ድረስ ለአገራችንና ለአካባቢው አገሮች የሰላም ጠንቅ ነው የሚሆነው። በሌላ ወገን ደግሞ በኢርትራ ውስጥ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ ስርዓት ለማምጣት በፍጹም አይቻልም። የተገለጸለት ኃይል ባለመኖሩ የኤርትራ ህዝብ እጣ የጨለማና የመሰደደ ኑሮ ብቻ ነው የሚሆነው።

ይህ ሁኔታ ምንን ነው የሚያረጋግጥልን ? ዛሬም ሆነ ወደፊት፣ በዚህ አገዛዝም ሆነ በሌላ አገዛዝ ኤርትራ ውስጥ ያለው አገዛዝና ወደፊትም ቢሆን ኢሳያስን የሚተካው ግለሰብም ሆን ቡድን ከደሙ ጋር የተዋሃደ ጭንቅላቱን አንቆ የያዘው የጨለመ አስተሳሰብ ስላለ ከበጥባጭነትና ከጦርነት ቀስቃሽነት በፍጹም ሊላለቀቅ አይችልም። ወጣቱና ሰፊው ህዝብም የዚህ የጨለማ አስተሳሰብ ሰለባ ስለሆነና በቀላሉ ሶሻላይዝድ ሊሆን ስለማይችል በኢትዮጵያና በኤርትራ መሀከል ሊፈጠር የሚችለው ግኑኝነት ምናልባት ከመቶና ከሁለት መቶ ዐመታት በኋላ የሚሆን ይሆናል። ዛሬ በአንዳንድ የዋህ ኢትዮጵያውያን የእነ ኢሳያስን አገዛዝ ለኢትዮጵያ አሳቢ አድርጎ ለማቅረብ መሞከርና፣ ውስጥ ያለንን ችግር ለመፍታት የሚያስችል አቅም ሳይኖረን በኤርትራና በኢትዮጵያ መሀከል ስለሚኖረው የወደፊቱ ግኑኝነት ደፋ ቀና ማለትና ሰሚናሮች ሲዘጋጁ ስናይ ይህ ደፋ ቀና የሚለው ኢትዮጵያዊ ኃይል ሁኔታው የቱን ያህል ያለተገለጸለት መሆኑን ነው የምንገነዘበው። አንዳንድ ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚሰሩት የማያስፈልግ ስራና ቅስቀሳ ብዙውን የዋህ ኢትዮጵያዊ እያሳሳተው ነው። በሌላው ወገን ግን በኤርትራና በኢትዮጵያ መሀከል ወደፊት ጥሩ ግኑኝነት እንዲመሰረት ከተፈለገ ቀናና ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸውን ኤርትራውያንንን መደገፍና ከእነሱ ጋር አብሮ መስራት አስፈላጊ ይመስለኛል። በግልጽ ለመወያየት ከፈለጉ ድረስ በሩን ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል። በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ተራማጅና በሰብአዊነት መርሆች ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ተራማጆችና የስብአዊነት አስተሳሰብ አራማጆች ከኤርትራውያን ተራማጆችና የሰብአዊነት ጠበቃዎች ጋር ቢሰሩና ሃሳብ ለሃሳብ ቢለዋወጡ ሁለቱም ህዝቦች ዕውነተኛ ወዳጅነትን ሊፈጥሩና፣ ቀጥሎም ወደ ኮንፌዴሬሽንና ከዚያ በኋላ ዳግሞ ሁኔታው ሲበስል ወደ ውህደት ሊያመሩ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ጉዳይ ሊታሰብ የሚችለው ከእነ ኢሳያስ ስሌትና አገዛዝ ባሻገር ነው።

ያም ተባለ ይህ፣ በአጠቃላይ ሲታይ በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔረሰብ እንቅስቃሴ መዳበርና ነፃ እንውጣ እያሉ እዚህና እዚያ የጦር ትግል ማካሄድ ከአጠቃላዩ የተበላሸ ፊዩዳላዊ አመለካከትና የሪፑብሊክ መንፈስ እጦትና ከተበላሸ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ ጋር የተያያዘ ነው። ያልተስተካከለ ዕድገት ወይም የተዛባ የኢኮኖሚ ፖሊስ የግዴታ ተጨቆን ለሚሉ ኃይሎች መፈናፈኛ መንገድ በመስጠት ያለውን ክፍተት ተጠቅመው በመሰረቱ በአገሪቱ ላይ ዘመቻ እንዲያካሂዱ ረድቶአቸዋል። ስለሆነም የብሔረሰብ እንቅስቃሴ በጊዜው የነበረው እጅግ የተዳከመ ኢኮኖሚና የህብረተሰብአዊ አወቃቀር ውጤትና በአገሪቱ ምድር ዲሞክራሲያዊ መብቶችና በነፃ መደራጀት ካለመቻል ጋር የተያያዙ ናቸው ማለት ይቻላል። የዚህኛው ወይም የዚያኛው ብሔረሰብ ተወካይ ነኝ የሚለው ኤሊት የስልጣን ተካፋይ አይደለሁም ብሎ የሚያራግበው ወሬ እንጂ በመሰረቱ ጥያቄውም ሆነ እንቅስቃሴዎቹ በምንም ዐይነት ሰፊውን የኦሮሞ ብሔረሰብም ሆነ የኤርትራ ህዝብ የሚመለከቱና የሚወክሉ አልነበረም። የእንቅስቃሴያቸው አጀማመርና ጎልቶ መታየት ተራማጅ የሚያስመስላቸው ቢመስልም፣ ከዛሬው ሁኔታ ተነሰተን እንቅስቃሴያቸውን ስንመረምር በብሔረሰብ አካባቢ ብቻ መሰባሰቡና ትግል መቀጠሉ ዕውነተኛ የነፃነት ትግል እንዳያራምዱ አድርጎአቸዋል። እንቅስቃሴያቸው እየጎለመሰ ሲመጣ ሳይንሳዊ መልክ እያጣና ነፃነት ተቀናቃኛች በመሆን የባሰውኑ የጥቁርን ህዝብ ነፃነትና ዕድገት በሚጠሉ የውጭ ኃሎች ጉያ ስር እንዲወድቁ አስገድዷቸዋል። እራሳቸው ነፃ እንወጣለን ብለው መንቀሳቀስ የጀመሩት ድርጅቶች ከዚህም ከዚያም ዕርዳታ በማግኝት በታሪካቸው ላይ ብቻ ሳይሆን የዘመቱት፣ ያለሙትንም ነፃነት መጎናጸፍ እንዳይችሉ ተደርገዋል። በዚህም መልክ እንቅስቃሴያቸውን ከብሔራዊ ባህርይው በማውጣትና ዓለም አቀፋዊ መልክ እንዲኖረው በማድረግ ኢትዮጵያንና ዕድገቷን ለሚጠሉ አገሮችና በሃይማኖት ስም ተጥቀመው አገራችንን ለመበታተን ለሚፈልጉ ኃይሎች ሁኔታው እንዲመቻች ለማድረግ በቅተዋል። ስለሆነም የጦር ትግላቸው በአገዛዙ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን የገዢው መደብ ተጠቃሚ ነው በሚለው የህብረተሰብ ክፍል ላይ፣ በተለይም በአማራው ላይ ጦርነት በመክፈት የብዙ ሰዎች ህይወት ተቀጠፈ፤ ብዙ ንብረትም አወደሙ። በሌላ ወገን ግን ይህ ዐይነቱ በየብሔረሰብ አካባቢ የተደረገ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲደመሰስ አደረገ። በተለይም ወጣቱ እየተመለመለ በመግባትና በጥላቻ ስሜት እንዲመረዝ በመደረጉ ብሔራዊ ወይም አገራዊ ስሜቱ ሙሽሽ ብሎ እንዲወድም ተደረገ። ይህ ዐይነቱ በኢትዮጵያ ላይ መዝመትና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ደብዛው እየጠፋ መምጣት በአንድ ወቅት ብሔራዊ አጀንዳ ይዘው ይታገሉ የነበሩ ግለሰቦችንም የብሔረሰብ አርማ ይዘው እንዲያራግቡ አስገደዳቸው። በተለይም የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ከያዘና ከኦሮሞ ህዝብ የነፃነት ድርጅት(OLF) ጋር አገር በሚያስተዳድሩበት ጊዜ፣ አንድ ወቅት ማርክሲስት ወይም ሶሻሊስት ነኝ እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ ይል የነበረው ሁሉ የቤተሰቡን ግንድ በመቁጠር እኔም ኦሮሞ ነኝ ማለት ጀመረ። ይህ የሚያሳየው የቱን ያህል የመንፈስ መረጋጋት አለመኖርና አርቆ አለማሰብን ነው፤ ለስልጣን መስገብገብንና በፕሪንሲፕል አለመመራትን ነው። እነዚህ ኃይሎች ወይም ግለሰቦች ዛሬ ደግሞ 180 ዲግሪ በመዞር እንደገና የኢትዮጵያ ጠበቃ በመሆን ወጣቱ ከድሮ አባቶቻችን መማር ያለበት ነገር አለ በማለት ሲናገሩ ይሰማል።

የወያኔ የክልል ፖሊሲና ጠንቁ!

በመጀመሪያ ደረጃ በተለይም አብዮቱ ከፈነዳም ሆነ ከመፈንዳቱ በፊት ብቅ ያሉትንና ወደ ጦር ትግል ያመሩትን የብሔረሰብ እንቅስቃሴዎች የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና ሁኔታ ስንመለከት፣ አብዛኛዎቹ በጊዜው የግራ ስም ቢይዙም ወይም በማርክሲዝም ሌኒንዝም ስም ቢምሉም ርዕያቸውም ሆነ ትግላቸው በምንም ዐይነት ከሶሻሊዝም ጋር ወይንም ከማርክሲዝም ጋር የተያያዘ አልነበረም። ትግላቸውን ለመጀመር ሲነሳሱ፣ በጊዜው የነበረው ጭቆና በብሔር ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ፊዩዳላዊ ባህርይ ያለውና፣ ይህ ጭቆና ጠቅላላውን የአገሪቱን ህዝብ የሚመለከት እንደነበር በፍጹም አልተገነዘቡም። የተወሰነው የገዢ መደበ ከአማራው ብሔረሰብ በመውጣቱ የአማራውን ብሔረሰብ ብቻ የሚጠቅም፣ የኑሮውን ደረጃ የሚያሳድግለትና ከሌሎች ብሔረሰቦች የበለጠና የተለየ መሆኑን የሚያሳይ ልዩ ዐይነት ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተከተለ አድርገው ነበር የቆጠሩት።

የሞናርኪውን አገዛዝ ጠቅላላውን የፖለቲካ አወቃቀርና ፍልስፍናውን ስንመለከት ግን፣ አገዛዙ የፊዩዳሉን፣ የአሪስቶክራሲውንና የንጉሳውያን ቤተሰብን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነበር። ርዕዮተ-ዓለሙንም ስንመለከት ፊዩዳላዊና የንጉሱን ፍጹማዊነትና አገራችንን ለመግዛት ከእግዚአብሔርር የተላኩ ናቸው በማለት ሰፊው ህዝብ አምኖ እንዲቀበል የሚያደርግ እንጂ በመሰረቱ አማራ ብሔረሰብ የሚባለውን ርዕይ የሚያንፀባርቅ አልነበረም። በተለያዩ የህብረተሰብ ታሪኮችም ውስጥ እንደታየው ስልጣን ላይ ያሉ የገዢ መደቦች የሚከተሉት ፖሊሲና ርዕዮተ-ዓለም ሁልጊዜ ከራሳቸው ጥቅምና ከሚደግፋቸው የህብረተሰብ ክፍል በመነሳት እንጂ የአንድን ህዝብ ወይም ብሔረሰብ ጥቅም አጉልቶ በማሳየት አይደለም። ከዚህ ስንነሳ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትና በዘፈንም ሆነ በምግብና በአለባበስ የሚገለጸው የአማራ ባህል ነው የሚባለው በመሰረቱ የአማራዉ ብቻ አልነበረም። አይደለምም። እነዚህ ዐይነት በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጹ ባህሎች ከህብረተሰቡ ዕድገት ጋር በህበረተሰብአዊ ሂደት ታሪክ ውስጥ ሰዎች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ያዳበሩት ነው። በተጨማሪም በአንድ አካባቢ የሚዳብር ባህል ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመዋሃድ ልዩ ዐይነት ዕምርታን የሚያገኝ ነው። በመሰረቱ በአንድ አካባቢም ሆነ ህብረተሰብ ውስጥ የሚፈልቅና የሚዳብር ባህል የተለያዩ ባህሎች ጥምር ውጤት(Synthetic) ነው። ስለሆነም ይህ የአማራው ባህል ነው፣ ያኛው የኦሮሞ ነው ብሎ መጥራት በጣም ያስቸግራል። አንድን ባህል ወይም ባህሎች ከላይ ወደ ታች የምትጭናቸው ነገሮች አይደሉም። የሰው ጭንቅላት ውጤቶች በመሆናቸው እንደየህብረተሰቡ የዕድገት ደረጃ እየተሻሻሉና ልዩ መልክ እየያዙ የሚሄዱ ናቸው፤ ወይም ቀጭጨው በመቅረት ለዕድገት፣ ለሰፊና ለተገለፀለት አስተሳሰብ እንቅፋት ይሆናሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ርዕዮተ-ዓለም የአገዛዝ መሳሪያ ሆኖ ከመታወቁ በፊት በአጋጣሚና ሰዎች በአንድ አካባቢ ሲሰባሰቡና ልዩ ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት ሲፈጠሩ የሚያዳብሩት ነው። በሌላው ወገን የሃይማኖትን ጥያቄ ስንመለከት ከደብቡ ይልቅ በመጀመሪያ ደረጃ በኃይል ተግባር የሆነው በአክሱም ግዛትና አካባቢው ብቻ ነው። የኋላ ኋላ ተቀባይነትን በማግኘት የተስፋፋ ነው ማለት ይቻላል። የአማርኛን ቋንቋና የግዕዝን ፊደል አመሰራረት ስንመለከት የህዝብ ቋንቋ የነበሩና በገዢውም መደቦች ቅርጽ በማግኝት የተስፋፉ ናቸው። ስለሆነም የአማርኛ ቋንቋ ልዩ የሆነና የጠቅላላው ህዝብ መግለጫ እየሆነ የመጣ ነው። እንደሚባለው ከሆነ ወደ 50% የሚሆኑ ቃላቶች ከኦሮምኛ ተወሰደዋል። በመሰረቱም ቋንቋ ሊዳብር የሚችለው ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር ሲገናኝና ሲዋሃድ ብቻ ነው። ለምሳሌ በጀርመንኛ ቋንቋ ውስጥ የእንግሊዘኛም ሆነ የፈረንሳይኛ ቃላቶች ተካትተዋል። በመሆኑም የአማርኛን ቋንቋ እንደ አገዛዝ መሳሪያና የአንድ ብሔረሰብ ቋንቋ አድርጎ መውሰዱ ስሀተት ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛም ነው። ጠቅላላው ህዝብ ደንቁሮ እንዲቀር የሚደረግ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ዘመቻ የሚካሄድበትና፣ በተለይም የውጭ ኃይሎች እንግሊዝና አንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከ1920ዎቹ ዓመታት ጀመሮ የሚያካሂዱት የማዳከምና፣ ህዝባችንን በጦርነት ዓለም ውስጥ በመንከር ርስ በርሱ እንዲጨፋጨፋ ለማድረግ የታቀደ የኢምፔሪያሊስቶች ሴራ ነው። በዚህ ዐይነቱ ሴራ ውስጥ ነው ወያኔም ሆነ በዚህም ሆነ በዚያኛው የስለላ ድርጀቶች የሰለጠኑ ኢትዮጵያውያን ዘመቻ የሚያካሂዱትና ለመጨራሻ ጊዜ የኢትዮጵያን ውድቀት የሚያፋጥኑት።

ያም ሆነ ይህ በአገራችን ምድር በብሔረሰብ ስም የተካሄደውና የሚካሄደው እንቅስቃሴና ጦርነት ፍልስፋና አልባና የዕውነተኛ ነፃነት መሰረት የሌለው ነው። በመጀመሪያ ደረጃ በማርክስዝምና በሶሻሊዝም ስም የሚምልና መመሪያው ያደረገ ትግልንና እንቅስቃሴውን በብሔረሰብ ደረጃ ሊገድበው አይገባም። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ያለውንና „ሁሉም ጭቁን ህዝቦች በአንድነት ተባብራቸሁ ተነሱ“ የሚለውን መፈክርና መመሪያ የሚቃውም ነው። እነ ሮዛ ሉክሰምበርግ የብሔረሰቦችን „የራስን ዕድል በራስ መወሰ“ን የሚለውን መፈክር ሲቃወሙ በመሰረቱ እንደዚህ ዐይነቱ አካሄድ ዓለም አቀፋዊነትንና ዕውነተኛ ነፃነትን የሚቃወምና፣ የነፃነትንንም ትግል የሚያደናቅፍ መሆኑን በመገንዘባቸው ነው። ከፕላቶን ፍልስፍና አንፃር ስንነሳ ደግሞ የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይልና በዕውቀት አማካይነት በማዳበር ለሁሉም ዜጋ የሚስማማ ህብረተሰብን ለመመስረት የሚያስችለውን አካሄድ የሚያደናቅፍ ነው። የሰውን የማሰብ ሃይል የሚገታና ተጨናግፎ እንዲቀር የሚያደርግ ነው። አንድ ግለሰብም ሆነ ብሔረሰቦች እግዚአብሔር የሰጣቸውን በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጸውን የማሰብ ኃይላቸውንና የፈጠራ ችሎታቸውን እንዳያዳብሩ የሚያግድ ነው። በዚህም ተባለ በዚያ የብሔረሰብ ጥያቄ በአንድ አገር ውስጥ ከሰፈነ አጠቃላይ የጭቆናና የፀረ-ዕድገት ፖሊሲ ጋር የተያያዘ ሲሆን ሊፈታም የሚችለው ጥቂት የብሔረሰብ ተወካይ ነን በሚሉትና በሚያካሄዱት የጦር እንቅስቃሴ አማካይነት አይደለም። ዕውነተኛ የነፃነትና የዕድገት እጦት በዚህ ዐይነቱ የፍልስፍና አልባ አካሄድ ተግባራዊ እንደማይሆን ከኤርትራው ትግልና ውጤቱ መማር ይቻላል። እንደምናየው ውጤቱ ፋሽሽታዊ አገዛዝና የጨለማ ኑሮ ነው። ውጤቱ ድህነትና መሰደድ ነው። ውጤቱ የህሊና ድቀትና ጠባብ አስተሳሰብን መጎናፀፍ ነው። በአጭሩ ውጤቱ ነፃነት ሳይሆን፣ በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽ የነፃነት እጦት ነው። አንድ ዲስፖቲያዊ አገዛዝ በመመስረትና ጦርነትን ፍልስፍናው በማድረግ አንድ ህዝብ ዘለዓለሙኑ እየተሰቃየ እንዲኖር የሚያደርግ ነው።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የወያኔ የክልል ፖሊሲ እንደምናየው ለየብሔረሰቦች ዕውነተኛ ነፃነትን ያጎናፀፈ አይደለም። ለከፋፍለህ ግዛ የሚያመች ፖሊሲ በመሆኑ፣ በየክልሉ አዲስ የዋር ሎርዶች(War Lords) እንዲፈልቁና ህዝቡን አድኸይተውና አደንቁረው ራሳቸው ተመቻቸውና ደልቶአቸው እንዲኖሩ አዲስ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል። በየአካባቢው ያለውን ሁኔታ ስንመለክት በዕቅድ የሚስራ ስራ የለም። ከተማዎችና መንደሮች በዕቅድ የተገነቡ ሳይሆኑ የድሮውን ሁኔታ በማባባስ ህዝባችን ከእንስሳ በታች እንዲኖር የተደረገበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በየአካባቢው በልማት ስም የሚካሄዱት እንቅስቃሴዎች የአበባ ተከላዎችና የስኳር አገዳ ተከላዎች ናቸው። ጨአትና ቡና በመትከል ህዝቡን ማደንዘዝና የውጭ ከረንሲ ለመቃረም የሚደረግ ሩጫ ነው። ያለፉትን የ25 ዓመታት የክልል ፖሊሲ ስንመለክት በህዝባችንና በታሪካችን ላይ ውድቀትን ያስከተለ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ እንደሰው የማሰብ ኃይሉን እየተጠቀመ እንዳይኖር የተደረገበት ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ ሰፍኗል። ይህ ዐይነቱ በብሔረሰብ ነፃነትና የራስን ዕድል በራስ መወሰን በሚለው ስም የሚካሄድ ፖለቲካ ለህብረተሰብአዊና ለሀብት እንቅስቃሴ(Social and Capital mobility) እንቅፋት የሆነ ነው። በአገሪቱ ውስጥ አጠቃላይ ህብረተሰብአዊ ሀብት(Soical Wealth)እንዳይዳብር ያገደ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በተለይም የአረብ አገሮችና ዕድገታችንን የሚቃወሙትንና፣ በተለያዩ ድሮች ያሰሩንን ኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው። ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የባህል ዕድገትና ምጥቀት እንዳይኖር የሚያግድና ድህነትን ያስፋፋና የሚያስፋፋ ነው። በመሰረቱ እንደዚህ ዐይነቱ ፖሊሲ የተፈጥሮንና የህብረተሰብ ህግን የሚፃረር እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። የሰውን ልጅ ወይም የእያንዳንዱን ዜጋ የማደግ ፍላጎት የሚያግድ ነው። በአንድ አገር ውስጥ ያለን ሀብት በስነ-ስርዓት እያወጡ በኃይልና(Energy) በማሽን አማካይነት እየተደገፉ በማምረት የሰውን ፍላጎት ለሟሟላት እንዳይቻል እንቅፋት የሚሆን ነው። በተፈጥሮና በሰው ልጅ መሀከል የሚኖረውን መደጋገፍና፣ እንዲሁም ደግሞ በሰዎች መሀከል በልዩ ልዩ መልከ መዳበር ያለበትንና ሊገለጽ የሚችለውን ግኑኝነት የሚጻረር ነው። የሰውን ልጅ ተፈጥሮአዊ የማሰብ ኃይል የሚያፍን የነፃነትና የዕድገት እንቅፋት ነው።

በመሰረቱ ከትግሬ ብሔረሰብ ወጣሁ የሚለውና ሃያአምስት ዐመታት ያህል አገራችንን የሚቆጣጠረውና የሚያተራምሰው አገርን የሚያዳከም እንጂ የብሔረሰቦችን መብት ተግባራዊ የሚያደርግና ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ የሚያደርግ አይደለም። እንደዚሁም የራሱን የትግሬን ብሔረሰብ ወይም ሰፊውን ትግሬን የሚጠቅም አይደለም። በዚያው ደንቁረው የሚያሰቃራቸው ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ለብሔረሰቤ ነፃነት የተጋልኩ ነኝ፣ ለዚህም ጠበቃ የቆምኩ ነኝ ካለና ድልን ከተቀዳጀ በኋላ መቀሌ ጠቅልሎ መግባት ነበረበት። መሀከል ከተማ ውስጥ ሆኖ በብሔረሰብ ስም ነፃነትና የራስን ዕድል በራስ መወሰን ስም እየተመጻደቀ በታሪክና በህዝብ ላይ መቀለድ አልነበረበትም፤ የለበትም። ታስቦም ሆነ ሳይታሰብ ወያኔ እዚህ ደረጃ መድረሱና በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች አርቲፊሻል መለያ መስጠቱ ለጊዜው የጠቀመው ቢመስልም፣ አንድ ቀን ህዝቡ ሆ ብሎ በአንድ ላይ ሲነሳ በወያኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በትግሬ ብሔረሰብና በዚህም በዚያም ብሎ ጥቅም አግኝቻለሁ ብሎ በሚሯሯጠው ላይ እንደሚነሳና መግቢያ እንደሚያሳጣው የታወቀ ነው። ስለሆነም የመጨረሻ መጨረሻ የትግሬ ብሔረሰብ እንዳለ ነው የሚጎዳው ማለት ይቻላል። በመሰረቱ ግን ወያኔ የተከተለው ፖለቲካ የትግሬን ብሔረሰብ እንዳለ የሚጠቅም ሳይሆን በቤተሰብ የተሳሰረ በአዲስ የገዢ መደብ የሚደገፍና፣ ከኤርትራ በመጡ በማፊያ መልክ በተደራጁ ኃይሎች የተከበበና በኢምፔሪያሊስት ኃይሎች የሚጠመዘዝና ማንኛውንም ድጋፍ የሚያገኝ ነው። ስለሆነም ህብረተሰብአዊ ትርምስና ድህነት እዚያው በዚያው እንዲቀጥሉ በማድረግ ህዝባችን የዕውነተኛ ስልጣኔ ባለቤት እንዳይሆን የሚያደርግ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። ዛሬ በአዲስ አበባ ውስጥ በየቦታው የሚታየው እጅግ አፀያፊ ተግባርና ሰፊው የአዲስ አበባ ህዝብ በቆሻሻ ቦታዎች እንዲኖር መገደዱ ከስግብግብነትና ከማን አለብኝነት ጋር የተያያዘ ነው። ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ከውጭ ኃይሎች ጋር በጥቅም በመተሳሰርና ተላላኪ በመሆን የታሪክን ሂደት በማጣመም በቀላሉ ልንወጣው የማንችለው የተወሳሰበ ችግር ውስጥ ጥለውናል ማለት ይቻላል።

ይህ ዐይነቱ አካሄድ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርና ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሔረሰብ የተውጣጣ ግለሰብ እንደሰውና እንደዜጋ እንዳይታይ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን የአገሩን ስም በስሙ እንዳይጠራ የሚያስገድደው ነው። በአንድ አገር ውስጥ ተወልዶ የአገሩን ስም እንዲጠራ ሳይሆን፣ ከአንድ ክልል ተወለድኩ ብሎ እንዲጠራ የሚያስገድደው ነው። „ከእናቴ ሳይሆን ከማህፀኗ ነው የተወለድኩት“ ብሎ እንደመናገር ዐይነት አስተሳሰብ ተስፋፍቷል፤ የጊዜው ፈሊጥም ሆኗል። ይህ ዐይነቱ ዘመቻና ጥላቻ በመሰረቱ አንድነትንና ሁለንታዊነትን፣ ወይም ደግሞ በአንድ ነገር የተጠቃለለን ግን ደግሞ ልዩ ልዩ ነገሮችን የያዘውን የተፈጠሮን ህግ የሚቃወም ነው። ተፈጥሮም ሆነ ሰው በአንድነትና በልዩ ልዩ ነገሮች ብቻ ነው የሚገለጹት። በአንድ በኩል እንደ ግለሰብአዊ፣ በሌላ ወገን ደግሞ እንደ ህብረተሰብአዊ አካል። ሰውነታችንም እንደዚህ አንድም ሁለንታዊም ነው። ማንኛውም ሰው እንደሰው የሚገለጸውና እንደሰውም የሚኖረውና የሚያስበው የተለያዩ ኦርጋኖችና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ሲኖሩት ብቻ ነው። እንደሚታወቀው የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በስራ-ክፍፍል የተደራጁና፣ በሌላ ወገን ደግሞ ስራቸውን በማቀነባበር እንደሰው እንድንቀሳቀስ፣ እንድናሰብና እንዲሁም እንድንፈጥርና እንድንሰራ የሚያደርጉን ናቸው። ከዚህ ስንነሳ በብሔረሰብ ስም ተሳቦ በወያኔ ተግባራዊ የሆነው የክልል ፖለቲካ ይህንን ተፈጥሮአዊ ህግ ወይም ዩኒቨርሳል ህግ የሚቃወም ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው ህዝብም ጠላት ነው ማለት ይቻላል።

የኢትዮጵያ ጠንቆችና ኢትዮጵያዊነትን የሚቀናቀኑ አካሄዶች!

ኢትዮጵያዊነትን አጉልቶ የሚጠራ ወይም ሞትኩልሽ እያለ ባንዲራ የሚያውለበልብና፣ ለስልጣን ብሎ እዚህና እዚያ የሚሯሯጥ ሁሉ ዕውነተኛ ኢትዮጵያዊ ወይም ሰው ነው ሊያሰኘው የሚያስችል አይደለም። ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት አፄ ኃይለስላሴና ደርግም ኢትዮጵያውያን ቢሆኑም በመሰረቱ የኢትዮጵያን አንድነትና የህዝቦቿን ፍላጎት አናግተው ነው የሄዱት። በመሰረቱ አንድ የገዢ መደብ ስልጣን ላይ በሚቆይበት ጊዜ የገዢ መደብ ነኝ ብሎ ለመመፃደቅ ሳይሆን መስራት ያለባቸው ታሪካዊና ህብረተሰብአዊ ግዴታዎች አሉ። አንድ መንግስትና በአንድ አገር ውስጥ ያለ ሀብት የገዢ መደቦች የግል ሀብት አይደሉም። በአንድ አገር ውስጥ ያለ ሀብት የጠቅላላው ህዝብ ሀብት ነው። መንግስትም ሆነ የመንግስት መኪና የህዝብ ተወካዮች እንደመሆናቸው መጠን አባትና እናት ልጆቻቸውን መንከባከብና በስነስርዓት ማሳደግ እንዳለባቸው ሁሉ አንድ የገዢ መደብና መንግስታዊ መዋቀሮች የአንድን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት በማሟላት ወደ ሚቀጥለው የዕድገት ደረጃ ለመሸጋገር አስፈላጊዊን ቅድመ-ሁኔታዎች ማዘጋጀት አለባቸው። ለዕድገት የሚሆኑ አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር አለባቸው። ከዚህ ስንነሳ በተለይም የአፄው አገዛዝ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ያሰጠበቀና አገሪቱ በፀና መሰረት ላይ እንድተገነባ ማድረግ የቻለ አልነበረም።

በመሆኑም በአንድ በኩል ኢትዮጵያ አገሬ እያሉና ባንዲራ እያውለበለቡ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ደህንነትና ብልጽግና እንዲሁም አገራችን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዳትሆን አጥብቀው የሚታገሉና ከተለያዩ የኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር የሚሰሩ ትላልቅ ሰዎች የሚመስሉ አሉ። በአብዛኛዎቻችን ዘንድ የተደረሰበት መደምደሚያ እዚህና እዚያ የሚንቀሳቀሱ የብሔረሰብ እንቅስቃሴዎች ብቻ ለአገሪቱ ደህንነት አደገኛ እንደሆኑ ነው። ከነዚህ ይልቅ እስከዛሬ ውስጥ ለውስጥ እንደነቀርሳ የሚሰረስረን በመሰረቱ ከፊዩዳላዊ አስተሳሰብ ያልተላቀቀና፣ ጥቅሙንና ህልሙን በተለይም ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር ያገናኘ የድሮው ቢሮክራሲና የአሪስቶክራሲ ልጅ፣ እንዲሁም ደግሞ አዲስ ብቅ ብቅ ያሉ የዓለምን ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር በደንብ ያላገናዘቡ ኤሊት ነን ባዮች ናቸው ለአገራችን አንድነትና መበልጸግ ጠንቆች የሆኑትና የሚሆኑት። የተሰጣችውን መድረክ በመጠቀም ወጣቱን የሚያሳስቱና፣ የሾለና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ኖሮት አገሩን በፀና መሰረት ላይ እንዳይገነባ የሚያደርጉ ናቸው። በተለይም የአገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሳይንሳዊ ፈሩን ለቆ ከወጣ ከዛሬ አርባ ዐመታት ጀምሮ የሁሉም ትግል ስልጣንን በመጨበጥ ላይ ያተኮረ ስለሆነ በፖለቲካ ስም የተካሄደው ውዝግብ ሰፋ ላለ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ሳይንሳዊ ክርክር አመቺ አልነበረም። ቡድናዊ ስሜትም ስላየለና ፖለቲካውም ይበልጥ በዘለፋና በጥላቻ ላይ የተመረኮዘ ስለነበር ስነ-ስርዓት ባለው መልክ ለመታገልና ወጣቱን ለማስተማር በፍጹም አልታቻለም። አብዮቱ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ድምጥማጡ ጠፋ ከተባለ በኋላም አዲስ ምሁራዊ ኃይል ብቅ በማለት ወጣቱን ማስተማርና የበሰለ አስተሳሰብ እንዲኖረው ማድረግ አልተቻለም። በመሆኑም ዕውነተኛ በሳይንስና በጥበብ ላይ የተመረኮዘ ኢትዮጵያዊ ስሜትን ማዳበር አልተቻለም። ዛሬም እንደትላንትናው ፊዩዳላዊ አሰትሳሰብ ከጥራዝ ነጠቅ የዘመናዊነት አስተሳሰብ ጋር በመዋሃድ ዕውነተኛ ኢትዮጵያዊ ስሜትን የሚያኮላሽ የመሳፍንት አገዛዝ ለማምጣት ደፋ ቀና እየተባለ እንደሆን እንመለከታልን።

ስለሆነም በአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት እዚህና እዚያ የተደረገውን መጯጯህና ጠላት ነው በሚባለው ላይ ያነጣጠረውን ተቃዎሞ ስንመለከት፣ ሁላችንንም አንድ የሚያደርገን አንድ ነገር ብቻ ነው። ሁላችንም በወያኔ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ አለብን። ይሁንና ግን ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ስንመጣ የሚያለያዩንና የማንስማማባቸው አያሌ ጉዳዮች አሉ። አንደኛ ፣ ወያኔ እንዴት ስልጣን ላይ እንደወጣና በዚህ ዐይነቱ አገር አፍራሽ ፖለቲካው ማን ከበስተጀርባው እንዳለና፣ የሃሳብና የማቴሪያል ድጋፍም እንደሚሰጠው በመሀከላችን ስምምነት የለም። ቢታወቅም እንኳ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ስሙ እንዲነሳ አይፈለግም። እንዲያውም በአንዳንድ ተቃዋሚ ነን፣ የዚህ ወይም የዚያ ድርጅት የውጭ ፖለቲካ ተጠሪ ነን በሚባሉት ቃለ-መጠይቅ ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ ለወዳጅ አገሮች አስታውቀናል እያሉ ነው። ይህ ዐይነቱ አባባል በመሰረቱ የትግልን ዲያሌክቲክንና ሎጂክን በፍጹም አይመለከትም። አንድ የውጭ ኃይል ስልጣን ላይ ካለ አገዛዝ ጋር እጅና ጓንቲ ሆኖ የሚሰራ ከሆነና፣ አገዛዙ አገራችንን በማፍረስ ፖለቲካው እንዲገፋበት ማንኛውንም ዐይነት ድጋፍ የሚሰጠው ከሆነ ሎጂካሊ ሲታሰብ አንደኛው ወዳጅ፣ ሌላው ደግሞ ጠላት ሊሆን አይችልም። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ እጅግ የተምታታና ከሳይንስና ከሎጂክ ጋር የማይጣጣም ትግል የሚባለው ፈሊጥ ለህዝባችንና ለአንድነታችን የሚደረገውን ትግል ዓላማ-ቢስ ያደርገዋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ አገዛዙ እስካሁን ድረስ በተከተለውና በሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይና፣ ህዝባችንን ወደ ድህነት በገፈተረው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ አንዳችም ስምምነት የለም። እንዲያውም በአብዛኛዎች አነጋገርና ግንዛቤ አሁንም ቢሆን በአገራችን ምድር በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው የሚካሄደው እየተባለ ነው የሚነገረን። ሀቁ ግን እነ አቶ መለስ ስልጣን ሲይዙ ከቀረበላቸው ቅድመ-ሁኔታዎች አንዱ የኒዎ-ሊበራል የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ነው። በመሆኑም በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ አማካይነት የዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው ባዘዘው መሰረት የነፃ ገበያ ቅድመ-ሁኔታዎች ናቸው አንድ በአንድ የዋሉት። እነዚህ ደግሞ በተግባር ሲተረጎሙ ስትራቴጂክ የሆኑ የአገሪቱ ሀብቶች በአገዛዙና በእሱ ስር በተደራጀው ኤፈርት በሚባለው ድርጅት ቁጥጥር ስር ነው እንዲወድቁ የተደረገው። ይህ ዐይነቱ በውጭ ኃይሎች ተዘጋጅቶ የመጣውና ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው አገራችንን መቀመቅ ውስጥ የከታት።

በመሀከላቻን ያለው ትልቁ ችግር ትግል በሚባለው መድረከ ውስጥ ከዚህም ከዚያም የተሰባሰበ፣ የዚህ ወይም የዚያኛው ድርጅት አባል ወይም ደጋፊ የነበረ፣ ክፉም ሆነ ደግ ስራ የሰራ በአንድ የትግል መድረክ ውስጥ መካተታቸው ነው። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታትም የጭንቅላት ተሃድሶ ስራ ስላልተሰራ ትግል የሚባለው ፈሊጥ በመግበስበስ የሚካሄድ እንጂ በጠራ ርዕይ ዙሪያ ጥናት እየተጠና አይደለም። ስለሆነም አንዳንዱ በሚጠይቅበት ጊዜ የሚሰጠው መልስ ወያኔን ከመጥላት የሚያልፍ አይደለም። አብዛኛው ታጋይ ወይም የአገር ተቆርቋሪ ነኝ ባይ፣ ትግሉ ይህንን ወይንም ያንን ድርጅት፣ ይህንን ወይንም ያንን ግለሰብ ከመደገፍና ከማምለክ የሚያልፍ አይደለም። ይህም ማለት እስከዛሬ ድረስ የሚካሄደው ትግል ህዝባችንን የስልጣኔ ባለቤት ለማድረግና አገራችንም በአካባቢው አገሮች ደግሞ ምሳሌ እንድትሆንና እንድትከበር ሳይሆን ስልጣን ላይ ለመቀመጥና ለመታወቅ ብቻ የሚደረግ ትግል ነው ። ከዚህ ስንነሳ ትግሉ የአገር ወዳድነት ስሜት ይኑረው አይኑረው ለማወቅ በጣም የሚያስቸግር ነው። መግበስበስ የበዛበት ትግል በመሆኑ ትግሉን መልክ ለማሲያዝና፣ ወዳጅና ጠላትን ለመለየት የማይቻልበት ሁኔታ ከተፈጠረ ረዘም ያለ ጊዜ ሆኗል ማለት ይቻላል።አንዳንዱ ግራ ይሁን ቀኝ፣ ፋሺስት ይሁን ሌላ፣ በአጭሩ ምን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም እንደሚከተል የሚታወቅ ነገር የለም። ስለዚህም ሰፋ ወዳ አለና ወደ ተወሳሰበው የዓለም ሁኔታ ስንመጣ አብዛኛዎቻችን፣ በተለይም ደግሞ በተከታታይ ለድህረ-ገጾች የሚጽፉም ሆነ ተጋብዘው ንግግር የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ስለዓለም ሁኔታና የዓለም ፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ አወቃቀር፣ እንዲሁም በአገራችን ላይ ስለሚኖራቸው ተፅዕኖ የሚያስተምሩንና የሚነግሩን ምንም ነገር የለም። መሰረታዊ በሆኑ ጥያቄዎች ላይ ግልጽነት ከሌለ ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነትና፣ እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ለተመሰረተ ሰፋ ላለ ኢኮኖሚ መታገል በጣም አስቸጋሪ ይሆናል ማለት ነው።

እንደሚታወቀው እ.አ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ የዓለም የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ ሁኔታ እጅግ እየተመሰቃቀለና፣ በተለይም አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮችና ህዝቦቻቸው ከአቅማቸው በላይ እየሆነ መጥቷል። ኮሙኒዝም ከፈራረሰ በኋላ ብቸኛው ኃያል መንግስት እኔ ብቻ ነኝ የሚለው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በሱ ቁጥጥር ስር ያሉ፣ የዓለም አቀፍን ስም የያዙ ኢንስቲቱሽኖችን መሳሪያ በማድረግ፣ በተለይም በአፍሪካ አገሮች ላይ ጫና በማድረግ ኢኮኖሚያቸውን ለማዘበራረቅ ችሏል። በነፃ ገበያ ስም አማካይነት ተግባራዊ የሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ፣ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ሲያደልቡ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሰፊው ህዝብ ወደ ድህነት እንዲገፈተር ተገደደ። የውጭው ገበያ ክፍት በመሆኑ ከውጭ የሚገባው አዳዲስና በጠቀሜታ ላይ(Second hand goods)የዋሉ ዕቃዎች ከውስጥ የማመረት ኃይላቸውን አዳከሙ። በዚህም ምክንያት የተነሳ አዳዲስ የስራ መስክ መከፈት ቀርቶ፣ ራሱ ሰራተኛው ሲሰራ ከነበረበት በመባረር የስራ አጥ ለመሆን ተገደደ። ይህ በራሱ በትላልቅ ከተማዎች ውስጥ አዲስ ዐይነት የህብረተሰብ ቀውስ በመፍጠር፣ ተከታታይና ጥሩ ገቢ የሌለው ሰፊ ህዝብ በቆሻሻ ቦታዎች(Slums) እንዲኖር ተገደደ። በሌላ ወገን ደግሞ አዳዲስ የሚሰሩት ህንፃዎችና የመኖሪያ ቤቶች ከተማዎቹ ውስጥ ካሉት የመብራትና የንጹህ ውሃ አቅርቦት ጋር እየተመጣጠኑ ባለመሰራታቸው በከፍተኛ ደረጃ ንጹህ ውሃንና ኃይልን በመጋራት ሰፊው ህዝብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዲወድቅ ተገደደ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አፍጦ አግጦ ይታያል።፡በግሎባላይዜሽንና በነፃ ንግድ ስም ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደምናየው አገራችን ከጥገኝነት ያላቀቀ ሳይሆን የባሰውኑ ዕዳ ውስጥ የከተተንና፣ ኢኮኖሚያችንን ያዘበራረቀ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ አገራችን እንደ አገርና ህዝባችንም እንደ ህብረተሰብ እንዳይታይና ህልሙንና ፍላጎቱን ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችልበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ተደርጓል። የኢትዮጵያዊነት ትርጉሙም እየጠፋና ሰፊው ህዝብ እየተናቀና ተመጽዋች እየሆነ ለመኖር ተገዷል።

ይህ በቻ አይደለም፤ የአሜሪካን ኃያል መንግስት በቻይናና በአንዳንድ በኢኮኖሚ እያደጉ በመጡ አገሮች የበላይነቱን ላለመነጠቅ ሲል በአንዳድን አፍሪካ አገሮች ውስጥ የጦር ሰፈሩን በመዘርጋት፣ ብዙ የአፍሪካ አገሮች በጦርነት እንዲታመሱ እያደረገ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ አገዛዞች ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው በማለትና መኮንኖችን በማሰልጠን የብዙ አፍሪካ መንግስታትን አትኩሮ ወደ ጦርነት እንዲያዘነብሉ ማድረግ ችሏል። ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለማህበራዊ ፕሮጀክቶች ሊውሉ የሚችሉ ሀብቶች በዚህ ዐይነቱ አሳሳቸ ፖሊሲ አገሮች እየወደሙ ናቸው። የወያኔ አገዛዝም በዚህ ዐይነቱ የፀረ-ሽበርተኝነት ፖሊሲ በመካተት ይኸው እንደምናየው ራሱን ማጎልመሱ ብቻ ሳይሆን የሰው አገር ድንበር ጥሶ በመሄድ አገራችን ተወዛግባ እንድትኖር አላስፈላጊ ሁኔታዎች ፈጥሯል።

በመሰረቱ እነዚህ ከላይ አጠር መጠን ባለ መልክ የዘረዘርኳቸው ጉዳዮች የፖለቲካ ፓርቲዎችና በየጊዜው በየተሌቪዠኑ እየቀረቡ ገለጻ የሚሰጡ፣ ወይም ስለ ዓለም ፖለቲካ የጥያቄና መልስ ምልልስ የሚያደርጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ተግባሮችና ግዴታዎች ነበሩ። እንደማየውና እንደምከታተለው ከሆነ ጋዜጠኞችም ሆነ ራሳቸው ተጠያቂዎቹ በዓለም ላይ ምን እንደሚካሄድ የማያውቁ ይመስል የሚጠይቁትና የሚሰጡትም መልሶች ከተጨባጩ የዓለም ሁኔታ ጋር በፍጹም የሚጣጣም አይደለም። ሁኔታው በዚህ መልክ የሚቀጥል ከሆነ ጋዜጠኞችም ሆነ ራሳቸው ተጠያቂዎች በብዙ ሺህ የሚቆጠር ወጣትን በማሳሳት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ደብዛው እንዲጠፋ ለማድረግ ይችላሉ። ዕውነተኛ የአገር ወዳድ ስሜትነት እንዳይዳብር በማድረግ ይህንን ወይንም ያኛውን ኃያል መንግስት እየተለማመጠ የሚኖር ትውልድ እንዲኮተኮትና የስልጣኔውም መንግድ እጅግ አስቸጋሪ እንዲሆን መንገዱን ሁሉ ያመቻቻሉ።

ስለሆነም የኢትዮጵያ ጠንቆችና ኢትዮጵያዊነትን የሚቀናቀኑ አስተሳሰቦችና የትግል ዘዴዎች ናቸው የምላቸው ነገሮች አብዛኛውን ጊዜ ዋና ምክንያታቸው በሰፊውና በሎጂካዊ መንገድ ካለማሰብ የመነጩ ናቸው። አብዛኛዎቻችን አንድ ወጥ አመለካከት አዳብረናል። አገርን በመገንባትና በማፍረስ መሀከል የተደረገውን በውስጥና በውጭ ኃይሎች መሀከል ያለውን የተወሳሰበ ትስስር ለማየትና ለመተንተን የምንችልበት መሳሪያ ያለን አይመስለኝም። በተለይም የተለያዩ ምሁሮች በአንድ ነገር ላይ ለምን የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል ብለን ጥያቄ ስለማናቀርብ ነገሩን በመናቅና በመናናቅ መሀከል ያለ፣ ወይም ያለመስማማት ችግር አድርገን እንወስደዋለን። በመሰረቱ በሁለት ሰዎች ወይም በተለያዩ ድርጅቶች መሀከል ስምምነት ሊኖር የማይችለው አንድን የህብረተሰብ ሁኔታ በተለያየ መልክ ስለሚተረጉሙትና የተለያየ መልስ ለመስጠት ስለሚፈልጉ ነው። ወደ አገራችን ስንመጣ ያለው ችግር ግን በመሰረቱ አንድን የህብረተሰብ ታሪክ ለማንበብ የሚያስችለን አስተሳሰብ ወይም ስልት(School of Thought) ለማዳበር ያለመቻላችን ነው። አብዛኛዎቻችን በምን ዐይነት ቲዎሪ እንደምንደገፍና አንድን ተጨባጭ ሁኔታ እንዴት አድርገን ማንበብ እንዳለብን የተገነዘብን አይመስለኝም። ካለቲዎሪ ተግባር ስለማይኖር፣ በጭፍኑ የሚደረግ ትግል ወደ አጉል ግብግብና ጥፋት ያመራናል።

ስለዚህም ለኢትዮጵያ ጠንቅ የሆኑ ነገሮች፣ 1ኛ) የሃሳብ ጥራት አለመኖር፣ 2ኛ) በአንዳች ዐይነት ርዕይ አለመመራት፣ 3ኛ፟) የሃሳብ ጥራትና ርዕይ ሳይኖር ይህንን ሆነ ያንን ድርጅት በመከተል ወደ ጠብ ማምራት፣ 3ኛ) ለመደማመጥ ያለመቻል፣ 4ኛ) በፕሪንሲፕል አለመመራትና ለህሊና ለመገዛት አለመቻል፣ 5ኛ) ለአገር ዕድገትና ስልጣኔ የሚደረገው ትግል ከፍተኛ ዕውቀትን እንዲመጠይቅ ለመገንዘብ አለመሞከር፣ 6ኛ) ስለሆነም በዕድገት ስም የሚምል ወይም ተማርኩ የሚል ሁሉ ስለ ዕድገት አንድ አንድ ዐይነት አመለካከት ሊኖረው እንደማይችል ለመረዳት አለመሞከር፣ 7ኛ፟) ይህንን በሚመለከት በምሁራን ዘንድ የተደረገውን ሰፋ ያለ ትግልና ክርክር ለማወቅ አለመጣር፣ 8ኛ) የፖለቲካን ትርጉም ለመረዳት ያለመቻል፣ 9ኛ) የዓለምን የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ አወቃቀር በየዋህነት መነጽር መመልከት 10ኛ፟) አሳሳች ኃይሎችን ለማወቅ ጥረት አለማድረግና ዝም ብሎ እነዚህ ወዳጃችን ናቸው፣ ይረዱናል ብሎ ዝም ብሎ በጭፍን ዕምነት መጓዝ… ወዘተ. እነዚህና ሌሎች አያሌ ነገሮች ለአገራችን ዕድገትና ሰላም ለሚደረገው ሰፊው ህዝባችን እንቅፋት በመሆን ተብትበውን ይዘዋል። ጤናማ የሆነ በሰብአዊነትና በዲሞክራሲያዊ መሮሆች ላይ የተመረኮዘ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዳይዳብር ያግዱናል። ከድህነት እንዳንላቀቅና ዘለዓለማችንን ተመጽዋች ተቀባይ እንድንሆን ያደርጉናል። ባጭሩ የሳይንስና የቴክኖሎጂውን መንገድና ለሁለ-ገብ የሚደረገውን በራስ ላይ የመተማመንን ትግል ያግዱብናል፤ ዘለዓለማችንን በጨለማ ዓለም ውስጥ እንድንኖር ያደርጉናል።

የብሔረሰብ ጥያቄ አፈታትና የፌዴራሊዝም ጉዳይ!

ለሁላችንም ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ የብሔረሰብን ጥያቄ በክልል እየከለሉ ችግሩን መፍታት በፍጹም አይቻልም። ከላይ ደረጃ በደረጃ ለማሳየት እንደሞከርኩት መስረታዊ ጥያቄ የተገለጸለት ዲሞክራሲያዊ ኢንስቲቱሽንና የፖለቲካ ጥበብን የተካነ መደብ አለመኖሩ ነው ያለውን መጠነኛ አለመግባባት ሊያባብሰው የቻለውና የሚችለው። በተለይም ያልተገለጸለትና ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ ኢንስቲቱሽንና የገዢ መደብ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመቆላለፍ ማንኛውንም አገር አፍራሽ ፖሊሲ የሚያካሄድ ከሆነና የጦር ሰፈርም በመስጠት በአካባቢው ሰላም እንዳይኖር የሚያደርግ ከሆነ ለብሔረሰብ ነፃነት እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች ነገሩን ሊያባብሱት ይችላሉ። ከእንደዚህ ዐይነቱ አስቸጋሪ ሁኔታ መውጣት የሚቻለው በሁሉም ነገሮች ላይ ግልጽ የሆነ ውይይትና ጥናት ሲካሄድ ብቻ ነው። በፍልስፍናና በሳይንስ ዙሪያ ግልጽ አቋም መያዝ የተቻለ እንደሆነና፣ የነፃነት ጉዳይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚመለከት መሆኑን ግንዛቤ ከተደረሰበት በቀላሉ መፍትሄ መስጠት ይቻላል።

በመሰረቱ የአንድ ብሔረሰብም ሆነ ህዝብ ጥያቄ በመጀመሪያ ደረጃ መሰረታዊ ነገሮችን፣(Basic Needs) ማለትም፣ የተስተካከለ ምግብ፣ ንጹህ ውሃ፣ መጠለያ ማግኘት፣ ህክምናና ትምህርት ቤት ማግኘት ናቸው። እነዚህ ነገሮች የማንኛውም ህዝብ ጥያቄዎችና ከመብትም ጋር በጥብቅ የሚተሳሰሩ ናቸው። ማንኛውም ብሔረሰብ ሰው እንደመሆኑ መጠን፣ ለመኖር፣ ለማሰብና ለመስራት ይችል ዘንድ በየጊዜው ተመጣጣኝ ምግብ ማግኘት አለበት። እንዲዚሁም ንጹህ ውሃ ማግኘት አለበት። የለም መጀመሪያ መብትህን ማግኘት አለብህ፤ ለዚህም የራስህን ዕድል በራስህ ለመቀዳጀት ከፈልግህ ታጋል የሚባል ከሆነ አንድ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳይቀዳጅ እንደማድረግ ይቆጠራል። በተለይም በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የብሔረሰብ ጥያቄ እንደመታገያ መሳሪያ ሆኖ ተወስዶ አይታወቅም። በአውሮፓ የትግል ታሪክ ውስጥ ቅድሚያ የተሰጣቸው ጭንቅላትን የሚያዳብሩ የፍልስፍናና የተፈጥሮ ሳይንስ እንዲሁም ቋንቋን ማበልጸግና በማዳበር ላይ ያተኮረ ነበር። በሁሉም አገሮች የተለያዩ ቋንቋዎች ይነገሩ ነበር። ይህ አካሄድ አለመግባባትን በመፍጠሩና፣ ለዕድገትም እንቅፋት በመሆኑ የግዴታ አንድ ቋንቋ መፍጠርና ማዳበር ተቻለ። በዚህ አማካይነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ስልጣኔ መቀዳጀት ተቻለ። ወደእኛ አገር ስንመጣ ግን የተያዘው የዳበረውን የግዕዝና የአማርኛ ቋንቋ በማጥፋት ሁሉም አዲስ በተፈጠረለት አዲስ ፊደልና በቋንቋው እንዲነጋገር በማድረግ ህዝቡ ጭንቅላቱን እንዳይከፍትና እንዳይፈጥር ማድረግ ነው። በተለይም የቋንቋ ምሁራን ነን የሚሉ የእንግሊዝ ሰላዮች በአገራችንና በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በመሰግሰግ አደገኛ ስራ እየሰሩ ነው። በውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ውስጥ የተሰገስጉ የእንግሊዝ ሰላዮችና ትላልቅ ህንፃዎች በመገንባት በዕርዳታ ስም የሚዘባነኑት ዋና ተልዕኮአቸው ብሔረሰብን ከብሔረሰብ ማጋጨትና በተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮች መሀከል መፋጠጥ እንዲኖርና የርስ በርስ ጦርነትም እንዲከካሄድ ማድረግ ነው። ለሁሉም ህዝብ ደህንነትና ለአገራችን ዕድገት እታገላለሁ የሚል ሁሉ ይህንን የተመሰጣጠረ ሁኔታ ጠጋ ብሎ መመልከትና መመርመር አለበት። በየዋህነት እዚህና እዚያ የሚደረገው መሯሯጥ የመጨረሻ መጨረሻ ገደል ውስጥ ነው የሚከተን።

ሰለዚህም የችግሩ አፈታት ከዲሞክራሲያዊ ሁኔታዎችና ቀስ በቀስ ብቃትነት ያላቸው አገር አቀፋዊ እንስቲቱሽኖች ከመቋቋማቸው ጋር የተያያዘ ነው። ብሔረሰብን በክልል አካልሎ ፌዴራላዊ አገዛዝ ነው ያለው ማለት ቀልድ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ፌደራላዊ አወቃቀር ከሪፑብሊካዊ አስተሳሰብና አገዛዝ ጋር የተያያዘ ነው። በሌላ አነጋገር የአንድን ግለሰብም ሆነ የአንድን ደርጅት ዲስፖታዊ አገዛዝና ሬሶርስን መቆጣጠር የሚቃወም ነው። ሪፑብሊካዊ አገዛዝ የግለሰብ ነፃነቶችንና ከዚህ ጋር የተያያዙ ማንኛውም መብቶችን፣ ማለትም የፕሬስ ነፃነትና በነፃ መደራጀትንና ሃሳብን መግልጽ የሚያከብር ነው። ሪፑብሊካዊ አወቃቀር በገዢው መደብና በመንግስት መኪና መሀከል ያለውን ልዩነት ቁልጭ አድርጎ የሚያስቀምጥና፣ የመንግስት ኢንስቲቱሽኖች የአንድ የገዢ መደብ የግል ሀብት እንዳልሆኑ የሚያረጋግጥ ነው። በመሆኑም በህግ አውጭው፣ አጽዳቂውና አስፈጻሚው መሀከል የስራ ክፍፍል መኖር አለበት። አንድ የገዢ መደብ በህግ አስከባሪ ፍርድ ቤት ውሳኔ ውስጥ መግባት የለበትም። ይህ ሲሆን ብቻ ወደ ፊዴራሊዝም ስርዓት ለማምራት ይቀላል።

በመሰረቱ የፌዴራላዊ ስርዓት አወቃቀር ሀብትን ለማንቀሳቀስና ለዕድገት የሚያመች ነው። በማዕከላዊ አገዛዝ አማካይነት ተግባራዊ ሊሆን የማይችለው ዕድገትና ከዚህ ጋር የተያያዙ እንስቲቱሽናዊ ለውጦችና መሻሻሎች ተግባራዊ ሊሁኑ የሚችሉት አንድ አገር በፌዴራል ደረጃ ስትዋቀር ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በክፍለ-ሀገሮች መሀከል ውድድር እንዲኖር በማድረግ ዕድገትን ያፋጥናል። ይሁንና ግን አንድን አገር በፌደራል ደረጃ ማዋቀር የግዴታ በየቦታው የተገለጸለትና የማሰብ ኃይሉ ከፍተኛ የሆነን አገዛዝንና የተማረ የሰው ኃይልን ይጠይቃል። እንደ አገራችን ባለ ሁኔታ ውስጥ በክልል ደረጃ የሚዋቀር ፌዴራልዝም የግዴታ ወደ ዋር ሎርድነት የሚያመራና ዕድገትን የሚቀናቀን አካሄድ ይሆናል ማለት ነው። በየክልሉ ተዋቀሩ የተባሉት የፌዴራሊዝም አስተዳደሮች በሙሉ በምንም ዐይነት ፊዴራሊያዊ የሚያሰኛቸው አይደሉም። በአጠቃላይ ሲታይ በአንድ ዲስፖቲያዊ አገዛዝ ቁጥጥር ስር ያሉና ባስፈለገበት ጊዜ ጣልቃ በመግባት በኗሪው ላይ ጦርነት የሚያውጅ ነው። በየቦታው የሚካሄዱትም የልማት ክንውኖች በሙሉ አገራችንን ወደ ማዕከለኛው ዘመን በፍጥነት እንድትጓዝ ያደረጉ እንጂ ሰፊውን ህዝብ ከድህነት ያላቀቁና ስርዓት ያለው ኑሮ እንዲኖር ያደረጉ አይደሉም።

ክዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ለመውጣት ቀደም ብዬ ባለፈው ጽሁፌ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በመጀመሪያ ደረጃ ከሁሉም ብሔረሰቦች የተውጣጡ ግለሰቦች የሚሰለጥኑበት ኢንስቲቱሽን ማዋቀርና እዚያው ውስጥ ገብተው እንዲማሩ ማድረግ ችግሩን ሊፈታው ይችላል ብዬ አምናለሁ። በመሰረቱ በአገራችን ያለው ችግር የብሔረሰብ ጥያቄ አለመፈታት ጉዳይ አሁንም አገራችን ፊዩዳላዊ ወይም ያልተገለጸለት አስተሳሰብ ባላቸውና ኋላ-ቀር በሆኑ እንስቲቱሽኖች መተዳደሯ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ህዝባችን እንዳይማርና እንዳያውቅ ተደርጓል። ርስ በርሱ እንዲጠራጠር ሆኗል። ይህንን ችግር ለመፍታት የሚቻለው ከኤሊት ትምህርት ባሻገር አጠቃላይ የሆነ የማስተማር ዘመቻ ሲካሄድ ነው። በቅርቡ በሁለት የዲሞግራፊ ፕሮፌሰሮች አማካይነት ተጽፎ ለንባብ ከቀረበ መጽሀፍ መገንዘብ የሚቻለውና ብዙ ጥናቶችም የሚያረጋግጡት ለአንድ አገር ችግር ዋው መፍትሄ ሰፊውን ህዝብ ያካተተ ትምህርትና ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕውቀት አስፈላጊ እንደሆኑ ነው። ከዚህ ስንነሳ የብሔረሰቦች ችግር እየተባለ የሚጠራውንና እንደ ጊዜ ቦንብ ሆኖ የሚፈራውን ችግር መፍታት የሚቻለው በዕውቀትና በተስተካከለ ዕድገት አማካይነት ብቻ ነው። በሌላ ወግን ግን ከዛሬ የክልል ፌደራሊዝም ይልቅ በክፍለ-ሀገር ደረጃ የዋቀረ ለስራና ሀብትን ማንቀሳቀስ የሚያመች ፊዴራላዊ አወቃቀር ቢዘረጋ ለዕድገት በጣም ያበጃል። በየክፍለ-ሀገራት የሚዋቀረውም አስተዳደር በዕውቀትና በችሎታ ሲሆን እንደ ቋንቋ የመሳሰሉትን ነገሮች በቀላሉ መፍታት ይቻላል። ያም ሆኖ የአማርኛ ቋንቋና ወደፊት ደግሞ ግዕዝ ብሔራዊ ቋንቋ ብቻ ሳይሆኑ የሳይንስና የፍልስፍና መማሪያዎች ሆነው መዳበር አለባቸው። እነዚህን በማዳከምም ሆነ በመከልከል ዕድገትን መቀዳጀት አይቻልም። እነዚህ ሁለቱ ቋንቋዎች በሁሉም ነገር የዳበሩና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ የሚያመቹ ናቸው። አሁን በቅርቡ በፊዚክስና በማቲማቲክስ በሰለጠኑ ኢትዮፕያውያን ፕሮፌሰሮች ከአማርኛ፣ ከግዕዝ፣ ከኦሮሞኛና አንዳንድ የእንግሊዘኛ ቃላት ታኮሎበት ለመማሪያ የቀረበው መጽሀፍ የሚያረጋግጠው በአገራችን ሁሉም የትምህርት ዐይነት በዚህ መልክ ቢቀርብ ለዕድገት ማምችቱ ብቻ ሳይሆን ለመግባባትና ሃሳብ ለሃሳብ ለመለዋወጥ በጣም ያመቻል።

ያም ሆነ ይህ ማካሄድ ያለብን ፖለቲካ ጥበብ የተሞላበት መሆን አለበት። የችግሩን መንስኤ በሚገባ መመርመር አለብን። ለመብታችን እንታገላለን የሚሉትን የዚህም ሆነ የዚያኛውን ታጋዮች ሁሉ እንደተገንጣይና እንደ አገር በታታኝ አድርገን መመልከት የለብንም። ያለውን ችግር ከሳይንስ አንፃር እንዴት እንደምንፈታው ቁጭ ብሎ ማጥናትና መወያየት ያስፈልጋል። በሌላ ወገን ደግሞ ሌሎች አንድነትን ይቀናቀናሉ ብለን ከመጻፉችንና ከማውራታችን በፊት የአገር አንድነት እንዲጠበቅና በህዝብ መሀከል መተማመን እንዲኖር ምን ምን ነገሮችን ሰራን ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። እንደሚታወቀው ለዛሪይቱ ኢትዮጵያ በዚህ ዐይነቱ እጅግ አስቀያሚ ሁኔታ ላይ መገኘት ሁሉም የየበኩሉን አስተዋፅዖ አድርጓል። ግራ ነኝ ከሚለው ጀምሮና ከቢሮክራሲውና ከአሪስቶክራሲው ወገን የተወለደው ሁሉ፣ ሁሉም በየፊናው ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ላይ መገኘት የየበኩሉን በየፊናው አስተዋፅዖ አበርክቷል። አብዛኛው ባለማወቅ ሲሆን፣ ጥቂቱ ደግሞ የራሱን የኢኮኖሚና የሶሻል ስታተስ ለመጠበቅ ሲል አሻጥር መስራቱና ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር ማበሩና ለመበታተን የሚያመች ኢንፎርሜሽን ማቀበሉ ኢትዮጵያን አዳክሟታል፤ ለዚህ ዐይነቱ ግራ የገባው አገዛዝ ሁኔታውን አመቻችቶ ሰጥቷል።

ለመቋጠር ያህል፣ የኢትዮጵያ አንድነት ሊጠበቅ የሚችለው የህዝቡ ኑሮ ሲሻሻል ብቻ ነው። ከድህነትና ከስንዴ ልመና ሲላቀቅ ብቻ ነው። በአዲስ የዕድገት ጎዳና በአንድነት ተነሳስቶ አገሩን ለመገንባት ሲንቀሳቀስ በቻ ነው። የኢትዮጵያ አንድነትና ህዝባችንም የሚከበረው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን ሲቻል ብቻ ነው። ሰፋ ያለ የስራ ክፍፍል፣ ቆንጆ ቆንጆ ከተማዎችና መንደሮች፣ እንዲሁም ጠቅላላውን አገሪቱን የሚያዳርስና አንዱን ክፍለ-ሀገር ከሌላው የሚያገናኝ፣ ከተማን ከገጠሩና ከመንደሩ ጋር የሚያይዝ የመገናኛና የመመላለሻ የባቡር ሃዲድ ሲዘረጋ የዚያን ጊዜ ሁሉም ጠብመንጃ ማንሳቱን ያቆማል። ሁሉም በየፊናው ሆዱን ለመሙላትና ቤት ለመስራትና ልጆችም ለመውለድና ለማሳድገ ደፋ ቀና ማለት ይጀምራል። አሁንም ለአንድነትና ለኢትዮጵያዊነት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ(Holistic) የኢኮኖሚ ግንባታ እጅግ አስፈላጊ ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብና በየፊናውና በቡድን ቡድን መደራጀቱና አሳሳቾችን እየጋበዙ የሆነ ያልሆነውንና፣ ከሳይንስ ውጭ የሆነ ነገር ንግግር እንዲያደርጉ ማድረግ የድህነቱና ያለመረጋጋት ዘመኑን ያራዝማል። ስለሆነም የውስጥ ለውስጥ ጨወታዎች መቅረት አለባቸው። ሁሉም ነገር ለሳይንስ፣ ለፍልስፍናና ለቴክኖሎጂ የሚለው አስተሳሰብ በሁላችንም ጭንቅላት ውስጥ መቀረጽና ተግባራዊ መሆን አለባቸው። በሌላ ወገን ግን ለብሔረሰቤ ነፃነት እታገላለሁ የሚለው ግለሰብም ሆነ ድርጅት ቆም ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት። እጅግ በተሳሰረና በብዙ ችግሮች በተወጠረ ህብረተሰብ ውስጥ እንዴት አድርጎ እሱ የሚለውን የብሔረሰብ ነፃነት ተግባራዊ እንደሚያደርግና ይህም ምን እንደሚምስል በዝርዝር ማስረዳት አለበት። ካለበለዚያ የብሔረሰቦች ጭቆና ሰፍኗል እያሉ ማራገቡ ብቻ የትም ሊያደርሰን አይችልም። ችግሩ የአንድ ወይም የሁለት ብሔረሰብ ችግር ብቻ አይደለም በአገራችን ምድር የሰፈነው። በአገራችን ምድር የሰፈነው ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና ጭቆና እንዲሁም ድህነትና ኋላ-ቀርነት ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚመለከት ነው። ችግሩ የአማራም የኦሮሞም ሆነ የጠቅላላው ብሔረሰብ ችግር ነው። ችግሩ የቋንቋ ሳይሆን የነፃነት እጦት ነው። መሰረታዊው8 ጥያቄ ሁሉንም ነገር ሊያካትት የሚችል ሰፊ የዕድገት እጦት ጥያቄ ነው።

ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ማስታወሻ፡- ይህ ጽሑፍ የኢትዮጵያውያን ፎረም በአውሮፓ፤ “ፌዴራሊዝም እና የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ሐምሌ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ደን ሐግ በተሰኘችው የኔዘርላንድ ከተማ ባዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ በፈቃዱ በቀለ (ዶክተር) ለውይይት የቀረበ ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ