ይገረም አለሙ

ታሪካዊው የጎንደር ሰልፍ / People in Gonder are protesting against Ethiopia's ruling party and land grabs, 31 July 2016.

በዚህ ሳምንት በወጣ በአንድ ድርጅት መግለጫ ውስጥ የተመለከትኳት “ወያኔ የበሰበሰ የሳር ጎጆ ነው” የምትል ቃል ከዓመታት በፊት አንድ ወዳጄ ያጫወተኝን አስታወሰችኝ። ወዳጄ ብሔራዊ ወታደር ሆኖ ያሳለፈ ነው። እንደ ዕድል ሆኖ በሠለጠነበት ማሠልጠኛ ውስጥ ተመርጦ ቀርቶ እዛው ነው የአገልግሎት ግዳጁን የተወጣው - ደዴሳ።

“ማሠልጠኛ ማዕከሉ ውስጥ ከአነጋገር ክህሎቱ ድፍረቱ የሚማርክ መቶ አለቃ የፖለቲካ ሠራተኛ ነበር። በዛን ግዜ ሊነገር ቀርቶ ሊታሰብ የማይችልን ነገር እሱ እያዋዛ በድፍረት ያውም በሚያስተምራቸው የጦር አባላት ፊት ስለሚናገር፤ እሱ ነው ዛሬ የሚያስተምረው ሲባል፤ ፖለቲካ ሲባል የሚያመው ሁሉ ሳይቀር ነበር የሚገኘው።

በወቅቱ ኢምፔሪያሊዝም የተነፈሰ ጎማ ነው የሚል መፈክር ይስተጋባ ነበር። ታዲያ ይህ መቶ አለቃ ሲያስተምር አጋጣሚ እየፈለገ “እውን ጎበዝ ኢምፔሪያሊዝም የተነፈሰ ጎማ ነው አይንቀሳቀስም፣ ኧረ ተዉ እንደውም በደንብ አየር የተሞላ በፍጥነት የሚንቀሳቀስ ጎማ ነው እንጂ” … ወዘተ ይል ነበር። ወዳጄ እንዳጫወተኝ።

ከዛ በኋላ የሆነውን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው። ፎካሪው ሶሻሊዝም በነበረበት እንኳን መቆም ተስኖት አይሆኑ ሲሆን፤ የተነፈሰ ጎማ ሲባል የነበረው ኢምፔሪያሊዝም ግን ዓለምን ተቆጣጥሮ ቀጥሏል።

ለበርካታ ዓመታት ወያኔን አሳንሰው፣ አቅለውና ደካማ አድርገው የሚገልጹ ንግግሮችን አድምጠናል፤ ጽሁፎችን አንብበናል፣ መግለጫዎችን ሰምተናል። ወያኔ ግን አለ፣ ሃያ አምስት ዓመት ገዝቶን ለሌላ ሃያና አርባ ዓመት እየተመኘ ነው። ጠላትን አሳንሶ ማየትም ሆነ አግዝፎ መመልከት ሁለቱም ጉዳት አላቸው። የመጀመሪያው ለዝግጅት ማነስ፤ ሁለተኛው ለሥነ-ልቦና ሽንፈት ይዳርጋሉ።

ወያኔ በዚህ በኩል ቀልድ አያውቅም። የበረሃ ትግሉን በአሸናፊት መወጣት፣ የቤተመንግሥት ቆይታውንም በበላይነት ማስጠበቅ የቻለው አይደለም ጠላቴ የሚለውን ድርጅት አንድ ግለሰብን እንኳን በንቀት የማያይ፣ በቸልታ የማያልፍ በመሆኑ ነው። በዚህ አድራጎቱም የሚቃወሙትን ብቻ አይደለም፤ ሊቃወሙኝ ይችላሉ በሚል ግምት ብዙ ኢትዮጵያውያንን በየዘመናቱ ያጠፋ ድርጅት ነው። ለሱ ከሥልጣን የሚቀድም ምንም ነገር ባለመኖሩ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ሰው መግደል አይደለም፤ ሀገርን ማፈራረስም ቢሆን ከመፈጸም ወደ ኋላ እንደማይል በሃያ አምስት ዓመት ድርጊቱ አሳይቶናል።

ተቀዋሚው ግን የወያኔን ጥንካሬ አምኖ ጠንካራ ጎኑን ለይቶና የጥንካሬውን ምንጭ ተረድቶ ለመገዳደር የሚያስችል አቅም ገንብቶና ስልት አውጥቶ ከመታገል ይልቅ፤ የወያኔን ደካማነት የሚገልጽበት አዳዲስ ቃላት እየፈጠረ ሲደሰኩር፤ እንደ ሶሻሊዝም ከምድረ ገጽ ባይጠፋም በ“አልሞትኩም ብዬ አልልም” አይነት ይኖራል። በርግጥ ወያኔን አሳንሰው የሚገልጹትና በባዶ ሜዳ የሚፎክሩት ሰዎች ምንም ሲሆኑ አላየንም፣ ሊሆኑም አይችሉም። የሚሞተው፣ የሚታሰረው፣ በየማጎሪያ ካምፑ የሚሰቃየው፣ የሚሰደደው ሌላው ዜጋ ነው።

ምርጫ በመጣ ቁጥር የምንሰማውን አንድ ነገር ላንሳ። ምንም አቅም ሳይገነቡ እናሸንፋለን እያሉ ሲፎክሩ ይቆዩና፤ ወያኔ የሚያሸንፈው ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ባለመሆኑ ነው ይላሉ። ይህ በየምርጫዎቹ ከሁሉም ፓርቲ ተብየዎች የምንሰማው ነው። በርግጥም በህዝብ ድምጽ ወያኔ ማሸነፍ አለመቻሉ የሚያከራክር አይደለም። ጥያቄ የሚሆነው ወያኔ በድምጽ ማሸነፍ አለመቻሉን ስለሚያውቅ ምርጫ ቦርድን ምርኩዙ ካደረገ፤ ያለምርጫ ቦርድ ምርኩዝ ወያኔ ምርጫ ማሸነፍ የማይችል “ደካማ” መሆኑን የተረዱት ፖለቲከኞች ከመናገር ባለፈ ምርኩዙን ለማሳጣት ምን ሠሩ? ካልቻሉ ደግሞ ወያኔ ምርጫ ቦርድን ምርኩዝ እስካደረገ ድረስ እንደማይሸነፍ እያወቁ ለምን አጃቢ ይሆናሉ? ለምን በምርጫ ስም ሰው ያስገድላሉ? የሚለው ነው።

እውን ወያኔ የበሰበሰ የሳር ጎጆ ነው?

ኧረ በፍጹም! በራሱ ሰዎች ቁጥጥር ስር ያዋለው የመከላከያ ኃይል ያለው፤ የዘራው የጎሠኝነት ዘር አፍርቶ አብዛኛው ሰው በጎንዮሽ ትግል ተጠምዶ ክንዱን ወደ እርሱ እንዳይሰነዝር ማድረግ የቻለ፤ ብዙዎችን በተለያየ ጥቅማ ጥቅም በጉያው አስገብቶ በህዝብ ላይ የሚያዘምት፤ አዳዲስ አጀንዳ እየፈጠረ የትኩረት አቅጣጫ የሚያስቀይር፤ አንዳንድ አገልጋዮቹን የጭዳ ዶሮ ከማድረግ ይቅርታ እስከመጠየቅ በሚደርስ የማስመሰያ ርምጃ የየዋህኖችን ልብ ማማለል የሚችል፤ በሴራም በሥራም፣ በሕግም በጉልበትም ዓላማውን ተግባራዊ እያደረገ ከመንገዱ ፈቀቅ ሳይል መጓዝ የቻለ ወያኔ፤ እንዴት ቁንቁን የበላው፣ እንዴት የበሰበሰ የሳር ጎጆ፣ እንደምን አንድ ኀሙስ የቀረው፣ … ወዘተ ይባላል። ኢምፔሪያሊዝም የተነፈሰ ጎማ ነው ይባል እንደነበረው መሆኑ ነው። ራስን መደለያ።

ይህ በየግዜው በተለያየ መልክ የሚሰማው ወያኔን አሳንሶ የመግለጽና በንቀት የመመልከት ነገር በብዙዎቹ ፖለቲከኞች ዘንድ ያለ ነው። እነዚህ ፖለቲከኞች ግን ህዝብ መስዋዕትነት የሚከፍልበት ትግል ብልጭ ባለ ቁጥር፤ እየተሯሯጡ መግለጫ ከማውጣት ባለፈ ይህ ነው የሚባል ተግባር የማይታይባቸው ናቸው። በተግባሩ ሳይኖሩበት ወያኔን ሲያናንቁና ሲፎክሩ ሃያ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ። እነርሱም ተምረው የተግባር ሰው አይሆኑ፣ ወያኔም ተምሮ ከዴሞክራሲ ጋር አይታረቅ፤ በዚህ መሀል ጭቆና ያንገፈገፈው፣ አገዛዝ ያስመረረው ህዝብ አደባባይ እየወጣ ሲያልቅ፤ ይቆጫል፤ ያንገበግባል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!