ይገረም አለሙ

የመብትና የነጻነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

ገና እንደባተ ታዋቂ ኢትዮጵያውያንን በተከታታይ ነጥቆ ኀዘን ያስቀመጠን የተሰናበተው የግፍ ዓመት ሊባል የሚችለው 2008 ዓ.ም.፤ የሞት መርዶ፣ የእስር፣ እንግልትና ስቃይ ዜና ሳይለየው ከል እንዳለበሰን ነው ወደ 2009 ዓ.ም. የተሸጋገርነው። ፈጣሪ በቃችሁ ካላለን በስተቀር፤ የ2009 ዓ.ም. አጀማመርም አስፈሪ ነው።

በ2008 መባቻ በሞት ከተለዩን ሰዎች አንዱ ዶ/ር ሽመልስ ተክለጻድቅ መኩሪያ በዚህ ሣምንት ሙት ዓመታቸው ሲታሰብ በተለያየ ግዜ ከአስነበቡን ጽሑፎች መካከል ግዜ የማይሽራቸው ተሰባስበው “የመብትና የነጻነት ጥያቄ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የታተመ መጽሐፍ ተመርቋል። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ግድም የጻፉትና በመጽሐፉ የተካተተው አንድ ጽሁፍ ውስጥ፤ ዛሬ የተጻፈ የሚመስል የእኛን ሁኔታ የሚገልጽ እንዲህ የሚል የጸሐፊው ስጋት ይገኛል።

የመብትና የነጻነት ጥያቄ በኢትዮጵያ“የትውልድን ርቀት በፍጡራዊ አስገዳጅነት ገጽታው ብናየው የሰላሳ ዓመት ገደማ ልዩነት ባላቸው አያት፣ እናት/አባት፣ ልጅ በሚል ሦስት የዕድሜ ክልል ተለይቶ ይገኛል። ይኸን የዕድሜና የኑሮአቸውን ሁኔታ ተንተርሶ ለነዋሪዎቹ የተለያየ ትኩረትና ግንዛቤ ቢሰጣቸው አያስገርምም። እንዲያውም የሚገርመው ልዩነት ባይኖር ነው። የጉዳዩን ቁም ነገር አቀለልከው ባትሉኝ፤ አያት ያለፈውን፣ እናት/አባት የጊዜውን፣ ልጅ ደግሞ የወደፊቱን የበለጠ ያስቡታል፣ ትኩረት ይሰጡታል ቢባል ግንዛቤው እምብዛም ከሐቁ አይርቅም።

“በትውልድ ልዩነትና መራራቅ ላይ በሚከሰት የኢኮኖሚ አቅም፣ በቤተሰብና ማኅበራዊ ኑሮ ላይ የተመሰረተ የተለያየ ደረጃ ላይ በመገኘት መንስዔነት በፖለቲካ ግንዛቤና አመለካከት፣ የምርጫ ዝንባሌ ዜጎች እንደሚለያዩ እነዚህ ጉዳዮች በመረጃ የተደገፈ ጥናትና ታሪክ ያላቸው ሀገሮች ተሞክሮ በግልጽ ያሳያል።

“የሦስቱን ትውልድ ያቀፈ ቤተሰብ፤ በጸጋ የሚኖረው የሦስቱንም ፍላጎት፣ ትኩረትና አመለካከት አዛምዶ ሲያቅፍ ነው። እንዲሁም እንደማንኛውም ግለሰብና ቤተሰብ፣ ሕብረተሰብም ያለፈውን ከጊዜው ጋር አገናዝቦ የወደፊቱን አልሞና ተልሞ መኖር ካልቻለ ብዙ ችግር እንደሚገጥመው እሙን ነው።

“እኛም ዛሬ በሀገራችን መካሪ አያት እንደሌለው አልባሌ ልቅ ሰው፣ ካለፈው ትውልድና ታሪክ ጋር ክህደት ላይ በተመሰረተ ጥል ስንናቆር፣ ልጅ እንደሌለውና እኔ ከሞትኩ ... እንዳለችው አህያ ሊገጥመን የሚችል የወደፊት የከፋ ችግር ከመከላከል ወይም ቢያንስ ተዘጋጅቶ ከመጠበቅ ይልቅ፤ ጊዜው የሚያቀርብልንን ያላመረትነውን ስንቃርም በሱም ስንብለጨለጭ የታሪክ ሂደት ርቃናችንን እንዳያስቀረን ያሰጋል።” ይህ 15 ዓመት ገደማ ያለፈው ጽሁፍ የያዘው መልዕክት፤ ዛሬም ወቅታዊ ነው። ምን አልባት ነገ ከነገ ወዲያም እንዲሁ።

ህዝቡ የወያኔን አገዛዝ የተሸከመበት ጫንቃው ተልጦ፤ ከአገዛዝ ይገላግሉኛል ብሎ ተስፋ ባሳደረባቸው ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ተስፋ ቆርጦ፤ ራሱን በራሱ አደራጅቶ ነጻነት ወይንም ሞት ብሎ በጀመረው ትግል መስዋዕትነት እየከፈለ ባለበት፣ ይህን የህዝብ ተቃውሞ በኃይል ለመጨፍለቅ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሠራዊቱን ማዘዛቸውን በእብሪት በገለጹበትና ትዕዛዙ ተግባራዊ ሆኖ ዜጎች በየቀኑ በገፍ እየተገደሉ ባሉበት ወቅት፤ ከወያኔ በተቃራኒ ያለን ዜጎች በትናንት መነታረኩን ትተን፤ የየግል ጉዳያችንን፣ ቁርሾአችንንና ድብቅ አጀንዳችንን ወደ ጎን ብለን ስለነገ ተጨንቀን በአንድ ለመነሳት አልቻልንም።

ግድያ፣ እስርና ስቃይ ለአንድ ዓመት ያህል የዕለት ተዕለት ዜና ሆኖ ህዝቡ በዚህ ሳይረታ ደረቱን ለወያኔ ገዳዩች አረር ሰጥቶ፣ ሞትን ንቆ፣ ነጻነቱን ሽቶ መስዋዕትነት ሲከፍል፣ ከሀገሩ እርቆ በስደት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በየሚኖርበት ሀገር በአንድነት ተነስቶ ብርድና ሀሩር፣ ዝናብና ፀሐይ ሳይል ተቃውሞውን ሲያሰማ፤ የፖለቲካ ድርጅት ነን ባዮች ከየጓዳቸው ሆነው መግለጫ ከማወጣት ሊያልፉ አልቻሉም። ዶ/ር ሽመልስ ከ15 ዓመት በፊት “ካለፈው ትውልድና ታሪክ ጋር ክህደት ላይ በተመሰረተ ጥል ስንናቆር” በማለት የገለጹት ልዩነት፤ በህዝቡ አንድነት በተወሰነ ደረጃ ቢረግብም በፖለቲከኞቹና ምሁራኖቹ ዘንድ ግን ዛሬም እንዳለ ነው። ይህም በመሆኑ በአደረጃጀት የተለያዩት ቀርቶ የአንድ ብሔር ስም ይዘው የተደራጁት እንኳን ወደ አንድነት መምጣቱ ቀርቶ በጋራ ለመታገል አልሆነላቸውም።

ወያኔ ያለርህራሄ እየገደለ፣ እያሰረና እያሰቃየ ሥልጣኑን ለማቆየት በሚያደርገው ጥረት፤ እስካሁን ከሆነው የወደፊቱ ሊከፋ እንደሚችል በጉልህ እየታየ ባለበት በዚህ ወቅት፤ በተቃውሞው ጎራ ወቅቱን የሚመጥን ተግባር እየታየ አይደለም። ወያኔ እያደረሰ ያለውን አደጋ በመከላከልና ትግሉን በማጠናከር ለድል የሚበቃበትን ሥራ መሥራትና፤ ከድል በኋላ በኢትዮጵያ እውን ሊሆን ስለሚገባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ከተቃውሞው ሰፈር የሚጠበቅ ወቅታዊ ተግባር ቢሆንም፤ ዛሬም ከአንድ ሰሞን ጩኸትና መግለጫ ያለፈ ተግባር ማየት አልተቻለም። ይህም “ልጅ እንደሌለውና እኔ ከሞትኩ ... እንዳለችው አህያ ሊገጥመን የሚችል የወደፊት የከፋ ችግር ከመከላከል ወይም ቢያንስ ተዘጋጅቶ ከመጠበቅ ይልቅ ጊዜው የሚያቀርብልንን ያላመረትነውን ስንቃርም በሱም ስንብለጨለጭ የታሪክ ሂደት ርቃናችንን እንዳያስቀረን ያሰጋል።” በማለት ዶ/ር ሽመልስ ከ15 ዓመት በፊት ከገለጹት ስጋት ዛሬም ያልተላቀቅን መሆናችንን ነው የሚያሳየው። ከዚህ ለመውጣት ስንት ዓመት ይሆን የሚያስፈልገን? የስንት ሰው ሕይወትስ ነው መጥፋት ያለበት? የወያኔ አረመኔያዊ ተግባርስ ከምን ደረጃ መድረስ አለበት? እያዳንዱ ፓለቲከኛስ ምን ሲያገኝ ወይንም እንደሚያገኝ ርግጠኛ ሲሆን ይሁን የሚተባበረው?

ትናንትን ስናስብ በቀዳሚነት ሊያሳስበን የሚገባው ለግማሽ ክፍለ ዘመን የዘለቀው ትግል ለመስዋዕትነት እንጂ ለድል ያልበቃው ለምንድን ነው? ዓላማውን ትግራይን ነጻ ማውጣት አደርጎ የተነሳው ኃይል እንዴት ኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት ሊደርስ ቻለ? ስሙን እንኳን ሳይቀይር ነጻ አውጪ እንደተባለ በአምባገነንነት ሃያ አምስት ዓመት ለመግዛት የመቻሉ ምስጢርስ ምንድን ነው? ወዘተ የሚለው ሆኖ ሳለ እኛ የምናስበው የታሪካችን መጥፎ ገጽታዎችን መመዘዝና ማጉላትን ነው። ወያኔዎች ግን ስለትናንት የሚያስቡት ከመቶ ዓመት በፊት ርቀው በመሄድ በዮሐንስ እጅ የነበረ የትግሬ ሥልጣን በማን እንዴት ለምንና በምን ሁኔታ እንደተነጠቀ፣ እንዴት እንዳስመለሱትና ያ ስለማይደገምበት ነው።

በተቃውሞው ጎራ ስለ ነገ መታሰብ የነበረበት ወያኔ ሥልጣኑን ለማቆየት የሚፈጽመውን አደጋ ስለመከላከል፤ እኔ ካልኖርኩ በማለት ሥልጣኑን ቢያጣ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያቀደው ሴራ ተግባራዊ እንዳይሆን ስለማድረግ፤ አደጋን በቀነሰ ሁኔታ ወያኔን ማስወገድ ስለሚቻልበትና ኢትዮጵያን ለአስተማማኝ የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚያበቃት መሰረት ስለ መጣል መሆን ሲገባው፤ ከግል ጥቅምና የሥልጣን ጥም ያለፈ ማሰብ አልተቻለም። በመሆኑም በዶ/ር ሽመልስ ጽሑፍ እንደተገለጸው ያላመረትነውን እየቃረምን፣ ባልሠራነው እየፎከርን ቃልና ተግባራችን እየተቃረነብን ዛሬን ብቻ መኖር ነው የተያያዝነው።

ወያኔዎች ግን ስለነገ የሚያስቡት “በመራራ ትግል” ከእጃቸው ያስገቡት ሥልጣን ዝንተ ዓለም ስለሚቆይበት ካልሆነም ወደ መነሻቸው ተመልሰው ትግራይን ስለሚገዙበት ነው። እንዲህ በማሰባቸውና በመሥራታቸውም ነው ሃያ አምስት ዓመት ተደላድለው ለመግዛት የበቁት። ወያኔዎች እንዲህ በማሰብና በመሥራት ብቻ አይወሰኑም። በአጼ ዮሐንስ የሆነው በእኛም ሊደገም ነው ብለው በሰጉ ሰዓት በጡረታ የተገለሉት፤ በመተካካት ስም ከፊት ለፊት ገለል የተደረጉት፤ ተወንጅለው የተባረሩት ሳይቀሩ ታውሞውን ለማብረድና የተነቃነቀውን የድርጅታቸውን ወንበር ለማጥበቅ በሚችሉት ይንፈራገጣሉ።

ስለትናንት አስቦ መነሳት ስለነገም ተጨንቆ መሥራት የማይታይባቸው የተቃውሞው ጎራ አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች ግን፤ የዘመመው እንዳይቃና የተነቃነቀው እንዳይረጋ ተባብረው ከመሥራት ቤተ መንግሥቱን አሸጋግረው እያዩና እየተመኙ በሚፈጥሩት ሴራና ፉክክር፤ ለወያኔ የዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒት በመሆን ብዙ አጋጣሚዎችን አምክነዋል። ከትናንት ተምረው ይህን ህዝባዊ አምቢተኝነት ወደ ድል የማሸጋገር ዝግጁነት አይደለም፤ ፍላጎት አይታይባቸውም። እንደውም በተቃራኒው ህዝቡ ወያኔን አጥብቆ የሚጠላውንና ለዓመታትም በብርቱ የሠራበትን ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት ሴራ በጣጥሶ የአንድነት ዜማ እያሰማ በመስዋዕትነቱ ያቀለመውንና በቁርጠኝነት የተያያዘውን ትግል ወደ ብሔር/ጎሣ ደረጃ በማውረድ ለወያኔ ማገገሚያ እንዲመች ለማድረግ ሲጮሁ መስማት፤ ሲደክሙ ማየት በእጅጉ ያሳዝናል። ወያኔ የህዝቡ አንድነት አበሳጭቶት እሳትና ጭድ በማለት ዛሬም ለማለያየት ቀን ተለሊት ሲደክም፤ በተቃራኒው ተቃዋሚዎች ህዝቡ ከእነርሱ ቀድሞ ሴራውን አክሽፎ በአንድነት በመነሳቱ ተደስተው ቀጣዩን የወያኔ ሴራና ሥራ ለማክሸፍና የህዝቡን አንድነት ለማጽናትና ለማጥበቅ መሥራት ሲገባቸው፤ ዛሬም በትናንት ዜማ ሲያቀነቅኑ መስማት በጣሙን ያማል። ነገር ግን ህዝቡ ቀድሟቸዋልና በእነርሱ ማዘን ካልሆነ በስተቀር ተስፋ አያስቆርጥም።

የበሽታችን ክፋቱ፣ ከራስ በላይ ለማሰብ ያለመቻላችን ግዝፈቱ፣ ተባብረን አንባገነን ሥርዓትን ለማስወገድ አላስችል ብሎን ሃያ አምስት ዓመት በጥቂቶች ያውም ራሳቸውን ነጻ አውጪ በሚሉ ኃይሎች ተገዛን። በዚህ መቆጨት ከድርጊቱም መማርና መለወጥ ሲገባን፤ ህዝቡ ከመመረር አልፎ ሕይወቱን እየገበረ ለነጻነቱ ሲታገል እንኳን፤ ከዓመታት በፊት ከቆምንበት መነቃነቅ የያዘነውን አቋም መለወጥ ተስኖን ህዝባዊውን ትግል መምራት ቢቀር ተከታይ መሆን አልቻልንም። በዚሁ ከተቀጠለ የህዝባዊው ተቃውሞ ውጤት ሁሉንም የሚጠራርግ እንዳይሆን ያሰጋል።

በህዝባዊው ማዕበል አብሮ መጠረጉም ሆነ፤ በዚህ ወሳኝ ወቅት ተገቢውን ተግባር ሳይፈጽሙ በተዓምር ከማዕበሉ መትረፍ መቻል ከታሪክና ከትውልድ ተጠያቂነት አያድኑም። የታሪክ ሂደት ርቃናችንን እንዳያስቀረን የሚለው የዶ/ር ሽመልስ ግዜ ያላደበዘዘው ስጋትም ይሄው ይመስለኛል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!