አብርሃ ደስታ

"ህዝቡ አሁን በአዋጁ ምክንያት የሚያጣው ዴሞክራሲያዊ መብት የለም። ምክንያቱም ከአዋጁ በፊትም ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተነፍጎ ነበረ። የአመጹ መንስኤም የዴሞክራሲ እጦት ነውና"

Abraha Desta

የኢህአዴግ መንግሥት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጇል። በሕገመንግሥቱ መሰረት አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይወጣል፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል። በሁለቱም ምክር ቤቶች ልዩነት ስለሌለ መፅደቁ አይቀርም።

የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚታወጀው አደጋ ሲያጋጥም ነው፤ ህዝብንና ሀገርን የሚጎዳ አደጋ። አደጋው የተፈጥሮ ወይ ሰው ሰራሽ ወይ የፖለቲካ (ለምሳሌ የውጭ ጠላት ሀገርን ሲወር) ሊሆን ይችላል። መንግሥት ህዝብን ከአደጋው ለማዳን ሲል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሊያውጅ ይችላል።

የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታወጀ ማለት የመንግሥት አካላት ከተለመደው ተግባራቸው ለየት ባለ መልኩ ሥራቸው ያከናውናሉ ማለት ነው። የዜጎችን የተለመዱ (ይከበሩ የነበሩ) ዴሞክራሲያዊ መብቶችም ለግዜው ይገደባሉ፤ አደጋውን ለማስወገድ ሲባል። ሰብዓዊ መብቶች ግን በየትኛውም ሁኔታ አይገደቡም።

አሁን አዋጁ የታወጀው በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት አይደለም። የወረረን የውጭ ጠላትም የለም። በፖለቲካ ተቃውሞ ምክንያት ነው። ህዝቡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተገደበና ታፈንኩ ብሎ ተቃወመ።

አደጋ ተደርጎ የተወሰደው ህዝባዊ ተቃውሞውን ነው። ህዝብ መንግሥትን የመቃወም መብት አለው። ፀረ-መንግሥት የሚደረግ ህዝባዊ ተቃውሞ ዴሞክራሲያዊ መብት እንጂ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚጠይቅ አደጋ አይደለም። የህዝብ ተቃውሞው ፀረ-ገዢው ፓርቲ የሚደረግ ነው። የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚያስፈልገው ህዝብንና ሀገርን ከአደጋ ለማዳን እንጂ ገዢውን ፓርቲ ከህዝብ ተቃውሞ ለመጠበቅ አይደለም። ለገዢው ፓርቲ ደህንነት ሲባል ህዝብ ሊቀጣ ነው? ፓርቲን ከህዝብ ተቃውሞ ለመከላከል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሊታወጅ አይችልም። ምክንያቱም ፀረ-ገዢው ፓርቲ የሚደረገው ህዝባዊ ተቃውሞ አደጋ የሚወገደው የችግሩ ምንጭ የሆነውን ገዢውን ፓርቲ ከሥልጣን በማባረር እንጂ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን በማወጅ መብቱን የጠየቀ ህዝብን በማፈን አይደለም። ስለዚህ የአዋጁን አስፈላጊነት የተሳሳተ ነው።

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ታወጀ። ምን ሊደረግ ነው? የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይገደባሉ። በኢህአዴግ ዘመን መቼስ የዴሞክራሲ መብቶች ተከብረው ያውቃሉ? ያልነበሩ መብቶች እንዴት ይታገዳሉ? በኢትዮጵያ ውስጥ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለ25 ዓመታት ፀንቶ ቆይቷል። የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሲታወጅ አንድምታው፤ ተከብሮላቹ የነበረውን ዴሞክራሲያዊ መብታችሁን ለግዜው ሊገደብ ይችላል ማለት ነው። መቼ ተከብሮልን ያውቃል? ዴሞክራሲያዊ መብታችን እኮ ሁሌ እንደተገደበ ነው። ሁሌ የአስቸኳይ ግዜ እንደታወጀብን ነው።

አሁን በአዋጁ ሊገደብ የሚችል ዴሞክራሲያዊ መብት ቢኖረን ኖሮ እንዴት ይህን ያህል ኢህአዴግ እንቃወም ነበር? የዴሞክራሲ መብት ቢከበር ህዝባዊ ተቃውሞስ መቼ ይኖር ነበር? ህዝብ ተቃውሞውን በሰላማዊ ሰልፍ የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ቢከበርለት ኖሮ እንዴት ያምጽ ነበር? ዴሞክራሲ ሰፍኖ ህዝብ ያለ ምንም ተፅዕኖ የፈለገውን መርጦ ድምፁ ተከብሮለት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ቢከናወን ኖሮ መቼ ህዝባዊ አመጽ ይኖር ነበር?

ህዝቡኮ የሚቃወመው ዴሞክራሲያዊ መብቱ ስለተከለከለ ነው። ስለዚህ ህዝቡ አሁን በአዋጁ ምክንያት የሚያጣው ዴሞክራሲያዊ መብት የለም። ምክንያቱም ከአዋጁ በፊትም ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተነፍጎ ነበረ። የአመጹ መንስኤም የዴሞክራሲ እጦት ነውና።

ስለዚህ አሁን አልነበረውም፤ አይቀንሰውም። ህዝቡ እየተቃወመ ያለው ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባልተከበሩበት ነው። ህዝቡ ያመፀው ኢህአዴግ እስካሁን የኃይል እርምጃ ስላልወሰደ አይደለም። ህዝቡ እየተጨፈጨፈ ነው እየተቃወመ ያለው። ከአዋጁ በፊትም ጭፍጨፋ አለ፤ ከአዋጁ በኋላም ጭፍጨፋ ይኖራል። አዋጅ የሚያመጣው አዲስ ክስተት የለም። ምክንያቱም ለ25 ዓመታት ሙሉ የኖርነው በተደነገገው ሕገመንግሥት ሳይሆን፤ ባልታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ነበር፤ አሁን ደሞ ታወጀ። ልዩነቱ የማወጅና ያለማወጅ ነበር።

በዚህ አዋጅ አዲስ ነገር ካለ፤ ኢህአዴግ መጨናነቁና ለህዝባዊ ተቃውሞው እውቅና መስጠቱ ብቻ ነው። ህዝባዊ ተቃውሞው ከኢህአዴግ ቁጥጥር ስር መውጣቱና ጣዕረ ሞት ላይ መሆኑ ያሳያል።

የችግሩ መፍትሔ ግን የአስቸኳይ ግዜ ማወጅ ሳይሆን፤ ሥልጣንን ለባለቤቱ ህዝብ ማስረከብ ነው። ሥልጣንን በክብር ለህዝብ ከመስጠት ይልቅ ሥልጣንን በኃይል እስክትነጠቅና ተገፍትረህ እስክትባረር ድረስ መጠበቅን የመሰለ አላዋቂነት የለም።

ኢህአዴግ ያለው ዕድል ሥልጣኑን በኃይል ሳይነጠቅ በፍቃደኝነት ለህዝብ ማስረከብ ብቻ ነው።

It is so!!!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!