ዮፍታሔ

Getachew Ambaye. ጌታቸው አምባዬ

- ችግሩ የተፈጠረው በኦሮሚያ እና ምናልባትም በአማራ ሆኖ እያለ በመላ ሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ማድረግ ለምን አስፈለገ?

- ኦሮሚያና አማራ ከዚህ ተመሳሳይ በሆነ ወታደራዊ ዕዝ (Martial law) ቆይተዋል። ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ግን አላቆመውም። ይህ ከሆነ ይህን አዋጅ ማወጅ ለምን አስፈለገ?

- ላለፉት 25 ዓመታት አገዛዙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳያውጅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ሊደረጉ ከሚችሉ በላይ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽም ኖሯል። እንዲህም ሆኖ በዚህ ሩብ ምዕተ ዓመት በአካል፣ በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ ባለሥልጣን፣ ፖሊስ፣ ደኅንነትም ሆነ ወታደር በሕግ ተጠይቆ አያውቅም። ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈለገው አገዛዙ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜ ለሚወስዳቸው ርምጃዎች ተጠያቂ እንዳይሆን ከሕግ ከለላ እንዲያገኝበት ነው ብሎ ማሰብ አይቻልም። ይህ ከሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማወጅ ለምን አስፈለገ?

- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ምክንያት የህዝብን ደኅንነትና የንብረትን ጉዳት ለመቆጣጠር ነው ተብሏል። በእውኑ አገዛዙ ካለው ታሪክና ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ከተጀመረ ጀምሮ ለሰው ሕይወትና ለህዝብ ንብረት ካሳየው ግዴለሽነት ለሕይወትና ለንብረት አስቦ የራሱን ደካማ ጎን ለህዝቡና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያጋልጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል ብሎ ማሰብ ይቻላልን?

እነዚህ ጥያቄዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዓላማ ሌላ እንደሆነ እንድንጠረጥር የሚያስገድዱ ናቸው።

ዓለም አቀፋዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት Martial Law (ወታደራዊ ዕዝ) እና State of emergency (አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ) ትንሽ ልዩነት አላቸው። ወታደራዊ ዕዝ ሙሉ በሙሉ በጦር ሠራዊቱ (ፖሊስም በቀጥታ በጦር ሠራዊቱ እንዲታዘዝ ይገደዳል) ሀገር ትተዳደራለች ማለት ነው። ይህም ቀደም ብሎ በኦሮሚያ በኋላም በአማራ “ክልሎች” ተግባራዊ ሆኖ ቆይቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማለት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ (እና በኢትዮጵያ ሕግ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩና እርሱ የሚመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት) በበላይነት ሀገር ያስተዳድራሉ ማለት ነው። ስለዚህ የታወጀው ወታደራዊ ዕዝ (Martial Law) ሳይሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (State of Emergency) መሆኑን በመጀመሪያ Washington Post ካወጣው ዘገባና በኋላም የፌደራሉ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ (ጌታቸው አምባዬ) ካቀረበው ዝርዝር ሪፖርት መረዳት ይቻላል።

በመጀመሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዝርዝር (በ”Washington Post” ዘገባ የሰዓት እላፊ አይኖርም ከመባሉ በቀር) አልቀረበም ነበር። ጠቅላይ አቃቢ ሕጉ ባቀረበው መግለጫ ደግሞ ተፈጻሚ የሚሆንበትን ጊዜና ቦታ (ቦታዎች) ባይጠቅስም ዝርዝሩን አስቀምጧል። በዚህም መሠረት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን ማሰር እንደሚቻል፣ የማንንም ሰው ቤት፣ ንብረትና መኪና በፈለጉበት ጊዜ መፈተሽና መበርበር እንደሚቻል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ (የሚኒስትሮች ምክር ቤት) ሁሉንም የግንኙነት መስመሮች (ስልክ፣ ፌስቡክና ሌሎችም) ሊያቋርጥ እንደሚችል፣ ስብሰባና ሰልፍ ማድረግ፣ ምልክት ማሳየት እንደማይቻልና የሰዓት እላፊ አዋጆች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሷል።

ስለዚህ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜ የሀገሪቱ ሕጎች በተግባር ላይ አይውሉም ማለት ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም አስፈላጊነት በሕጋዊ መንገድ ችግሩን መፍታት ስላልተቻለና ሕጉም እንቅፋት ስለሆነ መነሳት ይኖርበታል ከሚል ነው። ስለዚህ የሀገሪቱ ሕግና ሥርዓት በሙሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በሚኒስትሮቹ ውሳኔ ይተካል ማለት ነው። ጦር ሠራዊቱ፣ ደኅንነቱም ሆነ ፖሊስ ለሚወስዱት ርምጃ በመደበኛ ፍርድ ቤት ተጠያቂ የሚሆኑ መሆናቸውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገበት የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 የጠቀሰው የለም። ከዚህ ይልቅ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 93 ቁ 5 የተጠቀሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚከታተልና ጠቅላይ ሚኒስትሩ (የሚኒስትሮች ምክር ቤት) የሚወስደውን ርምጃ በዝቷል (“ኢሰብዓዊ ሆኗል”)፣ ጥሩ ነው ወይም አንሷል እያለ ለአገዛዙ ሃሳብ የሚሰጥ 7 አባላት ያሉት “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ” እንደሚቋቋም ነው የሚገልጸው። አንቀጽ 93 ቁ. 6 መ. እንዲሁ በደምሳሳው “ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ” ቢልም ስለአፈጻጸሙ የሚገልጸው ስለሌለና የመርማሪ ቦርዱ አባላት እነማን እንደሚሆኑ ስለሚታወቅ በዚህ መዘናጋት አያስፈልግም።

Washington Post ባወጣው ዘገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የሠፈሩትን መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች አይጥስም/ The state of emergency will not breach basic human rights enshrined under the Ethiopian constitution” ብሏል። ሆኖም ይህ የለበጣ ንግግር ብቻ ነው የሚሆነው። በሕገ መንግሥቱ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገው አንቀጽ 93 ቁ. 1 ሀ. እንዲህ ይላል፦

“የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጡትን መሠረታዊ የፖለቲካና የዲሞክራሲ መብቶችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ እስከ ማገድ ሊደርስ የሚችል ነው።”

ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ “መሠረታዊ የፖለቲካና የዲሞክራሲ መብቶች” እንደሚጣሱና እርሱም ደግሞ “ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ” እንደሚሆን ይገልጻል ማለት ነው። ጠቅላይ አቃቢ ሕጉም ስለአስቸኳይ አዋጁ ያቀረበው ዝርዝር ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። ስለዚህ ደኅንነቱ፣ የጦር ሠራዊቱና ፖሊስ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ መጠራጠር አይገባም።

የትግራይ ጎሣ አባላትንና ከትግራይ የሄዱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከኦሮሚያና ከአማራ ወደትግራይ ያሸሸበትን ምክንያት ስናስብ በአማራና ኦሮሚያ “ክልሎች” ደኅንነቱና ጦር ሠራዊቱ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ለመዘጋጀታቸው አንድ ተጨማሪ ምስክር ነው። በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመስከረም መጨረሻና በጥቅምት መጀመሪያ ወደነዚህ ክልሎች ሄደው ትምህርት እንዲጀምሩ ካደረገ በኋላ በተማሪዎች ላይ ምንም ዓይነት ማስፈራሪያም ሆነ ጉዳት ሳይደርስባቸው የአማራንና የኦሮሞን ክልል ጥለው እንዲወጡ ማድረግ የተወጠነ ክፉ ነገር መኖሩን ግልጽ የሚያደርግ ነው። በቅርቡ በአማራ ክልል ይህ መፈጸሙም መረሳት የለበትም።

ሕገ - መንግሥቱ ክልሎች የራሳቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እንደሚችሉ (አንቀጽ 93 ቁ. 1. ለ.) ይገልጻል። ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሻ ምክንያት በኦሮሚያና በአማራ የተፈጠረው ህዝባዊ ተቃውሞና እምቢተኝነት ከሆነ ቀደም ሲል የነበረውን የወታደራዊ ዕዝ (Martial Law) ማስረዘም ወይም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕጋዊ ማድረግ ብቻ ይበቃ ነበር። ነገር ግን አገዛዙ ይህን በማድረግ ፈንታ በመላ ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቷል።

ስለዚህ ከዚህና ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ተነሥተን የአገዛዙን ባሕሪና ያደረጋቸውን ድርጊቶች በመፈተሽ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አገዛዙ ሥልጣኑን በተቻለ መንገድ ለማራዘምና፤ ያ ካልሆነም እያሰበው ላለ ተከታይ ዕቅዱ ማስፈጸሚያ ሊያደርገው እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይህን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዴት ማስፈጸም ይቻላል?

እርግጥ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአገዛዙ የወታደሩን፣ የደኅንነቱንና ይልቁንም የፖሊስን ታዛዥነት ሊጨምርለት ይችላል። በወገናችን ላይ አንተኩስም፤ ከተኮስንም ያስጠይቀናል ብሎ ይፈራና ያመነታ የነበረውን ያለስጋት በወገኑ ላይ የፈለገውን እርምጃ እንዲወስድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ነፃ ያደርገዋል። በዚህ አገዛዙ ከወታደሩ፣ ከደኅንነቱና ከፖሊስ የተሻለ ታዛዥነትና ትብብር ሊያገኝበት ይችላል። ነገር ግን ዋናው ምክንያት ይህ አይደለም።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከ16 ዓመት በፊት በትግሪኛ ቋንቋ "አማራ እና ኦሮሞ አብረው መቆም ከጀመሩ ድርጅቴ ህወሓት ያኔ ማቅ ትለብሳለች። የትግራይ ህዝብ ህልውና በአማራው እና በኦሮሞው ቡድን ፍች ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ላፍታም መዘንጋት የለብንም። መልሰው ጋብቻ የሚፈጥሩበት platform ካገኙ ህወሓት በይፋ ያከትምላታል" በማለት እንዳስቀመጠው፣ ባለፈው 40 ዓመት ሁለቱን ጎሣዎች ለመለያየት ህወሓት የትጓዘበትን ርቀት ለተከታተለና በቅርቡ የአማራውና የኦሮሞው ሕብረት ያስገኘው እመርታና በአገዛዙ ውስጥ የፈጠረውን መብረክረክ ለታዘበ አገዛዙ ሥልጣኔን የማቆይበት ዋናው መንገድ በአማራና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ግጭት መፍጠር ነው ብሎ ሊወስን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። አስቀድመን አውቀን ካልተዘጋጀን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይህን ለማስፈጸም በጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕጉ በማብራሪያው እንደጠቀሰው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሀገሪቱ የጦር ኃይል ሙሉ በሙሉ በአንድ ዕዝ (Command Post) ስር ይሆናል። ይህን በማድረግ በቀላሉና በግልጽ የአማራውን ወታደር በኦሮሚያ፣ የኦሮሞውን ወታደር ደግሞ በአማራ አዝምቶ ርምጃ እንዲወስዱ በማበረታታት፣ በህዝቡ ዘንድ እውነተኛ መረጃዎች እንዳይደርሱ በመግታትና የአገዛዙን የፕሮፖጋንዳ መሣሪያዎች በመጠቀም በሁለቱ ታላላቅ ጎሣዎች መካከል የእርስ በእርስ ግጭትና መቃቃር እንዲፈጠር ማድረግ ዋናው ዓላማ ሊሆን እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሌላው ድብቅ ዓላማ ምን ሊሆን ይችላል?

የህወሓት አገዛዝ በህዝብና በሀገር ላይ ይህን ሁሉ ክፉ ሥራ ከፈጸመ በኋላ በሥልጣን ላይ ሊቆይ እንደማይችል የተረዳ የሚመስልበት ምልክቶች አሉ። ለዚህም ገንዘብ ከባንክና ከመሀል ሀገር ማሸሽ፣ ብርን ወደዶላር መመንዘር፣ ልጆንና ቤተሰቦችን ማሸሽ፣ የትግራይ ጎሣ አባላትን ከሌሎች ክልሎች ማሸሽ ወዘተ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው። ነገር ግን ህወሓት ወደማይቀረው ከመሄዱ በፊት በስፋትና በምስጢር ሊያከናውናቸው የሚያስባቸው የቀሩ ነገሮች ካሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለህወሓት ይህን ለማከናወን የተሻለ ዕድል ይሰጠዋል። ለምሳሌ የሰዓት እላፊውን ተጠቅሞ ንብረትና ሀብት ማሸሽ፣ ማንኛውንም ለኢትዮጵያ አቅም ሊሆን የሚችል መሠረተ ልማት መመዝበር፣ ከአገልግሎት ውጭ ማድረግ ወይም ማውደም፣ አጥፊና አውዳሚ መሣሪያዎችን ወደመሀል ሀገር ማስገባት ወዘተ።

ምን ይደረግ?

የኢትዮጵያ ህዝብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በቀጥታ በራሱ (በህዝቡ) ላይ እንደታወጀ ጦርነት ተመልክቶ እውቅና ሊሰጠው አይገባም። ይህም ማለት እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ ሳይሆን ተጠንቅቆና ተዘጋጅቶ መጠበቅ ይኖርበታል ማለት ነው።

ወታደሩ በተለይም የአማራና የኦሮሞ ጎሣ አባል የሆነው የጦር ሠራዊት፣ የደኅንነትና የፖሊስ አባል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰበብ የተደገሰለትን በመገንዘብ ከህዝብ ጎን መቆም ይጠበቅበታል። በግልጽ ከህዝብ ጎን ለመቆም የማይችልበት ምክንያት ካለ ደግሞ በሚሠማራበት ቦታ ማሣሪያውን ወደህዝብ ከማዞር ይልቅ በህዝቡ ላይ እርምጃ ሊወስዱ የተዘጋጁትን ኃይሎች በስልታዊ መንገድ በመቆጣጠር የሰውን ሕይወት፣ የህዝብን ንብረትና መሠረተ ልማት በመጠበቅ ለሀገርና ወገን አኩሪ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል።

ከዚህ አልፎ የህዝብ ልጆችን በመግደልና በማሰር የሚደረግን የጦር ሠራዊቱንና የደኅንነቱን ትንኮሳ የህወሓት አገዛዝ ሆን ብሎ የአማራውንና የኦሮሞውን ጎሣዎች ለማጋጨት ያጠመደው ትልቅ ወጥመድ መሆኑን በመረዳት ህዝቡ በብልህነት፣ በትዕግስትና በጽናት እንዲቋቋመው ያስፈልጋል።

ትግሉ አሁን ከደረሰበት ደረጃ በመነሣት በሰላማዊ ሰልፍና በባዶ እጅ ለተቃውሞ መውጣት ራስን የሚያጋልጥ ነው። ስለዚህ ሌላ ዓይነት የትግልና የተቃውሞ ስልቶችን በሚስጥር እስከመንደፍ ድረስ ሊታሰብበት ይገባል። እነዚህን ስልቶች የታሰበውን ጥፋት ታሳቢ በማድረግና አስፈላጊ ከሆነም ተመጣጣኝ ኃይል በመፍጠር ማደራጀት ያስፈልጋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ