ኃብተወልድ ተሾመ

Facebook banned in Ethiopiaሀገሬ ይህን ጊዜ ባታይ እመርጥ ነበር፤ ከ54 የአፍሪካ ሀገራት በህዝብ ብዛት ናይጄሪያን ቀጥላ በሁለተኝነት የምትቀመጠው ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ባለፉት ሩብ ክፍለ ዘመን ዕይታ የማታውቀው አይነት ነው። በየቦታው በየአካባቢው ወጣቶች ይታሰራሉ፤ ወጣቶች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ይፈጸምባቸዋል፤ ባስ ሲልም አንዲት ሕይወታቸውን የሚያጡበት ጠያቂ የበዛበት መልስ የሌለበት ዘመን ላይ ደርሰናል።

የቀድሞ ሥርዓት ወጣቶችን እየገደለ የጥይት ሂሳብ እያስከፈለ፤ የፍየል ወጠጤ እያዘፈነ ሰውን ከእንስሳ በታች ያደረገ ሥርዓት ሀገሪቷ አሳልፋለች፤ አሁንም ቢሆን ሕግን ከለላ በማድረግ ከቀድሞ የሚተካከል ተግባር እየተፈጸመ እያየን እየሰማን እንገኛለን። ማኅበረሰባችን እጅጉን ሰላሙን ካጣ ቆይቷል፤ ነገር ግን የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀገሪቷ ወደ ሰላሟ እንደተመለሰች በቴሌቪዥን መስኮቶች እና በሬዲዮ ጣቢያዎች ለህዝቡ ይነግሩታል፤ ነገር ግን ሀገሪቷ ላይ የሚታየው የሰላም ሁናቴ እና በጆሯችን የምንሰማሰው ዜና “ፍየል ወዲህ …” እየሆነብን ተቸግረናል።

ብዙ ሰው በኦሮሚያ፤ በአማራ እና የተወሰኑ የደቡብ ክልሎች የህዝብ አስተዳደር ሥርዓቱ ራሱ ሰላሙን አሳጥቶታል፤ ውስጣችን ሁሌ “ዛሬ ደሞ ምን ይፈጠር ይሆን?” የሚል ስጋት ያርደዋል። መንግሥትም ሰላሟን እንድታጣ ያደረገው አካል ሰላሟን ለመመለስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጣ ቀናት ተቆጠሩ። ይባስም ብሎ የህዝቡን የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዳይኖር፤ የመረጃ ፍሰቱ ሰዎች ጋር ደርሶ ሌላ መልስ ይዞ እንዳይመጣ እንደ ገደል ማሚቱ ተጋጭቶ እንዲመለስ በማሰብ ማኅበራዊ ሚዲያውን በማን አለብኝነት ከዘጋ ቀናት ተቆጠሩ … እውን ለዚች ሀገር ሰላም መመለስ ፌስቡክና መሰል ማኅበራዊ ሚዲያዎች ምን ያህል ሚና አላቸው? ብሎ የሚጠይቅ አካልም አላገኝንም።

የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን መረጃ በማጠናቀር የሚታወቅ “ኢንተርኔት ወርልድ ስታትስ” ድረገጽ፤ የ2016 መረጃው እንደሚያመለክተው በዓለም ላይ በጠቅላላ 1.6 ቢሊየን ሰዎች ፌስቡክ እንደሚጠቀሙ ያስቀምጣል፤ ከነዚህ ውስጥ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙት 146 ሚሊየን ሰዎች መሆናቸውን በመቶኛ ሲቀመጥ 9.4% ብቻ እንደሆኑ ያሳያል። በአፍሪካ የ46 ሚሊየን ህዝብ ባለቤት የሆነችው አልጄሪያ 15 ሚሊየን የፌስቡክ ተጠቃሚ ሲኖራተ፣ ግብጽ ከ90 ሚሊየን ህዝቧ ውስጥ 32 ሚሊየን ያህሉ የዚህ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ መሆኑን ያሳያል። ኢትዮጵያ 102 ሚሊየን ከሚደርሰው ህዝቧ ውስጥ 4.5 ሚሊየኑ ይህን ሚዲያ ይጠቀማል ብሎ ያስቀመጠ ሲሆን፣ በመቶኛ ከመቶ ሰዎች ውስጥ 4 ሰው ብቻ የፌስቡክ መጠቀሚያ ስምና የይለፍ ቃል እንዳለው ያስረዳል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፤ በሀገራችን የታዩትን መሰረታዊ የሕግ የኢኮኖሚ እና የማንነት ጥያቄዎች በማደባበስ፤ ለጥያቄዎቹ ተገቢውን መልስ በተገቢ ጊዜ ባለመስጠት፤ ከጥያቄዎቹ ጋር ምንም ተያያዥነት የሌላቸውን አካሎች ተጠያቂ በማድረግ፤ መንግሥት ካለበት አፍዝ አደንግዝ ሥርዓት ለመላቀቅ ባለማሰብ እና ህዝብን ለሚቀጥሉት አርባ እና ሃምሳ ዓመታት በዚህ መንገድ እገዛለሁ በሚል የእውር መንገድ ባለመውጣት ለህዝብ ተጠቃሚነት የተሠሩትን የመገናኛ መሰረተ ልማቶች በሚፈልጉበት ጊዜ እየዘጉ፤ ሲያሻቸው እየከፈቱ፤ ህዝቡ ከመረጃ፣ ከነባራዊ ሁኔታ እና ከዓለም ተቆራርጦ እንዲቀር የሚያደረግ ሥራ፤ የደነዘዘን ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚደረግ ድርጊት መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል።

የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዱአለም በአንድ ወቅት ከሪፖርተር ሀገሪቷ ላይ አለመረጋጋት በተፈጠረ ቁጥር ኢንተርኔትን ለምን እንደሚዘጉ ተጠይቀው የሰጡት መልስ፤ “ይህ የእኛ ኃላፊነት አይደለም፤ ይህን የደህንነቱን ሥራ የሚሠራ ሌላ አካል አለ” በማለት ነበር መልስ የሰጡት። መንግሥትም ይህን የቴሌኮም ዘርፍ ለግል ባለሀብቶች ክፍት የማያደርግበት የመጀመሪያው ምክንያቱ “ደህንነት” ብቻ ነው። ዘርፉን “የምትታለብ ላም” እያሉ ተቋሙን ላም፤ የህዝቡን አገልግሎት አግኝቶ መክፈል ከሚገባው በላይ እያስከፈሉ፤ የህዝብን ገንዘብ ከላም የሚገኝ ወተት አድርጎ ማሰብ ለሀገርም ሆነ ለህዝብ የሚበጅ አይደለም። መሰረተ ልማቱ የተሠራው የሀገሪቱን መጻዒ ተስፋ በመረጃ እና በቴክኖሎጂ በማገዝ አደጉ ከሚባሉት ሀገራት ዘንድ ማሰለፍ ከሆነ ይህ ዘርፍ እጅጉን ሊታሰብበት ይገባል። ያለበለዚህ የህዝብን የመናገር የመጻፍ፤ መረጃን የማግኝት እና መረጃን የማስተላለፍ መብት ላይ ከሕግ ውጪ የሚደረግን ተግባር በሂደት ሁሉም ዋጋ የሚከፍሉበት ይሆናል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!