ሸንቁጥ አየለ

Out of Many WE are ONE!

ኢትዮጵያ በምልዓት ድና እና ተፈውሳ ማዬት የምትፈልጉ ኃይላት "አንድ ኢትዮጵያ! አንድ ሀገር! አንድ ህዝብ!" የሚለውን የአስተሳሰብ አድማስ እንዳትለቁ። ለነገሩ ይሄ አስተሳሰብ ከተሸነፈ ቆዬ። የፀረ-ኢትዮጵያዊነት ኃይላት በመጀመሪያ ወደ ምድር ከስክሰው በእግራቸው የረገጡት እና ያስረገጡት ይሄን አስተሳሰብ ሐሰት ነው በማለት ነው። የአንድን ወገን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚነፋ ፕሮፖጋንዳ ነው በሚል ሐሰተኛ ቀመር ተነስተው ነው ውድቅ ያደረጉት። የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም አንድነት የለውም ብለው ተነስተው ይሄው ዛሬ ሀገሪቱን የህልውናዋ ማክተሚያ ወደ ሆነ አፋፍ ላይ ገፍተዋት ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ ጥለዋታል። ከዛሬው ትርምስ ይልቅ የነገው ትርምስምስ ይበልጥ አሳሳቢ ነው።

ሆኖም ሁሉም ቢተራመስ የመጨረሻው አሸናፊ እና ገዥ ሃሳብ ሆኖ የሚወጣው እና ህዝቡን የሚታደገው "አንድ ኢትዮጵያ! አንድ ሀገር! አንድ ህዝብ!" የሚለው አስተሳሰብ ነው። አብዮት የሚባል ደንባራ ፈረስ በኢትዮጵያ ምድር ከተነሳበት ዘመን ጀምሮ፤ ወያኔ እና ሻዕቢያ የፖለቲካውን አስተሳሰብ ከተቆጣጠሩበት ዘመን ጀምሮ ይሄን የተቀደሰ አስተሳሰብ ከሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን አፈር አስግጠውታል። መጀመሪያ እንዲሸነፍ እና ኢትዮጵያውያን ለዘበተኛ ወይም ግዴለሽ አቋም እንዲይዙ የተደረገው በዚህ አስተሳሰብ ላይ ነው። ሲገፋም ይሄ "አንድ ኢትዮጵያ! አንድ ሀገር! አንድ ህዝብ!" የአንድን ብሔር ጥቅም ለማስጠበቅ እንደተነገረ ወይም እንደሚነገር በማስመሰል ፀረ-ኢትዮጵያውያን ብዙ አራግበውታል። አሁንም እያራገቡትም ነው።

ለመሆኑ "አንድ ኢትዮጵያ! አንድ ሀገር! አንድ ህዝብ!" ምን ማለት ነው?

1. አንድ ሀገር

አንድ ሀገር ማለት የማይከፋፈል በአንድ የሕግ የበላይነት ስር ያለ የተባበረ ሀገር ማለት። ወያኔ እንደ ቀመረው አንቀጽ 39 ግን አንድ ሀገር የሚባል የለም። ማንም ተነስቶ ከፍቶኛል፣ ኢትዮጵያዊነት አስጠልቶኛል ብሎ ሀገሩን አፈራርሶ ይሄዳል። ለምን ኢትዮጵያዊነት ከትዳር እንኳን ያነሰ ዋጋ አለውና። የመጨረሻው የፀረ-ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ማለት ይሄ ነው። አሜሪካኖቹ የተባበረች አሜሪካ ሲሉ የማትከፋፈል አንድነቷ የተጠበቀ ታላቅ እና ማንም የማይደፍራት ሀገር ማለታቸው እንደሆነው ሁሉ፤ መላው ዓለም የአንድ ሀገርን ጽንሰ ሃሳብ በማራመድ ነው የተከበረ እና ታላቅ ህዝብ ሆኖ የወጣው። ፀረ-ኢትዮጵያዊው ወያኔ እና የፀረ-ኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝ ኃይላት ግን ይሄ አንድ ሀገር የሚለው ሃሳብ የኢትዮጵያ ነገሥታት በተንኮል አንድን ወገን ለመጥቀም እንደፈጠሩት በማስመሰል አሁን ድረስ የሐሰት መርዛቸውን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ይተፋሉ። ከሞላ ጎደል ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳቸው በትውልዱ ልብ ውስጥ ቅቡልነት አግኝቷል።

2. አንድ ህዝብ

የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ህዝብ ነው ሲባል፤ ከዘረ መል (DNA) አንድነቱ ይጀምራል። ቢገፋ የኢትዮጵያ ልጅ ቢሄድም የዮቶር ልጅ ሄደም ከተባለ የኖህ ልጅ ነው። በፍጻሜውም የአንድ የአዳም ልጅ ነው። በመሃሉ ያሉት የቋንቋ ልዩነቶች በመሰረታዊነት የተለያየ ህዝብ ነው የሚያስብሉት አይደሉም። የኢትዮጵያ ህዝብ ወንድማማች እና በደም የተሳሰረ፣ በባህል የተቆራኘ፣ በስነልቦና የተሰናሰነ ብሎም የጋራ ታላቅ የወደፊት ራዕይን ያነገበ ህዝብ ነው። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ የሚለውን ሃሳብ/ህዝብ/ የመሰረተው ፀረ--ኢትዮጵያውያን እንደሚሰብኩት ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር እራሱ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ወይም በሰው ልጅ ታሪክ አላምንም ማለት መብት ነው። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደሚያስረግጠው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። አንዳንዱ መርዙን ለመርጨት ሲነሳ ይሄ የቆዬ ተረት ተረት ነው ብሎ መተርተር እና መዋሸት ይጀምራል። ታሪክ እና እውነት አውቆም የቆዬ እና የጥንት መሆኑ ጠፍቶት ሳይሆን አንድ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚለውን እውነት ለመካድ ስለሚፈልግ ነው። ጥላቻው እውነትን ለመካድ ድፍረት ስለሚሰጠው ነው።

እናም ትንቢተ አሞጽ 9፣ 7 የእውነታውን ማስረገጫ እንዲህ ብሎ ያቀርበዋል፦

”የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?” ይላል እግዚአብሔር። እንደዚህ አይነት በርካታ እውነታዎችን ጥንታዊው መጽሐፍ ያቀርብልናል። የኢትጵያዊው መልኩ፣ መልክዓምድሩ እና ስነምግባሩ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ በደንብ ግልጽ ሆኖ ተነግሯል።

3. አንድ ኢትዮጵያ

እናም አንድ ኢትዮጵያ! ዛሬ ፀረ-ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያዊነትን መሰረታዊ እውነታዎች በሙሉ ክደው እና አስክደው የጩኸታቸው ከፍታ አድማስ ጥጉን ተቆጣጥሯል። "አንድ ኢትዮጵያ! አንድ ሀገር! አንድ ህዝብ!" የሚለው አስተሳሰብ ደግሞ ወደ ስርቻ ተገፍቷል። ሌላው ቀርቶ የአንድነት ሃሳብ እናቀነቅናለን የሚሉት ወገኖች እራሱ ይሄን ሃሳብ እና እውነት ሽሽት ላይ ናቸው። ከታጠቡ እስከ አንገት ነው። ከታረቁ ከአንጀት እንዲሉ ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጋር ነን የምትሉ ኃይሎች "አንድ ኢትዮጵያ! አንድ ሀገር! አንድ ህዝብ!" የሚለውን የአስተሳሰብ መሰረት አትልቀቁ። ከዚህ አድማስ ላይ ወርዳችሁ ኢትዮጵያዊነትን በድፍረት ማራመድ ከቶም እንደማትችሉ እወቁት።

ፀረ-ኢትዮጵያውያንን መጀመሪያ በአስተሳሰብ ማሸነፍ ካልተቻለ ፀረ-ኢትዮጵያውያንን በተግባር ማሸነፍ አይቻልም። የፀረ-ኢትዮጵያውያን የአስተሳሰብ የበላይነት የሚከሽፍበት ዘመን ሲመጣ ያኔ የፀረ-ኢትዮጵያውያን ግብዓተ መሬት እውን ይሆናል። ፀረ-ኢትዮጵያውያንን በአስተሳሰብ ማሸነፍ ሳይቻል ኢትዮጵያን ማዳን አይቻልም።

4. ፀረ-ኢትዮጵያውያን እንደሚሰብኩት፤ "አንድ ኢትዮጵያ! አንድ ሀገር! አንድ ህዝብ!" የሚለው አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ህዝብ መሃከል ያሉ የቋንቋ እና ሌሎች ልዩነቶችን የማቻቻያ ስልት የለውም ይላሉ። ይሄ ግን ያው የተለመደ ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳቸው ነው። በሀገሪቱ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ብሔራዊ ቋንቋዎች በማስፈን እንዲሁም ፌደራላዊ/አሃዳዊ/ወይም ምንም አይነት የመንግሥት አወቃቀሮችን እውን በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብ በተሻለ የሚተዳደርበትን የተሻለ ሥርዓት መገንባት "አንድ ኢትዮጵያ! አንድ ሀገር! አንድ ህዝብ!" የሚለውን አስተሳሰብ ማሳለጫ ነው። የህዝቡን አንድነት፣ የሀገሪቱን ህልውና እና ሕብረት መጠበቅ ብሎም የተሻለች የበለጸገች ሀገር መፍጠር የሚቻልበትን ማንኛውንም ዘመናዊ አስተሳሰብ መከተል የሚያስችል ሰፊ መሰረት አለው። ግን ሁሉም ማጠንጠኛው መሆን ያለበት "አንድ ኢትዮጵያ! አንድ ሀገር! አንድ ህዝብ!" የሚለው የጋራ መዳረሻ ሀገራዊ የአብሮነት ራዕይ ነው።

ማስታወሻ:-
የኢትዮጵያ ነገሥታት "አንድ ኃይማኖት፣ አንድ ሀገር" የሚል ሃሳብ ያራምዱ ነበር ስለሚለው ሐሰተኛ ክስ
”አንድ ኢትዮጵያ! አንድ ሀገር! አንድ ህዝብ!” የሚለውን መርኅ አንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያውያን ሆን ብለው ከኃይማኖት ጋር እያሳከሩ ኢትዮጵያዊነት ብሔረተኝነት እንዳያብብ ስለሚያደናብሩ፤ ”አንድ ኢትዮጵያ! አንድ ሀገር! አንድ ህዝብ!” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ከኃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ማብራራት ይገባል። ፀረ-ኢትዮጵያውያን እና ሐሰተኞች ቆርጠው በመቀጠል ኢትዮጵያዊነት ላይ ያላቸውን የጥላቻ መርዝ ለመትፋት ሲሉ ነገሥታቱ "አንድ ኃይማኖት፣ አንድ ሀገር" የሚል ሃሳብ ያራምዱ ነበር በማለት ሳያፍሩ እና ሳይሸማቀቁ፣ ዓይናቸውን በጨው ታጥበው ይከሳሉ። አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው ፈቃድ ተነስተው የሚናገሩትን አስተሳሰብ በኢትዮጵያውያን ነገሥታት ላይ በመለጠፍ የዚህን ዘመን ትውልድ በጥላቻ ጭቃ ውስጥ ይረግጥ ዘንድ ወያኔ እና ሌሎችም ፀረ-ኢትዮጵያውያን ብዙ ሐሰተኛ ወሬዎችን አናፍሰዋል። እያናፈሱም ነው።

ሆኖም በአጼ ሚኒልክም ሆነ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ”ኃይማኖት የግል፤ ሀገር የጋራ” የሚል መፈክር እንደነበረ ማስታወስ ተገቢ ነው። ኢትዮጵያውያን ነገሥታት በዓለም ላይ የነጻ ፈቃድ አስተሳሰብ አራማጅ ስለሆኑ ነው እስልምናን ከመጥፋት ያዳኑት። እስልምናን ማዳን ብቻ ሳይሆን፤ እስልምና በኢትዮጵያ ህዝቡ ፈቃድ ተቀባይነት ካገኘ እንዲስፋፋ በፈቃዳቸው ክርስቲያኖቹ ኢትዮጵያውያን ነገሥታቶች አዋጅ አስነግረው ሙስሊሞቹን አትንኳቸው ብለው የነብዩ መሐመድን ተከታዮች ሁሉ አክብረው ሃሳባቸውን በነጻ እንዲያራምዱ ፈቅደው ነበር። ዛሬ ምናምንቴው ትውልድ አባቶቻችን ላይ ጣቱን ለመቀሰር እና በባለጌ መንፈሱ ለመሳደብ ምንም የሞራል ብቃት የለውም። ወያኔዎች እና ሌሎችም ፀረ-ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚያናፍሱት ወሬ ሐሰት መሆኑን እያወቁ፤ ግን በሬ ወለደ ፕሮፖጋንዳቸውን ቀጥለዋል።

ክድህደት እና ሐሰት መገለጫው የሆነው የአብዮቱ ዘመን እና ይሄኛው ትውልድ ግን ሁል ጊዜ የቀደሙ አባቶቻችንን እውነተኛ ማንነት መካድ ባህሪው ነው። እፉኝቱ ትውልድ የቀደመውን ዘመን በሙሉ በማጥፋት እና በእግሩ በመረጋገጥ ዘመናዊ የሆነ ይመስለዋል። ስለዚህ ይሄ ትውልድ ስለአባቶቹ የቀደሙ ነገሥታት በተገቢው ደረጃ ማወቅ አለበት። የነበሩን አባቶች ማንንም ተነስተው በግድ ይሄ እምነት ይኑርህ አላሉም። የዚያን ዘመን በሚመጥን ደረጃ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያኛው ዘመንም በዘለለ ደረጃ ነጻ ሀገር የመሰረቱ፣ የመሩ ብሎም ነጻ አስተሳሰብ ያራምዱ የነበሩ ነገሥታት አባቶች ነበሩን። እፉኝቱ ትውልድ ይሄን ቢክድ ወይም ባይክድ ለውጥ የለውም።

የቅርቡን እንኳን ብናስታውስ፤ ፕሮቴስታንት ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ አጼ ኃይለሥላሴ የፕሮቴስታንት ሰባኪዎችን አትንኩ በማለት የስብከት አካባቢያቸውንም ለህዝቡ አሳውቀው በክብር በኢትዮጵያ ስብከታቸውን ሲያከናውኑ ኖረዋል። ይሄ ትውልድ ግን ውለታ መረጋገጥ መሰልጠን ስለሚመስለው የቀደመውን ሥራ ሁሉ ካላንቋሸሸ ከቶም አዲስ ሃሳብ የገለጸ አይመስለውም። ስለዚህ የዚህ ሁሉ አስተሳሰብ ሰለባ የሆነውን ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ በማስተማር ማዳን ይገባል።

"አንድ ኃይማኖት፣ አንድ ሀገር" የሚል አስተሳሰብን አባቶቻችን ነገሥታቶች ፈጽመው አራምደው አያውቁም። ይሄ የሐሰት ክስ በአባቶቻችን ላይ ከሚነዛው የፈጥራ ክሶቹ አንዱ መሆኑን ይሄ ትውልድ ማወቅ አለበት። ኃይማኖት የሰማይ መንግሥትን የሚያወርስ ምስጢር ሲሆን፤ ሀገር ደግሞ የምድር መንግሥት ጉዳይ መሆኑን የቀደሙ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት አባቶች ጠንቅቀው የሚያውቁ በመንፈሳዊነታቸውም የሠለጠኑ ኃይላት ነበሩ። ስለዚህ የምድሩን እና የሰማዩን መንግሥት የሚቀላቅሉ አልነበሩም። ሁሉንም በየመልኩ እና በየፈርጁ መያዝ የሚችሉ ኃያላኖች ነበሩ እንጅ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!