ዩሱፍ ያሲን

Gonder protest

1. ኢትዮጵያ በለውጥ ዋዜማ

በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ቀጣይነት ሊኖረው የሚችል ሁኔታ አይደለም (Unsustainable) ሲባል ሰንበትበት ብሏል። አንድ ሐሙስ ቀረው እየተባለ መነገር የጀመረው ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። የሥርዓቱ ዕድሜ ካንድ ሐሙስ ይልቅ ከላይ ወደ ዜሮ በሚደረግ የኋሊት መቁጠር የሚዳዳቸው ታዛቢዎቹም አሉ። በፈረንጅኛው Count Down የሚሉት ስሌት መሆኑ ነው። እንደ ተለመደው ኢትዮጵያ ታሪካዊ መጋጠሚያ ላይ ቆማለች፣ በመንታ መንገድ ላይ ናት መባሉ እንደገና እየተዘወተረ መጥቷል። ሁሉም ግን ኢትዮጵያ ወዴት? የሚለውን ጥያቄ እያስጨነቀው ነው። ኢትዮጵያ አሁንም ታሪካዊ መጋጠሚያ ላይ መቆሟ አያነጋግርም።

ወያኔ/ኢህአዴግ አንድ ሐሙስ ቀርቷታል ትንበያ ላይ ሁላችን ባንስማማም በለውጥ ዋዜማ ላይ ናት መባሉ ያስኬዳል። “በለውጥ ማዕበል ዋዜማ ላይ መገኘቷ ሁሉን ቢያስማማም የጉዞዋ አቅጣጫ ወዴት እንደሆነ ግን አነጋጋሪ ይሆናል። ሀገራችን በዲሞክራሲ ለውጥ አቅጣጫ ትከንፋለች ወይስ ፍርስርሷ ወጥቶ ትበታተናለች? ምኞትና ሟርት፣ ተስፋና ስጋት የሚደበላለቅ ቢሆንም መፃኢ እጣ ፋንታዋ ብዙዎችን ስጋት ላይ ጥሏል። የተወሰኑ ዜጎቿን ያስቆዝማል፤ ያሳስባልም። ”ይህንን የከተብኩት የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ነው”1 ። ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ ናት መባሉም ትክክል የሚሆነው በሀገሪቷ የሰፈነው ሊቀጥል የሚችል ሁኔታ አይደለም ከሚለው መሠረታዊ ግንዛቤ ነው። ፈረንጆቹ Unsustainable የሚሉት ዓይነት መሆኑ ነው። ወያኔ/ኢህአዴግ አደርገዋለሁ ያለው ጥልቅ ተሓድሶ ለጊዜው ወደ ጎን አቆይተን በጥልቅ የለውጥ ማዕበል ዋዜማ ላይ ናት መባሉ ያስኬዳል። ልክ እንደ 1974 (1966)። ልክ እንደ 1991 (1983)።

2. የገዢው ፓርቲና መንግሥት ግብረ መልስ - መካድ እና መገረም

ወያኔ/ኢህአዴግ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መነጋቱን ተቀብሏል። ለምን? ምክንያቱ ቀውሱን በኢሕገ መንግሥታዊ በሆነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መልስ ለመስጠትና ለማስተናገድ እየሞከረ ነው። ለዚህ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው፣ ባለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማስተናገድ ወይም ማስተዳደር የማይቻል አስገዳጅ ሁኔታ በመፈጠሩ ። ባንዳንድ ቋንቋዎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁኔታ ከተለመደ ሕጋዊ አሰራር ውጭ ያፈነገጠ አሰራር የሚጠይቅ ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ነው። ኢአዘቦታዊ የሆነ ሁናቴ ውይም ያልተለመደ ሁናቴ መኖሩን መቀበል። ይህን ያልተለመደ ሁኔቴ በቁጥጥር ሥር ለማውል የግድ ከተለምዶ ያፈነገጠ የሕግ አሰራር አስፈለገ ማለት ነው። በነበረው ሕግ ማስተዳደር የማይቻል አፈንጋጭና ኢአዘቦታዊ ኩኔት ማስተናገድ አልተቻለም ነው በሌላ አባባል። በነገራችን ላይ፣ የአማርናችን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገላለጽ ራሱ ሁኔታውን በትክክል አይገልጸውም ማለት ይቻላል። በጀርመነኛና በእስከንደናቪያ ቋንቋዎች Ausnahmestand ውይም Unntakkstand ያልተለመደ ኩኔት (Exceptional ወይም Extraordinary) መሰኘቱ ይበልጥኑ ይዘቱን ያንጸባርቃል ቢባል ያስኬዳል። ስለዚህ በውስጠ ታዋቂነት ከመንግሥት ቁጥጥር ያፈነገጠ ሁኔታ ተከስቷል ነው። በሌላ አነጋገር፣ ሀገሪቷ Ungovernable ደረጃ ላይ ናት ማለት ነው። አንዱ የህዝባዊ ኢምቢተኛነት ዒላማም ይህው ሥርዓቱ ሚዛኑን አስቶ እንዲናጋ ማድረግ ነው።

ወያኔ ኢህአዴግ አደረገዋለሁ ያለው በጥልቀት መታደስ፣ ምርጫ ሕግ መለወጥ፣ ከለማዳ የሀገር ቤት ፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት መጀመር፣ ደመውዝ መጨመርና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ሀገሪቷን እያናወጠ ያለውን ቀውስ መመለስ እንደማይቻል እስካሁኑ ግንዛቤው አላገኘም፣ በእነሱ ዘንድ። የመንግሥት ባሥልጣናትም ሆኑ ደጋፊዎች ወገኖች ከመገነዘብ ይልቅ በጋህድ እውነታን የመካድ (SELF DENIAL) አባዜ ውስጥ ናቸው ማለት ይቀላል። ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ገለልተኛ ታዛቢዎችና አሜሪካና የኤውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ በርካታ የውጭ መንግሥታት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ችግሩን ያባብስ እንደሆነ ነው እንጂ ከቶ አይፈታውም ማለታቸው በግምት ሳይወሰድ። ከመጤፍ አይቆጥሩም ማለት እንኳን አይስኬድም።

በሀገር ቤት ያሉት የትግራይ ተወላጆችም ሆኑ ውጭ በዲያስፖራ ካሉት ውስጥም የተወሰኑት ለምን ቀሪው ኢትዮጵያዊ እንደጠላቸው በአግርሞት የሚጠይቁም አይጠፉም። ከGeoroge Bush Jr. ጋር በሚመሳሰል ግራግር መገረም Why do they hate us (ለመሆኑ ለምንድነው የሚጠሉን!) !) የሚጠይቁትን ማለቴ ነው። አልፎ ተርፎ፣ ያውም ያን ያክል ማስዋዕትነት ከፍለን ከደርግ ዲክታቶሪያዊ ሥርዓት ነፃ አውጥጣናቸው ውለታችን ይህ ሆነ ወይ ብለው የኢትዮጵያ ህዝብ ውለታ-ቢስነት እንጂ በሀገሪቷ የሰፈነው ሁኔታ አሳሳቢነትም ሆነ በሥርዓቱ ላይ የደቀነው የሕልውና አደጋ ገና የማይከሰትላቸው ማለቴ ነው። እርግጥ በዲያስፖራው የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ ሆነው የዚህ መንግሥት ተቃዋሚዎች በዝግምትኛ ጭማሬ ሳይሆነ በጆመትሪካዊ (Geometrical Proportions) እምርታ እየጨመሩ ናቸው። በዚህ መንግሥት ምትክ ጊዜያዊ መንግሥት ይመሥረት የሚሉት ደብዳቤ ፈራሚዎች ከ 12 ወደ 24 ብሎም ወደ 36 መሻቀብ ዓይነቱ ድርብ ድርብ የመባዘቱ ከስተት ማለቴ ነው። እርግጥ እነዚህ ኃይሎች ሀገር ውስጥ ካሉት ኃይሎች ጋር የሚገምዱት ቅንጅት ፣ ትብብርና እቦታው እስከሌለ ድረስ በሂደቱ ላይ ትርጉም ያለው ተጽእኖ ላያሳርፉ ይችሉ። በትግራይ ብሔራዊ ክልል በሕወሕት ውስጥ ባሉት አንጃዎች መካከል የሚፈጠረው የኃይል ሚዛንም ወሳኝ ነው። በአባይ ወልዱ የሚመራው የክልሉና ህወሓት እንኳን ከተቃዋሚ ሃይል ጋር ቀርቶ ከራሱ በተለያዩ ምክንያት ያለተግባቡ ወገኖች እንደገና ወደ ድርጅቱም ሆነ ወደ ትግራይ ህዝብ እቅፍ የመመለሱ ተግባርና ሂደት አስቸጋሪ አድርጎታል። በህወሓት አንጃዎቹ በኩል እሱን ገለል አድርጎ በፈትለወርቅ ገብረ እግዛአብሔር (የመለስ ትሩፋት መጽሐፍ ሞንጀሪኖ) ተክቶዋል ተብሎ ሰሞኑ የሚናፈስው ወሬ እንኳን እንደ አንድ አለዛቢና በመሃል አገናኝ ተድርጎ የሚገመተው ለዚህም ገመድ ጉተታ ይሆናል ። ወሳኙ የጅምላዊ እምርታው (Critical Point) ግን በበርካታ የሶዮሶ- ዳይናሚክስ (አንደራዳሪ ግፊቶች) እና ተጽእኖቹ ውጤት ይሆናል ተብሎ ይገመታል። አሁንም የሚታወቁ አይታወቄዎች ሊበል! ያ ቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ዶናልድ ራምስልድ ታዋቂ Unknown Knowns አባባል በመዋስ። ራሱ በወያኔ የሚካሄድ የኃይል አሰላለፍ፣ የኢህአዴግ ግንባር መሥራች ድርጅቶች የእርስ በርስ ግንኙነት፣ የብሔረተኛ ኃይሎችና ተቃዋሚ ድርጅቶች ትብብር፣ የውጭ ኃይሎች ጠልቃ ገብነትና ተጽእኖቸው እንደምታዎች፣ በመሳሰሉት ላይ የሚሞረከዝ ይሆናል። እነዚህ ፋክቶሮች ሁሉ የሚገናኙበትና የሚለያዩበት ነቁጣዎች ለይቶና ነቅሶ ለውሳኔ ሰጪዎች ማመቻቸት የአጥኒዎች ተግባር መሆን ይኖርበታል።

3. የአማራ ብሔረተኛነትና የወደፊት አቅጣጫው

የአማራና የኦሮሞ ኃይሎች ለዚህ መነሳሳት ሁለት ለኳሽ ፈንጂዎች በወያኔ ላይ የጠመዱበት ይመስላሉ። ኦሮሞቹ የአዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ የመስፋፋቷን ጉዳይ ምክንያት አድርጎ የዛሬ ዓመት (ኖቪምበር 12) የአማራ ወገን ደግሞ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጉዳይ አንግቦ በሰሜኑ ክፍል የጦርነቱን ፊሽካ መንፋቱ ነው። የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አማራ ራሱ እንደ አማራ ተመልክቶ ራሱን እንደ አማራ አደራጅቶ የሚደርስበትን ጥቃት ለመመከት በር የከፈተና የሁሉን አማራ ጠቅልል (Pan-Amhara) ስሜት ፈጣሪ የሆነ ድርጊት ነው። ከሓምሌ 5 ቀን 2008 ጀምሮ በሰሜን ጎንደርና በቀሩት የአማራ አካባቢ የሚደረገው ፀረ “የወያኔ-ትግሬ” ተጋድሎ የአማራ ትግል ተብሎ እንዲታወቅላቸው ይሻሉ። ትግሉ ከፍ ብሎ “ኢትዮጵያዊ” ወደ አካባቢያው ወርዶ “የጎንደር” እንዲሰኝ አይፈልጉም በሌሎች ስም እንዲጠራ አይሹም። የአማራን ኢትዮጵያዊ ብሔረተኛነት በምር ወደ አማራ ብሔረተኛነት ያሸጋገረ ድርጊት ነው ማለት ይቻላል። ጉዳዩ ከጎንደር የተወሰዱ መሬቶች ወደ አማራ ክልል ዳግም የመመለስ ጥያቄ ይመስላል ከላይ ላይ ሲታይ። ታስቦበት ይሁን ሳይታሰብበት ከስሜት ወደ እንቅስቃሴ መለወጥ ላይ ያለ በፖለቲካዊ ንድፍ የሆነ ነው። የሕግ ባለሙያዎች Status Quo Ante የሚሉት ዓይነት ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ ከመመለስ በላይ ነው። ያ ቢሆን ኖሮ የጎንደር ጉዳይ ብቻ ይሆን ነበር። ወልቃይቶች ዛሬ ራሳቸውን እንደ አንድ አማራ አካልና እንደ አማራ ብሔር አካልነታቸው ማንነታቸውን ሲጠይቁ ቀሪው አማራ ይህንን ጥያቄ እንደራሱ ጉዳይ አድርጎ የተነሳበት እንቅስቃሴ በመሆን ላይ ነው። ጉዳዩ የወልቃይትን የአማራ ማንነት ጥያቄ ምክንያት አድርጎ ይነሳ እንጂ፤ በአሁኑ ወቅት ከጎንደርነት ያለፈ ጥያቄ ሆኗል። ሌሎች በትግራይ የተጠረነፉ የወሎ መሬቶች ለጊዜው አልተካተተቱም። ይህ አስቀድሞ የታሰበበት ይመስላል። ጉዳዩ አከላለሉን ብሎም ማንነት ተኮር ፌዴራሊዝምን ከሥር መሠረቱ በጥያቄ ውስጥ የሚከት አካሄድ ነው። አማራ በአማራነት ይደራጅ ወይስ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ የሚለው ክርክር ገና አልተቋጨም። አማራ አለ ወይስ የለም የሚለው ክርክር ግን የተደመደመ ይመስለኛል። አማራ አለ ወይስ የለም ክርክር አብቅቶ ፣ አማራ ብሔረተኛነት ወዴት አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል? የኢትዮጵያን አንድነትና እጣ ፋንታ ላይ ምን ዓይነት ድባብ ያጠላል የሚሉትን ጥያቄዎች ወደ ማንሳት እየመራን ነው። የአማራን ብሔረተኛነትና ተፈታታኝ ተግዳሮቶቹን በሚገባ መልኩ ለመፈተሽ ጠለቅ ያለ እውቀትም ትንሽ ምርምር ብጤ ይጠይቃል።

የብአዴን እዚህ ውስጥ የሚኖረው ሚና መፈተሽ ይኖርበታል። የአማራ ብሔረተኛነት መገለጫዎችና ምክንያቱ በትግራይ የተካለሉ ሌሎች መሬቶች ወደ ነበሩበት መመለሱንና አማራን ከሚሰነዘርበት ጥቃት መከላክል እንደ አንድ መወናጨፊያ መሬት ተጠቅሞ በስሜት በኩል አድርጎ ወደ ሁሉ-አቀፍ አማራ እንቅስቃሴ ማደግ ላይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የምንመለከተው ይህንኑ ነው። እስከ አሁን የአማራውን ህዝብ እንወክላለን ብለው ሕልውናቸው ያስታወቁ እነ ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት፣ ቤተ አምሃራ፣ ዳግማዊ መላ አማራ ድርጅት፣ የአማራ ህዝብ ዲሞክሪያሲያዊ ንቅናቄና የመሳሰሉ ድርጅቶች ገና ብዙ ሥራ ይቀራቸዋል። ለፍልሚያ ብቁ የሚያደርጉ ዝግጅቶቻቸውን ገና እየተያያዙት ነው። ገና በጅምር ካለው የአማራ ድምጽ ራዲዮ በስተቀር። በሌላ በኩል አብዛኛዎቹ የአማራ ልሂቃን ዛሬም ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን አስቀድመው በሕብረ ብሔር ድርጅትነት ሥር የተጠለሉ ናቸው። እነዚህ በተለያየ ስም የሚጠሩ የአማራ ድርጅቶች በአንድ ላይ እንዲሠሩም ሆነ ባንድ ድርጅት ማጠቃለሉ ገና አልቻሉም። ከዚህም የተነሳ አካባቢያዊ ድርጅታዊ ቅርጽ የያዙት የጎንደርና የጎጃም ድርጅቶች እንኳን ራሳቸውን ማዋሃድ እስካሁን አልቻሉም ። እነዚህ በአማራ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ስራዬ ብለው የተያያዙት ይህንኑ ቅስቀሳ ነው። ራዲዮውም ዕለታዊ ተግባሩ አድርጎ የያዘው ይህንኑ ነው።

በሌላ በኩል ሁሉም በብሐረሰቡ እንዲደራጅ አብሶ አማራ ወዶ በግዱ የሚደርስበትን ጥቃት ለመመከት The Hard Way በብሐረሰብ መደራጀቱ እንዲቀበል ተደርጓል። አማራ መሉ በሙሉ በአማራነቱ እንዲደራጅ የገፋፉም የፈለጉ ወገኖችም የዛሬው አዝማሚያው እንደማይጥማቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። የዛሬ 25 ዓመት የተፈለገው ግን ይህ ነበር። አማራ እንደ ማንኛው “ብሔር፣ ብሔረሰብ” እንዲደራጅ ነበር ያኔ የወያኔ ፍላጎት። አሁን ግን ወያኔ የፈጠረውን የአማራ ብሔረተኛነት መቆጣጠር የማይቻለው ጭራቅ ሆኖበት ጉዳዩ በላቦራቶሪ ያበጃጁት የፋራንኪንእስታን ታሪክ መስሏል። አንድ በላብራቶሪ ሕይወትን ፈጥሮ ነገር ግን የፈጠረውን ፍጡር ተመልሶ ያስደነበረው ያንድ ሳይንቲስት ታሪክ ጋር እስከ ማመሳሰል ያደርሱታል። ፈጣሪውን ያስደነገጠ ፍጡር ሆኖ አረፈው ነውና፣ ብሔረተኛቱ የራሱ ሕይወትና አቅጣጫ ቀይሶ። The story of a scientist who created life and was horrified by what he had made የተባለለት ተመራማሪ።

4. አማራና ኦሮሞ - ትብብርና ፉክክር

ልክ የዛሬ 160 ዓመት በፊት የሁለቱ ህዝቦች መሪዎች የንገሡቹ አንጋሽና ገዳይ የሚባለው ራስ ስሁል ሚካኤልን ከጎንደር ወደ አድዋ እንዲመለስ ያደረጉበት ብልሃት ዛሬ መሥራቱ አጠራጣሪ ሆኖዋል። ራስ ስሁል ሚካኤል አንድ ተጽእኖ ፈጣሪ ራስ ነበሩ እንጂ የተደራጀ ያንድ ክልልና ብሔረሰብ ኤሊት ኃይል አልነበሩም። ጊዜውም ቦታውም ታሪካዊ ዳራውም ይለያል። የሁለቱ የትግል አጋርነት፣ የአማራን የአማራ የትግል አጋርነት በፀረ ወያኔ ትግሉ የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን ባንጠራጠርም ትብብሩ በተደላደሉ መሠረቶች ላይ መቆሙን ግን እርግጠኞች አይደለንም። ለዚህ ጥርጣሬ በርካታ ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል። ሁለቱም በ1983ቱ ላይ ባልተዘጋጁበት ሁኔታ መጋፈጥ ነበረባቸው። ወያኔ/ኢህአዴግ የተሰኘ ድርጅት መሥርቶ እነሱን እንዳሻው አንዱን ከደምቢዶሎ አፈናጠጥኩ/ride ብሎ ለጊዜው ከተጠቀመባቸው በኋላ አስፈላጊነታቸው እንዳበቃ ሲገነዘብ በቦሌና በባሌ አባረራቸው። በወቅቱ ያለ ውክልና ቀርቶ በነበረው በአማራ ስም አሥመራ ድረስ ልዑካን ልከው “ይቅርታ” እንዲጠይቁ ተድርጓል። ይህንን ሁኔታ ዳግም እንዳይደገም ነው በአሁኑ ወሳኝ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲገኙ የተፈለገው። “አማራ የሌለበት ቀርቶ የሚገባውን ውሳኔ አንኳ እንዲያሳርፍ ያልተደረገበት ስብሰባና ውሳኔ ከንቱ ቅዥት ነው” እያሉ ናቸው የአማራ ወጣት ብሔረተኞች። ይህንን ለማድረግ የፈረጠመ ክንድ ያስፈልጋል። የአማራ ብሔረተኛ ኃይሎች እየገነባን ነን የሚሉት ይህን አቅም ነው። ጆሓር መሓመድ ለኦሮሞው ትግል ገነባሁ የሚለውም ይህንኑ Capacity Building ነው። ይሀ ፉክክር አሁንም እንዳለ ነው። ፉክክሩ ጤናማነት ከጎደለው ሊመለስ ወደማይችል ፍጥጫ እንዳያመራ ስጋቱ እንዳለ ነው።

በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ባለፉት 25 ዓመታት የሠራበትን የተደራጀ የፉክክር ሥርዓት እንዲሁ በዋዛ ልናልፈው አንችልም። ይህ የተደራጀ ፉክክር የግድ መርገብ ይኖርበታል። ባለፈው የ 1983 ሰኔ ኮንፈረንስ እንዳልወከል ተድርጌያለሁ የሚል ፖለቲካዊ ኃይል በአሁኑ ክብ ጠረጴዛ ዙርያ ከውሳኔ ሰጪዎቹ መሃል እንጂ በእጣ ፋንታቸው በሚወሰንባቸው ተራ ውስጥ አልኖርም ብሎ ቆርጦ የተነሳ ይመስላል። ኦሮሞ ከደምቢዶሎ የመፈናጠጥ እድል (Ride) ሰጠናችሁ እንጂ መቼ ተዋጋችሁ ዓይነቱ የወያኔን ልግጫ ዳግም መስማት አይፈልግም። እንዲያውም የስብሰባ ጥሪ ወረቀት አዳዮች መሆንም ይዳዳቸዋል። Why Not! ምን ያንሳቸዋል! ማለት ነው። “በሀገራዊ ኃላፊነት” ከተንቀሳቀሱ የምትለዋን ሓረግ ባክልበት ምንም ክፋት የለውም። ሙስሊም ወገኖቻችንም ይኸው ተመሳሳይ ቅሬታ አላቸው። ቪዥን ኢትዮጵያ የተባለው ድርጅት ከኢሳት ጋር በጠራው የሰሞኑ የጥናት ሰሚናር አንድም የሙስሊም ስም ያለው ሰው አለመጋበዙ ጭምር ቅር እንዳሰኛቸው መግለጣቸውም ከዚህ ጋር የተገናኘ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ”If your not on a negotiating table talking probably you might find yourself on a menu to be eaten” የሚትለዋን የፈረንጅ አባባል አሁን አሁን ሁሉም የተዋሃዳቸው ይመስላሉ።

“አሁን ትብብር በኋላ ላይ ፉክክር” የምትል የተቃዋሚ ድርጅቶች መፈክር የሚታስታውሱ ትኖራላችሁ። አሁን ግን ያ ትብበር አናይም። ይልቅስ የምንመለከተው ፉክክርን ነው። ያ ያስፈራል! 25 ዓመታት ከተደራጀና የሥርዓት ቅርጽ የያዘው ፉክክር በኋላ ዋና ዋና ሁለቱ ብሔረሰቦች በየፊናቸው የተጠመደበት “የአቅም ግንባታ” ውድድር እንጂ “የወያኔ ትግሬዎችን” የተከዜን ድንበር የማሻገር ዝግጅት አልመስል እያለ ነው። የሁለቱ ብሔረሰቦች ትስስርና ግንኙነትና የውደቱ አንደራዳሪ ኃይሎቹ በዚህ ሂደት አንዱና ዋናው ያልታወቀ አይታወቄ ቀመር ነው። የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ የሁለት ማሕበረሰቦች የውል የዘር ምንጭ ግኝትም ሆነ ማረጋገጫ ወይም የሁለቱ ህዝቦች ጎን ለጎን የበቀሉ ዛፎች ምሳሌዎች የሚጠግኟቸው ክፍተቶች አይመስሉም። ሁለቱ ከተስማሙ የሀገርቷ ችግር በሙሉና በቅጽበት እልባት የሚያገኝ የሚመስላቸው ወገኖች እንዳሉ፣ ይህ ትብብር በእነሱ ኪሳራ ሊሆን እንደሚችል የምሰጉ ወገኖችም አልጠፉም። ሁሉቱም ቦታ ሊኖረው የማይገባ ነው። መነጋገሪያ ነጥብ ሆኖ እልባት ማገኘት አለበት፣ የፍራቻው ምንጭ ተፈትሾ። አማራ በብሔረሰብ መደራጀት ግራ የሚያገባቸው የትግራይ የሥልጣን ኤሊቶች ብቻ አልሆኑም። የአማራ አክቲቪስቶች ወደ እዚያ ጎራ መቀላቀል ሃብትና ሪሶርስን ይሻማብናል ወይም ከእነ አካቴው ያነጥፍብናል ስጋት የሚያንገላታቸው ወገኖች ናቸው። ከሰሞኑ የፌስ ቡኩ መጎሻሸም አርበኞች ግንቦት 7 እና ኢሳት የዚህ ፍራቻ ሰለባዎች ውስጥ መክተት ያስኬዳል። ይህ በግልፅ ውይይት ካልተፈታ ጎኒዮሽ መወራረፍ ሆኖ በተራው ከዋናው ፍልሚያ ያዘናጋል። በጋራ ዓላማ ብሔራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ መነጋገር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በሥልጣን ያለው መንግሥትና ገዢ ፓርቲ አሁንም ሁለቱ ብሔረሰቦች እንዳይገናኙ ከመጣር አይቦዝንም ብቻ ሳይሆን ላንዳቸው ወይም ለሌላኛው የገበረና ልዩ ልግስና የቻረ በመምሰል እንዳይቀራረብ ማድረግም ሆነ ወደ ራሱ ለመሳብ መሞኮሩን በትጋት እንደሚቀጥልበት ሳይታለም የተፈታ ነው። እነዚህን በሌሎችን ጭምር በክብ ጠረጴዛ ያስቀመጠ ውይይት ለብሔራዊ መግባባትና ሰለማዊ ሽግግር ሆነ በሀገሪቷ እጣ ፋንታ ጊዜ፣ ጥረት፣ መነጋገር፣ ዳግም መናገርን ይጠይቃል። በሽግግሩ ተግባራ ውስጥ በእነዚህ ጉዳዮች የሚነጋገርበት ጊዜ ያስፈልገናል።

5. የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት

ተቃዋሚዎችም ሆኑ ገዢው ፓርቲና መንግሥት የውጭ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነት አይጠሉም። እንዲያውም ይፈልጉታል ማለት ይቀላል። ለነጻነቱና ለሀገር ሉዓላዊነቱ ቀናኢ የሆነ የአድዋና የጣይቱ በጡል መንፈሳዊ መጣቀሻነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ ሊጨምር መሰለኝ። ሁለቱም ይቺ የአካባቢያችን ሰላም Oasis የሆነችው ሀገር መመሰቃቀል ከሚያስከተለው አካባቢያዊ የጸጥታ ብክለት ያስጠነቅቃሉ። ሌላ ጊዜ እንደዚያ ሚስቱ ጋር ግብግብ ገጥሞ ” ልንገዳደል ነው” በማለት የድረሱልኝ ጥሪ አስተጋባ እንደ ተባለው ጀግናው ባል በቄንጥ የፈረንጆቹን እይታ ያሽኮርምማሉ። የዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት እንደ ጊዜ ከተጀመረ ማቆሚያው የት እንደ ሆነ የሚወስኑት እነሱ ናቸው። ጣልቃ ገብነቱ ከገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴነት እስከ ሰላም አስከባሪ ኃይል ማሰማራት ሊደርስ ይችላል። በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ጋባዥነት እስከ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት አንቀጽ ሰባት ሙርኩዝነት የሚሰጥ ውሳኔ መሠረት ሠራዊት እስከ መላክ ድረስ ሊሄድ ይቻላል። በሊቢያ የዘለቁት በ ተመድ የጸጥታ ምክር አማኻኝነት ነው። ወደ ሶሪያ ሩሲያ የገባቸው በሥልጣን ባለው መንግሥት ጋባዥነት ነው። ሌሎች ያሰማሯቸው አሽበሪዎች ለማደን ነው። ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው ውጤቱ ግን አንድ ነው። የምንገምታቸው እንጂ የማናውቃቸው አይታወቄዎች በርከትከት ብለዋል። ዶናልድ ረምስፈልድ የሚታወቁ አይታወቄዎች የሚላቸው ታሳቢዎች እንበላቸው። ዛሬ በሶሪያ ጉዳይ የሚነጋገሩት ሁለቱ ኃያለን መንግሥታት ወኪሎች (ላቭሮቭ እና ጆን ኬሬ) ናቸው። ያውም የሶሪያ የመንግሥትም ሆነ የተቃዋሚ ወኪል ባልተገኘበት ስብሰባ። ለመግባት እድልም ቀዳዳም ካገኙ የት ላይ እንደሚቆም ባላገሩ አይደለም ወሳኙ ለማለት ነው። በዚህ ጽሑፍ በነጥብ 6 ላይ “ዋናዎቹ የሽግግሩ ጋሬጣዎችና ተግዳሮቶች” ሥር በተጠቀሱት ነጥቦች ውስጥ ዙሪያ ገቡ የአካባቢችንና የዓለማቀፉ የኃይል አሰላለፍ መመልከቱ ክፋት የለውም።

6. ሽግግርና ቅድመ ሁኔታዎቹ

ሽግግር ሲባል ወያኔ/ኢህአዴግ በወደቀ ማግሥት በሚደረግ ኮንፈረንስ ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ፣ ሚናና ተግባር ላይ ያተኮረና የተጠመደ ይመስላል። ከዚህ በፊት በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲነጋገር ማስገደድ ወይም ከእነአካቴው በግንቦት 20 ቀን 1983 እንደሆነው የነጻነት ታጋዮች በድል አድራጊነት 4ኪሎን መቆጣጠር ሊኖርባቸው ነው። እኛ ስለ ሽግግር ስንነጋገር የሚቀናን ስለሚደረገው ሁሉን አቀፍ ኮንፈረንስ ይመስላል። ምናልባት ያ የወታደራዊ ክንፉ ተግባርና ኃላፊነት በመሆኑ ምስጢር ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። እኔ የምጠይቀው ምናልባት ባለማወቅ ” በአይጧ ጭራ ላይ ቃጭሉን የሚያስረው ማን ነው ዓይነት” ገራገር ጥያቄ ነው። ሽግግሩ በሰኔ ኮንፊረንስ ላይ ሳይሆን በግንቦት 20 ላይ የሚጀምረው።

ሁሉም ሽግግሩ በሰላም ቢጠናቀቅ ይመርጣል። ቢቻል ኖሮ ወያኔ በሰላም ሥልጣኑን እንዲለቅ ይመኛል። አብዛኛው ሂደት ያለ ደም መፋሰስ እንዲሆን በማሰብ። ይህ እንደማይሆን ሁሉም ይገነዘባል። ቀዳሚ ጥያቄው በአመጽ በኩል አድርጎ ሰለማዊ ሽግግር ማድረግ ይቻላልን? ስለዚህ በርካታ ሲናሪዮዎች ያወጣል፣ ያወርዳል። አንዳንድ ጸሐፊዎች ሲናሪዮዎችን 6 ያደርሱታል (ያሬድ ጥበቡ)። ሌሎች ሦስት ያደርጉታል። ወደ ሁለት ምርጫ ዝቅ የሚያድርጉትም አይጠፉም። ሀገሪቷ ሰላማዊ ሽግግር ታስተናግዳለች ወይም በእርስ በርስ ጦርነት ትተረማመሳለች ዓይነቱ ነጭና ጥቁር የሚታያቸው ወገኖች አሉ። ሁሉም ከእይታ ማዕዘኑ ይበጃል ብሎ ያሰበውን ወርውሯል። የመፍትሔ ሃሳቦች ከየአቅጣጫው የተወረወሩ ናቸው። ማስፈራሪያዎችም አሁንም ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተዥጎደጎዱ ናቸው። ሁለቱም ክፋት የለውም። በርካታ መፍትሔ ሃሳቦችም እየቀረቡ ናቸው፣ ከውጭም በሀገር ቤትም። አንዳንዶቹ የሽግገር ምክር ቤቱ አባላትንም ጭምር መጠቋቆም ድረስ ይሄዳሉ። እነዚህን ሃሳቦች መሰብሰቡና ማጠራቀሙ በኋላ ለብሔራዊ ውይይትና መግባባት ኮንፊረንስ መልካም እርሾ ሆነው ያገለግላሉ። ሁሉም የጋራ ምኞትና መልእክት አሏቸው። ሁሉ በሀገሪቷ አንድነትና ሕልውና ዘላቂ ጉዳት የማያስከትል ሽግግር ይሻሉ። በርካታ ያልታወቁ አይታወቄዎች (Known Unknowns) እንቅልፍ ይነሱናል። ከ 42 ዓመት በፊትም ሆነ 25 ዓመት በፊት የነበረው ሁኔታ ዛሬ በኢትዮጵያ የምንመለከተው ሁኔታ ከለውጥ ዋዜማነቱና ከህዝባዊ መነሳሳቱ በስተቀር እምብዛም አይመሳሰልም። ያን ጊዜ ያልነበሩ ዛሬ ግን ወሳኝ አንደርዳሪ ኃይሎችን ገረፍ ገረፍ አድርገን እንመልከታቸው እስቲ።

ልክ በ 1974 (1966) እና ልክ 1991 (1983) ሀገሪቷ በለውጥ ዋዜማ ላይ ናት። ያሁኑ ግን ከ1974 (1966)ቱ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ውድቀት ወይም ከደርጉ 1991 (1983) ውድቀት ከሥር መሠረቱ ይለያል። ያሁኑ ለውጥ ከ 1991 የለውጥ ይልቅ የዋዜማ 1974 ጋር እየተመሳሰለብኝ አስቸገረኝ። ልክ 1974 አመጹን ወይም አብዮቱን በመምራት ላይ ነኝ ባዩ ወገን አልበረከተም። በስልጣን ያለውን መንግሥት የታጠቀ ኃይል ወይም ብሔራዊ ሠራዊት እያፈረካከሰ በቦታ የሚተካ ኃይል አይታየኝም። አለን ባዮቹ ቢኖሩ ከሁሉ በላይ የሚያሳስበኝ ግን ለሠራዊቱ ኃይሎች የሚደረገው ክዳና የህዝቡን አመጽ ተቀላቀል ጥሪ ነው። አሁንም በየቀኑ እየከዱ አመጹን እየተቀላቀሉ ያሉ ወታደሮች እንዳሉ ነው እየተነገረን ያለው።

የመንግሥት ግልበጣዎች ተሞክሮዎች ቱኒስ 2011 ግብጽ 2011፣ ሠራዊቱ እንደ አንድ ታዛዥ ኃይል በአለቆቹ ትእዛዝ በመንግሥት ቁንጮ ላይ አምጾ ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን እንዲወርዱ ወይም ገለል እንዲሉ አስገደደ። እምብዛም አማራጭ ያልነበረው መሪ ትእዛዙን ተቀብሎ ከሥልጣን ለቀቀ፣ እግሬን (ሂሊኮፕተሬን?) አውጭኝ ብሎ ፈረጠጠ/ገለል አለላቸው። በሌላም አገላለጽ ርእሰ ብሔሩ በሠራዊቱ አመራር ለሀገሪቷ ደህንነት ሲባል ተባረረ። በ1991 በጎረቤት ሶማሊያ በአምባገነኑ ዚያድ ባሬ ውድቀት ላይ የተከሰተው ከዚህ ለየት ይላል። በእነዚህ ዓይነቱ ጥሪ መሠረት የሠራዊቱ አባላት ሁሉ ወደ እናት ክፍላቸው ወይም ጎሳቸው ፈረጠጡ። ኮሎኔል ዓብዱላሂ ዩሱፍ እና ኮሎኔል ፋራህ አይዲድ የጦር አበጋዝነት ጅማሮው የዚህ የሠራዊቱ መከፋፈል ነው። ይህ ብሔራዊ የሠራዊትና የብሔራዊ መንግሥት ብተናና መፈረካከስ አጥኒዎቹ ሶማሊያይዜሽን የሚል ስያሜ ሰጡት። ሊባኖስን ከ1975 እስከ 1999 ድረስ ባተረማመሰው የርስ በርስ ጦርነት ሠራዊቱ ወደየእምነት ተጋሪዎቹ ዘንድ ነበረ የተሰለፉትና ሰልፋቸውን ያሳመሩት። ይህ ደግሞ ሊባናይዜሽን ተሰኘ። እያንዳንዱ መፈረካከስ የራሱ የሆነ ገላጭ ባሕርያት አሉት። የተጨናገፉ መንግሥታት (failed states) ታሪክ አብዛኛው ጊዜ የሚቆራኘው ከተሰነጣጣቁ ኤሊቶች (Factionalized Elites) ጋር ብቻ ሳይሆን ወደ የራስ-ራስ ጎሳ ጎጆ የተበታተነ የሠራዊት ተፈረካካሽነት ጋርም ጭምር ነው።

እንደ ሶማሊያው ብሔራዊ ሠራዊት በ1991 የተደረገለትን ጥሪ ተቀብሎ ወደ የጎሳው እንደ ተበታተነው ሁሉ የእኛም ሠራዊት በ”ብሔረ፣ ብሔረሰቡና ህዝቡ” ተበታትኖ በጎሳው ኮሎኔል ሥር እንዳይሰለፍና ብሔራዊነቱና አንድ ወጥነቱ አፈር ድሜ እንዳይበላ ጥንቃቄ ማስፈለጉን ማስታወስ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። በኮሎኔል ፋራሕ አይዲድና ዓብዱላሂ ዩሱፍ እንደተሰለፉት ለጎሳ (ለብሔረሰብ) ሚሊሺያ እርሾ ይሆንና ያ በተራው ለዎርሎርዶቹ (ለጦር አበጋዞቹ) አመቺ መንገድ ይከፍትና ትርምሱ የታጠቁ የሚሊሺያዎች ፍጥጫ ሆኖ ቁጭ ይላል ነው አሳሳቢነቱም፣ ስጋቱም ፍራቻውም። ይህ ሁኔታ የማያሳስበው ሰው ካለ አጉል ደፋር እንጂ ጀግና ሊባል ከቶ አይችልም።

የሽግግር ቻርተሩም ወይም የሽግግር የመንገድ አመልካች ካርታ (Road Map) እስከ ምርጫ ያለው ሂደትና በዚህ ጊዜ ማን ምን ይሠራል ዓይነት የጊዜና የክንዋኔዎች ሠንጠረዥ እንደሚሆን ነው የሚገባኝ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሕገ መንግሥት የማርቀቁና የማጽደቁ ዓቢይና ወሳኝ ተግባር ይኖራል። በማን ይረቀቅ ማን ያጽድቀው ራሱን የቻለ ታሪክ ነው። ብሔራዊ መግባባትና ውይይት እስካሁን ያልነበረ ክንዋኔ ምዕራፍ ነው።

ኢትዮጵያ በለውጥ ዋዜማ ላይ ናት ይህ አያጠያይቅም። ወዴት እንደሚያመራም እርግጡን የሚናገርም ሆነ የሚያውቅ ግን ያለም አይመስልም። በርካታ ሲናሪዮችን ተመልክተናል። ያለፉት ሳምንታት እድገቶች ፈረንጆችንም አሳስቧል። አንዳንዶቻችንን ከማሳሰብም አልፎ ስጋት ላይ ጥሎናል። ምን ያስፈራችኋል ባዮችም አልጠፉም። በቅርቡ ለውጥ ፈላጊ ድርጅቶች በሚፈጣጠሙት መግባቢያ ሃሳቦች ሰለማዊ ሽግግሩን በጽኑ መሠረቶትች ላይ እንደሚገነቡት ሊያረጋግጡልን ይፈልጋሉ። የኃይል ሚዛኑን ከመሠረቱ አናግቶ ወያነ/ኢሓዴግን ወደ ክብ ጠረጴዛ ወይም ነጭ ባንዴራ አውልብልቦ እጅ እንዲሰጥ የሚያስገድዱ መልክቶች አንመለከትምና አንዝናናም። የሀገሪቷ እጣ ፋንታ በተመለከተ ማለቴ ነው። ዋናው ጥያቄ በአመጽ በኩል አድርጎ ሰላማዊ ሽግግር ማድረግ ይቻላልን? የሚለው ጥያቄ መልስ ይሻል። የኦሮሞና የአማራ ትብብር፣ ከመፈክር ባሻገር በተደላደሉ መሠረቶች ላይ መቆማቸውን ማረጋገጥ ይጠይቃል። ከእነሱ ውጭ ያሉት ወገኖች በክብ ጠረጴዛው ዙሪያ መኖራቸው ብቻ ሳይሆን በነዳፊነትም እንዳሉበት ማረጋገጡ የማይታለፍ ቅድመ ሁኔታ አድርገው እየተመለከቱት ነው። የነዚህ ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ሙስሊሞች ያነሱት የተሳትፎ ጥያቄ ልብ ማለት ሊያስፈልግ ነው። ስለ ኦሮሞና አማራ ሚና ወሳኝነት ሲወሳም በደቡቡ ክፍላችን 16 ሚሊዮን ህዝባችን ብቻ ሳይሆን በጠረፎች ያሉት አፋሮች፣ ሶማሌዎቹ፣ ጋምቤላዎቹ፣ ቤንሻንጉሎችና ሐረሬዎችን በተባለው ክብ ጠረጴዛ ዙሪያ መኖራቸውን ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ተግባር ነው። ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኔር “A genuine leader is not a searcher for consensus but a molder of consensus.” - Martin Luther King, Jr እውነተኛው መሪ መግባባት የሚሻ ወይም ፈላጊ ብቻ ሳይሆን ራሱ መግባባትን ሠሪና ነዳፊ ነው ” ብሏል። እንደዚህ ዓይነት መሪም ያስፈልገናል። አሳባሳቢ የሆነ። ያሉንንም እንጠቀምባቸው። የሚሰበሰበው ደግሞ በአሰባሳቢ ያንድ ሀገር ዜግነትና ልጅነት መሆኑን ላንድ አፍታም መዘንጋት የለብንም። ይህንን መግባባት በሰላማዊ ሽግግርም ሆነ በሀገሪቷ እጣ ፋንታ ጊዜ፣ ጥረት፣ መነጋገር፣ ደጋግሙ አሁን መነጋገርን የግድ ይላል። ተሳታፊዎቹ በሽግግሩ ተግባራት ውስጥ በነዚህ ጉዳዮች የሚነጋገሩበት በቂና አመቺ ጊዜ ያስፈልጋል። የየመን 10 ወራት ብሔራዊ ዲያሎግ (ውይይት?) አድርጎ ዛሬ የዚያ ውይይት ውጤቶች እንደ አንድ መመለሻ ማጣቃሻ ተደርገው ተቀምጠዋል። በጎረቤት ሱዳን ምንም እንኳን በመንግሥት አመራር ሥር መሆኑ ባይካድም ውይይቱ እስከ ዛሬ ቀጣይ ነው። በሶሪያ፣ በሲሬ ላንካና በኮሎምቢያ እንዲሁ። ብሔራዊ ውይይትና መግባባት (National Dialogue and Consensus) ሥር ጎግል ቢደረግ የበርካታ ሀገራት የውዝግብ አፈታት ጥረቶችንና ሂደቶችን ያስጎበኘናል።

7. ዋናዎቹ የሽግግሩ ጋሬጣዎችና ተግዳሮቶች

1. በ 1983 ከሰሜን እየገሰገሰ የመንግሥት ወታደራዊ ኃይልን፣ ከተሞችንና የአካባቢ ህዝብን በቁጥጥሩ ስር እያዋለ ወደ 4 ኪሎ የሚገሰገስ የታጠቀና የተደራጀ ክንዱ የፈረጠመ ወታደራዊ ኃይልን የመሰለ ተመሳሳይ ሃይል ዛሬ በአድማሱም አይታየንም። ሀገሪቷ ከቁጥጥር ውጭ (Ungovernable) ማድርግ መቻል በራሱ ብቻ govern አድራጊ ወይም መንግሥት የነበረውን መተካት መቻልን አያመለክትም። ይህንን ማድረግ የሚችል የተደራጀ አማራጭ ኃይል መኖሩን ለኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ወለል ብሎ በመሬት መታየት ሊኖርበት ነው። ይህም ተገቢ ግንዛቤ የሚያስፈልገው የሽግግር ቅደመ ሁኔታ ነው። 25 ዓመታት በተሰበከው የክልልና ተፎካካሪ የማንነት የኢህአዴግ አወቃቀር ሥርዓት የተበጀለት ፉክክር (Organized Rivalry) አለመተማመኑና በጎሪጥ መተያየቱ ጣራ በነካበት ዘመን ሁሉ በብሔረሰቡ ተደራጅቶ የራሱን ወገን በመተሓራ ፋንታለ (ፋንቲ-ዓለ) ከአዲስ አበባ 230 ኪሎ ሚትር ላይ የሚገኙት አፋሮችን እንዴት፣ እንዴት በጠረፍ ያሉት ማለት ትደፍራላችሁ ብዬ ሽንጤን ገትሬ ከወዳጆቼ ጋር መከራከርዬን እንዳልዘናጋሁ ለማስታወስ ብቻ ነው። ጥቅም ለማስከበር አልፎ ተርፎ የራሱን ህዝብ ሕይወት ብቻ ለመታደግ የራሱን አቅም ግንባታ (Capacity Building) በምር ታያይዟል አሊያም አጠናቋል። ለተፎካከሪ ፍልሚያ ተዘጋጅቷል ማለት ይቀላል።

2. ልክ “ብሔራዊ” ሠራዊትን ወደ ወገን ካምብ ማስኮብለሉ እንደተጧጧፈው ለወገን አቅም ግንባታ ሁሉ የራሴ የሚላቸውን የተማረ ኃይል፣ የሃብት ሪሶርስ ለራሱ አቅም ግንባታ (Capacity Building) መሻማቱ ላይ የተጠመደ ይመስላል። ይህ በአማራ ምሳሌ ጎልቶ የምንመለከተው ከሕብረ ብሔራዊ አደረጃጀትና የነጻነት ትግል ኃይል የመሻማማቱ በጊዜ አስፈላጊው መተማመን በመፍጠር መግታት ካልተቻል ራሱ የቻለ አሳሳቢ ጋሬጣና ተጨማሪ ተግዳሮት ይደቅናል።

3. የሰሞኑን የመጀመሪያ በሥልጣን ያለው መንግሥት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ፀረ መንግሥት ግልበጣ አካሄዷል የሚሉ አሉ። የመንግሥት ግልበጣ እንዳይሞከርበት የዘየደው ፀረ ግልበጣ ክትባት መሆኑ ነው። የተወሰነ እውነተኛነት አያጣውም።

4. ዋናው ተግዳሮቱ ወያኔ/ኢህአዴግ መንግሥትን ማስወገዱ ወይም ወደ ክብ ጠረጴዛ ውይይት ማስገደዱ በኋላ የሽግግር መሠረቶች ላይ ተስማምቶ እስከ አዲሱ ምርጫ ድረስ ያለው ሂደት፣ ተግባራትና አስፈጻሚ አካላት ላይ የጋራ ስምምነት መደረሱ በቦታው አሉ ብሎ የሚገምታቸውና በታሳቢነት ከሚያስቀምጣቸው ቅደመ ሁኔታዎች አንዱም ይኸው ነው።

5. የወያኔ/ኢህአዴግ ኮኮብ እያዘቀዘቀ ከመጣ ወደ ኢትዮጵያ የራሷን ሠራዊት ማሰማራት የምትችለው ኤርትራ ብቻ ስትሆን ውጤቱ ምን መሆን እንደሚችል መተንባይ አይቻልም። ወያኔ ካርዶችን ከሥር መሠረቱ ለመበወዝ አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮልናል ብሎ ወደ አሥመራ ፊቱን ሊያዞር ይችላል፣ ያለ የሌለ ኃይሉን አንቀሳቅሶ። ሱዳን በአሁኑ አቋሟ ከቀጠለች የግብጽ ጣልቃ ገብነት ወያኔ/ኢህአዴግን ሊያስፈራራው አይችልም። በሶማሊያና በሌሎች ሀገሮች በሰላም አስከባሪነት የተሰማራውን ሠራዊት በመመለስ የሚከተለውን ትርምስ ለማመልከት ይሞክራሉ። አሁን ከሶማሊያ በተሳበው ሠራዊት ቦታ በመተካት አልሸባብ አፎጎይን (45 ኪሎ ሚትር ከሞቃዲሾ) መቆጣጠር መቻሉ ዓይነት መልዕክቶች ማስተላለፍ ይቻላል።

6. በዓረቡ ዓለም ትርምስምሱ ሰፍኖ ግብጽ ጨብጣው የነበረችው የዓረቡ ዓለም መሪነት እነ ሳዑዲያ ዓረቢያ ዘይት አማራጭ ገልፍ ሀገራት ትከሻ ላይ መውደቁ ሌላው አዲስ በግምት የሚወሰድ ታሳቢ ነው። እነሱም ከግብፅ ጋር እየተራራቁ ነው እንጂ እየተቀራረቡ በመሄድ ላይ አይደሉም።

7. የውጩ ጣልቃ ገብነት ሲታሰብ እነዚህና የመሳሰሉትን አወሳሳቢ አካባቢያዊና ዓለማቀፋዊ ኩነቶችን ግምት መውሰድ ይኖርበታል። ገለልተኛ አደራዳሪዎች በመሆን በጎ ተጽእኖ በማሳደር ሁሉንም ወደ ክብ ጠረጴዛና አግባቢ ስምምነት እንደደረሰ ለውጥና ሰለማዊ ሽግግር በማዋለድ ኢትዮጵያውያን መረዳት ሚና መጫወት የሚችሉት እኛ አሁን የምናደርጋቸው መቀራረቦች ወደ አንድ ብሔራዊ ማግባቢያ ስምምነት ወይም ስምምነት- መሰል ደረጃ ላይ ሲናደርሰው ነው። ስምምነት መደረሱ በቦታው አሉ ብሎ የሚገምታቸውና በታሳቢነት ከሚያስቀምጣቸው ቅደመ ሁኔታዎች አንዱም ይኸው ነው።

8. በአካባቢያችን ሁለት አዳዲስ መንግሥታት (ኤርትራና ደቡብ ሱዳን)፣ ሁለት ውላቸው የጠፋ መንግስታት (ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን) የባህር በር አልባ ሀገር፣ የተለያዩ ሀገራት የጦር ኃይል ካምፖቻቸውን በገነቡባት ጂቡቲ ሰፈሯል፣ የእነሱ ምላሽ (reaction) በውል አይታወቅም። በተለይም የቻይናና የሩሲያ ምላሽ። ቻይና ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር እስካሁን ሠራዊት አሰማርታ አታውቅም። ያ ማለት አታደርገውም ማለት እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል። ከሩሲያ ቢሪክስ ሀገሮች (ቻይና፣ ሕንድ፣ ብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካ) ጋር አዲሱ የዓለም አቀፍ ሥርዓትን በመቅረጽ ድርሻዋን እየተወጣች ነው። የአዲሱን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ግብግቦች ከሶሪያ በገልፍ ሀገራትና በየመን በኩል አድርገው ቀይ ባሕርን ተሻግረው ወደ ደጅፋችን እየተጠጉ ይገኛሉ። እነዚህ ኩነቶች የአካባቢያችንን የኃይል አሰላለፍን በሱኒ-ሺዓ ውዝግብና የዓረቦችና ዓረብ ያልሆኑት ከኢራንና ከቱርክ ጋር ያቆራኘዋል።

9. የወያኔ /ኢህአዴግ ኮኮብ እያዘቀዘቀ ከመጣ ልክ ቱርክ የኢራቅን መንግሥት ሳታስፈቅድ በሞስል ከተማ ከአይሲስ ነጻ ማውጣት ዘመቻ ላይ ካላታሳተፍኩ እንደምትለው ወደ ኢትዮጵያ የራሷን ሠራዊት ማሰማራት የምትችለው ኤርትራ ብቻ ስትሆን ውጤቱ ግን ምን መሆን እንደሚችል ከወዲሁ መተንባይ ያዳግታል። ወያኔ ካርዶችን ከሥር መሠረቱ ለመበወዝ አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮልናል ብሎ ወደ አሥመራ ፊቱን ሊያዞር ይችላል። ያለ የሌለ ኃይሉን አንቀሳቅሶ። ሱዳን በአሁኑ አቋሟ ከቀጠለች የግብጽ ጣልቃ ገብነት ወያኔ/ኢህአዴግን ሊያስፈራራው አይችልም። በሶማሊያና በሌሎች ሀገሮች በሰላም አስከባሪነት የተሰማራውን ሠራዊት በመመለስ የሚከተለውን ትርምስ ለማመልከት ይሞክራሉ። አሁን ከሶማሊያ በተሳበው ሠራዊት ቦታ በመተካት አልሸባብ አፎጎይን (45 ኪሎ ሚትር ከሞቃዲሾ) መቆጣጠር መቻሉ ዓይነት መልዕክቶች ማስተላለፍ ይቻላል።

10. በዓረቡ ዓለም ትርምስምሱ ሰፍኖ ግብጽ ጨብጣው የነበረችው የዓረቡ ዓለም መሪነት እነ ሳዑዲያ ዓረቢያ ዘይት አማራጭ ገልፍ ሀገራት ትከሻ ላይ መውደቁ ሌላው አዲስ በግምት የሚወሰድ ታሳቢ ነው። እነሱም ከግብፅ ጋር እየተራራቁ ነው እንጂ እየተቀራረቡ በመሄድ ላይ አይደሉም።

11. የውጩ ጣልቃ ገብነት ሲታሰብ እነዚህና የመሳሰሉትን አወሳሳቢ አካባቢያዊና ዓለማቀፋዊ ኩነቶችን ግምት መውሰድ ይኖርበታል።

8. ማጠቃለያ

አሁን ከየአቅጣጫው በሚቀርቡት መፍትሔ ሃሳቦችና ጥናቶች የምርምር ውጤቶች ላይ ብዙ ወይይት ማድረግ ያስፈልጋል። በብሔራዊ ደረጃ መግባባትና ስምምነት የተደረሰባቸው ጽንሰ ሃሳቦች ለስኬት የበቁት ለበርካታ ወራት አንዳንዴም ለዓመታት የሕብረተሰቡ ወሳኝ ኃይሎችና የፖለቲካ ድርጅቶች ያለ መታከት የተሳተፉበት በርካታ ውይይትና ክርክር ተደርጎባቸው እንደሆነ ሊታወቅ የሚገባ ነው። እነዚህ የውይይት ውጤቶች ለሕገ መንግሥት አርቃቂ ምክር ቤት ወይም ኮሚሽን ይቀርቡና እንደገና ውይይት ያደረግባቸዋል። በቀጣይም ለሕገ መንግሥታዊ አንቀጾች መንደርደሪያና መነሻ ይሆኑና የመጨረሻ ይሁንታ እንዲያገኙ ለውሳኔ-ህዝብ ቀርቦ ሲጸድቅ ሀገሪቷ የምትደዳርበት ሕገ መንግሥት ፍጥጥም መልክ ተላብሶ ሕገ መንግሥት ይሆናሉ።

ያን ጊዜ ሕገ መንግሥት ያንድ ሥልጣን የጨበጠ ኃይል ፕሮግራም ወደ ሕገ መንግሥት ተለወጠ ሳይሆን በማንኛውም መለኪያ ትክክለኛ የአጸዳደቅ ሥነ ሥርዓት ተከትሎ የጸደቀ ሕገ መንግሥት ወይም ሥርዎ ሕግ ሆነ ማለት ነው። ይህ ረጂም ሂደት ነው። ነገር ግን ከዚህ በፊት የተቀረጹት ሕግጋተ መንግሥት የይድረስ ይድረስ (quick fix) ቅጽ ከመሆን ያድናል። ንጉሡ ለሚወዱት ህዝባቸው የሰጡት ወይም አንድ አሸናፊ ቡድን ራሱ አንደሚመቸውና እንደሚፈልገው ያበጃጀውን የራሱን ፕሮግራም ሕገ መንግሥት አድርጎ ያጸደቀበት አብነት እንዳይደገም ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ይህ እንዳይሆን ደግሞ ተገቢ ትኩረትና በቂ ጊዜ፣ ያላሰለሰ የጋራ ጥረትም፣ መግባባትም ከሁሉም ወገን ይጠይቃል። እነዚህ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚቀርቡ ሃሳቦች ለብሔራዊ ውይይትም ሆነ መግባባት መሠረት ሆነው ማገልገል ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ። አለባቸውም።

የህዝባዊ ትግሉ ማስፈጸሚያው ህዝባዊ አመጽ ሆኖ መዳራሻው ወደ ሆነው ሰላማዊ ሽግግር ዘንድ ያሸጋግረናል ወይ? በሌላ አባባል ህዝባዊ አመጽ ሰለማዊ ሽግግርን ያዋልዳል ወይ? የሚለውን ፍራቻና ጥያቄ እንዲያምጽና ከሠራዊቱ ኮብልሎ ከነትጥቁ ህዝባዊ አመጽን እንዲቀላቀል ጥሪ የሚደርግለት ሠራዊት አባላት ወደ የብሔረሰባቸው ድርጅትም ሆነ የጦር አበጋዝ ዘንድ በመሄድ የጎሳ ሚሊሺያ እርሾ ሆነው ሊያገለግሉ አይችሉም ወይ? ብዬ ነው ደጋግሜ የጠየቅኩት። ይህ ታስቦበታል እንደሚባልም አልሳትኩም። 25 ዓመታት “የብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝቦች” የተደራጀ ፉክክርና የምንመለከታቸው በፊናቸው የተያያዙት “የአቅም ግንባታው” ትክክለኛው መነጣጠሪያ ዒላማው በውል እስከ አልታወቀ ድረስ ስጋቴን ያጣናክረው እንደሆነ ነው እንጂ አያለዝበውም።

በማጠቃለያ የአፋር ዘማቾች የጦር ውጊያ ዝግጅታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በባሕሉ ከውጊያ ስምሪት በፊት ከትንቢት ተናጋሪዎች የሚጠብቁት ትንቢት አለ። ነቢይቷ ሴት ከሆነች “ባዲቶ” ወንድ ከሆነ ደግሞ “ግኒሊ” ይባላሉ። የመጨረሻ ስንብት ከማድረጋቸው በፊት የመጪውን ውጊያ ትንቢት እንዲነገራቸው የሚለዋወጡት “ምን ይታይሻል” “ምን ይታይሃል? “ቅኔ ዘረፋ ብጤ ታሪክ ልመርቅላችሁ። “ባዲቶ” ወይም ትንቢት ተናጋሪዋ እንዲህ በማለት ትጀምራለች” አዎ፣ ይታየናል ረጅሙ ለግላጋው ባለ ሎቲው ሲደናቀፍ.፣ ትቀጥልና ራሰ በራው ዘመዱ ላይ ላይ ሲወድቅ ፣ ታዋቂው ጀግናው ዉሃ ውሃ ሲል…. እያለች ዘማቹ ጦር መስማት የማይፈልገውን የወገን ኪሳራና ሟርት- አዘል ትንበያ ስታበዛባቸው ” ዝም በይ፣ አንቺ ቀባዣሪ፣ ውሸታም” እያሉ ከቀኝ ከግራ ዘማቾቹ ሲወራርፏት “ዮኦ ዲራብለ ሲኒህ አበይ ይ ራቦው” በማለት አሳርጋ ትሸኛቸዋለች። አባባሏ ወደ ቀላሉ አማርኛ ሲመለስ “ፈጣሪ አምላኬ፣ እኔኑ ውሽታም ያድርግላችሁ” ብላ ነው የምትጸልይላቸው። እኔ ትንተናየን በዚህ ሟርት እያሳረግኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። ይታሰብበት! ነው መልእክቴ። የእጃችሁን አጣጥፋችሁ ተቀመጡ ጥሪም ግን በፍጹም አይደለም። የኃይል ሚዛን መለወጥ አለበት ብዬ የምደሰኩር ሰው ነኝ። እየተለዋወጠም ነው። እያየነው ነው። ስጋቴን ብቻ ያልደበቅኩበት በቂ ምክንያት አለኝ። ሥርዓትን ብቻ እንቀይራለን ብለው ተነሳስተው ባልጠበቁት ከፍተኛ አብዮት እንቅስቃሴ ትርምስምስ መሓል ሀገራቸውን ጭምር ያጡ ወገኖች (ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ኢራቅ) እንደ መማማሪያና ልብ መግዣ እየተመለከትን ነው። ይህንን እያዬን ለምንስ አንፈራም! ። መማሪያ አታሳጣን እንጂ እኛኑ ለሌሎች መማማሪያ አታድርገን በማለት የዘወትር ጸሎታችንን አሁንም እናደርሳለን። እናንተም አድርሱ!

ፀሐፊውን በዚህ email መድረስ ይቻላል። This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!