Ethiopian parliamentክንፉ አሰፋ

በቤተ ሙስና፣ የ"ጥልቅ ተሃድሶ"ው ድራማ ተጀምሯል! የእርስ በርስ እና ራስን በራስ መተካካት ቧልት እና ፌዝ።

ከመጋረጃው ጀርባ ስብሃት ነጋ፣ አቦይ ጸሃይ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ደብረጽዮን እና በረከት ስምኦን የሚቆምሩትን ካርታ፤ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደቬጋስ አጫዋች ፊት እያመጣ ይዘረጋዋል። በዲዮጋን ያደረጉት አብዮታዊ እና ልማታዊ "ምሁራን" ፍለጋ ውጤት ነበረው። "የዶክተር ያለህ" ፍለጋ ጥቂት ታማኝ አገልጋዮችና፣ በርካታ ሮቦቶችን አስገኝቷል። "በዲሞክራሲ" በተመረጠው "የሕዝብ ምክር ቤት" የሚኒስትሮቹ ስም ይፋ በሆነ ግዜ፤ ለይስሙላ እንኳን ተቃውሞ፣ አልያም ድምጸ-ተአቅቦ ቢያደርግበት ድራማውን ያሳምረው ነበር። በሙሉ ድምጽ ጸደቀ ተባለ። የነዚህ ሮቦቶች ምርጫ የፍልፍሉን ቀልድ ያስታውሳል።

የድሃው ልጅ ለሀብታሙ ልጅ፣ "ምን ያንጠባርርሃል? አንተም የምትበላው አንድ እንጀራ፣ እኔም የምበላው አንድ እንጀራ ..." ይለዋል።

የሀብታሙ ልጅ መለሰለት፣ "እንጀራውን ተወውና ስለ ወጡ እንነጋገር?"

ነገሩ ወዲህ ነው። ተጫዋቾች እና አጫዋቾች። መቼም ሹመኛው ሚኒስትር ነኝ ብሎ ደፍሮ ቢያወራም፣ ሚኒስትር ነኝ ብሎ ግን ደፍሮ ውሳኔ አይሰጥም። ውስጡን ያውቀዋል። ስለዚህ ስለ ተጫዋቾቹ ሳይሆን ስለ አጫዋቾች እንነጋገር። ስለ ሚኒስትሮቹ ሳይሆን ስለ ምክትሎቹ እናውራ። በቀላል አማርኛ "ዶክተሩ" ከላይ ይቀመጣል። ከስር ያለው ካድሬ እንደ እንዝርት ያዞረዋል። ላለፉት 25 ዓመታት ከዚህ የተለየ ነገር አልነበረም። ወደፊትም ከዚህ የተለየ አይሆንም። ጨዋታው እንደነበረ ይቀጥላል። የሳሞራ የኑስ የግል ንብረት የሆነው የመከላከያ ሚኒስቴርን ሲራጅ ፈጌሳ ይመራዋል ብሎ የሚያምን ካለ፤ ልጅ ወይንም ጅል መሆን አለበት። ለውጥ የሚመጣው ጌታቸው አሰፋ የደህነንቱን ስፍራ ለተቀናቃኝ አስረክቦ ቢሄድ ነበር። ወርቅነህ ገበየሁ ወ/ኪዳን የተሰጠውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነገር ወደ ኋላ ልመለስበት። ድራማውን ስንቃኘው አሁንም በ“ጥልቅ ተሃድሶ” ስም ቀልድ ነው የተያዘው። ይህቺ አገር ገና ከአሁኑ የባሰ አንባገነን፣ ሙስና፣ ስቃይ እና አፈና ይጠብቃታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንስ እያሳዘኑን መጡ። በእርግጠኝነት ለመናገር ማን እንደተሾመ እንኳን ለፓርላማው ከማንበባቸው በፊት አያውቁትም። በሙስና እና በወንጀል እጃቸው የተጨማለቁ ሰዎችን ጭምር ሹመት አደባባይ ወጥተው ሲናገሩ፤ በኩራት ሳይሆን በፍርሃት ነበር መሆን የነበረበት። እሳቸው ግን ትልቅ እና ግዙፍ ለውጥ ነው ብለው ተናገሩ። በዚህ "ጥልቅ ተሃድሶ" ሕዝባዊ አመጹ ይቆማል ብለውም ያምናሉ። በጥይት እና በጭስ ከ700 ሕዝብ በላይ ሲያልቅ የተኩስ ድምጽ አልነበረም ብሎ በዓለም አቀፍ ሚድያ ለሚናገር ምስኪን ጠቅላይ ሚኒስትር ማዘን እንጂ ማውገዝ አይገባም።

የሚኒስትሮቹን ምክር ቤት የእግር ኳስ ቲም አስመሰሉትኮ። የመብት ጥያቄ በመጣ ቁጥር የሚፐወዝ ቲም። ጥያቄው የሥርዓት ለውጥ እንጂ የሰዎች መገለባበጥ አይደለም። ካቢኔውን ሺህ ግዜ ቢፐውዙት፤ ለአገሪቱ ችግር መፍትሔ አይሆንም። የእግር ኳስ ቲምም ቢሆን እኮ ሲገነባ የእያንዳንዱ ተጫዋች ብቃት እና ሥነ ምግባር በባለ ሞያዎች ተገምግሞ ነው። እጃቸው በደም እና በሙስና የጠጨማለቁ ሰዎችን እያመጡ፤ የሕጻን አይነት ድብብቆሽ መጫወት ግዜ ለመግዛት ይረዳቸው ይሆን እንጂ፤ ሕዝባዊ ቁጣውን ሊያቆመው አይችልም። በዚያ ሰሞን በቴሌቭዥን ቀርበው መንግሥታችን ጥልቅ በሆነ ሙስና ተዘፍቋል ያሉን እነሱው ናቸው። ሙሰኞቹ አሁንም አሉ። በጥልቅ ሙስና የተዘፈቁ ሰዎች የችግር እንጂ የመፍትሔ አካል እንደማይሆኑ እያወቁ በሕዝብ ላይ ማፌዙ ለምን አስፈለገ? የሚደረገው ድራማ ለመግለጽ የአናንያ ሶሪን ቃል ልዋስ፣ "በዚህ ሁኔታ የሚመጣው በጥልቅ መታደስ ሳይሆን በጥልቅ መበስበስ ነው።"

"ጥልቅ ተሃድሶ" ሲሉን ቢያንስ አዲስ ምርጫ ያደርጋሉ ብለን ጠብቀን ነበር። እውነት ይቀየራሉ ብለን አምነን ተሳስተናል። እነሱ ግን ሕዝብን ሳይሆን ራሳቸውን ነው እይታለሉ ያሉት።

ከተሾሙት ሚኒስትሮች ውስጥ ሁለት ፕሮፌሠሮች፣ ሁለት ኢንጅነሮች እና አስራ አራት ዶክተሮች ይገኙበታል። ያልተገነዘቡት ከለውጥ ይልቅ የዶክተር መደርደር ሾተልን ወደ ሰገባ፣ ቁጣን ወደ ትእግስት እንደማይመልሰው ነው። የዶክትሬቱ ዲግሪም እኮ ከየት እንደመጣ ለሕዝብ የተደበቀ ነገር አይደለም። ግን የዶክተር ያለህ እየተባለ ከየስፍራው ሲለቀም፤ ጀነራል ባጫ ደበሌ ለምን ተረሳ? ምሁር የሚያሰኘው የዲግሪ ወረቀቱን ከሁሉም በፊት እሱ ገዝቷል። ጀነራል የሚለውን የፉገራ ማዕረግም ከፕሮፋይሉ ላይ አንስቶት ነበር። አባ ዱላ ገመዳስ ቢሆን ለአዲሱ ካቢኔ ምን ያንሰዋል? ሳይማር ዶ/ር አባ ዱላ እየተባለ አይደል የሚጠራው? ፕ/ር ቆስጠንጢኖስም ከሴንቸሪ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ገዝቷል። እሱስ ቢሾም ምን ይለዋል?

ከሆነ አይቀር ለምን ሁሉንም ሚኒስትሮች በባለ ዶክተር ማዕረጎች አልተኩትም ነበር? ለወረቀቱም ቢሆን ችግር የለም። የሲቪል ሰርቪስ ወፍጮ ዶክተሩን እና ፕሮፌሠሩን በገፍ እያመረተ ነው። ዘንድሮ ከአንዳንድ የርቀት ትምህርት ቤቶች በሳምንት ግዜ ፕሮፌሠር መሆን ይቻላል።

በሸገር የሚነገር አንድ ቀልድ አለ። ወያኔ ሥልጣን ሲይዝ መጀመርያ የወረረው ወታደራዊ ካምፖችን ነበር። መኮንኖችን ለመያዝ። ወያኔ ሲወድቅ ደግሞ ተቃዋሚው ኃይል መጀመርያ የሚወርረው ሲቪል ሰርቪስ "ኮሌጅ"ን ነው። እንደ ድንጋይ የሚያስቡትን እያመረተ ሕዝብን የሚፈጅ ተቋም!

መቼም ተቀለደ። ተቀልዶ ግን አይቀርም። መዳኛ ያልተገኘለት የህወሓት የፖለቲካ መፍትሔው የሕዝብ ድምጽ ነው። የሕዝብ ድምጽ ደግሞ በሦስት ቃላት ተገልጿል። ለውጥ!

"መተካካት" እያሉ ጆሮ ሲያደነቁሩ የነበረው ይኽንን ነበር እንዴ? ወርቅነህ ገበየሁ ወ/ኪዳን ከትራንስፖርት ሚኒስትር አንስቶ በወርቅነህ ገበየሁ ነገዮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መተካት? እርግጥ ነው ፈረንጆቹ በጥቂቱም ቢሆን ተሸውደዋል። አሶሺየትድ ፕሬስ ዜናውን ሲዘግብ፣ "The new ministers of foreign affairs - Workneh Gebeyehu, a former transport minister is Oromo, replacing the Tigrayans who previously held the posts." ኦሮሞው ወርቅነህ ገበየሁ ትግሬ ይዞት የነበረውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተክቶታል ብሎናል።

ምነው እነ ደብረጽዮን በወርቅነህ ኦሮሞነት አመረሩ? እኔ ያልገባኝ ወርቅነህ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት በሚፈቅደው ”ጉዲፈቻ” እና ”ሞጋሳ” ባህል መሰረት ወደ ኦሮሞነት ቀይረውታል እንዴ? ይህ ነገር ግልጽ ይሁን። ካልሆነ የሱን ማንነት የሚገልጸውን ዶክመንት እንልቀዋለን። ጥያቄው ሹመቱ ላይ አይደለም። ሲፈልጉ ጠ/ሚኒስትርም ያድርጉት። ግን በኦሮሞ ካርድ አስይዘው ማጫወታቸው ነው የሚደብረው። የህወሓት አባል ሆኖ ጨዋታውን በዚያው ካርድ ቢያደርገው ችግር የለውም። ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል የሚለውን የሂትለሩን ጎብልስ ብሂል የሙጥኝ ያሉም ይመስላል።

የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት መወገድ ያልተጠበቀ አልነበረም። ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች የድል አጥቢያውን ታጋይ፣ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን እንደማይወደዱት በስፋት ይነገር ነበር። ዶ/ሩ ፌስ ቡክ በብዛት ይጠቀማል። ሥራውን ብርሃነ ገብረክርስቶስ ስለሚያከናውንለት ለፌስ ቡክ በቂ ግዜ ነበረው። እታች ወርዶ ከተራው ዜጋ ጋር በማኅበራዊ ሚድያ መነጋገሩ ግን በህወሓት ዘንድ "ፖፑሊስት" የሚል ስያሜ አሰጥቶታል - ልክ እንደ አርከበ እቁባይ። በዘር መስፈርት ብቻ ከመንገድ ተወስዶ የተቀመጠ ሚኒስትር ነበር። "ይሰረዝ !" ብለው ከፈረዱበት ቆይቷል። ከዚያ በፊት ግን ሁነኛ ሰው መፈለግ ነበረባቸው። እነሆ አሮምኛ ተናጋሪ ትግሬ ተገኘ። የማኬያቬሊ ሊቅ!

በአሮጌ ጠርሙስ አዲስ ወይን ቢያቀርቡ አንድ ነገር ነው። በአዲስ ጠርሙስ አሮጌ ወይን ቢጨምሩ ደግሞ ሌላ የተለየ ነገር ሊመስል ይችላል። የነሱ ሙከራ ሁለቱም አይደለም። በአሮጌ ጠርሙስ አሮጌ ወይን ይዘው የተሃድሶ ዘፈን ይዘፍናሉ። በአስተሳሰብም በመልክም አንድ የሆኑ የድሮ አሻንጉሊቶችን እንደ እላቂ እቃ እያሽከረከሩ ያመጧዋቸውና ተሃደሶ ይሉናል። ችግሮችን መፍታት ሲሳናቸው ስህተትን እንደመፍትሔ ይወስዱታል። ሁለት ስህተት ደግሞ አንድ እውነት አይሆንም። አሸዋወዱንም አላወቁበትም። ዳሩ ሕዝብ ቀድሟቸው ሄዶ እንዴትስ ያታልሉታል?

አካሄዳቸው የሚነግረን ነገር አለ። እነዚህ ሰዎች አሁንም ለለውጥ ዝግጁ አይደሉም። ህወሓት ፈጽሞ አይታደስም!

ህወሓት በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ግድያ፣ ሙስና እና አፈና ከአገሪቱ አይጠፋም። "አደገኛ ፎርስ ናቸው ... ይጥፉ ወይንስ እንጥፋ!" ያለው ማን ነበር?

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር የምትወጣው ይህ ፋሽታዊ አገዛዝ ሲጠፋ ብቻ ነው!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!