ፍትሕ ይንገሥ (የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ሁኔታ ከሚያሳስባቸው ዜጎች አንዱ)

ከሁሉ በፊት አንባቢያን ሊገነዘቡት የሚገባው ጉዳይ ይህ ፅሁፍ ጥናት ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን ነው። መነሻው በዋነኛነት የግል ትዝብት ሲሆን ከሌሎች የኢህአዴግ ደጋፊዎችና ገለልተኛ ሊባሉ ከሚችሉ ወገኖች ጋር የተደረጉ ውይይቶችም ውጤት ጭምር ነው። ለማንኛውም ግን ፅሁፉ ላይ የተነሱትን ችግሮች በተመለከተ ኢህአዴግ እንደተለመደው የተከላካይ (defensive) መንፈስ ይዞ ባያያቸው ይመረጣል። ይልቁንም የተነሱት ችግሮች አሉ ወይስ የሉም ብሎ በቅንነት ቢያያቸውና ራሱን ቢፈትሽ ያጠናክሩታል እንጅ ለጉዳት አይዳርጉትም። ይህን ለማድረግ ደግሞ የግድ የሮኬት ሳይንስ ማጥናት አያስፈልግም።

ኢህአዴግ ማድረግ የሚገባው ወደሥልጣን ከመጣበት ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የሚነሱ ቅሬታዎችን በተጨባጭ ለማወቅ ገለልተኛ የሆነ የጥናት ኃይል በማቋቋም ነፃና ገለልተኛ የሆነ ጥናት እንዲካሄድ ማድረግ ነው። የዚህ የጥናት ቡድን ተልእኮ ሊሆን የሚገባው ህዝቡ ውስጥ ቅሬታ ያሳደሩ ዋና ዋና ችግሮችን ባጠቃላይና በተለይ ደግሞ ሚዛናዊ የሆነ የሥልጣንና የሃብት ክፍፍል መኖርና አለሞኖሩን ለይቶ ማውጣትና ለህዝብ ማሳወቅ እንዲሁም ኢህአዴግ ከጥናቱ ተነስቶ መሰረታዊ የሆነ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ማስቻል ይሆናል። እዚህ ላይ ጥናቱ ለምን ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ይሆናል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ጥያቄው አግባብ ያለው ቢሆንም መልሱ ደግሞ ግልፅና ግልፅ ነው። ከ1983 ዓ.ም. በፊት የነበሩት ስርአቶች ያማራውን ገዥ መደብና ተከታዮቹን ያላግባብ ሲጠቅሙ የነበሩ መሆኑ እሙን ነው። በዚህም ምክኒያት ደግሞ ህዝቡና ኢህአዴግ ታግለው ባመጡት ለውጥ በቀድሞ ስርአቶች ተፈጥሮ የነበረውን ኢ-ፍትሃዊነት የማስወገድና የማስተካከል ስራዎች እያከናወኑ የቆዩ መሆኑ ይታወቃል። ይህን የማስተካከል ስራ በማከናወን ሂደት ላይ ግን ብዛት ያላቸው የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ከሌሎች ዜጎች በላቀ መንገድ እየተጠቀሙ ያሉበት ሁኔታ ያለ ይመስላል። ለዚህም ነው ጥናቱ ከ1983 ጀምሮ መካሄድ ያለበት። ይህን ማድረግ ከተቻለ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ የተፈጠሩ ችግሮችን በተለይ ደግሞ የየትኛው ፓርቲ አባላት ወይም ህዝብ በፌደራል ደረጃ ሚዛናዊ ያልሆነ ድርሻ እንደያዙ ለማወቅ ያስችላል። የጥናቱ ውጤት ችግሮች እንዳሉ የሚያመላክት ከሆነ በቅንነት ተቀብሎ ለህዝብ መግለፅና ከህዝቡ ጋር ተባብሮ መፍትሔውን ማስቀመጥ ተገቢ ይሆናል። በሌላ በኩል የጥናቱ ውጤት ቁጥሩ ቀላል በማይባል ህዝብ እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎች መሰረት የሌላቸው መሆኑን የሚያሳይ ከሆነ ይህንኑ ለህዝቡ ገልፆ ችግሮች የተባሉት ለምን እየተነሱ እንዳሉና የተሳሳቱ መነሻዎቻቸውን ማስረዳትና ግንዛቤ መፍጠር ከህዝብ ጋ የበለጠ የሚያቀራርብ አሰራር ይሆናል። ለማንኛውም ላሁኑ ይህ ፅሁፍ የሚያጠነጥነው በኢህአዴግና በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ዙሪያ ሲሆን ተቃዋሚዎችን ህዝቡንና ለሎች አካላትን የተመለከቱ ጉዳዮችን ደግሞ ወደፊት በሚቀርቡ ፅሁፎች ለመዳሰስ ይሞከራል። በተረፈ መልካም ንባብ በመመኘት ማንኛውንም አይነት ተመሳሳይም ይሁን የተለየ ሀሳብ በማቅረብ በሰለጠነ መንገድ መወያየት በዴሞክራሲአዊ ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ የጎላ ሚና ሊኖረው እንደሚችል በመገንዘብ ሁሉም የየራሱን ድርሻ በሚችለው መንገድ ቢወጣ ሃገራዊ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል። በመጨረሻም በዚህ ፅሁፍ ውስጥ "ኢህአዴግ" ሲባል ድርጅቱን ብቻ ሳይሆን እንደየአግባቡ እርሱ የሚመራውን መንግሥትም የሚመለክት እንደሆነ አንባቢያን እንዲረዱት ያስፈልጋል።

ወደ ፅሁፉ ዋና ይዘት ሲገባ ረዘም ላሉ ዓመታት የፍትህ የእኩልነት የእኩል ተጠቃሚነት እንዲሁም የሌሎች መብቶች መከበር ፍላጎቶች ሲያንገበግባቸው የነበሩ ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች መተኪያ የማይገኝለት ህይወታቸውንና አካላቸውን ገብረው ኢህአዴግን ለሥልጣን ካበቁ ይሄው 26 ዓመታት ሊሞሉን ነው። በነዚህ 26 ዓመታት ውስጥ በጎ የሆኑም ያልሆኑም ተግባራት መፈፀማቸው ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። በበጎ ጎናቸው ሊታዩ የሚችሉ ተግባራትን ለማሳያነት ዋና ዋናዎቹን ከማንሳት በዘለለ እያንዳንዱን እየነቀሱ ማብራርያ ለመስጠት መሞከሩ ተገቢ አይሆንም። ምክንያቱ ደግሞ ህዝባዊ ነኝ የሚል መንግሥት ለሚመራው ህዝብ በጎ ተግባር ከመፈፀም ባለፈ ሌላ አላማም ይሁን ፍላጎት ሊኖረው አይገባምና ነው። ይህ ፅሁፍ ለማሳያነት የሚያነሳቸው በጎ ስራዎችም ይሁን ተግዳሮቶች በሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጠኑ ይሆናሉ። እነዚህም ከሕገ-መንግሥቱ፣ ከማንነትና ከልማት ጋር የተያያዙ ናችው።

የኢትጵጵያ ፌዴራላዊ ዴሞራሲያዊ ሕገ-መንግሥት ሲረቀቅና ሲፀድቅ ህዝባዊነት የተላበሰ እንዲሆን ብዙ ጥረቶች እንደተደረጉ አብዛኛው ህዝብ ይረዳል። ህዝቡ በስፋት ወጥቶ በረቂቁ ላይ እንዲወያይበት ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል። ይሁን እንጂ ባወያዮቹም ሆነ በህዝቡ የግንዛቤ እጥረት የተነሳ ውይይቱ የፈጠረው ግንዛቤ መሆን የሚገባውን ያህል የተሳካ ነበር ለማለት አያስደፍርም። በሌላ አነጋገር ሕገ-መንግሥቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ እንዲሁም የመንግሥትን ሥልጣን የሚገድብ ትልቅ መሳሪያ መሆኑን መላው ህዝብ በሚገባ ጠንቅቆ ግንዛቤ ፈጥሯል ለማለት የሚቻል አይሆንም። አይደለም መላ ህዝቡ ፊደል የቆጠረው የማኅበረሰብ ክፍልም ቢሆን የሕገ-መንግሥቱን ምንነት ተረድቶታል ለማለት አያስደፍርም። ለዚህም ነው አንዳንድ የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌዎች በበጎ ጎን የማያዩ አካላት ጥያቄ ባነሱ ቁጥር የተነሱት ችግሮች ሁሉ በዚያው በሕገ-መንግሥቱ መሰረት መፍትሔ ያገኛሉ የሚል ጠንካራ አቋም ከመያዝ ይልቅ የማይናቅ ቁጥር ያለው የማህበረሰብ ክፍል አብሮ ሲደናገር የሚታየው። ለዚህ ማሳያ የብሔር ብሔረሰብ መብቶችን በተለይም ደግሞ አንቀፅ 39ኝን ልብ ይሏል።

ማንነትን በተመለከተም ሕገ-መንግሥቱን መሰረት አድርገው የተሰሩ ወሳኝ ጉዳዮች አሉ። ከነዚህ ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ ቋንቋቸው ባህላቸውና ወጋቸው በወሳኝነት የተከበረ መሆኑና አጥጋቢ ባይሆንም በፌደራል መንግሥት ደረጃ ውክልና እንዲያያገኙ መደረጉ የሚጠቀሱ ናቸው። ይሁንና እንዚህ በጎ የሆኑ ማንነትን የማስከበር ስራዎች መሰራታቸው እንደተጠበቁ ሆነው በሌላ በኩል ደግሞ ለሀገራችን ዴሞክርሲያዊ አንድነት እጅግ በጣም ጠንቅ የሆኑ ሁኔታዎች መኖራቸው አልቀረም። እነዚህም ሁለት የሚፃረሩ ግን ደግሞ እርስ በርሳቸው የሚመጋገቡ አመለካከቶች ሲሆኑ እነርሱም ጠባብነትና ትምክህት ናቸው።

ጠባብነት በሌላ አነጋገር ሲገለፅ ራስ ውስጥ መደበቅ ማለት ነው። ይህም ማለት አንድ ብሔር፣ የቋንቋ የዘር፣ የባህልና ሌሎች ምክንያቶችን ለጥጦ በማሳየት ራሱን ከሌላው ነጥሎና ከልሎ ለመኖር እንዲያስችለው የሚያቀነቅነው አመለካከት ነው። ጠባብነት የተጠናወተው የሕብረተሰብ ክፍል በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊጎለብቱ የሚገባቸው የጋራ የሆኑ እሴቶች፣ ጥቅሞችና መብቶች ምኑም አይደሉም። እነዚህ የጋራ የሆኑ ያማስተሳሰሪያ ገመዶች ላልተው ቢፈቱ ለማጥበቅ የሚጨነቅ አካልም አይደለም። ይልቁንም ቶሎ የሚፈቱበትንና የሚበጠሱበትን መንገድ ነው ያሚያመቻቸው። ለጠባብነት ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል። የመጀመሪያው ያካባቢውን ሃብት ያለምንም ተቀናቃኝ ለመቆጣጠር የሚፈልግ ሀይል መኖሩ ሲሆን ይህ ሀይል ሥልጣንን ከማንም ጋር መጋራት የማይፈልግና ራሱ አዛዢ ናዛዢ ሆኖ ለመኖር የሚፈልግ ነው። ሁለተኛው ምክኒያት ደግሞ ከእውነተኛ ስጋት የሚነሳ ሲሆን ሌላው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ህዝብ የበላይነቱን ይጭንብኛል ከሚል አስተሳሰብ የሚመንጭ ነው። ይህ አስተሳሰብ ሰፊ መሰረት የሚኖረው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያንድ ብሔር፣ ብሔርሰብ ወይም ህዝብ የበላይነት ወይም አዝማሚያው ሲኖር ነው። በተለይም ደግሞ ባንድ ሀገር ውስጥ በታሪክ አጋጣሚ ይህ አይነት ሁኔታ ተከስቶ ከነበረ የጠባብነት አመለካከትን እጂግ በጣም ያጎላዋል። ይህን አመለካከት በኢትዮጵያ ሁኔታ ለመረዳት የግድ የትምክህት አመለካከትን ማንሳት ተገቢ ይሆናል።

ትምክህት በመሰረቱ የሚያጠነጥነው ከኔ በላይ ላሳር በሚለው አስተሳሰብ ዙሪያ ነው። በዚህም ምክኒያት የትምክህት አመለካከት የተጠናወተው አካል የኔ ዘር፣ ቋንቋ ባህል፣ ወግ ልምድ፣ ብቃትና የመሳሰሉት መስፈርቶች ከሁሉም የላቁ ናቸው ብሎ ያምናል። ይህ ብቻ ግን አይደለም። ከዚህ አልፎም የኔ የማንነት መገለጫ አስተሳሰብ፣ ልምድና ብቃት በሌላው ማህበረሰብ ላይ መጫን አለባቸው ብሎ ያምናል። ይህን ለማስፈፀም ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ተቋማትን ለርሱ በሚመቸው መንገድ ያቋቁማል፣ ይገነባል እንዲሁም ይጠቀምባቸዋል። በኢኮኖሚው ረገድም ቢሆን ሁሉንም ዋና ዋና ተቋማት ይቆጣጠራል ወይም ደግሞ ለመቆጣጠር ይሞክራል። ፍትሃዊ የሥልጣን ክፍፍልም እንዲኖር አይፈልግም። ይልቁንም ሁሉንም የሥልጣን ርከኖች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ለመቆጣጠር የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። እኔ ከሌለሁ አገር ትጠፋለች የሚል ጭፍን አመለካከትንም ያራምዳል። ይህን የትምክህት አመለካከት በኢትዮጵያ በሁለት መንገድ ከፍሎ ማየት ይቻላል።

አንደኛው በታሪክ አጋጣሚ በሀገራችን ኢትዮጵያ ከአማራው ብሔር የወጣው ገዢ መደብ ቋንቋውን፣ ባህሉን፣ ወጉን፣ ልምዱንና የመሳሰሉትን ሁኔታዎች በሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላይ ያለፍላጎታቸው ጭኖባቸው ቆይቷል። በዚህ ረገድ ምንም እንኳን ድሃው የአማራ ህዝብ የተጠቀመው ነገር ባይኖርም በስሙ ስለተነገደበት ብቻ በሌሎች ብሔር፣ ብሔርሰቦችና ህዝቦች በጥርጣሬ ሲታይ ቆይቷል። አሁንም ቢሆን ይህ ጥርጣሬ ሙሉ በሙሉ አልተፋቀም። በተለይም ደግሞ አሁንም ይህንኑ የትምክህት አመለካከት የሚያራምዱ የተወሰኑ ህይሎች በመኖራቸው አማራው እንደገና የበላይነቱን ሊጭንብን ነው በሚል የበለጠ የመጥበብ ሁኔታ የሚታይባቸው ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖራቸው አይካድም። ይህ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት ጠንቅ መሆኑ አልቀረም።

ሁለተኛው ደግሞ አዲስ እያቆጠቆጠ የሚመስለው ከህወሓት ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ህወሓት ከመጀመርያው ሲቋቋም የብሔር ነፃ አውጭ ድርጅት ሆኖ ነው። ይህም ማለት ህወሓት ገና ከውልደቱ የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያ ነፃ አወጣለሁ ብሎ የተቋቋመ ድርጅት ነበር። ከዚህ አንፃር ሰፋ ያለ ቁጥር ያላቸው አባላቱ በፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ውስጥ በሁሉም ካልሆነም ደግሞ ባብዛኛው ቦታዎች እጃቸውን ማስገባት እስከጀመሩበት ወቅት ድረስ ሊገለፅበት የሚችለው የጠባብነት አመለካከት ነበር። እነዚህ አባላት ከጊዚያት በኋላ ሁሉም ነገር በቁጥጥራቸው የገባ መስሎ ሲሰማቸው በህወሓት ውስጥ የትምክህት አመለካከት እያቆጥቆጠና እያደገ ያለበት አጋጣሚ የተፈጠረ ይመስላል። ለዚህም ነው ዋና ዋና የሚባሉ ተቋማት በህወሓት የበላይ አመራር እየተንቀሳቀሱ ያሉት። ለምሳሌ ያህል ብንጠቅስ መከላከያ ሰራዊቱ ህወሓት በፈለገው መንገድ ሊዘውረው እንዲችል ሆኖ የተዋቀረው። በግልፅና በቅንነት እንነጋገር ከተባለ መከላከያ ተቋማት ውስጥ በማእረግ፣ በኀላፊነትና ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን በመያዝ ወደር የሌላቸው የህወሓት ሰዎች ናቸው። ይህ ኃይል በትንሹ እንኳን ሲታይ የሰራዊቱን ግንባታ ፅሁፍ ሲያዘጋጅ ፅሁፉ የአማርኛን ሥርዓት እንዲከተል የተጨነቀ አይመስልም። መቼም የእርማት/የአርትዖት (editorial) ስራ መስራት የሚችል አማርኛ ተናጋሪ የሰራዊት አባል ጠፍቶ አይደለም፤ ንቀትና እብሪት ካልሆነ በስተቀር። ፖሊስን (በተለይም ደግሞ ወንጀል ምርመራን፣ አሻራ ክፍልን፣ አድማ በታኝና ሌሎቹንም ክፍሎች) የተቆጣጠሩት የህወሓት አባላት ዎይም ደጋፊወቻቸው መሆናቸውን የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች አሉ። ደህንነት ጋ ስንመጣም የተለየ ነገር አናይም። ከአመራር ጀምሮ እስከተራው አባል ድረስ እየተቆጣጠሩትና እየመሩት ያሉት እነዚሁ የህወሓት ሰዎች ናቸው። ጉምሩክ፣ አየር መንገድ፣ የሲቪል ሰርቪስ መስርያ ቤቶች፣ የሚድያ ተቋማትና የዲፕሎማቲክ መስኩ ውስጥም ቢሆን በቻሉት ሁሉ የነሱ ሰዎች ያንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ ጥረት አድርገዋል ተሳክቶላቸዋልም። በንግድ ረገድ እንኳን ከነሱ ጋ የተቆራኙ ተቋማትና ግለሰቦች ሳይቀር በኢኮኖሚው ውስጥ ያሻቸውን የሚያደርጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህ የህወሓት ሰዎች እምነት የጣሉት ከራሳቸው ዘር ውስጥ የወጣ ሰው ሲሆን በሌላው እትዮጵያዊ ዜጋ ላይ ከፍተኛ የሆነ የመጠራጠር ስሜት እንዳላቸው የሚያሳዩ በርካታ መገለጫዎች አሉ።

በሌላ አነጋገር ህወሓት ውስጥ እኛ ከሌለን የኛ የአመራር ጥበብ ተግባራዊ ካልሆነ፤ የኛ የትግል ተሞክሮ ተቀባይነት ካላገኘ ኢትዮጵያ እንደሀገር ልትቀጥል አትችልም የሚል አመለካከት እንዲሰርፅ የተቻላቸውን ሁሉ እየሰሩ የሚገኙ ዘመኑ የኛ ነው የሚሉ አባላቱና ተከታዮቻቸው ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደሉም። ከዚህ አልፎም ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የኛ መኖር ከሁሉም በላይ የላቀ ሚና አለው እያሉን ይገኛሉ። ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባለው ከ1983 ዓ.ም. በፊት የአማራው ገዥ መደብና ተከታዮቹ የኢትዮጵያ አንድነት ጠበቃዎች፣ ባላና ምሰሶዎች እኛ ነን ይሉ እንደነበረው ሁሉ አሁን ደግሞ የህወሓት ሰዎችና ተከታዮቻቸው ራሳቸውን የኢትዮጵያ አንድነት፣ ባላ፣ ማገርና ምሰሶ አድርገው መቁጠር ጀምረዋል። ያሁኑ የኢትዮጵያ አብዮት ጠባቂዎች (vanguards) እኛ ነን እያሉ በተለያየ መንገድ ይገልፁታል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ብዙ መስዋእትነት ከተከፈለበት ትግል ተፃራሪ በሆነ መንገድ ራሳቸውን በማግዘፍ ሌሎቹን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንኳሰስ፣ መጠራጠርና መናቅ ይመስላል። ለዚህም ነው ህወሓት ውስጥ ትምክህት እያቆጠቆጠና ቀስ በቀስ እያደገ ነው ሊባል የሚችለው።

ልማትን በተመለከተ ኢህአዴግ የሥልጣን መንበሩን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ በተለይም ደግሞ ክ1997 ምርጫ ወዲህ በርካታና የሚደነቁ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በዚህ ረገድ የተለያዩ የልማት ፖሊሲዎችን ቀርፆ በመተግበር ኢትዮጵያ አይታው የማታቀውን እድገት ሲያስመዘግብ ቆይቷል። እድገቱ ዘርፈ ቢዙ ሲሆን በተለይም ደግሞ በግብርናው መስክ፣ በመሰረተ-ልማት፣ በሀይል አቅርቦትና አሁን አሁን ደግሞ በኢንዱስትሪው መስክ እየተመዘገበ ያለው እመርታ መካድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይሁን እንጂ ህዝቡ ከልማቱ እኩል ተጠቃሚ ሆኗል የሚል ማስረጃ ማቅረብ የሚቻል አይሆንም። ይልቁንም ከልማቱ ተጠቅመዋል ሊባሉ የሚችሉት በሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ተሰግስገው ያሉ ስነ-ምግባር የጎደላቸው ባለሥልጣናትና ለነሱ የቀረቡ ሰዎች ናቸው። በተለይም ከህወሓት ጋር ባንድ ወይም በሌላ መንገድ ግንኙነት ያላቸው በርካታ ባለሥልጣናትና በዙሪያቸው ያሉ አጋሮቻቸው፣ ወዳጆቻቸው፣ ዘመዶቻቸው፣ ጓደኞቻቸውና የጥቅም ተጋሪወቻቸው ያላግባብ እየተጠቀሙ እንደሆነ ለማሳየት የግድ ድንጋይ መፈንቀል አያስፈልግም። በያካባቢው ያላቸውን ግንባታዎች፣ ቪላ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ ተሽከርካሪዎችና የመሳሰሉትን በግልፅ ማየት ይቻላል። እነዚህ ሰዎች የህወሓት ባለሥልጣን አባል ወይም ደጋፊ መሆንን እንደ ፓስፖርት ይጠቀሙበታል። የፈለጉትን ለማግኘትም ሆነ ጉዳይ ለማስፈፀም ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ይሆንላቸዋል። ይህ የሆነው በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው። አንደኛው ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ብዙ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ቁልፍ ቁልፍ ቦታወቺን እንዲይዙ የተደረገ በመሆኑ እርስ በርሳቸው እንዲጠቃቀሙ በር ከፍቶላቸዋል። ሁለተኛው ምክኒያት ደግሞ ጥቂት የማይባሉ በብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን ውስጥ ያሉ አመራሮችም ይሁኑ አባላት ደረጃው ቢለያይም ለህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ያደሩ በመሆናቸው ነው። የነዚህ ሦስት ድርጅቶች ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው አባላትና ደጋፊዎች ለህወሓት አባላትና ደጋፊወቻቸው የተለየ እይታ ማድረግ "መንግሥተ ሰማያት" የሚያስገባ መስሎ እስኪሰማቸው የደረሱ ይመስላል።

በተጨማሪም ኢህአዴግ ውስጥ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮና እጅ ለኢጅ ተያይዞ ይደግ የሚል ቁርጠኛና ቅን የሆነ አመለካከትና ተግባር ያለ አይመስልም። ይህን ለማስረዳት አንድ አብይ ምሳሌ ማንሳት ተገቢ ይሆናል። እንደሚታወቀው ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በጦርነት የተገኘን ገንዘብና ንብረት መነሻ በማድረግ የልማት ድርጅቶችን (endowments) በየክልላቸው አቋቁመዋል። እነዚህ ክልላዊ ድርጅቶች ህጋዊ መሆን አለመሆናቸውን ወደ ጎን ትተን የሚጠቅሙት አነሰም አደገም የየተቋቋሙበትን ክልል ነው። በዚህ ረገድም ቢሆን ዋና ተጠቃሚ የሆኑት ሃይሎች ህወሓት ከሚመራው ህዝብ የወጡና ለርሱ የቀረቡ ሰዎች ብቻ ናቸው። ምክኒያቱም በትጥቅ ትግሉ ወቅት በዚህ መንገድ ብዙ ገንዘብና ንብረት ያፈራ ድርጅት ቢኖር ህወሓት ነው። ይህ ደግሞ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚፃረር መንገድ ነው።

ከላይ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ነጥቦች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አሁን ያለው ሁኔታ ከቀጠለ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል። ምናልባት አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የፀጥታ አስከባሪ ተቋማት ጥንካሬ በማየት ችግሩ የጎላ አይሆንም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይችላል። ይሁን እንጅ ባለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለው ተሞክሮ ይህንን አያሳይም። የተፈለገውን ያህል ጠንካራ የፀጥታ አስከባሪ ሀይል ቢኖርም ህዝቡ እንደህዝብ ከተነሳ መመለስ የሚቻል አይሆንም። ምክኒያቱ ደግሞ በያንዳንዱ ጎጥ መንደር ቀበሌና ወረዳ የፀጥታ አስከባሪ ማቆም ስለማይቻል ነው። ይህን ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት የግድ 100 ሚሊዮን የፀጥታ አስከባሪ ያስፈልገዋል። ይህ ደግሞ ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብም የሚችል አይደለም። እነዚህን ሁኔታዎች በመውሰድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ባስቸኳይ መፍታት ለህዝብ፣ ለሀገርና ለራሱ ለኢህአዴግም ቢሆን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። የችግሮቹ አፈታት መንገዶች ደግሞ ለይስሙላ የሚከናወኑና ህዝቡ በጣም ያልበላው ላይ የሚያክኩ ሳይሆኑ ልባዊና የህዝቡን ስሜት በሚገባ የተረዱ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

በርግጥ አሁን ላይ ሆነን ስናየው ችግሮቹን ለመፍታት ኢህአዴግ የዳመነበት ይመስላል። ይሁን እንጂ መሽቶበታል ብሎ መደምደም አይቻልም። አሁንም ቢሆን ሁኔታዎችን የማስተካከል እድሉ አለው። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ኢህአዴግ ውስጥ ብልጣብልጥነትን ያስወገደና ቅንነት የተሞላበት የፖለቲካ ሂደት እጅግ በጣም አስፈላጊ የመሆኑ ጉዳይ ላይ ፅኑ የሆነ እምነት መፍጠርና ይህንም እምነት ተግባር ላይ ማዋል ሲቻል ብቻ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችም ሆኑ አመራሮቻቸው እንዲሁም አባሎቻቸው ከየድርጅት አጥሮቻቸው አልፈው እጅግ በፀና ኢትዮጵያዊነት መንፈስ መፍትሔው ላይ ሊረባረቡ መቻል ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

ከመፍትሔዎቹ የመጀመሪያውና ቁልፉ ጉዳይ ኢህአዴግና የሚመራው መንግሥት ሕገ-መንግሥቱን ማክበር የሚገባቸው መሆኑ ነው። ሕገ-መንግሥቱ አነሰም በዛ ህዝብ የተወያየበት ሲሆን፤ አንድ ሕገ-መንግሥት ሊያሟላ የሚገባቸውን ድንጋጌዎች በመሰረታዊነት ያካተተ ነው ሊባል ይችላል። ሌላው ይቅርና ህዝቡ ሕገ-መንግሥቱን አልፈልገውም ቢል እንኳ እንዴት ሊያሻሽለውና ሊቀይረው እንደሚችል ራሱ ሕገ-መንግሥቱ ግልጽ የሆኑ አካሄዶችን አስቀምጧል። ከዚህ በመነሳት ይህ ሕገ-መንግሥት መከበሩ አሁን እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች ሁሉ መሰረታዊ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል ብሎ ደፍሮ ለመናገር አስቸጋሪ አይሆንም። ይህ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንደሚከተለው ለማብራራት ይሞከራል።

አንደኛውና መሰረታዊ የሆነው ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሕገ-መንግሥቱ መሰረት እኩል ሊታዩ የሚገባ መሆኑ ነው። ይህም ማለት የትኛውም የማህበረሰብ ክፍል ባለው/በነበረው አስተዋፆ፣ ባካበተው ልምድ፣ በትግል ቆይታና በመሳሰሉት ምክንያቶች የተለየ ጥቅምም ይሁን እይታ ሊቸረው አይገባም ማለት ነው። ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ያካባቢያቸው ሁኔታ በፈቀደ መጠን አፋኙን የደርግ ሥርዓት በመጣል የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል፡: ደርግን ባብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚደግፈው ቢሆን ኖሮ ከተወሰነ የኢትዮጵያ ክፍል መሳሪያ ስለተነሳ ብቻ ሊወድቅ የሚችል ኃይል አልነበረም። የደርግ መውደቁ ትልቁ ምስጢር ይከተለው የነበረው ሥርዓት ፍትሃዊ ስላልነበረና አብዛኛው የኢትዮያ ህዝብ አንድም ፊት ለፊት ስለታገለው፤ ሌላም ድጋፍ ስለነፈገው ነበር። ከዚህ አንፃር ህወሓት የከፈለው መስዋእትነት ከሎሎች ጋር ሲነፃፀር የላቀ ቢሆንም ደርግ የውደቀው ኢህአዴግ በተለይም ደግሞ የህወሓት ታጋዮች ካለም የተለየ ጀግንነት ስለነበራቸው አልነበረም። ይልቁንም የደርግ ውድቀት መነሻው የራሱ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ሥርዓት መንሰራፋቱ ነበር። ስለዚህ አንድ ብሔር ብሔረሰብ ወይም ህዝብ በምንም ምክኒያት የተለየ እይታ ሊቸረው አይገባም። በሌላ በኩል በዚህ ፅሁፍ መጀመሪያ አከባቢ እንደተገለፀው ንፁሃን ወገኖቻችን መተኪያ የማይገኝለትን ህይወታቸውንና አካላቸውን የገበሩት አንድን ገዥ መደብ ከሥልጣን አውርደው ሌላውን ለመጫን አልነበረም። ይህን ለማድረግ መሞከር ቅርቶ ማሰብ እንኳን አጥፊና የተሳሳተ ታሪክን መድገም ብቻ ሳይሆን፤ ውድ መስዋእትነት በከፈሉ ጀግኖች ህይወት ላይም የእቃ እቃ ጨዋታ የመጫወት ያህል ነው።

ከላይ ከተጠቀሰው መፍትሔ ባልተናነሰ መልኩ ሊታይ የሚገባው ደግሞ በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የመከበር ጉዳይ ነው። እነዚህ መብቶች መንግሥት ሲፈልግ የሚቸራቸው ሳይፈልግ ደግሞ የሚነሳቸው ሊሆኑ አይገባም። ሁሉም ዜጎች ከብዙ በጥቂቱ በማንነታቸው ሊከበሩ፣ በህይወት የመኖር መብታቸው ከህግ አግባብ ውጭ ላይጣስ፣ የመንቀሳቀስ፣ በነፃ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ ተቃውሞን በሰላማዊ መንገድ የመግለፅ፣ የመምረጥ፣ የመመረጥና የመሳሰሉት መብቶች መከበር እንዲችሉ ህዝቡ አሻራውን ባስቀመጠበት ሕገ-መንግሥት የተደነገጉ ናቸው። ይሁንና ኢህአዴግ እነዚህን መብቶች ሲሻው በግልፅ ወይም በስውር፤ ካልሆነም ደግሞ ፍትሃዊነት የጎደለው "ህጋዊ" መንገድን በመከተል ሲሸራርፋቸው ቆይቷል። እንደምሳሌ ለመጥቀስ ያህል በነፃ የመምረጥ፣ መመረጥ፣ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና ከአካል ጥቃት ነፃ የመሆን መብቶችን እናንሳ።

የመምረጥ መበት በሕገ-መንግሥቱ ለያንዳንዱ ዜጋ የተሰጠ መብቱ ብቻ ሳይሆን፤ ብቸኛ ሥልጣኑም፣ ኃይሉም ነው። የመመረጥ መብትም እንዲሁ። እነዚህ መብቶች ፍትሃዊ በሆነ የህግ አግባብ ካልሆነ በስተቀር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊከበሩ የሚገባቸው የግልም፣ የቡድንም መብቶች ናቸው። ኢህአዴግ እነዚህን መብቶች ቢያከብርና እንዲከበሩ ቢያደርግ ጥቅሙ ለባለመብቶቹ ብቻ ሳይሆን ለራሱም ጭምር ነው። አንደኛ እነዚህን መብቶች ማክበሩ በህዝቡ ዘንድ አመኔታ እንዲያገኝ ይረዳዋል። ሁለተኛ ባንድ ምርጫ ተመረጠም አልተመረጠ አባላቱ በማንኛውም ጊዜ ያለስጋት አገራቸው ውስጥ እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። እነዚህን ዋና ዋና ፍሬ ነገሮች መሰረት በማድረግ ኢህአዴግ ከመምረጥና መመረጥ ጋር በተያያዘ ሊያስተካክላቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ።

የመጀመሪያውና ትልቁ ነገር ምርጫ ቦርድ ነፃና ገለልተኛ ተቋም መሆን እንደሚገባው በኢህአዴግ በኩል በፀና ሊታመንበት ይገባል። በዚህም መሰረት የምርጫ ቦርድ አባላት ሆነው የሚመረጡ ሰዎች ኢህአዴግን ጨምሮ ለማንም የፖለቲካ ድርጅት ወገንተኛ ያልሆኑ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት። በተግባር ግን ይሄ ሲሆን አይታይም። ሁሉም ወይም ባብዛኛው የምርጫ ቦርድ አባላት የኢህአዴግ አባላት ወይም ጠንካራ ደጋፊዎች እንደሆኑ የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አሉ።

በሁለተኛ ደረጃ ምርጫ ቦርድ ከማንም ጣልቃ ገብነት ነፃ መሆኑ መረጋገጥ አለበት። ይሁን እንጅ ኢህአዴግ በደጋፊዎቹ አማካኝነት ጣልቃ መግባቱን ያቆመ አይመስልም። በሌላም በኩል በነበሩት የምርጫ ሂደቶች ሁሉ ኢህአዴግ ትንንሽ በሚመስሉ ግን ደግሞ የምርጫ ሂደቱን ሊያዛቡ የሚችሉ አላስፈላጊ ተግባራት ውስጥ ሲዘፈቅም ይታያል። ለምሳሌ የህዝብ ታዛቢዎች የሚባሉትን ሳይቀር የራሱ አባላት ወይም ደጋፊ የሆኑትን ለማድረግ የሚችለውን ሁሉ ይጥራል። ይህ አይነት አካሄድ ደግሞ ለሃገሪቱ የሚፈይደው አንዳችም ነገር አይኖርም። ይልቁንም እየተደጋገመ በሄደ ቁጥር ህዝቡ በኢህአዴግ ላይ ያለው አመኔታ የበለጠ እየተሸረሸረ እንዲሄድ ያደርጋል። ስለዚህ ኢህአዴግ ስህተቶቹን አርሞ ወደፊት የሚካሄዱ ምርጫዎች ሁሉ እኩል በሆነ የመጫወቻ ሜዳ ላይ እንዲካሄዱ ማድረግ ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ኢህአዴግ ከልቡ ማመን ያለበት ትልቁ ቁም ነገር፤ ዜጎች በነፃ የመምረጥና የመመረጥ እድሉን አግኝተው በምርጫው ሂደት ቢሳተፉና አንፈልግህም ቢሉት እንኳን ትልቅ ድል እንደተጎናፀፈ መቁጠር ያለበት መሆኑን ነው። ይህ አይነት አሰራር እንዲሰፍን ነው እነኛ ውድ ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ የኢትዮጲያ የቁርጥ ቀን ልጆች ጥለውት ያለፉት አደራ። ምነው ታዲያ ኢህአዴግ ይህን አደራ ረሳው? ስግብግብነት ወይስ አላዋቂነት? መልሱን ለራሱ ለኢህአዴግ መተው ይመረጣል።

ለማንኛውም ግን ቢያንስ ቢያንስ በ1997 ዓ.ም. የነበረው የምርጫ ሂደት አይነት አሰራር አገሪቱ ውስጥ በሚካሄዱ ምርጫዎች ላይ ተግባራዊ ቢደረግ ብዙ ችግሮችን መቅረፍ በተቻለ ነበር። በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ኢህአዴግ ስልጡንነቱን ያሳየበትና ዴሞክራሲውን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ተግባራትን የፈፀመበት ሂደት ነበር። ይሁን እንጅ ይህ ስልጡንነትና ዴሞክራሲአዊነት ሩቅ አልተጓዘም። የምርጫውን ውጤት መነሻ በማድረግ ሁሉም ነገር ወደነበረበት እንዲመለስ ተደረገ። ይህ እንዲሆን ደግሞ ብዙ የኢህአዴግ አመራሮችና አባላት አሉታዊ ሚና እንደነበራቸው የሚያጠራጥር አልነበረም። እነዚህ አመራሮችና አባላት በወቅቱ ያዩትና የፈሩት ሥልጣን ለመልቀቅ የመጨረሻው ጫፍ ላይ መድረሳቸውን ነበር። ከዚህ በመነሳት የመረጡት መንገድ ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ሰፍኖ አገሪቱ በፅኑ መሰረት ላይ እንድትገነባና እንድትጓዝ ሳይሆን፤ እንደለመዱት ማንኛውንም አይነት መንገድ ተከትለው ገደብ የሌለው ሥልጣን ላይ ተጣብቆ መቆየትን ነው። ይህ ምርጫቸው ነው ከሌሎች ችግሮች ጋር ተደማምሮ በተለያዩ ጊዚያትና ቦታዎች ለሀገር ሰላም፣ እድገት ብሎም ዴሞክራሲያዊ አንድነት ከፍተኛ አደጋ ሊሆኑ የሚችሉ ቀውሶች እያስከተለ ያለው።

የመደራጀት መብትን በተመለከተ ሕገ-መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ ራሱ ነፃና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይገልፃል። ይህ ግን ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ እንጅ ተግባር ላይ ሲውል አይታይም። ማንኛውም የሙያም ይሁን ሌላ የማህበረሰብ አደረጃጀት ሲታሰብ የኢህአዴግ የመጀመሪያ ተግባር የሚሆነው እኔ እንዴት አድርጌ ልዘውረው እችላለሁ የሚለው ነው። ለዚህም ይረዳው ዘንድ አባላቱን አደራጅቶ የሚፈጠሩትን አደረጃጀቶች እሱ በሚፈልጋቸው ሰዎች እንዲመሩ ያደርጋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ማህበራቱን እሱ ወደፈለገው አቅጣጫ እንዲያሽከረክራቸው የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጥርለታል። እነዚህ ማህበራት ነፃና ገለልተኛ መሆናቸው ቀርቶ ጭራሹን የኢህአዴግ አካልና አምሳል ሆነው ያርፉታል። ኢህአዴግ ይህን ከሚያደርግ ይልቅ ማህበራቱ በነፃና በፍላጎት ተደራጅተው አመራሮቻቸውን መርጠው የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ቢፈጠር ይጠቅመዋል እንጅ አይጎዳውም። በሌላ አነጋገር ማህበራቱ በተደራጀ መንገድና ያለምንም ስጋት ስህተቶችን ነቅሰው በማውጣት ለኢህአዴግ ሊያሳውቁት የሚችሉበት ሁኔታ ስላለ ጥንካሬን ይፈጥርለታል። በሁለተኛ ደረጃም ህዝብ በኢህአዴግ ላይ አመኔታ እንዲያሳድር አይነተኛ መሳሪያዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም በመሆኑ በማህበራት አደረጃጀት ዙሪያ ጣልቃ የሚገቡ ባለሥልጣናት ህገ-ወጦችና የፖለቲካ ሙሰኞች ስለሆኑ ኢህአዴግ ሊያስቆማቸው ይገባል።

በሰላማዊ ሰልፍ ዙሪያም ቢሆን ኢህአዴግ ቁርጠኛ የሆነ አቋም ሊወስድ ይገባል። ባንድ በኩል ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ መብት ነው ሲል ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል። በሌላ በኩል ደግሞ የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ሲቀርብ የተለያዩ ምክኒያቶችን በመደርደር እንዲታፈኑ ያደርጋል። ይህ አካሄድ በፍጥነት መታረም ይኖርበታል። ዜጎች ሀሳባቸውንና ብሶታቸውን ባደባባይ እንዲገልፁ ማድረግ ኢህአዴግን ይጠቅመዋል እንጅ አይጎዳውም። በአንድ በኩል ከዜጎች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ሰምቶ ጊዜ ሳይወስዱ የመፍታት እድል ይሰጠዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ ብሶቱን ባደባባይ በመግለፁ የሚሰማው ርካታ ስለሚኖር በኢህአዴግ ላይ አመኔታን ያሳድራል። እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ኢህአዴግ ሰላማዊ ሰልፎችን አፍኘ የአገዛዝ ዘመኔን አራዝማለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ሁኔታውን በግልባጩ የተረዳው ይመስላል። ይልቁንም ኢህአዴግ በእጅጉ ሊያጤነው የሚገባው የታፈነ ነገር ሁሉ መተንፈሻ ካጣ ግድቡንና አጥሩን ጥሶ ሊወጣ እንደሚችል ነው። በዚህ መንገድ የገነፈለ ህዝብ ደግሞ ልመልስህ ቢሉት የሚመች አይሆንም። በነገራችን ላይ ኢህአዴግ በዚህ ረገድ የፖሊሲ ችግር የለበትም። ይህም ማለት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ በፖሊሲ ደረጃ ይፈቀዳል። ችግሩን የሚፈጥሩት ሥልጣናቸውን የሙጥኝ ያሉ ህዝቡን አፍነን ጥቅማችንን እናሳድዳለን ብለው የሚያስቡ በርካታ ስግብግብ የኢህአዴግ ሹመኞች ናቸው። እነዚህ ሹመኞች ህዝቡ ሀሳቡን በነፃ ገልፆ ተጠያቂነት ከመጣም ኀላፊነቱን እንወስዳለን የሚል የጠነከረ እምነት ስለሌላቸው አፈናን ይመርጣሉ። በነዚህ ሹመኞች ምክኒያት የሚፈጠር ችግር ደግሞ ጦሱ የሚተርፈው ለነሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ንፁሃን የሕብረተሰብ ክፍሎችም ይሆናል። ስለዚህ ኢህአዴግ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ሰላማዊ ሰልፍ የሚከለክሉ ወይም የሚያደናቅፉ ሹመኞች የፖለቲቻ ሙስና እየፈፀሙ ያሉ በመሆናቸው ሊያንጓልላቸውና ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይገባል።

የአካል ደህንነት መብትን በተመለከተም ኢህአዴግ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይገባዋል። በመጀመርያ ደረጃ ኢህአዴግ ለአባላቱም ሆነ በመንግሥትነቱ ለሚመራቸው የፀጥታ አስከባሪ ተቋማት እመርታዊ ለውጥ በሚያመጣ መንገድ ሰው ክቡር መሆኑን ሊያስረዳና ሊያስገነዝብ ይገባል። ማንም የመንግሥት ሹመኛም ይሁን የፀጥታ አስከባሪ ሀይል ፍትሃዊ ባልሆነና ህግ ከሚፈቅደው ውጭ ምንም አይነት የአካል ጥቃት ማድረስ የማይፈቀድ መሆኑ በማያወላዳ መንገድ ሊገለፅለት ይገባል። ይህ የመንግሥት አካል በተለይም ደግሞ ፀጥታ አስከባሪው ከሰወች አያያዝ ጋ ያለውን አመለካከቱን፣ አቅሙንና ብቃቱን እንዲያሳድግና እንዲያጎለብት ቀጣይነት ያለው ስልጠናና ትምህርት እንዲሁም እገዛ ሊደረግለት የሚገባ መሆኑን ኢህአዴግ ከልቡ ማመንና መቀበል እንዲሁም ለተግባራዊነቱ ቆርጦ መነሳት ይኖርበታል። ይህን አልፎ የአካል ጥቃት አድርሶ በተገኘ ሀይል ላይ ደግሞ የማያዳግም ህጋዊ ርምጃ እንዲወሰድበት ኢህአዴግ ያላሰለሰ ጥረት ሊያደርግ ይገባዋል። ከህግ ተጠያቂነት ባሻገር የፖለቲካ ጉዳይም ስለሆነ ጥፋተኛው ብቃትና ችሎታ እንደሌለው ተቆጥሮ ከየክፍሉ የሚወገድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል። የሚወሰደው ርምጃም ችግሩን ባደረሰው ሰው ብቻ ታጥሮ መቅረትም የለበትም። ይልቁንም በየደረጃው ያሉ አመራሮች ለችግሩ መፈጠር የራሳቸው የሆነ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው ስለሚችል ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር መዘርጋት መቻል አለበት።

ሁለተኛው አብይ ጉዳይ ከፍትሃዊ የሥልጣን ክፍፍል ጋር ተያይዞ ሊወሰድ የሚገባው የመፍትሔ አቅጣጫ ነው። በዚህ ዙሪያ ብሔር፣ ብሔረ-ሰቦችና ህዝቦች በየክልሎቻቸውና አካባቢዎቻቸው ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር መጀመራቸው ትልቅ ርምጃ ነው። ይህ ብቻ ግን ዴሞክራሲአዊ አንድነትን ሊያጎለብት አይችልም። ከዚህም ባሻገር ሊወሰዱ የሚገባቸው ርምጃዎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ ዋናውና ትልቁ መፍትሔ በፌዴራል ደረጃ ፍትሃዊ የሆነ ሁሉንም ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያመጣጠነ የሥልጣን ክፍፍል መኖር እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑ ነው። ልምድ፣ ብቃትና ተሞክሮ እየተባለ አንዱን ፓርቲ ከሌላው ገዝፎ እንዲታይ ማድረግ ኢ-ፍትሃዊነት ብቻ ሳይሆን በምንም የሞራል መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ለዚህ ለዚህማ የቀድሞ ያማራ ገዥ መደቦችና ተከታዮቻቸው ሊወቀሱ አይገባም ነበር። ምክኒያቱም የአማራው ገዥ መደብና ተከታዮቹ እኮ በተለየ መንገድ በብዙ ቦታዎች ቅድሚያ የነበራቸው የተሻለ ያስተዳደር ብቃት ልምድና ተሞክሮ አላቸው በሚል ሽፋን ነበር። ይህ የሆነበት ምክኒያት ደግሞ ታስቦበትም ባይሆን ለትምህርትና ለሥልጣኔ ቅርበት ስለነበራቸው ነው። የትግሉ መነሻም ይህ አይነቱ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ሰርአት እንዲቀጥል ስላልተፈለገ ነበር። ታድያ አሁን ህወሓት የትግል ተሞክሮና ብቃት አለው በሚል ሂሳብ ብዛት ያላቸው አባላቱ በፌደራል መንግሥት ደረጃ ያሉ ተቋማትን እንዲመሩና እንዲሰገሰጉ መደረጉ ከምን የመጣ ነው? ለዚህ ነው አሁን ያለው የህወሓት ዝንባሌ ለትግሉ የተከፈለውን መስዋእትነት የረሳ የሚመስለው።

ከዚህ ስንነሳ ኢህአዴግ ማድረግ ያለበት ሁሉንም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ያመጣጠኑ ተቋማትን መገንባት ነው። በዚህ ረገድ በግንባር-ቀደምትነት የሚነሳው የፀጥታ ተቋሙ ነው። መከላከያውም ይሁን የፖሊስ ሀይሉ እንዲሁም የደህንነት ተቋሙ የህዝቡና የህዝቡ ነፀብራቅ ሊሆኑ ይገባል። ካመራር ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ባግባቡ ሁሉም ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተመጣጠነ ሀይል እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ብቃትና ልምድ እንዲሁም ተሞክሮ እንደሽፋን እየተወሰደ አንድ ብሔር ብቻ ገዝፎ የሚታይበት አካሄድ ዛሬ ነገ ሳይባል ባፋጣኝ መወገድ ይኖርበታል። ልምድና ብቃት የግድ ባገልግሎት ብቻ መለካት የለበትም። አጫጭርና ረጃጅም ስልጠናዎች በማዘጋጀት የሰውን ብቃት ማዳበር ይቻላል። ይህን በማድረግ ያብዛኛውን ህዝብ ልብ ማሸነፍ ቀልብንም መግዛትና በዚያውም ተቀባይነትን ማግኘት ይቻላል። ተሞክሮና ብቃት በሚል ሽፋን ያንድን ብሔር አባላት ከሌላው በተለየ መንገድ ጎልተው እንዲታዩ በማድረግ በሌሎቹ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ውስጥ ቅሬታን ከመፍጠር ይልቅ የወሰደውን ያህል ገንዘብና ጉልበት ወስዶ በስልጠናና በትምህርት ብቃትን በመገንባት የተመጣጠነ የሥልጣን ክፍፍል በማድረግ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ማጠናከር መተኪያ የሌለው የምፍትሄ አቅታጫ ነው።

ይህን በማድረግ ሂደት ሊተኮርበት የሚገባው አብይ ጉዳይ ግን አለ። ሁላችንም እንደምናቀው የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹና እህቶቹ ቀደም ብሎ ራሱን ከደርግ አገዛዝ ነፃ አውጥቷል። ይህ ማለት ደግሞ ህወሓት ሁሉንም የትግራይ ህዝብ ማግኘት ችሏል። ይህም በመሆኑ ትግራይ ውስጥ አለ ሊባል የሚችል የሰው ኃይል በተሟላ መንገድ በአባልነትና በደጋፊነት አሳትፏል። ሌሎቹ ድርጅቶች ግን ምንም እንኳን ደረጃው የተለያየ ቢሆንም ይህን እድል አላገኙም። የሰው ኃይላቸው ምንጭ በሁሉም የብቃት ደረጃ መመዘኛዎች ሲታይ በጣም ውሱን ነበር። ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ ህወሓት ገዝፎ እንዲወጣ የበኩሉን ድርሻ ተጫውቷል። ኢህአዴግ ደርግን ጥሎ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላም ቢሆን በህወሓትና በሌሎች የኢህዴአግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለውን የብቃትና የልምድ ልዩነት መሰረታዊ በሆነ መንገድ ማጥበብ አልቻለም። ምንም እንኳን በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከነበረው ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ የተሻለ ነገር የመጣ ቢሆንም ከህወሓት ውጭ ያሉ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ህዝቡ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ሊያገኙ ይገባቸው የነበረውን የሰው ሀይል ማግኘት ተስኗቸው ቆይቷል። የሰው ሀይል አፍርተናል ቢሉም እንኳን በጣም የተወሰነው ካልሆነ በስተቀር ባብዛኛው ለጥቅም ብሎ የተጠጋ እንጅ የየድርጅቶቹን አላማና የትግል ስልት ተርድቶ ለዚህም ህይወቱንም ሆነ ጥቅሙን አሳልፎ ሊሰጥ የሚችል ሀይል እንዳልሆነ የሚያሳዩ በርካታ መገለጫወች አሉ። በዚህ ረገድ በትንሹ እንኳን ሲታይ ያባልነት መዋጮን መክፈልና በድርጅት ስብሰባወች መገኘት ትልቅ ዳገት ሆኖ የሚሰማቸው አባላት ቁጥራቸው ቀላል ግምት የሚሰጠው አይመስልም።

ከአባላቱና ከደጋፊዎቹ ውጭ ያለው አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍልም ቢሆን ዳር ሆኖ ከመጠራጠርና ታዛቢ ከመሆን ያለፈ ሚና አልነበረውም፣ የለውምም። ይህ የሆነበት አብይ ምክኒያት ደግሞ ሆን ተብሎም ይሁን በቸልተኝነት በተፈጠሩ ሁኔታዎች ኢህአዴግ የሚመራውን ትግል የሚዘውረው ህወሓትና ህወሓት ብቻ ነው የሚል አመእለካከት ህዝቡ ውስጥ በስፋት በመስረፁ ነው። ይህ አመለካከት በህዝቡ ብቻ ሳይሆን ድርጅት ውስጥ ባሉ የማይናቅ ቁጥር ባላቸው አባላት የሚቀነቀን መሆኑ በተለያየ መንገድ ሲገለጽ ይሰማል።

በርግጥ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ታቅፈው የሚገኙ አመራሮችና አባላት በስፋት ፍትሃዊ፣ ቅንና፣ የህዝብ ውግንና ባጠቃላይም በኢህአዴግ በራሱ አባባል አቢዮታዊያን ቢሆኑና ኢህአዴግም ወደሃገራዊ ፓርቲነት ተቀይሮ ቢሆን ኖሮ አንድን ተቋም ከየትኛውም ዘር የመጡ ብቃት ያላቸው ሰወች ቢመሩትና ቢሰሩበት ለሃገር እድገት ከፍተኛ አስተዋፆኦ ያደርግ እንደሆን እንጅ የሚያስከትለው ጉዳት አይኖርም ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ያለውን የኢህአዴግ ሁኔታ ስናይ በውስጡ ያሉት አብኛዎቹ አመራርና አባላት የአብዮታዊነትን መስፈርት ሊያሟሉ ቀርቶ ባጠገቡም የሚያልፉ አይመስሉም። ይህ በሆነበት ሁኔታ ደግሞ አንድን ተቋም ካንድ ብሔር ብቻ የወጡ ስዎች በብዛትም ሆን በበላይነት የሚያሽከረክሩትና የሚተውኑበት ከሆነ ሃገሪቱ ውስጥ በስፋት ያለው የሙስና እና የዝምድና አሰራር በይበልጥ የሚጠቅመው የዚህኑ ብሔር ተወላጆች ሊሆን ግድ ነው። ይህ ደግሞ የሌሎቹን ብሔር፣ በሄረ-ሰቦችና ህዝቦች ተወላጆች በስፋትና በኩልነት ያማያሳትፍና የበይ ተመልካች የሚያደርግ በመሆኑ ሀገሪቱ ያንድ ብሔር እጅ ብቻ ረዘም ብሎ የሚታይበት መሆኗን አይቀሬ አድርጎታል። በዚህ ምክንያት የተጠቃሚው ብሔር ተወላጆች መንግሥት የኛ ነው እንዲሉና ሌሎቹ ደግሞ በጥርጣሬና በስጋት አይን እንዲያዩት እያደረገ ያለበት አጋጣሚ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።

ከዚህ በመነሳት መሰረታዊ የሆነ ፍትሃዊ የሥልጣን ክፍፍል ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ መሆን የለበትም። በዚህ ሂደት ሶስቱ የኢህአደግ አባል ድርጅቶች ማለትም ብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን እንዲሁም ኢህአደግ አጋር ብሎ የሚጠራቸው ድርጅቶች ብቃት ያለው የሰው ሀይል ማፍራት በከፍተኛ ደረጃ ይጠበቅባቸዋል። በአባልነት ወይም በደጋፊነት ያልታቀፈ ግን ደግሞ ብቃት ያለው ማንኛውም ዜጋ ኀላፊነት እንዲይዝ ማድረግም ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ይህ አሰራር ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ በብቃትና ልምድ ማነስ ምክኒያት የብሄራዊ ተዋጿቸው ያልተጠበቀላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የተመጣጠነ ውክልና የሚያገኙበት እድል ይፈጠራል። ይህ ሁኔታ ደግሞ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ባለው ሥርዓት ላይ ተነፃፃሪ እምነት እንዲያሳድር ይረዳል። ከዚህ አልፎም በህዝቦች መካከል ባጠቃላይና በተለይ ደግሞ በህወሓትና በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን የእርስ በእርስ መጠራጠር አዙሪት (vicious circle) ሊሰብረው ይችላል። ባጠቃላይ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ግንኙነቶች እየዳበሩና እየጠነከሩ እንዲሄዱ አብይ ሚና ይጫወታል።

ሦስተኛው ሊተኮርበት የሚገባው የመፍትሔ አካል ነፃ ተቋማትን የመገንባት ጉዳይ ነው። ነፃና ገለልተኛ ተቋማት መገንባት ሲባል ለሕገ-መንግሥቱና ለህዝቡ ብቻ ተገዥ የሆኑ ተቋማት ማለት ነው። ከነዚህ ተቋማት ውስጥ ይህ ፅሁፍ ዋና ዋና በሚባሉት ሶስቱ ላይ ያተኩራል። እነዚህም የመከላከያ ተቋሙ፣ የዳኝነት አካሉና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ናቸው። እነዚህ ተቋማት ተልኳቸውን በሚገባ ሊወጡ ከሆነ ከማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሊሆኑ ይገባል።

መከላከያውን ወስደን ዋና ተግባራቱ ሀገርን ከውጭ ወራሪ የመከላከልና የብሄራዊ ደህንነትን የሚያሰጋ የፀጥታ መደፍረስ ሲከሰት የሚያረጋጋ ተቋም መሆኑ ነው። ከዚህ ባሻገር ሄዶ ላንድ ፓርቲ ውግንና የሚያሳይበት አሰራርም ሆነ ፍላጎት ሊኖረው አይገባም። ያንድ ፓርቲ የፖለቲካ ራእይ ማስፈፀሚያ ተቋም መሆንም የለበትም። የመከላከያ ተቋሙ በምርጫ ሥልጣን የያዘውን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምንም አይነት ቅድመ-ሁኔታ ሳያስቀምጥ በእኩል አይን ሊያያቸው ይገባል። በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኢህአዴግ ጋር ያለውን ግልፅም ይሁን ስውር ቁርኝት ሊበጥሰው ይገባል። ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ሥልጣን የያዘው ፓርቲ ማንም ይሁን ማን ሀገራችን ውስጥ ሰላምና መረጋጋት የማይናወጥ መሰረት እንዲኖረው ማድረግ ነው። ለዚህም ነው የሀገር መከላከያ ኃይሉ ከፖለቲካ ፓርቲ ጥቅም ይልቅ በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው። በጥቅሉ ሲታይ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኢህአዴግ በምርጫ ሥልጣን ቢለቅ አብሮ ሊለቅ እንደገና ሥልጣን ላይ ቢወጣ ደግሞ ሊመለስ የሚገባው ተቋም ሊሆን አይችልም። ይልቁንም ለሕገ-መንግሥቱና ለህዝቡ ተገዥ ሆኖ በቀጣይነት ሙያውን እያዳበረና ብቃቱን እያጎለበተ የሚቀጥል ሰራዊት እንዲሆን ያስፈልጋል። ስለዚህ ኢህአዴግ በሚቀጥለው ምርጫ ሥልጣን ቢለቅ አሁን ያለው የመከላከያ ሰራዊት እንዳለ የመቀጠሉ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። መቸም ቢሆን በምርጫ ወደሥልጣን የሚመጣ ፓርቲ ሁሉ በየኪሱ የመከላከያ ሰራዊትም ይዞ ይምጣ የሚል መከራከርያ ሊቀርብ አይችልም፡

በርግጥ አሁን ያለው የመከላከያ ሰራዊት እርሾ የኢህአዴግ አባላት የነበሩ መሆናቸው የሚካድ አይደለም። ከዚህ አንፃር ምንም እንኳን ኢህአዴግ በግልፅ ሁሉም የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከድርጅት አባልነታቸው የተሰናበቱ መሆናቸውን በወቅቱ ያወጀ ቢሆንም ውስጥ ለውስጥ ግን ግንኙነቱና ለኢህአዴግ ያለው ታማኝነት ተበጥሷል ማለት አይቻልም። ይህ ሁኔታ በጣም አደገኛና በህዝቡ ዘንድ አመኔታ የሚያሳጣ ተግባር ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ በህዝቡ ለመከበርና ለመታመን ከመከላከያ ጋር ያለውን የተለየ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ሊያቋርጠው ይገባል። ከዚህ አንፃር ኢህአዴግ ለይስሙላ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ትዝብትና ብሎም ጥላቻ እያስከተለበት እንደሆነ ባንክሮ ሊገነዘበው የግድ ይለዋል። አይናችሁን ጨፍኑና ላሙኛችሁ አይነት ነገር እንኳን በፖለቲካ ፓርቲና በህዝብ መካከል ይቅርና በግለሰቦች ደረጃ የሚፈጥረው ቁርሾና መቃቃር እጂግ በጣም ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ለነገሩ እንዳለመታደል ሆኖ እንጂ ያኔ ኢህአዴግ ደርግን አስወግዶ ሥልጣን በያዘበት ወቅት መከላከያ ሰራዊቱ እንደ አዲስ ገለልተኛ ሆኖ ቢዋቀር ኖሮ አሁን ለግጭትና አለመግባባት መነሻ አይሆንም ነበር።

የዳኝነት አካሉም ቢሆን ተገዥ መሆን ያለበት ለሕገ-መንግሥቱና ለህሊናው ብቻ ነው። ይህ አካል ህጉን ነፃና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ተግባር ላይ ማዋል ያለበት አካል ነው። በምንም መንገድ ቢሆን የፖለቲካ ፓርቲ አላማ ማስፈፀሚያ ሊሆን አይገባውም። በዚህ ረገድም ቢሆን ኢህአዴግ ብልጣብልጥነት የተሞላበት መንገድን መከተል ማቆም አለበት። የራሱ አባላት ወይም ደጋፊዎች የነበሩ ሰዎችን ከአባልነታቸው ለቀዋል በሚል ሽፋን በየደረጃው ባሉ የዳኝነት እርከኖች እንዲሰገሰጉ ማድረጉና እያደረገ ያለ መሆኑ ህዝቡ በትዝብት እንዲያየው አደረገ እንጅ ያተረፈለት ጥቅም ያለ አይመስልም። በሞሆኑም ኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት ዳኞችን በሚሾምበት ጊዜ ከፖለቲካ ፓርቲ ውግንና ነፃ የሆኑ፣ ለሕገ-መንግሥቱና ለህሊናቸው ብቻ ተገዥ የሆኑ እንዲሁም ብቃትና ልምድ ያካበቱ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተገቢም ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም መሆኑን ከልብ እንዲያምንበት የግድ ይለዋል።

ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ውስጥ ሲገባም ስራዎቹን ገለልተኛ በሆነ መንገድ ለመፈፀም የሚያስችለው ሁኔታ መፈጠር ያለበት መሆኑ የሚያጠራትር አይደለም። ለዚህ እንዲያመችም ከመነሻው ተጠሪነቱ ላስፈፃሚው አካል መሆኑ ቀርቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆን ይገባዋል። ለሁሉም ግልፅ እንደሚሆነው ሙስና በስፋት ሊፈፀም የሚችለው ባስፈፃሚው አካል ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ሙስናን በቁርጠኝነት ለመከላከል እንዲያስችለው የፀረ-ሙስና ኮሚሽኑ ካስፈፃሚው አካል ቁጥጥር ውጭ መሆን ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስናን መከላከል ቀርቶ ራሱም ሙስና ውስጥ ላለመግባቱ ዋስትና ማግኘት አይቻልም። በዚህ ረገድ ሌላው ሊነሳ የሚገባው አብይ ጉዳይ ሙስና ሲባል ከገንዘብ ከንብረት ያለአግባብ ከመጠቀም ከአድልኦና የመሳሰሉት ጋር የተገናኘው ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሙስናም እጂግ በጣም ትኩረት የሚሻ ችግር መሆኑን በግልፅ መተማመን ላይ መድረስ ያስፈልጋል። የፖለቲካ ሙስና ከገንዘብና ከንብረት ጋር ከተያያዘው ሙስና እጂግ የከፋ ቀውስ ሊያስከትል እንድሚችል ኢህአዴግ በሚገባ ሊያጤነው ይገባል። ለምሳሌ ሕገ-መንግሥቱንና እሱን መሰረት አድርገው የወጡ ህጎችን መጣስ የፖለቲካ ሙስና ሊሆን ይችላል። ሥልጣንን ተጠቅሞ ፍትሃዊ ያልሆኑ ህጎችን በማውጣት የተለያዩ ሚዲያዎችንና ህዝባዊ አደረጃጀቶችን እየተከታተሉ ለማፈንና ለማቀጨጭ መሞከርም የፖለቲካ ሙስና መፈፀም ሊሆን ይችላል። የነዚህና የመሳሰሉት ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ የኢህአዴግ አካሄዶችና ውጤታቸው ደግሞ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ማናጋት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የፖለቲካ ሙስና የሚፈፅም ማንኛውም አካል ተገቢውን ህጋዊ ቅጣት ሊያገኝ ይገባል። በርግጥ የኢትዮጵያ ፀረ-ሙስና ተቋም አሁን ባለበት አቋሙ የፖለቲካ ሙስናንም ጨምሮ ይስራ ማለት አቅሙን ያላግባብ ለጥጦ ምንም ስራ እንዳይሰራ ማድረግ ይሆናል። ተገቢ የሚሆነው በዚሁ ተቋም ስር አንድ ራሱን የቻለ ክፍል በማቋቋም የፖለቲካ ሙስናን እንዲዋጋ ማድረግ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ተቋሙን በሰው ሀይልም ይሁን በቁሳቁስ አቅሙን መገንባት የግድ ይላል።

ሌላው በዚህ ተቋም ውስጥ ሊሰራ የሚገባው አብይ ነገር የጋራ የሆኑ ጥቅሞችንና ፍላጎቶችን እንዲሁም ስነ-ምግባርን ለመገንባትና ለማዳበር የሚረዱ ሕገ-መንግሥታዊና ሞራላዊ ትምህርቶችን ለሕብረተሰቡ እንዲደርሱ ማድረግ ነው። ይህ ስራ አሁን እንዳለው ወጣ ገባ የሆነ አካሄድ ተሂዶ የትም አይደርስም። ስራው መከናወን ያለበት በተናጠልና ያዝ ለቀቅ በሚል ሁኔታ ሳይሆን፤ በተደራጀና ከሚመለከታቸው ሌሎች መንግሥታዊም ይሁን ማህበረሰባዊ ተቋማት ጋር በተቀናጀ መንገድ ሊሆን ይገባል። ይህ ሲሆን ቁሳዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሙስና መሸከም ያማይችል ማህበረሰብ መፍጠር ይቻላል።

አራታኛው መፍትሔ ከውስጣዊ የድንበር ማካለል ጋር ተያይዞ የሚነሳ የማንነት ጥያቄን እልባት ለመስጠት የተወሰደውንና እየተወሰደ ያለውን ውሳኔና ተግባር የተመለከተ ነው። ይህን በተመለከተ የሚነሳ ማንኛውም ጥያቄ መፈታት ያለበት ህዝብን ብቻ ማእከል ባደረገ መንገድ የሚሄድ አቅጣጫን በመከተል ነው። በሌላ አነጋገር በውስጣዊ የድንበር ማካለል ሂደት መታየት ያለበት ዋናው ቁምነ-ገር ህዝብ እንጂ የመሬት ማስፋፋት ፍላጎት መሆን የለበትም። በዚህ ረገድ ነባር የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች ግልፅነት በተሞላበት ሁኔታና ነፃ በሆነ መንገድ ህዝቡ ሊወስንባቸው ይገባል። ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ስለድንበር ጉዳይ የተለየ አቋም ሊይዝ ይችላል። ይሁን እንጅ ችግሩ መፈታት ያለበት ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና በተሰጠው የህዝቦች ውሳኔን በሚያረጋግጥ መልኩ መሆን አለበት። በዚህ ረገድ ሊነሳ የሚችለው አንድ አብይ ምሳሌ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል የነበረና ያለ የድንበር ውዝግብ ነው። በነዚህ ሁለት ክልሎች የነበሩት የድንበር ማካለል ጥያቄዎች የተፈቱት ህወሓት ከትጥቅ ትግል ጀምሮ የያዘውን አቋም መሰረት በማድረግ ይመስላል። በሌላ አነጋገር በነዚህ አካባቢዎች የተደረጉ የድንበር ማካለል ስራዎች ሲፈፀሙ በየአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ቅድመ-ኢህአዴግ ነዋሪዎች የተጠየቁበትና የወሰኑበት ሁኔታ አልነበረም። ይሄ ደግሞ በህወሓት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲቀነቀን የነበረ የግዛት መስፋፋት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። አሁንም ቢሆን ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ያለአግባብ የተሰራው ስራ እንደገና መከለስ ይኖርበታል። ይሄን ለማድረግ ደግሞ ቦታዎቹን ኢህአዴግ ከመቆጣጠሩ በፊት ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ድምፅ እንዲሰጡና እንዲወስኑ መደረግ ይኖርበታል። ህዝበ-ውሳኔው ቦታወቹን ኢህአዴግ ከተቆጣጠራቸው በኋላ የሰፈሩ የትግራይ ተወላጆችን (ይህ ከትግሉ የተቀነሱትን የቀድሞ ታጋዮችም ይማለከታል) ሊጨምር አይገባውም። ምክኒያቱም እነዚህ ዜጎች ከመነሻው በቦታዎቹ ላይ እንዲሰፍሩ የተደረገው ህወሓት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲያቀነቅነው የኖረው የግዛት መስፋፋት ህልም እውን እንዲሆን የተጠቀመበት ብልጣብልጥነት የተሞላበት መንገድ ስለሚመስል ነው። ህዝበ-ውሳኔው ቦታዎቹን ኢህአዴግ ከመቆጣጠሩ በፊት ይኖሩ በነበሩ ነዋሪዎች እንዲሆን የሚያስፈልገው ፍትሃዊ ባልነበሩትና ማንነትን በጨፈለቁት የድንበሮች ማካለል ሂደቶች የተጎዱ ህዝቦችን ፍትህ ለመስጠት እንጂ በየአከባቢው ማን መኖር አለበት የሚለውን ለመወሰን አይደለም። የመኖር መብትማ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ግልፅ ሆኖ ተቀምጧል። በዚህ ሕገ-መንግሥት መሰረት ማንም እትዮጵያዊ በመረጠው አከባቢ ሁሉ ተዘዋውሮ መኖርና መስራት ይችላል። ለማንኛውም ከላይ በተገለፀው መልኩ የተካሄዱ የድንበር ማካለሎች ተከልሰው ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በህዝብ ውሳኔ ካልተፈቱ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተተከሉ ፈንጂዎች ሆነው ጊዜያቸው ሲደርስ እየፈነዱ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ አንድነት አደጋ ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ ኢህአዴግ በአንክሮ ሊያጤነው ይገባል። በነገራችን ላይ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ብአዴን ሊመልሳቸው የሚገባው እጅግ በጣም ትልልቅ ጥያቄዎች አሉ። ከእነዚህም አንደኛ ድንበሮቹ ሲካለሉ የህወሓትን አስተሳሰብ እንደ ቱቦ ተቀብሎ ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ያካባቢው ህዝቦች እንዲወስኑ ምን ምን ርምጃዎችን ውስዷል የሚለው ሲሆን፤ በሁለትኛ ደረጃ ደግሞ ባሁኑ ሰዓት በተለይም ደግሞ በወልቅይት አካባቢ ያሉ አማራዎች ያነሱት ጥያቄ አግባብ ሆነም አልሆነም ብአዴን እንደ አማራ ድርጅትነቱ የኔነት ስሜት አድሮበት ጥያቄው ርግጠኛ የህዝብ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለማጣራትና ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ ሊያገኝ እንዲችል ያደረገው ጥረት ምንድነው የሚሉት ናቸው።

አምስተኛው ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የመፍትሔ አካል መሰረታዊ የሆኑ የሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎችን ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ማሳወቅ ነው። ይህ ጉዳይ በትምህርት ቤቶችና በፀረ-ሙስና ኮሚሽን በኩል መተግበር ያለበት ቢሆንም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም በጥልቀትና በቀጣይነት ሊሰሩት የሚገባ ነው። በዋናነት የሰብአዊ መብቶችና የእንባ ጠባቂ ተቋማት አብይ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። እነዚህ ተቋማት በተለይም በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የተፈፀሙ ግድፈቶችን ከማረምና ከማስተካከል በዘለለ ሁሉም ዜጋ መብቶቹንና ግዴታዎቹን እንዲያቅ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ስራው ደግሞ ያዝ ለቀቅ የሆነ የዘመቻ ስራ ሳይሆን ቀጣይ በሆነና ለሎች የሚመለከታቸውን አካላት በሚያካትት መንገድ መሰራት የሚገባው ነው።

ስድስተኛው የመፍትሔዎቹ አካል ሆኖ ሊወሰድ የሚችለው ደግሞ ኢህአዴግና የሚመራው መንግሥት ጆሯቸውን በደንብ በማፅዳት የመስማት ችሎታቸውን ማዳበር ያለባቸው መሆኑ ነው። የኢህአዴግ አንዱ ትልቁ በሽታው ጀሮዎቹ ራሱን ብቻ እንዲሰሙ የሚፈልግና ለዚሁ የተቃኙ መሆናቸው ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብን የሚመራ የፖለቲካ ፓርቲና መንግሥት ከዚሁ ህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ትችቶችን ለማድመጥ ያቆበቆበ መሆን አለበት። ኢህአዴግ ይህን ቢያደርግ በሁለት መንገድ ሊጠቀም ይችላል። አንደኛው ችግሮቹ ገዝፈው ሳይወጡና ስር ሳይሰዱ ከወዲሁ እንዲስተካከሉ ይረዳል። ሁለተኛው ደግሞ ህዝቡ መንግሥት ይሰማኛል፣ ለኔ ጥያቄዎችና ትችቶች ቦታ ይሰጣል በሚል ለኢህአዴግ ያለው ክብር ይጨምራል። ኢህአዴግ የመስማት ችሎታውን በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ሊያዳብር ይችላል።

የመጀመሪያው ረፖርት የሚያቀርብ ማንኛውም አካል በውነተኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ መሆን እንዳለበት ከታች ጀምሮ እስከላይኛው የሥልጣን መዋቅር ድረስ ጠንካራ ግንዛቤና የተጠያቂነት መንፈስ መፍጠር ያስፈልጋል። ይህን የረፖርቶች እውነታ ላይ የተመሰረቱ መሆን የሚከታተልና የሚቆጣጠር (counter-check) የሚያደርግ ኃይል ሊኖርም ይገባል። ይህ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት አልፎ አልፎ ግን ደግሞ ቀጣይ በሆኑ የመስክ ጉብኝቶችና የህዝብ ውይይቶች ሊከናወን ይችላል። እዚህ ላይ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ይህን ተግባር የሚፈፅመው አካል ሙያተኛና ገለልተኛ እንጂ እንደተለመደው እርስ በርሱ እንዳይሆን ነው። ገለልተኛ የማይሆን ከሆነ ግን የመንግሥትን እጆችና የገንዘብ ኪሳራ ከማብዛት የዘለለ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም።

ሌላው ወሳኝ የሆነው መንገድ ደግሞ የሚድያ ተቋማትና ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን ሙያዊ ብቃት በተላበሰ ሁኔታ እንዲፈፅሙ ማስቻል ነው። ከዚህ አንፃር የመንግሥትና በዙሪያው ያሉ ሚዲያዎች ቱቦዎች ከመሆን አልፈው ያለምንም ፍርሃትና መሸማቀቅ መልካም ስራዎችንና ገፅታዎችን በማጉላት፤ ችግሮችን ደግሞ ያለርህራሄ በመለየት ለህዝብና ለመንግሥ ጆሮ እንዲደርሱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ኢህአዴግና መንግሥትም ይህን መንግድ መከተሉ አማራጭ የሌለው መፍትሔ እንደሆነ ቁርጠኛ አቋም ላይ መድረስ ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ምንም እንኳን የግሉ የሚዲያ ተቋማት አብዛኛዎቹ የሙያዊ ስነ-ምግባር ችግሮች ያሉባቸው ቢሆኑም፤ የሚያነሷቸውን ችግሮችና ትችቶችን ሰምቶ ወደውስጥ ማየት ኢህአዴግን ይጠቅመዋል እንጅ አይጎዳውም። ይልቁንም እነዚህ የግል ሚዲያ ተቋማት የዴሞክራሲው ሂደት አካል ተደርገው ቢወሰዱና ከመንግሥት ተቋማት መረጃ እንዲያገኙ ቢደረግ በስማበለው በተገኘ ተባራሪ ወሬ ላይ ተመስርተው ከመፃፍ ያድናቸዋል። ይህ ደግሞ እዛው እንዳለ ህዝቡ ሚዛናዊ ዘገባ እንዲያገኝ ከፍተኛ ሚና ይጫወት ነበር። ሌላው ከግሉ ሚዲያ ተቋማት ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው አብይ ቁምነ-ገር መንግሥት እንዚህን የግል ሚዲያ ተቋማት ፍትሃዊ ባልሆነ ህግ እየተከታትለ ከማቀጨጭና ብሎም እንዲከስሙ ከማድረግ ድርጊቱ ሊገታ የሚገባው መሆኑ ነው። እንዲያውም ጠቃሚ የሚሆነው እነዚህ ተቋማት ብቃታቸው እንዲጎለብት አስፈላጊው እገዛ እንዲደረግላቸው ማበረታታት ቢሆን ነበር።

ሰባተኛው ከልማት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የመፍትሔ አቅጣጫን የሚመለከት ነው። ከልማት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው ከህዝቡና ህዝቡ ጥቅም ላይ ብቻ በመቸከል ነው። ይህ ማለት ደግሞ የግል ጥቅምን ህገ-ወጥና አግባብ ባልሆነ መንገድ መጠቀም መሻትን ማስወገድ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ሙስና፣ አድሎና የመሳሰሉት የህዝብን ጥቅም የሚፃረሩ ድርጊቶች መፀየፍ ማለት ነው። ይህን ለማድረግ የተለያዩ መንገዶችን መከተል ይቻላል። የመጀመሪያው መንገድ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና አሰራሮች ለሁሉም ተደራሽና ሁሉንም በእኩል የሚያስተናግዱ መሆን አለባቸው። ለምሳሌ አንድ ሰው ሰርቶና አልምቶ መጠቀም ያለበት በዜግነቱ እንጅ ባለው የፖለቲካ አመለካከት የዝምድና ወይም የጥቅም ትሥሥር ሊሆን አይገባውም። በኢህአዴግ ዘመን ያየነው ጉድ ግን ከፊሉ ልማታዊ ባለሃብት የሚባለው አንድም የኢህአዴግን ፖለቲካ እደግፋለሁ የሚል ሌላም ባልሥልጣናትን የሚጠቅም ካልሆነም ደግሞ በዝምድናና በጓደኝነት ባጠቃላይም በመረብ (net-work) የተሳሰረ ሲሆን ነው። ይህ አይነቱ ባለሃብት ግን የልማት ሳይሆን የጥፋት ባለሃብት ነው። ከዚህ ስንነሳ እንዲያውም በዚህ ዘመን ልማታዊ ባለሃብት ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው ከመንግሥት ሹመኞች ጋር የሚያሞደሙደውና ልማታዊ ተብሎ የሚጠራው ሳይሆን በነዚህ የኢህአዴግ ሹመኞች ኪራይ ሰብሳቢ እየተባለ ከሚጠራው ውስጥ በርካታው ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆነ ይህ አንድ ባለሃብት ውይም ደግሞ ሰርቶ ለመጠቀም የሚፈልግ ዜጋ ልማታዊ የሚሆነው ህጋዊና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ብቻ ስራውን ሲሰራ ነው። ከዚህ ባለፈ ባቋርጭ ሄጀ እከብራለሁ የሚል ባለሃብትም ይሁን ባለሥልጣን በጊዜ ቦታውን እንዲይዝ ቢደረግ ይመረጣል። እንደዚህ አይነት ባለሃብትና ባለሥልጣን ከራሱ አልፎ የሚጠቅመው ሰው ስለማይኖር ብቻ ሳይሆን፤ ለህዝብና ላገር ነቀርሳ በመሆኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተጠያቂ ሊሆንም ይገባል። ይህ ሊሆን የሚገባው ደግሞ በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ማንም ሰው እኩል በመሆኑና ሁሉም ጥፋተኛ በጥፋቱ ልክ መጠየቅ ስላለበት ነው። እዚህ ላይ ኢህአዴግ ባንክሮ ሊመለከተው የሚገባው ጉዳይ ለፖለቲካ ፍጆታ ወይም የጥቅም ትሥሥርን መሰረት አድርጎ ሰውን ከህግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ማድረግ ህዝብን መናቅ ብቻ ሳይሆን ለፍትህና ለኩልነት ሲሉ የተሰው የንፁሃን ዜጎችን ህይወት ከቁጥር ያለማስገባት ይመስላል።

ከልማት ጋር ተያይዞ ሊቀመጥ የሚገባው ሌላው የመፍትሔ አቅጣጫ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የተቋቋሙትን የልማት ድርጅቶች (endowments) የተመለከተ ጉዳይ ነው። ምንም እንኳን እነዚህ የልማት ድርጅቶች የተቋቋሙት በትግሉ ወቅት በተገኘ ገንዘብና ንብረት ነው ቢባልም፤ የገንዘቡ ምንጭ ዞሮ ዞሮ የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ኪስ ነው፡ ስለዚህ እነዚህ ድርጅቶች ኢህአዴግ በሚመራቸው አራት ክልሎች ብቻ የታጠሩ ከሚሆኑ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቢደራጁና ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ሊጠቅሙ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው በበለጠ በህዝቦች መካከል የልብ ለልብ ግንኙነት እንዲጎለብት ያላቸው ሚና ከፍተኛ ይሆናል።

ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለእኩል ተጠቃሚነትና ለህግ የበላይነት ሲሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መስዋእትነት ከፍለዋል። ይህ የተከፈለ መስዋእትነት ደግሞ ያመጣቸው መሰረታዊ የሆኑ አወንታዊ ለውጦች መኖራቸው የሚካድ አይደለም። ሂደቱ አነሰም በዛ ህዝቡ የተሳተፈበት ሕገ-መንግሥት እንዲኖርና ብሔር፣ ብሔረስቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳደሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር አስችሏል። ብዙዎቹ ፖሊሲዎችም ቢሆኑ ህዝብን ሊጠቅም በሚችል መንገድ የተቀረፁ ናቸው። ይሁን እንጅ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ አሉታዊ የሆኑ ሁኔታዎች መደጋገማቸው አልቀረም። እነዚህ አሉታዊ የሆኑ ሁኔታዎች ደግሞ ብዙውን ጊዜ የሚታዩት ባፈፃፀም ረገድ ነው። በዚህ ዘመን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲታይ መርሆቹ በተለያየ መንገድ ተሸራርፈው አልቀው ባፈጻጸም ላይ የሚታዩ ችግሮች እንደመርህ እየተወሰዱ ያሉበት ደረጃ የተደረሰ ይመስላል። ከዚህ በመነሳት እነዚያ መተኪያ የሌለው ህይወታቸውን ለህዝብ ጥቅም ሲሉ አሳልፈው የሰጡ ዜጎቻችን ላንድ አፍታ ስትንፋስ ዘርተው ቀና ብለው የወደቁለት አላማ ወደኋላ እየተመለሰ እንደሆነ ቢያዩ እጅግ በጣም ሊከፉና ሊያዝኑ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም። በተለይም ደግሞ ሚዛናዊነት የጎደለው የሥልጣን ክፍፍል፣ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ስርጭት፣ በዘር ላይ ይሁን በሌሎች ሁኔታዎች የተመሰረተ የአድሎ ስራዎች፣ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች፣ የህግ ጥሰቶች፣ ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀምና የመሳሰሉት ከትግሉ አላማ ያፈነገጡ አካሄዶች ኢህአዴግን ጠፍረው የያዙት ይመስላል። እነዚህ ችግሮች መፈጠራቸውና እያደጉ መምጣታቸው እጅግ በጣም አሳሳቢ ቢሆንም መፈታት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብሎ መውሰድ ግን አያስደፍርም። በርግጥ ችግሮቹ በጣም ከባድና ውስብስብ ናቸው። ይሁን እንጅ ቁጥራቸው ጥቂት ሊሆን ቢችልም አሁንም ኢህአዴግ ውስጥ ቅን፣ ጠንካራና የህዝብ ውግንና ያላቸው አመራሮችና አባላት ሊኖሩ ስለሚችሉ፤ እነዚህ ደግሞ አሸንፈው ወጥተው ሌላውንም ህዝባዊ አላማ ማላበስ እስከቻሉ ድረስ የሚደርሰውን ኪሳራ ሁሉ ችሎ እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት አሁንም የመሸ አይመስልም።

ዋናው ነገር ኢህአዴግ በቁርጠኝነት ራሱን አሳልፎ ለህዝብ መስጠት እስከቻለ ድረስ ከህዝቡ ጋር ሆኖ የማይፈታው ችግር አይኖርም። ይህን ለማድረግ ደግሞ ቢኢህአዴግ በኩል መፈፀም የሚኖርባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ከነዚህ ውስጥ አብይና መሰረታዊ የሆነው ጉዳይ ኢህአዴግና መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ሙሉ በሙሉ ማክበርና ለነሱም መገዛት የሚኖርባቸው መሆኑ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ መንገድም ሆነ በተጨማሪ ምርጫ በሚካሄድበት ጊዜ ነፃና ገለልተኛ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ፍትሃዊ የሥልጣንና የሃብት ስርጭት እንዲኖር ማድረግ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች በተሟላ መንገድ ማክበርና ማስከበር፣ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ ተቋማትን መፍጠርና ማሳደግ፣ መሰረታዊ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ለሕብረተሰቡ ማሳወቅና የመሳሰሉ ጉዳዮች ጊዜ ሳይወስዱ መከናወን ያለባቸው መሆኑን ኢህአዴግና እሱ የሚመራው መንግሥት ከልብ ሊያምኑበትና ለተግባራዊነቱ ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ይህ ከሆነ ደግሞ ለኢህአዴግ የዳመነ የሚመስለው ግርዶሽ ተግፎ ብርሃን እንደሚፈነጥቅለት ይሚያጠራጥር አይሆንም። እዛው እንዳለም ሀገራችን ላይ የተጋረጠ የሚመስለውን አደጋ በማስወገድ ረገድ እጅግ በጣም የጎላ ሚና ይኖረዋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ ንፁሃን ዜጎች ረዕይ ተቀልብሶ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ቢናጋ ኢህአዴግ ከቀደሙት ሥርዓቶች ሁሉ እጅግ በጣም በከፋ ሁኔታ የታሪክ ተወቃሽ እንደሚሆን መገንዘብ ይኖርበታል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!