ይገረም አለሙ

Pres. Dr. Mulatu Teshome and PM Hailemariam Desalegne

ፕሬዝዳንት ሙላቱ በዘንድሮው ፓርላማ መክፈቻ ንግግራቸው አንዳንድ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ገልጸዋል። የመንግሥቱን ሥልጣን በበላይነት የሚቆጣጠሩት ህወሓቶች የገጠማቸውን የሕዝብ ተቃውሞ ለማስተንፈስ ያስችለናል ያሉትን፤ ግን የማይፈጽሙትን የማሻሻያ ርምጃ ጽፈው ሲሰጡዋቸው ከማንበባቸው በፊት ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ሊያገናዘቡ በተገባ ነበር። አንደኛው በአምናው የመክፈቻ ንግግራቸው ከተናገሩት ያልተፈጸሙት ይልቃሉና የማተገብሩትን ተናገር እያላችሁ ቃል አባይ ፕሬዝዳንት አታድርጉኝ ማለት፤ ሁለተኛው ደግሞ የተባሉት ማሻሻያዎች ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚነገሩ ሳይሆን በርግጥ ታምኖባቸው ተፈጻሚ እንዲሆኑ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ከሆነ፤ አንዳንዶቹ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መንገድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እናደርጋለን የሚል በንግግራቸው እንዲካተት ማድረግ ይገባቸው ነበር።

የርሳቸው ሲገርም ጠቅላይ ምኒስትሩ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል አስፈላጊ ቢሆን እንኳን ... ማለታቸው መንግሥታቸው አሻሽላቸዋለሁ ብሎ በፕሬዝዳንቱ ያስነገራቸው ጉዳዮች፤ አንዳንዶቹ የሕገ መንግሥቱን መሻሻል የሚጠይቁ መሆናቸውን አለመገንዘባቸውን ያሳያል። ይህ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ካለማወቅ ወይንም ከቁብ ካለመቁጠር የሚመጣ ነው።

የህዝቡን ቁጣ ያበርዳል፣ የሥልጣን ፍርፋሪ ናፋቂዎችን በጉጉት ማኖር ያስችላል፣ አውቆ ለሚታለለው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም እጅ መንሻ ይሆነናል ወዘተ ተብሎ ከተነገረው የማሻሻያ ሃሳብ ውስጥ አንዱ የሆነው የምርጫ ሕግ እነርሱ በማን አለብኝነት ካልፈጸሙትና ተቃዋሚው ለእኛ እስከጠቀመ ድረስ ብሎ በዝምታ ካልተቀበለው በስተቀር፤ የሕገ መንግሥቱን መሻሻል የሚጠይቅ ነው። የምርጫ ሕጉን ማሻሻል የተፈለገው ፕሬዝዳንቱ እንደነገሩን የምርጫ ሥርዓቱን ወደ ተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት ለመቀየር ይሁን፤ የቀድሞው ቃል አቀባይ እንደገለጹት ከተመጣጣኝና ከአብላጫ ሥርዓቶች የተዳቀለ ሥርዓት ለመፍጠር ሕገ መንግሥቱ ሳይሻሻል የሚሆን አይደለም። እንዲህ አይነቱን ነገር እነርሱ ሆን ብለው ለማደናገሪያነት የሚያቀርቡት በመሆኑ አይደንቅም፤ አዲስም አይደለም። ሌሎች ግን የምርጫ ሕጉን ለመለወጥ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል እንደሚጠይቅ ባለማጤን እንደ መልካም ነገር ቆጥረው የተነገረውን እንደ ወረደ ተቀብለው ሲያስተጋቡትና ሲተቹት ማየትና መስማት ያስገርማል።

ወያኔዎች ዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒት ይሆነናል ብለው ካሰቡ ሕገ መንግሥት ምናቸውም አይደል። መጀመሪያም መጨረሻም ጉዳያቸው ሥልጣን ነውና በነጋሪት ጋዜጣ ያወጁትን በጓዳ ሊሽሩት በአደባባይ የተናገሩትን እንዳልነበረ ሊያደርጉት ግድ አይሰጣቸውም። ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻሉ የሚገባቸው አንቀጾች አሉት ብሎ መናገር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማፍረስ አስብሎ ሲያስወነጅል በቅርቡም ከዳኝነት ሥራ ሲያስባርር አይተናል። ህወሓቶች ግን ሊጥሱትም እስከ መኖሩ ሊረሱትም ሌላውን ሊያጠቁበትም ዕድሜ ለጠብ መንጃቸው መብት አላቸው። ይህ ደግሞ ከጫካ ጀምረው ደንባቸውን በመተላለፍ በአዋጅ ያጸደቁትን በጓዳ በማፍረስ ሌሎችን ጥፋት ብለው የወነጀሉበትን እነርሱ ይጠቅመናል ባሉ ግዜ በመፈጸም እያዳበሩት የመጡት አብሮ አደጋቸው የሆነ ተግባር ነው።

ለዚህ ማሳያ የሚሆኑኝ ሁለት ማስረጃዎችን ልጥቀስና ወደ ርዕሰ ጉዳዬ እመለሳለሁ። ምን ያህል ሰው ልብ እንደሚለው አላውቅም እንጂ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚል አጠራር ከተጀመረ ሦስት ዓመት አልሞላውም። ታሪክ የማይረሳቸው በሕገ መንግሥቱ ጉባኤ ላይ ብቸኛ ኮከብ የነበሩት ሻለቃ አድምሴ ዘለቀ የጎሣና የቋንቋ አከላለሉን ተቃውመው በተለይ ደግሞ ምስራቁን አካባቢ ሲሆን የሶማሌ ክልል ባትሉት፤ እምቢ ካላችሁ ደግሞ የሚሆነው አይታወቅምና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ብትሉት በማለታቸው የወረደባቸውን ዘለፋና ስድብ አንረሳውም። ያኔ የነፍጠኛ አስተሳሰብ ያሉት ሰዎች ዛሬ እነርሱ ሲሉት የነፍጠኛ አስተሳሰብ አራማጅ ሆነው ነው ማለት ነው! ወያኔዎች ለሥልጣናችን ማቆያ ይጠቅመናል ካሉ እንዲህ ናቸው።

ዋናው ጉዳይ ግን ይህ አይደለም፤ የሻለቃ አድማሴ ተቃውሞ ኋላ ቀር የነፍጠኛ አስተሳሰብ ተብሎ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሶማሌ ክልል ተብሎ ነውና የሰፈረው ሕገ መንግሥቱ ሳይሻሻል የተደረገው የስም ለውጥ የሕገ መንግሥት ጥሰት ነው። እነርሱ በማን አለብኝነት ጣሱት፤ እኛ በምን አገባኝ ዝም አልን። ሕገ መንግሥታችን እያሉ የሚመጻደቁብን ሰዎች ለሕገ መንግሥታቸው ያላቸው አክብሮትም ሆነ እውቀት እዚህ ድረስ ነው።

በሁለተኛ ማሳያነት የማቀርበው በህወሓት ክፍፍል ወቅት ቢኒያም ዮሃንስ የተባሉ ጸሀፊ ህወሓት - ምን ነበር? ምንድን ነው? ምን ሊሆን ይችላል? በሚል ርዕስ ሪፖርተር መጽሔት ሚያዝያ 1993 እትም ላይ ካቀረቡት ጽሁፍ የተወሰደ ነው። እንዲህ ይላሉ፤ “ማሌ ካለ ድል አለ የተባለለትን ማሌን ስሙን አትጥሩ፣ ማሌሊትን አታነሱ፣ ማጭድና መዶሻ አታሳዩ፣ ባንዲራውን ደብቁ የሚል ሹክሹክታ የአባላቱን ጆሮ ሞላው። በፀሐይ የተፎከረለት ማሌ በጨለማ ለመናገር አሳፈረ፣ ታጋዩ አመራሩ ምን እንደሚል ለመስማት ቢጠብቅም አመራሩ ግን ዝም ሆነ። ቢያንስ አቶ መለስ ማሌን አይጥሉትም፣ አቶ አለምሰገድም እንዲህ አያደርጉም ብሎ ጆሮውን አንቅቶ ቢጠብቅ ሁሉም ጭጭ አሉ። ያን ያህል የተዘመረለት ሌሎችን ‘ፕራግማቲስቶች’ አስብሎ ከድርጅቱ ያስገለለ ርዕዮተ ዓለም በየኬላው እየተፈተሸ እንደሚቀር የኮንትሮባንድ እቃ የእንጦጦን ኬላ ሳያልፍ ቀረ” ይላሉ። አዎ በወያኔዎች ዘንድ ሁሉም ይደረጋል ለሀገርና ለሕዝብ ሳይሆን ለሥልጣን ሲባል።

ስለ ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት የሚገልጸው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 በንዑስ አንቀጽ 2 ላይ “የም/ቤቱ አባላት በአንድ ምርጫ ክልል ውስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምጽ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ በሚሆንበት የምርጫ ሥርዓት ይመረጣሉ። የተለየ ውክልና ያስፈልጋቸዋል ተብሎ የታመነባቸው አናሳ ብሔረሰቦች አና ሕዝቦች በምርጫ የሕ/ተ ም/ቤት አባል ይሆናሉ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ይላል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል የተባሉ ጉዳዮች ብዙዎቹ ሕጉ ያልወጣላቸው ሲሆን፣ በዚህ አንቀጽ የተገለጸው ዝርዝር ሕግ ወጣም አልወጣም አናሳ ብሔረሰቦችን እንጂ ውክልና ያላገኙ ፓርቲዎችን አይልምና፤ ሕገ መንግሥቱን ሳያሻሽሉ ፓርቲዎችን በችሮታ ወደ ፓርላማ የማስገቢያ መንገድ ማበጀት አይቻልም።

ስለሆነም የምርጫ ሕጉን እናሻሽላለን የሚለው የፕሬዝዳንቱ ንግግር ኋላም ጠቅላይ ምኒስትሩ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል እንኳን አስፈላጊ ከሆነ ... በማለት የገለጹት ይህን የሕገ መንግሥት አንቀጽ ያላገናዘበ ወይንም ሆን ብሎ የጣሰ ነው። ሌላው ሰውም ባለማወቅ፣ በየዋህነት ወይንም ሆነ ብሎ ለማስቀየሻነት እየተቀባበለ እንደ ድንቅ ተግባር ያስተጋባዋል። የተቃውሞው ጎራ በአብዛኛው የፊት የፊቱን እንጂ ግራና ቀኙን አለማስተዋል፤ የዕለት የዕለቱን እንጂ የትናንቱን አለማስታወስ ለወያኔዎች የማጭበርበር ጉዞ በእጅጉ ተመችቶአቸዋል፣ ጠቅሞአቸዋልም። መቼም ለበጎ ነገር ሕገ መንግሥት ቢጣስ ምን አለበት የሚል ተከራካሪ ይኖራል ብዬ አልገምትም።

ስለሆነም የተወራው የምርጫ ሕግ ማሻሻያ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ መሻሻል የሚጠይቅ መሆኑ ታውቆ፤ ለዚሁ ሲባል የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንደሚደረግ አለመገለጹ ጉዳዩ የተነሳው ለማደንዘዣነት እንጂ ለተግባራዊነት አይደለምና፤ በዚህ ለመታለልም ለመደለልም ራስን ማዘጋጀት አያስፈልግም። በአንጻሩ ከላይ በማሳያነት እንደቀረበው የሶማሌ ክልልን ስም ያለ ሕግ መንግሥት ማሻሻያ እንደለወጡት ሁሉ ይህንስ ቢያደርጉት ብለን ብናስብ ሕገ መንግሥቱን የጣሱት ለመልካም ተግባር ነውና ግዴለም ተብሎ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችል አይመስለኝም።

ስለዚህ የምርጫ ሕጉን በማሻሻል የተወሰኑ ተቃዋሚዎችን በፓርላማ እንዲታዩ ማድረግ የሚለው ትኩሳት ማብረጃ ከመሆን ባለፈ ቢያንስ በእነዚህ በተጠቀሱት ምክንያቶች ተግባራዊ ሊሆን አለመቻሉ ግልጽ ነው። የግድ የሕገ መንግሥት መሻሻያ ይጠይቃልና። በማን አለብኝነት ወይንም ለተቃዋሚዎች የሚጠቅም ስለሆነ አይቃወሙትም በሚል ተግባራዊ ቢደረግ ደግሞ የሕገ መንግሥት መጣስ ወንጀሉን ተቃዋሚዎችንም በእኩል ተካፋይ ያደርጋል።

ከአንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም እንዲሉ፤ ወያኔዎች የምርጫ ሕጉን አገራዊ ጉዳት ተገንዝበው እሱን በማሻሻል ለውጥ ለማምጣት ከልብ ያሰቡበትና ያመኑበት ከሆነ እሱን የሚመለከተውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ ማሻሻል ለእነርሱ በጣም ቀላል ነው። ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሰረት ሕገ መንሥቱን የማሻሻል ሥልጣን ያላቸው ፓርላማውም ሆነ የክልል ምክር ቤቶች በህወሓት ቁጥጥር ስር ናቸውና። ነገር ግን አንድም በመቃብራችን ላይ ካልሆነ በስተቀረ እያሉ ሲፎክሩለት የኖሩትን ሕገ መንግሥት በሕዝባዊ አመጽ ተገዶ ማሻሻል ለእነርሱ ከሽንፈትም በላይ ሞት ሆኖ ስለሚታያቸው፤ ሁለትም የሕገ መንግሥቱን መሻሻል የሚፈልጉ ብዙ የሕዝብ ጥያቄዎች በር ላይ አሉና አንዴ ከተጀመረ ከዚህም ከዛም እየተናደ ሥልጣናችንን የሚያሳጣን ደረጃ ያደርሰናል ብለው ስለሚሰጉ አይነኬ የሚሉትን ሕገ መንግሥት ማሻሻል ውስጥ አይገቡም። ለዚህም ነው ጥያቄ በተነሳና ህዝባዊ ቁጣ በተቀሰቀሰ ቁጥር በሕገ መንግሥቱ አግባብ የሚለውን ቃል የሚያስቀድሙት። አቶ ኃይለማርያምም የሕገ መንግሥቱን መሻሻል የሚጠይቅ ማሻሻያ እንዳላቀረቡ ሁሉ፤ ማሻሻል ቢያስፈልግ እንኳን በማለት የገለጹት። ስለሆነም የምርጫ ሕግ ማሻሻያ ዲስኩሩ ከፕሮፓጋንዳ አልፎ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አይደለምና ከወያኔም ባህርይ ሥልጣንን የማጥበቅ እንጂ ከሕዝብ የመታረቅ ተግባር አይጠበቅምና፤ ለመሰረታዊ ለውጥ ሳይሆን ለዕድሜ ማራዘሚያ ለተግባራዊነት ሳይሆን ለማደናገሪያና ለማስቀየሻ ከወያኔ ሰፈር በሚነገሩ ጉዳዮች አለመዘናጋት የነጻነቱን ቀን ለማቅረብ ይበጃል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!