Girma Seifu Maru. Photo TheGuardianግርማ ሰይፉ ማሩ

የሰሞኑን የካቢኔ ሹመት አስመልክቶ ብዙ አስተያየት እየተሰጠ ነው። አስተያየት መስጠቱ ትክክል ነው። በሕይወታችን ላይ ከፋም-ለማም ውሳኔ የሚያሳልፉ ሰዎች ምደባ በመሆኑ የመሰለንን አስተያየት መሰንዘር ተገቢ ይመስለኛል። በእኔ እምነት ኢህአዴግ ባልሆንን ሰዎች፣በተለይ ደግሞ የተሻለ አማራጭ ይታየናል፣ አለንም ለምንል ዜጎች ዋናው ጉዳይ የኢህአዴግ ፖሊሲ በምን ዓይነት ካቢኔ በደንብ ተግባራዊ እንደሚሆን መምከር አይመስለኝም።

እኛ በእጃቸን ያለውን አማራጭ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ የምንችልበት የፖለቲካ ምኅዳር መመቻቸት ጉዳይ ነው የእኛ ጥያቄ መሆን ያለበት። በእግረ መንገድም ኢህአዴግ ፖሊሲውን እንዲፈፅሙ የተመደቡት ሰዎች መስመር ሲስቱ ማጋለጥ ዋነኛ ተግባራችን ነው። ብዙዎች እንደሚጠብቁት ፖሊሲዎቹ ያላቸውን በጎ ጎን እየጠቀሱ ኢህአዴግን ማወደስ፣ በአንዳንዶቹ አባባል እውቅና መስጠትም ኀላፊነታችንም ግዴታችንም አይደለም። ይህን አስተያየት በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደ ዜጋ በጋራ መቆም ከሚለው መርኅ ጋር ማምታታት በፍፁም ተገቢ ካለመሆኑም በላይ ለኢህአዴግ ተደጋጋሚ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆንን ነው የሚያመለክተው።

አንድ አንድ ሰዎች አሁን በሹመት ወደ ኀላፊነት የመጡት ሰዎች በብዛት አዲስ አድርገው ይገምታሉ፤ (ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከዘጠኙ በስተቀር በሚል አሳሳች መልዕክት እንዳስቀመጡ ሳንዘነጋ)። በቁጥር ሁለት ሲበዛ ሦስት ከሚሆኑት ውጭ የኢህአዴግን ፓርቲ መታወቂያ ከመውሰድ በስተቀር ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ ለመሆን የሚሞክሩ፣ በነበሩበት ተቋም በተገቢ ሁኔታ ኢህአዴግን አሁን ለደረሰበት ውድቀት የዳረጉ ጭምር ናቸው። በዚህ ጉዳይ በዝርዝር መግባት ተገቢ አይደለም። እነዚህ ሹመኞች ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ የፖለቲካ ሥልጣን የላቸውም። ያለ ፖለቲካ ሥልጣን የሚኒስትርነት ቦታ በፖለቲካ አቋም በየመስሪያ ቤቱ ከሚገኙ የፖለቲካ ምድብተኞች ጋራ ለመጋጨት ካልሆነ ትርጉሙ አይታየኝም። ደርግ በመጨረሻ ዘመኑ የክልል አስተዳዳሪዎቹን በተለያየ ዘርፍ ትምህርት የቀመሱ በዘርፋቸው ምርጥ የተባሉ ምሁራንን አድርጎ ነበር። የዚህ ሹመት ውጤት የሆነው ከኢሠፓ ሹሞች ጋር የዕለት-ከዕለት ግጭት ነበር። በኢህአዴግ ውስጥ ፓርቲ መሪ ስለሆነ እነዚህ “አዲስ ተብዬ” ሹሞቾ የፓርቲ መመሪያ ሲጠብቁ ሥራ ተገተሮ እንዳይቀር ስጋት አለኝ።

እነዚህን ሹሞች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በድፍረት ጥያቄ ሊጠይቋቸው ይችላሉ። በፓርቲ ውስጥ አለቃ ስለአልሆኑ፣ ጠብ እርግፍ አድርገው ሊያብጠለጥሏቸው ይችላሉ። ወይም ጥፋት ካጠፉ ወደ ዘብጥያ ለማውረድ የፓርቲ ግምገማና አቋም ላይጠየቅላቸው ይችላል። በዚህ ሁኔታ አሁን ያሉት ሚኒስትሮች አንዳንዶቹ ሚኒስትሮች (እነ ወርቅነህ፣ ደብረፅዮን፣ የመሳሰሉት) ከፖለቲካ ጡንቻ ጋር ሲሆኑ፤ የተቀሩት ይህን ዋና የፖለቲካ ጉልበት ባለመያዝ ነው በአንድ መድረክ የተገናኙት። እነዚህ የፖለቲካ ጡንቻ ያላቸው ሚኒስትሮች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደነገሩን በሲኒየር ሚኒስትርነት በውስጠ ዘ-ምክርና መመሪያ የሚሰጡ ይሆናሉ ማለት ነው። ከዚህ ዘለል ባለ መስመር የሚሄድ ሚኒስትር ካለ ወደፊት የምናየው ይሆናል። ለምሣሌ የአሁኑ የመንግሥት ኮሚኒኬሼን ሚኒስትር ማድረግ ያለባቸው በመዝገብ ታሽጎ ፈቃድ የተከለከሉ ጋዜጠኞች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ፣ በሽመልስ ከማልና አለቆቹ ትዕዛዝ ወህኒ እንዲወርዱ፣ በየፍርድ ቤቱ የሚንከራተቱ ጋዜጠኞች ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ከግምት በማስገባት ከእስር በመፍታት፣ የፍርድ ቤት ምልልሱን በማቋረጥ የሚዲያ ምኅዳሩን ክፍት እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህን ካልቻሉ እስኪባረሩ ሳይጠብቁ ምክንያታቸውን ለሕዝብ ገልፀው ከሹመት መልቀቅ ይጠበቅባቸዋል።

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከላይ እስከ ታች የተንቀሳቀሰው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ወ/ሮ ዘነቡ ታደሠ፣ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ወዘተ ... ከሥልጣን ይውረዱልን የሚል ጥያቄ አንስቶ አይደለም። በመሰረታዊነት እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያን ፖለቲካ ምኅዳር ለማፈን ያላቸው ሚና ዜሮ ነው። የአንድ አንዶቹ ሚና ከተላላኪነት የሚዘልም አይደለም። የእነዚህ ሚኒስትሮች ከሥልጣን ተነስቶ እዚህም እዚያም ሥርዓቱን ሲያገለግሉ በነበሩ ቴክኖክራቶች በመተካት የአገራቸውን ኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ አያመጣም። ከቴክኖክራት ሚኒስትሮች የሚጠበቀው የቴክኒክ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ሕዝብ የሚጠብቀውን የፖለቲካ ሪፎርም እንዲመጣ ማድረግ ነው። ይህን ማድረግ አቅም አላቸው ወይ? ብለን ስንጠይቅ ጥርጣሬ እንደሚያጭር እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ምክንያቱም እነዚህ አዲስ ሹሞች የፖለቲካ ሥልጣን የላቸውም። በኢህአዴግ ቤት ደግሞ ሥልጣን ያለው ፓርቲ ነው። ከፓርቲም በህወሓት እጅ ነው። በአማራም በኦሮሚያም የነበረው እንቅስቃሴ ውስጥ ጎልቶ የወጣው የአንድ ፓርቲ/የህወሓት የበላይነት ይቁም የሚለው ነው። ለዚህ ጥያቄ ተገቢ የሆነ ምላሽ አልተሰጠም።

በመግቢያዬ ላይ እንዳልኩት ኢህአዴግ የፈለገውን ካቢኔ ሚኒስትር የመሾም መብት አለው። በኢትዮጵያችን የተፈጠረው ችግር በኢህአዴግ ካቢኔ የሞያ ስብጥር ምክንያት አይደለም። የኢትዮጵያ ችግር የፖለቲካ ምኅዳሩ ኢሕአዴግና ለኢሕአዴግ ለገበሩ ብቻ በሚሆን መልኩ የተደራጀ መሆኑ ነው። በአገራችን ኢትዮጵያ መንግሥት ከሚፈልገው ውጭ መናገርም ሆነ መሥራት በመከልከሉ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በሕገ መንግሥት በግልጽ የተደነገገን የመደራጀት መብትን፣ ተደራጅቶም ሃሳብን የማቅረብ መብትን መተግበር ባለመቻሉ ነው። በኢትዮጵያችን የመንግሥት ተቋማት ዜጎችን አገልግሎት የሚሰጡት በሕግ አግባብ ሳይሆን የየትኛው ብሔር አባል ነው በሚል መመዘኛ መሆኑ ነው። በኢትዮጵያችን መንግሥት የሚባው አካል ተጠያቂ ያለመሆን ብቻ ሳይሆን ማንነታቸው የማይታወቅ አካላት የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በስውር ያዛሉ። የሚጠሉትን ፓርቲ ከሕግ አግባብ ውጭ ያፈርሳሉ። የግል አገልግሎት መስጫዎችን፣ ማተሚያ ቤቶችን በስልክና በግንባር እየቀረቡ ያስፈራራሉ። በአገራችን ኢትዮጵያ የደንብ ልብስ የለበስ ፖሊስ አባላት ከነ ማዕረጋቸው ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ዜጎችን ለማፈን ሲሞክር መታወቂያ መጠየቅ የማይቻልባት አገር ነች። ስንቱን ዘርዝሮ ይቻላል። ይህን ችግሩን የሚያሰማበት መድረክ ያጣ ሕዝብ በብሶት ተነሳስቶ የዜጎች ሕይወትና ንብረት እንዲወድም አድርጓል። ይህ ውድመት የአፈና ውጤት ነው። አፈናን በማፈን ማስታገስ ደግሞ አይቻለም።

አሁንም በአገራችን የሥርዓት ለውጥ በሥርዓት እንዲመጣ ፍላጎት ብዙዎች አለን። ፍላጎት በራሱ ግን በቂ አይደለም። በእኔ እምነት ሥርዓት በሌለው ሁኔታ ለውጥ እንዲመጣ ከማንም በላይ ፍላጎት እያሳዩ ያሉት መንግሥት እና ገዢው ፓርቲ ናቸው። መንግሥት በሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ የመሪነቱን ሚና መጫወት ይኖርበታል። በቅድሚያ ማንኛውም ከመንግሥት ጋር ያልተግባባ ኃይል ከመፈረጅ መታቀብ አለበት። በዋና ዋና የአገር ዕልውና ላይ የማይደራደሩ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ማድረግ የሚከለክል አሠራር ሊዘረጋ ይችላል። ከዚህ በመለስ ኢሕአዴግ እራሱን “በጥልቅ ማደስም ይሁን አፍርሶ መሥራት” የራሱ የቤት ሥራ ሲሆን፤ “መንግሥት” በግልፅ ከፓርቲው መለየቱን ለማስመስከር ባለበት ኀላፊነት ኢህአዴግን አውራ ፓርቲ የማድረግ ተግባሩን በማቆም በአገራችን የሃሳብ ልዮነትን መሠረት ያደረጉ ፓርቲዎች ምድር እንድትሆን ለማድረግ ቁርጠኛ እርምጃ መውስድ ይኖርበታል። ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ፤

፩· በኢትዮጵያ ውስጥ የሚጀመረውን የፖለቲካ ሪፎርም ሊመራ የሚችል ኮሚሽን በማቋቋም፤ በሀገሪቱ ያሉት ችግሮች ደረጃ በደረጃ በውይይት የሚፈታበትን ተግባር እንዲያከናውን ሥልጣን መስጠት። ይህን ኀላፊነት የሚወስድ ማንኛውም ሰው በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ማድረግ። ፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ መልክ እንዲደራጁ መፍቀድ፣ ሚዲያ በነፃነት እንዲሠሩ መፍቀድና ማገዝ፣ ህዝቡ የመሰለውን የፖለቲካ አቋም እንዲያራምድና እንዲደግፍ ማበረታታትና ማገዝ፣

፪· በማንኛውም ሁኔታ ከመንግሥት መዋቅር ውጭ መመሪያ የሚሰጡና የሚያስተገብሩ አካላትን ድርጊት በግልፅ ማስቆም (ለምሳሌ የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር መስሪያ ቤትን በሚኒስትርነት ደረጃ ለማቋቋም የተጀመረውን ሥራ ማጠናቀቅ፤ ተጠያቂ የሆነ የደህንነት ጉዳዮች ሚኒስትር በይፋ መሾም)፣ ኢትዮጵያዊ ደህንነት መስሪያ ቤት ማቋቋም፤

፫· ከሃያ አምስት ዓመት በኋላም በመከላከያ ውስጥ የሚታየውን ያልተመጣጠነ የኀላፊነት ቦታ ምደባን ለማስተካከል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ። ብቃትን መሰረት ያደረገ ምደባ በማድረግ ተሰናባቾችን በክብር ማሰናበት። ... የመሳሰሉት ይገኙበታል።

እነዚህ እርምጃዎች መላው የአገራችን ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ድምፁን ለማሰማት እድል የሚፈጥሩ ስለሆነ፤ ከግብታዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴ የሚገታው ይሆናሉ። የሚወሰዱት ተግባራዊ የፖለቲካ ምኅዳር የማስፋት እርምጃዎች ለቀጣይ በተረጋጋ ሁኔታ በአገር ፍቅር ስሜት እና በባለ አገርነት ስሜት በነፃነት የዕለት ተግባሩን ከማከናወን በዘለለ፣ ከፍ ወደሚል አገራዊ ኀላፊነት ስሜት እንዲያድግ ያግዘዋል።

ነፃነት ባለበት ዲሞክራሲ ያብባል። ይህን ጊዜ ዘላቂ ሰላምና እድገት ለትውልድ ይተላለፋል። ለዚህ ሲባል ገዢው ፓርቲ/መንግሥት አሁን ያላቸውን ሕገወጥ ቁርኝት በመለየት ፓርቲውም እንደ ፓርቲ፤ መንግሥትም እንደ መንግሥት ኀላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። በምንም ሁኔታ የመንግሥት ሥልጣን ገዢውን ፓርቲ በተለየ ሁኔታ መጥቀም አይኖርበትም። የካቢኔ ሽግሽግ የፓርቲው ጉዳይ ነው። በሥርዓት የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ትክክለኛውን እርምጃ በትክክለኛው ጊዜ መውሰድ ይኖርብናል።

ኢትዮጵያ አገራችን እና ሕዝቧን እግዝአብሔር በበረከቱ ይጎብኝልን!!!!
ቸር ይግጠመን!!!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!