አመለ በየነ

በቅድሚያ ተማጽኖ፣

1. ትግሉ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ ይሁን!

ለራስ ሥልጣን አልሞ የሚደረግ ትግል ለምንይልክ ቤተመንግሥት አይደለም ለፓርላማ ወንበርም እንዳላበቃ አይተናል፣ አልተማርንበትም እንጂ ቤተ መንግሥት ደርሶም መገፍተር እንደሚያስከትል በኦነግ አይተናል፣ እናም ይቅር ተዉት፣

2. እኔ እበልጥ ይቅር!

ኢህአፓና መኢሶን አይደለም ደርግ እንዳያንሰራራ ማድረግ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ የመለወጥ አቅም ነበራቸው። በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ሲሻኮቱ ሁለቱም በደርግ ተበለጡ። መበለጥ ብቻ ሳይሆን ወጣቱን ለስዋዕትነት አገሪቱን ለወታደራዊ ግዞት አበቁ። ግን እስከ ዛሬም ከዛ አልተወጣም፣

3. ስሜታዊ ድጋፍና ጭፍን ጥላቻ ይወገድ!

ስም መጥቀስ ሳያስፈልግ በድርጅትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ያመናቸው ሲከዱን፣ የተከተልናቸው አውላላ ሜዳ ላይ ጥለውን ሲሸበለሉ አይተናል። ጭፍን ጥላቻም ጉዳቱ በግልጽ ይታወቃል፣ እናም ድጋፋችንም ሆነ ተቃውሞአችን ምክንያታዊና በሐቅ ላይ የተመሰረተ ይሁን። በእውነት ስለ እውነት ከራስ በላይ አገር ብለን እንነጋገር፣ በማስረጃ እንከራከር፣

4. ሰጥቶ መቀበልን ባህል እናድርግ!

ሁሉም በየራሱ አጥር ክልል ቆሞና በራሱ ፍላጎትና አስተሳሰብ ተገድቦ መቀራረብ አይቻልም። ካልተቀራረቡ ደግሞ መነጋገር የለም። ካልተነጋገሩ መስማማት አይኖርም። ስለሆነም ኢትዮጵያችንን መሃከል ላይ አስቀምጠን ወደ ዳር መጎተት ሳይሆን፣ ወደ መሃል መራመድ እንቻል። የምንሻውን ማግኘት የምንችለው ሌሎች ከእኛ የሚፈልጉትን ለመስጠት ስንችል ነው፣ “እኔ ብቻ ትክክል ነኝ” ማለት የትም አላደረሰም፣ የትም አያደርስምም፣

መፈክር ለመደርደር ያበቃኝ፣ አንድም ተደራጀን የሚሉትም ሆኑ በደጋፊነት ተሰልፈው የሚሻኮቱት ሁሉም ማለት በሚያስችል ሁኔታ ከአገር ውጪ መሆናቸው፣ ሁለትም ከማኅበራዊ ድረገጽ አልፎ መሬት የረገጠ ነገር ስለመኖሩ ባለመገለጹ፣ በዋናነት ደግሞ ከዕለት ዕለት እየበዙ መሄዳቸው ... ወዘተ ነው። መፈክር ነው ከአንዱ አንዱ እየተቀባበለ የሚያስተጋባው፣ የሚያባዛው። ድርጅት የጎደለውን እያሟሉ፣ የዘመመውን እያቃኑ ያጠነክሩታል እንጂ አያባዙትም። ለአንድ ድርጅት የማይበቃ ሰው አራት አምስት ድርጅት መመስረት የጥቂቶች ስብስብ እንጂ ድርጅት አያሰኝም። በውይይቱ ከገፋን ወደ ፊት ብዙ ማለት ይቻላል።

ከስሜት ኮርኳሪው ቅስቀሳ በስተጀርባ ምን ይኖር ይሆን?

ነብሳቸውን ይማርና በአጭር የተቀጩት ፕ/ር አሥራት ወልደየስ፣ በየመድረኩ በተደጋጋሚ ግዜ፣ “የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በመሬት ላራሹ ልብ አማላይ መፈክር ተታለው ሳያውቁት ለኤርትራ መገንጠል አስተዋጽኦ አድርገዋል” ይሉ ነበር። ዛሬ ይህን ለማስታወስ ምክንያት የሆነኝ፣ “አማራ በዘሩ መደራጀት አለበት” የሚለው ስሜት ቀስቃሽ እንቅስቃሴ የፕሮፓጋንዳ ይዘቱና የተግባራዊነት እንዴትነቱ ነው።

ዘመቻው የሚካሄደውም ሆነ በየዕለቱ ተፈጠሩ የሚባሉት ድርጅቶች ዓላማ የሚገለጸው በማኅበራዊ ድረገጽ ነው። ከጥቂቶቹ በስተቀር ሰዎቹ በአካል ቀርቶ በስም አይታወቁም፣ በዚህ ሁኔታ ግን ደጋፊ ነኝ ያለ ጎራ ለይቶ ርሱም ማንነቱን ከልቶ በቃላት ይታኮሳል። እነዚህም ኢትዮጵያውያን ናቸው እስከሚያስብለን ድረስ በጸያፍ ቃል ይወራረፋል። እናም ይህን ስታዘብ የፕ/ር አሥራትን አባባል ቀየር በማድረግ፤ “የዘመናችን የፌስ ቡክ የአማራ አርበኛ አማራ በማንነቱ መደራጀት አለበት በሚለው ልብ አማላይ መፈክር ተታልሎ ለኢትዮጵያዊነት መዳከም አስተዋጽኦ እያደረገ እንዳይሆን” ማለትን ወደድሁ።

የሚካሄደው ሰበካ በአንድ በኩል በአማራነት ለመደራጀት ኢትዮጵያዊነትን አውልቆ መጣል እንደሚገባ ይገልጻል። ኢትዮጵያዊ አማራ ነኝ የሚሉም ዘለፋና ውግዘት ይደርስባቸዋል። አገራዊ አንድነት ማለት ፀረ አማራነት ተደርጎ ይፈረጃል። ይህን የሚሉትና የሚያደርጉት ግን በአማራነት በቅጡ መደራጀት አልቻሉም። ይሄ ነው እንግዲህ እንቆቅልሽም ጥራጣሬ ፈጣሪውም ነገር።

ኢትዮጵያዊነት ሲፈልጉ የሚደርቡት፤ ሲሻ አውልቀው የሚጥሉት ይመስል፤ በአንድ በኩል “አማራ የተጎዳው ኢትዮጵያዊነት እያለ ነውና፤ ኢትዮጵያዊነቱን ጥሎ አማራነቱን ብቻ መያዝና መደራጀት አለበት” እያሉ፤ በሌላ በኩል እነርሱ በአማራነት አንድ ሆነው መደራጀት ተስኖአቸው መታየታቸው፤ ከመፈክሩ በስተጀርባ አማራው ከኖረበት ኢትዮጵያዊነትም፣ ከታሰበለት አማራነትም ሳይሆን፤ ከሁለት ያጣ እንዲሆን የማድረግ ዓላማ ይኖር ይሆን የሚል ጥርጣሬ አይጋብዝም ትላላችሁ? በመሬት ላራሹ ልብ አማላይ መፈክር ጀርባ ኤርትራን የመገንጠል ሴራ እንደተሠራው ሁሉ፤ አማራ በማንነቱ ይደራጅ ከሚለው እንቅስቃሴ ጀርባ፤ የእንቅስቅሴው አራማጆች አብዛኛዎቹ በማያውቁት ሁኔታ ኢትዮጵያዊነትን ቢቻል የማጥፋት፤ ካልሆነም የማዳከም ስውር ሥራ እየተሠራ ቢሆንስ? ከሆነ አውቆ ለመጠንቀቅ፤ ካልሆነም የተበታተኑትን ወደ አንድ ለማምጣትና ለማጠናከር በሚረዳ መልኩ በጨዋነትና በጥሞና እንነጋገርበት።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!