ሸንቁጥ አየለ

U.S. President Barack Obama shakes hands with Donald Trump

አሜሪካኖቹ የተዋጣለት ሥርዓት እና ተቋም በመገንባታቸው ብቻ የተለያዩ ውስብስብ እና አስቸጋሪ አስተሳሰቦችን እና ዕይታዎችን ይዘው የሚመጡ ፖለቲከኞችን ማስተናገድ የሚችል ሁኔታን፤ ብሎም አሜሪካ እንደ አገር የምትቀጥልበትን ጥልቅ መሰረት ጥለዋል። ለምርጫ ሲወዳደሩ ያለው ሂደት፣ ምርጫው ሲጠናቀቅ የሚያሳዩት የሠለጠነ ባህሪ እና የሥልጣን ሽግግሩ አስደማሚ ሂደት ሁሉ የአንድ ነገር ውጤት ነው። ተገቢውን ሥርዓት እና ተቋም በመገንባታቸው።

ከዚህች አገር እና ሕዝቦች ምርጫ አንድ ነገር ብቻ መማር በቂ ነው። እንደተባለውም እንዴት የተዋጣለት ሥርዓት እና ተቋም በመገንባት የማይናወጥ አገራዊ መሰረት ላይ ማስቀመጥ እንደሚቻል ማሰላሰል።

ይህችን ጽሁፍ እያዘጋጀሁ ትናንትና ከአንድ ወዳጄ የሰማኋት የበሰለች ነገር ትዝ አለችኝ። እናም ከአሜሪካኖቹ ምርጫ ምን መማር እንዳለብን ብዙ ለመጻፍ የተነሳሁት ሰውዬ፤ ልቤም እጄም ብዙ ለመጻፍ አልታዘዝም አሉኝ። ይሄ ወዳጄ ካንድ ጓደኛው ጋር ከአሜሪካ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ምን እንደሚቀስሙ ይወያያሉ።

የወዳጄ ጓደኛም "ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካ ምርጫ ብዙ ሊማሩት የሚገባ ነገር አለ" ብሎ ለወዳጄ ሰፋ አድርጎ ያብራራለት ይጀምራል። ወዳጄም በአጭሩ "ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ ገና ሳይስማሙ ስለምርጫ ምን ሊማሩ ይችላሉ?" የሚል ጥያቄን ለጓደኛው ያቀርባል።

እናም ይሄ ወዳጄ ያነሳው ጥልቅ ሃሳብ እውነት ነው እና፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካኖቹ የምርጫ ሂደት የምንማረው አንድም ነገር ላይኖር ነው ማለት ነው? ብዬ ሃሳብ ማንሳት እና መጣል ጀመርኩ። በርካታ ፖለቲከኞች በአሁኑ ወቅት ከግራም ከቀኝም፣ ከፊትም ከኋላም ኢትዮጵያ ስትፈርስ ነው ለብሔራችን ምቹ ሁኔታ የሚፈጠረው የሚል የደናቁርት ጩኸት እየጮኹ መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው። እነዚህ በክፋት፣ በጥላቻ እና በአላዋቂነት የታነቁ ፖለቲከኞች ነገርን ሳስብ ነገሬን በአጭር ሸከንኳት።

ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ የመኖር ሕልውና ላይ ላለመስማማት እየሄዱበት ያለው የተጠናገረ ሃሳብ፤ ስለ ዲሞክራሲ ለመወያዬት ያለው ዕድል ብዙ ሩቅ መሆኑን በከፊል የሚያስረዳ ነውና፤ ከዲሞክራት አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አበጃጀትን እና ተቋማት አፈጣጠርን ቅሰሙ ብሎ መስበክ ከፊል ኮሜዲ ነው የሚመስለው። ሆኖም እንደሰው ልጅ ደግሞ ሰው የመማር ሂደት ውጤት ነው እና ሙሉ ለሙሉ ተስፋ መቁረጥ አይገባም።

የሆነ ሆኖ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች ትራምፕ ወይም ሂላሪ ስለማሸነፏ ሰፋፊ ትንታኔ ከሚሰጡ ይልቅ፤ ይሄን የአሜሪካውያንን መሰረት ላይ የቆመ የዲሞክራሲ ሥርዓት እና የተቋም ግንባታ ሂደት፤ እንዴት መቅሰም እንደሚቻል ቢመክሩበት መልካም ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!