የትነበርክ ታደለ

Fasil hotel, Addis Ababa

ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም መባቻ ጀምሮ የተያዘው አዲስ ልክፍት ገጽታ ግንባታ የሚል ነገር ነበር። ሁሉም ነገር ወደ ገጽታ ግንባታ። ሕንጻውም፣ አስፋልቱም፣ ቀለሙም፣ ዳንሱም፣ ዘፈኑም፣ ውበቱም የሚታየው ነገር ሁሉ የአገሪቱን ገጽታ ስለመገንባት ብቻ እንዲያወራ ይደረግ ዘንድ ግድ ሆነ።

በዚህም ምክንያት ታላላቅ ሆቴሎች እዚህም እዚያም ቁጭ ቁጭ ይደረጉ ገቡ። (ለነገሩ ጊዜው ካለፈ በኋላ ብዙዎቹ ሆቴሎች ዓለም አቀፍ ደረጃን የማይመጥኑና ምንም እንኳ በፎቅ ብዛት ወደ ሰማይ የተመነጠቁ ቢሆኑም፤ ኮከብ አልባ እንደሆኑ የደረጃዎች መዳቢ ኤጀንሲ ከዓመት በፊት ገልጾልናል።)

እናላችሁ እነዚህ የልጆቻችንን የመጫወቻ ሜዳ ጭዳ ያደረግንላቸው፣ አስፋልቶቻችንን ለዓመታት ከርችመን የሥራ ጊዜያችንን ያጣበብንላቸው፣ የደሃ ጎጆዋችንን ደምስሠን የነሱን ድንጋይ የተሸከምንባቸው ሆቴሎች እውነት የአገራችንን ገጽታ ገንብተዋል ወይ? ይህን ታላቅ ጥያቄ ለመመለስ ጥቂት ጥናት ማድረግ የግድ ቢሆንም፤ እኔ ግን በአንድ ዘርፍ ብቻ መዝኛቸው ብዙዎች ገጽታ አጥፊዎች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።

ከላይ የዘረዘርኳቸው መሰረታዊ ነገሮች እንዳሉ ሆነው እነዚህ ሆቴሎች ላያችን ላይ ሲታነጹ ብዙ ዛፎችን፣ በርካታ የሜዳ ሳሮችን፣ ሕይወት የምንዘራባቸውን መስኮቻችንን አሳልፈን ሰጥተናቸዋል። ይሁን እንጂ ስንቶቹ ናቸው በምትኩ ዛፎች የተከሉልን? ለኛ ምስኪን ነዋሪዎቹ አስበውም እንኳ ባይሆን የራሳቸውን ደንበኞች የዓይን ዕይታ ለመሳብና ያሉበትን አካባቢ ለማስዋብ ሆቴላቸውን በደን የከበቡት ስንቶች ናቸው?

ይህ ቀላል ጥያቄ ነው። አንዳቸውም ይህ ጉዳያቸው አይደለም። ብዙ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። እነሱ የያዙትን ቦታ እንዴት አድርገው ለቢዝነስ እንደሚያውሉት እንጂ ከአካባቢው አጠቃላይ ሁኔታ ጋር የተሰናሰለ ቁም ነገር መሥራት ቁም ነገራቸው አይደለም።

ለነሱ ገጽታ ግንባታ ማለት የታጠበ አንሶላና የተወለወለ መስታወት እንጂ ከሕንጻው ውጪ ያለው ሕይወት አይደለም። ለነሱ ዛፍ መትከልና አካባቢን ማስዋብ ወጪ እንጂ ገቢ ስላልሆነ የሚያሳስባቸው ቁም ነገር አይደለም።

እናም ሆቴሎቻችን የአገራችንን ገጽታ ገነቡልን ልንል አንችልም። አፈረሱብን እንጂ ...!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ