ይገረም አለሙ

በቅድሚያ መልዕክት፤
ርዕሱን አይተው የጽሁፉን አጠቃላይ መልዕክት በጥሞና አንብቦ ለመረዳት ትእግስት በማጣት የጭቃ ጅራፍ ለማጮህ ለሚጣደፉ ወገኖቼ ለአገር አንድነት፤ ለሀዝብ አብሮነት፤ ለነጻነት ትግሉና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንቅፋት እስካልሆነ ድረስ ማናቸውም ሰው በመሰለው መንገድ መደራጀት መብቱ መሆኑን የማምን መሆኔን እወቁልኝ። ይህች አስተያየቴ መጻፌ በአማራነት ለመደራጀት ለምን አሰባችሁ? ለምንስ ሞከራችሁ? ሳይሆን፤ በአማራ ይደራጅ ስም የሚነገር የሚጻፈው ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ሳይሆን ቆምንለት የምትሉትንም አማራነት የማይጠቅም ሆኖ ስለታየኝ ነው።

መንደርደሪያ፤

ወያኔ በአስራ ሰባት ዓመት አጭር የትጥቅ ትግል ለሥልጣን የበቃው በዘር ተደራጅቶ አማራን በጠላትነት ፈርጆ በመንቀሳቀሱ ነው ብለው ይህን እንደ መልካም ተሞክሮ ወስደው በወያኔ የተጠቃው የእነርሱ ብሔር ብቻ እንደሆነ አድርገው የሚቀሰቅሱና የሚደራጁ፤ እንዲሁም አንድ ብሔር ጠላት ፈጥረው ዘረኝነት የሚሰብኩ ሰዎች ከሥልጣን ፍላጎት ቅዠት ያለፈ አገራዊ ራዕይ አላቸው ለማለት የሚያበቃ ነገር አይታይባቸውም። ሊኖራቸውም አይችልም። ወያኔ ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ ቤተ መንግሥት ተቀምጦ አገራዊ ራዕይ መያዝ አይደለም ኢትዮጵያ አገራችን ብሎ መጥራትን መለማመድ እንኳን ያልቻለው ከዘረኝነት አስተሳሰብ በመነሳቱ ነው። ስለሆነም በዘር ተደራጅተን ራሳችንን ከጥቃት ታድገን ወደ ኢትዮጵያዊነት እንሸጋገራለን ወይም እንመለሳለን ማለት መሆን ከመቻሉ አለመቻሉ ነው ሰፊ ዕድል ያለው። የዘረኝነት ዓይነ ርግብ አጥልቀው ሁሉን ነገር በሱ ከተመለከቱ በኋላ ዓይነ ርግቡን ማውለቅ ይቸግራል፤ እንደምንም ማውለቅ ቢቻል ደግሞ አዕምሮአቸው ውስጥ ተቀርጾ የቀረው በዘረኝነት ዓይነ ርግብ የተመለከቱት ነውና ከዓይነ ርግቡ መጣል ጋር በአዕምሮ ተቀርጾ የተቀመጠው ወጥቶ ሊጣል አይችልም። የዘረኝነት አረንቋ ሲገቡበት ቀስ በቀስ ነው እስከ ወገብ ከሰመጡበት በኋላ በራስ ጥረትም ሆነ በሌሎች ድግፍ ለመውጣት በጣም አስቸጋሪ ነው። ዛሬ በየመድረኩ አንዴ ኢትዮጵያዊ ሌላ ግዜ ደግሞ የጎሣ ፖለቲካ አራማጅ እየሆኑ ሲቸገሩ የምናቸው ለዚህ በቂ ምሳሌ ናቸው።

በመደራጀት ንትርክ ወቅቱ ነውን!

ወያኔ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ባወጣው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ተጠቅሞ በዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለው ኢሰብዓዊ ድርጊት ኃያላን የሚባሉትን መንግሥታት፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶችን የመንግሥታቱን ድርጅት ወዘተ በእጅጉ ያሳሰበ ሆኖ ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ስጋታቸውን እየገለጹ የሚገኙበት ወቅት ላይ ነን። እነርሱ እንዲህ በሚያስቡበትና በሚጨነቁበት ወቅት ኢትዮጵያውያን በድርጅትም ሆነ በየግል በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሽፋን የሚፈጸመውን ኢ.ሰብዓዊ ድርጊት ለማስቆምና ለስድስት ወር የታቀደውን ለማጨናገፍ መምከር፣ ማቀድ፣ በተግበር፣ ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን በተገባ ነበር። ይህ ሊሆን በሚገባበት በዚህ ወቅት ራሳቸውን የአማራ ተወካይ አድርገው በስሙ ድርጅት ሲፈጥሩ የሚያድሩቱ ፖለቲከኛ ነን ባዮች በአንድ በኩል በመደራጀት ጉዳይ ርስ በርሳቸው ሲፋጁ በሌላ በኩል በአገራዊነት በተደራጁና በተግባር ላይ ባሉት ላይ የቃላት አረራቸውን ሲተኩሱ መስማት የሚሉትን እንዳናምን ብቻ አይደለም ማንነታቸውንና ምንነታቸውን እንድንጠራጠር ያደርጋል። ለምንድን ነው ይህን የሚያደርጉት? በርግጥ በአማራው ጀርባ ላይ ያለው ቁስል በእነርሱም ጀርባ ላይ ኖሮ እየቆጠቆጣቸው? አማራው ከወያኔ አገዛዝ መላቀቅ አለበት ብለው አምነው ለዚህ ትግል ራሳቸውን አዘጋጅተውና የሚያስፈልገውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል በቆራጥነት ተነስተው? ለነዚህ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ መስጠት አይቻልም፤ ይህን የምለው ደግሞ ከተግባራቸው እንዳይባል ሰርተው ያሳዩት ነገር የለምና ከሚሉትና ከሚጽፉት በመነሳት ነው። ለዚህም የሚከተሉትን በአስተውሎት እንመልከት።

አማራው ራሱን ከጥቃት እንዲከላከል ለማብቃት የድርጅት ብዛት አያስፈልገውም፤

እንደሚነግሩን በአማራነት ለመደራጀት ምክንያት የሆናቸው እኔ በአልገዛም ባይነቱ የምለው እነርሱ በአማራነቱ የሚሉት በአማራው ላይ የደረሰው በደል ከሆነ በዳዩ ወያኔ ተበዳዩ አማራ ነውና አምስት ስድስት ድርጅት ለመመስረት የሚያበቃ ምንም ምክንያት የለም። ስለሆነም በየቀኑ ድርጅት እየመሰረቱ ስድስት ነው ሰባት ድርጅት የደረሱት ወገኖች የየራሳቸውን ፍላጎት በዚህ ሽፋን ለማሳካት ያስችለናል በሚል እንጂ በአማራው ጀርባ ላይ ያለው ቁስል በእነርሱም ጀርባ ላይ ኖሮ እየቆጠቆጠ አላስተኛ ብሏቸው ነው ለማለት አያስችልም። አማራው በአማራነቱ ብቻ ተበደለ እያሉ የሚተርኩትም ሕዝቡን በቀላሉ ለማነሳሳትና ልክ እንደ ወያኔ ፍላጎታችንን በአጭር ግዜ ለማሳካት ያስችለናል ያሉትን የዘረኝነት መርዝ ለመርጨት እንጂ በርግጥ ለአማራው ነጻነት አስበው ተጨንቀው መሆኑን አያሳምንም። እንደሚጽፉትና እንደሚያወሩት አማራ ራሱን ከጥቃት ለመከላከል እንዲችል ለማብቃት ቢሆንማ ኖሮ፤ ጥቂት አማራ ነን ባዮች ብዙ የአማራ ድርጅት መሰረትን ባላሉ ነበር። ሁሉንም የምናውቃቸው በማኅበራዊ መገናኝ ነውና ምን አልባት እንዳንዶች ከሚለጥፉት አርማና ይህንኑ ከሚሠሩ ሁለትና ሦስት ሰዎች ውጪ ሰውም ላይኖራቸው ይችላል።

አማራውን ከወያኔ አገዛዝ ለማላቀቅ ግንቦት ሰባትና ኢሳት ላይ መዝመት አያስፈልግም

ኢሳት በመላው ዓለም በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እውቅና ያገኘና አድናቆት ያተረፈ በተግባሩም ወያኔን እየተፈታተነ ለመሆኑ ወያኔ ራሱ የመሰከረለት የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ነው። አገር ውስጥ እንዳይታይና እንዳይሰማ ለማድረግ ወያኔ በቢሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት ማፍሰሱ ከዛም አልፎ ኢሳትና ኦ.ኤም.ኤን. ላይ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እገዳ መጣሉ፤ በዓለም መድረክ ከሚደርስብኝ ፖለቲካዊ ውርደት ኢሳት የሚያደርስብኝ የሥልጣን ማናጋት ይበልጣል ብሎ እንደሆነ ህሊና ያለው ሁሉ የሚገነዘበው ነው። ግንቦት ሰባትም በአሸባሪነት የተፈረጀውና ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሽ ባለ ቁጥር ከመንግሥት ባለሥልጣኖች አፍ የማይጠፋው እየሠራ መሆኑን እንጂ ሀፍረተ ቢሶቹ እንደሚሉት አስመራ መመሸጉን አይደለም የሚመሰክረው። ለሥልጣን በማስጋቱ እንጂ የወያኔ ፍቅረኛ በመሆኑም አይደለም።

ታዲያ በአማራነት ተደራጀን የሚሉን ወገኖቻችን እንዲህ በወያኔ በራሱ በተረጋገጠውና በተፈራው ለወያኔ ሥልጣን አስጊ በሆኑት ኢሳትና ግንቦት ሰባት ተግባር ደስተኛ አለመሆናቸው ከምን የተነሳ ነው። አሁን ሁለቱም ድርጅቶች በተግባር ከደረሱበት ደረጃና ካተረፉት ህዝባዊ አመኔታ አንጻር ከማኅበራዊ መገናኛ ወሬ ያላለፉ ሰዎች ይሉኝታ ቢስ መንፈራገጥ ረሳቸውን ለመላላጥ ይዳርጋቸው ካልሆነ በስተቀር የሚያደርሱት ጉዳት አይታየኝም። ቢሆንም ግን ጦራቸውን የሰበቁት ኢትዮጵያን ከወያኔ አገዛዝ አላቆ ዴሞክራሲያዊት አገር ለማድረግ በተጀመረውና አያሌ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት በከፈሉበትና አሁንም በየቀኑ መስዋዕትነት እየከፈሉበት ባለው ትግል ላይ በመሆኑ በቸልታ የሚታለፍ የትም አይደርሱም ተብሎም በንቀት የሚታይ አይደለም። እናም መረጃ እየፈለፈሉ የትናንት ማንነታቸውንና የዛሬ ምንነታቸውን እያነፈነፉ በሐቅ ማጋለጥ የአገር ወዳዶች ግዴት ይሆናል። ወያኔ የሚፈራውንና የሚጠላውን ተቋም እንዴት የወያኔ ተቀዋሚ ነኝ የሚል በተመሳሳይ ሊፈራውና ሊጠላው ይችላል? እንቆቅልሽ፤

ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት አዲሱ ስልት

በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን የሚደረግ ትግል በማንም ተከናወነ በማን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ ነው። እኛ የሚመለከተን የአማራ ጉዳይ ብቻ ነው ስለ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለመሆን አያገባንም እስከሚል ጽንፍ ቢሄዱ እንኳን አማራው የኢትዮጵያ አካል መሆኑን እስካልካዱ ድረስ አማራውም አንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ ነውና በማናቸውም መልክ ከወያኔ አገዛዝ ጋር የሚካሄደውን ትግል የሚያደናቅፉበት ታጋዮችንም የሚነቅፉበት ምክንያት ሊያቀርቡ አይችሉም።

እዚህ ላይ ስንደርስ ሁለት ነገር በግልጽ ማየት የሚቻል ይመስለኛል። አንደኛው ወያኔ በትግሬ ወካይነት ለቤተ መንግሥት እንደበቃው ሁሉ እኛም በአማራ ወካይነት ለሥልጣን መብቃት እንችላለን ብለው መነሳታቸውን። ግን ይህን ያሉና የሚሉ ብዙ ሆኑና በየዕለቱ አዳዲስ የአማራ ድርጅት መመስረት ሆነ ሥራቸው። ህወሓት ለሥልጣን የበቃው በወቅቱ በትግሬ ስም የተደራጁ ሌሎች ድርጅቶችን ሁሉ በልቶ ብቸኛ የትግራይ ተወካይ ሆኖ ለመውጣት በመቻሉ እንደመሆኑ እነዚህም ተበላልተውም ይሁን ተግባብተው አንድ የአማራ ወካይ ቤተ መንግሥቱን አሸጋግሮ የሚያይ ድርጅት እስከሚፈጠር ምጽዓት ይደርሳልና የሚያሳዝነው አንዳቸውም ያለሙትን የማያገኙት መሆኑ ነው። አስተሳሰባቸውን የቀየደው ነገር ይህን እንኳን ለማየት አላስቻላቸውም።

ሁለተኛው በኢሳትና በግንቦት ሰባት ላይ ከያዙት ዘመቻ አንጻር የምንረዳው ጉዳይ ወያኔያዊ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን ነው። ወያኔ ከመነሻው ኢትዮጵያዊነት አምነትና አስተሳሰብን ለሥልጣኑ አስጊ አድርጎ ማየቱ አከራካሪ አይመስለኝም። ሊያጠፋው ባይችልም ኢትዮጵያውያን በገነቡት ቤተ መንግሥት ተቀምጦ ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ በኢትዮጵያዊነት ላይ መዝመቱ ከዚሁ የተነሳ ነው። አማራው ደግሞ በኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝነቱ ይታወቃል፤ በመሆኑም አማራንና ኢትጵያዊነትን ለመለያየት ብዙ ተሠርቷል አልሆነም። በህወሓት አቃጅነት በብአዴን አስፈጻሚነት ብዙ የተሞከረውና ያልተሳካው የአማራ ብሔረተኝነት ለአማራው ታስቦ ሳይሆን አማራውን ከኢትዮጵያዊነት ለማፋታት ነበር ሳይሆን ቀረ እንጂ።

ይህን ሁሉ ዙሪያ ገብ ሰንቃኝ የአሁኗ አማራው ራሱን ከወያኔ ጥቃት ለመከላከል በማንነቱ መደራጀት አለበት የምትለዋ ዘመቻ ሰሟ “አማራን ማደራጀት”፤ ወርቋ “አማራን ከኢትዮጵያዊነት ማለያየት”፤ አጠቃላይ ግቧ አማራው ከኢትዮጵያዊነትም ከአማራነትም ከሁለቱም ሳይሆን ለአገሩም ለራሱም የማይበጅ በማድረግ ወያኔ የፈራውን ኃይል መገላገል ነው። ከነገሮቹ መረዳት ከወያኔ አድራጎትም መገመት እንደሚቻለው ይህን የሚያደርጉት ዋናዎቹ ጥቂቶች ሲሆኑ፤ እነርሱም አንድም በተለያየ መንገድ ለወያኔ ያደሩ፤ ሁለትም ወያኔ ቀይ ካርድ እያሳየ የሚያስገብራቸው ናቸው። አብዛኛዎቹ ግን ይህን የጀርባ ሴራና ሥራ ባለመረዳት በሚያዩትና በሚሰሙት ስሜታቸው እየተጎዳ ሳያውቁ ለሚከተሉዋቸው ደጋፊና ተባባሪ የሆኑ ናቸው። በአማራው ውስጥ ጥላቻ እንዲስፋፋና ለዚህ የበቃሁት ኢትዮጵያ በማለቴ ነው ብሎ በአማራነት እንዲያስብ ለማድረግ ወያኔ ሆነ ብሎ አስቦና አቅዶ በደሎችን ይፈጽማል፣ ለዚሁ ተግባር ተመልምለው ምን አልባትም በቀጥታ ወይ በተዘዋዋሪ ሥልጠና ወስደውና መመሪያ ተሰጥቶአቸው የተሰማሩት ደግሞ የወያኔን ፀረ አማራ ድርጊት እያጎሉ ዘረኛ ቅስቀሳ ያካሂዳሉ።

ከላይ ብዙዎች ያልኩዋቸው በዚህ እየተታለሉም ስሜታቸው እየተጎዳም ስለ አማራነታቸው እንዲያስቡ የተገደዱ ናቸው። የመጀመሪያዎቹን ከተግባራቸው ማቀብም ሆነ ከወያኔ ማለያየት ከባድ ነው፤ ከተባበርን ግን ማጋለጥና ከዚህ አልፈው እንዳይሄዱ፤ ሌሎችንም እንዳያታልሉ ብሎም ከጨዋታ ውጪ ማድረግ ይቻላል። ከሚያዩትና ከሚሰሙት ጀርባ ያለውን ለመረዳት ባለመቻል ወያኔ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ለሚያደርገው ሥራ ተባባሪ የሆኑትን ደግሞ መርዳት አስፈላጊም፣ የሚቻልም፣ የሚገባም ነውና፤ ባለማወቅ በጥፋት ላይ የተሰማሩ ወይንም ለአጥፊዎች የሚተባበሩ ወገኖችን የማዳን ሥራ እንሥራ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ