አንተነህ መርዕድ

ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ ሕዝቧም ነፃነት እንዳለው ዜጋ ለመኖር ያለው ተስፋ አደጋ ላይ እየወደቀ ያለበት ሁኔታ ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም፤ ፅንፈኝነት ጉልህ ቦታ የያዘ ይመስለኛል። የፅንፈኝነትን ፅንሰ ሃሳብ መተንተን ለባለሙያዎች ልተወውና እንደ አንድ ዜጋ የሕመማችንን ምክንያት አቅሜ በፈቀደው አንድ ነገር ማለት አስገደደኝ።

በተለይ ፅንፈኝነቱ የአገሪቱን ሰማያት፣ የዜጎቿንም አዕምሮ እንደማዕበል እያላጋ ሚዛን ሲያሳጣንና ሊበትነን ሲታገል ዝምታን መምረጥ ይከብዳል። በፖለቲካው፣ በጎሣው፣ በኃይማኖቱና ዘመኑ በፈጠረው ሶሻል ሚድያ የሚማሰለው የፅንፈኝነት ማዕበል፤ ብዙ ፈተና ያለባትን ኢትዮጵያን ይቅርና ጥሩ መሰረት ላይ አለን የሚሉ አገሮችን ሊፈታተን የሚችል ነው።

በ1966 ዓ.ም. ብሶቱ ጣራ ነክቶ ሕዝቡ ለአመጽ ሲነሳ ድሉን የሚያስጠብቅበት ብዙ ዝግጅት አልነበረውም። ብሶትና ተቃውሞ መነሳት ቀላል ባይሆንም ሊተካው የሚችለውን ሕዝባዊ ሥርዓት በእርግጠኝነት ለመመስረት ራዕይና መሰረት ጣይ ሥራ መሥራት የበለጠ ከባድ ነው። ስለዚህም ነው ከአውሮፓና ከሰሜን አሜሪካ በአንድነት ቁጭ ብለው ስለ ኢትዮጵያ እንጨነቃለን የሚሉ ጓደኛሞችና ወጣት ምሁራን የአገሪቱንም ሆነ የሕዝቧን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ፤ እነሱም በቅጡ ያልተረዱትን ርዕዮተ ዓለም ጭነውበት በቡድን ለመግዛት የያዙት ፅንፈኛ አቋም እነሱንም እንዳይተርፉ፤ የኢትዮጵያ ተስፋ የሆኑ ወጣቶችም እንዲቀጠፉ ለታጠቀ ኃይል አሳልፈው ሰጡ። ዴሞክራሲ እንዲሰፍን እንታገላለን ቢሉም፤ በውስጣቸው የሚፈጠርን ልዩነትም ሆነ ከተፃራሪያቸው መፍትሔ ያደረጉት መገዳደልን ነበር። ወንድም ወንድሙን፣ አባት ልጁን የገደለበት አሳፋሪ ታሪክ ታቅፈን ተቀምጠናል። በዚያ ቢያበቃ መልካም ነበር። በዚያን ጊዜ የተጣባን መጥፎ መንፈስ አልጠፋ ብሎ፤ አሁንም የክፍፍሉ አውራ ተዋናይ እኛው የዚያ ትውልድ ውርዴዎች ነን።

የአሁኑ ፅንፈኝነት ማጠንጠኛ ደግሞ የጎሣ ጉዳይ ሆኗል። ኦስትሪያዊነቱ የሚያመዝነው ሂትለር፤ ለንፁኅ የአርያን ዘር እየማለ ሚሊዮኖችን እንዳስገደለ ሁሉ፤ ከኤርትራና ከሌላው የኢትዮጵያ ዘሮች ሐረግ መሳብ የሚችሉ ህወሓቶች ለንፁኅ የትግራይ ሕዝብ መብት ቆምን ቢሉም ለግል ሥልጣናቸውና ለግል ብልፅግናቸው ብቻ እንደቆሙ በአደባባይ አሳይተውናል። የሚገርመው ነገር ሌሎችም ይህንኑ የህወሓት ፈለግ የሚከተሉ መበርከትና ሃሳባቸውንም እንድንቀበል በሚያሳፍር ሁኔታ ሲገፉበት ማየቱ ነው። እዚህ ላይ ግልፅ ማድረግ ያለብኝ ነገር ቢኖር የኦሮሞን፣ የትግሬን፣ የአማራን፣ የሶማሌን፣ የአፋርን ... ወዘተ መብት ለማስከበር መደራጀትንና መታገልን ከልቤ የምደግፈው መሆኑን ነው። ነገር ግን ቆምንለት የሚሉትን ሕዝብ ከለላ በማድረግ የረጅም ታሪኩንና የአብሮነት ባህሉን በመካድ ወይንም በማኮስመን፤ ለጠባብና ለተሸፈነ ዓላማቸው ከሌሎች ወንድሞቹ በተፃራሪ እንዲቆም ብሎም እንዲነጠል የሚገፉትን ፅንፈኛ አቋም በአደባባይ መሞገት ያስፈልጋል።

የሩቁን ሳይሆን የቅርቡን ብንመለከት፤ የኢትዮጵያን ህልውና የሚያጠፋ የውጭ ጠላት በመምጣቱ አፄ ምኒልክ “አመልህን በጉያ፣ ስንቅህን በአህያ” አድርገህ ተከተለኝ ሲሉ አገር በማስፋፋቱም ሆነ በሥልጣን ይገባኛል አፄ ምኒልክ ላይ ቂም የቋጠሩ መሳፍንትና መኳንንት “የኢትዮጵያ ህልውና ከምኒልክ ይበልጥብኛል” ብለው ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩአትን አገር ዛሬም በርካታ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የጋምቤላ፣ የሶማሌ፣ የአፋር ልጆች በወያኔ ጥይት ተደራርበው እየወደቁ “ደምህ ደሜ ነው” እያሉ የያዙትን አገር “ኢትዮጵያ ትበተን” የሚል ከንቱ ቢያናፋ ለሺህ ዓመታት የኦሮሞ አባቶቻችን የአቆዩአትን የኢትዮጵያን ታሪክ በጥገኝነት ዕድሜውን የሚገፋበትን አገር ያህል እንኳ የማያውቅ መሆኑን ያስገነዝበናል።

አማራው መደራጀት አለበት የሚለው ሃሳብም አሁን አየሩን ሞልቶታል። የአማራው በአማራነቱ ብቻ እየተነጠለ መገደል፣ መታሰር፣ መሰደድና መዘረፍ የቆጫቸው ወገኖች በአማራነት ተደራጅተው ለህልውናው መታገል አለብን የሚሉ ወገኖች መነሳታቸው የሚደገፍ ነው። የኦሮሞው፣ የሶማሌው፣ የአፋሩ መብት ይከበር የሚሉ እስከአሉ ድረስ የአማራው መብት ይከበር ብሎ መነሳት ነውር የለውም። እውቁ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስና በርካታ ኢትዮጵያውያን ለአማራው ሲጮሁ መስዋዕት መክፈላቸውን ልንዘነጋውም አይገባም። ከዚህ በተፃራሪ ነውር የሚሆነው አጥፊ የሆነ ፅንፍ ይዞ ትናንት አማራው ለኢትዮጵያ የከፈለውን መስዋዕትነት ትቢያ ላይ በመጣል “ኢትዮጵያዊነት” አስጠቅቶናል በሚል ሰበብና ድንክ ሃሳብ አማራው አሁን በደረሰበት ጥቃት ምክንያት ኢትዮጵያዊነቱን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶ ወያኔና እነሱ በሰፉለት ጠባብ የጎሣ ጎጆ እንዲገባ መከጀል አማራን አለማወቅና ከወያኔ በከፋ በአባቶቻቸው አጥንት ላይ መረማመድ መሆኑን ሊያውቁት ይገባል። እነዚህ ጠባቦች ሰሚ ካገኙ አማራን ከአማራነት አውርደው ወደ መንደር፤ ከመንደር አውርደው ወደ ቤተሰብ፤ በመጨረሻም ወደራሳቸው ግለኛ ፍላጎት እንደሚወስዱት ታሪክን በመፈተሽ ልንዳክር አይገባል። ህወሓት ብዙ ዋጋ እየከፈልን ያለንበት ጥሩ መማርያ ናሙናችን ነው። ተነሳሁ ያለው ለትግራይ ሕዝብ መብትና ነፃነት ነው። እየወረደ የአድዋ፣ የሽሬ ... ወዘተ ከዚያም የመለስ፣ የስብሃት፣ የአባይ ወልዱ ቤተሰብ እያለ የህወሓት ወፍራም ድመቶች ግለሰባዊ አምባነንነት ሕያው ሞዴል እያየን ነው። የዘረኝነት ወይም የጎሣ ፖለቲካ የመጨረሻ ውጤት ፎርሙላ ይሄው ነው።

በኦሮምኛ “ኢትዮጵያ ብትኔሽና” ብሎ ለንደን ላይ የተናገረው ወንድማችን በስብሰባው የተሳተፉትንና ብዙ ኢትዮጵያውያንን አበሳጭቷል። መበሳጨት መፍትሔ አይሆንም እንጂ፤ ለኢትዮጵያዊነት ሲሞት የኖረውን የአማራ ሕዝብ ታሪክ ወደ መንደር ካልወረደ ብለው በኢትዮጵያዊነት ላይ የዘመቱ ዘመነኛ አማሮች “ኢትዮጵያ ትበተን”ን በአደባባይ ባይናገሩትም ኢትዮጵያዊ አቋም አለው በሚሉት ላይ ሁሉ የሚወረውሩት ነውረኛ ተራ ዘለፋ “ብትኔሽና” መሆኑን ለማወቅ አይከብድም። ለመሆኑ ይህንን አቅማቸውን ስለአማራው ሰቆቃ፣ ስለሌላውም ኢትዮጵያዊ መከራ ለማብራራትና እየተዋደቀ ላለው አማራና ሌላውንም በማገዝ የአገርና የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠላት የሆነውን ወያኔን ማዳከም ሲችሉ ጦር ሰብቀው ሌላው ላይ ለመዝመት ምን አደከማቸው። ለዚህማ ወያኔ መች አነሰ? እየረዱ ያለው ለሱ መሆኑ ረሱት ወይንስ በፔሮሉ ውስጥ ገቡ?

ቴክኖሎጂው ያስገኘልንን የሶሻል ሚድያን መድረክ ጠቃሚነት ጨለማን ተገን አድርገው ሃሳባቸውን ለሕዝብ ለማድረስ ሲታገሉ የሞቱትን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሕዝብ ልጆች ስናስታውስ የመስዋዕታቸውን ከባድነትና ለዚህ የደረስነውን የእኛን መታደል አጉልቶ ያሳየናል። ሁሉም በጎ ነገር ለበጎ የሚያውሉ ያሉትን ያህል እኩያንም ለእኩይ ሥራቸው መጠቀምያ ያደርጉታል። የተደራጁም ሆኑ በነጠላ ያሉ ፅንፈኞችን ወያኔ ካሰማራቸው ተቀጣሪዎች ተደብለው የሕዝቡን የትግል አቅጣጫ ለማስቀየር በሶሻል ሚድያው መድረክ ብርቱ ትግል ላይ ናቸው።

ሁሉንም ዓይነት ፅንፈኞች ለምንመኛት፣ በመግባባት ላይ ለተመሰረተች፣ የሁላችን የሆነች ኢትዮጵያ መገኘት እንቅፋት ናቸው። የሌላውን ስም በጥፋትና በወንጀል የራሳቸውን ትልቅነት የገነቡ ይመስላቸዋል። ስለአገርና ሕዝብ አንድነት፣ ስለፍቅር፣ ስለበጎው ታሪካችን የሚናገርን ሁሉ አንገት ለማስደፋት የወያኔን ያህል አጥብቀው ይደክማሉ። ጫጫታቸው ጊዜአዊና በእውነት ላይ የተመሰረተ ስለአልሆነ እውነትን ጨብጦ መቋቋምና ስህተታቸውን ማሳየት ያስፈልጋል።

ቢሊየነሩ ትራምፕ፣ ሂላሪ ሆኑ ኦባማ የተለዋወጧቸውን የምርጫ ዘመቻ ቃላት እናስታውስ። ያ ሁሉ መወጋገዝና መዘላለፍ ከአገራቸው ህልውናና ዘላቂ ጥቅም በላይ ስለማይሆን አሜሪካንን በተመለከተ አንድ ላይ ይቆማሉ። ግለሰብ ዜጎች ትልቅ ሲያስቡ ነው አገር ትልቅ የምትሆነው። የእኛ ትንሾች አገርንም ከነሱ በታች ትንሽ እንድትሆን ያውጃሉ። “የቤቴ መቃጠል ለትኋኑም በጀ” እንዳለው ቂል የጋራ ቤታችንን ኢትዮጵያን አቃጥለው አመዷ ላይ ራሳቸውን የሚፈልጉ እብዶች ናቸው።

“ታሪክ እናውሳ ብንል ብዙ በደሎች ተፈፅመውብናል። አገዛዞች ያደረሱብን በደሎች ተዘርዝረው አያልቁም። ያም ሆኖ የአፋር ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ማንነቱ ጥያቄ ውስጥ ወድቆበት አያውቅም። በጭራሽ።” ብለዋል ዶክተር ኮንቴ ሙሳ። በአንድ ቀን ብቻ ከአራት መቶ በላይ ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው በወያኔ የተጨፈጨፉባቸው ኦባንግ ሜቶና ባልደረቦቹ “ከጎሠኝነት ሰብዓዊነት ይቅደም!” አሉ እንጂ ኢትዮጵያዊነታቸውን ለድርድር አቅርበው አያውቁም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ባለትልቅ ድርሻ የሆኑትን የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ተበደሉ የሚል “ዓላማ” ያነገቡ ወገኖች የሕዝባቸውን ትልቅ የታሪክ ድርሻ ትቢያ ላይ ጥለው ኢትዮጵያዊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡት ሕዝባቸው ከአኝዋኩ፣ ከአፋሩ፣ ከጉራጌው የበለጠ ተበድሎ ሳይሆን የወያኔ መኳንንት በትግራይ ሕዝብ ስም ዛሬ የያዙትን ሥልጣንና ጥቅም እነሱም በሚጠሩት ሕዝብ ስም ለመያዝ መሆኑ ግልፅ ነው።

የማከብረውን የአቶ አሰፋ ጫቦን አባባ ልጠቀምና ፅንፈኛና ዘረኛ የነገ መኳንንት “በኪሳቸው ትንንሽ ዘውድ” ይዘው ለመንገሥ እየተንቀሳቀሱ ነው። በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የአባቶቻቸውን የዘመነ መሳፍንት የጨለማ ጊዜ ሊያመጡልን ይቧችራሉ።

ትግሉ ዛሬ መልኩን ቀይሯል። በተወሰነ ጥቅምና ዓላማ ዙርያ የተሰበሰቡ ቡድኖች በአዳራሽ፣ በጠረጴዛ ዙርያ ወይንም ከኮምፒዩተር ጀርባ ሆነው ሕዝቡን የሚመሩና ለመስዋዕትነት የሚማግዱበት ጊዜ አይደለም። ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ ሕፃናትና እናቶች ሳይቀሩ በወያኔ አረር እየወደቁ፤ ብዙ መቶ ሺዎች በእስር እየተማገዱ፤ ጫካ የገቡትም በጎበዝ አለቃ እየተደራጁ አጋዚን ጥለው እየወደቁ ባለበት ሰዓት ትግሉን እንደማገዝ አየሩን በጥላቻና በዘረኝነት መበከል የጥቂት ፅንፈኞች ተልዕኮ ሆኗል።

በአገር፣ በሕዝብና በግለሰብ ላይ ጥላቻን የሚያራግቡ ከንቱዎችን ከወያኔ ባልተናነሰ ልንቋቋማቸው ያስፈልጋል። ለሕዝብ መቀራረብ፣ የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የአቅማችንን እናድርግ። ትግሉን እናግዝ። የፅንፈኞችን፣ የዘረኞችን እኩይ ዓላማ እናጋልጥ። የሚሰነዝሯቸውን ከንቱ ሃሳቦች ሁሉ ያለምንም ስጋት እንወያይባቸው። የመሰዳደብ ሳይሆን ተከባብሮ በጨዋነት የመነጋገር ባህል እናዳብር። ካልተነጋገርን መግባባት፣ ካልተግባባን መቀራረብ፣ ካልተቀራረብንም በአንድነት ነፃነት ያለው ሕብረተሰብ መመስረት አንችልም።

አንተነህ መርዕድ
ኖቬምበር 2016 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!