ማስተዋል በለጠ

ሰሞኑን በኢትዮጵያውያን መሃል የገባብን ወያኔያዊ ንፋስ ደግሞ ከሌላው ጊዜ ለየት ይላል። ከአንዱ ንትርክ ወጣን ስንል ሌላ ይተካል፤ “መቃቃርን አስወገድን፤ ወደ አንድነትም መጣን” ብለን ከመደሰታችን በአንዱ አቅጣጫ የካብነውን የሚያፈርስ ነገር ብቅ ይላል። ከለንደኑ የኦሮሞ የሕግ ምሁራን ስብሰባ ወዲህ እስከ አትላንታው የዚያው ስብሰባ ቀጣይ ክፍል ድረስ እየታዬና እየተሰማ ያለው ነገር ደግሞ ለብዙዎቻችን እምብዝም የሚጥም አልሆነም። ይሁንና ነገር ሁሉ ለበጎ ነው እንዲሉ ብዙ መረበሽ ያለብን አይመስለኝም። ሁሉም ነገር በጊዜው እየተፍረጠረጠ መውጣቱ ለቁስሎቻችን በአፋጣኝ መጥገግና ማንን ከማን ለይተን መጠጋት ወይ መራቅ እንዳለብን ለማወቅ ይጠቅመናል።

በርዕሴ የጠቀስኩትን አማርኛ-ነክ እንግሊዝኛ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ሰሞኑን በኦኤምኤን ቲቪ በተላለፈ አንድ የአማርኛ ዝግጅት ላይ ዶ/ር ፀጋየ አራርሣ ሲናገረው ነው። ቲቪውን የከፈትኩት ፕሮግራሙ ከተጀመረ በኋላ ቢሆንም ዶክተሩ ለምን እንደዚያ እንዳለ ገብቶኛል። የኦሮሞ ምሁራኑ ሲወያዩ የነበሩት ኢትዮጵያን ከአማርኛና ከአማሮች ጋር ከሚያቆራኙ ባህላዊና ትውፊታዊ ዕሤቶች እንዴት ማለያየት እንደሚቻል ይመስኛለል። ከዐውድ ውጭ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ለመታረምም ሆነ ለመማርና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ከልብ ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ነኝ። ወደተነሣሁበት ከመግባቴ በፊት ግን የኦሾን መጽሐፍ ሳነብ ያገኘኋትንና በጣም ደስ የምትለኝን አንዲት አጭር ትርክት ላስታውስ።

ሁለት ወይ ሦስት የሂንዱይዝም እምነት ተከታይ የሆኑ ወንዶች መነኮሣት ወደ አንድ አካባቢ በመሄድ ላይ ሳሉ አንድ ወንዝ ዳር ይደርሳሉ። በነዚህ መነኮሣት ኃይማኖታዊ ቀኖና መሠረት ወንዶች ሴቶችን መንካትም ሆነ መጨበጥ ክልክል ነው። እነዚያ ሦስት መነኮሣት ከአፍ እስከ ገደፉ ከሞላው ወንዝ አጠገብ ደርሰው ወንዙን ሊሻገሩ ሲሉ፤ አንዲት ልጃገረድ የሚያሻግራት ሰው አጥታ ስትቸገር ይመለከታሉ። እንዳይረዷት ደግሞ የኃይማኖታቸው ቀኖና ጉዳይ አስቸገራቸው። ከመካከላቸው ግን አንደኛው - የመጣው ይምጣ ከሚል ይመስላል - ሴቲቱን አፈፍ ያደርግና በትከሻው ተሸክሞ የሞላውን ወንዝ ያሻግራታል። ሦስቱም መነኮሣት የመሰላቸውን እያወሩ ብዙ መንገድ ከተጓዙ በኋላ በሆዱ ነገር ይዞ ሲያብሰለስል የቆየው አንደኛው መነኩሤ ያን ሴቲቱን ያሻገራትን መነኩሤ እንዲህ ይለዋል፤ “አንተ፣ ቀኖናችንን አፍርሰህ እንዴት ሴቲቱን በትከሻህ ተሸክመህ ወንዙን ታሻግራታለህ?” ብሎ በአግራሞት ይጠይቀዋል። ተጠያቂው መነኩሤም “አሃ! እኔ እኮ አንዴ ነው ተሸክሜ ወንዙን ያሻገርኳት! አንተ ግን ይሄውና እስካሁንም ድረስ እንደተሸከምካት አለህ” ብሎ ይመልስለታል።

አዎ! ይህ የመነኩሤው አነጋገር አጥንትን ዘልቆ የሚገባ ትልቅ የፍልስፍና አነጋገር ነው። ነገር እንዳላበዛ እንጂ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም የሥልጣን ዘመን እርሳቸው እንደፈጸሙት ሲወራ በጊዜው የሰማሁትና ወደዚህ ታሪክ የሚቀርብ አንድ የኮሎኔሉ ገጠመኝ አለ።

በመሸታ ቤት ውስጥ ሰዎች ተሳክረው አንደበታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው በነበረበት ወቅት አንድ ሰው ኮሎኔል መንግሥቱን “ባሪያ” ብሎ ይሳደባል አሉ። አንደኛው መሸተኛ ደግሞ እርሳቸውን የሚወድ ካድሬ ኖሮ ነቃሽ ቆጥሮ ፋይል ከፍቶ ክስ ይመሠርታል። ክሱ ከባድ መሆኑ ግልጽ ነው። ያ ክስ በይግባኝ ሲገለባበጥ ከርሞ በታች ፍ/ቤቶች ለመፍረድ ከባድ ይሆንና እርሳቸው ዘንድ ይደርሳል - ዙፋን ችሎት መሆኑ ነው። እርሳቸውም - ኮሎኔል መንግሥቱም ማለት ነው - ከሳሽንና ተከሳሽን አስቀርበው በመስቀለኛ ጥያቄ የክሱን እውነትነት ካረጋገጡ በኋላ እንዲህ አሉና ክሱን ዘጉት ይባላል፡- “ተከሳሽ በመጠጥ ኃይል ተገፋቶ አንዴ በመሳደብ ስሜቱን ተወጣ። ከሳሽ ግን እኔን የጠቀመና የሚሾም የሚሸለም መስሎት በየፍርድ ቤቱ ሲያስቅብኝና ስሜን ሲበክል፣ ሰድቦ ለሰዳቢ ሲዳርገኝም ከረመ። ስለዚህ ጥፋተኛው አንዴ የሰደበኝ ሣይሆን ስድቤን ላልሰማው ሁሉ ሲያሰራጭ የነበረው ከሳሹ ነውና፤ እኔ የምፋረደው እርሱን ነው።” ... ትልቅ ብልኅነት ነው። አስተዋይ ማለት እንዲህ ነው። ይህን ታሪክ በርግጥም ኮሎኔሉ ፈጽመውት ከሆነ በበኩሌ በጣም አደንቃቸዋለሁ።

አማርኛ በአማርኛነቱ ምንም ጥፋት የለበትም። “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” እንዲሉ ሆኖ እንጂ፤ አማርኛን እየተናገሩ ከፍተኛ የአስተዳደር በደልና ጥፋት ያደረሱ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አማሮች ብቻ እንዳልነበሩ በተደጋጋሚ ተነግሯል። በመቶም ይሁን በሦስት ሺህ ዓመታት ኢትዮጵያን ለመሥራት ታላቅ አስተዋፅዖ ካደረጉ ዘውጎች መካከል እርግጥ ነው አማሮችም የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል፤ ይህ ተግባራቸው ደግሞ ሊያስመሰግናቸው እንጂ ወያኔን የመሰለ አገራዊ ነቀዝ ተፈጥሮ በክተት ዐዋጅ ከምድረ ገጽ ሊያስጠፋቸው ባልተገባ ነበር። ይህ ዓይነቱ የመንግሥት ግንባታ ሂደት ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የተወሰነ ሣይሆን ዓለም አቀፍ ሂደት ነው። የጣሊያኑ ጋሪባልዲ - ለምሣሌ፣ 37 ወይ 38 ብጥቅጣቂ ግዛቶችን ወደ አንድ አማክሎ አንዲት ኃያል አገር ልትፈጠር የቻለችው በተዓምር ሣይሆን ዐመጠኛን በጉልበት አስተዋይን በብልኃት አሳምኖ በማስገበር ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የተፈጸመ አዲስ ታሪክ የለም። እነ አፄ ምንሊክም ያደረጉት ይህንኑ ነው።

ቋንቋን በሚመለከት አንድ ቋንቋ በምን በምን ምክንያቶች ብሔራዊ ወይም የሥራ ቋንቋ ሊሆን እንደሚችል ማጥናትና እውነቱን መረዳት ይገባል። በእርግጠኝነት ለመናገር ግን በአሁኑ ወቅት አማራ የሚባሉ ዜጎች ቋንቋቸው የኢትዮጵያ የሥራም ይሁን የኦፊሴል ቋንቋ እንዲሆንላቸው በሰላማዊ መንገድም ይሁን በትጥቅ ትግል የጠየቁበት ሁኔታ በታሪክ አልተመዘገበም። ይህን ሁሉ የመከራ ዶፍ ያዘነበባቸው ብቸኛ ነገር ሲጤን ቋንቋው ሣይሆን እነሱ ራሳቸው ለዚህች ሀገር የነበራቸውና ያላቸው ፍቅር ነው። ተደጋግሞ እንደተባለው አማራ የተጎዳው በኢትዮጵያዊነቱ ነው። አማራነትን በኢትዮጵያዊነት የጋለ ብሔራዊ ስሜት በመተካቱ ምክንያት በብቸኝነት ሊጠቃ ችሏል። አማራ የሚያኮርፍበት ዘውጋዊ ማንነት አልነበረውም። በአማራነት መደራጀትንም ቢያንስ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሲጠየፈው ቆይቷል። የሚጠየፈውም አማራነቱን ጠልቶ ወይም በአማራነቱ ሳያምን ቀርቶ ሳይሆን፤ ከብሔራዊው አስተሳሰብ ይልቅ በጎሣና በነገድ መደራጀት አጠቃላይ ስብዕናንና የአንድ አገር ዜግነትን ስለሚያጫጫ ወይም ስለሚያኮስስ ነው። አዲስ ነገር በቀላል አይለመድም። ...

ዶ/ር ፀጋየ የሚለን ከፍ ሲል አማራነትን፤ ዝቅ ሲል ደግሞ አማርኛን እናጥፋ ነው። አማራን ማጥፋት የሚቻል አይመስለኝም (እንደታዘብኩት አማራና ሸምበቆ በቆረጧቸው ቁጥር የሚበዙና በድብቅም ቢሆን የሚለመልሙ ይመስለኛል)። አማራን ለማጥፋት ብዙ ተሞክሮ አልሆነምና ከዚህ ቅዠት በመውጣት በፍቅርና በመተሳሰብ መኖሩ ሳይሻል አይቀርም። አማርኛን ግን ማጥፋት ይቻላል። ግን ምትክ ማዘጋጀት መቅደም አለበት። “የዛሬውስ ብርድ አጭር ሴት ያስታቅፋል” ቢል አንዱ፤ “አጭር ሴትስ ብትሆን ቀድመው ካላዘጋጁዋት አሁን ከየት ትገኛለች” ብላለች አሉ - ማፍቀሯን ገልጣለት በአጭርነቷ ሳቢያ ቀደም ሲል ፊት የተነሣች አፍቃሪ - ተረት እንዳረጉት ነው መቼም። እናም አካሄዳችን በጥበብ ይሁን። ሕዝቡን ከባቢሎን እናውጣው እንጂ ወደባቢሎን ግንብ አንውሰደው። መማራችን ሊጠቅመን ሲገባ ይብስ ሊያደነቁረን አይገባ። የመማር አንዱ ምልክት ደግሞ ሆደሰፊነትና መረጃን አጣርቶ ሐሰትን ከእውነት መለየት መቻል ነው። በስሜት መነዳት ወደ ገደል ይጨምራል።

በዓለም ውስጥ - ቆይ አንዴ ጉግል ላድርግማ - አዎ፣ በዓለም ውስጥ 7106 ቋንቋዎች በሰባት ቢሊዮኑ የምድራችን ነዋሪዎች እንደሚነገሩ የ2014 አንድ መረጃ ይገልጻል። ከነዚህ ውስጥ ከ83 እስከ 90 የሚደርሱ ቋንቋዎች በአገራችን እንደሚነገሩም ይገመታል። የአንድን ጎሣ ወይም ነገድ አንድን ቋንቋ ተናጋሪነት ያየን እንደሆነ በዓለም እንደመንደሪን (ቻይንኛ ነው)፣ በኢትዮጵያ ደግሞ እንደኦሮሚፋ ብዙ ሕዝብ የሚናገራቸው ሌሎች ቋንቋዎች የሉም። የቻይናው መንደሪን ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ የማያንስ፣ የኢትዮጵያው ኦሮሚፋ ደግሞ ከ30 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ተናጋሪዎች እንዳሏቸው የድረገጽ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የነዶ/ር ፀጋየ “ስህተት” መባቀያ እንግዲህ እዚህ ላይ መሆን አለበት። “ኦሮሚፋን የሚናገረው የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝብ ከሚገመተው በላይ ብዙ ሆኖ ሳለ ከርሱ ያነሰ የተናጋሪ ቁጥር ያለው አማርኛ ለምንና እንዴት የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ ሊሆን ይችላል?” የሚል ይመስለኛል የብዙዎች “ራስ ምታት”። ነገር ግን የቋንቋን ባሕርይ ካለመረዳት የሚመነጭ የሞኝ ጥያቄ ነው። እንደኔ እንደኔ አማርኛ ዕረፍት ቢወጣና ኦሮሚፋም ሆነ ሌላ ቋንቋ ተተክቶ “የቀባጭ ምሱን” ቢያገኝ ደስ ባለኝ ነበር። ግን ይህም አይሆንም። ለምን ቢባል የቋንቋ ልደትና ዕድገት እኛ በስሜት እንደምንፈነጭበት የውቂው ደብልቂው የጉሽ ጠላ ስካር አይደለምና።

ይሄውልህ - የነፀጋየ ትክክለኛ የሚመስል ግን ከቋንቋ ዕድገትና ተፈጥሮ ጋር የሚጋጭ አስተሳሰብ እውነትነት ቢኖረው ኖሮ በአሁኑ ሰዓት መንደሪን የዓለም ቋንቋ በሆነ ነበር። 335 ሚሊዮን ሕዝብ አካባቢ በአፍ መፍቻነት የሚናገረው እንግሊዝኛ፣ አንድ ቢሊዮን አካባቢ ሕዝብ በአፍ መፍቻነት የሚናገረውን መንደሪንን “በልጦ” የዓለም ቋንቋ ሊሆን የቻለው በዐዋጅና በቀላጤ ሣይሆን፤ በራሱ በሥነ ልሣን ደንብና ሥርዓት ነው። ይህ ዓይነቱ ሂደት የአንድ ወይ የሁለት ትውልዶች ሥራም አይደለም። የፍላጎት ጉዳይም አይደለም። የፍላጎት ጉዳይ ቢሆን ኖሮ አፄ ዮሐንስና አቶ መለስ ዜናዊ ለምን በትግርኛ አላስተዳደሩም ነበር? የኦሮሞው የ(?) ጉዲሣ የልጅ ልጅ (ማዕረጋቸውን ስላላወቅሁ ነው ይቅርታ) አፄ ኃይለ ሥላሤና ፕሬዝደንት መንግሥቱ ኃ/ማርያም እንደኦሮሞነታቸው ለምን በኦሮሚፋ አልገዙም? ስላልፈለጉ አይመስለኝም - ስላልቻሉና ስለማይችሉም እንጂ።

የንግድ ልውውጥ፣ ኃይማኖት፣ ቅኝ ግዛት፣ የኢኮኖሚ ግንኙነት፣ ማኅበራዊና ማኅበረሰብዓዊ ተራክቦ፣ ድምበር ዘለል ጦርነት፣ ባህላዊና ሥነ ልቦናዊ ትስስር፣ ወዘተ ... ለአንድ ቋንቋ መስፋፋትም ይሁን መቀጨጭ ያላቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ጥናቶች ይገልጻሉ። ከዚህ ውጪ በተናጋሪ ብዛት፣ ለሌሎች ባለን ጥላቻና ቂም በቀል፣ በቅናትና በሤራ፣ ለራስ ቋንቋና ባህል በሚኖር የተለየ ግምትና አምልኮታዊ ፍቅር፣ ወዘተ ... አንድን የነበረ ነገር እንዳልነበር ለማድረግ ብንሞክር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ይህን ደግሞ ማስተዋል እያቃተን እንጂ ባለፉት 25 ዓመታት በብዙ ወጪ ተምረናል።

ዛሬ ጧት ካዳመጥኳቸውና ካነበብኳቸው ውስጥ በጣም የመሰጡኝ ሁለቱ ናቸው። አንዱ ገብረ ፃዲቅ አበራ የሚጽፈው የኢሳቱ የሃሳብ መንገድ ሲሆን፤ ሌላው ፕሮፌሰር መስፍን የጻፉት ወቅታዊ መጣጥፍ ነው። እነዚህ ሁለቱ አሁን እኔ ከምለው ጋር በጣም ይመሳሰላሉ። ጋበዝኳችሁ።

እናላችሁ በበኩሌ የነፀጋየ ፍላጎትና ምኞት ቢሳካ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ነገር ግን ከወጣትነት ወይም ከስሜታዊነት ወይም ምናልባት የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች የዘመናት የመከፋፈያ ስብከት ከማዳመጥና በሱም ከመሸነፍ አንፃር ሊሆን ይችላል አንዳንድ ወጣት ዜጎች በባዕድ ንፋስ እየተወሰዱብን የሚሠሩ ሥራዎችን እያጠለሹ ናቸው። አሠርን ስንል የሚፈቱ፣ ቋጨን ስንል የሚተረትሩ አንዳንድ ማኅበረሰብዓዊ ጉዳዮች ሊኖሩ የቻሉት በነዚህ የሰው ችግር በማይገባቸው ልጆቻችን ነው። እዚሁ እኛው ጋ ቢኖሩ ችግራንን ያውቁልን ነበር። እነሱ ግን በሞቀ ቤትና ሁሉም ነገር በተሟላለት ከባቢ ስለሚኖሩ የኛ ብሶትና መከራ አይታያቸውም። ከወለጋ የመጣ ጎልማሣ የጋራ መግባቢያ ቋንቋን ባለማወቁ ምክንያት አዲስ አበባ ላይ እንዴት እንደሚቸገር እኔ አውቃለሁ - ለምሣሌ፤ ያንን ክፍተት ማን ይሙላለት? የራሱን ቋንቋ ኦሮሚፋን ይዞ አማርኛን ቢያውቅ ግን ከ83 እስከ 90 ከሚገመተው የኢትዮጵያ ዘውግ ጋር መግባባትና የትም ሄዶ የዕለት እንጀራውን ማሸነፍ ይችላል።

ፕሮፌሰር መስፍን ከፍ ሲል በጠቀስኩት መጣጥፍ እንዳሉት የብዙ ደመሞቃት ዘውገኞች ችግር ነገሮችን ሁሉ ከአማራና ከኦሮሞ ወይም ከትግሬ ጋር ብቻ ማገናኘታቸው ነው። ጉራጌውስ? ከምባታውስ? ኮንሶውስ? ጠምባሮውስ? ሐረሪውስ? ሃዲያውስ? ... እነዚህም እኮ ከሌሎች ጋር መግባባት አለባቸው፤ ሁሉም እኩል የእምዬ ኢትዮጵያ የዘጠኝ ወር ልጆች ናቸው። ሁሉም ዜጋ 90 ቋንቋ ያጥና እንዳይባል ደግሞ የምድር ኑሯችን እንኳንስ 90 ቋንቋ ሁለትና ሦስትም ለማጥናት የማትበቃ ቅጽበታዊ ናት፤ ይህ እሳቤ ተምኔታዊ ነው። ለዚህች ቅጽበትም ነው እንግዲህ እንዲህ የምንጨቃጨቀው - ነገ ትተናት ለምንሄደው። ለምን ሰፋ አድርገን አናይም? ሕዝቡ እንዴት እንደሚኖር ለምን ራሳችንን ከየሰቀልንበት ቆጥ ወደ መሬት አውርደን እውነቱን አንገነዘብም? ለመሆኑ የአሁኑ ችግራችን ቋንቋ በተለይም አማርኛ ነው ወይንስ ግፈኛውና ዘረኛው የሕወሓት አገዛዝ እያደረሰብን ያለው በደል ነው? ለምንድን ነው “በቅሎ አባትሽ ማን ነው” ስትባል “እናቴ ፈረስ ነች” በሚል ቅኝት እየተነዳን ሕዝብን ለተጨማሪ ሰቆቃና ሰው ሠራሽ ግጭት ለመዳረግ የምንቋምጠው - ለዚያውም ራሳችንን ከጠቡ አምባ በሺዎች ማይሎች አርቀን ሰላማዊ ቦታ እየኖርን። ግፍ እንፍራ እንጂ! ለልጆቻችንም እናስብ እንጂ!

አማራንም ሆነ አማርኛን ማጥፋት የምትፈልጉ ሁሉ በወያኔ ተሸንፋችኋል ወይም ልዩ ተልዕኮ አንግባችኋል። በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢው ጥያቄ የወያኔ አፓርታይድ ሥርዓት መሆኑን ሁሉም እያወቀ፤ የሌለ ችግር እንዳለ በማስመሰል ሕዝብን በተለይም ወጣቱን በማይጨበጥ የተስፋ ቃል ስሜቱን በመያዝ ለማማለል መሞከር ዛሬ ቢቀር ነገ በታሪክና በትውልድ ያስጠይቃልና “ሰከን” ማለት ይገባል። ኦሮሞና አማራም ይሁኑ ትግሬና ሌላው ሕዝብ ለሺዎች ዓመታት አብረው በመኖራቸው አንድን የመከራ ዘመን እንዴት እንደሚያልፉት ያውቁበታል። የፖለቲካ ድርጅቶችና መንግሥታት ግን እንደጥላ የሚያልፉ ጊዜያዊ ኑባሬያት ናቸው። ስለዚህ አሁን የስሜት ፈረስ እየጋለባችሁ በሕዝባችን ዘንድ የነገር ሽብልቅ የምትቀበቅቡ ዜጎች ወደ ኅሊናችሁ ተመለሱ። በምታደርጉት አፍራሽ ነገር የተወሰነ ሥነ ልቦናዊ እርካታ ታገኙ ይሆናል፤ የተወሰኑ ዜጎችን ልብ በማሸፈት መጠነኛ የነፃነታችንን መጓተት ልትፈጥሩ ትችሉ ይሆናል። ከወጪ ቀሪ ግን በመጨረሻ የምትከስሩትና በመጥፎ አስተዳደጋችሁ፣ በማይረባው አፍራሽ ስብዕናችሁ የምትወቀሱት እናንተው ናችሁ።

ለኢትዮጵያ ነፃነት ስትሉ የሞቀ ሕይወታችሁን ጥላችሁ በዱር በገደል የምትንከራተቱ ውድና ብርቅዬ ልጆቻችንን እግዚአብሔር ይጠብቃችሁ፤ ከጎናችሁ ሆኖ ለድል ያብቃችሁ። በቅርብ ይቅናቸሁና መጪውን ብሔራዊም ይሁን ኃይማኖታዊ በዓል በጋራ እየተደሰትን ለማሳለፍ ያብቃን። ለአንድዬ የሚሣነው ነገር የለምና የመከራ ደብዳቤያችንን አሁኑኑ ቀዳዶ ይጣልልን። ለጠላቶቻችንም ልብ ይስጥልን።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!