የትነበርክ ታደለ

King Mohammed VI and PM Hailemariam

ሰሞኑን የሞሮኮው ንጉሥ ወደ አገራችን ጎራ ማለታቸው አንድ አዲስ ዜና እንድንሰማ አድርጎናል። ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የ2.4 ቢሊየን ዶላር ስምምነት ተፈራርመዋል። የ2.4 ቢሊየን ዶላር የማዳበርያ ፋብሪካ ለማቋቋም ነው ስምምነቱ። ጠቅላላ ኢንቨስትመንቱ 3.7 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል ነው የተባለው። እ.ኤ.አ. በ2022 ሲጠናቀቅ በዓመት 2.5 ሚሊየን ቶን ማዳበርያ የሚያመርተው ይህ ፋብሪካ የአገሪቱን የማዳበሪያ ፍላጎት ያሟላል ተብሏል።

ይህ ጥሩ ዜና ነው። የኔ ጥያቄ ግን ከዚህ ወጣ ይላል። በየጊዜው የሚፈረሙ ፕሮጄክቶችን ቀንና ማታ እንደ መረጃ ከማሰራጨት ጎን ለጎን ከዚህ ቀደም የነበሩትን ሁነቶች እያስታወሱ መጠየቅ የዜግነትም የሙያም ግዴታ ይሆናል። ከዚህ አንጻር የሚከተሉትን ነጥቦች ለማንሳት ፈለኩ።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ማዳበሪያ በአገራችን መሬት ላይ መዋል የጀመረው እ.ኤ.አ. 1960ዎቹ ማብቅያ ላይ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዩሪያና ዳፕ የተሰኙ ሁለት የማዳበሪያ አይነቶች ብቻ በገበሬው ማሳ ላይ ሲፈስ ዛሬ ደረስን።

(ማዳበሪያዎች እንዴት ወደ ሀገር ይገባሉ? በየትኞቹ ክልሎች በምን ይሰራጫሉ? ገበሬውስ በምን አይነት ሁኔታ ነው ማዳበሪያዎቹን የሚቀበለውና ጥቅም ላይ የሚያውለው? ዋጋውስ? ... ወዘተ የሚሉትን ቁም ነገሮች ወደ ጎን ትተን አንድ ጉዳይ እናንሳ)

ከላይ እንደገለጽኩት በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች በሁሉም የአፈር አይነቶች ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው የማዳበሪያ አይነት ሁለት ነው። ዳፕና ዩሪያ።

አፈር እንደ አየር ጸባይ፣ ለአገልግሎት በቆየበት ጊዜና እንዳገለገለው የሰብል አይነት እንዲሁም በመሬት አቀማመጥ ገጽታው የተነሳ የተለያየ ንጥረ ነገር (nutrient) እንዳለው የታወቀ ነው። ይህም ማለት ደቡብ ክልል ያለው የአፈር አይነት የያዘው ንጥረ ነገርና በምስራቅ ያለው የአፈር አይነት ይለያያል ማለት ነው። በሌላውም ክልል እንደዝያው። እና ይህን ያህል የሚለያይ የአፈር አይነት ላይ ሁለት አይነት ማዳበሪያ መዝራት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ያውም ከዓመት ዓመት ...

የሆነ ሆኖ የግብርና ሚኒስቴር ይህንን ችግር ይቀርፉልኛል ያላቸውን ሥራዎች እየሠራ እንደሆነ ከነገረን ሰነበተ። ከአምስት ዓመት በፊት በአፋር ክልል የተገኘውን ፖታሽ ተጠቅሜ የተለያዩ ውህድ ማዳበሪያዎችን (Blended fertilizers) በፋብሪካ እቀምማለሁ። ለዚህም ከ12 በላይ ፋብሪካዎችን በየክልሉ አቋቁማለሁ። እ.ኤ.አ. በ2014 በሁለት ሺህ የገበሬ ማሳዎች ላይ ሙከራ አደርጋለሁ ብሎ ሥራ መጀመሩን የምስራች እንዳለን አልዘነጋነውም።

ለዚህም ሥራ አላና ፖታሽ የተባለ ድርጅት ዋስትና ወስዶ ማዳበሪያዎቹን ለመቀመም የሚያስችል ፖታሽ ከአፋር ክልል እያመረተ እንደሚያቀርብ ፊት አሳላፊ ሆኖ ቀረበ። ግን 2014 እንደ ቀልድ አለፈና የተባለውም ቀረና በ2015 አላና ፖታሽ ሥራውን ለእስራኤል ኩባኒያ ሸጦ ተፈተለከ። አካፋውን ከአላና ፖታሽ የተቀበለው የእስራኤል ኩባንያም እንዲሁ በቅርቡ በአገሪቱ ውስጥ የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ሰበብ አድርጎ እብስ አለ።

... አሁን ስለነዚህ የማዳበሪያ ቅመማ ፋብሪካዎች ማንም ምንም ያለን ነገር የለም። ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም። የተፈረሙ ፊርማዎች ሊሰረዙ ይችላሉ፣ ሰነዶች ሊቀደዱ ይችላሉ። ነገር ግን የተገቡ ቃል ኪዳኖች በህዝብ ዘንድ እንደቀልድ አይዘነጉም።

ሌላው ጥያቄዬ፤ ይህን ከላይ "እናደርገዋለን" የተባለውን የማዳበሪያ መቀመም ሥራ ለመሥራት የአገሪቱ መሬት የአፈር ልኬት (soil mapping) በቅድሚያ ሊሠራ እንደሚገባ ይታወቃል። በየአካባቢው የሚገኘው አፈር ምን አይነት ንጥረ ነገር እንደጎደለው ሳያውቁ ማዳበሪያ ማምረቱ ተመልሶ እምቦጭ ነውና። ይህ ጉዳይስ የት ደርሶ ይሆን? ከአስር ዓመት በላይ የፈጀው የሶይል ማፒንግ መጨረሻው ምን ሆነ? እምንስ ደረሰ?

ጠቅለል ለማድረግ ያህል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከንጉሥ መሐመድ ጋር ያሳረፏት ፊርማ ይህን ሁሉ ከግንዛቤ አስገብታለች ወይስ ያው የተለመደው አይነት ውልና ስምምነት ነው?

ዘጠና አምስት ከመቶ ያህሉ በተራ የግብርና ሙያ በሚተዳደርባትና የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንቷ ግብርና በሆነባት አገራችን በዘርፉ የሚገቡት ቃሎች፣ የሚፈረሙ ፊርማዎች በዋል ፈሰስ እየሆኑ እንዲቀሩ መፍቀድ ትርፉ ነገም ረሃብ ነው፣ ነገም እርዳታ ነው፣ ነገም ድርቅ ነውና ከወረቀት የዘለሉ ድርጊቶችን አሳዩን።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!