ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

መግቢያ
ያለፉትን 40 ዓመታት ፖለቲካችንን ለመረመረ አገርን በሚመለከት የሚሰነዘሩት አስተያየቶች ወይም የሚሰጡት ትንተናዎች ሁሉ ሳንይሳዊ ይዘት ይኑራቸው አይኑራቸው የሚጠይቅ የለም። በተለይም ፖለቲካ ፍልስፍናዊ መሰረት ያለው ታላቅ ፅንሰ-ሃሳብ መሆኑ ግንዛቤ በሌለበት አገርና፣ ማንኛውም ሕብረተሰብንና የአገርን አጠቃላይ ሁኔታ በሚመለከት ረገድ የግዴታ ሳይንሳዊ ትንተና መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ቀርቶ ስሜት ዋናው መመሪያ በሆነበት አገር የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ትክክል መሆናቸውንና አለመሆናቸውን ቁጭ ብሎ በሰከነ መንፈስ ለመመርመር የሚቃጣ ሰው በፍጹም የለም።

እንደሚታወቀው በተለይም በአብዮቱ ወቅት ሳይንስና ፍልስፍና መመሪያ መሆናቸው ቀርቶ ስሜት የፖለቲካውን መድረክ በመያዙ እንደተከታተልነው ለብዙ መቶ ሺህ ሕዝብ መሞትና ለአገር ውድመት የራሱን አስተዋፅዖ አበርክቶ አልፏል። ዛሬ አገራችን ለምትገኝበት እጅግ አስቸጋሪና አደገኛ ሁኔታ በአብዮቱ ወቅት የተከሰተውና የተካሄደው ስሜት አዘል ፖለቲካ በተለይም የፖለቲካ ተዋናይ ነን የሚሉትን ጭንቅላት በመያዙ ከሳይንሳዊ ትንተናና ውይይት እንዲሁም ክርክር ይልቅ ስሜት በመቅደሙ ሁሉም የሚፈራራና የሚገዳደል ወደ መሆን አበቃ። ይህ ቁስል ዛሬም ያለና ከአብዮቱ የተረፈው የተወሰነ ኃይል ዛሬም ከቂም-በቀል ፖለቲካውና ሰውን ከማስፈራራት ለመላቀቅ ያልቻለ ሆኖ እናገኘዋለን። አብዮቱ ከሸፈና ወደመ ከተባለ ከአርባ ዓመት በኋላም የጭንቅላት ተሃድሶ ባለመካሄዱ የድሮው ዐይነት በተለይም በተንኮልና በቂም በቀል ላይ የተመሰረተው ፖለቲካ የሚሉት ፈሊጥ አሁንም እንዳሰፈሰፈ እንመለከታለን።

ባለፉት 25 ዓመታት በአገራችን ምድር የተንሰራፋውን እጅግ አሳዛኝና አገር አፍራሽ ሁኔታ በምንመረምርበት ጊዜ ዋናው ምክንያት በተለይም በፖለቲካ መድረክ ውስጥ የሚሳተፉት ሰዎች ወይም ድርጅቶች አዕምሮ የቱን ያህል ያልበሰለና መንፈሰ-አልባ መሆኑን ነው የምንገነዘበው። በክርክርና በውይይት ያልታነፀ ጭንቅላት፣ በተለይም ደግሞ ፍልስፍናና ሳይንስን መመሪያው ያላደረገና፣ በየጊዜው አስተሳሰቡንና ድርጊቱን ለመመርመር የማይችል ኃይል የመጨረሻ መጨረሻ የታሪክ ወንጀል ሰርቶ እንደሚሄድ መገንዘብ እንችላለን። ከዚህ ስንነሳ የምንገነዘበው ዋና ሀቅ ለአገራችን መዘበራረቅና ውድመት ተጠያቂው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን የፖለቲካ ኤሊት የሚባለው እንደሆነ መረዳቱ ከባድ አይሆንም።

ስለሆነም በእልክና በአወቅሁኝ ባይነት፣ እንዲሁም ለከፋፍለህ ግዛ እንዲያመች፣ ይሁንና ደግሞ የመጨረሻ መጨረሻ ራሳቸው የተንኮሉ ጠንሳሽ የሆኑ ሰዎችንም ብዙም የማያራምዳቸው በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የብሔረሰብ ክልላዊ አስተዳደር የሚሉት ፈሊጥ አዳዲስና ጭንቅላታቸው ያልበሰለ ወጣቶችን በመፈልፈሉ የፖለቲካውን መድረክ አጣበውታል። አገዛዙና የውጭ ኃይሎች አገራችንን ለማዳከምና ለመበታተን በፈጠሩት የታሪክንና የሕብረተሰብን ህግ ያላካተተ ”ፌዴራላዊ የክልል ፖለቲካ“ ተግባራዊ በመሆኑ፣ በተለይም በዛሬው ወቅት የወያኔ አገዛዝ በሕዝባችን ላይ በሁሉም አቅጣጫ የከፈተውን ጦርነትና በሕዝባችን ላይ የሚፈጽመውን ፋሺሽታዊ ድርጊት ለመዋጋት ኃይላችንን መሰብሰብና በጋራ መታገል ሲገባን የብሔረሰብ-አጀንዳ ሜዳውን በማጣባብ የብዙዎቻችንን አመለካከትና የትግል ስትራቴጂ እየቀየረው መጥቷል ማለት ይቻላል። አገዛዙ የሚያካሂደውን አገር አውዳሚ ድርጊትና በሕዝባችን ላይ የሚፈጽመውን ፋሺሽታዊ ጭፍጨፋ ለማቆምና በአገራችን ምድር ሰላም እንዲመጣ ከመታገል ይልቅ የሁላችንም ፍርሃት ”ይህች አገር ልትበታተን ነው፤ እንዴት አድርገን ነው ይህ ሁኔታ እንዳይከሰት መታገል ያለብን“ በሚለው ላይ እንድናተኩር ተገደናል።

የዛሬውን የተተረማመሰ ፖለቲካ ለራሳቸው ሥልጣን መወጣጫና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር አገራችንን ወደ ልዩ አቅጣጫ ለመውሰድ የሚፈልጉ ኃይሎችና፣ በዚያውም መጠን የድህነቱን፣ የተበዝባዥነቱንና የኋላ-ቀርነቱን ዘመን ለማራዘም የሚፈልጉ ኃይሎች የፖለቲካ ሜዳውን ወጥረው በመያዝ የአብዛኛዎቻችን አመለካከት ሊቀይሩት በቅተዋል። በተለይም ለንደን የተካሄደውና ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ አትላንታ የተካሄደው ”የኦሮሞ መሪዎች ስብሰባ” (Oromo Leadership Convention) የሚባለው ስብስብ ላይ የተሰጠውን ፓለቲካዊና ሳይንሳዊ ትንተና ሳይሆን ከምሁራን የማይጠበቅ ሀተታ-መሳፍንት አብዛኞቻችንን እንድንጯጯህ ሲያደርግ፣ አንዳንዶቻችንን ደግሞ አስደንግጦናል። ይህንን ዐይነቱን ሕብረተሰብን አፍራሽና ኋላ-ቀርትነትን እዚያው ፈርጥሞ እንዲቀር ከሚያደርገው ስብሰባ ላይ የሚሰነዘረውን አስተያየትና በየቴሌቪዥኑም የሚስተጋባውንና፣ የወጣቱን መንፈስ የሚበርዘውን በታሪክና በሳይንስ ያልተደገፈና ሊረጋገጥ የማይችል አመለካከት ካለምንም ርህራሄ መዋጋት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እንደምከታተለው ከሆነ መሪ ነን የሚሉት ሰዎች ጭንቅላት የደነደነ ስለሆነና፣ ለጊዜውም ቢሆን የልብ ልብ ስለተሰማቸው ከእነዚህ ሰዎች ጋር በቲዎሪና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ውይይትና ክርክር ማድረግ በፍጹም የሚቻል አይመስለኝም። ስይንሳዊና የቲዎሪ ክርክርና ውይይት የሚገባቸው አይመስለኝም። ስለዚህም ያለው አማራጭ መንገድ እየመላለሱ ሌላው እንዲረዳው እነሱን በሳይንሱ መንገድ መዋጋቱ ፍቱንና ሊታለፍ የማይችል መሳሪያ ነው ብዬ አምናለሁ።

ችግሩ የዘመናዊነትና የተሃድሶ እጦት ወይስ የብሔረሰብ ጥያቄ!

የብዙ አገሮችን ታሪክና የሕብረተሰብ አገነባብን ታሪክ ለተመለከተ ብዙ ውጣ ውረድ እንደሚያስፈልገው መረዳት ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ ማንኛውም ነገር ከአንድ ሁኔታ በመነሳት እንደየሁኔታው ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረገው ሂደት ውስጥ እየተሰበጣጠረና ከሌሎች ጋር እየተቀላቀለ፣ በዚያው መጠንም የመጀመሪያው አስተሳሰቡ እየከሰመና አድማሱ እየሰፋ ይመጣል። የማደግ፣ የመበሰጣጠርና፣ እንዲሁም ከሌላው ጋር በመቀላቀልና በመጋባት፣ የአስተሳሰብ አድማስን ማስፋት የሚቻለውና እያንዳንዱ ግለሰብም ከተተበተበበት ዕድገትን ከሚያደናቅፍ ወይም ትራዲሺናል ቫልዩ (Traditional Values) በመላቀቅ ራሱን በራሱ ማግኘት የሚችለው በዚያ ሕብረተሰብ ውስጥ በአንዳች ተዓምር ብቅ የሚሉ ግለሰቦች ጥያቄ መጠየቅ ሲችሉና ስርዓቱን መጋፈጥ የቻሉ ከሆነ ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብን ማዳባር በተለያዩ ሕብረተሰቦች ልዩ ልዩ ዐይነት መልክ የያዘ ቢሆንም፣ የበለጠ መዳበር የቻለው በጥንታዊቱ ግሪክና፣ በአውሮፓ ምድር ደግሞ ከአስራአራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል።

ይህ ዐይነቱ ተሃድሶና መሻሻል የበለጠ እየተስፋፋ ሲመጣ በአንድ አካባቢ የሚኖር ሕዝብ በዚያው ባለበት ረግቶ እንዳይኖር ተገደደ። በቴክኖሎጂና በሳይንስ እንዲሁም በከተማዎች ማደግ ምክንያት የተነሳ ከተለያየ ቦታ ፈልሰው የሚመጡ ሰዎች በመኖርና የመፍጠር ችሎታቸውንም በማሳደግ መቋቋም ሲችሉ ከዚያ በፊት የነበራቸውን ውስን አስተሳሰብ አሽቀንጥረው በመጣል ከአዲሱ ሁኔታ ጋር የበለጠ እየተላመዱና ከሌላ ክልል ከመጣው ጋር በመጋባት ራሳቸውን የዚህ ወይም የዚያ ብሔረሰብ አካል ነኝ ብለው ሳይጠሩ የሚኖሩበት አካባቢ አካል መሆናቸውን እየተገነዘቡ መምጣት ቻሉ። የማደግና በሕብረተሰብ ውስጥም ተቀባይነትን የማግኘት ኃይል ሊወሰን የሚችለው እያንዳንዱ ግለሰብና ኩሙኒቲ በታታሪነትና በሰለጠነበት ሙያ ለሕብረተሰቡ በሚያደርገው አስተዋፅዖ ብቻ እንጂ ከዚህ ወይም ከዚያ ብሔረሰብ በመምጣቱ እንዳይደለ ግንዛቤ ውስጥ ተገባ። ከዚህም በመነሳት እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ዕድል ራሱ ወሳኝ መሆኑን ሲገነዘብ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አንዱ ከሌላው የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ሲል የፈጠራ ችሎታውን በማሻሻል ራሱን ማሳደግ የኑሮው ፍልስፍና ድርጎ ለመውሰድ በቃ። በዚህ መልክ ሁሉም በየችሎታው በመሰመራት ሰፋ ላለ የአመራረት ዘዴ ሁኔታዎችን አመቻቸ። የበለጠ ሊያመርት የሚችልበትን የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመፍጠር ራሱን ማሳደጉ ብቻ ሳይሆን፣ ለሕብረተሰብዓዊ ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት ቻለ።

በዚህ መልክ የዳበረው የስራ-ክፍፍልና እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱን በራሱ አግኝቶ ማደግና ራሱን መግለጽ መቻል ቀሰ በቀስ ከዳበረው የፖለቲካ ፍልስፍና አስተሳሰብና ተግባራዊ እየሆነ ከመጣው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በመጣመር የኋላ ኋላ ሕብረ-ብሔር ወይም ኔሽን (Nation) ለሚለው አስተሳሰብ መሰረት በመጣል ለካፒታሊዝም ዕድገት በር መክፈት ቻለ። በሌላ አነጋገር፣ የብሔርና የብሔራዊ ስሜት አስተሳሰብ (Nation and Nation-hood) ቀስ በቀስ ሊዳብሩና መሰረታቸውን ማረጋገጥ እየቻሉ መምጣት ከአስተሳሰብ መዳበር፣ በስራ-ክፍፍል (Division of Labour) ማደግና መስፋፋት ጋር የተያያዙ እንደሆን ብቻ ነው። ለምሳሌ በዘመነ ፊዩዳሊዝም ወይም በከብት እርባታ ላይ ብቻ ተሰማርቶ የሚገኝ ሕዝብም ሆነ ብሔረሰብ እንደ አንድ ብሔር ሊታይ በፍጹም አይችልም። አንድ ሕዝብ ብሔር ሆኖ እንዲጠራ ከተባለ ለስራ-ክፍፍል መዳበርና ለቴክኖሎጂ ግኝትና ምጥቀት አስፈላጊውን መሰረት በመጣል በዚያው መጠንም የአስተሳሰብ መጎልመስን መቀዳጀት መቻል አለበት።

የእኛንና ዛሬ በጎሣና በኃይማኖት የሚተራመሱ አገሮችን ሁኔታ ስንመለከት ያለው ችግር በየጊዜው የአስተሳሰብ ለውጥ ለማድረግ ያለመቻልና ጥያቄ ለመጠየቅ ዝግጁ ያለመሆን ነው። እንደሚታወቀው አንድ ሰውም ሆነ አንድ ሕዝብ ጥያቄ ሲጠይቅ ብቻ ነው መልስ ለማግኘት የሚችለው። እንደሚታወቀው ራስን እየመላለሱ መጠየቅ የሎጂካዊ አስተሳሰብና የሳይንሳዊ ግኝት ዋናው መክፈቻ መንገድ ነው። በተለይም ከሬናሳንስ ጀምሮ ያለውን የአውሮፓውን የህብረተተሰብ ዕድገት ሁኔታ በምንመረምርበት ጊዜ ጥያቄ መጠየቅና ለአንድ ለተዘጋ ነገር መልስ ማግኘት መጣጣር ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ዋናው ቁልፍ ነገር መሆኑን መገንዘብ እንችላለን። ጥያቄዎችን መጠይቅና ራስን ማስጨነቅ፣ እንዲሁም ደግሞ የመከራከር ልምድ በሌለበት አገር ዕውቀትን ከማዳበር ይልቅ ጭቅጭቅና መነዛነዝን ማስቀደም ይቀድማል። ሰለሆነም እያንዳንዱ ግለሰብ ሎጂካዊ በሆነ መልክ በማሰብና ከመከራከር ይልቅ ወደ ንትርክና እንዲያም ሲል ወደ ድብድብ ያመራል። ብዱናዊና ክልላዊ ስሜት ባየለበት እንደኛ ባለበት አገር ደግሞ የባሰውኑ ወደ ጦርነት በማምራት ታሪክን ማፈራረስና ሕዝብን ማፈናቀል እንደሙያ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህም ምክንያት የተነሳ የብሔረሰብ ፖለቲካንም ሆነ ወይም ”ብሔራዊ ፖለቲካን እናራምዳለን“ የሚሉትን ሁሉ በምንም ዐይነት በክርክርና በጥሞና ውይይት ማስተማር፣ መማር፣ ማሳመንና ማመን በፍጹም አይቻልም። ጭንቅላታቸው በተወሰነ አስተሳሰብ ስለተቀረጸና ህይወታቸውም ከመጠርጠር ጋር የተያያዘ በመሆኑ የነገሮችን ሂደት በሎጂካዊ መንገድ ለማሳመን በፍጹም አይቻልም። በደነደነው አስተሳሰባቸው በመግፋት የአገር አፍራሽ ተግባራቸውን በተለያየ መንገድ ያፋጥኑታል። ስለሆነም እየተጯጯሁና እየተደናበሩ መኖር ትግል የሚሉት ፈሊጥ ዋናው ስልት ከመሆን አዳዲስ አስተሳሰቦችን በማዳበር ወደ ፊት መጓዝ በፍጹም አይቻልም። በዚህ ዐይነቱ ትግል በሚሉት ፈሊጥ የኋሊት ጉዞ የሚሄዱ ነው የሚመስለው እንጂ እንደሰለጠነ ሰው በሳይንሱ መንገድ ለመወያየትና ለመከራከር በፍጹም አይችሉም።

ወደ መነሻዬ ልምጣና፣ በአገራችን ምድር ውስጥ የጭንቅላት ተሃድሶና ከዚህ ጋር የተያያዘ ቴክኖሎጂያዊ ለውጥ (Technological Revolution) ባለመካሄዱ አሁንም ስለብሔረሰብ ጭቆናና በቁጥር ስለመብለጥና አለመብለጥ፣ እንዲሁም ከቁጥር መብለጥ ጋር የሚመጣጠን ፖለቲካዊ ድርሻ ስለማግኘት ጉዳይ እያነሳን ችግርን ወደ ማይፈታ ጭቅጭቅና ንትርክ ውስጥ በመግባት ተፈጥሮ የሰጠንን የማሰብ ኃይል ብቻ ሳይሆን፣ እንዲሁም የማቴርያል ሀብትም እናወድማለን። ዋናው ችግራችንም የብሔረሰብን ጥያቄ አድርገን በመወሰድና በማመን መሰረታዊና ለሰው ልጅ ከሚያስፈልገውና የሰውን ልጅ ችግር ከሚፈታው ሳይንሳዊ ምርምር እንሸሻለን።

በቁጥር ብልጫ ላይ የተመሰረተ አስተዳደር የአንድን ሕዝብ ችግር ሊፈታ አይችልም!!

የታሪክንና የሕብረተሰብን ሂደት ማህደር በደንብ ሳያገላብጡና ሳይመረምሩ የኦሮሞ ኤሊት ነን ባዮች ቀድሞሞ ሆነ ዛሬ እየመላለሱ የሚነግሩን ”የኦሮሞ ብሔረሰብ ከቆዳው ስፋትና ከቁመቱ ጋር የሚመጣጠን የፖለቲካ ሥልጣን አልተሰጠውም” እያሉን ነው። ይህንን ዐይነቱን አስተሳሰብ ሲያስተጋቡና ሲያስፋፉ ምን ለማለት እንደፈለጉ ለማብራራት ባይችሉም፣ ውስጣዊ ይዘቱን ስንመረምረው ግን ሊሉን የሚፈልጉት በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ውስጥ አንድ ብሔር ብቻ ለብዙ መቶ ዓመታት የፖለቲካ ሥልጣንን በመጨበጥ ሀብታችንን (Resources) በመበዝበዝና ዕድላችንን በመወሰን ወደ ኋላ እንድንቀር አድርጓል ይሉናል። ብዙም ሳይራመዱ ደግሞ እዚያው በዚያው ከብዙ መቶ ዐመታት በፊት ተግባራዊ እናደርግ የነበረውን ለዲሞክራሲ ማበብ፣ ለነፃነት መስፋፋትና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ የማያመቸውን የጋዳ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንፈልጋለን ይላሉ። ይሁንና ግን በዚህ ዐይነቱ ሥርዓት እንዴት አድርገው ቴክኖሎጂን በማሳደግ ብሔራዊ ሀብት አዳብረው ሕዝባቸውን ከድህነት እንደሚያላቅቁት በፍጹም አይነግሩንም። በአጠቃላይ ሲታይም ምን ዐይነት ሕብረተሰብ ለመመስረት እንደሚፈልጉም አያስረዱም ወይም አያብራሩም። በአስተሳሰቡ አንድ ወጥ የሆነ፣ አንድ ኃይማኖት ያለው፣ በስራ-ክፍፍል ያልዳበረ፣ ወይንስ ደግሞ የተሰበጣጠረና በስራ-ክፍፍል ላይ በመሰማራት የራሱን ዕድል ራሱ በመወሰን ራሱን በራሱ አግኝቶ ሕብረተሰቡንም የሚጠቅም ሥርዓት ለመገንባት? ከዚያም በመነሳት የገበያ ኢኮኖሚና ካፒታሊስታዊ ሥርዓት ለመገንባት ወይስ ዝም ብሎ ብቻ በከብት እርባታና በሳይንስ ላይ ባልተመሰረተ የእርሻ ክንዋኔ ላይ ብቻ በመሰማራት የሚኖር ብሔረሰብ ነው? ለመመስረት የሚፈልጉት። ይህንን ጉዳይ ግልጽ ካላደረጉ ደግሞ ዝም ብለው ነው የሚደናበሩት ማለት ነው። አዲሶቹ የኦሮሞ ኤሊት ነን ባዮች እየደጋገሙ ”ስለብሔረሰባቸው መጨቆን“ ሲነግሩን ጠቅላላው ኦሮሞ እያሉ የሚጠሩት የሕብረተሰብ ክፍል ምንም ዐይነት የዲያሌክት ቋንቋ ልዩነት እንደሌለውና፣ የሚያልመው ህልምና ፍላጎቱ አንድ ዐይነት እንደሆነ፣ ሲነሳም ሲተኛም በአንድ ጊዜ እንደሆነና፣ ኃይማኖቱም አንድ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን፣ በስራ-ክፍፍልና በመደብም ሆነ በገቢ እንዲሁም ደግሞ በህሊና አወቃቀር (Pyschological makeup) ያልተከፋፈለ ወይም ያልተለያየ (undifferenciated) እንደሆነ ነው ለማሳመን የሚሞክሩት። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ ኢ-ሳይንሳዊ አቀራረብ ነው። ለዕቅድና ለዕድገት የሚያመች አቀራረብ አይደለም።

ያም ሆነ ይህ አንድን ወጣት ትውልድ ለማደናበርና ጭንቅላቱን አጨልሞ በጥላቻ መንፈስ እንዲወጠር ከማድረግ በስተቀር በብዙ መንገድ እንደተረጋገጠው በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ዕድገትና የአገዛዝ ታሪክ ውስጥ፣ በተለይም ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ አንድ ብሔረሰብ ብቻ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትን በመቀዳጀት የሌሎችን ብሔረሰቦች ዕድል ያጨለመበትና ለኋላ-ቀርነታቸውም ምክንያት የሆነበት ሁኔታ የለም። የኢትዮጵያን የፖለቲካ አወቃቀር ስንመለከት በሥልጣን ላይ የተቆናጠጡት ኃይሎች ሁሉ በተለያየ ሁኔታ ከዚህኛውም ሆነ ከዚያኛው ብሔረሰብ ጋር በደም የተሳሰሩ እንደነበር ታሪክ ያረጋግጣል። በተለይም ኦሮሞዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች መስፋፋት ከጀመሩ ከ16ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ የፖለቲካ ማትሪክሱን በመጋባትና በመዋለድ የሕብረተሰቡን አወቃቀር እንደለወጡት መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም ስምንት መቶ ዓመት ያህል አንድ ብሔረሰብ ብቻ ነው ሲገዛን የነበረው፣ ከሕዝባችን ስፋት ጋር የሚመጣጠን የፖለቲካ ሥልጣንና ሀብታችንን ወይም ሬሶርሳችንን የመቆጣጠር ዕድል አላገኘንም የሚለው የተረት ተረት ወሬ ብቻ እንጂ በታሪክም ሆነ በሳይንስም የሚረጋገጥ ጉዳይ አይደለም። ስለ አገሪቱ ኋላ-ቀርነት ሲወራ ደግሞ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ከውጭው ዓለም ከነበረን እጅግ ከላላ ግኑኝነት ጋር የሚያያዝ እንጂ የአንድ ብሔረሰብ የበላይነቱን በመቀዳጀቱ የተከሰተ ችግር እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል፟።

ስለሆነም በኢኮኖሚና በማኅበረሰብ ያለማደግን ጉዳይ ስንመለከት አንድን ብሔረሰብ የሚመለከት ብቻ ሳይሆን፣ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሥልጣኔና ለዕድገት የሚያመች ዕድል በታሪኩ ውስጥ እንዳላጋጠሙት እንመለከታለን። በተለይም በ20ኛው ክፍለ-ዘመን በውስን መልክ በዘመናዊነት (Modernization) ስም የገባው የኢንዱስትሪ ፖለቲካው የነበረውን ሥርዓት የባሰውኑ ድህነትን ከመፈልፈል በስተቀር አጠቃላይ የሆነ ብሔራዊ ሀብት (National Wealth) እንዳላዳበረና፣ ጠቅላላውን ሕዝብ እንዳልጠቀመ በምድር ላይ የሚታየው ሀቅ ራሱ በቂ ማስረጃ ነው። ስለዚህም ስለ ዕድገትና ስለ ኋላ-ቀርነት በሚነሳበት ጊዜ ነገሩን፣ 1ኛ) ከምሁራዊ ብስለትና ሰፋ ያለ ክርክር ካለመኖር ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል። 2ኛ) በዚህም ምክንያት የተነሳ በራሱ የማሰብ ኃይል ሊዳብርና ሊንቀሳቀስ የሚችል የተገለጸለት የሕብረተሰብ ኃይል (Middle Class) መፈጠር ባለመቻሉ ስርዓቱን መጋፈጥ አልተቻለም። በመሆኑም የፊዩዳሉ ሥርዓት ዘመናዊ ከሚባለው ጋር በመቆላለፍ የአስተሳሰብ ግድፈት እንዲስፋፋና ድህነት መለዮአችን እንዲሆን ተደረገ። 3ኛ) አገዛዙ ራሱ የተከተለው ለፈጠራ የማያመች የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ሰፋ ያለ በስራ-ክፍፍል ላይ የዳበረ የውስጥ ገበያ እንዳይዳብር አገደ። ይህም ማለት ስለአንድ ብሔረሰብ መበደል ወይም መጨቆን በምናውራበት ጊዜ ከጠቅላላው የአገሪቱ ፖሊሲና፣ ከአገዛዙ ውስን አስተሳሰብ ነጥሎ ማየት ከባድ ስህተት ነው። በተጨማሪም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረው አዲሱ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ሁኔታ ለእኛ ዕድገት አመቺ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን የዚህን ውስብስበ አዲስ ሁኔታ የመረዳትና ስትራቴጂ የመቀየስ ምሁራዊ ኃይል አልነበረነም። ስለሆነም በተለየያ የዕውቀት ዘርፎች ላይ በመሰማራትና አድማሳችንን ለማስፋት ዕድል ባለማግኘታችን ከውስጥ ያለውን ኋላ-ቀርነትን ከሚያራምደው ፖለቲካና ከውጭ የሚመጣውን ግፊት ደግሞ መጋፈጥ አልተቻለም። ዛሬም ያለን ዋናው ችግር እንደዚህ ያለውን ምህራዊ ዝግጅት ያለማድረጉ ነው። ማንኛውንም ነገር ለመቆጣጠር የሚቻለው ሰፋ ያለ የበሰለ የሳይንስና የምሁራዊ ኩሞኒቲ ሲኖር ብቻ ነው። አገር ወዳድነትና ዕድገትም መዳበር የሚችሉት በዚህ አማካይነት ብቻ ነው።

በቁጥር መብለጥና ይህንን ተመርኩዞ ተወካይነትን ከዚያው ብሔረሰብ ለወጣ የፖለቲካ ኤሊት ኃላፊነትን ስለመስጠቱ ጉዳይ ስንመለከትና በኢምፔሪካልም ለማረጋገጥ እንደሚቻለው ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ ስሌት አካሄድ በፍጹም ሊስራ የሚችልና ለዕድገትም የሚያመች አይደለም። እንደሚታወቀው ከአንድ ብሔረሰብ የተውጣጣ ብቻ ሳይሆን፣ ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጣ የፖለቲካ ኤሊትም ሆነ የገዢ መደብ ራሳቸው ባዳበሩት ቲዎሪና ሳይንስ ስለማይመሩ የባሰውኑ ከዕድገት ይልቅ ፀረ-ዕድገትን ነው የሚያስፋፉት። ሀብትን ከመቆጣጠር ይልቅ ሀብት በውጭ ኩባንያዎች እንዲመዘበርና አካባቢ ወድሞ ሕብረተሰብ እንዲመሰቃቀል ከማድረግ በስተቀር ሀብትን በሥርዓት የመቆጣጠርና ቴክኖሎጂዎችን የማዳበር ዕድል በፍጹም አይኖርም። የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲውን የሚወክሉት ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች (IMF & World Bank) የማይሆን ምክር በመምከርና ተፅዕኖም በማድረግ የባሰውኑ ድህነት እንዲስፋፋና ነፃነትም እንዲገፈፍ ያደርጋሉ። ይህንን ጉዳይ በብዙ አገሮች የምንመለከተው ሃቅ ስለሆነ የኦሮሞ ኤሊት ነኝ ባዩ ከዚህ ዐይነቱ አጋር አፍራሽ ዕድል ሊያመልጥ አይችልም።

ይህ ዐይነቱ አካሄድ በተለይም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተሞክሮ በፍጹም አልሰራም። የደቡብ አፍሪካ ጥቁሩ ሕዝብ ወይም የሕብረተሰብ አካል ከአፓርታይድ ለመላቀቅ ያደረገው ትግልና ለጊዜውም የተጎናጸፈው ዕድል የሚደገፍ ቢሆንም፣ ከ25 ዓመት በኋላ ጥቁርን እንወክላለን ከሚል አገዛዝ ስፊው ጥቁር የሕብረተሰብ ክፍል የዕድገት ተጠቃሚ ሊሆን በፍጹም አልቻለም። የኤኤንሲ (ANC) አገዛዝ ተግባራዊ እንዲያደርግ በተገደደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ (Neo-Liberal Economic Policy) አማካይነት፣ ጥቂት የፓርቲው ካድሬዎች ተጠቃሚ ከመሆንና ሀብት ከማካበት በስተቀር የሰፊው ጥቁር አፍሪካዊ ህይወት ሊሻሻል በፍጹም አልቻለም። የዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ሀብትን ማካበት ውጤት ማኅበራዊ ቀውስና (Social Crisis) ከዚህ ጋር የተያያዘ ወንጀለኝነት መስፋፋታና በኤድስ በሽታ መለከፍ ነው። እንደምንሰማው የአገዛዙ አባሎች ከውስጥም ሆነ ከውጭ የንግድ ሰዎች ጋር በመመሰጣጠር ሀብት የሚያሸሹና የተቀረውንም በማከማቸት ራሳቸው ተንደላቀው እንዲኖሩ ሆነዋል። ስለሆነም በጥቁር ይበልጣል የሚባለው የኦሮሞ ብሔረሰብ በራሱ ኤሊት ቢወከል ከመቆርቆዝና ሀብቱ ከመበዝበዙ በስተቀር የሥልጣኔን ዕድል በፍጹም ሊጎናጸፍ አይችልም ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ጥያቄው በቁጥር በልጦ የመገኘቱ ጉዳይ ሳይሆን በሳይንስ ጭንቅላቱ የዳበረ ሰፋ ያለ ምሁራዊ ኃይልና ሕብረተሰቡንም ለመለወጥ ዝግጁ የሆነ፣ እንዲሁም ሕዝቡንና አገሩን ወዳጅ ኃይል ለዕድገት እጅግ ወሳኝ መሆኑን የሕብረተሰብን ዕድገት ታሪክ ላገላበጠ መገንዘብ ይቻላል። አገር ወዳድነትና ሕዝብን መውደድ ደግሞ ከብሔራዊ ባህርይ ጋር የሚጣመሩ ሲሆን የብሔረሰብን አርማ ለሚያራግብ አገር ወዳድነትና ሕዝብ ማለት ምን እንደሆኑ አይገባውም።

በሳይንስና በሎጂክ ሊደገፍ የማይችል የቁጥር ብዛት!!

የኦሮሞ ኤሊቶች እየደጋገሙ የሚሉን ጠቅላላው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ ውስጥ በቁጥር በልጠን የምንገኘው እኛ ስለሆን ሥልጣኑም ለኛ የሚገባ ነው፣ ካለበለዚያ ተገንጥለን የራሳችንን ግዛት እንመሰርታለን እያሉ ነው የሚያስፈራሩት። ለብዙ ዓመታት ይህንን ያህልም ሳይረጋገጥ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘው የኦሮሞ ብሔረሰብ ቁጥር 31 ሚሊዮን ያክላል እየተባለ ነበር። ከሁለት ሳምንት በፊት አውስታራሊያ ለሚገኘው የአማርኛ ራዲዮ አዘጋጅ ለሆነው ለአቶ ካሳሁን ዶ/ር ኃይሌ ላሪቦ በሰጡት ሰፊና ትምህርታዊ ትንተና የኦሮሞ ብሔረሰብ ቁጥር ከ7 ሚሊዮን እንደማይበልጥ እቅጩን ነግረውናል። አሁን ደግም የኦሮሞ የአመራር ኮንቬንሽን ላይ ከተሳተፈ ግለሰብ በቃለ-መጠይቅ ምልልስ የሰጠው መልስ የኦሮሞ ብሔረሰብ ከ50 ሚሊዮን በላይ እንደሚቆጠር ነው። እነዚህን የተምታቱ ቁጥሮች ስሰማ፣ ብዙ ካሰላሰልኩ በኋላ የደረስኩበት መደምደሚያ የኦሮሞ ብሔረሰብ ከማንኛውም ደም ጋር ሳይቀላቀል በንጹህ መልክ ይህንን ያህል ቁጥር ሊኖረው አይችልም የሚለው ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ላይ ነው ለመድረስ የቻልኩት። በሌላ አነጋገር የኦሮሞን ብሔረሰብ ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ከተፈለገ በታሪክና በሕብረተሰብ ውህደት ውስጥ ያደረገውን መቀላቀሎች በልዩ መሳሪያ በማውጣት የነሱ ደምና ጂን ልዩ መሆኑን ከተረዳን የተቀረውን መጠን ካወጣን በኋላ በእርግጥም የኦሮሞ ብሔረሰብ ቁጥር ይህንን ያህል ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል። ይህንን ዘዴ ከተጠቀምን ደግሞ የግዴታ የኦሮሞ ብሔረሰብ ቁጥር በጣም አነስተኛ ይሆናል ማለት ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ የአንድ አገር ሕዝብ በቤተሰብ (Households) አማካይነት በተደራጀ መልክ ሲቆጠር ዝም ብሎ ለመቁጠር ያህል ሳይሆን ለኢኮኖሚና ለማኅበራዊ ዕቅድ ወይም ፕላን እንዲያመችና፣ ከዚያ በመነሳት እንደየደረጃው ከቤት አንስቶ እስከ ትምህርትቤት፣ ህክምና መስጫ፣ ክሊኒኮችና ሌሎች ለአንድ ሕብረተሰብ ያስፈልጋሉ የሚባሉ የንጹህ ውሃንና የኃይልን አቅርቦት ለማደራጀትና ለማምረት ነው። በዚህ መልክ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ሕዝብ በቤተሰብ ደረጃ (Households) ቆጠራ ሲካሄድ የተለያየ ክፍል ያላቸው ቤቶችና ልዩ ልዩ ነገሮች በመታቀድ ይሰራሉ። ከዚህ በተጨማሪ የወሊድ ቁጥር አስቸጋሪ እየሆነ በመጣበት በኢንዱስትሪ አገሮች ውስጥ የሕዝብ ቆጠራ አዲስ በሚወለዱና በታዳጊው እንዲሁም እድሜው በጠና መሀከል የሚደረግ የሕዝብ ቆጠራ (Demography) ይካሄዳል። በዚህ መልክ የሚወለደው የሕዝብ ቁጥር እያነሰ የሚሄድ ከሆነ አዲስ የሰራተኛ ኃይል እጥረት ስለሚኖርና ቀረጥና የጡረታ አበል የሚከፍል ኃይል ስለሚያጥር አይ ሕዝቡ እንዲወልድ ልዩ ድጎማ ይሰጣል ወይም ደግሞ የኢሚግሬሽን ፖሊሲ ይካሄዳል። በዚህ መልክ የዲሞግራፊን ችግር መቅረፍ ይቻላል። በተጨማሪም በሕዝብ ቆጠራ ውስጥ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን የሴቶችና የወንዶች መጠን ለማወቅ ተያይዘ ቆጠራ ይካሄዳል። ሌላው የሕዝብ አቆጣጠር ዘዴ ደግሞ በገቢና በሀብት ክፍፍል ደረጃ የሚካሄድ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ አካሄድ የሀብትንና የገቢን አከፋፈል ዘዴ ለማወቅና የተዛባ ሁኔታ ካለ ማስተካከያ ዘዴ ለመፈለግ ነው። ከዚህም በላይ በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ሰዎችን ለማወቅ ሲባል የሚካሄድ አቆጣጠር ሲሆን፣ ይህም የሚያገለግለው በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠነ ሰው እጥረት በሚኖርበት ጊዜ የተማረ ኃይል እጥረት እንዳይኖር ሲባል ዝግጅት ለማድረግና አስፈላጊውንም እርምጃዎች ለመውሰድ ሲባል ነው። በዚህ መልክ የሚካሄድ የሕዝብ አቆጣጠር ዘዴ ለኢኮኖሚና ለማኅበራዊ ዕቅድ ያመቻል። ይሁንና ግን በጀርመንም ሆነ በሌሎች የኢንዱስትሪ አገሮች የተለያዩ የውጭ አገር ስዎች ቢኖሩም በተናጠል እየወሰዱ አንተ ከዚህ በሔረሰብ ወይም ከዚህ አገር የመጣህ ነው እየተባለ ለየት ያለ ቆጠራ አይካሄድም። በሂደት ውስጥም አብዛኛው ከጀርመን ጋር በመጋባቱ የተነሳ፣ ከአንድ አገር የመጣው ከሌላ አገር ጋር ከመጣችው ጋር ስለሚጋቡ የሕዝብን ቁጥር በጎሣ ደረጃ እየለያዩ መቁጠር እጅግ አስቸጋሪ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድም እጅግ አደገኛና ወደ ዘረኝነትም የሚያመራ ስለሆነ በጎሣ ላይ ያተኮረ ቆጠራ ሳይንሳዊ ባህርይ ሊኖረው በፍጹም አይችልም። ስለሆነም የሕዝብ መቀላቅል ስላለ ጀርመኑን ከሌላው ለመለየት የሚያስቸግርበት ጊዜ ይኖራል። በተለይም ከላቲንና ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች መጥተው እዚህ እየሰሩ የሚኖሩትንና የተጋቡትንና ልጅ የወለዱትን ከጀርመኑ ለመለየት እጅግ ያስቸግራል።

ወደ አገራችን ስንመጣ በተለይም ዶ/ር ሃይሌ ላሪቦ በሚገባ እንደተነተኑት ኦሮሞዎች ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ሲስፋፉ ከተቀረው ብሔረሰብ ጋር በመጋባት ተቀላቅለዋል። በሳቸው አባባል በወለጋ ሆነ በአርሲ ኦሮሞዎች በቁጥር ብዛት ይበልጣሉ ተብሎ ቢገመትም፣ ሀቁ ግን በወለጋ ውስጥ አብዛኛው ከጎጃሙ ጋር የተጋባና የተዋለደ ሲሆን፣ በአርሲ ደግሞ ከጉራጌ ጋር በመጋባት ኦሮሞዎች ጥንታዊ በሆነ መልክ እንደማይገኙና ከማንኛውም ብሔረሰብ ጋር ሳይቀላቀሉ በንጹህ መልክ ሊኖሩ እንደማይችሉ ነው የሚነግሩን። ስለሆነም ይላሉ ምሁሩ፣ ቋንቋ ብቻውን ስለቁጥር መብለጥ መለኪያ ሊሆን አይችልም ብለው እቅጩን ይነግሩናል። ወደ ከፋም ስንመጣ ከኩሎኮንታዎችና ከከፋዎች ጋር በመጋባትና በመቀላቀል ተዋልደዋል። ለምሳሌ የድሮው በኢህአዴግ ተመርጠው የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በአያታቸው ከፍቾ እንደሆነ ይታወቃል። እሳቸው ግን ንጽሁ በንጹህ መልክ ኦሮሞ እንደሆኑና በአፄ ምኒልክ ዘመን ተገደሉ የተባሉ ኦሮሞዎችን መቃበር ሲያስቆፍሩ ነበር። እንደዚሁ የኦሮሞ ነፃ አውጭ ድርጅት (OLF) እያለ ራሱን የሚጠራው ድርጅት መሪዎች አብዛኛዎቹ በአባቶቻቸው የጎንደርና የመንዝ ቄሶች እንደሆኑ ይታወቃል። እነሱ ግን ንጹህ በንጹህ ኦሮሞዎች ነንና ተጨቁነናል በማለት ነው ስንትና ስንት የዋህ ሰዎችን ሲያሳስቱና ሲያስገድሉ የከረሙት። አሁንም በየሜዳው የሚቧርቀው የዘመኑ ተዋናይ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ጃዋር መሐመድ በአባቱ የመናዊና በእናቱ ደግሞ ወሎ እንደሆነ ይነገራል። ሌላው የሚናፈሰው ደግሞ ጃዋር በአባቱ ኦሮሞ ሲሆን በእናቱ መንዜ ነው እየተባለ ነው። ይህ አንደኛው ሲሆን፣ የኦሮሞ መጨቆንን የሚያነሱት ኤሊት ነን ባዮች ከደሃው የሕብረተሰብ ክፍል የወጡ ሳይሆን በሶሻል ስታተሳቸው ሻል ካለ ቤተሰብ ከመጡና የመማር ዕድልም ለማግኘት ከቻሉት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ቀደም ብለው ከውጭው ዓለም አገር ግንኙነት ስለሚፈጥሩና የጥላቻ ሰለባ ስለሚሆኑ ፖለቲካ የሚባለውን ትልቅ ፅንሰ-ሃሳብ የራሳቸው ጥቅም ማስጠበቂያ አድርገው በመውሰድ ሰፊውን ሕዝብ ወደማሳሳት ያመራሉ።

ያም ሆነ ይህ የኦሮሞ ኤሊት ለማሳመን እንደሚሞክረው የኦሮሞ ብሔረሰብ ቁጥር በምንም ዐይነት 31ና 50 ሚሊዮን ሊሆን አይችልም። አንድንም ብሔረሰብ በጎሣ እየለያዩ ቆጥሮ ይህን ያክላል ማለት ለሳይንሳዊ ትንተናና ለኢኮኖሚ ፕላኒንግ በፍጹም የሚያመች አይደለም። በታሪክ አጋጣሚ የኦሮሞ ብሔረሰብ በመስፋፋቱና በሄደበት ቦታ ሁሉ ከሌላው ጋር በመጋባቱና በመዋለዱ፣ በዚህም የተነሳ የቋንቋ ተፅዕኖ ስላደረገ በቁጥር ይበልጣል የሚያሰኘው አንዳችም ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ሊኖር አይችልም።

ለአንድ ምሁር ወይም የፖለቲካ ታጋይ ነኝ ለሚል ዋናው መለኪያ የአንድ ብሔረሰብ በቁጥር በልጦ መገኘቱ ሳይሆን፣ የምርምር መነሻውና የአተናተን ዘዴው፣ በዚያ ሕብረተሰብ ውስጥ የሚገኘው የፖለቲካና የመንግሥት አወቃቀር፣ በዚህም የተነሳ የኢኮኖሚና የማኅበረሰብ አደረጃጀት፣ ስለሆነም ብሔራዊ ሀብት የመፍጠርና ያለመፍጠር ጉዳይ ናቸው መነሻና ሳይንሳዊ መንገድ መሆን ያለባቸው። ከዚህም በመነሳት ሥልጣንን የጨበጠ የገዢ መደብ ከውጭው ዓለም ጋር ያለው ፓለቲካዊ፣ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ ግኑኘነትና፣ ይህ ዐይነቱ ግኑኝነት የዕድገት አጋዥ ነው ወይስ ሀብትን የሚያዘርፍና ወደ ጦርነት እንድናመራ አድርጎ የተደላደለ ሕብረተሰብ እንዳንገነባ የሚያግደን ነው? የሚለው የምርምርና የአተናተን ዘዴ ትክክለኛው ሳይንሳዊ መንገድ ነው። በዚህ አማካይነት ይህንን መሰረት በማድረግ ነው፣ ስለ ፖለቲካ፣ ስለማኅበራዊና ስለኢኮኖሚ እኩልነት ወይም ጀስቲስ (Jusitce) መታገልና የተደላደለና ጤናማ ሕብረተሰብ እንዲፈጠር የሚቻለው። አንድን ሕብረተሰብ በብሔረሰብ ደረጃ እየከፋፈሉ መቁጠር የሚያመቸው ዕድገትና ስላምን ለሚቀናቀኑ ኃይሎች ብቻ ነው። ስለሆነም ማትኮር ያለብን ስለጠቅላላው ሕዝባችን አኗኗርና፣ አሁን ካለበት አስከፊ ሁኔታ እንዴት አድርገንና በምን ዐይነት ስትራቴጂያዊ ዘዴ ልናወጣው እንችላለን በሚለው መርህ ላይ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ትግል ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን ያራዝማል። በጦርነት ዓለም ውስጥ እንድንኖር ያስገድደናል።

ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ኅዳር 22፣ 2016 ዓ.ም.
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!