ሸንቁጥ አየለ

Ethiopia

፩ኛ- ወያኔዎች ለ25 ዓመታት በየሚዲያው፣ በየመጠጥ ቤቱ፣ በየጓዳቸው እና በየስርቻው የሚለፈልፉት አንድ የምቀኝነት ንግግር አለ። "እኛ ታግለን፣ እኛ ሞተን፤ ለማን ብለን ነው ሥልጣኑን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለተቃዋሚ የምናስረክበው?" የሚል ነው። ይሄም ሲፈታ ምን ማለት ነው? በኛ ደም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከምትገነባ፤ ኢትዮጵያ በመከራ ለዘመናት እየተሰቃየች ትኑር ማለት ነው።

፪ኛ- ቅንጅት በ1997 ዓ.ም. ምድር አንቀጥቅጥ ምርጫ አድርጎ ከወያኔ ከ180 ወንበር በላይ (ቁጥሩን አንዳንዶች ከ250 በላይ ነው ይላሉ) ማሸነፍ ችሎ ነበር። ያኔም ሕብረት የሚባለው ድርጅትም ደህና ውጤት አስመስግቦ ነበር። ሕብረት እና ቅንጅት በጋራ ተባብረው ፓርላማ ቢገቡ ወያኔን ብዙ ነገር ያለማምዷታል። በሂደትም የሥልጣን ሽግሽግ እና የሥልጣን ቅብብሎሽ ባህል በኢትዮጵያ እንዲፈጠር መንገዱን ይቀይሳሉ ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ተስፋ አድርጎ ነበር። የሆነው ግን አጀብ የሚያስብል ነበር። የሕብረቱ መሪዎች ተሯሩጠው ወደ ሚዲያ ወጥተው "የቀኝ ኃይሎች ክንፍ እያንሰራራ ነው። የቅንጅት በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የቀኝ ኃይሎች እንደገና በኢትዮጵያ ምድር ሥልጣን ሊቆጣጠሩ መዘጋጀታቸውን ያሳያል። ይሄም ለብሔረሰቦች እኩልነት መልካም ሂደት አይደለም" ብለው ቁጭ።

ያኔ የአገሪቱን የምርጫ እንቅስቃሴ ከመከታተልም በላይ የግል ጋዜጣ ላይ ሃሳቤን አካፍል ስለነበረ፤ "አሁን ከመነቃቀፍ በሂደት የምትገነባው ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በመተባበር ላይ ቢተኮር ጥሩ ነው። ወያኔም በሂደት የሰላማዊ ሥልጣን ሽግግር ሂደቱ አስፈሪ እንዳልሆነ እየገባው ሲመጣ ሥልጣን ለማካፈል ብሎም በሂደት አገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም የቀኝ የግራ የሚለው ከንቱ መካሰስ ቀርቶ የጋራ ትብብር የሚፈጠርበት ቢታሰብበት" የሚል ምክር ብጤ ሰንዝሬ ነበር። ሆኖም የሕብረት እና የቅንጅት ጎራ ባልተጨበጠ ሥልጣን ላይ መነቋቆር ላይ በጣም ተጠምዶ ነበር። ጽልመታዊ አገራዊ የምቀኝነት መንፈስ መሆኑ ነው።

፫ኛ- አቶ ገብረ ክርስቶስ የተባሉ ጸሀፊ ቅንጅት ከየት ወዴት የሚል መጽሐፍ ጽፈዋል። በጽሁፉ ውስጥ እጅግ ብዙ ቀልብ የሚስቡ ታሪኮች አሉ። ከዚሁ ከምቀኝነት ጋር የሚሄድ አንድ ታሪክ ግን ልምዘዝ። ቀስተ ደመና የሚባለው ፓርቲ እራሱን የምሁራን ስብስብ አድርጎ የፈረጀ ነበር ይሉናል አቶ ገብረ ክርስቶስ። እናም መኢአድ የሚባለው ፓርቲ የነበረው ሰፊ ሕዝባዊ መሰረት ያበሳጨው ነበር። እንዲሁም ቀስተ ደመና መኢአድን እንደ መሀይሞች ስብስብ ይመለከተውም ነበር። ስለሆነም የቀስተ ደመና ሰዎች ሁሌም ሲገናኙ መኢአድ የሚባለውን ድርጅት እንዴት እንደሚውጡት ይመካከሩ ነበር።

መኢአዶችም ይሄን እውነት ሲረዱ ገና ቅንጅቱ በግሩ ዳዴ ሳይል በመኢአድ እና በቀስተ ዳመና መሃከል ከፍተኛ ፍጥጫ ነበር ይላሉ - አቶ ገብረ ክርስቶስ። ይታያችሁ በመዋሃድ ላይ ያሉ ፓርቲዎች ገና ምንም ሳይሠሩ እንትናን እንዋጠው በሚል መርኅ በምቀኝነት ፍልስፍና ሲዳክሩ። ተዋህደው ሊከስሙ እየሠሩ ያሉ ድርጅቶች መሃከል እንዲህ አይነት መንፈስ እንደ ማንበብ ያለ ጽልመታዊ ምቀኘት ከቶም አስገራሚ ነገር ያለ አይመስለኝም።

፬ኛ- ይባስ ብሎ ቅንጅቱ እራሱ ጉድ መዞ፣ ጉድ አንግቦ መጣ። ከቅንጅቱ መሪዎች ውስጥ "ቅንጅት ከዘጠና ፐርሰንት በላይ አማራ ነው። ስለዚህ ቅንጅት መፍረስ አለበት" የሚል ስንጸ ሃሳብ ይዘው የመጡ መሪዎች ተገኙ። እናም ከአገር ቤት እስከ ውጭ አገር እንዲሁም ታዋቂ ጋዜጣ ነን የሚሉ የወቅቱ የጥላቻ አርገብጋቢ ጋዜጦችም ይህችኑ መፈክር ትንታኔ መሳይ ነገር ሠሩባት። አንዱ ታዋቂ ነኝ ባይ ጋዜጣ እማ በታዋቂ ጋዜጠኞቹ በኩል አምስት ገጽ ሙሉ ትንታኔ ለቅልቆ ይዞ መጣ። እናም ትንታኔው ሲጨመቅ ለቅንጅቱ መፍረስ ዋናው ምክንያት በውጭ አገር የዲያስፖራ አማሮች በቅንጅቱ ደጋፊነት መብዛታቸው ነው ብሎ ቁጭ። ላልተጨበጠ ሥልጣን ልታገል ወይም ላግዝህ ያለን ወገን ለመንቀፍ ጥቂትም ቅር ያለው ወገን አልነበረም። ከዚህ ክስ ጀርባ ግን ያው የምቀኝነት መፈስ ነው የሚቦካው።

፭ኛ- የኦሮሞ ጽንፈኛ አክራሪ እና እንገነጠላለን ባይ ፖለቲከኞች "ለምንድን ነው የምትገነጠሉት? ከምትገነጠሉ የኦሮሞ ሕዝብም፣ ሌላው ኢትዮጵያዊም የሚስማማበት እና የሚመቸው ዲሞክራሲ የሰፈነበት፣ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበት አገር እንዲገነባ የመሪነቱን ሚና ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችሁ ጋር ለምን አትወስዱም? በተለይም ትልልቅ ቁጥር ያላችሁ የኦሮሞ እና የአማራ ብሔረሰብ አባላት በመነጋገር አንድ የሆነ የሚያግባባ ነገር ብዙ ተጨቃጭቃችሁ እና መክራችሁ ለምን አታመጡም?" ተብለው ሲጠየቁ የሚመልሱት መልስ፤ "ኦሮሚያ ሀብታም ነች። ሰፊ እና ለም መሬት አላት። ሌላው ብሔር ከዚህ ለም ነገር ሊጠቀም አይገባውም። በዚህ መሬት መጠቀም ያለበት ኦሮሞው ብቻ ነው" ብለው ይመልሳሉ። እነዚህ ኦሮሞ ይገንጠል የሚሉ ፖለቲከኞች የት ነው የመሸጉት። ደጉ አሜሪካ። ደጉ አውሮፓ ነው። ደጎቹ አሜሪካ እና አውሮፓ አንተ ከኛ ሀብት አትጠቀምም አላላቸውም። እንዲኖሩ እና ሀብት እንዲያፈሩ መብታቸው እንዲጠበቅ ዕድል ሰጥቷቸዋል።

እነሱ ግን ከኦሮሞ መሬት ሌላው እንዳይጠቀም በሚል ምቀኝነት ይባክናሉ። ለዚያውም ጦርነት የሚወስነው የመሬት ስፋት ጉዳይን እንደ ቁምነገር አንግበው ለም ለሙን ሁሉ በካርታ ላይ አስፍረው በጠባብ ሕልም ይዳክራሉ። ታዲያ ሌላ የሚያስደምም ታሪክ አብሮ ተጎትቶ መጥቶላቸዋል። አማራን እገነጥላለሁ ያለው ኃይልም እነሱ ለም ለም ብለው ያሰቧትን መሬት ጥቅልል አድርጎ የአማራ ካርታ ብሎ ሠርቶላቸዋል። ውጤቱን የሚወስነው ጦርነት ብቻ ይሆናል ማለት ነው። የሶማሌ ተገንጣዮችም ባሌ እና አርሲን ሲብስም እስከ መሃል ሸዋ የሕልማቸው መተንተኛ አድርገው ያቀርቧታል። ሲዳማውስ አገር ሲፈራርስ ምን የማይጠይቀው ለም መሬት ይኖረዋልም? ሲዳማዎችም በልባቸው የሚቀምሩት ለም መሬት ቀላል አይደለም። አንዱ የምቀኝነት መንፈስ የሚወልደው መንፈስ የጠነከረ እና የበረታ ነው። ምቀኝነት ምቀኝነትን ይወልዳል። ቅዱስ ዳዊት ያለምክንያት እንዲህ አላለም "ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ። መዝ 18፣25"

፮ኛ- አሁን ደግሞ አማራ መገንጠል አለበት የሚሉ ቡድኖች ተነስተዋል። ቡድኖች ያልኳቸው የተሰባሰቡበት ድርጅት እሁለት ቦታ ተለያይቷል የሚል መረጃ ለሕዝብ ስለተለቀቀ ነው። አንደኛው ቡድን በመግለጫው የመገንጠል ሃሳባችንን አንስተናል ብሎ ስላለ ነው። ሆኖም የመገንጠል ህሳቤ የሚያራምዱት ቡድኖች አሁንም ያችኑ መጀመሪያ ጀምሮ ሲሏት የነበረችውን ሃሳባቸውን አልለቀቋትም። "ለምን አማራ ይገነጠላል? አማራ መገንጠል አያስፈልገውም። አማራ ማድረግ ያለበት እራሱን አጠንክሮ ወያኔን ከሌሎች ጋር በመተባበር በኃይል ከኢትዮጵያ አስወግዶ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነው።" ተብለው ሲመከሩ የሚመልሱት መልስ ያስገርማል። "አማራ ለማንም አይሞትም። አማራ የሚሞተው ለራሱ ብቻ ነው። አማራ ምን በወጣው ነው ለቀሪው ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ዲሞክራሲ የሚታገለው?" ብለው ቁጭ። ይሄም መራራ ምቀኝነት ነው።

አማራ ታግሎ ለራሱም ለኢትዮጵውያን የምትመች አገር ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ቢፈጥር ያኮራል እንጅ አያበሳጭም። ግን የምቀኝነት መንፈስ ማለቂያ የለውም እና እንደ ወያኔዎቹ አማራ ታግሎ ምን በወጣው ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊት ያደርጋል ብለው ይሞግታሉ። ወያኔ ምን አለ? ትግሬ ታግሎ ኢትዮጵያን ምን በወጣው ዲሞክራሲያዊ ያደርጋል ብሎ ነው የሚሞግተው። ትግሬ ታግሎ ትግሬ ብቻውን ኢትዮጵያን ግጦ ይጨርሳት ብሎ ነው ወያኔ በጥጋብ እስኪፈነዳ በእብሪት ተወጥሮ አገር የሚያምሰው። ይሄም መራራ ምቀኝነት ነው።

፯ኛ- ባለፈው የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ሲመሰረት ኮሌኔል ዳዊት ወልደጊዮርጊስ የተናገሩት ንግግርም ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። "ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ የታፈሩ እና የተከበሩ በድርጅቶች መሃከል የጋራ ንቅናቄ እንዲፈጠር ብዙ የጣሩ" ብዬ በልቤ አወድሼ ሳልጨርስ፤ ያችው የምቀኝነት መንፈስ ተመዝዛ እዚያው አደባባይ ላይ ዱብ አለች። "አማራ የተደራጀ እና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ድርጅት ስለሌለው ለጊዜው በአንድ ሰው እንዲወከል አድርገናል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የአማራ ሕዝብ አደራጅቶ ይወክለናል ብሎ ወደዚህ የላከልን ድርጅት ስለሌለ አማራው በአንድ ሰው እንዲወከል ግድ ሆኗል። እንግዲህ እኛ ወደፊት ለአማራው ድርጅት እንፈጥርለታለን።" ብለው የቀድሞ የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት ወጣቶች መሪ የነበረውን ሰው ለህዝቡ አስተዋወቁ። አጀብ ሸዋ! አልኩ በልቤ። እዚያ የተደረደሩትን ድርጅቶች ሕዝብ መርጦ እና ወክሎ ነው ማለት ነው የላካቸው? ለራሴ ጥያቄ አነሳሁ። ይሄ መልሱ ሐሰት መሆኑን ሁሉም ያውቃል። እናም በልቤ እንዲህ አልኩ "አይ የሀበሻ ክፋት እና ተንኮል? መቼ ነው ማለቂያሽ?"። እንዲህ ብዬ የጠየቅሁት ያለ ምክንያት አይደለም።

የአማራ ድርጅት ነን ብለው ከአምስት በላይ ድርጅቶች እያሉ ሁሉንም የሉም ብሎ በመደምሰስ የአማራ ድርጅት ስለሌለ ብሎ ማወጅ ክፋት እና ምቀኝት ብሎም ሐሰት እና ሸፍጥ መሆኑ ወዲያው ፍንትው ስላለልኝ ነው። ቢያንስ በሃሳብ "ለጊዜው ስላልተስማማን ነው፣ ድርድር አድርገን የአማራ ድርጅቶችንም እናቅፋለን" ብሎ በአክብሮት መግለጽ ሲገባ፤ እየታገልን ነው የሚሉ ድርጅቶችን አንድም የሉ ብሎ መደምሰስ አስደናቂ ሸፍጥ ነው። በዚያችው ቅጽበትም በአማራ ድርጅቶች እና በግንቦት ሰባት መሃከል መራራ ጥላቻ እንደሚወለድ ገምቼ ነበር። እና ውጤቱ ምን ሆነ? አሁን በግንቦት ሰባት እና የላችሁም በተባሉት የአማራ ድርጅቶች መሃከል መራራ የመጠላለፍ ፍልሚያ እየተደረገ ነው። ሆኖም ቁጭ ብለው ይሄን ነገር ለመነጋገር እና ለመፍታት የሚደረግ ጥረት አይታይም። የኢትዮጵያ ሕዝብም በዚህ መሰሉ የመጠላለፍ እና የመነቋቆር ሂደት ልቡ በየቀኑ ዝቅ ይላል። ሕዝቡ አንድ ነገር ይፈልጋል። ወያኔ ወድቃ ማየት። አንዲት ዲሞክራሲያዊት የበለጸገች ኢትዮጵያ ተፈጥራ ማየት።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የክፋት ጽልመት ሂደቱ ግን ይቀጥላል። እንዲህ አይነት ጽልመታዊ የክፋት መንፈሶች ግን ፈሪ እና አድርባይ ናቸው እና አንድ አንባገነን ሰባብሮ ይጥላቸዋል። ኢትዮጵያ ግን ወደ ዲሞክራሲ እንዳትሸጋገር ብዙ መጓተት እና መጎተት እየደረሰባት ነው። ምናልባትም ሀገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ሳይሆን ወደ ሌላ ወደ ክፉ አንባገነን እጅ ልትወድቅ ትችላላች። ወይም ወደከፋ ሁኔታ ውስጥ ገብታ ልትቀረቀር ትችላለች። በፖለቲከኞች ጥልመታዊ የምቀኝነት መንፈስ የተነሳ። ምክንያቱም ፖለቲከኞች በሥራቸው ጥመት እና ክፋት ሲበዛበት እግዚአብሔርም ሥራቸውን አያከናውንላቸውም። እግዚአብሔር ቅንነቱ ከቅኖች ጋር ብቻ ነው። ጠማሞች ላይ ግን ያው መጽሐፍ እንዳለው ነው። ነገሮች የሚከናወኑት፤ "እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ። ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ። መዝ 18፣25" እንዳለው ነውና።

ፖለቲከኞች ሆይ! እባካችሁ ሌላውን ጉሳንጉስ እና ኩሳንኩስ ተንኮልን እና ምቀኝነትን ተዉት። እግዚአብሔር ሥራችሁን እንዲያቀናው፣ ይህችን መከረኛ አገርም እንድትታደጓት ለአንድ እውነት ብቻ በቅንነት ሥሩ። አንዲት ዲሞክራሲያዊት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የምቀኝነት መንፈስ ካጸለመው ሕሊናችሁ ወደ ብርሃናማው አገራዊ የፍቅር መንፈስ ዞር በሉ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!