ይገረም አለሙ

Colorful Ethiopia

ለማናቸውም ዓላማ ሰዎች ተሰባስበው ድርጅት የመፍጠር መብት አላቸው፤ በአንጻሩ ለድርጅታቸው የሚሰጡት መጠሪያ እናራምደዋለን የሚሉት ዓላማ እና እንደርስበታለን የሚሉት ግብ በተናጠል ግለሰብንም ሆነ በወል ማኅበረሰብንና አገርን ሊነካ ስለሚችል ከዚህ አንጻር ሊፈጽሙት የሚገባ ግዴት አለባቸው። በመሆኑም በሕገ መንግሥትም ሆነ በፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጆች ውስጥ እነዚህ ከመደራጀት አንጻር ተግባራዊ የሚሆኑ መብቶችና ግዴታዎች ሰፍረው ይገኛሉ። ነገር ግን በፌስ ቡክ ድርጅት ሲመሰረት የመስራቾቹ ቅን ፍላጎትና ራስን ለሕግ የማስገዛት ሰውነት ከሌለ በስተቀር ለሕግም ለሞራልም ግዴታዎች እንዲገዙ የሚገደዱበት ሁኔታ አይኖርም።

ይህም በመሆኑ ነው አንዳንዶች በፈለግነው ስም ለፈልግነው ዓላማና ግብ የፈለግነውን የሕብረተሰብ ክፍል/ሕዝብ እንወክላለን ብለን መደራጀት መብታችን ነው፣ ለምን ብላችሁ አትጠይቁን፣ እንዴት ብላችሁ አትናገሩን የሚሉት። ስለራሳቸው የመደራጀት መብት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩና አትናገሩን ብለው ሲፎክሩ እንወክልሃለን ብለው ስሙን በመጠሪያነት፣ ብሶት በደሉን በመቀስቀሻነት፣ የሚጠቀሙበት ግለሰብም ይሁን ሕብረተሰብ የመጠየቅ፣ የመተቸት፣ የመቃወም በጣም ከገፋም በሕግ እስከማስቆም መብት እንዳለው የተረዱ አይመስልም። ይህን ቢያውቁ ኖሮ ዓላማቸውን አስረድተው በሚችሉት አቅም የሚሉትን በተግባር ሆነው በመገኘት ደጋፊ ለማብዛት ይጣጣሩ ነበር እንጂ፤ በጩኸት፣ በዘለፋና በስድብ አፍ ለማስያዝ ተቆጣጣሪ የሌለውን ማኅበራዊ መገናኛ ሲያናውጡት ባልታዩ ነበር።

በማኅበራዊ መገናኛዎች የምናነባቸውና የምንሰማቸው አንዳንዶቹ የሚጠቀሙዋቸው ቃላቶች አይደለም ፖለቲካ ሊያራምዱና ለወግ ማዕረግ በቅተው የአገር ኀላፊነት ሊሸከሙ ቀርቶ በኢትዮጵያዊ ባህልና ጨዋነት ተኮትኩተው ማደጋቸውን እንኳን እንድንጠራጠር የሚያደርጉ ናቸው። መቼም ፖለቲከኛ ነን በሚሉ ሰዎች ዘንድ ሕዝብ እና ዴሞክራሲ እንደሚባሉ ቃላቶች መቀለጃም ማላጋጨም የሆነ የለምና፤ ማንነታቸውም ቁጥራቸውም የማይታወቅ ሰዎች ተነስተው አርማ ሠርተው፣ ስም አውጥተው፣ እከሌ የሚባለውን ሕዝብ እንወክላለን ብለው በፌስ ቡክ ብቅ ሲሉ እንወክልሃለን ያሉት የሕብረተሰብ ክፍል አባል የሆነ ግለሰብም ይሁን ቡድን ማናችሁ ብሎ ሲጠይቅ፣ የያዛችሁት ዓላማ እኔን አይወክልም፣ እንደርስበታልን የምትሉት ግብም የእኔ ራዕይ አይደለም በማለት ሙግት ሲያቀርብ በርግጥ ዓላማ ያላቸው ታግሎ ለማታገል ቆርጠው የተነሱ፣ ወዘተ ከሆኑ ለጥያቄው መልስ፣ ለሙግቱ በመረጃ የተደገፈ መከራከሪያ ማቅረብ ነው የሚጠበቅባቸው። የምናይ የምንሰማው ግን ይህን የምትጠይቅ አንተ የእኛ ሰው አይደለህም፣ እንዲህ የምትሟገተው ወያኔ ስለሆንክ ነው ወዘተ የሚሉ ምላሾችን ነው። እንዲህ የሚሉት ሰዎች መሰረትነው የሚሉት ድርጅት ከአየር ላይ ወርዶ መሬት ያልረገጠ፣ የመሪዎቹ ማንነት ያልተለየ፣ የአመራር አባሎቹ ስንትነት ያልታወቀ፣ መደራጀት መብታችን ነው ከማለት ያለፈና ከፌስ ቡክ ፉከራ የዘለለ የሚታይ ተግባር የሌላቸው መሆናቸው በጀ እንጂ እንደ ፉከራቸው በተግባር ያሉ ቢሆኑ እንደ ትናንቱ ትውልድ የርስ በርስ መተላለቅ በተፈጠረ ነበር። እባብ የልቡን አይቶ አግር ነሳው ነው የሚባለው።

ከለማበት የተጋባበት እንዲሉ፤ የትናንቶቹ እንዳላዋጣ አይተው እየተዉት ያለውን ዘረኝነት በአዲስ ወኔ የተያያዙት ወገኖች እንደሚሉት በወያኔ አገዛዝ በሕዝብ ላይ የተፈጸመውና አሁንም የሚፈጸመው በደል አማራ፣ ኦሮሞ፣ ኮንሶ፣ ጋምቤላ፣ ... ብሎ የለየ አይደለም። ጥቃት ፈጻሚው ወያኔ፣ ተጠቂው ሁሉም ኢትዮያዊ ሆኖ ሳለ፤ እነርሱ እንወክለዋለን የሚሉት ሕብረተሰብ/ሕዝብ ጥቃት የደረሰበት በማንነቱ ነው የሚለው ዘረኛ ቅስቀሳ የተፈለገው አንድም ሕዝብን ለማነሳሳት ቀላሉ መንገድና ስሱ ብልት እሱ በመሆኑ፤ ሁለትም ወያኔ ለሥልጣን የበቃው በዚህ መንገድ ነው ከሚል እሳቤ ነው። የእኔ ብሔር አባላት በማንነታቸው ምክንያት ብቻ ነው በወያኔ የሚጠቁት የሚሉን ወገኖች ቢያንስ ሁለት ጥያቄዎችን መመለስ ይጠበቅባቸዋል፤ ግን አይሞክሩትም። አንደኛ ከእነርሱ ብሔር ውጪ የሆኑት ከ80 በላይ የሚሆኑት የሌሎች ብሔር ብሔረሰብ አባላት ኢትዮጵያውያን በወያኔ ምንም በደል አልደረሰባቸውም ማለት ነው? ሁለተኛ በብሔሩ ምክንያት ብቻ ነው የተጠቃው ከሚሉት ብሔር አባላት አብዛኛው ቁጥር በአንድ ወይንም በሌላ መልኩ ቀጥተኛ ጥቃት ያልደረሰበት ነውና ይህን ምን ይሉታል? ወይንስ በወያኔ የተጠቃው ብቻ ነው የዛ ብሔር አባል ተብሎ ሊገለጽ የሚችለው?

በተግባር ከደረሰብኝም ሆነ በቅርብ በሌሎች ሲደርስ ካየሁት የተረዳሁት፤ እኔ ሰው ነኝ ክብር ያለኝ ነጻነት ያለኝ፣ ለአምባገነን አገዛዝ አላጎበድድም፣ ሕሊናየን ለሆድ አልለውጥም፣ በሰውነት መብቴ አልደራደርም፣ ሕግ አክብሬ ሕግም ተከብሮልኝ መኖር ነው የምሻው ወዘተ ያለ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ጋምቤላ፣ ሲዳማ፣ አፋር፣ ... ወዘተ ሳይል የወያኔ የጥቃት ሰለባ ሆኗል፤ እየሆነም ነው። በአንጻሩ “ጎበዝ ምንድን ነው መላው አያያዙን አይተህ ወደሚያደላው” የሚለውን አባባል የተከተሉ ብሔራቸው ከየትም ይሁን ከየት ተጠቂ ሳይሆኑ በአጥቂነት ተሰልፈው የኢኮኖሚውም የፖለቲካውም ተጠቃሚ ሆነው ኖረዋል፤ እየኖሩም ናቸው። በሌላም በኩል ለሥርዓቱ ድጋፍ ባይኖራቸውም፣ የሚያዩት የሚሰሙት ሁሉ የሕሊና እረፍት ቢነሳቸውም በተለያየ ምክንያት ለመቃወም ባለመቻል ጎመን በጤና ብለው ሆነው ሳይሆን መስለው የሚኖሩት እጅግ በርካታ ቁጥር የሚይዙት ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ ባይሆኑም ሥርዓቱን ባይፈልጉትም ቀጥተኛ ጥቃት ሳይደርስባቸው፣ በደል ሳይፈጸምባቸው እየኖሩ ስለመሆኑ አሌ የሚል ካለ ዓይኔን ግንባር ያድርገው የሚል ብቻ መሆን አለበት።

ስለሆነም የወያኔ ጥቃት በዘር ማንነት ላይ ሳይሆን በአመለካከት ላይ የተመሰረተ ነውና መፍትሔውም በዘር ሳይለያዩ፣ የቋንቋ ገድብ ሳይፈጥሩ፣ በኃይማኖት ሳይራራቁ፣ በደል በቃን ነጻነት እንሻለን የሚሉ ወገኖች ሁሉ በአንድ ተሰልፈው መታገል ነው። ስለሆነም እገሌ የሚባለውን የሕብረተሰብ ክፍል ወይንም ሕዝብ እንወክላለን በማለት ድርጅት መስርተው ያለ ውጤት ዓመታት ያስቆጠሩትም ሆኑ ከእነርሱ ባለመማር በዘር መደራጀትን እንደ አዲስ የተያያዙት ወገኖች ወያኔ ሲያጠቃ የኖረውና አሁንም እያጠቃ ያለው ለሥልጣኔ ያሰጋኛል ያለውን ማናቸውንም ኢትዮጵያዊ ዘር ቋንቋ ኃይማኖት ሳይለይ ነውና የእኔ የሚሉት ወገን ብቻ የተጠቃ አድርገው የሚነዙትንና በወያኔ የጠላውንና ወያኔም (በእምነት ሳይሆን ለማስቀየሻ ስልት) እየተወው የመጣውን የዘረኝነት መርዝ መርጨት አቁመው፤ ሲሆን በኢትዮጵያዊነት ቢደራጁ፣ ኧረ ምን ሲደረግ ካሉም በመሰላቸው ስምና መንገድ ይደራጁ፣ ዘረኝነቱን ግን ይተዉት፤ የጎንዮሽ ንትርኩን ያቁሙት፤ እኔ ብቻ ትክክል የሚለውን ግራና ቀኝ ማየት የማያስችል ግርዶሽ ያስወግዱት። (በነገራችን ላይ ወያኔ ብዙ ነገሮችን ቀስ በቀስ እያለማመደ ወደ እሱ መስመር አስገብቶናል። የቀበሌውም ነዋሪ የዞኑም የወረዳውም የክልሉም ሕዝብ ይባላል፣ የወለጋ ሕዝብ፣ የኦሮሞ ሕዝብ፣ የጎንደር ሕዝብ፣ የአማራ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ አጀኢብ ነው፤ የሚከተል እንጂ የሚያርም የለም)

ሕብረተሰቡን የሚያሳምኑበት ዓላማና የሚታመን የመታገያ አጀንዳም ሆነ የሚሉትን ሆነው ለመገኘት የሚያበቃ የተግባር እንቅስቃሴ የሌላቸው፣ ለሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት መብቃትና ለአገራዊ ዴሞክራሲ እውን መሆን ሳይሆን ለግል የሥልጣን ፍላጎት የቆሙና በአጭር መንገድ ቤተ መንግሥት ራሳቸውን ለማየት የሚያልሙ ወገኖች የሚታያቸው የጎሠኝነቱ መንገድ ነው። ለዚህ ምሳሌያቸው ደግሞ ወያኔ ነው። ነገር ግን ኦነግንም ማየት ቢችሉ አስተሳሰባቸውን ሚዛናዊ ለማድረግ ያስችላቸው ነበር። በአንድ ወገን ዕይታ ብቻ ውሳኔ ላይ አይደረስም።

ዘረኝነት አንዴ ከገቡበት በቀላሉ ሊወጡት የማይችሉት አረንቋ ነው። በጎሣ ተደራጅተን ለሥልጣን ስንበቃ ኢትዮጵያዊነትን እንላበሳለን ማለት ዘበት ነው። ለአንዳንዶቹ ኢትዮጵያዊነትን አውልቀው ጥለው ጎሠኝነትን ለመላበስ እንደቀለላቸው ከጎሠኝነት ወደ ኢትዮጵያዊነት መምጣት ቀላል ሊሆን አይችልም። ሰፊን ነገር ማጥበብ ይቻላል፤ ጠባብን ነገር ለማስፋት ግን አይቻልም፤ ከተቻለም ብዙ አድክሞ ነው። ገና ለሥልጣን ሳይበቁ በእጃቸውም በደጃቸውም ምንም በሌለበት ዘረኝነት እንዲህ የሚያናግራቸው፤ ለቤተ መንግሥት ቢበቁና ማጥቂያውም (ጦሩ) ማውሪያውም (ሚዲያው) ስኳሩም (ኢኮኖሚው) በእጃቸውና በደጃቸው ቢሆን ወደ ኢትዮጵያዊነት መመለስ አይደለም ምን ሊሆኑና ሊያደርጉ እንደሚችሉ ለመገመት ነብይነት ወይንም ጠንቋይ መቀለብ አይጠይቅም።

ስለሆነም ከአራባ ዓመታት በላይ ጎሠኝነትን ያቀነቀኑ እንዳልጠቀመ ተረድተው ከዛ ለመውጣት እየታተሩ ባለበት ወቅት፤ ዛሬ በድንገት ተፈጥረው ከእኔ ዘር በስተቀር ለማለት የበቁትና አገራዊ ድርጅቶች ላይ የሚንጠላጠሉት የውልደታቸው የትነትና የእድገታቸው እንዴትነት ያልታወቀው ዘረኞች በዘረኝነቱ አረንቋ ውስጥ እስከ አንገታቸው ከመዘፈቃቸው በፊት ሰከን ብለው፣ አደብ ገዝተው፣ ፊትና ኋላቸውን ቢያዩ ግራና ቀኛቸውን ቢመረምሩ የሚበጃቸው ይመስለኛል። መሬት ላይ ያለውን እውነት እንዳይመለከቱ፣ በቀናነት የሚነገራቸውንም በጥሞና እንዳያዳምጡ ያገዳቸውን የዘረኝነት ግርዶሽ ከፊታቸው በመግፈፍና መደራጀት መብታችን ነው ከሚለው ደረቅ ሙግት በመውጣት ትናንትን አስታውሰው ዛሬን ተገንዝበው ነገን በመተንበይ የመደራጀት መብታቸውን ከዘረኝነት አስተሳሰብ የጸዳ፣ በግል የሥልጣን ጥም ያልተሸበበ፣ ከራስ በላይ አገርና ሕዝብ በሚል ቅዱስ አስተሳሰብ የተቃኘ ቢያደርጉት ዛሬም ግዜው አላቸው።

እነርሱ የመደራጀት መብት አለን እንደሚሉት ሁሉ፤ እንወክልሃለን የሚሉት ግን ውክልናውን ያልሰጣቸው ወገንም ከመጠየቅ እስከመቃወም መብት እንዳለው፣ እነርሱም ጥያቄውን የመመለስ ተቃውሞውን የማስተናገድ ግዴታ እንዳለባቸው መረዳት ይኖርባቸዋል። የመደራጀት መብት አለን ከሚል ደረቅ ሙግትና በኢትዮጵያዊነት ተደራጅተውና አገራዊ ዓላማ ሰንቀው የአቅማቸውን በተግባር እየሠሩ ያሉትን በጠላትነት ከማየት መላቀቅ የሚቻለው፤ መጀመሪያ ከዘረኝነት ልክፍት ሲጸዱና ጭምብሉን አውልቀው መጣል ሲችሉ ነው። ያኔ ሆኖ መገኘት ቢያቅት እንቅፋት ከመሆን መታቀብ ይመጣል። አገራዊ አስተሳሰብ መያዝ ቢገድ ኢትዮጵያዊነትን ከማጥላላት መቆጠብ ይኖራል፣ መደገፍ ባይቻል ማደናቀፍ ይቀራል። ምን አልባት ይህ የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ምክር ይሰጥ ይሆን።

የሐዋርያው የጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ም. ፲፬፣ ቁ. ፲፫
እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ ርስ በርሳችን አንፈራረድ፣ ይልቁን ግን ለወንድም እንቅፋትን ወይንም ማሰናከያን ማንም እንዳያኖርበት ይህን ቁረጡ፤

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ