የትነበርክ ታደለ

Gambia election 2016

"ነጻነትን እንደ ዛሬ አይቻት አላውቅም!" አንድ ጋምቢያዊ የተናገረው ነው። 22 ዓመት ሙሉ በውስጡ የተሸከመው መርግ ልክ ረዥም ርቀት በጀርባው ኩንታል ተሸክሞ ማውረጃው ሲደርስ ሸክሙን 'ድብ' አድርጎ ወርውሮ እፎይ እንዲል አዲስ የነጻነት ትንፋሽ እየተነፈሰ።

የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋምቢያ ላለፉት 22 ዓመታት በአንድ ኃይለኛ እጅ ተጨምድዳ ተይዛ ኖራለች። ሁለት ሚሊየን እንኳ የማይሞላው ሕዝቧ ያህያ ጀርሚያን (ፕሬዚዳንት) ብቻ ያፈራች ይመስል፣ አማራጭ የሌላት ይመስል አንድ ድምጽ ብቻ እየሰማ ሁለት አስርት ዓመታት አሳልፏል።

ፕሬዚዳንት ያህያ ጀርሚያ ከጦር አለቅነት ወደ መንግሥትነት የተቀየሩት እ.ኤ.አ. 1994 ነበር። ይህ ማለት ደግሞ በጦሩ ውስጥ 10 ዓመት ብቻ ካገለገሉ በኋላ ገና በወጣትነታቸው ነው ሥልጣን የጨበጡት። በመንግሥት ግልበጣ።

ከዚያማ ማን ነክቷቸው። አራት ጊዜ በተካሄዱት አገራዊ ምርጫ ሁሉ እያሸነፉ በትረ ሥልጣኑን ጨብጠው እስከ ትናንትናው ቀን ደርሰዋል።

በሥልጣን ዘመናቸው በርካታ አፋኝ ሕጎችን አወጡ። በዚህም የሚጠቀሰው በነጻው ፕሬስ ላይ የወጣው ሕግ ነው። ይህ ሕግ "ጋዜጠኞች በሙሉ ለመንግሥት ታዘዙ፤ አልያም ወደ ገሀነም እልካችኋለሁ" ያሉ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ ደይዳ ሀድራ የተባለ ታዋቂ ጋዜጠኛ ግድያ ላይ እጃቸው እንዳለበት ይነገራል።

ኤብሪማ የተባለ ጋዜጠኛም እንዲሁ ፕሬዚዳንቱን የሚገዳደር ጽሁፍ በመጻፉ ሳቢያ ለእስር የተዳረገ ሲሆን በኋላም መሞቱ ተነግሯል።

ሰውየው ለጋ ተማሪዎች ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንኳ ታጣቂዎቻቸውን በመላክ በርካታ ተማሪዎች በአደባባይ እንዲገደሉ ማድረጋቸውም በወቅቱ ተዘግቧል። በፍርድ ቤትም ቢሆን የሞት ቅጣት የተለመደ የለት ተለት ተግባር ነበር ሲል አንድ ጋዜጣ ጽፏል።

ፕሬዚዳንቱ ከሕግ አውጪነትም አልፈው ባህላዊ የኤች.አይ.ቪ. መድኃኒት ቀምመው ማግኘታቸውን ለዓለም የተናገሩ ሲሆን፤ በዚህም "ሳይንቲስት" ነኝ እስከማለት ደርሰው ነበር። ይህን ድርጊታቸውን የሞገተችና የተቃወመች የውጭ አገር ዜጋ በ24 ሰዓት ውስጥ አገር ለቃ እንድትወጣም ተደርጋለች።

በዚህ ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በርካታ ጋምቢያውያን ከቤታቸው እየተወሰዱ የት እንደገቡ ሳይታወቅ ቀርተዋል። የጀርሚያን መንግሥት በአፍም በጽሁፍም መቃወም ብቻ ሳይሆን አለመደገፍ መጨረሻው እጅግ የከፋ ነበር። በጠቅላላው ሕይወት ስቃይ ነበር ለጋምቢያውያን።

ቀን ያጋደለባቸው ጀርሚያ ትናንት በምርጫ ውድድር በተቃዋሚዎቻቸው በዝረራ ሊሸነፉ ሰዓታት እንኳ ሲቀራቸው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎትን ጥርቅም አድርገው ዘግተው ነበር። ግን አልቀረላቸውም። አዳማ ባሮው ምርጫውን አሸንፈው ሥልጣን ጨብጠዋል። አገሪቱንም "አዲሲቱ ጋምቢያ" ሲሉ ጠርተዋታል።

ጋምቢያውያን ለዓመታት የናፈቁትን ቀን አይተዋል። ለውጥ አይተዋል። ለዚህም ነው ያ ወጣት "ነጻነትን በዓይኔ አየኋት" ሲል በደስታ እየተፍለቀለቀ ለቢቢሲ ያለ ፍርሀት የተናገረው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!