Hararግርማ ካሳ

ኅዳር 29 ቀን 2009 የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሚል በታሪካዊቷ የሐረር ከተማ በዓል ተዘጋጅቶ ነበር። በዝግጅቱ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር አድርገዋል። ይህ ዝግጅት ለአሥራ አንደኛ ጊዜ ሲሆን በሐረር የተከበረው፣ በአሉን የሕዝቦች እኩልነት፣ አብሮ የመኖር የመቻቻል እሴቶችን ለማጎልበት የታሰበ እንደሆነ የገለጹት፣ ጠ/ሚኒስትሩ አሁን ያለውን ሕገ መንግሥት የሕዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ ሲሉም አሞግሰውታል። ቢሆን ደስ ባለን ነበር፤ ግን ሜዳ ላይ ያለው ሁኔታ ካሉት በጣም የተለየ ነው።

የሐረር ከልል በኢትዮጵያ ካሉ ዘጠኝ ክልሎች መካከል አንዷ ስትሆን፣ እንደሌሎች ክልሎች የራሷ ሕገ መንግሥት አላት። የክልሏ ሕግ መንግሥት ውስጥ በርካታ አንቀጾች ተቀምጠዋል። ሦስት ነጥቦችን ብቻ በማንሳት፣ አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት አሁን ያለው የፌዴራላዊ አወቃቀር በሕዝቦች መካከል መቻቻል፣ መከባበርና አብሮነት እንዲኖር ያደረገ ሳይሆን በአንድ “አማራ” በሚባለው እና አማራ ባይሆንም አማርኛ ተናጋሪው ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ለማሳየት እንሞክራለን።

በ1994 የሕዝብ ቆጠራ መሰረት የሐረሪ ክልል ሕዝብ 131139 ነበር። በ2007 ቁጥሩ ወደ 183415 አድጓል። በ1994 ቆጠራ ውጤት መሰረት አፋን ኦሮሞ አንደኛ ቋንቋቸው የሆኑ 49% ሲሆኑ አማርኛ ተናጋሪዎች 37% ነበሩ። አደሪኛ ተናጋሪዎች 7%፣ ጉራጌኛ ተናጋሪዎች እና ሶማሌኛ ተናጋሪዎች 1% ነበሩ። በ2007 የሕዝብ ቆጠራ ውጤት፣ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ከ49% ወደ 56% ቁጥራቸው ሲያድግ፣ አማርኛ ተናጋሪዎች የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች 27%፣ አደሪኛ ተናጋሪዎች 8%፣ ሶማሌኛ ተናጋሪዎች ደግሞ 3% ሆኑ።

- የሐረሪ ክልል ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 6 ላይ የክልሉ የሥራ ቋንቋ አደርኛና ኦሮምኛ ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል። በዚህም ምክንያት በሐረር ከአደሬዎች ብዛታቸው በሦስት እጥፍ የሚበልጡ፣ የክልሉ አንደ ሦስተኛ የሚሆኑ አማርኛ ተናጋሪዎች በአማርኛ ከክልሉ መንግሥት አስተዳደር አገልግሎት እንዳያገኙ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሄ በሞራል፣ በፍትህ፣ በዴሞክራሲ አንጻር ትልቅ በደል ነው።

- የ1994 እና የ2007 የሕዝብ ቆጠራን ብንመለከት የአማርኛ ተናጋሪዎች በመቶ እጅ ሲታሰብ ቁጥራቸው ቀንሷል። ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ከ49% ብዛታቸው ወደ 56% ብዛት ሲያድግ፣ አማርኛ ተናጋሪዎች ግን ከ37% ወደ 27% ወርደዋል። ይሄ የሆነበት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው። ሥርዓቱ፤ አገዛዙ ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ ይሄንን ማኅበረሰብ ታርጌት ስላደረገ፣ ብዙ አማርኛ ተናጋሪዎች የሚወዷትን፣ የተወለዱባትን፣ ያደጉባት ሐረር፣ አመች ስላለሆነች ጥለው ወደ አዲስ አበባና ድረዳዋ እየተፈናቀሉ ነው።

- የሐረሪ ክልል ሕገ መንግሥት መግቢያው ላይ “የሐረሬ ሕዝብ ምንም እንኳን በምእተ ዓመታት ለሚቆጠር ዘመን ራሱን በራሱ ያስተዳድር፣ በራሱ ታሪክ ወግና ባህል ይኮራ የነበረ ቢሆንም፣ በ1886 ዓ.ም በተደረገበት ወረራ በነፍጠኛው ሥርዓት ሥር ከመውደቁም በላይ ይሄን ሥርዓት ለማስወገድ በተለያዩ ጊዜያት ባደረገው ንቅናቄና ትግል ምክንያት ለግርፋት ለእስራትና ብሎም ለስደት በመዳረጉ በራሱ ክልል በቁጥር አናሳ መሆኑ የተነሳ ልዩ አወካከል ማስፈለጉን በመረዳት“ የሚል ተጽፎ እናገኛለን።

የሐረሬ ብሔረሰብ አባላት የሐረሬ ክልል 7% ብቻ ለመሆናቸውና ቁጥራቸው ለማነሱ የክልሉ ሕገ መንግሥት ተጠያቂ የሚያደርገው በ1886 የተደረገው እና በአጼ ሚኒልክ አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የጨለንቆን ጦርነት ነው። የክልሉ ሕገ መንግሥት፣ ሐረሪዎች የራሳችው አስተዳደር እንደነበራቸውና ከጨለንቆ ጦርነት በፊት በአካባቢው ብዛት እንደነበራቸው ነው ለመግለጽ የሞከረው። ሰነዱ ለይቶ ነው ነፍጠኛ የሚለውን የአማርኛ ተናጋሪ ማኅበረሰብን የሚከሰው።

አሁን ያለው የፌዴራል ሆነ የሐረሪ ሕገ መንግሥታት፣ አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት የሕዝቦችን እኩልነት, አብሮ የመኖር የመቻቻል እሴቶችን ለማጎልበት የታሰቡ ሳይሆን፣ አማራ የሚባለውን እና አማርኛ ተናጋሪውን ማህበሰብ አዎንታ ያላገኘ፣ ይሄን ማኅበረሰብ ሆን ብሎ ለማጥቃትና ለማዳከም የተወጠነ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሁሉም የአገሪቷ ግዛት ሳይሸማቀቁ፣ ሳይፈሩ በእኩልነት መኖር የሚችሉባት አገር እንድትኖር የሚያደርግ፣ ለዜጎች ሙሉ ዋስታና የሚሰጥ፣ ዘመናዊና በዘር ላይ ያልተመሰረተ ሕግ መንግሥት ሆኖ ከስር መሰረቱ መሻሻል ያለበት ነው። በአጭሩ ሐረሪ የሚባል ክልል መኖር አልነበረበትም። ድረዳዋ፣ ሐረርን ያጠቃለለ አንድ ሕብረ ብሄራዊ፣ የ21ኛ ክፍልስ ዘመን አዲስ ክልል ነው እዚያ አካባቢ የሚያስፈልገው።

የሐረሪ ሕግ መንግሥት ስለ ጨለንቆ ጦርነት ሲያወራ በአካባቢው ሌሎች ጦርነቶችን፣ሌሎች ወረራዎችን ያልጠቀሰበት ምክንያቱ ለምንድን ነው? ሐረር አጼ ሚኒልክ በሃይል አስገበሩ ተብሎ አጼ ሚኒልክ እንደ “አውሬ” ተደረገው ሲታዩ፣ ሌሎች ነገሥታቶች፣ ሱልጣኖች፣ የኦሮሞ ገዢዎች፣ ቱርኮች፣ ግብጾች በሐረር የፈጸሙት በደል አለመነሳቱስ ለምን? እንዴት ነው አበባ በትነው ነው የተመለሱት? ደግሞስ ሐረር ከተቆረቆረች ጊዜ ጀመሮ፣ ከግብጾች በኋላ ለጥቂት ዓመታትካልሆነ በቀር፣ በታሪኳ የራሷ ነጻ አስተዳደር ኖሯት የሚያውቀው መቼ ነው? ለነዚህና ለሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ፣ በህወሓቶች፣ በኦነጎችና በጸረ-ሚኒሊካውያን የሚነሱ የተዛቡ የፈጠራ ታሪኮችን ለማስተካከል የሚሞክር አጠር ያለ የሐረር ታሪክ ዳሰሳ ለማድረግ እንሞክራለን።

ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት። በተለያዩ ጊዜ በአገራችን የተለያዩ መንግሥታት፣ ሥልጣኔዎች ነበሩ። አጼ የኑኖ አምላክን በ1287 አካባቢ ሥልጣን ጨብጠው የነበረ ጊዜ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ግማሹን ጅቡቲ፣ ሐረርጌን ሶማሌላንድ የመሳሰሉትን ያካተተ ጠንካራው የሙስሊም መንግሥት የይፋት ሱልጣኔት ነበር። (“Sultanate of Yifat”)። ዋና ከተማውም ዘይላ (አሁን ሱማሌላንድ ያለችው ወደብ) ነበረች።

በዚህ ወቅት፣ የይፋት መንግሥት ግዛት ስር በነበረችው በሐረር አባድር ኡመር አልሪዳ የተባሉ ሼክ ከበርካታ ሌሎች የሙስሊም አስተማሪዎች ጋር በመሆን፣ ከየመን መጡ። በአካባቢው ከሚኖሩ የአርጎባ፣ የሃራላና የጋቱሪ አናሳ ብሔረሰቦች ጋር በመሆኑ በዚያ አካባቢ መኖር ጀመሩ። እንግዲህ የሐረሪ ነዋሪዎች መሰረታቸው ይሄ ነው።

በይፋት ሱልጣኔትና በደጋማው ኢትዮጵያ ክርስቲያን ነገሥታት መካከል በተለያዩ ጉዜያት የተለያዩ ጦርነቶች ተደርገዋል። በወቅቱ የይፋት መንግሥት ዋና ከተማ ሆና ታገለግል የነበረችው አሁን በሶማሌናድ የምትገኘው የዘይላ ወደብ ነበረች። በ1332 አጼ አምደጽዩን የይፋትን ሱልጣን አሸንፈው፣ ጀማላዲን ሱልጣን አድርገው ሾመው ተመለሱ። የይፋት መንግሥት ለአጼ አምደጽዩን ገበሩ። ጀማላዲንን ተክተው የጀማላድኒ ወንድም ናስራዲን ሱልጣን ሆኑ። ከናስራዲን በኋላ የተተኩ የይፋት ነገሥታት በማመጻቸው ጦርነቶች ይባባሱ ጀመር። በ1403 አጼ ዳዊት አንደኛ ዜይላ ድረስ በመዝለቅ ሱልጣን ሳአዲን ሁለተኛን ማርከው ይገድሏቸዋል። የሱልጣኑ ልጆች አምልጠው ወደ የመን ይሻሻሉ።

በዚህ ሁሉ ወቅት ሐረር በይፋት ሱልጣኔት ስር ነበረች። በ1415 ሳብራዲን ሁለተኛ ከየመን ተመልሰው ከሐረር ከተማ በስተደቡብ በነበረች ዳካር ተብላ ትታወቅ በነበረው ከተማ ሰፈረ። በዚህ ሁኔታ የይፋትን እስላማዊ መንግሥት ተክቶ የአዳል እስላማዊ መንግሥት ጀመረ።

የአዳል መንግሥት ራሱን በራሱ ማስተዳደሩ ቢቀጥልም፣ በሱልጣን ሞሐመድ ኢብን ባድሌ እና በአጼ በእደ ማሪያም መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት፣ የአዳል መንግሥት አመታዊ ግብር ያስገባ ነበር። የግዛቱ የኢኮኖሚክ ማእከል የሆነችው የዜይላ ኤሚር፣ ላዴይ ኡስማን፣ ግብር አልከፍልም ብለው አመጹ። ሱልጣኑ ላይ ጦርነት ከፍተው የዳካርን ክከተማ ተቆጣጠሩ። ረገብ ብሎ የነበረው በክርስቲያን ነገሥታት እና በሙስሊም ገዢዎች መካከል የሚደረገው ጦርነት እንደገና ቀጠለ። ኤሚር ማህፉዝ የተሰኑ ጦረኛ የሙስሊም መሪ በ1500 የአጼ ናኦድን ጦር አሸነፉ። አጼው በጦርንቱ ላይ ተገደሉ። ሆኖም ግን በሌላ ጦርነት በ1517 አጼ ዳዊት ሁለተኛ (ኣጼ ልብነ ድንግል) ኤሚር ማህፉዝን ገደሉ።አንዱ እያሸነፈ.፣ ሌላው እየተሸነፈ ድደም መፋሰሱ ቀጠለ።

በ1554 ሱልጣን አቡበከር ኢብን መሐመድ፣ የአዳል መንግሥትን መሪ ሆኑ። ሱልጣኑ ከሦስት መቶ ዓመታት በፊት ከየመን የመጡ እነ ሼክ እነ ሼክ አባድር ኡመር አሪዳ የሰፈሩባትን ሐረር የአዳል መንግሥት ዋና ከተማ አደረጓት። ከተማዋን ከተራ መንደርነት ወደ ተደራጀ ከተማነት ለወጧት።

የአቡበከርን ስልጣን የያዘው በትክክለኛ መንገድ አይደለም በሚል፣ ኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ (ወይም በተለምዶ ግራኝ መሐመድ ተብለው የሚታወቁት)፣ ይቃወማሉ። ከሱልጣኑ ጋር በተደረገ ጦርነት ሱልጣን አቡበከር ይሞታሉ። ግራኝ መሐመድ ወንድማቸውን ኡመር ዲንን ሱልጣን አድርገው ይሾማሉ። የአዳል መንግሥት ሱልጣን የሆኑት ኡመር ዲን ቢሆን፣ የአካባቢው የመስሊም ጦር መሪ ሆነው፣ ከአዳል ግዛት አልፈው በመሄድ፣ ከተወሰኑ ቦታዎች በቀር ድፍን ኢትዮጵያን ማለት ይቻላል፣ ግራኝ መሐመድ፣ ለመቆጣጠር ቻሉ። ግራኝ መሐመድ በጦርነት ላይ ይሞታሉ። እርሳቸውን ተክተው ኤሚር ኑረዲን ሙጃሂድ የሙስሊም ጦር መሪ ሆነው ይቀጥላሉ። እንግዲህ እኝሁ ኤሚር ናቸው ጀጎል ተብሎ የሚታወቀው የሐረር ግንብ የገነቡት።

ከግራኝ ጋር ይደረግ በነበረው ጦርነት፣ አጼ ገላውዲዮስ ወደ ጎንደር አካባቢ ይሸሻሉ። ግራኝ ከሞቱ በኋላ የክርስቲያን መንግሥታት ማዓከል ከሸዋ ወደ ጎንደር ዞረ። ዋና ከተማዋ ሐረር በሆነችው በአዳል ግዛት እና በክርስቲያን ነገሥታት መካከል ይደረጉ የነበሩ ጦርነቶች ቀንሰው በኦሮሞ ተስፋፊዎችና በአዳሎች መካከል ሆነ ችግሩ። በሐረር ይገዙ የነበሩት ኢማም ሙሐመድ ጃሳ ከኦሮሞዎች በሐረር አካባቢ ተከታታይ ጥቃትና ጦርነት ይደረግ ስለነበር፣ ወንድሙን የሐረር እንደራሴ አድርገው የመንግሥታቸውን ዋና ከተማ ከሐረር ወደ አውሳ (ወደ ሰሜን ራቅ ብሎ ከአፋር ድንበር ጋር ወደ ሚገኝ ቢታ) አዞሩ። ኦሮሞዎች የሐረርን አካባቢ በስፋት መቆጣጠር ጀመሩ። ሆኖም ግን በግምቡ መካከል ይኖሩ የነበሩ የቀድሞ ነዋሪዎች፣ በአውሳ ሥር ሆነው ለተወሰኑ ጊዜ ከቂዩ በኋላ፣ በቱርኮች የበላይ ጠባቂነት የሐረር ኤሚሬት (መንግሥት) አቋቋሙ። አሊ ኢብንዳዎድ በ1647 የሐረር የመጀመሪያው ኤሚር ሆኑ። እስከ 1875 ዓ.ም ድረስ የኤሚር አሊ ልጆች በሐረር፣ በኦሮሞዎች ተከበውና ከኦሮሞዎች ጋር ተስማምተው መግዛት ቀጠሉ። ኦሮሞዎች ሙስሊም በመሆናቸውም ከአካባቢው ሕዝብ ጋር ተደባልቆ መኖር አልከበዳቸውም።

በ1870ዎቹ ግብጽ ከቱርክ ነጻ ወጣች። በቱርክ ሥር የነበረችው ሐረርም በግብጾች ቀጥተኛ አገዛዝ ሥር ወደቀች። በ1884 እንግሊዝ መልሳ ግብጽን በመያዟና እንግሊዞችም የሐረርን አካባቢ ስለተው ሐረር እንደገና በማንም ስር ያልሆነች ነጻ ኤሚር ሆነች። ከሁለት ዓመት በኋላ አጼ ሚኒልክ የነ አጼ ዳዊት አንደኛ እና የነአጼ አምደጽዩንን ኩታ በመቀጠል ወደ ሐረር አመሩ። ከሐረር ወጣ ብላ በምትገኝ የጨለንቆ ከተማ በተደረገ ጦርነት የሐረሩ ኤሜር አብዱላሂ ሞቱ። ራስ መኮንን ስዩም የሐረር አገረ ገዢ ሆነው መቀመጫቸውን ሐረር አድርገው መግዛት ጀመሩ። አጼ ሃይለስላሰእም በሀረር የተወለዱት አባታቸው ራስ መኮንን በዚያ ስለነበሩ ነበር። የአጼ ሚኒልክ ወታደርም ሆነው ብዙ አማሮችን ኦሮሞዎች ከሸዋ በመምጣት በሐረርጌ ሰፈሩ። ራሳቸው ራስ መኮንን በአባታቸው ኦሮሞም ነበሩ።

እንግዲህ ከዚህ የምንማራቸው መሰረታዊ ቁም ነገሮች አሉ፡

- ሐረር የብቻዋ አስተዳደር ቢኖራትም ነጻ አስተዳደር (ከሌሎች ሃይሎች ጥገኛ ነጻ ሆና) የነበራት ጊዜ በጣም ውስን ነው። በታሪኳ መጀመሪያ በይፋት፣ ከዚያ በአዳል፣ ከዚያም በቱርክና በግብጽ ሥር የነበረች ከተማ ናት። አዳልና ይፋት ደግሞ ለሸዋ ነገሥታት ይገብሩ የነበረበት ሁኔታ ነው የነበረው። እርግጥ ነው ግብጾች ከሄዱ በኋላ፣ አጼ ሚኒልክ እስኪቆጣጠሯት ድረስ፣ ራሷን የቻለች፣ በማንም ተጽኖ ሥር ያልሆነ፣ ነጻ አስተዳደር ነበራት። ሆኖም ጊዜው ከሦስት ዓመት የማይበልጥ ነበር።

- እነ አጼ አምደጽዩን፣ አጼ ዳዊት የይፋትና የአዳልም መንግሥታት ሲያስገብሩ፣ ግብር እስከከፈሉ ድረስ ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ነበር ያደረጉት። አንዱ ያመጸ ሱልጣን ሲገድሉ፣ ሌላ ሙስሊም ሱልጣን ነበር ተክተው የሚሄዱት።

- በይፋት፣ በአዳል እና በሐረር መንግሥታት ታሪክ ከክርስቲያን ነገሥታት ጋር የተደረገው ጦርነት እንደተጠበቀ፣ በሙስሊሞች መካከል የተለያዩ ከፍተኛ ጦርነቶች ተደርገዋል። በተለይም ከግራኝ አህመድ ሞት በኋላ ዳግማዊ አጼ ሚኒልክ እስኪመጡ ድረስ በሐረር አካባቢ ከክርስቲያን ነገሥታት ጋር ጦርነቶች የተደረጉበት ሁኔታ አልነበረም፡

- አሁን አደሬዎች ወይንም የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት በሐረር ለመቶ ዓመታት የኖሩ ናቸው። ሆኖም ግን ሐረር፣ በተለይም ከጀጎል ውጭ፣ በኦሮሞዎች ቁጥጥር ስር በመሆኗ፣ ከኦሮሞዎች ጋር ሲነጻጸር ቁጥራቸው በጣም ሊዋጥ ችሏል። የሐረሪዎች ብዛት የቀነሰው በዋናነት በኦሮሞዎች መስፋፋት ነው። ታሪኩ ሃቁ ይሄ ሆኖ እያለ፣ ለአደሬዎች ቁጥር ማነስ የጨለንቆውን ጦርነት እንደምክንያት ማቅረብ ታሪክን ማዛባት ነው።

- የሐረሩ ኤሚር አብዱላሂ ለአጼ ሚኒልክ አልገብርም ስላሉ እንጂ የጨለንቆ ጢርነት የተደርገው፣ አጼ ሚኒልክ ጸረ-ሙስሊም ስለሆኑ፣ ወይንም ጦርነትን ስለሚፈልጉ አልነበረም። በጂማ ሌላ ገዢ ጂማ አባጅፋር የአጼ ሚኒልክ ቡራኬ አግኝተው ነበር ሲገዙ የነበሩት። በሰላምና በስምምነት።

የሐረሪ ክልል ሕግ መንግሥት እና የ2007 ሕዝብ ቆጠራ ውጤት ለማወቅ የሚከተሉትን ሊንክ ይመልከቱ፡

https://chilot.files.wordpress.com/2012/02/harari-regional-state-constitution.pdf
http://catalog.ihsn.org/index.php/catalog/3601

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ