Dr Fekadu Bekeleበሰፊ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ያልተደገፈ የፖለቲካ ትግል የሥልጣኔ እንቅፋት ነው!

ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

መግቢያ

በአብዛኛዎቹ የሦስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮችና፣ በጠቅላላው የካፒታሊስት አገሮች ተብለው በሚታወቁትና የሳይንስና የቴክኖሎጂ የበላይነትን በተጎናጸፉት አገሮች ያለውን ልዩነት ስንመለከት ልዩነቱ እጅግ ከመስፋቱ የተነሳ እንደዚህ ዐይነቱን የተወሳሰበ ሕብረተሰብ ለመገንባት የብዙ መቶ ዓመታት ሥራ እንደሚያስፈልገን ይታየኛል። በአጠቃላይ ሲታይ የካፒታሊስት አገሮች ይህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ደርሰው ዓለምን መቆጣጠር ሲችሉ እኛን ምን ነካን ብለን የምንጠይቅ ብዙ ላንሆን እንችላለን።

እንደሚታወቀው እንደዚህ ዐይነቱን ጥያቄ ሊያነሱ የሚችሉት ሰዎች በጣም የተወሰኑና የአንድን ሕዝብ ዕድል ሥልጣን ከመያዝ ባሻገር ሊያዩ የሚችሉ ሰዎች ብቻ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ያም ሆነ ይህ የእነሱን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሚሊታሪ የበላይነትና ዓለምን መቆጣጠር ጠጋ ብለን በምንመረምርበት ጊዜ የምናገኛው መልስ እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈውና፣ በተለይም ደግሞ የአዕምሮን ዋና ቁልፍነት በመረዳትና፣ ከዚህ የሚፈልቀውን የማሰብ ኃይል ቅድሚያ በመስጠት እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። ይሁንና ግን የአውሮፓውን የምሁር እንቅስቃሴና የሕብረተሰብ አገነባብ ታሪክ ለተከታተለ የተፈጥሮንና የሰውን ልጅ ሚና፣ እንዲሁም የፖለቲካን ትርጉም ለመረዳት የተለያየ አስተሳሰብና የጦፈ ትግልም ይካሄድ እንደነበር መገንዘቡ እስከዚህም ከባድ አይደለም። በተጨማሪም ሥልጣን መጨበጥና በአንድ ዶግማ ወይም አመለካከት መመራት ስር የሰደደም እንደነበር እንገነዘባለን። ይህም ማለት አንዳንዶች ካልሆኑ በስተቀር ሥልጣን ላይ ቁጥጥ የሚሉት ኃይሎች ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልጓቸው ዕቅዶች ሁሉ በጊዜው በነበረው ምሁራዊ ኃይል ጥንካሬና የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ፣ በራሳቸው ሥልጣን በጨበጡት ኃይሎች የንቃተ-ህሊና ሁኔታና በአካባቢያቸው ባሉ አገሮች የዕድገትና የፀረ-ዕድገት ሁኔታ የሚወሰን እንደነበር መገንዘብ እንችላለን።

የአገራችንና የሌሎችን የአፍሪካ አገሮችን ሁኔታ ስንመረምር ግን ከሃምሳ ዓመት “የፖለቲካ ነፃነት“ በኋላ አሁንም ቢሆን እዚያው በዚያው ሲንደፋደፉና፣ ሥልጣን ላይ ቁጥጥ የሚሉት ኃይሎች በሙሉ የራሳቸውን ኑሮ ከማደላደልና ዝናን ከመጎናጸፍ በስተቀር ሕብረተሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፓለቲካዊና እንዲሁም የባህል ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዳልሆኑ በምድር ላይ የሚታየው ሁኔታ ያረጋግጣል። ለዚህ ዋናውና አንደኛው ምክንያት የባሪያ ንግድና የቅኝ-ግዛት አስተዳደር የአፍሪካን የሕብረተሰብ አወቃቀር ስላዘብራረቁትና ቀስ ብሎ የማደግ ዕድገቱን ስላጨናገፉበት ታሪክ ሊሰራ የሚችል የሕብረተሰብ ክፍልና ኢንስቲቱሺናዊ አወቃቀር ሊዳብሩ ያለመቻላቸውን ታሪክ ያረጋግጣል። በተጨማሪም የፖለቲካ ነፃነትን ተቀዳጁ ከተባለ በኋላ በራሳቸው ጥረት አገሮቻቸውን እንዳይገነቡ ብዙ አሻጥሮች ይሰራባቸው እንደነበር ይታወቃል። ፖለቲካዊ መረጋጋት እንዳይኖርና አትኩሮአቸው በበሕብረተሰብ ግንባታ ላይ እንዳይሆን የአብዛኛዎቹ አፍሪካ አገሮች ከስድሳ በላይ የሚቆጠሩ የመንግስት ግልበጣዎች ተካሂዶባቸዋል።

ወደ ኢትዮጵያችን ስንመጣ ግን አገራችን የሦስት ሺህ ዓመት ታሪክ ያላትና በቅኝ-ገዢዎች ቁጥጥር ስር ያልነበረች አገር ነች እያልን ብንመፃደቅም፣ የሕብረተሰብን አገነባብና የኢኮኖሚ ዕድገትን ጉዳይ፣ እንዲሁም ደግሞ አጠቃላዩን የሥልጣኔ ፕሮጀክት በሚመለከት እስከዚህም ድረስ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሽለን የምንገኝ እንዳልሆነ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታና የራሳችንም የፖለቲካ ትግልና የአስተሳሰባችንም ሁኔታ በበቂው ያረጋግጣል። ያለፈውን የሃምሳ ዓመት ታሪካችንን ለተከታተለ በተደጋጋሚ በረሃብ የሚታወቅና ለልመና የዓለምን ማኅበረሰብ የሚማፀን እንደኛ ያለ አንድም የአፍሪካ አገር የለም። ይህም የሚያረጋግጠው እኛ የሦስት ሺህ ዓመት የሥልጣኔ ታሪክ አለን እያልን የምንመፃደቀው እስከዚህም ድረስ የማኅበረሰብዓዊና የሕብረተሰብዓዊ ኃላፊነት እንደሌለንና፣ ንቃተ-ህሊናችንም ሕዝባችን ከሚመኘው የሥልጣኔና የሰላም ፕሮጀክት ጋር በፍጹም የሚጣጣም እንዳልሆነ ነው።

ከዚህ ስነነሳ በተለይም አብዮቱ ፈነዳ ከተባለበት ጀምሮና እስከዛሬ ድረስ ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍና ሁኔታ ስንመረምር የፖለቲካ ተዋናይ ነን የሚሉት ዋና ተግባርና ዓላማ ሥልጣንን ከመጨበጥ ጋር የተያያዘ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። በጊዜው የተነሳው የፖለቲካ ጥያቄ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ትክክል ቢሆንም፣ ይህ በራሱ የሥልጣኔ ፕሮጀክትና ቁልፉም እንዳልሆነ በሳይንስ ማረጋገጥ እንችላለን። ያም ሆነ ይህ በተለይም ሥልጣኔን ማዕከላዊ ያላደረገ የፖለቲካ አካሄድ የመጨረሻ መጨረሻ ለደም መፋሰስና ዛሬ አገራችን ለምትገኝበት ሁኔታ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል ማለት ይቻላል። በጊዜው የፖለቲካ ተዋንያን የነበሩት ድርጅቶችና ዛሬም በህይወት የሚገኙት መሪዎቻቸው ለመቀበል የማይፈልጉትና የማይዋጥላቸውም ነገር እነሱ ብቻ የታሪክ መነሻና መጨረሻው አድርገው መውሰዳቸው ብቻ ሳይሆን፣ እነሱ ብቻም የዕውቀትን ቁልፍ እንደያዙ መረዳታቸውን ስንገነዘብ በጣም ነው የምናዝነው። ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት የታሪክን ኃላፊነት ሊወጣ የሚችለው በየጊዜው ራሱን መመርመር የቻለና ከሌሎች እሱን ቀድመው ከሄዱ ጋር ማወዳደር ሲችልና ትምህርትም ሲቀስም ብቻ ነው። ይህንን በሚመለከት ያ ብዙ የተጠበቀበትና ወደ መጨረሻ ላይ ደም ማፋሰስ ያበቃ አብዮት ለምንድነው ያልተሳካ? ብሎ ከራሱ ስሜት ውጭ ኦብጀክቲብ በሆነ መንገድ የራሱን ቦታ የመረመረና በጥናት መልክ ለተከታዩ ትውልድ ያቀረበ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ የለም። ሁሉም በየፊናው የራሱን ሚና ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ስለሚፈልግ በአብዮቱ ውስጥ ላልተሳተፈው እንደኛ ላለው የነበረውን ሁኔታ በቀላሉ ሊገነዘብው በፍጹም አይችልም። አዲስ ኃይል ብቅ ብሎ ወገናዊ አቋም ሳይወስድ የብዙ ዓመታት ምርምር ካደረገ በኋላ ምናልባት ሀቁን መረዳት እንችል ይሆናል።

ያም ተባለ ይህ በማንኛውም አገር አንድ ሕዝብ የዕድገትና አጠቃላይ የሆነ የሥልጣኔ ባለቤት እንዲሆን ከተፈለገ ተቀባይነትን ካገኘ (Conventional Wisdom) የትግልት ስልትና ዕውቀት ባሻገር አልፎ መሄድ እንዳለበት መረዳት አለበት። እንደምንመለከተው ከስላሳ ዓመት የግሎባል ካፒታሊዝም የበላይነት ዘመን በኋላ የዓለም ማህብረሰብ በመረጋጋት ላይ ያለ አይደለም። አብዛኛዎቹ የሦስተኛው ዓለም አገሮች ተብለው የሚጠሩት፣ በተለይም የአፍሪካ አገሮች በትርምስ ውስጥና የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ። ከዚህ በመነሳት የታወቁ የሥልጣኔ ተመራማሪዎች እንደሚሉትና እንደሚያረጋግጡት የዓለም ሁኔታ በዚህ መቀጠል ያለበት ሳይሆን የግዴታ በከፍተኛ ንቃተ-ህሊና በመታገዝ (Quantum Consciousness) ወደ ዕድገትና ወደ ከፍተኛ ሥልጣኔ ማምራት እንዳለበት ያሳስባሉ። ስለሆነም እኛም ከዚህ ውጭ መሆን ያለብን አይመስለኝም። በአገራችን ምድር ዕውነተኛ ሥልጣኔና በግለሰብ ፈጠራ ላይ የተመረኮዘ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ዲሞክራሲያዊ ነፃነት እንዲመጣ ከፈለግን የትግል ስልታችንን መቀየር አለብን። ሽወዳን ሳይሆን ሀቀኝነትንና ፕሪንስፕልን በማስቀደም ወደፊት ወጥተን መታገል አለብን። መድረኩን ሰፋ ላለ ምሁራዊ ጥናትና ክርክር መክፈት አለብን። ታሪክ እንደሚያረጋግጠው አስተሳሰቡን የገደበና ለክርክርና ለውይይት ያልተዘጋጀ ሕብረተሰብ በምንም የሥልጣኔ ባለቤት ሊሆን እንደማይችል ነው።

በታሪክ ውስጥ ከላይ ወደታች የመጣ ሥልጣኔና ዴሞክራሲያዊ ነፃነት አልታየም

በታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው ሥልጣንን የጨበጡ ኃይሎች በራሳቸው ፈቃድ ዲሞክራሲን ያወጁበትና የሥልጣኔ ፕሮጀክት የነደፉት ጊዜ በጣም አነስተኛ ነበር። ይህም በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን፣ ሶሎን የሚባለው መሪ ልዩ የሆነ ፍጡርና ጊዜው የወለደው (Zeitgeist) ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ሶሎን ተራ ፖለቲከኛ ሳይሆን ሕብረተሰብና ሥልጣኔ ማለት ምን ማለት እንደሆኑ የገባውና የሰውን ልጅነት ምንነት የተረዳ ታላቅ መሪ እንደነበር መገንዘብ እንችላለን። ፈላስፋና ገጣሚ እንዲሁም የቲያትር ደራሲ እንደመሆኑ መጠን ፖለቲካን የተረዳው ከቀን ተቀን ተግባራዊ ሂደት አልፎ ሰፋ ያለ የሥልጣኔ ፕሮጀክት መንደፊያ አድርጎ በመረዳቱ የግሪክ የፊዩዳል አሪስቶክራሲ መደብ ጭንቅላቱን ከተበተበውና የሕብረተሰብን ዕድገት ከሚቀናቀነው አስተሳሰቡ እንዲላቀቅ በማድረግ ሕብረተሰቡን አንቀው ያየዙ ማነቆዎችን ለማስወገድ ቻለ። በሱ ሰፋ ያለ የጥገና ለውጥ የተነሳ ለመጀመሪያ ጊዜ በግሪክ በተለያዩ ግዛቶች ውስጥ በተለይም ሂሌን በሚባሉት ግዛቶች ውስጥ ሥልጣኔ ማሸብረቅ ቻለ። ፍልስፍና፣ ማቲማቲክስ፣ አርኪቴክቸር፣ ሰዕልና ድራማ፣ እንዲሁም ግጥሞችና ሙዚቃ፣ ክርክርና የሊትሬቸር አጻጻፍ፣ በተጨማሪም ልዩ ዐይነት የታሪክ አተረጓጎም ሥራዎች እንደአሸን በመፍለቅ በተለይም የታዳጊውን ትውልድ ጭንቅላት በመያዝ የሥልጣኔ መረብ ውስጥ ከተቱት። የግሪክ ሕዝብ ራሱን በራሱ ሲያገኝ ዋናው የዲሞክራሲና የነጻነት እንዲሁም የሥልጣኔ ፕሮጀክት ከራሱ የሚመጣ እንደሆነ መረዳት ቻለ። ሥራዎች ሁሉ በስርዓትና በግንዛቤ የሚሰሩ፣ ዲሞክራሲያዊ ህይወትና ሥልጣኔ እንዲሁም ግለሰብዓዊ ነፃነትና ሕብረተሰብዓዊ ኃላፊነት፣ በተጨማሪም ሞራልና ስነ-ምግባር ተያይዘው እንደሚሄዱ ግንዛቤ ውስጥ ተገባ። ይሁንና ግን ሥልጣን ላይ የተቀመጡት ኃሎችም ወሳኝ ሚናን የሚጫወቱ ስለሆነ፣ ተፈጥሮአዊና የኮስሞስን ሕግ ሳይሆን በራሳቸው ስሜትና ኤጎ የሚመሩ ከሆነና ወደ ውስጥ ጭንቅላታቸውን የማይመለከቱ ከሆነ የግዴታ የጦርነትና የድህነት ምንጮች ሊሆኑ እንደሚችሉ በፕላቶንና በሶክራተስ እንዲሁም በአርስቲቶለስ ዘንድ ከፍተኛ ግንዛቤ ነበር። ስለዚህም ነው ፕላቶ ፖለቲከኞች የፍልስፍና አዋቂዎች መሆን አለባቸው ወይም ደግሞ ፖለቲካ በፈላስፋዎች መመራት አለበት የሚለው።

የሶክራተስና የፕላቶን እንዲሁም የአርስቲቶለስ አመለካከት በፖለቲካ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ስለ ኢኮኖሚ ያላቸው ግንዛቤም የቱን ያህል እንደነበረ መገንዘብ እንችላለን። በነሱ ትክክለኛ አመለካከት አንድ ማኅበረሰብ የግዴታ በሥራ-ክፍፍል መደራጀት ሲኖርበት፣ በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች መሀከል በገንዘብ ሊገለጽ የሚችል የንግድ ግኑኝነት መፈጠር እንዳለበት ያሳስባሉ። ይህም ማለት አንድ ሕብረተሰብ የግዴታ ተከታታይነት ሊኖረው የሚችለው ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መሰረት ሲዘረጋለትና፣ ሕዝቡም በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰማርቶ የመፍጠር ችሎታውን ተግባራዊ ለማድረግ አመቺ ሁኔታ የተፈጠረለት እንደሆነ ብቻ መሆኑን ያሳስባሉ። ይሁናን ግን የገንዘብን ጉዳይ በሚመለከት ከሕብረተሰቡ ፍላጎት ውጭ መውጣት እንደሌለበትና የሰውንም ሞራል እንዳያበላሽ ሆኖ መካሄድ እንዳለበት ያሳስባሉ።

ያም ሆነ ይህ በግሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለው ዲሞክራሲ አንዳንድ የኢትዮጵያ የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች በጊዜው ለማሳመን እንደሚሞክሩት ከገዢው መደብ አንፃር ብቻ ታይቶ ተግባራዊ የሆነ ሳይሆን፣ ስፋ ያለ ፕሮጀክት ያለውና፣ ለሥልጣኔና ለግለሰብዓዊ ነፃነት በር የከፈተ ከፍተኛ የጥገና ለውጥ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ስለሆነም ነው ይህ የዲሞክራሲና የሥልጣኔ ፕሮጀክት ከአሥራአራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ብቅ ላለው የተሃድሶ (Renaissance) መሰረት ሊሆን የበቃው።
በአሥራአራተኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያለውና እየተስፋፋ የመጣው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ከግሪኩ ለየት የሚያደርገው ከላይ ወደ ታች የተወረወረና ከስር በመነሳት ደግሞ እየተቀጣጠለ በመምጣት ለሥልጣኔ በር የከፈተ ሳይሆን ግለሰቦች በራሳቸው ተነሳሽነት ያቀጣጠሉትና፣ አንድ ሕዝብ በጊዜው ሰፍኖ በነበረው እጅግ አሰቃቂ ሁኔታ መኖር የለበትም ብለው በተረዱ በከፍተኛ ዕውቀት በታነጹ ምሁራኖች አማካይነት ነው። የነዚህ ምሁራንም ዋና ዓላማ ሥልጣንን መያዝ ሳይሆን በሁሉም መልክ የሚገለጽን ሥልጣኔን ማምጣት ነበር። ዳንቴ፣ ጀርመናዊ ቄስ ኩዟኑስ፣ ፔትራርካ፣ ጋሊሊዮ፣ ዳቪንቺ፣ ሚካኤል አንጀሎና ብሩኖ ጋርዲያኖና፣ ሌሎችም ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ ፈላስፋዎች፣ የማቲማቲክስና የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች፣ የህንፃና የከተማ ዕቅድ አውጭዎችና፣ ለተፈጥሮ ልዩ ውበት ለመስጠት የሚንቀሳቅቀሱ የተገለጸላቸው ኃይሎች በሙሉ ጭንቅላታቸው በሥልጣን የተሳከርና ሥልጣን ለመያዝ የሚቅበዘበዙ ሳይሆኑ፣ ዋናው ዓላማቸው ሥልጣኔ ወይም ሞት ብለው በመነሳት ዲሞክራሲያዊ ህይወት ሁለንታዊነት ያለውና የተፈጥሮና የህዋን ሕግ በመረዳትና ተግባራዊ በማድረግ ይገለጻል ብለው በማመናቸው ነው ውብ ውብ ነገሮችን ሊሰሩ የቻሉት። አስተሳሰባቸው ልቅ ያለ ሳይሆን በፍልስፍና ላይ የተመሰረተና ስልትን የተከተለ ሳይንሳዊ አካሄድ ነበር።
የሪፎርሜሽንና የኋላ ኋላ ደግሞ በኢንላይተንሜንት የተገለጸውን ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ስንመለከት በጊዜው ከነበረው የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ባሻገር የተደረጉ በግለሰቦች ተነሳሽነት ተግባራዊ የሆኑ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ታሪክ ያረጋግጣል። የግዴታ በተለያየ መልክ የሚገለጹት እንቅስቃቅሴዎች እየተስፋፉና ስር እየሰደዱ ሲመጡ ሥልጣን ላይ ተቀምጠው ድህነትን የሚያራምዱትን መሪዎች መፈናፈኛ አሳጧቸው። የገዢ መደቦችና የኃይማኖት መሪዎች አንዳንድ ሊቃውንቶችን በማቃጠልና በመስቀል እንቅስቃሴውን ሊያግዱት ቢሞክሩም የመጨረሻ መጨረሻ እየተስፋፋ የመጣው እንቅስቃሴና በተጨማሪም ደግሞ ራሱን እየቻለ በማደግ ላይ የሚገኝውን በኢኮኖሚ ተሳትፎነት እየበለጸገ በመጣ ኃይል በመወጠራቸው የሥልጣኔውን ፕሮጀክት በፍጹም ሊያቆሙት አልቻሉም። ይህ ዐይነቱ ሂደት በተለይም የማርቲን ሉተሩ የኃይማኖት ህዳሴ እንቅስቃሴ ብቅ ካለበትና ሰፋ እያለ ከመጣበት ጀምሮ በኃይማኖትም ሆነ በፖለቲካ መሀከል ያለውን አሰላለፍና የአስተሳሰብ ልዩነት ግልጽ እያደረገው መምጣት ቻለ። በተለይም የፕሮቴስታንት ዕምነትን የተቀበሉት የሕብረተሰብ ክፍሎች በካቶሊክ ኃይማኖት ተከታዮች ላይ በማመጽና አብዮት በማካሄድ ለከበርቴው አብዮትና ለኢንዱስትሪ ካፒታሊዝም በር እንደከፈቱ ግልጽ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደ ሊበራሊዝም የመሳሰሉት አስተሳሰቦች በመስፋፋትና የከበርቴውን የበላይነት በማወደስ ለካፒታሊዝም ዕድገት የበላይነትን መቀዳጀት ሁኔታውን እንዳመቻቹ እንመለከታለን። እዚህ ላይ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ኃይልም ለሕብረተሰብዓዊ ዕድገትና ለቴክኖሎጂ ምጥቀት ወሳኝ ሚናን እንደተጫወቱ መረዳት ይቻላል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምሁራዊ አስተሳሰቦች እየተስፋፉ በመምጣት እንደ ፖለቲካ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉት ራሳቸውን የቻሉ ዘርፎችና መከራከሪያ ነጥቦች ሆነው በመውጣት እያደገ በመምጣት ላይ ላለው የከበርቴ መደብና የፖለቲካ ተጽዕኖ ማድረግ ለቻለው የሕብረተሰብ ክፍል ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን በስነስርዓት ሊያካሂድና ግለሰብዓዊና ሕብረተሰብዓዊ ሀብት ለመፍጠር የሚችልበትን ዘዴ ማግኘት ቻለ። የሊበራሊዝም አስተሳሰብ ሲስፋፋና ነፃ የገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚለው በመንግስት ደረጃ ሲካሄድ ተጠቃሚው ጠቅላላው ሕዝብ መሆኑ ቀርቶ የከበርቴው መደብ ብቻ ሆነ። ይህ ዐይነቱ የነፃ ገበያ ፖሊሲ በእንግሊዝ አገር ድህነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፋ አደረገ። እንደዛሬው የሦስተኛው ዓለም አገሮች አስከፊ ሁኔታዎች በመፈጠር በደሃና በሀብታም መሀከል ያለውን ልዩነት ጉልህ አድርጎ ማሳየት ቻለ።

ይህ ዐይነቱ የሊበራሊዘም አስተሳሰብ ዕውነተኛ ሕብረተሰብዓዊ ነፃነትን ሊያመጣ እንደማይችል የተረዱ የጀርመን ፈላስፋዎች የእንግሊዙን ኢምፔሪሲስታዊ አስተሳሰብ በመቃወምና የራሳቸውን አስተሳሰብ በማዳበርና ከግሪኩ ጋር በማነፃፀር ለጀርመኑ የሥልጣኔ ፕሮጀክት መሰረት ይጥላሉ። ይህንና ግን ይህ ዐይነቱ የሥልጣኔ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለመሆን የግዴታ ሥልጣን በያዙ ኃይሎች ዘንድ ፉክቻን እንዳስከተለና፣ የኋላ ኋላ ከእንግሊዙ ለየት ያለ የሊበራል አስተሳሰብ ያላቸው ኃይሎች የበላይነትን በመቀዳጀት ሰፋ ላለው የሥልጣኔ ፕሮጀክት በር እንደከፈቱና እስከተወሰነም ደረጃ ድረስም የመሬት ከበርቴውን የበላይነት ገፍትረው ለመጣል እንደቻሉ መገንዘብ እንችላለን። ልክ እንደ ጣሊያኑና እንደ እንግሊዙ የኢላይተንሜንት እንቅስቃሴ የጀርመኑም በግለሰቦች የተካሄደና አንድ ቦታ ላይ በመቀጣጠል ቀስ በቀስ ሰፋ ላለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በር የከፈተ ነው። ኬፕለር፣ ጋውስ፣ ሁለቱ ወንድማማች አሌክሳንደር ሁምቦልድና ቪሊሄልም ሁምቦልድ፣ ሳይንቲስቱና ፈላስፋው ላይቢኒዝ፣ ሺለርና ጎተ፣ ካንትና ሄገል እንዲሁም ማርክስ፣ እነዚህና አያሌ ፈላስፋዎችና የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ሥልጣንን ሳይሆን ሥልጣኔን በማስቀደም ሰፋ ላለው የሕብረተሰብ ፕሮጀክት በር የከፈቱ ታላላቅ ምሁራን ናቸው። በእነሱ የምርምር ዘዴና የቴክኖሎጂ ግኝት አማካይነት ነው ካፒታሊዝም ቀስ በቀስ የበላይነትን ሊቀዳጅ የቻለው። ይሁንና ግን የእነዚህ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ምርምርና ዕውቀት ዓለም አቀፋዊ (Universal) ሲሆን፣ ዓላማቸውም በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ ሰላምና ስምምነት እንዱሁም ሥልጣኔ እንዲዳረስ ማድረግ ነበር። ዓላማቸውም ካፒታሊዝምን ማሳደግ ሳይሆን በቴክኖሎጂ ምጥቅት አማካይነት የሰውን ልጅ ኑሮ ለማሻሻል ነበር። ትምህርታቸው ዓለም አቀፋዊ እንጂ ብሔራዊ እንዳልሆነ ጹሁፋቸውን ላነበበ መረዳት ይቻላል። አስተሳሰባቸው ከማንኛውም ተንኮልና ዕቡይ አስተሳሰብ ውጭ የነበረና ሰብዓዊነትን ያካተተ ከፍተኛ የጭንቅላት ሥራ መሆኑን እንረዳለን።

ይህ ዐይነቱ ሰፋ ያለና ስር የሰደደ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በአስተሳሰቡ የዳበረ፣ የፖለቲካን ትርጉም የተረዳና ብሔራዊ ባህርይ ያለው የሕብረተሰብ ክፍል ብቅ እንዲልና፣ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ ያለውንና ዕድገትን የሚቀናቀንን ኃይል ገፍትሮ በመጣል ኃይሉን ሁሉ በኢንዱስትሪ አብዮት ላይ በማትኮር ብሔራዊ ኢኮኖሚ እንዲገነባ ማድረግ እንዳስቻለው መገንዘብ ይቻላል። ይህ የሕብረተሰብ ክፍል የተገለጸላቸውን የሚሊታሪና የሲቪል ሰዎችን ያቀፈ ሲሆን፣ የእነዚህ ምሁራን ዋና ዓላማ ርስ በርስ መሻኮትና ተንኮል በመሥራት ብሔራዊ አጀንዳን ማጨናገፍ ሳይሆን አንድ ሕብረተሰብ እንዴት አድርጎ በጠነከረ መሰረት ላይ ሊገነባ ይችላል በሚለው ላይ ያተኮረ ነበር። ሃርደንበርግ፣ ፍራይኸር ፎን ስታይን፣ ቢስማርክ፣ ግናይዘናውና ሻርንሆርስት፣ አርኪተክቸሩ ሺንክል፣ ኢንጂነሩ ቦይትና ሌሊች የሲቪልና የሚሊታሪ ሰዎች ሰፋ ያለውና ጥልቀትን ያገኘው የምሁራዊ እንቅስቃሴ ውጤቶች ናቸው። እነዚህ ምሁራን በጊዜው ቀድመው የሄዷቸውን እንግሊዝንና ፈረንሳይን በመጎብኘት ከተመለሱ በኋላ ከእነሱ የተሻለና ጥበባዊ ሕብረተሰብ መገንባት አለብን ብለው በቆራጥነት የተነሱ ታላላቅ ሰዎች ናቸው። ዕውቀታቸውም ሁለ-ገብና የጠለቀ በመሆኑ ሥራዎቻቸው በሙሉ ዘላቂነት ያለውና ጥበባዊ ነበር። ስለሆነም ከዚያ በኋላ የተነሳው ተከታታይ ትውልድ አገሩን በዚያው ላይ ተመርኩዞ ለመገንባትና ለማጠናክር ከፊቱ የተደቀነ አስቸጋሪ ሁኔታ አልነበረበትም። ይሁንና እንደዚህ ዐይነቱ ፖለቲካ በአውሮፓ ውስጥ ተመሳሳይነት አልነበረውም። ብሔራዊ ባህርይን ባላዳበሩ እንደነ ፖርቱጋልና ስፔይን የመሳሰሉ አገሮችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ወርቅና ብርን በመዝረፍ ባተኮሩ አገሮች ወደ ውስጥ በቀጥታ ብሔራዊ ባህርይ ያለው መደብ እንዳይፈጠር እንቅፋት በመፍጠር ዕድገትን አጨናግፈዋል ማለት ይቻላል። የተገለጸላቸውንና ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸውን በተለይም አይሁዲዎችን በማባረር ዕድገትን ለማጨናገፍ በቅተዋል። እነዚህ ኃይሎች ሆላንድና እንግሊዝ አገር በመሰደድ ለዕድገትና ለሥልጣኔ መሰረት ሊጥሉ ችለዋል።

ከዚህ ሁሉ እጅግ አጠር መጠን ብሎ ከተዘረዘረው ምሁራዊ እንቅስቃሴ የምንረዳው ቁም ነገር ለሥልጣን የሚታገሉና ሥልጣኔን ተግባራዊ እንዲሆን የሚታገሉ ኃይሎች የተለያየ ዓላማ እንዳላቸው ነው። በተጨማሪም አንድ የሕብረተሰብ ኃይል ብሄራዊ ባህርይ ለመያዝና ሰፋ ያለ የሥልጣኔ ፕሮጀክት ለመንደፍ ራሱ ሰፋ ያለ የምሁራዊ እንቅስቃሴ ውጤት መሆን አለበት። ዕድገትንና ሥልጣኔን ሁለመንታዊ በሆነ መልክ ለመረዳት ሁለ-ገብ የሆነ ምሁራዊ እንቅሳቅሴ ለአንድ ሕብረተሰብ ቀሰ በቀስና እንዲሁም በሰከነና በጠነከረ መሰረት ለመገንባት ዋናውና መሰረታዊ ቅድመ-ሁኔታ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በሌላ ወግን ደግሞ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ኃይሎች የፖለቲካ ስልትና አካሄድ በኃይል አሰላለፍ መለዋወጥ እንደሚለወጥና፣ በኢኮኖሚ ጠንከር ብሎ የሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል በፖለቲካው መስክ ላይ ተጽዕኖ ማድረግ እንደሚችልና የዕድገትንም አቅጣጫ ለሱ በሚስማማው መልክ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ እንደሚችል ከአውሮፓው የሕብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ውስጥ መማር ይቻላል። ስለሆነም ለሥልጣን የሚታገሉና ሥልጣንም ላይ ቁጥጥ የሚሉ ኃይሎች ዕድገት የሚለውን ፕሮጀክት የሚረዱትና ተግባራዊም የሚያደርጉት በተወሰነ መልክ ብቻ ይሆናል። አስተሳሰባቸው የፖለቲካን ትርጉም ከሥልጣን መያዝ ብቻ ጋር ስለሚያያይዙትና ሥልጣንንም ቶሎ ብለው ላለመልቀቅ ስለሚፈልጉ የሆነ ያልሆነ ዘዴ በመፈለግ አንድን ሕዝብ መሉ በሙሉ ነፃ ሊያወጣ የሚችለውን የሥልጣኔ ፕሮጀክት አሽቀንጥረው ይጥላሉ። በተለይም ዕውቀት የሚባለውን ነገር በሌላ መልክ በሚተረጉሙትና ወደ ርዕዮተ-ዓለምነት በሚለውጡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አማካሪዎች በሚከበቡበት ጊዜ ሳይወዱ በግድ የተወሰነ ሕብረተሰብ-ክፍልን ጥቅም ብቻ የሚያንፀባርቅ ፖሊሲ በማውጣት ተግባራዊ ያደርጋሉ። በዚህም መልክ የዲሞክራሲና የነፃነት ጥያቄ ተጣሞ እንዲቀር በማድረግ በአንድ ሕብረተሰብ ውስጥ የሀብት ክፍፍል በተዛባ መልክ እንዲዳረስ ያደርጋሉ። በሌላ ወገን ግን በከበርቴው ሕብረተሰብ ውስጥ ሰፋ ያለ የሲቪል ማኅበረሰብ ስለዳበረና በየጊዜው የሚከሰቱ መዛባቶችን ስለሚያጋልጥ ሥልጣንን የጨበጡ ኃይሎች እንደፈለጉት የአንድን ሕብረተሰብ ጥቅም የሚያስጠብቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብቻ በቀላሉ ተግባራዊ ሊያደርጉ አይችሉም።

ያም ሆነ ይህ ዕድገት ሁለንታዊ ባህርይ እንዲኖረው ከተፈለገ ሰፋ ባለ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ክርክር መደገፍ እንዳለበት ከአውሮፓው የሕብረተሰብ አገነባብ ታሪክ መገንዘብ ይቻላል። በሁሉም መልክ የሚገለጽ በጭንቅላት ምርምር ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ በማይካሄድበት አገር ዕውነተኛ የሥልጣኔ ፕሮጀክት በፍጹም ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። በተለይም በአሁኑ ዘመን በካፒታሊዝም መስፋፋትና በኒዎ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ የሁላችንንም ጭንቅላት በያዘበትና በሚያሽከረክርበት ዘመን የግዴታ የሃሳብ ጥራት እስከሌለና ህይወትንም እስከማጣት የሚያደርስ ድፍረት የተሞላበት ክርክር እስካልተካሄደ ድረስ አንድ ሕዝብ ዕውነተኛ ነፃነትንና ሥልጣኔን ሊጎናጸፍ በፍጹም አይችልም። ስለዚህም ትግሉ ሥልጣኔን በሚመኘው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብና፣ በዚህም በዚያም ብሎ የሕዝባችንን ህልምና ምኞት ለማኮላሸት እዚህና እዚያ በሚሯሯጠው፣ ይህንን ወይም ያንን የፖለቲካ ፓርቲ ስም በያዘ መሀከል የሚደረግ የሞት-የሸረት ትግል ነው ማለት ይቻላል። ወደድንም ጠላንም የወደፊቱ ትግልም ሥልጣኔን በሚመኙትና፣ ተግባራዊ ለማድረግ በሚፈልጉ በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሥልጣንን ለመያዝ በሚሽቀዳደሙና ዕውነተኛ ዕድገት እንዳይመጣ በሚፈልጉ ኃይሎች መሀከል ይሆናል።

በአገራችን ምድር ለዲሞክራሲና ለሥልጣን የተደረገውና የሚደረገው ትግል

የአገራችንን የፖለቲካ ትግል ታሪክ ለተገነዘበ ሰፋ ባለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ላይ የተመረኮዘ እንዳልሆነ በራሱ በተማሪው ማኅበር ይወጡ የነበሩ ታገልና ታጠቅ የሚባሉትን መጽሔቶች ላገላበጠ መረዳት ይቻላል። ከጽሁፎቹ ይዘት መረዳት የሚቻለው የመሬት ላራሹ ጥያቄ፣ የዲሞክራሲና የብሔረሰብ ጥያቄዎች ዋናውን ድርሻ ሲይዙ፣ ለአገራችን ዋናው የዕድገት እንቅፋቶች ፊዩዳሊዝም፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም ናቸው የሚሉ አስተሳሰቦች ነበሩ። ሌሎች አስተሳሰቦች የሚስተጋቡ ቢሆንም፣ በእነዚህና በሌሎች የሕብረተሰብ ጥያቄዎች፣ በተለይም የመንግስት አወቃቀርና የዕድገት ጠንቅ መሆንና በአገሪቱ ውስጥ በተበላሸ የኢንዱስትሪ ፓለቲካ አማካይነት እንዴት የተዛባ ዕድገት የሚመስል ነገር እንደተፈጠረና የተወሰነውንም የሕብረተሰብ ክፍል የህሊና አውቃቀር እንደበረዘውና እንዳዘበራረቀው በደንብ ተብራርቶ ውይይትና ክርክር የሚካሄድበት የምሁራዊ እንቅስቃሴ አልነበረም። በተጨማሪም ለአገራችን የሚስማማና ሕዝባችንን ከድህነት አውጥቶ ወደ ከፍተኛ ደረጃ በሚያደርሰው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ውይይትና ከርክር ይካሄዱ እንዳልነበሩ ዶኩሜንቶች ያረጋግጣሉ። ራሱ የተማሪው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ፊዩዳሊዝምና ውጥንቅጡ የወጣ ካፒታሊዝም ውጤት በመሆኑ እንደ አውሮፓው የምሁር እንቅስቃሴ ነገሩን ሰፋ አድርጎ በማየት ተከታታይነት ለሚኖረው የሥልጣኔ ፕሮጀክት ሊታገል አልቻለም። በኋላ ላይ የአስተሳሰብ አለመግባባት ሲፈጠር የሚወጡት ጽሁፎች ትምህርታዊ መሆናቸው ቀርቶ የእንካ ስላንቲሃ በመሆን የፓለቲካ ትግሉን መንፈስ መበረዝ ቻሉ። ይህ ጉዳይ የኋላ ኋላ አብዮቱ ሲፈነዳ የባሰበትና ወደ ርስ በርስ ጦርነት እንዲያመራ ያደረገ ሁኔታ ነው። ከክርክርና ከውይይት ይልቅ የጊዜው ጥያቄ የመሳርያ ጥግል ጥያቄ ነው በሚለው ላይ በማትኮሩ የጠቅላላውን የአብዮት ሂደት መልኩን ሊቀይረው ችሏል። ለዚህ አስከፊ ሁኔታ መፈጠር ደግሞ ሁሉም የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች ተጠያቂ ሳይሆኑ፣ በዚህም በዚያም ብሎ ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚሽቀዳደመውና፣ ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሔራዊ አጀንዳ ከሌለው የብሔረሰብ እንቅስቃሴ ጋር የተባበረውና ኃላፊነት የጎደለው የጦር ትግል የሚሉትን ፈሊጥ ማካሄድ የጀመረው ኃይል ነው ተጠያቂው።

አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ የታየውና ወደ ጦርነት ያመራው መከፋፈልና መገዳደል በወታደሩ ውስጥ በመስፋፋቱና ወታደሩን በመከፋፈሉ አመኔታ እንዳይኖር አደረገ። ወታደሩ ለሁለት ወይም ከዚያ በላይ በመከፋፈሉ ርስ በርሱ እንዳይተማመን ተደረገ። በጊዜው የተፈጠሩት ወይም ብቅ ያሉት አምስት የማርክሲስት-ሌኒንስት ድርርጅቶችና ከውጭ ሆኖ የሚታገለው ኢህአፓ የወታደሩና የተቀረውን የሕብረተሰብ ክፍል ርስ በርስ በመቀራመት ለቡድናዊ ስሜት መዳበርና የኋላ ኋላ ለርስ በርስ መገዳደል አመቺ ሁኔታን ፈጠሩ። ዋናው ዓላማቸውም ብሔራዊ አጀንዳን መከተልና ኃይልን ሰብስቦ ወደ አገር ግንባታ ላይ ከመሰማራት ይልቅ ሁሉም ድርጀት ራሱን ለማጠንከር ሲል ካድሬዎችን በመመልመልና በማግበስበስ ሕብረተሰብዓዊ ቅራኔውን አስፋፉት። በዚህ ላይ ሲአይኤ (CIA) የራሱን ሥራ ይሰራ ስለነበር በአንድ በኩል አብዮቱ ሊጨናገፍ የሚችልበትን ሁኔታ ከውስጥ ሲሰራ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የብሔረሰብ እንቅስቃሴዎች የሚባሉትን በማስታጠቅና ጦርነቱ እንዲፋፋም በማድረግ ቢያንስ ለዕድገት የተነሳሳው ኃይል አትኩሮው በሱ ላይ ብቻ እንዳይሆን አደረገው። ሽኩቻው ሥልጣን ከመያዝ አልፎ እንዴት አድርጎ ራስንና ድርጅትን ማዳን ይቻላል በሚለው ላይ አተኮረ። የኋላ ኋላ የወታደሩ አገዛዘ ራሱ በጠፈጠፈውና ከዚህም ከዚያም ባግበሰበሰው ኃይል በመታገዝ የተቀረውን ምሁራዊ ኃይል በመደምሰስ አገሪቱን የምሁር አልባ አደረጋት። የወታደሩም ዋና ዓላማ አገርን መገንባት ሳይሆን እንዴት አድርጌ ሥልጣን ላይ መቆየት እችላለሁ በሚለው ላይ ያተኮረ በመሆኑ በተለይም ለውጭ የስለላ ድርጅቶች በሚሰሩ በመከበቡና ወታደሩም በጦርነት በመዳከሙና ራሱም በሰላዮች በመቦርበሩ ውድቀቱን አፋጠነው። ወያኔና ሻቢያ በሲአይኤ በመታገዝና ሥልጣንን በመጨበጥ የኢምፔሪያሊስት ፕሮጀክቶችን ማካሄድ ጀመሩ። ጨቅላ አስተሳሰባቸውን ተግባራዊ በማድረግ አገራችን ከውስጥም ተዳክማ በውጭ ኃይሎች በቀላሉ ልትጠቃ የምትችልበትን ሁኔታ አመቻቹ። አጀንዳቸውም ሁሉ ጠንካራ የሆነ ብሔራዊ ኢኮኖሚና ሕብረተሰብ እንዳይገነባ ማድረግ ነበር፤ ነውም።

ከፖለቲካው ፕሮጀክት ባሻገር በአገራችን ምድር የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ብሔራዊ ባህርይ ያለውና ብሔራዊ ሀብት ሊፈጥር የሚችል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተግባራዊ እንዳይሆን በመታሰቡ ነው። በጊዜው ይህንን ፖሊሲ የሚቃውም የነቃና የገባው ኃይል ባለመኖሩ እነ መለሰ ዜናዊ ከእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና (IMF) የዓለም ባንክ ጋር በመመካከርና ትዕዛዝ በመቀበል ተግባራዊ በማድረግ ራሳቸው ሊናጥጡና ሕብረተሰቡን ሊያራቁቱት በቁ። ከዚህም መገንዘብ የምንችለው ለሥልጣን የሚስገበገብና በተለይም ደግሞ በቂም በቀል የተወጠሩ ኃይሎች የሥልጣኔ ተልዕኮ እንደሌላቸው ነው። ራሳቸው ወያኔና ሻቢያ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ የማቴሪያል ሁኔታና የባህል ውጤቶች በመሆናቸው ሰፋ ያለና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ የሚያመች ብሔራዊ ፕሮጀክት በፍጹም ሊኖራቸው አይችልም። ከሌላው ተነጥለው በራሳቸው ዓለም ብቻ ሊኖሩ የሚችሉ ስለመሰላቸው ሰፋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያ እንዳይገነባ የዘረፋ ተግባራቸውን አጧጧፉት። ራሳቸውንና ብሔረሰባቸውን የጠቀሙ ስለመሰላቸው ባካሄዱት የተፈጥሮንና የሕብረተሰብ ሕግን በሚጻረር አጉል ፖለቲካቸው የራሳቸውንም ዜጋ በመንፈስም ሆነ በማቴሪያል አራቆቱት። በርግጎ እንዲኖር አደረጉት። ነፃነት እንዳይሰማው አደረጉት።

እስከ ግንቦት 7 ድረስ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ስንመለከትና በጊዜው መጽሔቶች ላይ ይወጡ የነበሩትን ጽሁፎች ስንመረምር እስከዚህም ድረስ በሰፊው ለማሰብ የሚረዱ የሥልጣኔን መልዕክቶች ያዘሉ እንዳልነበሩ ማረጋገጥ እንችላለን። በተለይም አገዛዙ ተግባራዊ ባደረገው በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ አንዳችም ትችት አይቀርብም ነበር ማለት ይቻላል። ያም ሆነ ይህ በ1997 ዓ.ም የተካሄደው የግንቦቱ 7 ምርጫ የመጨረሻ መጨረሻ በእነ መለስ ዜናዊ የተጨናገፈ ሳይሆን ራሳቸው በአሸናፊነት በወጡት የቅንጅት መሪዎች ሁኔታውን በቅጡ ባለመረዳታቸውና፣ በተለይም ደግሞ በውጭ ኃይሎች በመመከርና በመተማመን ለሥልጣኔ ሳይሆን ለሥልጣን በመስገብገባቸውና የውስጥ ሽኩቻ በመጀመራቸው ነው። ቀደም ብለው በደንብ የተዘጋጁ ኃይሎች ባለመሆናቸውና ብሔራዊ ባህርይንም ያላዳበሩ በመሆናቸው ለሕዝባችንና ለአገራችን ጠበቃ በመሆን ከውስጥ የሚደረገውን ትርምስና ከውጭ የተቀነባበረብንን ሴራ ለመዋጋት የሚያስችል ሳይንሳዊ መሳሪያ አልነበራቸውም። ስለሆነም በእነሱ የስትራቴጂ ስህተት የኢትዮጵያ ሕዝብ 12 ዓ.ም ያህል እንዲሰቃይ ተደረገ። በራስ ያለመተማመንና በውጭ ተማምኖ ሰፊውን ሕዝብ መናቅ የመጨረሻ መጨረሻ ልንወጣ የማንችለው ማጥ ውስጥ እንደከተተን መረዳት እንችላለን።

ከአብዮቱ መክሸፍ በኋላና ከግንቦቱ ሰባት ምርጫ ድል መነጠቅ በኋላ አሁንም ቢሆን ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል ብዙም የተማረው ነገር የለውም። ዋናው ዓላማም ሥልጣኔን ማምጣት ባለመሆኑ ኃይልን ወደሚሰበስብ ሰፋ ወዳለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ሊያመራ በፍጹም አልቻለም። እዚህና እዚያ የሚመሰረቱት ፓርቲዎች ነን የሚባሉት ነገሮች በመሰረቱ የግለሰብ ኩባንያዎች የሚመስሉ እንጂ በደንብ ተደራጅተው የሚያስተምሩና የሚማሩም አይደሉም። በዚህ ዐይነቱ ፊዩዳላዊ ጨዋታቸውም ተከታታይነት ያለውና የጠነከረ፣ እንዲሁም ታሪካዊ ኃላፊነትን ሊሸከምና የሥልጣኔ ፕሮጀክት ሊነድፍ የሚችል ድርጅት እንዳይፈጠር እያገዱ ነው። እዚህና እዚያ የሚደረጉት „የትብብር ሥራዎችና የአንድነት መፈክሮች“ ሰፋ ያለ ምሁራዊ መሰረት ያላቸው አይደሉም። ሰፋ ካለ ምሁራዊ ክርክርና ውይይት በኋላ የተፈጠሩም ባለመሆናቸው ስለ ወደፊቱ የሕብረተሰብ ዕድገትና የሥልጣኔ ፕሮጀክት፣ ስለዲሞክራሲና ስለ ግለሰብዓዊ ነፃነት፣ ስለሳይንስና ስለቴክኖሎጂ፣ ስለከተማዎችና ስለመንደሮች በዕቅድ ስለመገንባት ጉዳይ፣ ለሕዝባችን መሰረታዊ ፍላጎቶችን በቅድሚያ ስለማሟላት ጉዳይና፣ እነዚህንም ተግባራዊ ለማድረግ ምን ምን እርምጃዎች በቅድሚያ መወሰድ አለባቸው በሚለው ላይ ውይይትና ክርክር እንዲሁም ጥናት ስለማይካሄድ ስብስቡ ሥልጣን ከመያዝ የሚያልፍ አይመስለም።

ከዚህ ስንነሳ ያለው አማራጭ አንድ ብቻ ነው። የአንድ አገር ዕድገት ሊወሰንና መስመር ሊይዝ የሚችለው ሰፋ ባለ ምሁራዊ ኃይል በመሆኑ ሥልጣንን ስሌቱ ውስጥ ያላስገባ ምሁር ሁሉ በየሙያው የየበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረግ አለበት። ይህ ዐይነቱ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በስዕል፣ በአርኪቴክቸር፣ በሊትሬቸር፣ በድራማ፣ በተፈጥሮ ሳይንስና በፍልስፍናና በሌሎችም የሚገለጽ መሆን ሲገባው፣ ማንኛውንም ለፖለቲካ ሥልጣን ብቻ የሚታገለውን መፈናፈኛ የማያሳጣው መሆን አለበት። ከሁሉም አቅጣጫ ግፊት ሲመጣ የፖለቲካው መድረክ አስተሳሰቡ በመስፋት ለሃሳብ መንሸራሸር አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በሌለበት አገር፣ የዛሬው አገዛዝ ቢወድቅም እንኳ ሁኔታው በዚያው መልክ ይቀጥላል ማለት ነው። የብዙ የሦስተኛው ዓለም አገሮች ልምድ ይህንን የመሰለውን ሁኔታ ነው የሚያስተምረን።

ስለሆነም አገራችንን ዛሬ ካለችበት የተወሳሰበ ችግር አውጥተን ሰፋ ባለ መሰረት ላይ ለመገንባት ከፈለግን የፖለቲካ ሥልጣን አሁኑኑ ከሚለው ስንኩል አስተሳሰብ መላቀቅ አለብን። ከቡድናዊ ስሜትና ከራስ ኤጎ በመላቀቅ ተሰባስቦ መከራከርና መወያየት እጅግ አስፈላጊ ነው።፡የዓለም የፖለቲካ ሁኔታ እጅግ አወዛጋቢ እየሆነ በመምጣቱና፣ በተለይም ደካማ አገሮች የመበታተናቸው ሁኔታ አመቺ በመሆኑ የግዴታ የአስተሳሰብ አድማስን ማስፋትና በሁሉም ሕብረተሰብን በሚመለከቱ ነገሮች ላይ መወያየትና መከራከር የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። አገርን በሚመለከት ጉዳይ ላይ ይሉኝታ የተሞላበት ፖለቲካ ትክክለኛው አካሄድ ስላልሆነ ሁሉም በድፍረት የሚፈልገውንና የሚያምንበትን ርዕዮተ-ዓለም በግልጽ ውጭ አውጥቶ ማስተማርና ለማሳመን መሞከር አለበት። በደፈናውና በጨዋነት የሚካሄድ ትግል የሚሉት ፈሊጥ ውጤቱ የሚያምር አይሆንም።

ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ታህሳስ 14፣ 2016
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!