አቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ

Ethiopia

እንደመግቢያ፤

እኔ ከአባቴ የአምቦ ጉደር ሙቱሉ ኦሮሞነቴ ወደኋላ አስር በሚቆጠሩ ዘሮቼ ከአያቴ ተቆጥሮልኝ ባጠናሁት፤ እና በእናቴ ደግሞ ከኮንሶ-ኦሮሞነት በነገረችኝ የዘር ሐረጓ አዲስ አበባ ተወልጄ ባድግም ኢትዮጵያዊነቴን እንጂ፤ አንዳንድ ትግሬነትን እንዳሸመቁበት፣ ጉጅሌው ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ቋንቋ እያስተማረና ለምድ እያለበሰ ሲያሰለጠናቸው በድብቅ ደም እንዳፈሰሱት ለአገር ሻጭ ጀሌዎች የገዳይ ተመልካች አልነበርኩም፤ አልሆንምም። የዚህ ሁሉ መገለፅ ምክንያቱ የኢትዮጵያዊነትን አሊያም የኦሮሞነትንም ሆነ የኤርትራዊነትን ጭምብል አድርገው ነፃነታችንን የሚወጉትን በአደባባይ ለማጋለጥ ነው።

የርዕሳችን መነሻዎች ሁለት ቃላት ናቸው፤ ኢትዮጵያዊነት እና ነጻነት ሲሆኑ፤ ውጤታቸው ሲሰላ ደግሞ አንድ ነው። የቃላቱን መተርጎም አስፈላጊነት፣ ቅ-አያቶቻችን "ነገር ከሥሩ ውሃ ከጥሩ" እንዲሉ:- የምናውቃቸው ቃላት ቢሆኑም እንኳ፣ ከመነሻችን ትንሽ ነገር ታዘናጋናለች እና እንዳናቀላት ነው።

እነዚህ፤ *ብሔር፣ *ዲሞክራሲ፣ *እኩልነት፣ *ነፃነት፣ *ኢትዮጵያዊነት፣ *ሥራ፣ *ምግብ፣ *መጠለያ የጠቀስኳቸውን ቃላት ናቸው አንዴ እየተብራሩ፤ ሌላ ጊዜ እየተሰነጠቁ፤ ሲያሻም እየተጦመሩ፤ እየተለጠጡና እየተቀናጁ ወደ አልተጠበቁ ተራ ጉዳዮች የሚያኖግዱን።

የመረጥኳቸውም ከልብ:- "ልብ" እንድንላቸው እንጂ "እንድናስተውላቸው" አይደለም። ማሸነፍም ልብን ነውና፤ አስተዋይ ከምንላቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ "ልባቸው" ለሚጠቅማቸው ነገር ተሸንፏል። ለዚህም ነው ጥቂት ልባሞች ብቻ ስላሉን በጉጅሌ የጣሊያን ፋሺሽት የጭካኔ አካፋና ዶማ የሕዝብ ልጆች ደማቸው በየጎዳናው፣ በየፍሳሽ ቆሻሻ መድፊያዎች ውስጥ እንደውሻ ከንቱ ሆኖ ባደባባይ እስኪደርቅ ድረስ ተመልካች ያጣው።

ወገኖቼ:- ደም ግን ሙት አይደለም፤ ፈሰሰም አልፈሰሰም፣ ሕይወት አለው ለዘላለም። ጥቂቶች ብንሆንም የማይሞት ልብ ያለን "ለነፃነት" አለን እንላለን። የብዙዎቻችን ልብ ከሕዝብ ጋር ቢሆንም ትንፋሻችንን ይዘናልና ጊዜ ዳኛውን እየጠበቅን እንገኛለን።

ልባቸው የተሸነፈ አስተዋዮች ግን ሥልጣን፣ ገንዘብና ሆድን አወቀና "ተሸነፈ" እንጂ ተሸንፎም አላበቃ፤ ባርነት አደረ፣ ማረጋገጫችንም ዜጎች ሲገደሉ እያዩ እንዳላዩ፤ በሕግ ሥም ዳኞች በግፍ ፍትሕን ሲያንቋት፣ ሲያስሯትና ከወህኒ ቤት ሲያጉሯት፤ ሲቃውን እንዳልሰሙ ሆነው እንዲኖሩ፤ ሥልጣን የሕሊና ስብዕናቸውን ገፎባቸው፣ ከሞቱት በላይ ከሚኖሩት በታች አቀርቅረው፤ በሆዳቸው እንደወደቁ "እየኖርን ነው" ይሉናል፤ አንድ ቀን ተራቸው ደርሶ እነሱም እንደነዚያ ታኝከው እንዳበቁት ሲ-ተ-ፉ ነገ ልናያቸው።

*   *   *

የትግላችን ቃላት

፩ኛ ነጻነት ሲተረጎም፤ ኣርነት፣ እንደልብ መኾን፣ ባለቤት፣ አዛዥ አለመኖር።

፪ኛ ባርነት ሲተረጎም፤ ነጻነት የሌለው፣ በጌታው ዐሳብ አዳሪ፣ ባለመከራ፣ እንደበሬ በግድ የሚሠራ።

፫ኛ ኢትዮጵ/ጲስ ሁለተኛ የኩሽ ሥም፣ የአገር ሥም፣ የኖባ ልጆች ከግብጽ ቀጥሎ ያለው አገር፣ ቆላ አገር፤ ኋላም ኢትዮጵያ (ኢቲዖፒኣ) ተብላ የተሰየመች (ሱዳን-በዐረ) አገር። (አለቃ ኪዳነ፡ወልድ፡ክፍሌ) እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያዊነት አፍሪቃዊ፤ ምሥጢሩ ጥቁረትና ቆለኛነት ነው። የነገድ፣ የሕብር፣ የመልክ፣ ኢትዎፕስ። ዕብራይስጥ እና ጽርእ ቋንቋዎችን የማያውቁ ናቸው ስለ ኢትዮጵያ የተመዘገበ ታሪክ የሚዘባርቁት።

"«አብርሐማዊ» ኃይማኖቶች [(በዕብራይስጥ፦ תיבת נח /ተይባት ኖዋሕ/፤ በመጽሐፍ ቅዱስ (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 6—9)፣ ዓረብኛ፦ سفينة نوح /ሣፊና ኑህ/) በቁርዓንም (ሱራ 11 እና 71)፣ እንዲሁም በሌሎች (ክርስቲያኖች)*] በብሉይና በአዲስ የተጣፈው መደበኛው "ኢትዮጵያ" ግን ታላቁን በረሓ ሰሐራን ጨምሮ የኖባ ክፍል ነው፤ ኢትዮጵስ የኩሽ ልጅ አይደለም። ኢትዎጲስ የኩሽ አባትም አይደለም።

በልጁ በኢትዮጲስ ስም ኢትዮጵያ ተባለች ይላሉ፤ የግምት አነጋገር ነው። ይባስ የኩሽ አገር ኹሉ በልጁ በኢትዮጵስ ስም ኢትዮጵያ ተባለች ይላሉ፤ ይህም የግምትና የመላ፣ አነጋገር ነው። ዕውነቱ በጽርእ ቋንቋ ኢትዮጵስ የተባለው፣ ያው በይብራይስጥ ኩሽ የተባለው የካም ልጅ ነው እንጂ።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ከካም ልጅ ከኩሽ ወይም ከኢትዮጲስ ብቻ የወጣ ስያሜ ነው። ይህ ኢትዮጵያዊነት በዘመናት ተጸንሶና የትውልድ ባሕላትን ተሸጋግሮ፤ የኖረ፣ እየኖረ ያለና ወደፊትም የሚኖር፤ ሥጋዊ፣ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ሕይወት ያለው፤ ረቂቅ ስያሜ ነው። እነሱ ሲጠሩንና እኛ ስንጣራበት ለየቅል ነው፤ እኛ ታሪካችንን ስንጽፍና እነሱ ለራሳቸው ስለእኛ ሲጽፉ እንደማለት ነው። በዚያ በኩል ያለም ሆነ አዚህ ጋ የሚያገባው ባለቤቱ ራሱ ባለቤቱ ነውና፤ ይህ የሐቅ መሠረት የሁሉም ዕውነታ ነው።

ለምድ እና ጭምብል፤

ኢትዮጵያን እናጠፋታለን ብለው ጭምብል አድርገው የተነሱትና የሚነሱት፣ የሥጋ ትሎችም ሆኑ በፋሺስት ዘረኛ ደዌ እና ቫይረስ የተከተቡ ባንዳዎች ሁሉ፣ መጀመሪያ የሚጋጩት ከሳይንስ ጋር ኃይል {ኤነርጂ} ሊጠፋ እንደማይችል ለማስገንዘብ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ወቸገል ዜናዊ እንኳ ሕዝብን ማጭበርበር እንደማይቻል በጊዜ በይፋ መናዘዙን ቢናገርም፤ በተግባር ግን እስከወዲያኛው በትውልድ ሊረገምበት የዘገየና ሳያርመው የተቀጨበት ነው እንጂ፤ ዛሬም ከሌላው ጥፋት የማይማሩ ባለጊዜዎች የሚያረፍዱት ይሄንኑ አለመገንዘባቸው ሳይሆን ሥልጣንና ገንዘብ ስለገዛቸው ብቻ ነው።

አንድ ሐሙስ በቀራት የመከራ ጭንቅ ውስጥ ሆናችሁ ሽልማት ስትሸልሙ፤ ሹመት ስትሰጡ፤ ባጀት ስትበጅቱ፤ አዋጅ ስታውጁ፤ ፕሮጄክት ስትነድፉና ስታፀድቁ ያንንና ይሄንን ስታደርጉ ትግሉ ተዳፍኗል ብላችኋል። ዛሬም ሙታን ቀባሪዎች ግብረ ኃይል አሰማርታችሁ ማታ ማታ በድብቅ ያለአልቃሽ በጅምላ ስትቀብሩ፣ ለማህሌት ያደሩ አባት ድንገት ስላዩአችሁ፤ የት እንዳደረሳችኋቸው ወደፊት የሚጣራ ይሆናል። አንባቢዎቼ አሁን ግን የመፍትሄውን ስሌት ከዚህ በታች ባለው ሁኔታ ልግለፅ።

የመፍትሄ መነሻ ሃሳቦች፤

መጀመሪያ ምንድን ነው የምንፈልገው? ነፃነት። ምን ዓይነት ነጻነት? "የኔነት" ነፃነት። የኔነት ነጻነት ማለት ምንማለት ነው? የዜግነት ነጻነት ማለት ነው። አንድ ሰው የዜግነት ነጻነት ካለው ቀሪው ትርፍና ባለን ነፃነት የሚመለስ መብት ይሆናል።

በኢትዮጵያ አገራችን ውስጥ በኢትዮጵያዊነታችን ሁሉንም ብሔር ስለሆንን የትኛውም ግዛት ያለምንም ሕገ ደንብ በነጻነት መሆንና ማድረግ እንችላለን፤ ምንም መግለጫ አያስፈልገውም። ሁሉንም ለማድረግ ነጻነት ቢኖረንም ይህንን ነጻነታችንን ደግሞ ማንም አይጠብቅልንም፤ ራሳችንን ጠባቂዎቹ ራሳችን ነን። በነዚህ መሠረታዊ ሃሳቦች ከተስማማን ያሉንን የነጻነት ምርጫዎች እንደቅደም ተከተላቸው እንመርምራቸው።

የነጻነት አንዲት ስሌት

በሳይንሳዊ አቀራረብ አኀዞች ከአንድ እስከ አራት ቢጻፉ መቅደም ያለብትን ለመናገር በጣም ቀላል ነው። ፩፣ ፪፣ ፫፣ ፬ ብለን እንጽፋለን። ከዚያ በላይ አኀዞች ሲቀመጡ ግን ለመምረጥ አይከብዱም ቢባልም፤ እንደመጀመሪያዎቹ የቀለሉ አይሆኑም። በምሳሌ እንየው፤ ፹፫ ፴፬ ፺፱ ፶፭ ፳፮ ተብለው የተጻፉትን አኀዞች፣ ከትንሹ ወደ ትልቁ በማንበብ በቅደም ተከተል እንድንጽፍ ብንጠየቅ የምንሰጠው ፳፮ ፴፬ ፶፭ ፹፫ ፺፱ መልስ ማለት ነው። የሚብሰው ችግር የቅደም ተከተሉን ውስብስብ የሚያደርጉት ደግሞ ጥያቄዎቹ ከአኀዞች ውጭ ሲሆኑ ነው። በተለይም የፖለቲካ ጉዳይ ሲሆኑ፤ በሳይንስ ቅመማን ሲከተሉ፤ ነገሮች በሕግ ተይዘው ለውጤት ሲፈተሹ፤ ከመላምቶች አሳማኙ ሲጠበቅ፤ እናም ከመወሳሰባቸውም የተነሳ ችግሩን ፈቺዎች "አበዱ ወይ?" እስኪያስብል መፍትሄው ወደ አልተጠበቀ ርዕሰ ጉዳዮች ይዟቸው ሲጓዝ፤ ለሰሚው ግራ ያጋባሉ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ውስጥም የሚታየው ይህ ውጥንቅጥ ነው።

ስለዚህ

መርሳት የሌለብን ገና "ምን ይደረግ?" ስንል እንደዚህ ውጥንቅጥ እንዲኖር የሚፈልግ አካል መኖሩን መገንዘብ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ "ግርግር ለሌባ እንደሚመች" አውቀን ይህንን ሁኔታ ለመፍጠር እንደመሳሪያ እንደሚጠቀሙበት ማወቅ ይኖርብናል።

ለነፃነት ጉዞ ወደ ተግባር፤

መዘንጋት የሌለብን፤

1. ኢትዮጵያ ወደድንም ጠላንም ዓለም የሚያውቀው፣ ሕዝብ የሚጠብቀው፣ ጠላት ሊደብቀው የሚፈልገው፤ ምድር ላይ የኢትዮጵያ ግዛት አላት።
2. ኢትዮጵያ ጥንትም የነበሩ፤ አሁንም የሚኖሩ፤ ወደፊትም የሚኖሩ ሕዝቦች አሏት።
3. ሕዝቦቿ ኢትዮጵያዊያን የሚያደርጋቸው በኢትዮጵያ ግዛት ስለሚኖሩ አይደለም፤ በሕገ መንግሥት ስለዜግነት በተደነገጉት መሠረት ነው። ***(ለጊዜያዊ የፖለቲካ ሥልጣን የወጡና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጻረሩ ሕጎች፣ ደንቦች እና ሌሎችም ማስፈጸሚያዎች ጊዜአቸውን ጠብቀው በኢትዮጵያ ሕዝብ ይደመሰሳሉ።)

ወደ ቀላሉ የችግር አፈታት ቅደም ተከተል እንምጣ፤ እንዳንዘነጋ የቅደም ተከተል ምርጫ ውስጥ መግባት ያለበት አማራጭ ለተንኮል ሲባል አይቀርብምና ሊኖር የሚገባውን አማራጭ ማንሳት የግድ ነው። አስመራጩ ባላጊዜ የሆነ አካል ምርጫውን ገና ሲያቀርብ ያስ ለምን ለምርጫ አልቀረበም በማለትና ሁሉንም አንመርጥም ብሎ መናገር የመምረጥ መብታችን መሆኑን መገንዘብ አለብን።

የትኛው መቅደም አለበት???

እነዚህን በቅደም ተከተል እናስቀምጥና ስለዚያ ርዕሰ ጉዳይ አፈጻጸም ብቻ ተግባራዊ እናድርግ።

*ብሔር፣ *ዲሞክራሲ፣ *እኩልነት፣ *ነፃነት፣ *ኢትዮጵያዊነት፣ *ሥራ፣ *ምግብ፣ *መጠለያ

እንግዲህ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እነዚህን ሁሉ ሳይሆን፤ አንዱን ብቻ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእነዚህ መካከል ነው በቅደም ተከተል ማስቀመጥ ያቃተን። ስለዚህ ለያንዳንዱ ቅደም-ተከተል የአኀዝ ደረጃ እንስጣቸው። ከዚያ በኋላ በአንደኛነት ስለተመረጠው ርዕሰ አኀዝ ብቻ እየተነጋገርን እንወስናለን።

ስለዚህም መጀመሪያ መቅደም ያለበት የቱ ነው??? ... ለምን??? ...

ማሳሰቢያ:-

የምናስቀድመው ርዕስ ከሁሉም በላይ የሚሆነው ለተቀሩት ርዕሶች መልስ ሊሆን እንደሚችል ስናረጋግጥ ብቻ ነው፤ ካለበለዚያ ምርጫችን ስህተት ስለሆነ ትክክል ማድረግ አለብን። ለምሳሌ:- ምግብ የምንል እንኖራለን፤ መልሱ ስህተት የሚሆነው ለምግብ ቅድሚያ የሚሰጥ ለመብላት ብቻ የተፈጠረ በመሆኑና ሰው ግን ለመብላት ብቻ ባለመፈጠሩ ምግብ አንደኛ አይሆንም ማለት ነው።

የእኔ ምርጫ አንደኛው ነጻነት ነው፤ ለምን ብትሉኝ ሁሉንም ነጻነት ካለን ልናገኛቸው ስለምንችል። ስለዚህ በቅድሚያ ነፃነትን ተግባራዊ እናድርግ። ለምን??? ቢባል በባርነት ቀንበር ውስጥ ስለሆንን። መረጃችንስ ምንድንነው??? ... የባርነትን ትርጉም ስለምናውቅ። የሚያሳዝነው እና ሰዎች የሚታለሉበት፤ ጉጅሌ ዲሞክራሲን ቅቤ ቀብቶበት የአይጥ ወጥመድ አድርጎታል፤ እኩልነትን ደግሞ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እንዳረከሰው የፋሽሺት ጣሊያን ዲዛይን የሆኑትን ባንዲራ አልብሶ ውስጡን በዘርና በትዕቢት አሳብጦ የወፈረና የጠገበ አስመስሎታል።

ማጠቃለያ፤

በመሠረቱ ነፃነት፤ ዲሞክራሲም፣ እኩልነትም፣ መፈታትም ሦስቱንም አይደለም፤ ነፃነት፣ ነፃነት ብቻ ነው ሲባል፤ ሁሉም ማለት ነው። ሁላችንም መጀመሪያ ለነፃነት ስንል እንታገል፤ አንተኛ። የስሌታችን መጀመሪያ መልሱ ይኼው፣ ነፃነት ብቻ ነውና ጉጅሌን እንገርስሰው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!