የትነበርክ ታደለ

Habtamu Ayalew

ከሦስት ዓመት በፊት ለአንድ በውጪ ቋንቋ ለሚታተም መጽሔት Seeking Cure Abroad Growing Number of Ethiopians Look for Medical Solutions in Foreign Lands የሚል ጽሁፍ አቅርቤ ነበር።

ይህን ዘገባ በምጽፍበት ወቅት አዲስ አበባ ከተማ በሚገርም ሁኔታ ሞንታርቦ በሚንቀለቀል የድምጽ ብክለት ትታወክ ነበር። ይህ በሚኒባሶችና በአይሱዙዎች የተጫነ ሞንታርቦ የሚያወጣው ድምጽ የሙዚቃ ወይም የቲያትር ማስታወቂያ እንዳይመስላችሁ።

እነዚህ መሸት ሲል መንገዱን በጩኸት የሚያተራምሱት የሞንታርቦ ድምጾች የልመና ድምጾች ናቸው። አድኑን፣ እርዱን የሚሉ የልመና ድምጾች። በመኪኖቹ ዙሪያ ከተለጠፉት ትልልቅ የሕመምተኛው ፎቶ በተጨማሪ ለሕክምና የሚውል ገንዘብ የሚለምኑ ድምጾች። "በአገር ውስጥ መታከም ስላልቻለ፣ ዶክተር ቶሎ ወደ ውጪ አገር ሄደህ ታከም ስላለው፣ ሕክምናው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሌለ ..." እባካችሁ እርዱን የሚሉ ልመናዎች።

በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ምጽዋት የሚሰበሰብላቸው አንድ ወይም ሁለት አይደሉም። በየቀኑ የሚታይ ትይንት ነው። ህጻን አዋቂ፣ ሴት ወንድ፣ ተማሪ ሠራተኛ ... በርካታ ሰው "ቶሎ ከአገር ውጣና ታከም" ተብሏል። ወደ ሕንድ፣ ኬንያ፣ ባንኮክ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጀርመን፣ ግብጽ ... ወዘተ። ምክንያቱም አገር ውስጥ ሕክምናው የለም።

እነዚህን ትርክቶች ይዤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወዳልኳቸው ቢሮዎች ተመላልሻለሁ። "ይሄ ሁሉ ሰው እንዴት ሆነ?" የሚል ጥያቄም አቅርቤ ነበር።

"እየሠራንበት ነው፣ በቅርቡ በሙሉ አቅማችን እንገባበታለን ..." የሚሉ ምላሾችን ያገኘሁ ቢሆንም፤ የችግሩን ውስብስብነትና ጥልቅነት ደግሞ ከማይክራፎን ውጪ (off the record) ተረድቻለሁ።

በየዓመቱ ቁጥራቸው የትየለሌ የሚባሉ ሕሙማን

1ኛ) በጣም ጥቂት መሣሪያና ባለሙያ ባለባቸው የሕክምና ዘርፎች ብዙ ሕሙማንን ማስተናገድ ስለማይቻል በቀጠሮ ብዛት ሳይመለሱ እስከወዲያኛው ያሸልባሉ።
2ኛ) ሕክምናው አገር ውስጥ ባለመኖሩ ምክንያትና ውጭ አገር ሄደው ለመታከም አቅም ስለሌላቸው ብዙዎች ትንፋሻቸው ለዘላለም ይቋረጣል።
3ኛ) ውጪ አገር ሄዶ ለመታከም የሞት ሽረት ጥረት ያደረጉ ዜጎች በሄዱበት አገር ገንዘባቸው ይበዘበዛል፣ መጉላላት ይደርስባቸዋል።
4ኛ) አገሪቱ በሌለ የውጭ ምንዛሪ አገር ውስጥ ማከም ሳትችል በመቅረቷ ዶላሮቿን ለሌሎች አገራት ታስረክባለች። ...

አገራት በሕክምና ዘርፍ ልክ እንደ ማንኛውም የቱሪዝም ዘርፍ Medical Tourism የውጭ አገር ዜጎችን ቀልብ በመሳብ ገንዘብ ይሰበስባሉ። በዚህ ደግሞ በአፍሪካ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካን የሚችላቸው የለም።

ከራሳቸው ዜጎች አልፈው ለበርካታ አገራት የሚተርፍ ጥራት ያለው የዘመነ ሕክምና ይሰጣሉ። በዚህም ምክንያት ለዜጎቻቸው የሚሰጡትን የሕክምና አገልግሎት በር ለበር (door to door) ከማድረሳቸውም ባለፈ፤ እጅግ ርካሽ በሆነ ዋጋ ጤንነታቸውን ይጠብቃሉ።

ይህን አርዕስተ ጉዳይ በዚህ አውድ

በዝርዝር ለመዳሰስ የሚቻል አይደለም። በሙያው ያሉት ደግሞ ቢተነትኑልን ምን ያህል ዓይናችንን በገለጡልንና ጉድለታችንን ባወቅነው ነበር።

ይሁንና ግን ኢትዮጵያ ዛሬም ለዜጎቿ የሚሆን የሚሰማ ጆሮ፣ የሚራራ ልብና የሚሠራ ጉልበት ልትፈጥር ይገባል። እነዚያ የሞንታርቦ ጩኸቶች አንድና ሁለት ብር ከሚመጸውቱ ዜጎች ጆሮ ሳይሆን፤ በሙያው ውስጥ ላሉት በተለይም የጤናውን ዘርፍ ለመምራት ወንበር ላይ ለተቀመጡት ጆሮዎች ይበልጥ ሊሰማ ይገባል።

ሀብታሙ አያሌው ዛሬ አሜሪካ ገባ ተብሎ የተሰማው የደስታ ብስራት ለኔ ለአገሪቱ እፍረት ሆኖ ነው የሚሰማኝ። ማንም ቢሆን በአገሩ የሕክምና ተቋም ውስጥ ተኝቶ በአገሩ ባለሙያ እየተዳሰሰ መታከም እንጂ ባዕድ ሀገር ለሕክምና መሄዱ ልባዊ ደስታና ኩራት የሚያመጣለት አይደለም። ሰው በአገሩ እንዲታከም ማስቻል ያቃተው መንግሥት በዚህ ሊያፍር ይገባል።

በተጨማሪም ለበርካታ ወራት በሆነ ባልሆነ ሰበብ የሕክምና ጉዞውን በማራዘም ሕመምና ስቃዩን በማብዛቱም ጭምር መንግሥት ሊያፍር ይገባል ባይ ነኝ።

ሰላም!!!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!