ኢትዮጵያዊነት እንደ ኢያሪኮ ግምብ በጩሀት የሚፈርስ ሳይሆን በፅኑ አለት ላይ የተመሰረተ ታላቅና ሕያው ማንነት ነው!!

ፍቅር ለይኩን

ጽሑፌን በአንድ ገጠመኜን በማስቀደም ልጀምር። ነገሩ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርንበት ጊዜ ነው። በ1990ዎቹ መጨረሻ ገደማ በአዲስ አበባ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች በ6 ኪሎ በዋናው ግቢ አንድ ትልቅ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው ነበር። የዚህ ለግማሽ ቀን የዘለቀ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ዋና ጥያቄ ደግሞ፣ "የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ፊንፊኔ/አዲስ አበባ እንጂ አዳማ አይደለችም!" የሚል ነበር። ይህን ጥያቄያቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ሐላፊዎችና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሰምተው ምላሽ እንዲሰጧቸው የጠየቁት ተማሪዎች ከግማሽ ቀን ቆይታ በኋላ የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ፕሬዝዳንት ወደ ሰልፈኞቹ ተማሪዎች ታጅበው መጡ። ፕሬዝዳንቱም ጥያቄያቸው ምን እንደሆነ በአገሪቱ/በፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ በሆነው በአማርኛ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑትን ተማሪዎች በርጋታ ምን እንደሚፈልጉ ጠየቋቸው።

ከዚህ በኋላ ነበር ያልጠበቅነው ነገር የተከሰተው። የተማሪዎቹ ተወካይ ለዚህ የተቃውሞ ሰልፍ የወጡበትን ምክንያት ለዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ቫይስ ፕሬዝዳንት በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ሲገልጽ ሌላኛው ተማሪ ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተርጎም ጀመረ። እንግዲህ ልብ በሉ ይህ ዙሪያ ጥምጥም አካሄድ የአማርኛ ቋንቋን ላለመናገር፣ ፈጽሞ ላለመጠቀምና ለቋንቋውና እንዲሁም ለቋንቋው ተናጋሪ ሕዝብ ያላቸውን ጥላቻ፣ ንቀት ለመግለጽ የሄዱበት የግቢያችን የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አሳፋሪ ክስተት ነው። ይህን ያይንና የሰማን የተቃውሞ ሰልፉን በቅርብ ስንከታተል ለነበረን ተማሪዎች ከእፍረትና ድንጋጤም በላይ ወዴት እየሄድን ነው?! የሀገራችን የኢትዮጵያ አንድነት ዕጣ ፈንታስ መጨረሻው ምን ይሆን ...?! ስንል በሥጋትና በአግራሞት ውስጥ ሆነን እርስ በርሳችን እነዚህንና መሰል ወቅታዊ የሀገራችንን ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን አንስተን መነጋገር ጀመርን።

በእርግጥ እነዚህ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች እንደሚሉት - ኦሮሚያና ሕዝቦቿ "በአቢሲኒያ/በኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ቀምበር ስር፣ በባርነትና በጭቆና የኖሩ ከሆኑ" መቼም እንደ ሌሎቹ በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ እንደነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ የቅኝ ገዥዎቻቸውን/የጌቶቻቸውን ቋንቋ መጠቀም አይቀላቸውም ነበር እንዴ ...?! ኦሮሚፋን ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ከመተርጎም ዙሪያ ጥምጥም አካሄድ ይልቅ የትኛው ይቀላል?! እንደው ለመሆኑ በምን አመክንዮና የሞራል ተጠየቅ ነው እነዚህ የኦሮሞ ብሔር ተማሪዎች - በቅኝ ግዛትና በባርነት መላው አፍሪካንና ሕዝቦቿን ወደር በማይገኝለት ጭካኔ ሲገዙና ሲያግዙ፣ እንደ ዕቃ ሲለውጡና ሲሸጡ የነበሩ፣ የቀንደኛ ቅኝ-ገዥ ሀገራት ቋንቋ የሆነውን የእንግሊዝኛን ለመጠቀም መምረጣቸው?! ለምንስ ይሆን እነዚህ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ወገኖቻችን ባሕር አቋርጠውና ተሻግረው - የአፍሪካን ታሪክና ሥልጣኔ፣ ባህልና ቋንቋ ያዋረዱ፤ ያቆረቆዙ የአውሮፓውያንን ቋንቋ ማማተራቸው?! ይህ ከአፍሪካዊነት ኩራት፣ የረጅም ዘመናት ታሪክ፣ ገናና ሥልጣኔና ቅርስ ጋር የሚጣረስ የኦሮሞ ወገኖቻችን ግብታዊነት የተሞላበት ዕውቀት አጠር ስሑት አካሄዳቸውና ከአውሮፓውያኑ/ምዕራባውያኑ የአፍሪካን የተሳሳተ የታሪክ ትርክት/Euro-Centeric Approach ቅኝት አለመውጣታቸውና የዚህ የተሳሳተ እሳቤ ምርኮኛ መሆናቸው አሳዘነን፣ አሳፈረን። ታሪካቸውንና ታሪካችንን በቅጡ አለማወቃቸውና አለመፈተሻቸውም አስቆጨን።

መቼም የአማርኛ ቋንቋ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚቀድም፣ በዓለም ታሪክ ጥንታዊ፣ የራሱ ፊደል ያለው፣ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ታሪክና ሥልጣኔ፣ ባህልና ቅርስ መገለጫ የሆነ ቋንቋ መሆኑን አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ አውሮፓውያኑ ምሁራን ሳይቀር ጭምር የመሰከሩለት ነው። ለአብነትም እግረ መንገዴን Ethiopic an African Writing System የሚለውን የታሪክ ምሁሩን የፕ/ር አየለ በከሬን መጽሐፍ ጠቆም አድርጌ ለማለፍ እወዳለሁ። የሚገርመውና የሚደነቀው ነገር ዛሬ ዛሬ እነ ፕ/ር ሕዝቅኤል ገቢሳና መሰሎቻቸው አማርኛን የማይናገርና ለቋንቋው ጽዩፍ/ባዕድ የሆነ ጀግና፤ ቆራጥ የቁቤ ትውልድ መፍጠር መቻላቸውን በአደባባይ በኩራት እየነገሩን፣ በድፍረት እያወጁልን ነው። ለእኚህ የታሪክ ምሁር ካለኝ አክብሮት ጋር ግን ደግሞ ይህን ንግግር ከአንድ አፍሪካዊ የታሪክ ምሁር፣ ፕሮፌሰር መስማት ደግሞ አሳፋሪና አስፈሪ ነው። ውድቀትና ክስረትም ይመስለኛል።

ይህን ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሆነ ገጠመኜን እንዳስታውስና ይህችን ትዝብትና ቁጭት አዘል የሆነች ጽሑፍ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝ አንድ ሰሞንኛ ጉዳይ ነው። ይሄውም ከሰሞኑን የታሪክ ምሁሩ ፕ/ር ሀይለ ማርያም ላሬቦ በኢሳት የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ ያቀረቡት የታሪክ ትንታኔ - ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ ካናዳ፣ መካከለኛው ምሥራቅና አውስትራልያ ድረስ ባሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ዘንድ ታላቅ ቁጣን፣ ተቃውሞን የቀሰቀሰበት የሰሞኑ ክስተት ነው። ምንም እንኳን አዲስ ባይሆንም ቅሉ። ይህ በኦሮሞ ምሁራንና ነፃ አውጪዎች ቁጣና ተቃውሞም እኚህን ምሁር ሞራልንና ሰብእናን ከሚነካ ተራ ስድብ፣ ማዋረድ፣ መዝለፍና ማንቋሸሽ ጀምሮ በይፋ ይቅርታ ይጠይቁ፣ ከሚያስተምሩበት የትምህርት ተቋም ሊታገዱ ይገባል በሚል የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰብ ድረስ የዘለቀ ነው። በተመሳሳይም የእኚህን የታሪክ ምሁር ቃለ-መጠይቅ ያስተላለፈው የኢሳት የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያም ከዚሁ ውግዘትና ኩነኔ አላመለጠም። የሶሻል ሚዲያውም ይህን ስድብና ዘለፋ፣ መሠረት የለሽ ተቃውሞ በማራገብና በማቀጣጠል ረገድ የበኩሉን የአንበሳ ድርሻውን እየተወጣ እንዳለ እያየን፣ እየታዘብን ነው።

ወደሌላኛው መረራ እውነታ ስንመለስ በዚህ ሁሉ ጩህትና ተቃውሞ ውስጥ ደግሞ እነኚህ የኦሮሞ ነፃነት ታጋዮችና ምሁራን "ኦሮሚያ የተባለ ነፃ ሀገርን" የመፍጠር ሕልማቸውን እውን ማድረግ የሚፈልጉት እንደ እነርሱ አባባል "ይህችን በምናብ ያለች፣ በምናብ የተፈጠረች" ኢትዮጵያ የተባለችን ሀገር በማፈራረስ፣ ከዓለም ካርታ እንድትወገድ በማድረግ ነው። የቁቤ ትውልድና የኦሮሞ ፈርስት አቀንቃኞች - እንደ ጀዋሃር መሐመድ፣ ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ፣ ፕ/ር ሕዝቅኤል ገቢሳ ያሉ የኦሮሞ ምሁራንም ኢትዮጵያን በማፈራረስ "ታላቋን የኦሮሞ ነፃ ሀገር" እውን ለማድረግ መሰሎቻቸውን ሰብስበውና ተማምለው፣ ሰልፋቸውን አሳምረው ወደ አደባባይ ወጥተዋል። ባገኙት አጋጣሚም ሁሉና ሌት ተቀን "ቅኝ-ገዥዋን" ኢትዮጵያን ሳያፈርሱ፣ ሳይበታትኑ ከትግላቸው አንድ እርምጃ ወደኋላ እንደማይሉም በድፍረትና በንቀት እየነገሩን ነው።

እንደእነ ፕ/ር ሕዝቅኤል ያሉ የኦሮሞ ምሁራንም በኦሮሚያ ምድር ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ፤ አማርኛ ቋንቋን የሚጸየፉ ቆራጥ፣ ጀግና ትውልድን በትጋት መፍጠር እንደቻሉም በታላቅ ኩራት ደጋግመው እየነገሩን፣ እያወጁልን ነው። ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በምንም መንገድ ለመስማት ፈጽሞ የሚቀፋቸው፣ የአማርኛ ቋንቋን የሚጸየፉና እንደ አባ ጨጓሬ የሚኮሰኩሳቸው አዲሱ የቁቤ ትውልድ፣ በኦሮሞ ነፃ መሬት ስም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከምድረ ገጽ ለማጥፋፋት ተማምለውና ተማምነው ወጥተዋል። በእርግጥ ይሄ በኢትዮጵያ/በአፍሪካ/በጥቁር ሕዝብ ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ ቅርስና ባህል ትልቅ ኩራትና ክብር ያላቸውን የብዙሃኑን የኦሮሞ ሕዝብ የሚወክል እሳቤና አቋም ነው ብዬ ለማሰብ አልደፍርም። የራሱ የሆነ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋና ቅርስ ያለው ታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ ይህን ውብ ባህሉንና እሴቱን ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የመጋራት አኩሪ ታሪክ ያለውና ለኢትዮጵያ ነፃነትና ሉዓላዊነት ውድ ሕይወቱን ሳይሣሣ መስዋዕት አድርጎ በደሙ የጀግንነት ታሪክን የጻፈ ክቡር ሕዝብ ነው። ይህን ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በደምና በአጥንት፣ በታሪክና በባህል፣ በሃይማኖትና በቋንቋ የተሳሰረ የኦሮሞ ሕዝብ ለመለየት የሚደረገው ዘመቻ፣ ስውር ሴራና መሰሪ ሐሳብ እውን ሊሆን አይችልም።

ምክንያቱም የኦሮሞ ሕዝብ በጠንካራ አለት ላይ በተመሠረተው በኢትዮጵያዊነት ፅኑ የአንድነት መንፈስ ውስጥ ያደገ፣ ያበበ ማንነት ነው ሊያውም በደም ማህተም የጸና!! ዛሬ ዛሬ አንዳንድ የኦሮሞ ምሁራን ደጋግመው በጠላትነት የሚያነሷቸው ዓፄ ምኒልክና መላው አውሮፓን ያሳፈረው የዓድዋው አንፀባራቂ ድል በኢትዮጵያ ታሪክና ማንነት ብቻ ውስጥ ሳይሆን በአፍሪካና በመላው ጥቁር ሕዝቦች ታሪክና የነፃነት ተጋድሎ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ፣ ልዩ ክብር አላቸው። በርካታ የኦሮሞ ጀግኖችም የዚህ አኩሪ ታሪክ ሠሪና ባለቤት ናቸው። ይህን የታሪክ ሐቅ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕ/ር መረራ ጉዲና በአንድ ወቅት በአሜሪካ ሜኔሶታ ከኦሮሞ ተወላጅ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ - ለምኒልክ ተቃዋሚዎች "የዓድዋ ጦር ግምባር በርካታ የኦሮሞ ፈረሰኞች፣ በታላቅ ወኔና ጀግንነት በደማቸው የነፃነት ታሪክን የጻፉ መሆናቸውን ነበር፤" አስረግጠው ለስብሰባው ተሳታፊዎች የተናገሩት። እስቲ ይህን የታሪክ ሐቅ በአፍሪካውያን ምሁራንና ዘንድ ያለውን እንድምታ በጥቂቱ ተንተን አድርገን ለማየት እንሞክር።

የኢትዮጵያዊነት መንፈስ/Ethiopianism እና ቅኝ-ገዥዎችን ያሳፈረው የዓድዋው ድል ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች ታሪክና ሥልጣኔ፣ ቅርስና ባህል መሠረት በመሆን፣ አፍሪካዊ ማንነትንና ብሔራዊ ኩራትን በመገንባት ረገድ የሞራልና የወኔ ስንቅ ሆኖ አገልግሏል። ከአድዋ ድል በኋላ በመላው ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ Ethiopianism/ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን ማዕቀፍ ያደረጉ የነፃነት ትግሎች፤

- በአፍሪካ፣
- በአፍሪካ አሜሪካውያን፣
- በካሪቢያንና በጃማይካና እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የተነሡ ብሔራዊ ንቅናቄዎች መነሻቸው የሺህ ዘመናት ታሪክና ቅርስ፣ ገናና ሥልጣኔና ባህል ባለቤት የሆነች፣ በነፃነቷና በሉዓላዊነቷ ተከብራና ታፍራ የቆየች ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት። የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ታቦ እምቤኪ እ.ኤ.አ. በ2010 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ባበረከተላቸው ጊዜ ባደረጉት ንግግራቸው ከላይ ያነሣሁትን የታሪክ እውነታ እንዲህ አረጋግጠውታል። ከንግግራቸው በጥቂቱ እጠቅሳለሁ።

"... You will be familiar with what the famous 1896 victory at Adwa meant for Africa and the world. The victory at Adwa continued to inspire pride among all Africans and confidence that Africa had something unique and valuable to contribute to human civilisation."

ታቦ እምቤኪ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ነፃነትና የዓድዋ ድል ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የብሔራዊ ኩራትና ምንጭ መሆኑን በመግለፅ ብቻ አላበቁም፤ በበርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የምትገኘው አፍሪካ ከዓድዋው ድል አንድ ምዕተ ዓመት በኋላ - በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን ዳግመኛ የነፃነት፣ የአንድነት፣ የአይበገሬነት የብሔራዊ ኩራት ምልክትና ትእምርት በሆነው የኢትዮጵያዊነት መንፈስና በዓድዋው ድል ወኔና ስሜት - አፍሪካን ወደተሻለ የሰላም፣ የዕድገትና ብልጽግና ጎዳና እንድትራመድ ማድረግ ረገድ የአሁኗ የአፍሪካ ትውልድ ታሪካዊ ሐላፊነትና ግዴታ መሆኑን ጭምር ነበር ያሰመሩበት። እንዲህ ሲሉ፣

"... Gathered here at this Convocation we should perhaps dare to ask ourselves whether Africa in the 21st century has such a central organising idea as Ethiopia provided a century ago, summoning us to act in unity to address our contemporary challenges and thus to add to the world the new civilisation of which Seme spoke a decade after the victory at Adwa! ..."

እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ የነፃነት አባት፣ የፀረ አፓርታይድ ታጋይና የሰላም የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ ከእስር በተለቀቁ ማግሥት በFree Ethiopian Church of South Africa ተገኝተው ባደረጉት ንግግራቸው - ኢትዮጵያዊነትን ብርቱ መንፈስ፣ የዓድዋውን ዘመን አይሽሬና ትውልድ ተሻጋሪ ቅርስነት እንዲህ ሲሉ ነው በኩራት የገለጹት፣

"... Fundamental tenets of the Ethiopian Movement were self-worth, self-reliance and freedom. These tenets drew the advocates of Ethiopianism, like a magnet, to the growing political movement. ... the Adowa Victory provided practical expression to Ethiopianism: self-worth, dignity, unity, confidence, self-reliance, race pride, spirituality & freedom from colonialism."

በተመሳሳይም ማንዴላ/ማዲባ ኢትዮጵያዊነት የአፍሪካዊ ማንነታቸው፣ ታሪካቸው፣ ኩራታቸው ስርና መሠረት መሆኑን "Long Walk to Freedom" በሚለው ራሳቸው በጻፉት የሕይወት ታሪክ መጽሐፋቸው እንዲህ ጠቅሰውታል።

"Ethiopia always has a special place in my imagination and the prospect of visiting Ethiopia attracted me strongly than a trip to France, England & America combined. I felt I would be visiting my own genesis, unearthing the roots of what made me an African."

እንግዲህ ኢትዮጵያዊነትን በጠላትነት ለፈረጁትና በርካታ የኦሮሞ ልጆችና ጀግኖች በደማቸው የነፃነት ሕያው ታሪክ የጻፉበትን- የዓድዋ ድልንም "የአቢሲኒያውያን የቅኝ ግዛት መስፋፋት ዘመቻ" አድርገው ለሚቆጠሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ "ነፃ አውጪ" ወገኖቻችን ይህን የታሪክ ሐቅ አስረግጠንና ደጋግመን ልንነግራቸው እንወዳለን። እንደ ሕልማቸውና ምኞታቸውም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ ማንነት እንደ ኢያሪኮ ግምብ በጩሀት የሚፈርስ፣ የሚናድ ማንነት ሳይሆን፣ ዘመናትን የሚሻገር በጽኑ አለት ላይ የተመሰረተ ታላቅ፣ ሕያው ማንነት ነው። ይህ ማንነትም አፍሪካውያን፣ መላው ጥቁር ሕዝቦችና በአጠቃላይም ነጻነታቸውን የሚፈቅሩና የሚያከብሩ የሰው ልጆች ሁሉ በፍቅር፣ በኩራት የሚጋሩት ታሪክና ቅርስ ነው። አበቃሁ!!

ክብር ለኢትዮጵያ፣ ለጥቁር ሕዝቦች/ለሰው ልጆች ነፃነትና አንድነት ደማቸውን ላፈሰሱና አጥንታቸውን ለከሰከሱ ጀግኖቻችን ሁሉ!!


ፍቅር ለይኩን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!