ይገረም አለሙ

Ethiopian political parties
ሰማያዊ ፓርቲ፣ መኢአድ እና አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ (ዲዛይን @ ኢዛ)

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ምክንያት የሆነኝ ከተቀዋሚው ጎራ የማይጠፋውና ሰሞኑን ከሰማያዊ ፓርቲ ሰፈር እየተሰማ ያለው መወነጃጀልና መፈራረጅ ብሎም ሰማያዊ ፓርቲን ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ ሊያፈርሱት ነው የሚለው ጩኸት ነው።

ትውስታ፤ የሰማያዊ ውስጣዊ ችግር ተባብሶ ለአየር መብቃት በጀመረበት ወቅት ሰማያዊ ይድን ይሆን! በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሁፍ “የፖለቲከ ስህተትና የሳንባ ነቀርሳ ጠንቆች የተመሳሳይነት ባህርይ አላቸው። ሁለቱም ችግሮች በለጋነታቸው ወቅት ከተነቃባቸው ችግሮቹን የማስወገድ ዕድል ከፍተኛ ነው። ችግሮቹ ሥር ከሰደዱ በኋላ የሚደረገው መሯሯጥ ግን ፈውስ የማስገኘቱ ሁኔታ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን የማይቻልም ሊሆን ይችላል።” የሚለውን የእንግሊዝ ጠ/ም የነበሩትን የማርጋሪት ታቸርን አባባል ጠቅሼ፣

የጽሁፌ ዓላማ “አውቀውት ግን ድፍረት በማጣት አለያም ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ሆኖባቸው ያላወቁትን በሽታቸውን ከነምክንያቱና ምልክቱ በማሳየት ደፍረው በበሽታቸው ላይ እንዲነጋገሩና መድኃኒቱንም ሁሉም አንደ ህመማቸው መጠን እንዲወስዱ ለማበረታታት” መሆኑን ገልጬ፣ “ነገር ግን ለዚህ ፈቃደኝነቱም ዝግጁነቱም ድፍረቱም ያላቸው ምን ያህል ሰዎች አንዳሉ አላውቅም። ቢሆንም ቀብሩ ላይ ከማልቀስ ከበሽታው እንዲፈወስ የሚቻለውን ማድረጉ ይሻላልና የአኔን ልወጣ።” በማለት የሰማያዊ ፓርቲን በሽታ ምንነት፣ የጅማሬውን መቼነትና እንዴትነት በማስረጃ አመላክቼ፣ መፍትሄ ያልኩትንም እንዲህ በማለት ገልጬ ነበር።

“በውስጥም በውጪም ያላችሁ አባላትም ሆናችሁ ደጋፊዎች ጎራ ለይታቹሁ በሽተኞቹን ወደ መቃብር የሚገፋ ሆይ ሆይታችሁን አቁሙና በሽታቸውን እንዲያውቁ መድኃኒቱንም እየመረራቸውም ቢሆን እንዲውጡ ለማበረታታት ከቻላችሁም ለማስገደድም ትጉ። መድኃኒቱ ግልጽ ቀጥኛና በሀቅና በድፍረት የሚካሄድ ውይይት ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ የቻላችሁ በአካል ያልቻላችሁ በማህበራዊ ድረ-ገጽ ለቀብሩ ትገናኛላችሁ። እኔ ግን ፈጣሪ መልካሙን ለመስማት ያበቃን ዘንድ እመኛለሁ።”

ነገር ግን ቀደምቶቻቸው በሄዱበት መንገድ ከመሄድ ሊወጡ ያልቻሉት የሰማያዊ አመራሮች በርስ በርስ ሽኩቻ እየተናጡ ፓርቲያቸውን ለአደጋ ዳርገው ያንኑ ከትናንቶቹ የወረሱትንና በደንብ የተለማመዱትን መዘላላፍ መፈራረጅ እና ወያኔን መክሰስ እያሰሙን ነው። እነርሱ ቤታቸውን ለማቃጠል እሳት ሲጭሩ ወያኔ እንዲያጠፋላቸው ያስቡ ነበር? ፕ/ር መረራ ስለ ፖለቲከኞቹ ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር። “የፓርቲዎቹ መሪዎች በቀላሉ የመከፋፈል ወጥመድ ውስጥ ይገባሉ። ባለመተማመን በሀሜት ይወድቃሉ፡ የሚያገኙትን ትርፍ እንኳን ሳያውቁ ወደ መከፋፈል ወጥመድ ውስጥ ይገባሉ።” (እንቢልታ ጋዜጣ ቅጽ 1 ቁ27)

ከወያኔ ምን ይጠበቃል፣

መጠሪያቸው ተቀዋሚ፣ ዓላማቸው ወያኔን ማስወገድ፣ ግባቸው ሥልጣን መያዝ መሆኑን አውጀው ፓርቲ መሰረትን የሚሉ ሰዎች በየግዜው የሚያሰሙት ወያኔ አፈረሰን፣ ከፋፈለን አዳከመን፣ የሚለው ጩኸታቸው በአበባ ምንጣፍ እንዲቀባላቸው፣ እየኮተኮተ እንዲያሳድጋቸው ብቻ አይደለም ሲጣሉ ፍትሀዊ ብይን እንዲሰጣቸው ሳይቀር ይመኙ ወይንም ያስቡ ነበር እንዴ የሚያሰኝ ነው።

ከመነሻው የሚቃወሙትን ኃይል ማንነት፣ ምንንት፣ አቅምና ተንኮል በሚገባ ተረድተው እቅዳቸውም ሆነ ዝግጅታቸው ከግማሽ በላይ እራሳቸውን ከወያኔ በመከላከል ተግባር ላይ ያተኮረ ማድረግ ነበረባቸው። እነርሱ ግን ትናንትም እንዳየነው እነሆ ዛሬም እያየንና እየሰማን እንዳለነው በተቃራኒ ፓርቲያቸውን ለጥቃት ያጋልጡና ወያኔ አንዲህ አደረገን እያሉ የአዞ አንባ ያነባሉ።

በአንድ ቤት ውስጥ በቤተሰብ አባልነትም ይሁን በደባልነት አብረው የሚኖሩ ሰዎች አምባጓሮ አንስተው በዚሁ ምክንያት እሳት ቢቀጣጠልና ርምጃቸውን እየለካ፣ ድምጻቸውን እያዳመጠ በቅርብ የሚከታተላቸው ባላጋራቸው አጋጣሚውን ተጠቅሞ እሳት ማጥፊያ ውኃ ይዞ የደረሰ መስሎ ነዳጅ ጨምሮ ቢያቀጣጥለውና ቤቱ አመድ ቢሆን ቤቱን አቃጠለ የሚባለው ማነው?

በሰሞነኛው የሰማያዊ ጉዳይ በማጀቢያነት እየተገለጸ ያለው አንድነት የፈረሰው፣ መኢአድና ሰማያዊ ወደዛው እያመሩ ያሉት በራሳቸው አባላትና ደጋፊዎች በተለይም አመራር ላይ በነበሩና ባሉት ሰዎቻቸው ነው። ይህን የራስን በሽታ አውቆ መድኃኒት ለመፈለግ ድፍረቱም ብቃቱም ባለመኖሩ የራስን ድክመት በወያኔ አረመኔያዊ ድርጊት እየሸፈኑ የዛሬዎቹም የትናንቶቹ በተጓዙበትና ለውጤት ባልበቁበት ጎዳና እንደቀጠሉ ናቸው።

የተቃዋሚ ፓርቲ ወንበር ሥልጣን ሆኖ ሽኩቻ

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ወያኔ አፈረሳቸው /አዳከማቸው እየተባሉ ተደጋግመው የሚነሱት መኢአድና አንድነት ሲሆኑ፤ አሁን ሰማያዊም እየተቀላቀለ ነው። ከፖለቲካው ሆያ ሆየ ጨዋታ ወጣ ብሎ፣ ድጋፍና ተቃውሞን በጭፍን ጥላቻና ፍቅር ማድረጉን ለደቂቃ ገታ አድርጎ ዙሪያ መለስ ማየት ለቻለ ሰው እነዚህ ፓርቲዎች የፈረሱትም ሆነ እየፈረሱ ያሉት በራሳቸው በተለይም አመራር ላይ በነበሩና ባሉ ሰዎቻቸው መሆኑን ለመረዳት ብዙ ጥረት አይጠይቀውም። ብዙ መረጃ በቅርብ ማግኘት ይቻላል ከታሰበበት። እኔ ዝርዘር ውስጥ ሳልገባ ትንሽ ማሳያ ላቅርብ፤

አንድነት፤ አንድነት ህመሙ የጀመረው ሊቀመንበሩ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ስትታሰር ነው። መድኃኒት የሚፈልግለት አይደለም በሽታውን የሚያውቅለት ጠፍቶ ለአምስት አመታት ከተሰቃየ በኋላ በሀገር ቤትም በውጪም የሚኖሩ ከአመራር እስከ አባል የነበሩ የግዛቸው ነኝ፣ የበላይ ነኝ በማለት በፈጠሩት የሥልጣን ሽኩቻ በሽታው ተባብሶ ግብአተ መሬቱ ተፈጸመ።በመቃብሩ ላይ የቆመው ትእግስቱ አዎሉም በየግዜው በሹመት ላይ ሹመት ሲሰጡት የነበረ ሰው ነው። ታዲያ ለአንድነት ሞት ቀዳሚው ተጠያቂ ወያኔ ወይንስ የሥልጣን ጥም ያናወዛቸው የአንድነት አመራሮችና የዲያስፖራ ብር ያናወዛቸው አጃቢዎቻቸው።

መኢአድ ስለ መኢአድ ባነሳሁ ቁጥር የሚከነክነኝ የዶ/ር ታዲዎስ ቦጋለ ነገር ነው። ከቅንጅት አመራሮች ጋር በሀሰት ተከሰው 21 ወራት ታሰሩ። የመኢአድ ም/ል ሊቀመንበር ሆነው በሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት በእነ ኢ/ር ኃይሉ ወንጃይነትና በምርጫ ቦርድ ተባባሪነት በሀሰት ተከሰው 17 ወራት ታስረው ይግባኛቸውን የተመለከተው ፍርድ ቤት በነጻ አሰናበታቸው። የራሳቸውን ሰው ያውም ም/ል ሊቀመንበር ከሰው በወያኔ የሚያሳስሩ ሰዎች የራሳቸው አጥፊነት ተደብቆ እንዴት ወያኔ አፈረሳቸው ይባላል ? ከዛም በኋላ አቶ አበባው ሊቀመንበር ሆነው እነ ማሙሸት አማረ በሀይሉ ሻውል ተሸሙ አንጂ በጉባኤ አልተመረጡም ብለው ያንኑ የሚያውቁትን እናም የለመድነውን ፍረጃና ዘለፋ አሰሙን፤ የሚገርመው ነገር አቶ አበባው ተነስተው አቶ ማሙሸት ሊቀመንበር ሲባል ደግሞ አቶ አበባው ባላወኩት ሁኔታ በኢ/ር ኃይሉ ሻውል ተገፍቼ ነው ከመድረክ የተባረርኩት አሉ። በዚህ ሁኔታ የሁለቱ ቡድን ሲፋተግ ቆይቶ አቶ አበባው ተመልሰው ወደ ሥልጣን መጡ፤ ከዛ ደግሞ ዶ/ር በዛብህ ተመረጡ ተባለ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን መዘላለፉ መፈራረጁ መወነጃጀሉ ወዘተ አላባራም። ወያኔም በምርጫ ቦርድ አማካኝነት በቅርብ እየተከታተለ ኳስ እያቀበለ ሲያጫውታቸው ቆይቶ ለዶ/ር በዛብህ ቡድን ምሥክር ወረቀት ሰጠ። ታዲያ ወያኔ ምን እንዲያደርግላቸው ታስቦ ነው አፈረሳቸው አዳከማቸው የሚባለው።

ሰማያዊ፣ በሽታው የጀመረው በቃል የወጣት ፓርቲ እየተባለ በተግባር ግን በዘልማዱ መንገድ በመጓዝ ሰርጎ ገብ፣ ፓርቲ አፍራሽ፣ አንጃ የሚሉ ቃላት በአመራሩ አካባቢ መሰማት በጀመረበት ግዜ ነው። ይህ በሽታው ከማጀት አልፎ ለአደባባይ ሲበቃ፣ አመራሮቹ ነገረ ስራቸው ከተለመደው መፈራረጅና መዘላለፍ አልፎ በገንዘብ ብክነት እስከመካሰስ ሲደረስ አረ ምንድን ነው ምክንያቱ፣ መፍትሄውስ ብሎ የሚቻለውን ለማድረግ የጣረ ቢኖር በጣም ጥቂት ነው። ታዲያ በሥልጣን በሽታ ጎራ ለይተው በለው ሲባባሉ ከርመው አሁን የየራሳቸውን ጉዳጉድ ደብቀው ወያኔ አፈረሰን ሲሉ እነርሱ ባያፍሩ እኛ ግን ልናፍርባቸው እንጂ በምንም መልኩ ጩኸታቸውን ልናስተጋባ ፓርቲው ለሞት ከበቃም ለቅሶ ልንቀመጥ አይገባም። ታሞ ያልጠየቀ ሀኪም ቤት ወይንም ጸበል ለመውሰድ ያልሞከረ፣ መድኃኒት መግዣ ብሎ ድንቡሎ ያረዳ ሲሞት ዋይ ዋይ ማለት ምን ይሉታል። ድምጻዊ ብዙነሽ በቀለ “በቁም ሳይጠይቁኝ ስሞት ማልቀሳቸው ውርስ ለማግኘት ነው ሀብታም መስያቸው” ብላ ዘፍና ነበር፣ ታሞ ሲማቅቅ፣ ወደ ሞት እያመራ መሆኑ ሲታወቅ ለማዳን ያልጣሩ አንደውም የሞቱን ግዜ የሚያፋጥን ሥራ ሲሰሩ የነበሩ ዛሬ ተነስተው ሊሞት ነው እያሉ ደረት መድቃታቸው ከሰማያዊ ሞት ምን የሚገኝ ነገር ቢኖሮ ይሆን!

በመጨረሻ አስገራሚ ገጠመኝ፣ ይህችን አስተያየት እየከተብኩ ሳለሁ ሀምሳዎቹን በአጋመሰው ዕድሜየ ሰምቼው የማላውቀው “አይ ዘመን” የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን አገኙሁ፣ ስንኞቹ ከዚህች ጽሁፍ ጋር የተዛመዱ መሆናቸው ነበር ለእኔ አስገራሚ ገጠመኝ የሆነብኝ። ትንሽ ጀባ ልበላችሁን ልሰናበት።

አይ ዘመን አይ ግዜ- እንደው የኛ ዘመን
የመኖርን ጥቅም ሳናውቅ አጣጥመን፣
ውስብስብ ውልክፍክፍ - ወዲያ ሲሉት ወዲህ
በዘ-ልማድ ብቻ ቀን ይገፋል እንዲህ
በመዋል በማደር ዘመን ያልፋል እንዲህ

ሁሉም ከአንገት በላይ- ሳቅ ጨዋታ ለዛ
ደግ አሳቢ አነሰ ክፋት ተንኮል በዛ፣
መሬት መሬት አየ አይን አቀረቀረ
በቃል ኪዳን መጽናት መተማመን ቀረ።

… ዘፈኑ ይቀጥላል እኛ ግን ይብቃን፣ የትናንቱ መንገድ ወዴትም አያስኬድ!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!