Christian and muslimባህር ከማል

እራስን ከጥቃት በመከላከል ሰላማዊ ህይወት ለመምራት ከሌሎች ሰዎች ጋር ተቻችሎና ተስማምቶ አብሮ የመሆን ባህርይ የሰው ልጅ በተፈጥሮ የሚያገኘውና በህወት ልምድም የሚያዳብር ችሎታ ነው ማለት ይቻላል። ይህ አብሮ የመሆን ልምድ ከቤተሰብ ጀምሮ በጉርብትና፤ በጎሳና ሀይማኖት መመሳሰል እያደገ አገርን እስከ መመሥረት ይደርሳል። በሂደትም አንድነት ኃይል መሆኑንም ያረጋግጣል። እነዚህ በየደረጃው ያሉት ስብስቦች በውስጣቸው ልዩነት መኖሩ አይካድም። ልዩነት በሀገር ደረጃ በተሰባሰቡ ሰዎች መሀከል ብቻ ሳይሆን በመንትዮች መሃከልም ይታያል። ሕዝቦች ልዩነታቸው አንደተጠበቀ ሆኖ በጋራ በሚያስተሳስራቸው፤ በሚያቀራርባቸውና ባሳለፏቸው ታሪካዊ አብሮነት ተመስርተው አንድነትን ፈጥረው በድንበር የተከለሉ አገራትን መስረተው አብረው ይኖራሉ።

ከአንድነት የሚገኙ በርካታ ጥቅሞች መኖራቸው በጣም ግልጽ ሆኖ ሳለ የሕዝቦችን አንደነት የሚጠላ ግለሰብም ይሁን ስብስብ መኖሩ ብዙዎቻችንን ግራ የሚያጋባ ክስተት ነው። ሀቁ ግን አንድነትን የሚጠላ በአንድነቱ የማይጠቀምና የሚጎዳ ብቻ ነው። እርግጥ ነው አንዳንድ ሰዎች ስብስብን የሚፈጥሩት ለክፉ ነገርም ሊሆን ይችላል። እንዲህ አይነት ስብስብ የሚፈጥሩት ግለሰቦች ግን ምንግዜም ቢሆን ሰው በዙሪያቸው የሚያሰባስቡት አንዱ ሌላውን እንዲጠላ በመስበክና ለሚቀሰቅሱት ህብረተሰብ ከነሱ ሌላ ወዳጃና መሪ እንደሌላቸ በመስበክ ነው። ለዚህም እኛም መሀከል ለግል ጥቅም ሲባል ሕዝብ ከሕዝብ እያናከሱ አንቱ ተብለው ለመኖር ልዩነትን የሚያሰፉ ፕሮፖጋንዳ በመርጨት የተጠመዱ ወገኖች ያሉን።

ህወሃት የሕዝቦችን አንድነት የሚፈራበት ዋነኛው ምክንያት ከኢትዮጵያ ህብረተብ ውስጥ በመቶኛ ሲሰላ "ውክልናው" ከአናሳ የህብረተሰብ ክፍል በመሆኑ እራሱ በሚያቀነቅነው የፓርላማ ዴሞክራሲ ቦታ ስለሚያሳጣው ነው። ለዚህም እድሜን ለማርዘም በከፋፍለህ ግዛ ዘይቤው ሕዝቦችንን መከፋፈልን ዋና መሳሪያው አድርጎት ይኸው ሀያ አምስት ዓመት አለፈው። ይሀንን ዘይቤ ከሞላ ጎደል በስኬታማነት እስከዛሬ ለመጠቀም የቻለባቸው ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ዋንኛው ግን ቀደም ሲል ለዘመናት የነበረውንና በተለያዩ ጊዜያት ብቅ ባሉት የገዥ ክፍሎች ወቅታዊ ምላሽ ያላገኙትን የብሄር ጥያቄዎችን በ1936-42 ጣሊያን በሀገራችን በወረረችበት ወቅት ለተመሳሳይ መሰሪ አላማ የተጠቀመችበትን ዘዴ (ከዚህ ቀደም ለማብራራት እንደሞከርትኩት) በመጠቀም የችግሩ ፈቺ መስሎ በመቅረብ የአዞ እምባ በማንባት ነው።

ለዘመናት በአንድነት በመቆም ከውጭ ወራሪ ነጻነታችንን ጠብቀን የቆየን ብንሆንም ወያኔ መከፋፈል ለእርሱ ሥልጣን ላይ መቆያ ብቸኛ መፍትሄ እንደሚሆነ በመገመት ሕዝባችንን የመከፋፈሉን ሴራ የጀመረው ጫካ ጠቅልሎ ከመግባቱ በፊት ነው። ታዲያ ለዚህ ከፋፋይ ሥራው እንቅፋት ሊሆንበት የሚችሉ ሁለት ኃይሎች የኃይማኖት አባቶችና ምሁራን ነበሩ ናቸውም። ሁለቱም ኃይሎች ሕዝቡን በማንቃት ወደ ትክክለኛው መንገድ በመምራት ረገድ ተፅእኖ የመፍጠር አቅም ስላላቸው ውጥኑን ሊያከሽፉበት እንደሚችሉ ከጥዋቱ ተረድቶ ነበር። በመሆኑም እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በጠላትነት በመፈረጅ ለማንበርከክና ለማጥፋት ጥረት የጀመረው ገና ከትግራይ በረሃ ሳይወጣ ነበር።

ለዚህም የህወሃት የመጀመሪያ ኢላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ናት። በታሪክ አጋጣሚ ቤተክርስቲያኒቷ በነበራት ሥፍራ ከአማራው ብሄር ጋር በማያያዝ አማራውን በጥቅል እንደ ጨቋኝና በዳይ በማቅረብ ከማጥላላት አልፎ የቤተክርታኒቷን መሬት በመንጠቅ ለደጋፊዎቹ አድሏል። መሪዎችንም ከአብተክርስትያን በማባረር ታዛዥ በሆኑት መሪዎች በመተካትና (ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ ገጽ 302) እነሱንም ቢሆኑ የስለላ መዋቅሩን በቤተክርስታኒቷ ውስጥ ገዳማት ሳይቀሩ በመዘርጋት ሰላዮችን በመነኩሴነት በማስቀመጥ እየሰለላቸው ነበር።

በወቅቱ በትግራይ የነበረው የሙስሊሙ ህብረተሰብ በቁጥር አነስታኛ ከመሆኑም በላይ ከክርስትና እምነት ታካታዮች በተለየ ሁኔታ ላይ ነበር (ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ ገጽ 318)። የመሬት ባለቤትነት የሌለው ከመሆኑም ሌላ አብዛኛው ሙስሊም በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራና በከተሞች ውስጥ የሚኖር ነበር። የሙስሊሙ ህብረተሰብ ህወሃት (ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ) ኃይማኖቱን ሊያዳክምበት እንደመጣ በመገንዘብ እርኩስ አላማውን ለመቋቋም በተለይም ከአፋር የእስልምና ተከታዮች (ገብረመድህን አርኣያ) ባደረገው ተጋድሎ የተነሳ ሀወሃት ከጥፋት ዘመቻው ጋብ ቢልም ኋላ ላይ ግን ይህንን የህብረተሰብ ክፍል በፋሽስቱ የጣሊያን ዘዴ “አዛኝ ቅቤ አንጓች” እንዲሉ አስመስሎ ከጎኑ ለማሰለፍ ስለመቻሉ መካድ ይከብዳል።

በተመሳሳይ መልኩ በምሁራን ላይም ዘመቻ በመክፈት በእንታረቅ ሰበብ በተኙበት ከመጨፍጨፍ አልፎ ውጊያ በመግጠም ብዙዎችን አስወግዷል። ለዚህም ከኢህአፓና ከኢዲዩ ጋር የነበሩትን ጦርነቶች መጥቀሱ ይበቃል። እነዚህ ግፎችና ህወሃት ጫካ በነበረበት ወቅት የተከናወኑ ደባዎችና ፍጅቶች ሲሆኑ ያኔ አብሯቸው ከነበሩ የቀድሞ አባሎቻቸው ባይነገረን ወይም ባይፃፍ ኖሮ “ማን ያውራ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” እንዲሉ እንኳንስ ሌላው ኢትዮጵያዊ ቀርቶ የትግራይም ሕዝብ ባላወቀው ነበር።

በለስ ቀንቷቸው አዲስ አበባም ከገቡ በኋላ ይህንን እርኩስ አላማቸውን በመቀጠል እነዚህን ሁለቱን የህብረተሰብ ክፍሎችን በተጠናከረ ሁኔታ ኢላማቸው አድርገው እስከዛሬ ቀጥለውበታል። ለዚህም የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ቀኖና በመጣስ ጳጳስ በህይወት እያለ በሌላ በመተካትና ሲኖዶሱን ለሁለት መክፈል፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዬች ጠ/ምክር ቤትን (መጅሊስ) ለመቆጣጠር በ1987 በአንዋር መጂድ በየፀጥታ ኃይሎች የተፈጠረው እልቂትና እስካ እዛሬ ድረስ ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ፈተና የሆነውና ለድምፃችን ይሰማ ንቅናቄ መፈጠር ምክንያት የሆነው፤ ብዙዎች የተሰውበት፤ ብዙዎች የታሰሩበትና የተሰቃዩበት "ከአንዮታዊ ዴሞክራሲ ጋር ሊሄድ የሚችለውን የአህባሽ ኃይማኖት ተቀበሉ" ወከባ መጥቀሱ በቂ ነው። ህወሃት ለመሰሪ አላማው ያሰጉኛል ያላቸውን ምሁራንንም ለማስወገድ የመጀመሪያ ኢላማው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር።

ወያኔ/ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንና በምሁራን ላይ ያደረሰውናን እያደረሰ ያለውን ጥቃትና ይህ ጥቃት በበኩሉ ለነፃነት በሚደረገው ትግል ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ ከቀላል አይደለም። ይህንን በተመለከተ ሰፊ ሃተታ የሚያሻ በመሆኑ ለጊዜው በይደር ልለፈውና ሃሳቤ ላካፍላችሁ ወዳቀድኩበት ጉዳይ ላይ ብቻ ላትኩር።

በ1987 የተፈጠረው ሁኔታ በአንዋር መስጊድ 29 ምዕመናን በ"መንግሥት" የፀትታ ሀይሎች ሲገደሉ በሁኔታ በማሳበብ ወያኔ/ኢህአዴግ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዬች ጠ/ምክር ቤት (መጅሊስ) በእጁ ከማስገባቱም ሌላ የተለያዩ የሙስልም በጎ አድራጎት ድርጅቶችን (NGO) በመዝጋት የሙስልሙን የእምነት ነጻነትን የማፈኑን ተግባር ተያያዘው ። ቀደም ሲል በነበሩት 5 ዓመታት ለሙስሊሙ ማህበራሰብ የቆመ በመምሰል የሌላው ህብረተብ እምነት በተለይም የክርስትያኑን ለማዳከምና በጁ ላማስገባት ለጊዜ መግዢያነት ተጠቅሟል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ህወሃት እስልምናን ለማዳከም የተያያዘው ጥረት ሙሉ በሙሉ ባለማሳካቱ ተስፋ ባለመቁረጥ ክፍፍሉን በማጠናከር በሁለቱ ተላላቅ ኃይማኖቶች መሃል ጥርጣሬን ማጠናከር ነበር። ለዚህም ሙስሊሞችን "እስላማዊ መንግሥት ሊመሰርቱ ነው" ክርስትያኑን ደግሞ "የድሮውን ሥርዓት ሊመልሱ ነው" ብሎ "ለተለያያዩ" አድማጮቹ (Audiences) ማሰማት ነበር። ይህም ለተውሰነ ጊዜ የሰራለት መስሎ ታይቶት ነበር። በእውናታ ላይ ያልተመሰረተ የፈጠራ ወሬ መልሶ ወረኛውን ስለሚጎዳ ወያኔ/ኢህአደግ የወረወረው ድንጋይ መልሶ መታው፤ እንግሊዞች (Pissing in the wind) እንደሚሉት፣ የበለጠ ጥላቻን አተረፈለት።

አምባገነኖች በሕዝባቸው ጫንቃ ላይ በቆዮ ቁጥር የሥልጣን ጥማት ስካራቸው እያየለ ይሄዳል በዚያው መጠን አሮጋንቲነታቸውና ለሕዝባቸው ያላቸው ንቀት ይጨምራል። የሚገዙት ሕዝብ እንዴት እንደሚበላ፤ እንዴት እንደሚናገርና ከማንጋር እንደሚናገር፤ የትና ወዴት መሄድ እንዳለበት፤ መንፈሳዊ እምነቱ ምን መሆን እንዳለበት በአጠቃላይ በዚች አለም ላይ እንዴት መኖር እንዳለበት ሊወስኑለት ይቃጣቸዋል። ወያኔ/ኢህአዴግም ሁሉንም ለማድረግ ሞክሯል "እንደኛ ኃይማኖት አልባ መሆን ካልቻላችሁ ለኔ የሚስማማኝን ኃይማኖት(sect) ልጥመቃችሁ" ብሎ አህባሽ የተባለ ከእስልምና እምነት ፈር የለቀቀ አምጥቶ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ በጉልበት ለመጫን ሞከረ።

ይህም ተገቢ አለምሆኑንና እሱ እራሱ የሚመጻደቅበት "ህገመንግሥት" የመንግሥት በኃይማኖት ጣልቃ መግባትን የማይፈቅድ መሆኑን የሙስሊሙ ህብርተሰብ ኮሚቴ በማቋቋም ችግሮቹን ለማስረዳት ቢሞክርም ህወሃት/ኢህአዴግ የመናገርና የማዘዝ እንጂ የማዳመጥና"ህገመንግሥቱ" የመተገበር በህሪዪ ያልተካነ "መንግሥት" በመሆኑ የመንግሥታዊ ህይማኖት ጫናውን ለማቆም ፍቃደኛ አልሆነም።

ሰላማዊ ትግልን መታገል ለሚሹ አርኣያ ለመሆን በሚችል አለም አቀፍ ተቋማት እውቅናን ባገኘው ሰላማዊና መራር በሆነው ትግልሙስሊሞች ህወሃት/ኢህአዴግ ድምጻቸውን እንዲሰማና ለጥያቄያቸው መልስ እንዲሰጥ ግፊት ለመፍጠር ቢሞክሩም መልሱ ሕዝቡ በፊርማው የመረጣቸው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የእስር ብቻ ሳይሆን የድብደባ፣ የግርፋት፣ የማዋረድ፣ የሰብዓዊ መብትም መገፈፍ ሰለባ ማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንን ማሰር፣ መግረፍ፣ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ደግሞ ለሰደት መዳረግ ነበር። ከዚያም አልፎ ሰላማዊ ዜጎች በግፍ ጥይት እየተደበደቡ ለሞት መዳረጋቸው ሊካድ የማይችል የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ምንም እንኳን ከህወሃት/ኢህአዴግ ካንጋሩ ፍርድ ቤት ፍትሃዊነት ባይጠበቅም የህብረተሰቡን ለመደለል የተደረጉ ሞከራዎች ውስጥ አንዱና ዋንኛው በራሱ ተለቪዢን ዘጋቢ ፊልሞችን አዘጋጅቶ ማሰራጨት ነበር። እነዚህ "ዘጋቢ" ፊልሞች ማለትም "አሸባሪው አል ሸባብ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ሕዋስ (cell) ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ ነው" (አዲስ ግንባር)፤ "በኢትዮጵያ የተገኘው ሁለተኛው የአልቃይዳ ሕዋስ" (ጂሃዳዊ ሃራካት)፤ "ሸህ ኑሩን ወሃቢስቶች ገደሏቸው" (ሀዘን ለመድረስ … ጉዞ ወደ ደሴ)፤ ከእስልምና እና ከሽብርተኝነት ጋር ተያይዘው የቀረቡት የጥፋት መልዕክተኞች እና የማንቂያ ደወል የሕዝብ ገንዘብ አለአግባብ ከማባከን በስተቀር ለህወሃት/ኢህአዴግ ያተረፈለት ነገር የለም ይልቁንም የሥርዓቱ ማንነት የበለጠ የተጋለጠበት አጋጣሚ ነው ማለት ይቻላል። ከህወሃት/ኢህአዴግ ባዚሁ ሳያበቃ በትግሉ ላማዳከም የይቅርታና የእርቅ ኮሞቴ "የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ" የሚባል አካል አዋቃሮ በሙስሊማን ላይ ከጅምሩ የከሸፈ"ተጸዕኖ" ለማሳደርም ሞክሯል።

በርግጥ የሥርዓቱ ሰለባ የሆንነው እኛ ሙሊሞች ብቻ ሳንሆን በዚያች ምድር የሚኖር ክርስትያኑም፤ አይሁዲውም፤ ዋቄፈቻውም፤ ኢ-አማኑ፤ ኦሮሞውም፤ አማራውም፤ ጉራጌውም፤ ኦጋዴኒውም፤ ትግሬውም፤ ከምባታውም፤ ሃዲያውም፤ ወላይታውም ... ነው። ለሙስሊሙም ሆነ ለሌላው መብት መከበር አንድ ላይ ሆኖ ለሥርአት ለውጥ መታገል ወሳኝ ነው። የእያንዳንዳችን ነጻነት ሲከበር እንደሙስሊም ወይም እንደሌላው የህበረተሰብ ክፍል አባልነታችን ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራነጻነታችን ይከበራል። ለነጻነት የሚደረገውን ትግል የፖእቲካ ሥራ ነው ብለን ካልን፤ ከፖሊቲካ ነጻ የሆነ ግለሰብ ወይም ማህበረስብ አለ ለማለት ባያስደፍርም አላህ (ሱ.ወ) የሰጠንን አንጻራዊ ነጻነትን የነፈገንን አካል መታገል ኃይማኖታችን (42:39) የሚፈቅድልን ይመስልኛል። የ"ድምጻችን የሰማ" እንቅስቃሴም የመብትና የነጻነት ጥያቄ ነውና። የሕዝብን ድምጽ የማይሰማ አካል ካለ እንዲሰማ መገደድ ይኖርበታል። አሊያም ቦታውን ለቆ ሕዝብ በሚመርጠው መተካት አለበት። አንድ የመንግሥት አካል የሚመረጠው ሕዝቡን ሊያገልግል እንጂ በሕዝቡ አንዲገለገል ከዚያም አልፎ መብቱንና ነጻነቱን እንዲነፍገው አይደለም። በአጭሩ መንግሥት የሕዝብ ተቀጣሪ አገልጋይ ደሞዝተኛ ነው።

አንድ ሙስልም የመጀምሪያ ግዴታው ከሁሉም በላይ ኃይማኖቱ (ዲኑ)የሚያዘውን ተግባራዊ ማድረግ ነው። በመሆኑም ከሌሎች ጋር አብሮ ለመስራት በጋራ ሊተገበሩ የሚችሉ ጉዳዮች ከዚህ ከየ እለቱ የኃይማኖት (ዲን) ግዴእታዎች ጋር የሚጋጩ ከሆነ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ከነዚህም ከብዙ በጥቂቱ፤ የየ እለት የሰላት ሰአታት፤ የአርብ (ጁምአሰላት)፤ የረማዳን ወር ጾም፤ የወንዶችና ሴቶች አንድ ላይ መሰባሰብና የመሳሰሉት ናቸው። የሁሉንም የተለያዩ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊያንን ተሳትፎ ለማጎልበት የጋራ መድረኮች ከቤተ እምነቶች ሰበካ ቢፀዱ መልካም ነው የሚሉም አሉ። ስብስቦቻችን በነሱ ባይባረኩ ምንም የሚጎላቸው ነገር አይኖርም። የእምነት አባቶች ከምዕመናን ጋር በየሚሰበሰቡበት ስፍራና ቤተኢምነቶች ለሕዝባችን የሚያደርጉት ፀሎት በቂ ነው ይላሉ።

እነዚህን አንደየ ሁኔታቸው ማስተናገድ (Accommodate) የሚቻል የመስለኛል። ከዚህ ውጭ መሰራታዊ የሆኑና ለአብሮ መስራት እንቅፋት የሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ ያሉ አይመስለኝም። ካሉ ግን ፊትለፊት መነጋገር መፍትሄ ለማግኘት የበጃል ብዬ አምናለሁ። ይህ ካልሆነ ግን እርስበርሳችን እየተጠራጠርን ሁላችንም ነጻነታችንን እንደ ተነፈግን ኖረን ለልጆቻችን "ባርነትን" አስረክበን እናልፋለን። ይህ ደግሞ የማንንም አባት ወይም እናት ፍላጎት አለመሆኑ ግልጽ ነው።

እስልምና አብሮ መስራትን ነው የሚያስተምረን። የአገራችንን ሁኔታ ስንመልከት ዘርና ጾታን ሳይለይ ምስራቅ ያለው ለምዕራቡ፤ ደቡብ ያለው ለሰሜኑ፤ እንዲሁም ለመሃል አገሩ ሙስሊምና ሌሎች የአገሩ ሕዝቦች መብት መከበር ተቆርቋሪና ለተግባራዊነቱ መታገል ይኖርበታል። አንዱ የህብረተሰብ ክፍል ነጻነት ከተነፈገ የሁሉም ነጻነት እንደተነፈገ ይቆጠራል። በአንድ አገር ያሉ ሕዝቦች የሚኖራቸው ነጻነት እኩል መሆን የኖርበታል። ከታሪክ እንደምንረዳው እስልምና የሚያስተምረን ይህንኑ ነው።

ይህ ከሆነ ታዲያ ለነፃነት በሚደረገው ትግል እኛ ሙስልማን እያደረግን ያለው አስተዋጽኦ በቂ ነው ማለት ይቻላል? ይህንን ጥያቄ የማቀርበው ለራሴ ጭምር ነው።

ኢትዮጵያ እስልምናን ከተቀበለች ለአስራ አራት ምዕተ-ዓመት ቢሆንም የቀድሞ ገዢዎቻችን 30% (በዚህ ቁጥር የሚከራከሩም አሉ) ሙስልም ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያ የክርስትያን ደሴት ናት ይሉ ነበር ዛሬ ግን ወያኔ ህንን ቀይሯል ብለን ከሆነ ተሳስተናል። ይልቁንስ ኃይማቶት የለሹ ወያኔ ሁሉም ኃይማኖቶች የተደፈጠጡባት የመከራና የአፈና ደሴት ነው ያረጋት። እርግጥ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ወጣቱ ትውልድ የእስልምና መጻሕፍቶችን በአገራዊ ቋንቋ በቀላሉ ማግኘት በመቻሉ እራሱ ለማስተማር ችሏል። ወያኔ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ለራሱ ጊዜ መግዢያ እስከ 1987 ድረስ ለቀቅ ባደረገው አንጻራዊ ነፃነት መስድጂዶችና የመማሪያ ተቋማት ሊገነቡ ቢችሉም በኋላ ላይ ግን በመጅሊሱ አማካይነት አህባሾች እንዲቆጣጠሯቸው ተደርጓል። ይህ ማለት ደግሞ ሁሉም በወየኔ ቁጥጥር ሥር ነው።

በኢትዮጵያ በእስልምና ተቋም (Institution) ደረጃ ባይሆንም በመካሄድ ላይ ባለው የነፃነት ትግል ውስጥ በግልም ሆነ ኃይማኖታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በመሳተፍ ላይ ያሉ ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አሉ ። ለዚህም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተደረጉና እየተደረጉ ያሉ ትግሎች በቂ ምሳሌዎች ናቸው።

መሪዎች በግልም ሆነ በስብስብ (Congregational) ሌላው ቢቀር እየተፈጸመ ያለውን ግፍና ሰቆቃ በማውገዝ ረገድ በሀገር ውስጥ ባለው የወየኔ/ኢህአዴግ ጫና ከባድ ቢሆንም ያ ስጋት በሌለበት በውጭ አለም በምንኖር በጋራም ሆነ በግል ለነፃነትና ለፍትህ ለሚደረገው ትግል ተሳትፎአችን በጣም አነስተኛ ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቶቹ ግን ከመላምት ባሻገር (በግልጽ ሥርአቱን የሚደግፉ እንዳሉ ሆነው) ይህ ነው ማለት ያስቸግራል።

ከመላምቶቹ መሃከል የተሻለች የሁሉም መብት የተከበረባት ኢትዮጵያን ለመገምባት በመታገል ላይ ያሉትን ኃይሎች በቅርበት ካለማወቅ የተነሳ በጥርጣሬ አይን የማየት፤ የወያኔን መሰሪነት ካለመረዳትና ከትናንቱ መገፋት (marginalization) በመነሳት ከልብ ሥርዓቱ እስልምና የቆመ አድርጎ መውሰድ፤ "የባሰ ይመጣ ይሁን?" ጥርጣሬ፤ "እኔ ምናገባኝ ድሮም አልነበርኩበትም"፤ እያወቁ ለጊዜያዊ ጥቅም መሸነፍን … የመሳሉትን ያጠቃልላል።

ኃይማኖታችን ለሃቅና ለፍትህ እንድንቆም ያስገድደናል። በጎሳና በነገድ ሳይሆን እንደ ሕዝብ አንድ ላይ ሆነን በደልን እንድናወግዝና ከተበዳዮች ጎን እንዲንቆም ያዘናል።

አላህ (ሱ.ወ) የሰጠንን አንፃራዊ ነፃነት የሱ ፍጡር በሆኑት አምባገነኖች ተነጥቀን ሲያዋክቡን፤ ሲያሰድዱን፤ ሲያስሩን፤ ሲያሰቃዮንና ሲገሉን መሪዎቻችን ምንም እንዳልተፈጠረ ፈታቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ በማዞር ዝምታን መምረጣቸውና አዳንዳንዶቹም ከነዚህ አምባገነኖች ጎን መሰላፋቸው ተገቢ አይመስለኝም።

የዛሬ 77 ዓመት የጣሊያ ወራሪዎች መጠቀሚያ እንዳደረጉን ህወሃት/ኢህአዴግ እንዲደግም መፍቀድ የለብንም። የግለሰቦች ነፃነት ሲረጋገጥ የሁላችንም ነፃነት እንደ ግለሰብም ሆነ አንደ ሰብሰብ ሰለሚረጋገጥ የነፃነት ትግሉ የሙስሊሞችም ነው። ዛሬ በትግሉ መሳተፍ ስንችል ነው ነግ "ይህ የዛሬ ነፃነት እኔም ትናንት የታገልኩለትና ወንድሞቼ፤ እህቶቼ፤ አባቴና እናቴ መስዋእትነት የከፈሉበት ነው" ብለን በሙሉ ልብ መናገርና የነፃነቱ ባለቤትነት ሊሰማን የሚችለው።

ትግሉን መቀላቀል የሚንችለው እኛ ወደ ትግሉ በመሄድ እንጂ ብቻ ነው፤ እኛ ወደ ትግሉ ካልሄድን ችግሩ ወደኛ መምጣቱ አይቀሬ ነውና። ቀደም ሲል የተጠቀሱት የኃይማኖታችን የዕለት ተዕለት ተግባራት (ዕባዳ) ጋር የተያያዙ የጊዜና ቦታ ጉዳዮችን ማስተናገድ የሚቻል ከሆነ ከዚህ ውጭ ያሉ እንዳንቀራረብ የሚያደርጉን ጉዳዮች ካሉም በግልፅ በመወያየት መፍትሄ ማግኘት ይቻላል። ከዛም ባለፈ ባጋራ ሊያስማሙን በሚችሉ ጉዳዮች ላይ አብሮ በመስራት ለነፃነት መብቃት የሚቻል ይመስለኛል።

ኃይማኖታችንን ፈጣሪያችን ባዘዘን መልኩ በትክክል መተግበር ያሚቻለው ነፃነት ሲኖር ነው። ነፃነትና ሀገር ደግሞ ተለያይተው አይታዩም፤ አንዱ ከሌለ ሌላኛው ትርጉም ያጣልና።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት የተለያዩ ኃይማኖቶች በተለይም በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች መሃከል በጥርጠሬ መተያየቱ ሊኖር ይችላል። እርግጥ በተለያዩ ዘመናት በሌላው የዓለም ክፍሎች ከታዮትና እየታዩ ካሉት የኃይማኖት ግጭቶች የራሱ በሆኑ ምክንያቶች በባህሪየም ሆነ በይዘቱ የተለየ ቢሆንም ግጭቶችም ሆኑ በጥርጣሬ መተያየቱ የነበረና ዛሬም ያለ መሆኑን መካድ አይቻልም። ይህም ዝምብሎ በአንድ ጀምበር የተከሰተ ሳይሆን ለብዙ ዘመናት አብረን የኖርን ቢሆንም በዚያው መጠን በተለያዩ ጊዚያት በአገሪቷ ውስጥ የተነሱት ገዚዎች ለሥልጣን መቆናጠጫና ሥልጣኑ ላይ ለመቆያ ሁለቱን ታላልቅ ኃይማኖቶችን በመሳሪያነት በመጠቀማቸው እርስ በርስ ጦርነት መሳበቅ የተደረሰባቸው ጊዚያት መኖራቸውና የበላይነትን የተቀዳጀው ክፍል በዚያው ለመቀጠል ያደረጋቸው ጥረት የወለደው የማግለልናን የመገለል ሂደቶች የጥርጣሬ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ።

ወያኔ የኢትዮጵያን ሙስሊሞች ፅንፈኛች፤ መሪዎችን ደግሞ (እጅ የሰጡትን ሳይጨምር) አሸባሪዎች እንደሚላቸው ሳይሆን፤ በተለይም የወጣቱ ትውልድ መሰረታዊ ባልሆኑ (ሰለፊ፤ ሱኒ፤ ተብሊጊ …) ላይ ከማተኮር ቁርአንና የነቢዩን (ሠ.አ.ወ) ሱናን በመከተል ትክክለኛና ጥሩ ሙስሊም መሆንን የመረጠ በመሆኑ በጥቅሉ መጠርጠር ተገቢ አይሆንም።

እርግጥ በማንኛውም ኃይማኖት ሆነ የፖለቲካ እምነት ውስጥ ካለማወቅም ሆነ አውቀው ለተለየ አላማ ከትክክላኛው መንገድ ወጣ ያለ የፅንፈኝነትን አቋም የሚያቀነቅኑ አንዳሉ ሁሉ በሙስሊሙም ህብረተብ ከላይ ከተጠቀሰው ባልተለየ ምክንያት መኖራቸው መካድ አይቻለም። ሆኖም እነዚህቡድኖች ጥቂቶች በመሆናቸው የስጋትና የጥሪጣሪ ምንጭ መሆን የለባቸውም። እንዚህንም የመወጋት የሙስሊሙ ህብረተሰብ መሰረታዊ ተግባር ነው።

የመልእክቴ መሰርታዊ አላማ ችግሮች ካሉ ለችግሮቹ መፍትሄ ለመሻት እንዲቻል ለውይይት ለመጋበዝ እንጂ ስለ እስልማና እውቀት አለኝ ብዬ በድፍረት ያልቀረብኩ መሆኔና ተሳስቼም ከሆነ ፈጣሪዬን ይቅርታ እየለመንኩ ለመታረምም ዝግጁ መሆኔን ላንባቢያንም ለመግለፅ እወዳለሁ።

ምንም እንኳን እንደ ህወሃት ላሉት (የዶክተር መራራ ቃል ልዋስና) እነሱ ከጫካ ቢወጡም ጫካ ከነሱ ውስጥ ላልወጣ ቡድኖች የማይሰራ ቢሆንም ዛሬ አለም በደረሰበት ዘመን መነጋገር፤ መወያየትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመረኮዘ የችግር አፍታት ዘይቤ ከፍተኛ ሥፍራ አለው ብዬ ስለማምንም ጭምር ነው። እንኳንስ አገርን የሚያህል ግዙፍና የህልውና ጉዳይ ቀርቶ በቤተሰብ መሃከል ለሚፈጠረው ችግር እንኳን በመነጋገርና በጋራ በመስራት ነው መፍትሄ የሚገኘው። በተናጠል ለጠላት ከመመቸት በስተቀር የትም አንደርስም።

አላህ ወደተቃናው መንገድ ይምራን።

አላህ ኢትዮጵያን ከነ ሕዝቦቿ ይጠብቃት። አሚን!!!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!