ግርማ ካሳ

New Shewa zone.
"ኦሮሚያ ስትኖር ኢትዮጵያ ልትኖር ትችላለች። ኦሮሚያ ስትፈርስ ግን ኢትዮጵያ የምትባል አገር ቅዠት ትሆናለች" መርጋ ኢብሳ

መርጋ ኢብሳ የተባሉ ጦማሪ የአዲስ አበባና አካባቢዋን ሕዝብ በተመለከተ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተው አነበብኩኝ። ትንሽ አሳቁኝም አናደዱኝም።

"ኦሮሚያ/ሸዋ ውስጥ ያሉ በትምክተኝነት ምክንያት ኦሮምኛ ያልቻሉ ጥቂት ማኅበረሰቦች ካሉ ሁለት እድል አላቸው። አንደኛ ኦሮምኛን ለምደው ተስማምተው የክልሉን ሕግ አክብረው መኖር። ሁለተኛ ትምክተኝነት የሚወጥራቸው ከሆነ ደግሞ ወደመጡበት በፍላጎት ሄደው በክልላቸው እንደፈለጋቸው መሆን ይችላሉ። ከዚህ ውጭ ኦሮሞን በጎጥ ለመከፋፈል የምትጥሩትን የሚሰማቹ የለም። ኦሮሞ አንድ ነው። ሁሉም የቦረኔ ባረንቱ ልጅ ነው። ሸዋ ሲነካ ወለጋ ተነካ፤ ሐረር ሲነካ ጅማ አርሲ፣ ባሌ፣ ሸዋ፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ ኢሉ፣ ወሎ(ኦሮሞ)ን ያገባዋል። ኦሮሚያ ስትኖር ኢትዮጵያ ልትኖር ትችላለች። ኦሮሚያ ስትፈርስ ግን ኢትዮጵያ የምትባል አገር ቅዠት ትሆናለች“ ነው ያሉት እኝህ ጦማሪ።

ይሄ አስተሳሰብ እንደ ኦነግ ያሉ ብዙ የኦሮሞ አክራሪ ብሔረተኞች የሚጋሩት ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ። ለዚህም ነው ላለፉት 25 ዓመታት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢ አፍቃቂ ኦነጋውያን የኦህዴድን ካባ ለብሰው፣ “ኦሮሞ አይደላችሁም፣ አገራችሁ አይደለም” በሚል ከፍተኛ ግፍና ሰቆቃ እየደረሰባቸው ከቅያቸው የተፈናቀሉት።

እኝህ ጦማሪ ኦሮሚያ የሚባለው የመጣው ከ25 ዓመታት በፊት መሆኑ የረሱ ይመስላል። ኦሮሚያ ኦነግና ሕወሃት፣ “አማራ” የሚሉትን እና የኢትዮጵያ ብሔረተኞች የሆኑትን (ትምክህተኞች የሚሏቸውን) ለማዳከምና ለመምታት ጠፍጥፈው የሰሩት ክልል ናት። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት የነበረች ናት። ያ ማለት ያለኦሮሚያ ኢትዮጵያ ለዘመናት ኖራለች። እዚህ ላይ ኦሮሞን ከኦሮሚያ መለየት መቻል አለብን። ያለ ኦሮሞ ኢትዮጵያ የምትባል ልትኖር አትችልም። ኦሮሞ ዶ/ር መራራ እንዳሉት የኢትዮጵያ ግንድ ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ ኦሮሚያ ብቻ ሳትሆን አሁን በዘር ላይ የተሸነሸው ፌዴራል አወቃቀር ራሱ ሰላምን እና መረጋጋትን ሊፈጥር የሚችል እንዳልሆነ በገሃድ እየታየ ነው። በወልቃይት ጠገዴ ያለው፣ እንደ ሞያሌ፣ ጭናክሰን ባሉ በርካታ ወረዳዎች፣ በአዲስ አባባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ... ያሉ ውዝግቦች፣ ለምሳሌ፣ “ይሀ ግዛት የዚህ ዘር ነው፣ ያ ግዛት የዚያ ዘር ነው” ከሚለው አሁን ካለው አወቃቀር የመነጩ ችግሮችና ቁውሶች ናቸው።

በአዲስ አበባና አካባቢዋ፣ እንደ አዳማ/ናዝሬት ያሉትን ጨመሮ በርካታ አማርኛ ተናጋሪዎች ከተለያዩ ብሔረሰብ የሆኑ ወገኖች የሚኖሩባቸው ናቸው። የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናትና ገዢዎች በአብዛኛው በዚህ አካባቢ የሚኖረውን ማኅበረሰብ ሥነልቦና የማይረዱ እንደውም፣ ይሄንን ሕዝብ በጥርጣሬ የሚያዩ ነው የሚመስሉት። በክልል መንግሥት ደረጃም የሚያራምዷቸው ፖሊሲዎች በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚኖሩ ሌሎች ማኅበረሰቦችን ጥቅም የሚያስከብር ሳይሆን መብታቸውን የሚረግጥ ነው። በአገራቸው ሁለተኛ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያደርግ።

ለምሳሌ በአዳማ ናዝሬት ያለውን ሁኔታ መመልከቱ ብቻ ይበቃል። በአዳማ ናዝረት አብዛኛው ነዋሪ ወደ 75% አማርኛ ተናጋሪ ነው። ሆኖም በአዳማ የከንቲባው ጽ/ቤት ሆነ በቀበሌዎች የሥራ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ ብቻ ነው። የፖሊስ ጣቢያዎች የቀበሌ ሰራተኞች፣ አማርኛ እየተናገሩ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ስለደነገገ ብቻ፣ እያስተረጎሙ ነው በቁቤ ደብዳቤ የሚለዋወጡት። ይሄ አይነቱ አሰራር ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። የአዲስ አበባ፣ የአዳማ፣ የቢሾፎቱ በአዲስ አበባና አካባቢው የሚኖሪው፣ ኦሮምኛ የማይናገረው በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ማኅበረሰብ፣ ጦማሪ መርጋ ኢብሳ እንዳሉት “ኦሮምኛን ለምደው፣ የክልሉን ሕግ አክብረው” ካልኖሩ ወይንም ወደ “መጡበት” ወደሚላቸው ቦታዎች አዲስ አበባን እና ሸዋን ለቀው መሄድ እለባቸው የሚል አመለካከት ነው ያለው።

በዚህ መልኩ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ዙሪያ መካከል ያለው ችግር ሊፈታ አይችልም። ይሄ ደግሞ በምንም መልኩ ተቀባይነት አይኖረውም። ወደ ለየለለት መተላለቅ የሚወስድ ነው።
ብቸኛው አማራጭ፣ የሚያዋጣው አማራጭ፣ ኦሮሞውን ሆነ ሌላው ሁሉ እኩል የሆኑበት፣ ለአስተዳደር በሚያመች መልኩ አካባቢውን እንደገና ማዋቀር ነው። በተለይም አዲስ አበባና አካባቢዋ የሚኖረው አብዛኛው የሸዋ ህዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደር መቻል አለበት። ለዚህም ነው አዲስ አበባን ያቀፈ ሸዋ የሚባል ክልል ቢኖር ጥሩ ነው የሚል ሐሳብ የማቀርበው።
አዲስ አበባ፣ የምስራቅ ሸዋ ዞን ሰሜኑ አካባቢ፣ እንዳለ የሰሜን እና የመራብ ደቡብ ሸዋ ዞኖች፣ ከሆለታ በስተምስራቅ ያለው የምእራብ ሸዋ ዞን፣ በአማራው ክልል ያሉትን የሰሜን ሸዋ ዞንና ከሚሴን ዞኖች እንዳሉ ያጠቃለለ፣ አንድ እራሱን የቻለ ሸዋ የሚባል ክልል ቢኖር ጥሩ ነው። ከዚህም ጋር በተያያዘ፤

1. የሸዋ የክልሉ የሥራ ቋንቋ አማርኛና አፋን ኦሮሞ ቢደረግ
2. አማርኛና አፋን ኦሮሞ በሁሉም ት/ቤቶች ከእንግሊዘኛ ጋር እንደ subject ቢሰጥ (ይሄ ማለት የአዲስ አበባ ህዝብ ሳይቀር አፋን ኦሮሞን የመማርና የማወቅ እድል ይኖረዋል። የበለጠ አዋጭ ይሆናል። ኦሮሞዎችም ሆነ ሌሎች የሚያጡት የሚጎድልባቸው ነገር አይኖርም። የሁሉም መብት ይከበራል። ሁሉም እኩል ይታያሉ። ሁሉም በፍቅር፣ ኦሮሞ፣ አማራ ሳይባባል ተከባብሮ፣ ተዋዶ ይኖራል።

ይሄን ሐሳብ ሳቀርብም፣ አንደኛ በአዲስ አበባ አካባቢዋ የሚኖረው ማኅበረሰብ፣ የራሱ የሆነ ባህሪ ስላለው ነው። በመሆኑም ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል። ሁለተኛ ለአስተዳደር የሚያመች ነው። አንድ ክልል በጣም ትልቅ ሲሆን ለአስተዳደር በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ሦስተኛ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል ያለው ውዝግብ ዘለቄታዊ መፍትሄ ያገኛል።

አፋን ኦሮሞ ብማር፣ ባውቅ ደስታዬ ነው። እንኳን የአገሬ ህዝብ የሚናገረውን ቀርቶ የሌሎች አገሮችን ቋንቋ ለመናገር እንማር የለም እንዴ? ቋንቋ ኃይል ነው። ቋንቋ የመግባቢያ መሳሪያ ነው። የአዲስ አበባ ተወላጅ እንደመሆኔ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖረው ገበሬ የሚናገረውን አለማወቄ ያሳዝነኛል። የአዲስ አበባ ልጆች አፋን ኦሮሞ እንድንማር መደረግ ነበረበት።

ሆኖም ግን በግድ የሚሆን ነገር የለም። በተለይም ኦሮምኛ የማትናገሩና የማትለምዱ ከሆነ ሸዋን ለቃችሁ ውጡ የሚለውን አነጋገር እንደ አዲስ አበባ ተወላጅ ልታገሰው የምችለው አነጋገር አይደለም። በተለይም ደግሞ የአዲስ አበባና የሽዋ ተወላጅ ያልሆኑ፣ የአዲስ አበባን የሸዋን ታሪካና ስነ-ልቦና የማይረዱ፣ በአዲስ አበባም ሆነ በሸዋ ጉዳይ ላይ ለመወሰን ሲሞክሩ ማየት ተቀባይነት አይኖረውም። ለዚህ ነው ያመንክኩበትን የምጽፈውና የምጦምረው። እዚህ ጽሁፍ ላይ ካቀረብኩ የተለየ፣ የተሻለ ሐሳብ ከቀረበ ለመማር ዝግጁ ነኝ። መመካከር፣ መከራከር እንችላለን። ግን በሰለጠነ መልኩ እናድርገው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!