ይገረም አለሙ

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ

22 ፓርቲዎች የፕሮፌሰሩን ፓርቲ ጨምሮ ከወያኔ ጋር በወያኔ ጋባዥነት ድርድር ጀምረዋል የሚለውን ዜና እየሰማን ባለንበት፤ መድረክ ከኢህአዴግ ጋር የብቻ ድርድር ይፈልጋል፣ ምክንያቱም ዋንኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ስለሆነ የሚል ነገር በፕ/ር በየነ አንደበት ሲነገር ሰማን። የፖለቲካ ፓርቲ እንመራለን የሚሉት ርስ በርስ ስለሚተዋወቁ እናንተ 22ትም ሆናችሁ 102 አትረቡም ጠንካራው እኔ የምመራው መድረክ ነው ማለታቸው ተቀባይነት ባይኖረውም አያስገርምም። ሕዝቡ መድረክን ርስተ ጉልት ስላደረጉት እርሳቸውም ሆነ ስለ መድረክ ምንም እንደማያውቅ ቆጥረው ይህን ማለታቸው ግን የድፍረታቸውን ልክ የንቀታቸውን መጠን ነው የሚያሳየው። በወያኔ መሪዎችም በተቀዋሚ ተብየዎችም አክብሮት የተነፈገው ሕዝብ።

የፕ/ር በየነን ንግግር እንደሰማሁ እኔ ከማውቀው በላይ ፈጥኖ በአእምሮየ የታወሰኝ አቶ አሰፋ ጫቦ በአንድ ጽሁፋቸው የገለጹዋቸው ነው። እንዲህ ይላሉ አቶ አሰፋ ፕ/ር በየነን ሲገልጹዋቸው። “በየነ ጴጥሮስ እላይ በጨረፍታ ለማሳየት ለሞከርኩት ሥራው መላውን ዓለም ደጋግሞ ዞሯልኮ! በዚህ 25 ዓመት ሙሉ የድርጅቶች መሪነቱ ምን ፈየደ? ምንስ ተናገረ? ምንስ ጻፈ? የሚል ቢኖር ጉዱ ይፈላ ነበር። የሚል ሰው አለመኖሩ የበጀው መሰለኝ። እንዳይኖሩ አድርጎ ይሆን? አሁን ግርማን ላከበት? አንዳንዴ ያኔ ከባንክ ገንዘብ ይዞ ጠፍቶ በኋላ የወያኔ አባል ሁኖ የገንዘብም ምክትል ሚንስትር እንደሆነው ሰውዬ በየነ ጴጥሮስም የወያኔ አባል ይሆን? እላለሁ ይኸው ለ25 ዓመት ያ ሁሉ ሰው ወህኒ ሲወርድ በየነ ዓለምን ይዞራል” ነበር ያሉት። አዎ! ለምን እንዴት ወዘተ ብሎ የሚጠይቅ ጠፋና እኝህ ሰው ከማንም የበለጥሁ ከሁሉም የታመንሁ ዋንኛው ተቀዋሚ እኔ ነኝ ለማለት በቁ። ወይ ድፍረት ወይ ንቀት።

ርሳቸውን ለዚህ ካበቃቸው ነገር አንዱ መድረክን ክፍት አድርገው ሳያዩ፤ ዋንኛው ተቀዋሚ እያሉ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ሥራ ነው። ቢታይ ግን መድረክ ቢከፍቱ ተልባ ነው። ይህም ብቻ አይደለም ያው ተልባውም በየነና በየነ ብቻ ነው ለማለት የሚያስችል ማስረጃ ማቅረብ ስለምችል በድፍረት እናገራለሁ።

በየነ በሁለት ካርድ

ፕ/ር በየነ በ1993 ዓ.ም. ሀ ብለው ፖለቲካውን ከጀመሩ ግዜ አንስቶ በሁለትና በሦስት ካርድ ነው ሲጫወቱ የኖሩት፣ አሁንም የሚጫወቱት። በአንድ ግዜ የብሔርም አገራዊም ፓርቲ ሊቀመንበብር ሲሆኑ አይተን ርሳቸውን ብቻ ሳይሆን በዚህ ሁኔታ ምስክር ወረቀት የሰጣቸውን ምርጫ ቦርድንም ታዝበናል። የኋላውን ልተወውና አሁን እያደረጉ ያለውን እንይ፤ ለድርድር የተዘጋጁት 22 ፓርቲዎች ናቸው ሲባል እነማን ናቸው ብዬ ፍለጋ ገባሁ። ከአገኘሁት ዝርዝር ውስጥ አንድ ቀድሞ ሰምቼው የማላውቅ ፓርቲ ስም አገኘሁና ስጠይቅ፣ ሳጠያይቅ፣ የፕ/ር በየነ መሆኑን ሰማሁ። (የሚመሩት ያላልኩበትን ምክንያት ተረድታችሁልኝ ይሆን!) በአንድ ወገን ፓርቲያቸው ከሌሎች ጋር በመሆን ለድርደር በሉት ለውይይት ተቀምጠዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በመድረክ ስም ተናጠል ድርድር ይጠይቃሉ። ምን አልባት ይህ አንዱ የዋና ተቀዋሚነታቸው መግለጫና ማረጋገጫ ይሆን?!

መድረክ ቢከፍቱ ተልባ

በስምንት ፓርቲዎችና በሁለት ታዋቂ ግለሰቦች የተመሰረተ ተብሎ ዋንኛው ተቀዋሚ ፓርቲ እየተባለ ሲሞካሽ ውስጡን የምናውቀው ሰዎች መድረክ በጠንካራ መሰረት ላይ ያልቆመ ምንም የማይፈይድ የት ሊደርስም የማይችል እንደሆነ ጽፌአለሁ። በዚህም ስድብ፣ ፍረጃ፣ ውንጀላ አስተናግጃለሁ። ዋንኛው ተቀዋሚ እያሉ የሚያሞግስቱም ሆኑ ዜና የሚሠሩት ወገኖች ግን ጠለቅ ብለው ለማወቅ ቀርቶ ትንሽ ገለጥ አድርገው ለማየት ፍላጎቱም የላቸውምና መድረክም እንደ ወያኔ በቁጥር ጨዋታ ቢከፍቱ ተልባነቱን ደብቆ ይኖራል።

መቼም መድረክ ጠንካራ ነው ከተባለ፤ ራሱ ፓርቲ አይደለምና በአባሎቹ ማንነትና ምንነት ነው የሚሆነው። ይህ እንዳይታወቅ አንድም አባል ፓርቲዎቹ በሙሉ አይገለጹም፣ ሁለትም በየግዜው የስም ለውጥ ይደረጋል። መድረክ ሲመሰረት ስማቸው የሰፈረውን ፓርቲዎች ይዛችሁ እነዛው በየግዜው ያደረጉትን ውህደት የስም ለውጥ ብትመለከቱ መድረክ ማነው የሚለው ይጠፋባችኋል። ይህ መለዋወጥ እንዳለ ሆኖ ከመስራቾቹ ወጣ የተባለ አልሰማንምና እዛ ላይ ተመልሰን ፓርዎቹን እንይና የመድረክን ጥንካሬ ወይ ድክመት እንመስክር።

ከመነሻው በስምንት ፓርቲዎችና ሁለት ታዋቂ ግለሰቦች የሚለው አገላለጽ ተገቢም ትክክልም አልነበረም፤ የቱንም ያህል ቢገዝፍ ግለሰብ ግለሰብ ነው። ወይ ሰዎቹ ዝና ካልፈለጉ ወይ ሌሎቹ በእነርሱ ስም የሆነ ነገር እናተርፋለን ብለው ካላሰቡ በስተቀር የሰዎቹ መጠራት አስፈላጊ አልነበረም፣ ሆኖም አልቀጠለምና አነጋጋሪነቱ አብቅቷል።

ሁለተኛው ስህተት ሕብረትና ግንባር አይደለም የተናጠል ፓርቲያቸውን መርተው አንድ ርምጃ ማስኬድ ያልቻሉ ሰው (ራሳቸውን ለምክትል ሚኒስትርነትና ለፓርላማ ወንበር ማብቃታቸው ርምጃ ነው ካልተባለ) ሊቀመንበር ማድረጉ ነው። ይህን መሰረት አድርጎ እስካሁን የዘለቀው ነገር ደግሞ መድረክ ከፕ/ር በየነ ይዞታ መላቀቅ አለመቻሉ ነው። እነርሱም እንደ ወያኔ ተጨፈኑ እናሞኛችሁ እያሉን ሊቀመንበርነት በዙር ነው ይሉናል እንጂ፤ ፕ/ር በየነ የመድረክ ፑቲን ሆነው ነው የምናያቸው።

የመድረክ አባል ፓርቲዎች፣

  1. አረና - ስለዚህ ፓርቲ በቂ መረጃ የለኝም፣ ቢሆንም ግን መድረክን ከበየነ ርስተ ጉልትነት ለማላቀቅ ባይችልም ከቁጥር መግለጫነት የዘለለ ፓርቲ እንደሆነ አስባለሁ።
  2. ኦፌኮ - የመድረክን መስራቾች ቁጥር ሰምንት አድርሰውት የነበሩት በአንድ ብሔር ስም የሚጠሩት የአቶ ቡልቻና የዶ/ር መረራ ፓርቲዎች ተዋህደው የፈጠሩት ነው ኦፌኮ። ፓርቲው በኦሮምያ አካባቢ ሰፊ መሰረትም ተቀባይነትም እንዳለው ቢታወቅም መድረክ ውስጥ ያለው በአቅሙ መጠን አይደለም። ሌላ ሌላው ቢቀር በኦሮምያ ከአንድ ዓመት በላይ ዜጎች ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ ኦፌኮ ያላባራ ጩኸት ሲያሰማ ከመድረክ በኩል የሰማነው ዋንኛ ተቀዋሚ ሊያሰኘው ቀርቶ የኦፌኮን አባልነት የሚመጥን አይደለም። በርካታ የኦፌኮ አመራሮች ሲታሰሩም የመድረክ ድምጽ ለስላሳ ነው። የም/ል ሊቀመንበሩን የዶ/ር መረራ እስር ደግሞ መድረክ አይደለም ዋንኛ ተቀዋሚ ተቀዋሚም እንዳልሆነ ያሳየ ነው። መሪው ታስሮ ዝም የሚል እንደምን ፓርቲ ሊባል ይበቃል። በአንጻሩ ደቡብ ውስጥ በተለይ ደግሞ ሀድያ አካባቢ አንድ ነገር ሆነ ከተባለ የመድረክ ጩኸት ነው ቀድሞም ገኖም የሚሰማው።
  3. የበየነ ፓርቲዎች - ከሀብዴድ እስከ ኢማዴ-ዴህአፓ ድረስ ፕ/ር በየነ የተጠሩባቸው ወይንም ይጠሩባቸው ፓርቲዎች ሕብረቶች ግንባሮች ወዘተ ግራ ስለሚያጋቡኝ ነው ጠቅለል አድርጌ የበየነ ፓርቲዎች ማለቴ ነው። መድረክ ውስጥ እንኳን ደቡብ ሕብረት፤ ኢዴኃህ፣ ሶሻል ዴሞክራሲ፣ ማኅበረ ዴሞክራሲ ደቡብ ሕብረት፣ … የሚባሉ በርሳቸው የሚመሩ ፓርቲዎች ነበሩ ወይንም አሉ። መድረክ ሲመሰረት ኢዴኃህና ደቡብ ሕብረት ነበሩ። ከትንሽ ግዜ በኋላ ደግሞ ደቡብ ሕብረትና ሶሻል ዴሞክራሲ ሆኑ፤ አሁን ያሉት ስንትና እነማን እንደሆኑ ባላውቅም (የምርጫ ቦርድ ድረ ገጽም አዲስ መረጃ አይሰጥም) አዲስ ፓርቲ መስረተው ይሁን ወይ አዋህደው ወይንም የአንዱን ስም ለውጠው ባይታወቅም የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ዴሞክራቲክ - ደቡብ ሕብረት አንድነት ፓርቲ በምህጻሩ ኢማዴ-ዴህአፓ የሚባል ፓርቲ አላቸው። በዚህ ፓርቲ አማካኝነትም ነው ከ22ቱ አንዱ ሆነው ለድርድር የቀረቡት።
  4. ኢዴአን - ይሄ ስሙም መሪዎቹም የማይታወቅ መድረክ ይህን ያህል ፓርቲዎች ስብስብ እያሉ የሚዘግቡ ጋዜጠኞችም ሆኑ የሚያወድሱ አባል ደጋፊዎች ለማወቅ ጥረት ያላደረጉበት ከስም ማጀቢያነትና ከቁጥር ማብዣነት ያለፈ ታይቶ የማያውቅ አሁንም በመድረክ የአባላት ዝርዝር ውስጥ ይኑር አይኑር የማይታወቅ ነው።
  5. ሶዲኃቅ - ስሙ እንደሚነግረን ቅንጅት ነው፤ ግን እንኳን የተቀናጁት ፓርቲዎቸ ራሱ ቅንጅት ተብየው ከነመሪዎቹ አይታወቅም። ለቁጥር ማድመቂያነት ግን ውሏል። አሁን በስም እንኳን መኖር አለመኖሩ አይታወቅም።

ይሄ ነው እንግዲህ ዋንኛው ተቀዋሚ ፓርቲ ተብሎ የሚነገርለት፣ ፕ/ር በየነንም ለድፍረትና ንቀት ንግግር ያበቃ፤ አጀኢብ ነው። በምርጫ 2007 ከ200 የበለጠ እጩ ማቅረብ ያልቻለ መሆኑንም አክሉበት።

በመጨረሻ የፕ/ር በየነ መድረክ በኢምፔሪያል ሆቴል ባዘጋጀው ሲፖዚየም ላይ ባቀረቡት የጥናት ወረቀት፤ የአንድና ሁለት ሰው ፓርቲዎች ፓርቲ እየተባሉ የሕብረት አባል እንዲሆኑ መደረጉ ላለፉት ሕብረቶች መዳከም ዋና ምክንያት ነው ብለው ነበር። ከላይ ያየናቸው የመድረክ አባሎች ስንቶቹ ከዚህ ነጻ ናቸው፣ የፕ/ር በየነን ፓርቲዎች ጨምሮ?

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!