ከ"ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ዕውቀት መለዋወጫ መረብ" የተሰጠ አስተያየት

አድዋ | Adwa.
የአድዋ ጀግኖቻችን

የትግሬ ነፍጠኛ፣ የሸዋ ፈረሰኛ፣ የጎጃም እግረኛ፣ የአማራ ስልተኛ ከቦ ይቀላው፣ ያናፋው፣ ያንደገድገው ጀመር። ከእንዝርት የቀለለ የጁየ፣ ከነብር የፈጠነ ቤጌምድር፣ ከቋንጣ የደረቀ ትግሬ፣ ከአሞራ የረበበ ሸዌ፣ ከንብ የባሰ ጎጃሜ እያባረረ በየጎዳናው ዘለሰው። አውሬ የነጨው ነጭ መንጋ እየመሰለ በየዱር ሆዱን ገልብጦ ወደቀና የአሞራ ቀለብ ሆነ።[1]
መጋቢት ፲፭ ቀን ፪ ሺህ ፱ ዓ. ም.

በወለላዬና በዶክተር ተድላ ሃሳብ ላይ ተጨማሪ፣

በቅድሚያ ክብር በደምና በአጥንታቸው አንድነት አገር ላቆዩልን ለአድዋ ጀግኖች በሙሉ፣ ወለላዬ በስዊድን የመቶ ሃያ አንደኛው ዓመት የአድዋን ድል መዘክርና በዝግጅቱ ላይ የነበሩትን ክስተቶች ስላሳወቁን ብቻ ሳይሆን ምላሽ በመስጠትዎና ለሚመለከተውም ጥሪ በማድረግዎ ምስጋናችን የላቀ ነው። በእኛም በኩል የመቶ ሃያ አንደኛው ዓመት የአድዋን ድል በመጣጥፎች ለመዘከር ዝግጅት በምናደረግበት ጊዜ አንዳንዶቻችን የእቴጌ ጣይቱን ታላቅ አስተዋጽዖ ለብቻው ማዘጋጀት ጀምረን፣ ነጥለን የምናወጣው ታሪክ ጎደሎ ሆኖ ስላገኘነው አድዋን ከመላው ጀግኖቹ ጋር መተረኩ የተሟላ ሆኖ አግኝተነዋል። (የወለላዬን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!) | (የተድላ ደ. ተክሌን (ዶ/ር) ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

ይህ ጽሑፍም በስዊድን የመቶ ሃያ አንደኛው ዓመት የአድዋን ድል ለመዘከር እ.ኤ.አ. ማርች አምስት (፭) ቀን (፪) ሁለት ሺህ አሥራ ሰባት (፲፯) ዓ.ም. በነበረው ዝግጅት ላይ ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ ያደረጉት ንግግር፤ ስንትና ስንት ሕይወት የተከፈለበትን የአድዋን ድል ”በዕድል ነው የተገኘ ነው” ማለታቸው ከአንድ አፍሪካዊ የሚጠበቅ ነው? ለምንስ ንግግራቸው ከቀድሞው የደቡብ አፍሪካ መሪ ከሚስተር ታቦ ምቤኪና ከፕሮፌሰር ዮናስ ሬይሞንድ ተቃራኒ ሆነ? ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬንና ታቦ ምቤኪን በማገናኘት የሰጡት የግል አስተያየትስ የጓደኛቸው የፕሮፌሰር ማሞን ጥልቅ የምርምር ጽሁፎችና አፍሪካዊ ሥራዎች ያንጸባረቀ ትክክለኛ መረጃ ነው? መረጃቸውና ንግግራቸውስ አነጋጋሪ ሆኖ "ሦስቱንም አጣጣሉ" ተብለውስ ለምን ስማቸው እንዲነሳ አደረገ? የምኒልክን ባህርይ የሚጻረር በመናገራቸውም 'እምዬ ምኒልክ ወላዋይ ነበሩ ወይ?'[2] ብለው ወለላዬ የተባሉ ጸሐፊ እንዲጠይቁ ስላነሳሳቸው ይህን ጥያቄ የታሪክ ባለሙያዎች በአግባቡ እንደሚመልሱት በመተማመን በዚህ ጽሑፍ ለጊዜው ከታላቁ የአፍሪካውያን ድል አንጻር ለመዳሰስ እንሞክራለን።

በቅድሚያ እቴጌ ጣይቱንና ታሪካዊ ድርሻቸውን ካለዳግማዊ ምኒልክ ታሪክና ስብዕና ማግዘፍ ይቻላል? በታሪክስ አይደለም በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ዛሬ በሠለጠነው ዓለም የትኛው ወንድ፣ የአገር መሪ፣ ወይም ባለሥልጣን ነው የትዳር አጋሩን፣ ሴትን ጦር ሜዳ ድረስ ይዞ የሚሄድ? አይደለም ትናንት ዛሬስ የትኛው ወንድ ነው ከውጭ አገር ሰዎች ጋር በሚደረግ ወሳኝ የአገር ጉዳይ ስብሰባ ላይ ሚስቱ እንድትገባና በውይይቱም የሴት ሃሳብ እንዲሰማ የሚፈቅድ? ዳግማዊ ምኒልክ ግን ጥንት በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ሴትን በሴትነቷ አክብረው፣ ጦር ሜዳ ላይ ሴት ልጅ ምን መሥራት እንደምትችል ለዓለም ያስመሰከሩ፣ አድዋ ላይ ሴትንና አገራቸው ኢትዮጵያን ክብር ያጎናጸፉ ፈር ቀዳጅ አፍሪካዊ መሪ ነበሩ።

በእርግጥ በዓለም ላይ በሥልጣኔ ያደገና የዘመነ ምዕራባዊ አገር፣ በሥልጣኔዋ ዝቅተኛነት በናቋት፣ በአንዲት አፍሪካዊት አገር መሸነፍን መቀበል ቀላል አይደለምም። አይጠበቅምም። በተለይም በሺህ ስምንት መቶ ሰባ ሰባት (፲፰፻፸፯) ዓ.ም. ጀርመን፣ በርሊን[3] ላይ ኃያላኑ የአውሮጳ አገራት አፍሪካን ለመቀራመት ያቀዱትን ዕቅድ ደጋግመው እንዲያጤኑት ያደረገውን፣ ዓለምን ያስደመመውን፣ ምዕራባውያን ሳይወዱ በግዳቸውም ቢሆን የሚቀበሉትን ታላቁ የአፍሪካውያንን ድል (የአድዋን ድል) መቀበል ለምዕራባውያን እጅግ በጣም ከባድ ነው። ይልቁንስ ምላሹ በጊዜው የኢትዮጵያ መሪ የነበሩትን ዳግማዊ ምኒልክን ስማቸውንና ሥራቸውን ማጉደፍ ብቻ ሳይሆን በድሉ ባለቤት፣ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የተወሰደው የበቀል እርምጃ ዛሬም መቆሙ አጠያያቂ ነው። በተቃራነው ግን አፍሪካውያንን ለነጻነታቸው ያነቃቃው ታላቁ የአድዋ ድል በዓለም ላይ ላሉ ለነጻነት ናፋቂዎች በሙሉ የነጻነት አርማ ነው። በመሆኑም ከአድዋ ድል በኋላ ጣሊያንና የቅኝ ግዛት ህልማቸው የተጨናገፈባቸው ምዕራባውያን ኢትዮጵያንና መሪዋን የተበቀሉበትና የሚበቀሉበት መንገድ፣ ከአርባ ዓመታት በኋላ ጣሊያን በድጋሚ ኢትዮጵያን በመውረር የተከለከለ የመርዝ ጭስ በመጠቀም ከሰላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ቀን እስከ መፍጀት ያደረሳቸው የበቀል እርምጃ ለአፍሪካዊያን በሙሉ ግልጽ በመሆኑ፤ ለፕሮፌሰር ተከስተም አይጠፋቸውምና ኢትዮጵያ ያሸነፈችው በዕድል ነው መረጃውም ያለው በተሸናፊው፣ በወራሪው፣ በጣሊያን እጅ ነው ማለት የፕሮፌሰር ተከስተን የቀድሞ ሥራዎች ለተከታተለ ሰው እውን ይህ አባባል የእርሳቸውን የምርምር ሥራ ይመጥናልን ያሰኛል።

በተለይ ከምንም በላይ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ዕውቀት መለዋወጫ መረብ፣ በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃሉ (Ee-JRIF: (V. 9, No. 1) Ethiopian electronics Journal for Research and Innovation Foresight) በዘጠነኛው እትም፣ ቁጥር አንድ፣ ልዩ እትሙ፣ የመቶ ሃያ አንደኛው ዓመት የአድዋን የድል በዓልን ለመዘከር የካቲት ሃያ ሦስት (፳፫) ቀን ሁለት (፪) ሺህ ዘጠኝ (፱) ዓ.ም. (March 2nd, 2017) በታተመው ልዩ እትሙ፣ ከጦርነቱ በፊትና በኋላ ምዕራባውያን ጋዜጦች[4] ምን እያሉ ስለአድዋ ጦርነት ይጽፉ እንደነበር፣ በመረጃ ተደግፎ የተዘረዘረው፣ በዶክተር ተድላ ተክሌ የቀረበው ሰፊ የምርምር ጽሁፍና ሌሎችም ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ መጣጥፎች በድረ ገጹ ላይ ከወጡ በኋላ በመሆኑ የፕሮፌሰር ተከስተን ንግግር ምሁራዊ ትንታኔ አጠያያቂ ያደርገዋልና የወለላዬን ብዕር አይንጠፍ እያልን 'እምዬ ምኒልክ ወላዋይ ነበሩ ወይ?' የሚለው ጥያቄን ለመመለስ ብዙ የአገር ውስጥና የውጭ ጸሐፊዎች የጻፉትን ለጊዜው ብናቆየው ጥንት በዚያ ዘመን ምኒልክ የወሰኑዋቸውን ውሳኔዎች፣ በጊዜው ከወሰዱዋቸው እርምጃዎቻቸው ጋር በማነጻጸር የንጉሡን ወላዋይ መሆን አለመሆን እስቲ እንፈትሽ።

ዳግማዊ ምኒልክ ለአድዋ ጦርነት ለመዘጋጀት ሲያስቡ ለአምስት ዓመታት ያህል ታላቅ ረሀብ በኢትዮጵያ በመከሰቱ ከባድ የረሀብ ዘመን ነበርና፤ በረሀቡ ምክንያት የሚሞተው ቀባሪ ያጣበት፣ የጋማ ከብት ስጋ የተበላበት፣ ሠራዊቱ የተመናመነበት፣ በባህላዊና ጊዜው ባለፈበት የጦር መሳሪያ በመጠቀም ጣሊያንን ለመከላከል አቅም የመነመነበት እና መኳንንቱም ተከፋፍለው በነበረበት ሰዓት በመሆኑ፤ ለጣሊያን ቅኝ ግዛትን ለማስፋፋት የተመቸ ጊዜ ነበርና፤ ይህንን ሁሉ ለማስተካከል ንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ ስላስፈለጋቸው የመጀመሪያዎቹን የንግሥና ዓመታት ምኒልክ ጥሩ ግኑኝነት ለመፍጠርና ኃይል ለማጠናከር በመጠቀም በሦስትና አራት የንግሥና ዓመታት ውስጥ፣

  • ከጣሊያን ጋር የነበረውን ግንኙነት ያለሳልሱ ጀመር።
  • መኳንንቱም ተደልለው ስለነበር በዘዴ በመያዝ አዲስ አበባ ጋብዘው በፍቅርና በደስታ ተቀብለው ታማኝነታቸውን አረጋገጡላቸውና መኳንንቶች ሁሉ ከምኒልክ ጎን ቆሙ።
  • የውስጥ ችግሮቻቸውን እያቃለሉ አታለዋቸው የነበሩትን ጣሊያኖችም እያታለሉ በዚህ ሁሉ መሀል መሳሪያ ማደራጀታቸውን ቀጠሉ።
  • ከሦስትና ከአራት የንግሥና ዓመታት በኋላ ያልተከፋፈለና የተነቃቃ ሕዝብ፣ በመሳሪያ የተደራጀ፣ ለመሪው ለምኒልክ ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ ሠራዊት፣ ጠንካራ ክንድ ያለው ብርቱ መሪ ለመሆን በቁ።

ደካማና ወላዋይ መሪ ይህንን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል ወይስ አርቆ ሀሳቢና ብልህ መሪ?

• ከአድዋው ጦርነት በፊት ለምኒልክ የውጫሌው ውል አለመስተካከል ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም የአውሮጳ መንግሥታት የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ዓላማ በድምጽ ብልጫ በማጽደቃቸው አዝነው ስለነበር፤ በኢትዮጵያ የሚኖሩትን ጣሊያኖች በሙሉ "ከአገሬ ይውጡልኝ፣ ወደፊትም አይምጡብኝ" ብለው ዶ/ር ትራቬርሲ በተባሉት ለጣሊያን መንግሥት ደብዳቤ ሲልኩ፤ የጣሊያን መንግሥት ግን ምኒልክን ለመደለል ሁለት ሚሊዮን የጥይት ስጦታ ቢልክላቸው፤ ምኒልክ ግን "እናንተ ጠብ ፈለጋችሁኝ እንጂ እኔ ወዳጅነታችንን ነው የምፈልገው" በማለት ስጦታውን ተቀብለው ጣሊያኖችን በሙሉ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ያደረጉ፣ በስጦታው ያልተደለሉ[5] እና በአገራቸው ሉዓላዊነት የማይደራደሩ መሆናቸው ነው እውነቱ ወይስ ወላዋይነታቸው?

• አድዋ ላይ የጦሩ አዛዥ ባራቲዬሪ የያዘው ምሽግ ባንድ በኩል የኢትዮጵያ ሠራዊትን በግላጭ ለማጥቃት ስለሚመቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዘማቹ ከቤቱ ከወጣ ከሰባት ወራት በላይ በማለፉ የሠራዊቱ ስንቅ፣ የከብቱም ቀለብ እያለቀ በመሆኑ ምኒልክ ከበው ለመቀመጥ ከሰባ ሺህ በላይ የሚጠጋው ሠራዊታቸውን የሚቀልብ ስንቅ ስለሌላቸው ሠራዊታቸውን ላለማስጨረስ ጦርነቱ ቶሎ እንዲካሄድ ፈልገው፣ ባራቲዬሪ በሰላዮቹ የኢትዮጵያውያንን እንቅስቃሴ ለማወቅ ሲሞክር የውስጥ አርበኞች የኢትዮጵያን ጦር አሳንሰው በመንገር፣ መኳንንቶቹም እንደታመሙ በማስመሰል፣ ስንቅ እንዳለቀና ንጉሡም ወደኋላ ለመመለስ አስበዋል መባሉን ባራቲዬሪ እንዲሰማ በማድረግ፣ (ፕሮፌሰር ተከስተ የጠቀሱት መረጃ ይህ ያታለሉበትን ነው?) የውስጥ አርበኞች እነባራቲዬሪ ከምሽጋቸው ወጥተው እንዲዋጉ አነሳስተው ጣሊያኖችን አታለዋቸዋል። ምኒልክም በውስጥ አርበኞቻቸው በኩል የባራቲዬሪ እቅድ በምስጢር ስለሚደርሳቸው፣ ባራቲዬሪ ለውጊያ ሲወስን የጠላትን ዝግጅት አስቀድመው ማወቅ ስለቻሉ ለመዘጋጀትም ጠቀማቸው። ጦርነቱም በፈለጉት መንገድ እንዲመራ ክፍተታቸውንም ለማስተካከል ጠቅሟቸው፣ አቋማቸውን ደብቀው በሙሉ ልብ ጦርነቱን እንዲመሩ አስችሏቸዋል። ሠራዊታቸውን ላለማስጨረስ ጦርነቱ ቶሎ እንዲጀመርና በፈለጉበት መንገድ እንዲሄድ ማድረግ የአስተዋይ፣ የብልህ እና አርቆ አሳቢ መሪ ችሎታ ነው ወይስ የደካማና የወላዋይ?

• በአድዋው ጦርነት አራት ሺህ ያህል የጣሊያን ምርኮኞች[6] በተማረኩበት ጊዜ ምኒልክ በአዋጅ ምርኮኞችን ሰው እንዲቀልብ በየመኳንንቱ ቤት ምርኮኞችን የሰጡ፣ ለምርኮኞችም ለመንገዳቸው ምግብና መድኃኒት፣ የቆሰሉትም ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙበት በቅሎ እንዲሰጣቸው፣ አዲስ አበባ ሲደርሱ ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩ በማድረጋቸው ምኒልክ የተናቀው የኢትዮጵያ መንግሥት የሠለጠነ መሆኑን ነው ያስመሰከሩት ወይስ ያልሠለጠነ ደካማና ኋላ ቀር መሆኑን?

• ከጦርነቱ በኋላ ብዙ ሺህ የጣሊያን ምርኮኞችን ለማስለቀቅ የጣሊያን የመጀመሪያው ሙከራ ምኒልክን እንታረቅ በማለት በማታለል ምርኮኞች ከተለቀቁ በኋላ ኢትዮጵያን በአዲስ መልክ ሊዋጋ ማሰቡን ምኒልክ በመጠርጠራቸው "አዲስ ውል ተዋውለን የውጫሌ ውል መፍረሱን ለዓለም ነገሥታት ሁሉ ካላሳወቃችሁ ምርኮኞችን አልለቅም"[7] በማለታቸው ጣሊያን ምርኮኞችን አስለቅቆ ውጊያ የመግጠም እቅዱ ስላልተሳካለት ጳጳሱ ሊዎን አሥራ ሦስተኛ ለምኒልክ ምርኮኞችን እንዲለቁ ደብዳቤ ጻፉላቸው። ምኒልክ ግን ጳጳሱን በጣሊያን በኩል ያለውን እንዲያስተካክሉ ጠይቀው ምርኮኞቹን እንደማይለቁ ያሳወቁት ጽኑህ መሪ በመሆናቸው ነው ወይስ ወላዋይነታቸውን የሚያሳየው?

• በመጨረሻም ጣሊያን ምርኮኞቹን ለማስለቀቅ ምኒልክ የጠየቁትን በሙሉ ለመፈጸም ሁኔታዎች ስላስገደዷት የውጫሌውን ውል የሚሰርዝ አዲስ ውልና ለጦርነቱም የሚከፈል ካሳ ተካቶበት ምርኮኞቹ እንዲለቀቁ ቢስማሙም፤ ምኒልክ ግን በአንድ በኩል የአውሮጳ መንግሥታት ማወቃቸውን ለማረጋገጥና የሚሉትንም መስማት ስለፈለጉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጣሊያን መንግሥት ማህተም ያለበት አዲስ የውል ሰነድ እስኪደርሳቸው ድረስ ምርኮኞቹን ከአምስት ወራት በላይ አቆይተው የጠየቁት ሲሟላላቸው ብቻ ምርኮኞቹን የለቀቁ፤ ለነጮች ያልተበገሩት አስተዋይና ብልህ በመሆናቸው ነው ወይስ ደካማና ወላዋይ?

የሸዋ ገዢ ሳሉ፣ ከአድዋው ጦርነት በፊት ምኒልክንና ሥራቸውን የሚገልጹትን ሁኔታዎች ደግሞ ብንመረምር፣

• በአጤ ቴዎድሮስ ስርወ መንግሥት እንግሊዞች አጤ ቴዎድሮስን ለመውጋትና እስረኞቻቸውን ለማስለቀቅ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ባሰቡ ጊዜ፣ ልክ እንደ አጤ ዮሐንስ ምኒልክንም ከጎናቸው እንዲሰለፉ ጠይቀዋቸው ነበር። ምኒልክ ግን የእንግሊዞችንና የአጤ ዮሐንስን ወዳጅነት ስለሚያውቁ፣ አጤ ቴዎድሮስ እንግሊዝን ካሸነፉም እንዳይወጉዋቸው በማሰብ መልስ ሳይሰጡ ቆይተው እንግሊዞች በድጋሚ ሲጠይቁዋቸው "የምትመጡት ኢትዮጵያን አስገብሮ ለመያዝ ከሆነ በነገራቹ አልስማማም"[8] የሚል ጽኑ መልስ በአገራቸው ሉዓላዊነት የማይደራደሩ አርቆ አሳቢ በመሆናቸው ነው ወይስ ደካማና ወላዋይ?

• ከአጤ ቴዎድሮስ ሞት በኋላም እንግሊዞቹ ለትግሬው ገዥ ለደጃዝማች ካሳ ላደረጉት ውለታ የጦር መሳሪያ ሰጥተዋቸው ስለነበር፣ ደጃዝማች ካሳ የጎጃሙን ንጉሥ ተክለ ጊዮርጊስን አሸንፈው በ(፲፰፻፷፬) ዓ.ም. በመላው ኢትዮጵያ ከነገሡ በኋላ የማረኩትና በስጦታ ያገኙትን መሳሪያዎች ተጠቅመው ሸዋን ለማስገበር ጦርነት ሲያውጁ የሸዋው ገዢ ምኒልክ ግን አቅማቸውን በማመዛዘን ለአጤ ዮሐንስ እየገበሩ የራሳቸውን ግዛት በማጠናከር ኃይላቸውን ማደራጀት የቀጠሉት[9] አቅማቸውን ማመዛዘናቸው ወላዋይ በመሆናቸው ነው ወይስ አስተዋይና አርቆ አሳቢ?

• በአጤ ዮሐንስ ስርወ መንግሥት ምኒልክ የጎጃሙ ራስ አዳልን ጦር ለመግጠም ደብረ ታቦር ከገቡ በኋላ፣ ከራስ አዳል የሚበልጥ የጦር ሠራዊት ቢይዙም ዓባይ ዳር ቆላና ደጋ ዳሞትን ራስ አዳልና ሠራዊቶቻቸው ይበልጥ ስለሚያውቁት ለምኒልክ ሠራዊት ግን አመች ባለመሆኑ ነገሩን በማመዛዘን ወደ ሸዋ መመለሳቸው[10] ብልህነት ነው ወይስ ወላዋይነት?

• አጤ ዮሐንስ የምኒልክ ግዛት የነበረውን የከፋን ግዛት ለጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ኃይማኖት አሳልፈው እንደሰጡባቸው እያወቁ በ(፲፰፻፸፫) ዓ.ም. አጤ ዮሐንስ የጎጃሙን ራስ አዳልን ሲሾሙ ለምኒልክ ግብዣ ሲደረግላቸው የንጉሠ ነገሥቱን ጥሪ ተቀብለው መሄዳቸው ታዛዥነታቸውን ለማሳየትና ተባብረው ጉዳት እንዳያደርሱባቸው ጭምር ነው።[11] ይህስ ጥንቃቄያቸው ብልህነት ነው ወላዋይነት?

• በአጤ ዮሐንስ ስርወ መንግሥት የእስልምና ኃይማኖት እንዳይኖርና እምቢ ያለውም በሙሉ በሞት ይቀጣ ነበርና በሺህ ስምንት መቶ ሰባ (፲፰፻፸) ዓ.ም. "በኢትዮጵያ ያለው እስላም ሁሉ በክርስትና እንዲጠመቅ በየአውራጃው ትዕዛዝ ስለአስተላለፉ በዚሁ ዓመት በያለበት ያለው እስላም ሁሉ በጭቃ ሹምና በመልከኛ ወደየአቅራቢያው ቤተክርስቲያን እየተነዳ በግድ እንዲቆርብ ተደረገ።"[12] በተቃራኒው ምኒልክ ግን ሰው በራሱ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር ኃይማኖት መቀየርን ያስቆሙ፣ ሠራዊታቸውም እንደአጤ ዮሐንስ ሠራዊቶች እንዳይዘርፍ በአዋጅ በመከልከል ባላገሩን ከጎናቸው እንዲቆም ያደረጉና ሕዝቡ በአጤ ዮሐንስ የተማረረባቸውን ነገሮች በሙሉ ያስወገዱት አስተዋይና አርቆ አሳቢ መሪ በመሆናቸው ነው ወይስ ደካማና ወላዋይ?

• ልክ እንደ አጤ ዮሐንስ ምኒልክም አጠቃላይ ኢትዮጵያን መግዛት ስለነበረ ሃሳባቸው በአሥራ ስምንት መቶ ሰባ ዓ.ም. በ(፲፰፻፸) አጤ ዮሐንስ የወሎውን ኢማም መሐመድ ዓሊን (በኋላ ሚካኤል የተባሉትን) ክርስትና ሲያነሱ ምኒልክ ደግሞ አባ ዋጠውን (በኋላ ኃይለ ማርያም የተባሉትን) ክርስትና አንስተው የወሎ ገዥ ቢያደርጉዋቸውም በአሥራ ስመንት መቶ ስልሳ ስምንት ዓ.ም. በ(፲፰፻፷፰) አባ ዋጠው በከዷቸው ጊዜ ተዋግተው ድል ካደረጉ በኋላ ወሎን በሙሉ ዮሐንስ ክርስትና ላነሱት ለመሐመድ ዓሊ ሰጥተው፣[13] በሕዝብ ፊት ከመሐመድ ዓሊ ጋር ሲበሉ በመታየት (በጊዜው ከእስላም ጋር መብላት እንደ ኃጢአት ይቆጠር ስለነበር)፤ የወሎ ሕዝብ ምኒልክን ተቀብሎ ገበረላቸው። ለመሐመድ ዓሊም ክርስቲያን የሆነችውን የእንጀራ ልጃቸውን ወይዘሮ ማናለብሽን በማጋባት የኃይማኖት ልዩነት ያልበገራቸው ይህስ የአገር መሪነት ችሎታቸውን ያረጋገጡበት ነው ወይስ ደካማና ወላዋይ መሆናቸውን?

ከአድዋ ድል በኋላ ልክ በዓመቱ በሺህ ስምንት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ በ(፲፰፻፰፱) ዓ.ም. የአፍሪካ የነጻነት ተጋድሎ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ምኒልክ አድዋ ላይ በተቀናጁት አፍሪካዊ ድል በሌሉበት የአፍሪካና የመላው ዓለም የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ የክብር መሪ[14] ብለው የሰየሙዋቸው የጉባኤው መሪዎች ተሳስተው ነው? ድሉስ በዕድል ተገኝቶ ነው የመላው አፍሪካውያንና የዓለም ጥቁሮች ድል የሆነው? ሄይቲስ ምኒልክን አስፈቅዳ የመቶኛ ዓመት የነጻነት በዓልዋን ለምን ኢትዮጵያ ውስጥ አከበረች? በአፍሪካውያን ዘንድ የምኒልክ ስምና አድዋስ ለምን እስከዛሬ ድረስ ታላቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆነው ቀጠሉ? ለዚህ ይሆን ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ሥራዎቻቸው የተገነዘቡትን ስሜት በማንጸባርቅ አምና ለመቶ ሃያኛው የአድዋ ድል መዘከር አድዋን ዓለም አቀፍ[15] የአፍሪካውያን የነጻነት ተጋድሎ ማዕከል እናድርገው የሚል መሪ ሃሳብ ያቀረቡት? በዘንድሮው የአድዋ ድል በዓል (እ.ኤ.አ. ማርች አምስት ቀን ሁለት ሺህ አሥራ ሰባት ዓ.ም.) አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተገኙት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ መሪ ሚስተር ታቦ ምቤኪ[16] ለአድዋ ድል የአመራር ብቃት፣ ጠንካራ ግኑንኙነትና የሕዝብ አንድነት ወሳኝ ድርሻ ነበራቸው ብለው እንደ አንድ አፍሪካዊ መሪ የሰጡት ምስክርነትስ የሚያረጋግጠው የምኒልክን ጠንካራ መሪነት ነው ወይስ ደካማነት? ጣሊያኖች በተቀነባበረ የመረጃ ልውውጥ ተታለው የውስጥ አርበኞች የኢትዮጵያን ጦር አሳንሰው በመንገር፣ መኳንንቶቹም እንደታመሙ በማስመሰል፣ ስንቅ እንዳለቀና ንጉሡም ወደኋላ ለመመለስ አስበዋል መባሉን የጦሩ አዛዥ ባራቲዬሪ እንዲሰማ በማድረግ፣ የውስጥ አርበኞች ጣሊያኖችን አነሳስተው፣ ከምሽጋቸው እንዲወጡና እንዲዋጉ ያደርጉዋቸውን የተታለሉበትን መረጃ ነው ጣሊያኖች አለን የሚሉን መረጃ?

ለማጠቃለል ያህል

'እምዬ ምኒልክ ወላዋይ ነበሩ ወይ?'

የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከላይ የዘረዘርናቸው ግኝቶች የሚያረጋግጡት ዳግማዊ ምኒልክ ከጠበቅነው በላይ ከዘመናቸው ቀድመው የተገኙ ብልህ፣ አስተዋይና አርቆ አሳቢ መሪ፣ በባህርያቸውም የዋህና ርህሩኅ እንደነበሩ ግልጽ ነውና፤ የተቀረውን ፍርድ ለአንባቢዎች እየተውን ጸሐፊና የሥነ ጥበብ ሥራ ባለሙያ የሆኑት ቃልኪዳን ኃይሉ የተባሉት ጸሐፊ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሚተላለፉት የጥበብ ሥራዎች ላይ ከሰሞኑ በዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ ባስነበቡን አስተያየት እናጠቃልላለን።

የኛዎቹ ፊልሞች ደግሞ ያሸነፍነው አድዋን በገዛ ድራማችን በገዛ ቴሌቭዥናችን ሽንፈትን ያከናንቡናል፤ ጠብቀንና አክበረን ያቆየነውን ሥነምግባር በገዛ ፊልምና ድራማዎቻችን አፈር እናስበላዋለን፡፡ የሁለት ሺህ ዓመት የክርስትና ታሪክ ያለን እኛ፤ ከሳውዲ ቀድመን እስልምናን በክብር የተቀበልን እኛ፤ ኃይማኖት የለሽ ሆነን በገዛ ቴሌቪዥናችን ትናንት እንደተፈጠረ ሕዝብ ታሪክ እንደ አዲስ ሲጻፍ ማየት ያመናል፡፡[17] (ቃልኪዳን ኃይሉ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
Ee-JRIF & NES-Global Managing Editors
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ዕውቀት መለዋወጫ መረብ | http://www.nesglobal.org/eejrif4/index.php?journal=admin&page=index

[1] http://www.tut.fi/en/conferment-ceremony/honorary-doctorates/previous-honorary-doctors/index.htm

[1] ጳውሎስ ኞኞ 1984 ዓ.ም.፣ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ፣ የመጀመሪያው እትም፣ ቦሌ ማተሚያ ቤት (ገጽ 208-210)

[2] http://www.ethiomedia.com/1000codes/was-emperor-menelik-wishy-washy.pdf

[3] ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1982 ዓ. ም. ፣ አጤ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት፣ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት (ገጽ 337-338)

[4] http://www.nesglobal.org/eejrif4/index.php?journal=admin&page=issue&op=current

[5] ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ፣ (1927-1928 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግስተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ ወይዘሮ ሰናይት ተክለማርያም በ 1999 ዓ. ም. እንዳሳተሙት፣ ሴንትራል ማተሚያ ቤት (ገጽ 113)

[6] ጳውሎስ ኞኞ 1984 ዓ.ም. ዳግማዊ አጤ ምኒልክ፣ የመጀመሪያው እትም፣ ቦሌ ማተሚያ ቤት፣ (ገጽ 225-226)

[7] ጳውሎስ፣ (ገጽ 222-223)

[8] ጳውሎስ፣ (ገጽ 47)

[9] ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ፣ (1927-1928 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግስተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ ወይዘሮ ሰናይት ተክለማርያም በ 1999 ዓ. ም. እንዳሳተሙት፣ ሴንትራል ማተሚያ ቤት ፣ (ገጽ 113)

[10] ብላቴን፣ (ገጽ 107)

[11] ጳውሎስ፣ (ገጽ 65)

[12] ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ፣ (1927-1928 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግስተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ ወይዘሮ ሰናይት ተክለማርያም በ1999 ዓ.ም. እንዳሳተሙት፣ ሴንትራል ማተሚያ ቤት፣ (ገጽ 201)

[13] ብላቴን፣ (ገጽ 105-107)

[14] Pan-African Conference 1897

[15] ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ (February, 2016) (Turning Adwa into a Pan-African Struggle Heritage Global Site! NES Commentary)

[16] አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ መሪ የታቦ ምቤኪ ንግግር ስለአድዋ ድል (Former South Africa President, Thabo Mbeki Speech, In Commemoration of the 121st Anniversary of the battle of Adwa: AAU, Ethiopia (March 4, 2017) Thabo Mbeki Foundation.

[17] http://www.zehabesha.com/amharic/?p=74151

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!