መስቀሉ አየለ

ደርግ የሚባል ለኮንጎ ዘማቾች ደመወዝ ለማስጨመር ከየክፍለጦሩ የተወከለ የወታደሩ ኮሚቴ ግዜያዊ ጣቢያውን አዲስ አበባ በሚገኘው አራተኛው ክፍለ ጦር አቋቁሞ፤ ከኃይለሥላሴ መንግሥት ጋር መደራደር ጀመረ። ነገሩ በወቅቱ ከነበሩት ካቢኔቶች በላይ ሄደና እንደ ቀልድ ከንጉሡ በመድረሱ አጋጣማውን እየተጠቀመ ወደ ቤተመንግሥቱ ወጣ ገባ ለማለት ዕድል ያገኘው ይኽ ኮሜቲ የንጉሡን ክፉኛ መድከም ለማስተዋል ግዜ አልወሰደበትም።

ነገሩ ይበልጥ እየጠነከረ ሄደና ቀስ በቀስ ምንጣፍ መጎተት ሲጀምር ሁኔታው ደስ ያላላቸው ከፍተኛው የካቢኔቱ አባላትና መኮንኖች ይሕንን ኮሚቴ እዚያው አራተኛ ክፍለ ጦር ቢሮ ውስጥ እንደተሰበሰበ በሙሉ በጦር ጄት ለመጨፍለቅ ሃሳብ ያቀርባሉ። ነገር ግን ሃሳቡ ሳይጀመር የጨነገፈው "ጥቂት ወታደሮችን ለመደምሰስ ሲባል በአካባቢው ያሉ ሌሎች ንጽሃን ሰዎችን አብረን መጉዳታች ስለማይቀር ይኽ ነገር አያስኬድም" የሚል የተቃውሞ ሃሳብ በመነሳቱ ነበር።

በመሆኑም ይኽ በእንጭጩ ሳይቀጭ ቸል የተባለ የጥቂት አስር አለቆች ስብስብ ባገኛት የማርያም መንገድ ተጠቅሞ ወደ ላይኛው መሰላል ለመንጠላጠልና ግርማዊነታቸውን ጨምሮ ያንን ሁሉ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የጦር ጀነራሎች፣ አሉ የተባሉ ልሂቃን፣ ፓትርያርኩንና አንድ ትውልድ ሙሉ የፊደል ሠራዊት ጨልጦ ለመጋገር በቃ። የግብርና መሩ ኢኮኖሚዋ በማንጸባረቅ ላይ የነበረችውና ከደቡብ ኮሪያ ጋር እኩል ቁመና ላይ ትወዳደር የነበረች አገር ሦስት ሺህ ዓመት የቆየችበትን የሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት አራግፋ ማርክሲዝም ሌኒንዝም የሚባል ድሪቶ ካባ በመልበስ ጥቂት አብዮት ጠባቂዎች እጅ ወደቀች።

ከጥንስሱ በጦርነት ዋዜማ የተወለደው የደርግ መንግሥት ከተራዘመ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሳይወጣ ወደ ማርጀቱ በመቃረቡና ዓለም ላይ እየተለወጠ የመጣው የኃይል አሰላለፍ ተዳምረው ውድቀቱን አይቀሬ እንደሚያደርጉት ግልጽ መሆን በመጀመሩ፤ አገሪቱ የግባችበትን አጣብቂኝ በፖለቲካዊ መፍትሄ ለመቋጨት "እንቅፋቱ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ብቻ ነው" ብለው ያመኑት ከፍተኛ የጦር ጀነራሎች መንግሥቱን በመፈንቅለ መንግሥት ለማስወገድና ብሎም ብሔራዊ እርቅ ለምማጣት ውስጥ ውስጡን መሥራት ጀመሩ። በመጨረሻም መንግሥቱ ለጉብኝት ወደ ምስራቅ ጀርመን ሲሄድ የሚሳፈርበትን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከደብረዘይት በሚነሳ የጦር አውሮፕላን በመምታት ፍጻሜውን መቋጨቱ ቤተመንግሥቱ ዙሪያ እርሱን ከሚጠብቁት ሦስት ሺህ ከሚሆኑት ታማኝ ልዩ ኃይል ጋር ከመፋጠጥ የተሻለና ቀላሉ መፍትሄ መሆኑን ቢጠቆምም ከኃይለሥላሴ ሚንስትሮችና ጀነራሎች ያልተማሩት የደርግ መኮንኖች፤ "መንግሥቱ በሚሳፈርበት አውሮፕላን ውስጥ የተወሰኑ የበረራ አስተናጋጆች፣ ፍላይት ኢንጂነርስ፣ ፓይለቶችና ካፒቴኑ አሉ፤ እነዚህ ደግሞ ንጹህ ኢትዮጵያውያን ናቸው፣ እርሱን ለማስወገድ ሲባል በነዚህ አስር ያህል ንጹሃን ዜጎች ላይ መፍረድ አለብን ወይ?" በሚለው ሃሳብ ተሸንፈው አውሮፕላኑም ሳይመታ በሰላም ወደ ጀርመን በረረ። መንግሥቱ ጀርመን እንደገባም ስብሰባ የተቀመጡት ጀነራሎች ከኩዴታው ባፈነገጡ ሰዎች በደረሰ ጥቆማ፤ በልዩ ኃይሉ ተከበው የተገደለው ተገድሎ፣ ለራሱ ክብር ያለው ራሱን ሰውቶ፣ የተረፈውም ተያዘ፤ ቢሆንም ግን የቀሩትንም እያወጣ እንደበግ ለማረድ መንግሥቱ ኃይለማርያም እንደነሱ የጭካኔ ችግር አልነበረበትም። ያንን ግማሽ ሚሊዮን ጦር ማን ሊመራልኝ ነው ብሎም አላሰበም። ከሻዕቢያ ጋር የነበረውም የውስጥ ለውስጥ ድርድር እዛው ላይ ሞቶ ተቀበረና ኢትዮጵያ በነመለስ፣ ሳሞራ የኑስ እና ስዬ አብርሃ ጫማ ልክ የተሠራች ትንንሽ አገሮች ለመሆን መንገዱን "ሀ" ብላ ጀመረችው።

ኢትዮጵያዊነትን ብሔር ብሔረሰቦች በሚባል ድሪቶ ተክቶ፣ ጎጠኝነትን በማራገብና ማዕከላዊነትን በማዳከም ሲሠራ የቆየው የዛሬው የትግራይ ገዥ ጉጅሌ ለራሱም ለአገሪቱም ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞ ፖለቲካውም ማነቆ የሆነ በሽታ መትከሉ ከመቸውም በላይ ግለጽ ሆኖዋል። አገሪቱ ልትበተን ትቻላለች በሚል ፍርሃት ስጋት ውስጥ የወደቀው ሕዝብ ተቃማሚዎች ላይ የሚሰነዝረው "ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ" የሚለውን ጫና ዛሬም አላቆመም። ቢሆንም ግን ገና ለገና ሕዝቡ ተባበሩ ብሎናል በሚል ስሌት ብቻ ምንም አይነት የጋራ ዓላማና ራዕይ ቀርቶ የጋራ አጀንዳ እንኩዋን የሌላቸው ፈጽሞ የማይመሳሰሉ የፖለቲካ ቡድኖች ነጋ ጠባ ሲዋሃዱና ሲፈርሱ ሩብ ምዕተ ዓመት አስቆጥረዋል።

ዛሬ ነፍጥ አንስቶ አገር ሊነቀንቅ ዱር ቤቴ ያለው የአንድነት ኃይል ሳይቀር ከዚህ ችግር ሳይወጣ አገር አድን ንቅናቄውን ለመፍጠርና ብሔርተኝነትን በመገዳደር አገራዊ ራዕይ ለመገንባት ያስችሉኛል ያላቸውን ግንባሮች ሲያባብል ጥቂት መስቀል አስተኩሷል። ነገር ግን ደምሂትም በሉት ኦነግ እንዲህ ያለውን ብሔራዊ ግማደ መስቀል ለመሸከም የሚያስችል ወርድና ቁመት ሙሉ ለሙሉ አምነውበት እስኪሸከሙ ምናልባት ሌላ አንድ ተጨማሪ ትውልድ ሊፈጅ እንደሚችል ግልጥ ብሎ ወጥቷል። "ኦሮሚያን በእስላማዊ ንቅናቄ ስር ብቻ ካልሆኑ የኦሮሞን ጥያቄ ብቻውን ይዞ አንድ እርምጃ እራመዳለሁ ማለት ከኦነግ አለመማር ነው" ብሎ ከሚያምነው ጃዋር ጀምሮ፤ "የአባሽን አስተምህሮ እንቀበልም" እስከሚሉ እስላሞች አንዳቸውም አገራዊ አጀንዳ የላቸውም። እራሱን ደምሂት ብሎ የሚጠራው አካል የዚህችን አገር እጣ ፈንታ አሁን ካለው የአደረጃጀት እጣ ፈንታ እንዴት እንደሚያስታርቀው ግልጽ ሆኖ ሳይወጣ ነው የአመጽ አዙሪት ያረገዘው የአገሪቱ ሰማይ ጎንደር ላይ የፈነዳው። ዛሬ የጎንደርን ሕዝባዊ ትግል ወደኋላ መመለስ አይቻልም። በቅርጽም በመልክም ወደ ሚያስፈራ ኃይል እየተቀየረ እንደመጣ ሰሞኑን አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ የተቀመጡት የወያኔ ጀነራሎ ሳይቀሩ በአንድ ድምጽ የተስማሙበት ሃቅ ነው።

የአገሪቱን ቀጣይ የፖለቲካ አቅጣጫ ለመወሰን የተሻለ ቁመና ላይ ያለው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ከእንግዲህ ኦነግና ደምሂት እያልኩ፣ "ካልተባበርኩ እሰባበራለሁ" በሚል የተለመደ ለቅሶ የወቅቱን ዳይናሚክስ መለኪያ ሜትር የሌላቸውንና እኒህን ዘመኑን መዋጀት የተሳናቸው ድርጅቶች ቆሞ በመጠበቅ አገሪቱ ለሦስተኛ ግዜ የቆመችበትን መስቀለኛ መንገድ ያባክናል ብለን አናምንም። ይልቁንም በሰሜን ከተነሳው ሕዝባዊ አብዮት ጋር አሰላለፉን ማሳመሩ በጣሙን የሚያኮራና ብቸኛውም አዋጭ መንገድ መሆኑን እያደረጋቸው ባለው እንቅስቃሴ በተግባር ታይቷል።

ዛሬ ጎንደር ላይ ያለው ሕዝባዊ ተጋድሎ ወደ ቀሪው የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ውስጡን በመዛመት ላይ ነው። ድርጅቱ መዋቅሩን ይበልጥ በማስፋት ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን ጉዞም ሆነ የወያኔ መሰረት የሆነውን ትግራይ ከአዲስ አበባ በመነጠል ከበባ ውስጥ የማስገባቱን ሥራ ማፋጠን የግድ ይለዋል። እነ ደምኺትን ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ይኽንን መሬት የረገጠ ትግል ገታ ለማድረግ እያባከናት ያለች አንዲት እላፊ ሰከንድ ካለችው፤ ነገ ከነወለዱ የምታስከፍል ብቻ ሳትሆን ይልቁንም አገሪቱ በታሪኳ ለሦስተኛ ግዜ መስቀለኛውን መንገድ ሳታቋርጠው ትቀርና የዚህ ትውልድ ተስፋ እንዳይመለስ ሆኖ ሊመክን የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!