በእውቀቱ ዘኢትዮጵያ

በአሁኑ ወቅት የአገራችን የኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ የሆነበትና የአገራችንም ህዝብ ከባድ መከራና ፍርሃት ውስጥ የተዘፈቀበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል፤ የአገሪቱ ሁኔታ ከፍተኛ ሥጋት ላይ መሆኑን ለችግሩ ዋና ምክንያት የሆኑት የወያኔ ገዢዋች እንኳን ሳይቀሩ አገሩ በእሳት ሊቃጠል እንደሚችል በግልፅ እየተናገሩበት ያለ ጉዳይ ነው። ይህ ሁኔታ አገርን በሚጎዳ መንገድ እንዳይሄድ ለማድረግ የምሁራን ድርሻ በጣም ከፍተኛ መሆን ይገባዋል። የአማራውና የኦሮሞ ህዝብ ያነሱት የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዋች በአገሪቱ ገዢዎች መሀከል ዘንድ ከፍተኛ ትርምስ የፈጠረና ሁኔታውም በየት አቅጣጫ እንዲሚሄድ ለማወቅ በሚያስቸግር በመንታ መንገድ ላይ እንገኛለን። የኢትይጵያ ህዝብም የወያኔ የእሳት ማገዶ እንዳይሆን ትልቅ ሥራ ከፊት ለፊት ተደቅኗል። በአማራው ህዝብ ላይ የተፈፀመውና በመፈፀም ላይ ያለው ከባድ ግፍና መከራ በአማራው ህዝብ ውስጥ ኃይለኛ ብሶትን ፈጥሯል። ነገር ግን ይህ ብሶት ወደ በጎ ድል እንጂ ወደ ሽንፈት እንዳይሸጋገር ትልቅ ሥራ ያስፈልገዋል።

የአማራው በጥንካሬ መደራጀት የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። አማራው በራሱ ላይ እየተፈፀመበት ያለውን ግፍና መከራ መመከትና ብሎም ኢትዮጵያን ሊያድን የሚችለው የጠነከር ድርጅት ሲፈጥር ብቻ ነው። አማራውን እራሱን ከጥቃት መከላከል ሳይችል፣ ኢትዮጵያን ከጥቃት እከላከላለሁ ማለት አስቸጋሪ ይሆናል። የአማራው ተጋድሎ በአገር ቤት የወያኔን አገዛዝ እንቅልፍ አየነሳ የሚገኝ ሲሆን፣ ለዚህም የአማራው ወጣትና የአማራው ገበሬ ከፍተኛ መከራና ከፍተኛ መስዎዕትነት በመክፈል ላይ ይገኛል። በውጭ አገር ከመከራውና ከመስዋዕትነቱ በጣም ርቆ የሚገኘው የአማራው ሊዕቃንና ፖለቲከኛ ይህንን በአገር ቤት ከፍተኛ መስዋዕትነት እያስከፈለ ያለውን ትግል በሞራል፣ በማቴሪያልምና ሌላም ሁሉን አቅፍ በሆነ መንገድ መርዳት አስፈላጊም ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው። ለዚህም ታዲያ ጠንካራ ድርጅት በመፍጠር ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል። አማራ ሲጎዳ ኢትዮጵያ ትጎዳለች፤ ኢትዮጵያ ስትጎዳ አማራ ይጎዳል። የአማራ ሕዝብ በአማራነቱ በጥንካሬ መደራጀትና ሁሉንም ነገዶች በእኩልነት የምታኖር ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት መታገል ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል። በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢው ጉዳይ ጠንካራ ድርጅት ፈጥሮ አገርቤት የሚደረገውን ትግል መደገፍ እንጂ የታሪክ መዛግብትን እየጠቀሱና የመካረሪይና የመለያያ አጀንዳዎችን በማንሳትና በማሰራጨት አማራውን ከሌላ ነገዶች ጋር እንዳይተባበርና አማራው ላይ ጠላት የማብዛት መንገድ ለተቀጣጠለው ሕዝባዊ ትግልና ተጋድሎ ጥቅም የሚያስገኝ የትግል መንገድ አይደለም። አማራው ጠንክሮ ለመደራጀት የግድ የኦሮሞ ወይንም የሌላ ነገዶች ጠላት መሆን አይገባውም። ጠንክሮ በነገድ ለመደራጀት ከባድ ጠላትና ከባድ ጥቃት አስፈላጊ ቢሆንም፤ ለዚህም ወያኔን የሚያህል የአማራና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ ጠላት አለ። ነገር ግን አማራው ጠንክሮ ለመደራጀት ፅንፈኛ መሆን አያስፈልገውም። ፅንፈኝነት የጥንካሬ ምልክት ሳይሆን የፀረ - ዲምክራሲያዊነት ምልክት ነው።

ይህ በአገር ቤት የተነሳውን የፍትህና የእኩልነትን ጥያቄ ያነገበ የአማራውን ተጋድሎ ባለመገንዘብ ይሁን ወይንም ሌላ የፓለቲካ ጥቅም ለማራመድ ታቅዶ ይሁን በአንዳንድ ጥቂት የአማራ ምሁራንና ድርጅቶች የሚቀነቀኑ ሀሳቦች አስደንጋጭና አስፈሪ እየሆነ እየመጡ ነው። ከነዚህም መሀከል ሞረሽ ዐማራ፣ ዳግማዊ መዐሕድ፣ ዶ/ር አበባ ፈቃደና ፕሮፌሰር ሙሴ ተገኝ የመሣሠሉትን ከአክብሮት ጋር መጥቀስ ይቻላል። በእነዚህ አካባቢ የሚቀነቀኑት ሀሳቦች የአማራውን ነገድ ከሌሎች ነገዶች ጋር የሚያቀራርብና የሚያስተባበር ሳይሆን፤ የአማራውን ጥያቄ ለብቻው የተለየና ከፍተኛ መንፈሳዊ ተልዕኮ ያለው በማድረግ፤ የአማራውን ህዝብ በአገር ቤት የሚያደረገውን የፍትህ፣ የእኩልነትና የመብት ተጋድሎ በተጣመመ መልኩ በመተርጎም የአማራው ተጋድሎ አላማው ለአማራው ብቻ የምትመች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንደሆነ አድርጎ መቀስቀስ የዋህነት ብቻ ሳይሆን፤ አገሪቱ ያለችበትን የፓለቲካ ሁኔታ መገንዘብ ያለመቻል ወይም ያለመፈለግ አስተሳሰብ ነው። ኢትዮጵያ ተረጋግታ ወደ ብልፅግና እንድትሄድ የሚያስብ የአማራ ምሁር አገሪቱ ጥቂት የአማራ ምሁር በሚፈልጉትና ለአማራው ነገድ ብቻ በሚስማማ አይነት ልትደራጅ ይገባታል ብሎ መቀስቀስ ወይንም የኢትዮጵያ የወደፊት ህልውና እኛ በምንለው መንገድ ብቻ ስለሆነ በዚ ጉዳይ ከማንም ጋር መደራደር አያስፈልግም የሚል አይነት አካሄድ ማራመድ እንኳን ለኢትዮጵያ ለአማራው ነገድም የሚበጅ አስተሳሰብ አይደለም። ህልምና ምኞት ሊሳካ ይችል ይሆናል። ነገር ግን መጥፎ ህልም መጥፎ ፍሬ እንጂ ጥሩ ፍሬ መስጠት አይችልም። በአሁኑ ወቅት በዲያስፖራ በሚገኙ አማሮች ላይ የሚነዛው የተሳሳተ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ አማራውን ከሌሎች ጋር ተባብሮ መስራት እንደማያስፈገውና፤ አማራው በራሱ ኃይል ብቻ የኢትዮጵያንም ሆነ የአማራን ችግር ሊፈታ ይችላልም ይገባውልም ብሎ ማመንና ይህንንም ከፅንፈኛነት፣ ከስሜታዊነትና ከፖፕሊዝም በቀር በምንም ማስረጃና ምርምር ያልተደገፈና በኢትዮጵያ ታሪክም ያልታየ አስተሳሰብ ህዝብ ላይ ማራገፍ ከምሁር የሚጠበቅ አስተሳሰብ አየደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ሁልጊዜ ጠላቱን የመከተው በመተባበር ነው። ትልቁ የሚያሳስበው ጉዳይ ደግሞ የዚ የፅንፈኝነት አስተሳሰብ አራማጆች በዕውቀት የበሰሉ፣ የተማሩና አንጋፋ ግለሰቦች በመሆናቸው በአማራው ወጣትና ፖለቲከኛ ላይ እያሳደሩ ያሉት ተፀዕኖ እየከበደ በመምጣት ላይ ይገኛል። የፅንፈት ዓላማ በዕውቀት ከታጀበ ሊያደርሰ የሚችለው ጥፋት ከፍተኛ መሆኑን በአገራችንም ሆነ በዓለማችን ላይ ብዙ ማስረጃዎች ይገኛሉ።

ባለፉት ጊዜያቶችና ታሪክ ይልተገዳደለ የለም፤ ወንድም ወንድሙን ገድሏል፤ እናት ልጆን ገድላለች። አሁን መትጋት ያለበን እንደዚ ዓይነት የጭካኔ ተግባር ከአገራችን እንዲጠፋ መታገል ሲሆን። ከዚህ በፊት በሕዝብም ይሁን በግለሰቦች የደረሱትን ግፎችን በተመለከተም አገራችንን ውስጥ ሕዝቡ የሚስማማበትን የአስተዳደ ሲመሰረት በሕዝብ የተመረጠ አጣሪ ኮሚሽን በማቋቋም የደረሱትን በደሎችንን በመርመር በግፍ ለተሰውት ወግኖቻችን ተገቢውን ክብር በመስጠትና በመዘከር፤ በአገራችን እንደዚህ ሁኔታ እንዳይፈጠር ቃል የምንገባበት ታላቅ የስማዕታት ማስታዋሻ ማስቀመጥ አንችላለን። በዚህ ጉዳይ ከሃያ ስድስት ዓመታት በላይ ስንነታረክ ኑረናል። መግባባታም ይሁን ስምምነት ላይ አልደረስንበትም። አሁን ደግሞ ይህንኑ መፍቻ የሌለውን ንትርክ ወጣቶቹ ላይ እያፈሰሰስን ነው። የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባየው የሚሆን እየመሰለ ነው። ያለፈው የርስ በርስ በደሎቻችን ብዙ ናቸው። አንዱን ብቻ በዳይ ወይም ተበዳይ፤ አንዱን ብቻ ለይቶ ቅድስ ማድረግና ሌላውን ወንጀለኛ ማድረግና ይህንንም ለማሳመን ጊዜ ማጥፈት የየዋህነት መንገድ ብቻ ሳይሆን የጋራ አገራዊ ራዕይና አስተሳሰብ ለመቅረፅም ሆነ፣ ይህንንም በህዝቡ ውስጥ ለማስረፅ አይረዱም። በተጨማሪም የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ በአማራውና በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍ፣ መከራና የአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ነው።

በማንኛውም ማህረሰብ ውስጥ በፅንፈኝነት፣ በስሜትና በፖፕሊዝም የሚሸነፍ ምሁር ይኖራል። አሳዛኙ ጉዳይ ግን ይህንን በፅንፈኝነት፤በስሜትና በፖፕሊዝም የሚመራና የሚረጭ አስተሳሰብን በድፍረትና በጥንካሬ ሊቃወሙ የሚችሉ ምሁራን ከአማራው ማህበረሰብ ውስጥ በርክተው መውጣት አለመቻላቸው ነው። እንደዚህ በስሜትና በፖፕሊዝም የሚነዳ ፅንፈኛ አሰተሳሰብን የሚቃረኑ ጥቂት የአማራ ምሁራንና ፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰውን የስድብ ውርጅብኝና ስብዕናን የማዋረድ ዘመቻ ስናይ የአብዛኛው የአማራ ምሁር ይህንን በዝምታ ማለፉ የሚያስፈራም የሚያስተዛዝብም የሚያጠራጥርም ይሆናል። ዝምታው ምንድነው? ፍርሃት ነው? ድጋፍ ነው? ወይስ ተቃውሞ? ለዚህም አንዳንድ ዋቢ ድርጊቶችን መጥቀስ ይቻላል። ብዙ የአማራ ምሁራን ኢትዮጵያን የሚጎዳ ድርጊቶችና ሀሳቦች ሲከሰቱ በብዛት በመውጣትም ሆነ በመፃፍ ተሳትፎ ያደርጋሉ። የቅንጅትንም ሆነ በኢንጅነር ኃይሉ ሻወል የተመራውን መኢአድን ለታላቅ ድልና ስኬት ያበቁት በርካታ የአማራ ምሁራንና ፖለቲከኞች መሆናቸ የማይካድ ሀቅ ነው። ታዲያ በዚህ አንገብጋቢ ወቅት የስሜታዊነትና የፅንፈኛ ሀሳቦች የአማራውን ዳያስፖራ ውዥንብር ውስጥ በዘፈቁበት ወቅት ለምንድነው የአማራው ምሁር በብዛት በመሆን በግልፅና በድፍረት በመውጣት የትኛው አቅጣጫ ያዋጣል የሚል የምሁራው ውይይትና የሀሳብ ልውውጥም ሆነ የሰለጠነ ውይይት እንዲደረግ መግፋት የተሳነው። የአማራው የዳያስፖራ ፓለቲካ መድረክ ጠቀሜታ በሌለው በፅንፈኝነት፣ በፖፕልስትና በስሜታው አጀንዳዎች እየተተራመሰ ባለበት ሁኔታ፣ ከደሙ ንፁ ነኝ የሚያስመስል የአማራው ምሁር ለዘበተኛነት አደገኛም ኃላፊነት የጎደለውም ነው። አማራው ፅንፈኛ ሳይሆን ዲሞክራሲያዊ የሆነ ጠንካራ የአማራ ድርጅት መፍጠር እንደሚችል ምሁራኖቹ መርዳት ይገባቸዋል። መኢአድን የመሰለ ጠንካራ ዲምክራሲያው ድርጅት መፍጠር የቻለ በርካታ የአማራ ምሁርና ፓለቲከኛ፤ ዛሬ የአማራው ፓለቲካ ፅንፈተኛና ስሜታዊያ በመሆኑ ምሁራንና ፖለቲከኞች ሲተራመስ እንዳላዩ ሆኖ ማለፍ ከባድ ስህተት ሊሆን ይችላል።

የአገሩ ሁኔታ እንቅልፍ ነስቶትና የሚያስብ ሰውና ኢትዮጵያዊ በመሆኑ የአገሩን ሁኔታ ለመከታተልም ሆነ አቅሙ በሚፈቅደው መጠን የሚችለውን ለመርዳት በየፓልቶክ መድረክ በሚሰባሰበውንና የኢትዮጵያ የነፃ ሚዲያዎችን በሚከታተለው የአማራ ዲያስፖራ ላይ የሚነዙት የጥላቻ፣ የፅንፈትና የስሜታውነት ሀሳቦች ለአማራው ይበጀው ይሁን ወይም አይሁን በማለት ሀሳባቸውን ለመግለፅ ለምነድነው የአማራው ምሁራን በብዛት በመሆን የማይወጡበት ሁኔታ? ይህ የፅንፈኛነት የጥላቻ አካሄድ አይጥቅምም ብለው ሀሳባቸውን በሚያቀርቡ የአማራ ምሁራንም ሆነ ፓለቲከኞች ላይ የሚደርሰው ዘለፋና ስብዕናን የማዋረድ ዘመቻ በአማራው የዲያስፖራ የፓለቲካ መድረክ ጥንካሬ እያገኝ ሊመጣ የቻለው፤ ይህ አካሄድ ጠቀሜታ የለውም ብለው የሚከራከሩት ጥቂት የአማራ ምሁራን ፖለቲከኞች ብቻ በመሆናቸው ነው። ስለዚህ አብዛኛው የአማራ ምሁራን በግልፅ በመውጣት የትኛው መንገድ ለአማራው ያዋጠዋል በማለት ሀሳቡን ማቅረብ ካልቻለና አሁን ያለውን አካሄድ ለአገሪቱ በሚጠቅም መልኩ ለመምራት ካልተቻለ፤ ያለፈውን የወንድሞቻችንን ስህተት እንዳንደግመው ያስፈራናል። አሁን በአንዳንድ በዲያስፖራው አማራ አካባቢ እየተስተጋባ ያለውን የፅንፈኝነት አካሄድ ለሚከታተል ሰው፤ አማራው ተነስቷል፣ የአማራው ኃይል ሁሉንም ይጠራርጋል ዓይነት አካሄድ፣ በፅንፈኛና በስሜታዊ አስተሳሰብ የሚታለሉትን አማሮችን ሊያሟልል ቢችልም፤ ከአማራ ነገድ ውጪ ለሚገኙ ለሌሎች ነገዶች ምሁራንና ፓለቲከኞች ዘንድ የሚጭረው አስተሳሰብ ግን አማራው ዲምክራሲያዊ ድርጅት ለመመሥረትም ሆነ ዲሞክራሲያዊ የሆነች ኢትዮጵያ በመመሥረት ከሌሎች ነገዶች ተባብሮና ተከባብሮ ለመኖር ችገር ያለበት ሊያስመስለው ይችላል።

በርግጥ ነው የህወሃት ገዢዎች ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት የአማራ ነገድ ላይ ከፍተኛ ዘመቻና ጥቃት አድርሰዋል እያደረሱም ይገኛሉ። አማራውንም ከሌሎች ነገዶች በማጋጨት የከፋፍለህ ግዛው ዕቅዳቸውን ብዙ ሠርተውበታልም ተጠቅመውበታል። ነገር ግን ታላቁ የአማራ ሕዝብ በጎንደር ላይ በትግሉ በፈጠረው አንድ የነፃነት ቀን ላይ በኦሮሞ ወንድሞቻችን ላይ የሚፈፀመው ግድያ ይቁም በማለት የሃያ ስድስት ዓመታትን የህወሃት መሰሪ ሥራ ፉርሽ ያደረገበት ሲሆን። ከኦሮሞዎችም በኩል አማራ ኬኛ፤ አማራ የኛ ነው በማለት አፀፋውን ሊመልሱ ችለው ነበር። ነገር ገን ህዝቡ በነፃነት ሀሳቡን መግለፅ ከቻለ የህወሃትን የከፋፍለህ ግዛ መሰሪ ዕቅድ ዜሮ እንደሚያደርግ ህወሃት በመረዳቱ ይህው ከዛ ጊዜ ጀምሮ አገሪቱን የወታደራዊ አገዛዝ በሚመስል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገሪቱን እየገዛ ይገኛል። በዳያስፖራው አካባቢም በአገር ቤት የታየውንና ያለውን የህዝብ የመተባበር መንፈስ ለማንፀባረቅ የመተባበር እንቅስቃሴውች እየተሞከሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ለዚህ የመተባበር መነሳሳትና እንቅስቃሴ ትልቅ እንቅፋት በመሆን ላይ የሚገኙት ከላይ የገለፅኳቸው በአንዳንድ የአማራ ምሁራንና ድርጅቶች የሚረጩት በፅንፈኝነት፣ በስሜታዊነትና በፖፕሊዝም የሚራመድ አስተሳሰቦች እየሆኑ መጥተዋል። የህወሃት መሰሪ የከፋፍለህ ግዛ ተግባር በአገርቤት ሲፈርስ፣ ነገር ግን በነፃነትና በዲምክራሲ የሚኖረው የአማራና የኦሮሞ የዲያስፖራ ፖለቲከኛ የህወሃት መሰሪ የከፋፍለህ ግዛ ተግባር ተሸካሚ የሆኖ ይመስላል። ከአማራውም ሆነ ከኦሮሞው አካባቢ የሚንፀባረቅ ማንኛውም የፅንፈኝነት አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአማራውም ሆነ ለኦሮማው አይጠቅምም። በአውሮፓና በአሜሪካ ሆኖ የትግሉ ወላፈን በማይደርስበትና መስዋዕትነት በማያስከፍልበት ቦታ ተቀምጦና የግል ኑሮን እያጣጣም ተደላድለው እየኖሩ፤ እኔ የምለው ብቻ መሆን አለበት ብሎ የፅንፈኛነት መንገድ መምረጥ፤ የአማራው ሕዝብ ወገን መሆን ሳይሆን ወይንም የአማራው ሕዝብ እየከፈለ ያለውን መከራና ስቃይ የሚቀነስበትን መንገድ ሳይሆን፤ እኛ በምንፈልገው የፅንፈኝነት መንገድ ካልሆነ በስተቀር የሕዝቡ ስቃይ አይሰማንም ዓይነት የሆነ የለየለት የራስ ወዳድነት፣ የክፋት ወይንም የፖለቲካ እውቀት ማነስ ምልክት ሊሆን ይችላል። ይህንን የፅንፈተኛነት አስተሳሰብን ሰብሮ መውጣት የሚችል ብዛት ያለው የአማራ ምሁር ማየት አለመቻል ግን፣ የዲያስፖራው የፓለቲካ መድረክ በአገርቤት ለሚካሄደው የእኩልነት፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የልማት ጥያቄ ላይ ገንቢ አስተዋፆ ሊያደርግ ይችላልን የሚለውን አስተሳሰብ ትልቅ ጥያቄው ውስጥ የሚከት ይሆናል።

አንድ ምሁር የሆነ ሰው የራሱን ነገድ ከሌላው ነገድ በጣም የተለየ ቅዱስና ፃድቅ አድርጎ መስበክ ዋናው የፅነፈተኛነት መገለጫ ነው። በሃይማኖታችንም እንኳን ቢሆን በነገዱም ሆነ በስብስቡ ምክንያት የሚፀድቅም ሆነ ቅዱስ የሚሆን የለም። ቅዱስናና ፅድቅና የሚገኘው እያንዳንድ ግለሰብ በእምነቱና በተግባሩ ነው። በስብስብ ውስጥም ሆነ በአንድ ነገድ ውስጥ የተላያዩ ተግባርና እምነት ያላቸው ግልሰቦች ይኖራሉ። በአንድ ነገድ ውስጥ ጥሩ ግለሰቦች እንዳሉ ሁሉ መጥፎ ግለሰቦችም ይኖራሉ። አንድን ሰው የአንድ ነገድ አባል ስለሆነ ብቻ የተቀደሰ፣ ፃድቅ ወይም ከሁሉም የተሻለ ብሎ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ከምሁራን አንደበት መስማት እጅግ የሚያሳዝን ነው። እነደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ይዘው የተነሱ ስዎች በዓለማችን ላይ ያደረሱትን ከባድ ጥፍትና መከራ የሚዘነጋ አይደለም። ገና ኃይልና ጥንካሬ ሳይኖር እንደዚህ አስከፊና አስፋሪ የሆነ የፅንፈኛ አስተሳስብና አመለካከት የያዘና የሚያሰራጭ ክፍል፣ ኃይልና ጥንካሬ ሲያገኝ ምን የጥፋት ተግባራትን ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ማንም ሊዘነጋው አይችልም። እንደዚ የፅንፈኛነት ሀሳብ ይዞ አገራዊ አጀንዳ አለኝ ብሎ መስበክ ለፖለቲካ አዲስ የሆነውን፤ በእውቀትም ላልበሰለ ወገንና በስሜታዊነትና በሆይ ሆይ ጭብጨባ ለሚሰክር ምሁር የሚጥም ይሆናል። ነገር ግን የአገሪቷን መሠረታው የሆኑ የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚና የፀጥታ ችግሮች ለመፍታት የሚችል አስተሳሰብ አይደለም። ጠንካራ የአማራ ድርጅትም ለመፍጠር የሚያስችልም አይደለም። በኢትዮጵያ የፓለቲካ መድረክ ላይ ጥንካሬነት የሚለካው በአንድ ነገድ ብቻ የሚወደድና የሚደገፍ ዓላማ በማንገብ አይደለም። ዋናው የጥንካሬ መለኪያ በአገሪቷ ውስጥ በሚገኙ ነገዶችም ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል የፓለቲካ አስተሳሰብና ዓላማ ነው። ትንንሽ ነገዶችን በማማለል ከጎን አሰልፌ ጠንካራ ኃይል መፍጠር እችላለው ብሎ ማሰብ ይቻላል፣ ነገር ግን ይህ አካሄድ ወያኔ የሚጠቀምበት የከፋፍለህ ግዛው ዓይነት አካሄድ እንጂ አገሪቷን ወደ ዲምክራሲያዊ አስተዳደር የሚወስድ አስተሳሰብ አይደለም።

የማንኛውም አገር ችግር በስሜታዊነትና በፖፕሊዝም ሆይ ሆይ በማለት አይፈታም። ከታሪክ በዙ ልንማር እንችላለን። የኢትዮጵያ ችግር ደግሞ በጣም የተዋሳሰበና ከባድ ነው። በተዋሳሰበ የጂኦፖለቲካል ክልል የሚገኝ የመቶ ሚልዮን ህዝብ ጉዳይ ቀላል አይደለም። ኃላፊነት በጎደለውና የግል ስሜትንና የአንድ ወገን ጥቅምን ብቻ በማስጠበቅ የሚፈታ አይደለም። አንድ ክፍል ብቻ እውነትን የያዘ ሌላው እውነትን ያልያዘ የሚል አስተሳሰብ ምናልባት በኃይማኖት ይሆን እንጂ በፓለቲካ አስተሳሰብ የሚሰራበትም የሚያዋጣም መንገድ አይደለም። የዐማራ ድምፅ የሚል የሬድዮ ጣቢያ ማቋቋም እሰይ በርቱ ጠንክሩ የሚያስብል ታላቅ ሥራ ነው። ነገር ግን የዐማራ ነገድን የመሰለ የታላቅ ህዝብ ስም ይዞ፤ የአማራ ህዝብ ታላቅነትንና ጨዋነት በማያንፀባርቅ መልኩ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ዘመናቸውን ሁሉ ለህዝብና ለአገር የደከሙና በመድከም ላይ ያሉ ግለሰቦችንና አዛውንቶች ላይ የሚወርደው ስብዕናን የሚያዋርድ የማንቋሽሽ ዘመቻ በዐማራ ህዝብ ከተሰየመ የሬድዮ ጣቢያ በተደጋጋሚ ማድመጥ አማራነት ወይም ኢትዮጵያዊነት ሊሆን አይችልም። የግለሰቦችን አስተሳሰብና አስተያየት በኢትዮጵያዊና በአማራ ሥነምግባር መተቸትና መቃወም ተገቢ ነው። ምክንያቱም በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የተለያይ አመለካከትና አስተያይት ይኖራል መኖርም ይገባዋል። ከዚህ ውጭ ግን የተለየ አስተሳሰብና አመለካከት ያለውን እንደ ጠላት በመቁጠር ስበዕናን የሚያራክስ ዘመቻ ማካሄድ ጠቃሚ ተግባር አይደለም። ድንጋይ ለጠላት ማቀበል የጠላትነት እንጂ የፀረ - ጠላት ተግባር በፍፁም ሊሆን አይችልም። ወያኔ ተቀናቃኞቹንና ተቃዋሚዎቹን የሚመታበት ብዙ ድንጋይ አለው። ከተቃዋሚ ጎራ ተሰልፎ ለወያኔ ድንጋይ ማቀበል ወያኔን ይጠቅማል እንጂ የተቃዋሚ ኃይሎችን አይጠቅምም። ዛሬ ወያኔ ለካድሬዎቹና ለኢትዮጵያ ህዝብ የተቃዋሚዋቹን ስም ለማጥፋትና ለማራከስ በብዙ የሚጠቀምበት ፕሮፖጋንዳ ምንም ድካም ሳያወጣበት የሚሰበስበው ተቃዋሚዋቹ እርስ በራስ በሚለዋወጡት የስድብና የጥላቻ ዘመቻ ነው።

ዕውቀትንና ትምህርትን በመጠቀም ህዝብን ወደ ተሳሳተና የማያዋጣ መንገድ መምራት ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ሲሆን። ነገር ግን በጣም ኃላፊነት የጎደለውና ከፍተኛ ስህተት የሚሆነው፤ ዕውቀትን ትምህርትን በመጠቀም ህዝብን ወደ ተሳሳተና የማያዋጣ መንገድ የሚወስድ አስተሳሰብን ደፍሮ በብዛት ወጥቶ መቃወም አለመቻል ይሆናል። ይህም የአብዛኛው የአማራ ምሁራን ከባድ ፈተና ሆኖል። በመሠረታዊና በትልቅ የአገር ጉዳይ ላይ ለዘብተኝነት ማሳየት ከባድ ስህተት ይሆናል። በዚህ ጉዳይ ላይ አብዛኛው የአማራ ምሁራን አስተያይትና አስተሳሰብ መስማት ለሚደረገው አገራዊ ትግል ትልቅ እገዛ ሊያደርግ ይችላል። ያለበለዚያ ግን የፅንፈት አስተሳሰብ በራሱ ይሞታል ብሎ በለዘብተኝነት ማለፍ የዋህነት ነው። የፅንፈት አስተሳሰቦች በህዝብ ላይ ተረጭተው ህዝብን በማወናበድ ብዙ እልቂትና ውድመት ሊያስከትሉ እንደቻሉ በአገራችንም ሆነ በዓለም ላይ ያየነው ክስተት ነው። ይህ እንዳይመጣ አብዛኛው የአማራ ምሁራን ተሳትፎውን ማሳየት ይጠበቅበታል። ነገሮች አቅጣጫቸውን ስተው ከባድ አደጋ ሳይስከትሉ በብልሀትና በጨዋነት በጊዜ ለማስተካከል መልፋት ያስፈልጋል። አደጋ ከተከሰተ በኃላ ግን ትችት ለማቅረብም ሆነ ለማዳመጥ ጊዜ ላይኖር ይችላል። ፅንፈኝነት መቼም ጊዜ ቢሆን ለአገርና ለህዝብ በዘለቄታነት የሚጠቅም የፖለቲካ መፍትሔ በየትም ቦታ አምጥቶ አያውቅም፤ ሊያመጣም አይቻልም። የወያኔ አገዛዝ መውደቁ የማይቀር ነው። ነገር ግን ከወያኔ መውደቅ በኃላ ግን ወያኔዎች በተደጋጋሚና በግልፅ እንደሚፎክሩት አገሩ በእሳት ይቃጠላል ይሉናል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ወደ እርስበርስ እልቂት እንዳትገባ ከአሁኑ አቅጣጫውን ማሳየት አንገብጋቢና የምሁሩ ታላቅ ኃላፊነት ይሆናል። የፅንፈኝነት አቅጣጫ ትልቅ አደጋ ያመጣል። በትጋት ሣይሰሩ ይህንን አደጋ ማስወገድ አይቻልም። አማራው ጠንካራ የሆነ ዲምክራሲያዊ ድርጅት ለመፍጠር ችሎታውም ብቃቱም እውቀቱም አለው። በአማራው ላይ የደረሰውና እየደረሰው ያለው ግፍ እጅግ የከፋ ነው። ይህ ግፍም ኃይለኛ ብሶትንና ጥንካሬን እየፈጠረ ይገኛል። ነገር ግን ይህ ብሶት የወለደው ጥንካሬ ወደ ጥፋትና ወደ ፅንፈኝነት እንዳይሸጋግርና ብሶቱና ጥንካሬው ለሁሉም ነገዶች የሚበጅ ኢትይጵያን እንዲፈጥር ከአማራው ምሁርና ፓለቲከኛ ብዙ ይጠበቃል። ኢትዮጵያውያን ስንተባበር ብቻ ነበር ጠንካራ የሆነው። ስንከፋፈል ግን ተሸንፈናል። መከፋፈል ለኢትዮጵያውያን አይበጃቸውም። የመከፋፈል ዋናው መንስኤው ደግም እርስበራስ መከባበር አለመቻል ነው።

አስተያየቶ ይጠቅማልና በሚከተለው ኢሜል አድራሻ ይላኩ። This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!