ክንፉ አሰፋ

ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ
ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር

የነጋዴዎች አድማ ዛሬም እንደቀጠለ ነው። ገዥው ፓርቲ ከየአቅጣጫው በመወጠሩ - የችግሩን ትኩረት አቅጣጫ ማስቀየር አለበት። የተለመደ የፉገራ ካርዳቸውን መዘዝ አድርገው ለዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ሰጡዋቸው።

ኦቦ ነገሪ ሌንጮ 34 የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ነጋዴዎች በሙስና ተጠርጥረው መታሰራቸውን ለመገናኛ ብዙኀን ትናንት ምሽት አብስረዋል። እነማን እንደታሰሩ ግን አልገለጹም። ታሳሪዎቹን ሊያውቁዋቸው ስለማይችሉ ሊገልጹ እንደማይችሉ ግልጽ ነው። እንደወትሮው ተጽፎ የተሰጣቸውን ከማንበብ ውጭ አማራጭ የላቸውም። የፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን መታሰር እንደማንኛውም ተራ ሰው በዜና የሰሙት ነገሪ ሌንጮ፤ ምን አፍ ኖሯቸው ስለ ባለሥልጣናት መታሰር ይነግሩናል? ስራዎቼን ሁሉ በግምት ነው የምሰራው - መረጃ እንኳን አይሰጡኝም የሚሉ ጠቅላይ ሚኒስትርስ ምን አቅም ኖሯቸው ጉዳዩን ያስፈጽሙታል?

የሙስና ጉዳይ በየዓመቱ ነው የሚነሳው። ችግር ሲመጣ እየጠበቁ ለአቅጣጫ ማስቀየርያ ይለቁብናል። አንዳንዴ በሙስና ታሳሪ ገጸ-ባህርያትን ይፈጥሩና አስቂኝ ድራማ ያሳዩናል። ሌላ ግዜ ደግሞ የንግድ ባላንጣዎቻቸውን ለመበቀል ይጠቀሙበታል። አንዳንዴም ለመታመን ሲሉ ተራ የመንግሥት ሰራተኞችን እና ነጋዴዎችን ይዘው ያጉሯቸውና ግርግሩ ሲረሳሳ ደግሞ ይለቋቸዋል።

በእርግጥ የሙስና ተጠርጣሪዎችን ማሰር ቢያስቡ፤ መጀመርያ አቦይ መስፍንን ወይንም አዜብ መስፍንን በማሰር ያሳዩን ነበር። ፀረ-ሙስናው ዘመቻ እውን ቢሆን ኖሮ የሕወሓት የጦር አለቆች በሙሉ መኖርያቸው ቂሊንጦ በሆነ። የአቶ ስብሀት ነጋ ልጅ ተከስተ ስብሀት ነጋ እና እህታቸው ቅዱሳን ነጋ ህልቕ መሳፍርት ንብረት ቢታገድ ነበር ፀረ-ሙስና ዘመቻ ተጀመረ ምንለው።

የሙሰኞች ንብረት ታገደ የምንለው የጄነራል ሳሞራ የኑስ፣ የሌ/ጄ ታደሰ ወረደ፣ የሌ/ጄ ገዛኢ አበራ፣ የሌ/ጄ ብርሃነ ነጋሽ፣ የሌ/ጄ ሳዕረ መኮንን ቦሌ ላይ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቤቶች ሲታገዱ ነው።

ሌ/ጄ ገዛኢ አበራ፣ ሌ/ጄ ብርሃነ ነጋሽ፣ ሌ/ጄ ሳዕረ መኮንን፣ ሌ/ጄ አበባው ታደሰ፣ ሜ/ጄ አብርሃ ው/ገብርኤል፣ ሜ/ጄ ዮሃንስ ገ/መስቀል፣ ሜ/ጄ ስዮም ሃጎስ፣ ሜ/ጄ ገ/እግዚአብሔር መብራቱ፣ ብ/ጄ ታደሰ ጋውና፣ ብ/ጄ ተክላይ አሽብር፣ ብ/ጄ ፍስሃ ኪዳነ፣ ብ/ጄ ፓትሪስ፣ ብ/ጄ መስፍን አማረ፣ ብ/ጄ ምግበ ኃይለ፣ ብ/ጄ ሃለፎም ቸንቶ፣ ኮ/ል ታደስ ንጉሴ፣ ኮ/ል ጸሃየ መንጁስ በሕዝብ ገንዘብ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ያሰሩዋቸው በሚሊዮኖች የሚገመቱ ቤቶች በወር ደሞዛቸው እንዳልሆነ ፖሊስና አቃቤ ሕግ ሳያውቁት ቀርተው ነው?

እነ ብርሃኔ ገብረ ክርስቶስ፣ አባዲ ዘሙ፣ ስብሃት ነጋ፣ ሽመልስ ኪዳኔ፣ አርከበ እቁባይ፣ አባይ ጸሃዬ፣ ገብረ መድህን ገብረ ዮሃንስ፣ ደብረጽዮን ገብረ ሚካአኤል፣ ቴዎድሮስ ሃጎስ፣ ታደሰ ኃይሌ፣ ሰምሃል መለስ ዜናዊ ከባህር ማዶ ያከማቹት በቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ እስቲ ይታገድ እና ነገሪ ሌንጮን እንመን።

ይህን መራራ ሃቅ የሚክድ የለም። ራሳቸውም የሚሉት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲፈሩ ሲቸሩ "ሙስና አለ - ማስረጃ የለም" ብለውናል። አቦይ ስብሃት ደግሞ በሰንደቅ ጋዜጣ አዳልጧቸው “መቶ ሚልዮን የሰረቁና ያስዘረፉ፤ 10ሺህ ብር የሰረቀውን ሲያገላብጡት ሲያስፈራሩት ይታያሉ” ብለው ነበር። የአገራቱን የሙስና መጠን ደረጃ በየዓመቱ የሚዘግበው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ተቋም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሙስና ከሚፈፀምባቸው አገራት አንዷ መሆኗን አመልክቷል። እንደ ተቋሙ ዘገባ ከሆነ ከኢትዮጵያ በሕወሓት ዘመን ተዘርፎ የወጣው ገንዘብ 17 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል። ጥናት ከተደረገባቸው 174 አገሮች መካከል ኢትዮጵያ 113ኛ ቦታን ይዛለች። ይህ ቁጥር መንግሥታዊ ሙስናው አገሪቱን ምን ያህል እንደ መዥገር እየመጠጠ መሆኑን ያሳየናል። ታቦ ምቤኪ የመሩት ሌላ ጥናት ደግሞ በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከኢትዮጵያ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ 10 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ወደ ውጭ እንዲወጣ ተደርጓል።

በአንድ ወቅት በፀረ-ሙስና ኮሚሽን የባለሥልጣናቱን ንብረት የመመዝገብ ደንብ ወጣና ስራውን ጀመረ። ብዙ የተወራለት ይህ ኮሚሽን ወደ ጀነራል ሳሞራ የኑስ ቤት ነበር ቀድሞ ያመራው። አይተ ሳሞራም የፀረ-ሙስናውን ቡድን አስቀምጦ "ስራችሁን አደንቃለሁ። ጥሩ ጅምር ነው። ግን ከላይ ጀምሩ" ብሎ ወደ አዜብ መስፍን መራቸው። ንብረት መዝጋቢዎቹ ወደ አዜብ ቤት ሳይደርሱ ግማሽ መንገድ ላይ እንደጠፉ ይነገራል። አዲዮስ ፌደራል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን!

የሲቪክ ማኅበራት በነፃነት መንቀሣቀስ በማይችሉበት፣ የፕሬስ ነጸነት በታፈነበትና የሕግ የበላይነት በሌለበት አገር ሙስናን እናጠፋለን ማለት በሕዝብ ሳይሆን በራስ ላይ መቀለድ ነው የሚሆነው። ዓላማው ከችግሩ አቅጣጫ ለማስቀየር ከሆነ ደግሞ ሌላ ካርታ መጠቀሙ የሚበጅ ይመስላል። ደጋግማችሁ በተባላ ካርታ አትጫወቱ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!