መንበሩ ከመሃል አራዳ

Bole, Addis Ababa
ቦሌ ሰፈር፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ወያኔዎች ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው አመታት ያጋጠማቸውን ፈተና ከሚወጡባቸው ስልቶ አንዱ፣ አዲስ አጀንዳ ፈጥሮ የፖለቲካ ተቃወሞውን ትኩረት ማስቀየር ነው። የሚገርመው ነገር ይህ ዘዴ የሥርዓቱን አድሜ በማስቀጠል ስኬት ብቻ ሳይወሰን፣ በግራም በቀኝም ያለው የተቃዋሚ ወገን፣ መሰረታዊውን የሥርዓት ለውጥ ጥያቄውን ረስቶ፣ ሙሉ ቀልቡን ወያኔ በተወረወረለት አጀንዳ ላይ በመራኮት፣ እርስ በርስ እየተባላ የትግል ግዜውን ያባክናል። ባለፈው አንድ ዓመት መጠነ ሰፊ የሕዝብ ተቃወሞ ያደናገጠው ወያኔ፣ ለመሰረታዊው ጥያቄ መልስ ሳይሰጥ፣ በልዩ ጥቅም መብት ሽፋን አዲስ የማደናገሪያ አጀንዳ ይዞ ብቅ ብሎአል። ለእሩብ ክፍለ ዘመን ያህል ሲሰራበት የነበረውን የከፋፍለህ ግዛው ስልት ያልተገለጸላቸው አንዳንድ ጽንፈኛ ወገኖች (ethno-chauvinist) ከወያኔ የተወረወረውን አቅጣጫ ማስቀየርያ አጀንዳ በመቀበል፣ ከሥርዓቱ የበለጠ በማስተጋባት ላይ ይገኛሉ።

በሕዝቦች እኩልነት እና መፈቃቀር ላይ የተመሰረተ የጋራ ማኅበረሰብ እንገነባለን የሚለውን ስብከት ላደመጠ፣ በተቃራኒ እንዲህ አይነት ቁርሾ ቆስቋሽ ድርጊት ጋር እንዴት እንደሚጣረስ ማን በነገራቸው። የዚህ የእብደት ጉዞ መዳረሻው ሌላ ምንም ሳይሆን እልቂት ብቻ ነው። ትላንት በዳር አገር የተፈጸመው ግፍ አልበቃ ብሎ፣ ዛሬ በመሃል አገር ለመድገም የመወራጨት ምን የሚሉት ብልግና እንደሆነ እናንተው መልሱ። የአዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ መስፋፋትን አምርረው ሲቃወሙ የነበሩ “ጥቂት የኦሮሞ-አክቲቪስቶች”፣ (militant oromo ethno chauvinist) የንጹሃን ደም ከፈሰሰ ዓመት በኋላ ከተማዋ ራሷ የእኛ ነች በሚል መፈክር ዙሪያ መንቀሳቀሳቸው ምን ያህል አላማ የለሽ እንደሆኑ አመላካች ነው።

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ የተጠቃሚነት መብት ለመደንገግ ተረቀቀ የተባለው አዋጅ ለአዲስ አበባም ሆነ ኦሮሚያ ለሚባለው ክልል፣ እንዲሁም በጠቅላላ የአገሪቱ ህልውና ላይ የሚኖረው አሉታዊ እንደምታ ቀላል እንደማይሆን ከወዲሁ መናገር ይቻላል።

ሲጀመር ረቂቅ አዋጁ ከአምስት ሚልዮን በላይ የሚገመተውን የአዲስ አበባ ነዋሪን መብት አልባ ያደረገ ብቻ ሳይሆን እንደሌለ በመቁጠር ህልውናውን የካደ ነው። በነገራችን ላይ አምስት ሚልዮን የሕዝብ ቁጥር፣ የአንድ ሉዓላዊ አገር ሕዝብ መሆን ይችላል። በመቀጠል ከተማውን አዲስ አበባ ያሰኙ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ- ሰብዓዊ ሁኔታዎች መኖራቸውን ከግምት ውስጥ ያላስገባ አንዳንድ ጠባብ ብሔረተኞች መርቅነው ባነሱት የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ላይ የተመሰረተ ነው። በደምሳሳው የአዋጁ መነሻ መንፈስ ከተማውን ሰው-አልባ (no-mansland) ባዶ የሆነ መሬት እንደሆነ በመቁጠር የተረቀቀ እንደሆነ መናገር ይቻላል። ሌላው የአዋጁ መንፈስ በከተማው ውስጥ ባለሁለት ደረጃ ዜግነት ለመፍጠር ያለመ ዘረኛ እና አግላይ ነው። ሰወች በአንድ አገር ዜጎች በመሆናቸው ብቻ ማግኘት የሚገባቸውን መብት እና ጥቅም፣ ለዚህኛው ብሔር ልዩ የሆነ የተጠቃሚነት መብት ይሰጠው ብሎ በአዋጅ መደንገግ፣ መብትን ከአንዱ ነጥቆ (Disposseing) ለሌላለው የመስጠት ጸረ-እኩልነት ድንጋጌ ነው። 2 የዚህ ልዩ ጠጠቃሚነት መብት ጉዳይ ወደ አገራችን ፖለቲካ የገባው የደርግ መንግሥት ወድቆ ሕወሓት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጋር በአጋርነት በፈጠረው የድህረ-ደርግ አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ (Post-Derg New political arrangement) መሰረት ነው። አላማው ሕወሓት በመሃል አገር ሊነሳበት ይችላል ብሎ የገመተውን ተቃወሞ ለማዳከም፣ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጋር ስልታዊ አጋርነት (tactical alliance) በመፍጠር ሥልጣኑን ማረጋጋት ነበር።

በዚህ የፖለቲካ ስሌት መነሻነት ነው፣ ዛሬ በአገራችን የሚሰራበትን የክልል አወቃቀር በሁለቱ የብሔር ነጻ አውጪዎች መሃከል በተደረገ ድርድር (ፖለቲካዊ ሰጥቶ መቀበል) የተቀረጸ መሆኑን ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል። የሚገርመው ነገር ከ80 በላይ ብሔር እና ብሔረሰብ ባለበ አገር ውስጥ፣ የተፈጸመው ይህ አግላይ ስምምነት ኢ-ዲሞክራሲያዊ ብቻ ሳይሆን፣ በአገራችን እየተከሰቱ ላሉ የጎሳ ግጭቶች መነሻ ምክንያት ሆኖአል። በዚህ ስምምነት ሕወሓት የትግራይን ክልል ከተከዜ አሻግሮ የወልቃይትን እና የሰሜን ወሎ ወረዳዎችን መጠቅለል ቻለ። በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ኦነግ ያቀረበው የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ተግባራዊ ተደረገ። በሂደቱ የአዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ይካተትልኝ የሚለው የኦነግ ጥያቄ አወዛግቦ እንደነበረ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ያስታውሳሉ። ሕወሓት ከኦነግ ጋር የፈጠረውን ስልታዊ አጋርነት ላለመጉዳት በአዲስ አበባ ላይ የኦሮሞ ክልል ልዩ መብትን በተመለከተ ወደፊት በሕግ ይደነገጋል በማለት እንዲታለፍ ተደረገ። ከዓመት በኋላ ሥልጣኑን በመሃል አገር ያረጋጋው (power consolidate) ሕወሓት፣ ኦነግን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ብቸኛ ተአገሪቱ ገዠ ለመሆን ሲበቃ የልዩ መብት ጉዳይ ወደ ጎን እንዲገፋ ተደረገ። የሚገርመው በዚህ ሁሉ ድርድር ውስጥ የአዲስ አበባም ሆነ የተቀረው የአገሪቱ ሕዝብ የተጠየቀውም ሆነ የሚያውቀው ነገር አለመኖሩ ነው። እንግዲህ ከዛ ወዲህ ነው ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጋው የአዲስ አበባ ነዋሪ መሪዎቹን መምረጥ እንዳይችል በእጅ አዙር የሕግ ክልከላ ውስጥ የሚገኘው።

እዚህ ጋር መነሳት ያለበት ሌላ ጥያቄ በእርግጥ ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ሆና ሳለች፣ ሁለት ጽንፈኛ የብሔር ነጻ አውጪዎች የሁላችንንም እጣ በሚወስን ጉዳይ ላይ የመወሰን መብት (ከጉልበት በስተቀር) እንዴት ሊኖራቸው ቻለ። ከሕግ፣ ከሞራል እና ከታሪክ አንጻር ተቀባይነቱ እስከምን ድረስ ይሆናል?፣ በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ መልስ ማግኘት ያለባቸው ጥያቄ ስላሉ፣ እራሱን በቻለ ሌላ ርእስ መዳሰስ ያለበት ሰለሆነ እዚህ ጋር ገታ አድርገን ወደተነሳንበት የአዲስ አበባ ጉዳይ እንመለስ።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ከሆነች 130 ዓመታት አስቆጥራለች። በዚህ ከአንድ ክፍለዘመን በላይ ጉዞ ከተማዋ ብዙ ወጣ ውረድ እና ስኬቶችን አስመዝግባለች። እንደማንኛውም የዓለም ከተማ አዲስ አበባ ከነበረችበት ትንሽ መንደርነት፣ ወደ ትልቅ ዓለም አቀፍ ከተማነት የማደግ ግስጋሴዋን ቀጥላለች። የዛሬ መቶ ሰላሳ ዓመት በፊት ከነበረችበት በተለየ የራሷ ባህል፣ ቋንቋ እና ስነ-ልቦና በማዳበር የኢትዮጵያ አገራዊ ፕሮጀክት ነጸብራቅ ሆናለች። የኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ማእከልነቷ ባጎናጸፋት እድል የተነሳ ከተማዋ ዓለም አቀፍ ይዘትን በመላበስ ላይ ነች።

ከዚህ ሁሉ ጉዞ በኋላ፣ እዚህ ላይ የደረሰችውን የከተማ እድገት ነው፣ የዛሬዎቹ ጽንፈኛ ጠባብ ብሔረተኞች (militant oromo ethno chauvinist) ጉዞዋን የሁዋሊዮሽ በመመለስ ወደ ጎጥ መንደርነት ለመመለስ እየታተሩ የሚገኙት። እዚህ ላይ ሕወሓታውያን እና ኦነጋውያን እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ተደጋግፈው የመሄድ ብዙ ልምድ እንዳላቸው ማስተዋል ይገባል። የዚህ ምክንያት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ አገራዊ ፕሮጀክት ራእይ መፈጸሚያ በመሆንዋ፣ ጽንፈኛ ጠባብ ብሔረተኞች ዋነኛ የጥቃት ኢላማቸው በማድረግ ሊያከስሟት እየሰሩ ነው። ይህ 3 ድርጊታቸውም በከተማዋ ውስጥ የሚንጸባረቀው ህብረ ብሔራዊነት ( multi-cultural cosmopolitanism) ላይ የተቃጣ አደጋም ነው። ስለዚህም ነው፣ በሥልጣን ላይ ያለው ሕወሓት፣ ጠባብ የኦሮሞ ብሔረተኞችን ከፈለገ ያስፈራራቸዋል፣ ወይንም ያስፈራራባቸዋል።

አክራሪ የኦሮሞ ብሔረተኞች (militant oromo ethno-chauvinists) በወያኔ ተረቆ የቀረበውን ድንጋጌ እንደወረደ ከመቀበል አልፈው፣ ያንሰናል ይጨመርልን በማለት የሚያነሷቸውን ክርክሮች ላየ ዘረኝነት በአገራችን ላይ እየጋረጠ ያለውን አደጋ መገንዘብ ይችላል። አዲስ አበባ የከተመችበት መሬት የኦሮሞ ተፈጥሮአዊ ግዛት ነው፣ የሚለው መነሻ በራሱ አሳፋሪ እና አንገት የሚያስደፋ አስተሰሳሰብ ነው። በሰው ልጆች ማኅበረሰብ እድገት ታሪክ ሕዝቦች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመዘዋወር ህይወታቸውን ይገፉ እንደነበር እንረዳለን። አንድ ሕዝብ በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ተዘዋውሮ መኖሩ ያለ እና የነበረ ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክም ከዚህ የተለየ አልነበረም። በተለይ ከ15ኛው ክፍለዘመን ወዲህ የአርብቶ አደር የአኗኗር ዘይቤ ይከተል የነበረው የኦሮሞ ማኅበረሰብ በተከታታይ 8 ገዳዎች ባደረገው መስፋፋት፣ ከባሌ ጫፍ ተነስቶ ወደ ሰሜን እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ተሰራጭቶ መኖር እንደጀመረ በታሪክ እና አርኪዮሎጂ መረጃዎች ጭምር የተረጋገጠ ሃቅ ነው። በዚህ መነሻነት ዛሬ የምንኖርባት ኢትዮጵያ ላይ ሰፍረን የምንገኝ ሕዝቦች ሁላችንም መጤ ልንባል የምንችል እንጂ አንዱ ነባር፣ ሌላውን መጤ የሚያደርግ ምንም ሰማያዊ ሆነ ምድራዊ ማስረጃ የለም።

አንደ አፓርታይድ አይነት ሥርዓት ካልሆነ፣ ለመሆኑ በየትኛው የዓለም ክፍል ነው፣ አንድን ሕዝብ ነጥሎ የልዩ መብት ተጠቃሚ የሚያደርግ አዋጅ ሲደነገግ ትክክል ተደርጎ የሚወሰደው። ኦሮሚኛ ተጨማሪ የስራ ቋዋንቋ መሆኑ ላይ የተነሳ ተቃወሞ አስካሁን አላጋጠመኝም፣ ቢሆን መልካም እርምጃ እንጂ የሚከፋ ወገን የለም። ይሁን እና የሌሎችን መብት ደፍጥጠን በልዩ መብት ስም የእኛን የበላይነት እንጭናለን የሚለው አስተሳሰብ ጤነኝነት ሊፈሽ ይገባል።

የአዋጁን መውጣት ተከትሎ ጥቂት በሚባሉ አክራሪ የኦሮሞ ብሔረተኞች (militant oromo ethno-chauvinists) የተንጸባረቀው ሃሳብ የአዲስ አበባ ሕዝብ ይህን ባይቀበል የሚጠጣውን ውሃ እናቆምበታለን፣ አምስቱምን የከተማይቱ በሮች ዘግተን ምግብ እንዳይወጣ እና እንዳይገባ በማድረግ እናምበረክከዋለን የሚሉ እንደነበሩ ታዝበናል። ይህ አይነት አክራሪ አስተሳሰብ በዩገኦስላቪያ የተከሰተውን እልቂት የሚያስታውሰን ሲሆን፣ አዲስ አበባንም የአፍሪካዋ ሳራየቮ በማድረግ የሚጠናቀቅ እንደሚሆን ካሁኑ መተንበይ ይቻላል። ወደ አዋጁ ስንመለስ ግልጽነት ጎደለው በብዙ አሻሚ አንቀጾችን የታጀለ እና ወደፊት ለሚነሱ ውዝግቦች በር የከፈተ እንደሆነ ገና ከአሁኑ የሕግ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን መስጠት ጀምረዋል። ልዩ መብት የሚለው የሕግ ሃረግ በራሱ የሚፈጥራቸው ለትርጉም አሻሚ የሆኑ ውዝግቦች የበዙ ናቸው።

የዚህ ሁሉ አዋጅ እና ልዩ-መብት ጥቅም እንድምታው ስንመለከት ትላንት በዳር አገር ሲፈጸም የነበረውን ብሔርን መሰረት ያደረገ እንግልት እና ማፈናቀል በመሃል ሀገር ለመድገም ነው። የማስታዎስ አቅማችን ካልደከመ በስተቀር፣ ከዛሬ 25 ዓመት ጅምሮ በሃረር-በደኖ፣ አርሲ-አርባጉጉ፣ ወለጋ-ጊዳኪራሞ፣ ጋሙ-ጎፋ ቤንችማጂ የመሳሰሉ ቦታዎች መጤ እና ነፍጠኛ ሰፋሪ ተብለው የተፈናቀሉ ወገኖች ስፍር ቁጥር የላቸውም። አውሮፓ እና አሜሪካ በጥገኝነት እየኖሩ፣ በዚህ ክልል የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች መጤ ሰለሆኑ ይውጡልን ወይንም ሁለተኛ ደረጃ ዜግነታቸውን ተቀብለው ይኑሩ ማለታቸውን መስማት ምጸት ነው። በተለይ ባሳለፍናቸው 25ዓመታት ኦሮሚያ 4 በሚባለው ክልል ነዋሪ የነበሩ ኦሮሞ ባልሆኑ ሌሎች የአገራችን ዜጎች ላይ የደረሰው በደል እና የተፈጸመው ግፍ ከብዙዎቻችን ህሊና ባልጠፋበት ሁኔታ፣ ድርጊቱን በአዲስ አበባ ለመድገም ዳርዳርታው ነቅተን እንድንጠብቅ ይገበባል።

አገራችን የባህር በር አጣች፣ ድንብሯ ተደፈረ ወዘተ ... ስንል፣ ዛሬ ዋና ከተማዋን የማጣት አደጋ ውስጥ የገባችበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። ሥልጣን ካጣን አባልተናችሁ፣ አዲስ አበባንም ለኦሮሞ ሰጥተን ወደትግራይ እንሄዳለን የሚለው የወያኔ ዛቻ መፈጸሚያው ቀን የደረሰ ይመስላል።

ለማጠቃለል በአንድ በኩል ሕዝባዊ ተቀባይነቱን ያጣ መንግሥት እና በሌላ በኩል በዘር ፖለቲካ ሰክረው ዘረኝነትን እንደ እኩልነት መብት በመውሰድ ኢትዩጵያን እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን አተራማሸ የሆነ አጀንዳ በመግፋት ላይ ያሉ አንዳንድ ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ቆም ብለው እንዲያስቡ ይመከራሉ። ሕግም ሆነ ሌላ የፖለቲካ ስምምነት መደረግ ያለበት ጥቂት ጠባብ ብሔረተኞች በሚያቀርቡት የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ላይ ተመስርቶ ሳይሆን፣ የሚመለከተው ነዋሪ ሕዝብ አውቆት እና ተወያይቶበት መሆን አለበት። ይህ ባልሆነበት እና አንዱን ለመጥቀም ሌላውን ለመጉዳት (Disposseing) መነሻ በማድረግ የሚወጣ ሕግ ፖለቲካዊ እንድምታው ከኢትዮጵያ አልፎ ለታላቁ የአፍሪካ ቀንድ የሚተርፍ መዘዝ እንዳለው መገንዘብ አስተዋይነት ነው። 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!