ግርማ ካሳ

ከአራት መቶ ዓመታት በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያ የሚያሳዩ ካርታ
ከአራት መቶ ዓመታት በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያ የሚያሳዩ ካርታ። በካርታው እንደምናየው ሸዋ የሚባል አካባቢ መሐል ላይ እናያለን። በምዕራብ ወሎም “አምሃራ” የሚባል ቦታም ነበር። ግን በጣም ትንሽ ቦታ ነበር፤ አሁን አማራ የሚባለው አልነበረም። ኦሮሚያ የሚባለው አንድ ቦታ አይታይም።

አዲስ አበባንና በዙሪያዋ ያሉ የሸዋ ዞኖችን ያካተተ አዲስ ክልል የመኖሩን አስፈላጊነት በተመለከተ ከዚህ በፊት አንዳንድ ጽሁፎችን ለንባብ ማብቃቴ ይታወቃል። ለደረሱኝ በርካታ የድጋፍና የማበረታቻ መልዕክቶች ያለኝም ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ። በርካታ ጸሐፊያንም የሸዋን ክልል አስፈላጊነት መጻፍና ግፊት ማድረግ መጀመራቸውም አስደሳች ነው።

ሆኖም ግን ሸዋ ራሷን የቻለች ክልል እንዳትሆን የሚፈልጉ ቡድኖች እንዳሉ መረሳት የለበትም። ለዚህም ነው በዚህ ዙሪያ በተደራጀ መልኩ ትግልና ግፊት መደረግ ያለበት። በተለይም የሸዋ ሕዝብ።

አንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶች የሸዋ ክልል መኖሩን አምረው ይቃወማሉ። ያም ለኦሮሞው ጥቅም ከማሰብና ከመቆርቆር ሳይሆን ኦሮሚያ የምትባለው ክልል ልትጠፋ ነው ከሚል ነው። ከዚህም የተነሳ “ኦሮሚያን” ከኦሮሞ ጋር በማገናኘት ይሄንን ሃሳብ በማቅረባችን “ፀረ-ኦሮሞ” ሊሉንም ይዳዳቸዋል። አንድ የዘነጉት ነገር ቢኖር ግን ኦሮሚያ የሚባል ነገር ከ26 ዓመታት በፊት ኖሮ የማያውቅ መሆኑን ነው። በአንጻሩ ግን ሸዋ ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት የነበረ ነው።

ወደ ሕወሓቶች ስንመጣ፤ ኦሮሞውም፣ አማራውም፣ ጉራጌውም፣ ድብልቁም፣ ሁሉም እኩል የሆኑባት አዲስ አበባን የምትመሥል፣ ሰፋ ያለች ክልል ተፈጠረች ማለት፣ የዘር ፖለቲካቸው ሥርዓታቸው ተናጋ ማለት ነው። ሕዝብ በዘር ላይ ሳይመሰረት መተያየት ከጀመረ፣ መደጋገፍ፣ መቀባበል፣ መያይዝ ይጀምራል። ያ ደግሞ ለነርሱ ሥልጣን ያሰጋቸዋል። በሥልጣን ለመቆየትም ሲሉ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ እያሉ የግድ መከፋፈል አለባቸው።

በሸዋ ያለው የኦሮሞ ማኅበረሰብ በሸዋ ካለው ከተሜው ጋር እድል ፈንታው የተያያዘ ነው። የሸዋ ኦሮሞ አክቲቪስቶች፣ በኦሮሞ ስም፣ በኦነጋዊያን፣ ለተረጨው የዘረኝነትና የጥላቻ ወሬ ጆሯቸውን ዘግተው፣ በአብዛኛው በገጠር የሚኖረውን የሸዋ ኦሮሞ ሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄና ጥቅም የሚያስጠብቅ ሥራ ነው መስራት ያለባቸው። ከነጃዋር፣ ከነጸጋዬ አራርሳ፣ ከነ አሰፋ ጀላታና ከመሳሰሉት ጋር አብሮ መንጎድና የኦሮሞው ማኅበረሰብ ከሌላው ጋር ማጋጨት፤ በተለይም የሸዋን ኦሮሞ የሚጎዳ ነው። ጎድቶታልም። የሸዋ ኦሮሞ ጥያቄና ጥቅም የሚከበረው በዋናነት የሸገር አዲስ አበባን፣ የአዳማን፣ የቢሾፍቱን፣ የዝዋይን … በአጠቃላይ የከተሜውን ሕዝብ antagonize በማድረግ ሳይሆን፤ ከከተሜው ጋር በመተሳሰር ነው።

አሁን ያለችዋ የኦሮሚያ ክልል በሸዋ ያሉ ከተሞች የሚኖረውን አፋን ኦሮሞ የማይናገር ማኅበረሰብ የምትወክል ክልል አይደለችም። የኦሮሞዎች ብቻ የሆነች ክልል ናት። ያ ደግሞ ተቀባይነት አይኖረውም። የዘር ግጭቶችን ጥላቻን ነው የፈጠረው።

እኛ ግን በጥላቻ ምትክ ፍቅር፣ በልዩነት ምትክ አንድነት፣ “ኦሮሞ፣ አማራ ...” በመባባል ምትክ በዜግነት መከባበርን፣ እንደ ድሮው ሥርዓት አማርኛ ብቻ ይሁን ወይንም አሁን በኦሮሚያ እንዳለው አፋን ኦሮሞ ብቻ ይሁን በሚለው ምትክ አፋን ኦሮሞም አማርኛም የሥራ ቋንቋዎች ይሁኑ የሚል፣ አስማሚ ሃሳብን ነው እያቀረብን ያለነው። የሸዋ ክልል መኖሩ በሸዋ ያሉ ሌሎች ማኅበረሰቦችም መብታቸው እንዲጠበቅ ከማድረግ ባሻገር፣ በሸዋ ያለውን የኦሮሞ ማኅበረሰብ የኢኮኖሚንም ጥቅም የሚያስጠበቅ ነው። የሸዋን ጉዳይ በዋናነት የሚመለከተው የሸዋ ነዋሪው ነው። እንጂ ከነጆና ከበደኖ የመጡ በሸዋ ጉዳይ ሊወስኑለት አይችሉም።

ሕወሓት በሥልጣን እስካለ ድረስ የሸዋ ክልል እንዲኖር ስለማይፈቅድ፤ የአዲስ አበባን ሕዝብ ጨምሮ የሸዋ ሕዝብ በወልቃይት ኮሚቴ አቋቁመው ሲንቀሳቀሱ እንደነበሩት፣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጀመር አለበት። በሕገ መንግሥቱ መሰረት ሕዝቦች የራሳቸውን ክልል የመመስረት መብት አላቸውና የሸዋ ሕዝብም ከኦሮሚያ መውጣት ከፈለገ፣ ያ ሙሉ መብቱ መሆኑ መታወቅ አለበት።

Ethiopian Map, 400 years ago (ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብሮ የተያያዘ አንድ ካርታ አለ። ከአራት መቶ ዓመታት በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያ የሚያሳዩ ነው። በካርታው እንደምናየው ሸዋ የሚባል አካባቢ መሐል ላይ እናያለን። በምዕራብ ወሎም “አምሃራ” የሚባል ቦታም ነበር። ግን በጣም ትንሽ ቦታ ነበር፤ አሁን አማራ የሚባለው አልነበረም። ኦሮሚያ የሚባለው አንድ ቦታ አይታይም)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!