ይገረም አለሙ

ሰሚ ጠፍቶ እንጂ- እዛም እዚህም ሰፈር

ቀድሞ የገባቸው አስጠንቅቀው ነበር፤

ለሁሉም አይቀሬ የሆነውና ክፉ ደግ ሀብታም ድሀ ምንዝር ባለሥልጣን ሳይልና ሳይለይ እኩል የሚወስደው ሞት በቅርቡ የነጠቀን አቶ አሰፋ ጫቦ ከመገናኛ ብዙሀን ጠፋ ብለው ሰነባብተው አላስችል ብሎአቸው ብቅ ሲሉ ትቼው ረስቼው አንደሚሉት መተው ሆነ መርሳት ይቻል ከሆነ ብዬ ልሞክር ጠፋ አልኩና አላስችልህ ብሎኝ እነሆ ብቅ አልኩ።

ለዚሀች አስተያየት መነሻ ወደ ሆነኝ ምክንያት ከመግባቴ በፊት ግን አቶ አሰፋ ጫቦን ባሰብኩ ቁጥር በአእምሮዬ ማህደር በመጀመሪያው ረድፍ ከተሰለፉትና ምላሽ ካጣሁላቸው ነገሮች ሁለቱን ላስታውስና በዚሁ ጋጣሚ የምታውቁ ንገሩኝ ልበል። ከሞታቸው ሳምንታት ቀደም ብሎ ምን አልባትም የመጨረሻው በሆነው ጽሁፋቸው ይመስለኛል አንድ ጽሁፍ ማዘጋጀታቸውን አብስረውን በቅርቡ ጠብቁኝ የሚል ት መልእክት ጽፈው ነበር። መልእክቱን እንዳላዛባ አንዳለ ኮፒ አድርጌ ላቅርበው።

“… “ያጋራ ቤታችንን” ጨርሼ በ10 ቀን ውስጥ አደባባይ አዋጣለሁ። አማራና ኦሮሞ የሚመለከት ነው የሚል Facebook ላይና ሌላም ቦታ ጠቃቀስኩ። ይህ እርግማንና ዘለፋ የተጀመረው ገና ባልታየ፤ ባልተነበበ ጹሁፍና አስተያየት ላይ ነበር። ያ ነው ይበልጥ የገረመኝ። ከማናውቀው ይሰውረን ማለት ይሆን ? ከምናውቀው ግን ከሸሸነው እውነት ሰውረን ነው? አውቀን የካንደነውን እውነት አታስታውሰን ማለት ይሆን? ይህንን ደህና ያጧጧፍነውን ሥራና ገበያ ይሻማብናል ማለት ይሆን? ሥራ ያሰኘኝ በተለየ አንዳንድ ዲያስፖራው ኗዋሪዎች መተደዳደሪያም ወደ መሆን የተቃረበ የሚያስመስል ፍንጭ ስለሚታይ ነው። በተፈጠረው የሕዝብ አመጽ ሳቢያ ታዋቂ ሆነን፤ አገር አውቆን፣ ፀሐይ ሞቆን፤ አንቱ የተባልንበትን ልታፈርስብንም ነው የሚል ስጋት ፈጥሮ ይሆን? የሚል መላ ምት ይፈጥራል።”

በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በግልጽ የሚታይ ነገር አለ የሚያጋግር የሚያደናግር። እሱን አልሄድበትም። ነገር ግን በ10 ቀን አወጣዋለሁ ያሉት ጽሁፍ አለመውጣቱ ይልቁንም ገና ለአደባባይ ሳይበቃ ለዛቻ የዳረጋቸው ጽሁፍ ሳይወጣ እርሳቸው በሞት መለየታቸው ይህን ተከትሎም ስለ አሟሟታቸው የተጻፈው አጠራጣሪ ነገር ከዛም ነገሮች ተድበስብሰው መቅረታቸው ማለትም የተጻፈው እውነት ከሆነ ገፍቶ አለመውጣቱ ካልሆነም አለመስተባበሉ አገጣጥመው ሲያቡት ለአቶ አሰፋ ባለ ቅርበት ርቀት ሳይሆን አንደ ሰው ይከነክናል። ምን አልባት ራቅ ብዬ ስለነበር የጠቀስኳቸው ሁሉ ተጽፈው ተነግረው እኔ ሳልሰማ ከሆነ ይቅርታ።

ሌላው የእርሳቸው መሞት በቀጠሮ ያቆዩትን ጽሁፍ ለአደባባይ ለማብቃት የሚገድ አይደለም፤ እንደውም ዪገፋፋ ነበር የሚሆነው፤ ግን አልሆነም ለምን? ጽሁፉን ያገኘው ሰው ሳይኖር ቀርቶ ነው ወይንስ እንዲወጣ ባለመፈለጉ ይሆን ልናየው ያልቻልነው የሚል ጥያቄ ውስጤ ያጫርል። የጽሁፉ ይዘት ምንነትና እንዴትነት በራሱ የሚሰጠው ምልከታ ይኖር ነበር፤ አሁንም ቢሆን ከአቶ አሰፋ ጋር አብሮ አልተቀበረምና የቱንም ያህል ብቸኛ ናችው ቢባል ይህን ያህል ነጠላ ናቸው ብሎ መገመት አይቻልምና በቅርብ የነበራችሁ ጓዳ ጎድጓዳቸውን የምታውቁ ሰዎች ይህን ጽሁፍ ለአደባባይ ታበቁት ዘንድ የህሊና ጥያቄ የሞራል ግዴታ ያለባችሁ ይመስለኛል።

ልመለስ፣ መጻፉንም ማዳመጥ ማንበቡንም ትቼው ረስቼው ከራርሜ ሀሙስ ነሀሴ 11/2009 ዓም የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮን ሳዳምጥ አንድ ሰው ፈጥነው ታወሱኝ። ብዙዎቻችሁ እንደምታስታውሱት ርግተኛ የምሆነው በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በሚመራው የሕገ መንግሥት አርቃቂ ነው አጽዳቂ ይባል በነበረው ጉባኤተኛ መካከል ሁለት የተለዩ ሰዎች እንደ ማጣፋጫ ቅመም ይታዩ ነበር፤ ከሁለቱ ደግሞ አንደኛው ይበልጥ ጎልተው ይታዩ የነበሩትና ዛሬ በሕይወት የሌሉት ሻላቃ አድማሴ ዘለቀ ናቸው ዜናውን ስሰማ ፈጥነው የታወሱኝ።

ርሳቸውን እንዳስታውስ ያበቃኝ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ዜና በአጭሩ እንዲህ የሚል ነበር። ሰውዬው አቶ ሙሳ አህመድ ይባላሉ፣ በኦሮምያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ጉርሱም ወረዳ የጸጥታና የተጎራባች ወረዳዎች ግጭት አስወጋጅ ቢሮ ሀላፊ ናቸው። በዚሁ ወረዳ በምትገኘው የትውልድ አካባቢያቸው ወደ ሆነችው ወረ-ጉየ ወረዳ አጃቢ ፖለሲ አስከትለው መኪናቸው በሾፌር እየተሸከረከረ ያመራሉ። ግና ካሰቡት ሳይደርሱ የሶማሊያ ክልል ልዩ ፖሊስ በአራት መኪና ይደርስና ፖሊሶቹ ወደ ባለሥልጣኑ ኪና በመጠጋት መሳሪያ ደግነው ከመኪናቸው በማወረድ ምን ልትሰራ ነው እዚህ የመጣህ እያሉ ወደ ጫካ ወስደው ያግቷቸዋል፡፤ አጃቢ የተባለው ፖሊሲ ሲያመልጥ እኒህ ባለሥልጣንና ሾፌራቸው ከ7- 10 ሰአት ድረስ ታግተው በፌዴራል ፖሊስ ቀጭን የስልክ ትዕዛዝ ለመለቀቅ በቅተዋል። ይህን የታናገሩት ራሳቸው ከራዲዮ ክፍሉ ጋዜጠኛ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው ነው። በዚሁ ዜና በርካታ ቀበሌዎች ለሶማሌ ክልል በመሰጠታቸው በአካባቢው ውዝግብ እንደቀጠለና የወረዳው ሽግሌዎች ለጠቅላይ ምኒስትሩ ቢሮ አቤት ለማለት አዲስ አበባ አንደሚገኙ ተዘግቧል።

ወያኔ አንድም ተረጋግቶ ኢትዮጵውያንን መግዛትና የአገሪቱንም ሀብት ለመዝረፍ ሁለትም ጸሀይ ጠልቃበት ሥልጣኑን ቢያጣ ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል እንዳትችል ለማድርግ የሚያስችለው የዘር ፖለቲካን ማስፋትና ማስፋፋት ሲችል መሆኑን አምኖ አቅዶና ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ሲያደርግ ብዙዎች በዝምታ፣ ከፊሎች ከጳጳሱ ቄሱ ሆነው ይህንን መንገድ በመከተል ወያኔ የዘራው ዘረኝነት ተመችቶች እንዲበቅል አብቦም እንዲጎመራ ተባብረናል።

የሶማሊ ክልል ፖሊሶች አድራጎትና የፌዴራል ፖሊስ ባላሥልጣን የተባሉትና በስም ያልተገለጹት ሰዎች በቀጭን ትዕዛዝ ማስለቀቅ መቻላቸውን በአንክሮ ካየነው፤ ወያኔ በዚህች አገር ላይ ያዘጋጀውንና በመጠባበቂያ ክርድነት እየተጠቀመበት ያለውን የዘረኝነት አደጋ በግልጽ የሚያሳይ ነው። የዘረኝነቱ አደጋ የከፋ መሆኑን የምንረዳው ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ በስልክ ትዕዛዝ አስለቀቀኝ ከሚለው የአቶ ሙሳ መግለጫ አንጻር ስናየው ነው። በዚህ ሁኔታ በየቦታው ዘረኝነትን ተላብሰው የተቀመጡት ሰዎች ወያኔ አዲስ አበባ ሆኖ በርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ የሚያንቀሳቅሳቸው መሆናቸው ነው ድርጊቱ የሚነግረን። እነዚህን ሲፈልገው ጃስ እያለ ለንክሻ ያሰማራቸዋል፤ ሲለው ከሁለቱም ወገን በማነሳሳት ግጭትና ጦርነት እንዲፈጠር ያደርጋል የሚፈልገውን ሲያሳካ እንደ ስፖርት ውድድር በፊሽካ ያቆመዋል አለበለዚያም ገላጋይ መስሎ ይገባል አስታራቂ ሆኖ ስምግልና ይቀመጣል። በዚህ ሁኔታ የተፈጸሙ ግጭቶች መለስ ብሎ ማስታወስ ነው። ይህ አይነቱ ድርጊት ወያኔ ሥልጣኑን ቢያጣ ወደ ምን ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይመስለኝም፡አቶ በረከት ሰምኦን የመረጃ መስሪያ ቤት ሚኒስትር ሆኖ ግን አሉባልታ በጻፈበት መጽሀፉ ቅንጅቶችን እረፉ ከ9 መንግስት ጋር ነው የምትታገሉት ብለን ነገርናቸው ነበር ያለውን እዚህ ጋር አምጥተን አዳብለን ካየነው የዘር ፖለቲካው ለወያኔ ሥልጣን ማስጠበቂያ አንዱ የመጠባቂያ ካርድ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን እንረዳለን።

ታዲያ ነብሳቸውን ይማረውና እንደተከበሩና እንደ ተደነቁ የሞቱትን ሻላቃ አድማሴን ከዚህ ጋር ምን አገናኛቸው ትሉ ይሆናል፣ አዎ የራዲዮኑን ዜና ስሰማ ፈጥነው የታወሱኝ ምስል ንግግራቸው ጭምር በአይነ ህሊናየ ድቅን ብሎ የታየኝ እኒህ ሰው ብዙዎች በወቅቱ የፖለቲካ ስካር ውስጥ ሆነው ከወያኔ በላይ ዘረኝነቱን እያቀነቀኑ ባሉበት ወቅት ተው ይሄ ነገር አያዋጣም ያሉ ይህን በማለታቸውም በልተጋራ ምላስ፣ ባልታረመ ቃል ብዙ የተባሉ ናቸውና ከዜናው ጋር መገናኘታቸው። በዛ ከሁለት ሰዎች በስተቀር በአንድ ሳንባ የሚተነፍሱ የሚመስሉ ሰዎች በተሞሉበት አዳራሽ ይክልሎችን ስያሜ የያዘው የህገ መንግስቱ ክፍል ላይ ውይይት ሲደረግ በቴሌቭዥን እንዳየነው ሻለቃ እጃቸውን አወጥተው እባካችሁ ወንድሞቼ እህቶቼ በሚል ተማጽኖ የጀመሩትን ንግግር ጌቶቼ ወደ ሚል ልመና አሸጋግረው ግድ የላችሁም ነገ የሚሆነው አይታወቅም ሲሆን ሲሆን ይህ አይነቱ አሰያየም ቢቀር አይሆንም ካላችሁ ደግሞ የሶማሊ ክልል ከምትሉት የኢትዮጵያ ሶሜሌ ክልል ብትሉት ብለው በመማጸናቸው ከኢሰፓ እስከ ነፍጠኛ ከድሮ ስርአት ናፋቂ እስከ የብሄር ብሄረሰብ ህዝቦችን መበት የማይቀበል ወተ እሰከሚል የደረሰ ውርጅብኝ ነበር የወረደባቸው።

ዛሬ በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ታፋኘየ ተደበደብኩ ያሉት የኦህዴዱ ሰው አቶ ሙሳ ያኔ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንደነበሩ ባላውቅም የህውሀት ተባባሪ በመሆን ድርጅታቸው የዘራውን የዘረኝነት መርዝ ትንሽም ቢሆን አደጋውን ለማየት የሚያስችል ፍንጭ አሳይቶአቸዋለ። ህሊናቸውን ሆዳቸው ካልሸፈነው።

የአቶ ሙሳ አህመድን መታገት መደብደብና መንገላታት ሰምቶ ይበለው የእጁን ነው ያገኘው የሚል ካለ የጨው ገደል ሲናድ ሞኝ ይስቃል ብልህ ያለቅሳል የሚለውን ብሂል ሊያታስውስ ይገባዋል። በየቦታው በወያኔ የተቀመጡና በሚሰጣቸው መመሪያ ዘረኝነትን እየኮተኮቱና ውኃ እያጡ የሚያሳድጉም ቢሆኑ አደጋው ለእነርሱም የሚተርፍ መሆኑን ከአቶ ሙሳ መማር ቢችሉ ለአገርና ለህዝብ የሚለው ቀርቶ ለራሳቸው ሕይወት መድህን መሆን ይችላሉ፤ ዛሬ ምንም በሌለበት አግቶ ጫካ ማስገባት ከመጣ የህውሀት ሥልጣን አደጋ ላይ ቢወድቅ እነዚህ ጃስ የሚባሉ አውሬዎች ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይህ በአቶ ሙሳ የደረሰ ነገር የረሳነውን ማስታወሻ ማንቂያ ደወል ይመስለኛል፡፤

ወያኔ ዓላማና ፍላጎቱን በግልጽ ከመናገር የቦዘነበት ግዜ የለም። በደም መስዋዕትነት የያዝነው ሥልጣን በእኛ እጅ ብቻ መቀጠል አለበት፣ እኛ አውራ ፓርቲ ደረጃ ላይ ደርሰናል፣ ከፈለጋችሁ ታማኝ ተቀዋሚ ሆናችሁ በመሰራታዊ ጉዳይ ሳይሆን በአፈጻጸም ጉድለት ላይ እየተቃወማችሁ መኖር ትችላላችሁ፣ ይህን አንቀበልም ካላችሁና ሥልጣናችንን ከተቀናቀናችሁ እኛ ሥልጣን ባጣን ማግስት ኢትዮጵያ የምትባል አገር አትኖርም ብሎናል፤ የእለት የእለቱን እያልን የትናንቱን እየረሳን እንጂ። ይህን ሲል ደግሞ ዝም ብሎ ላለመሆኑ የጽጥታ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ሰው አቶ ሙሳ በራሳቸው ግዛት በሆነው ወረዳ ላይ ተቀምጠው ማእከል ላይ ካሉ ወያኔዎች ቀጥተኛ ትዕዛዝ በሚቀበሉ ፖሊሶች የደረሰባቸው ድርጊት በቂ ማሳያ ነው። ወያኔዎች ሥልጣናቸውን እንደሚያጡ ርግጠኛ በሆኑ ቅጽበት ጃስ ብለው የሚያስነሱዋቸው ኃይሎች ማሳሪያ አስታጥቀው የዘርኝት መርዝ በደማቸው አሰራጭተው በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ማስቀመጣቸውን ለመገንዘብ በዚህ ጽሁፍ የተገለጸውና በአሜሪካ ደምጽ ራዲዮ የቀረበው ዜና ብቻውን በቂ ነው።

ለሥልጣን ሳይሆን ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ አብቦ እንዲፈካ የማየት ህልሙ ያላቸው እውነተኛ ታጋዮች ትልቁ ችግር ወያኔን ማስወገዱ ሳይሆን ከወያኔ በኋላ ስለምትኖረው ኢትዮጵያ ማሰብ መጨነቁ፣ ማቀድ መስራቱ ነው የሚሉት ይህን የወያኔ ካልበላሁት ጭሬ አፈሰዋለሁ እኩይ ፖለቲካ በመረዳታቸው ይመስለኛል። ዘረኝነት አደጋው ለሁሉም ነው የሚተርፈው.ተቀዋሚ ደጋፊ፣ አባል ነቃፊ ገለልተኛ መስሎ አዳሪ አይልም አይለይም። ያ ቢሆን የኦህዴዱ ሰው አቶ ሙሳ በተራ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ጫካ ተወስደው ባልታገቱ ነበር። እናም ጎበዝ ሳይቃጠል በቅጠል በማለት ዘረኝነት የወያኔ መጫወጫ ካርታ እንዳይሆን ነቅተን መጠበቅ፣ ተግተንም መስራት አንድነት ፈጥረንም ማምከን ይኖርብናል። እሳትና ጭድ የሚለውን የአቶ ጌታቸውን ከአፍ አምልጦ አፋፍ የዋለ ንግግር ማሳታወሱም ጠቃሚ ነው። ለዚህ ደግሞ ከፊታችን የሚጠብቀንን የዘመን መለዋጫ የቁጥር ለውጥ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ የአቋምና የድርጊት ለውጥ የምንጀምርበት አናድርገው። 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!