በቀለ ደገፋ (ከኦስሎ፣ ኖርዌይ)፣ ጳጉሜን 2009 ዓ.ም.

ሕወሓት/ወያኔ
ለ26 ዓመታት ሥልጣንን የሙጥኝ ይዞ ያለው ወያኔ/ሕወሓት

ወያኔ ሥልጣንን የሙጥኝ ይዞ አገራችንንና ሕዝቧን ቁም ስቅል ማሳየት ከጀመረ እነሆ 26 ዓመታት ተቆጠሩ። ከጀሌዎቹና ፍርፋሪ ከሚበትንላቸው አጨብጫቢዎቹ ያለፈ እዚህ ግባ የሚባል የሕዝብ ድጋፍ ሳይኖረው፤ ይልቁንም በሕዝብ ተጠልቶና ተተፍቶ ከሩብ ምዕተዓመት በላይ ሥልጣን ላይ የመቆየቱ ነገር እንቆቅልሽ የሆነባቸው እጅግ በርካታ ናቸው። በአንፃሩ ሥርዓቱን ለማስወገድ በተለያየ አቅጣጫ የሚደረገው ትግል ውጤት አልባ መሆን ተስፋ አስቆርጧቸው የወያኔ ከወንበሩ መነሳት የማይታሰብ እንደሆነ የደመደሙም አልጠፉም።

ይህ ፅሁፍ የገዢው ቡድን የሥልጣን ዕድሜ እንዲህ የተንዘላዘለበትንና እስካሁን የተደረጉ የለውጥ ትግሎች ውጤት ያላመጡባቸውን ምክንያቶች እንዲሁም ወደፊት ወያኔን ለማስወገድ የሚደረጉ ትግሎች ከግንዛቤ ቢወስዷቸው መልካም የሚሆኑ ነጥቦችን ለመዳሰስ ይሞክራል።

ለወያኔ ዕድሜ መርዘም በቀዳሚነት መጠቀስ ካለባቸው ምክንያቶች አንዱ ቡድኑ በኢትዮጵያ ታሪክ የራሱና የግሉ የሆነ ፓለቲካዊ ስልትና አደረጃጀት ይዞ መምጣቱ ነው። ከቀድሞ ስርዐቶች በተቃርኖ የአገር አንድነትን ጉዳይ ጫማው ስር ጥሎና የዘር ፓለቲካን እስከጫፍ ለጥጦ ብቅ ላለው ወያኔ ብሔር ተኮሩ የጨዋታ ህግ ለከፋፍለህ ግዛ ሁኔታዎችን አሳምሮ ያመቻቸለት ከመሆኑም በላይ ሕዝብ ስለአንድነትና አብሮ መኖር እንዳይመክር የመግባቢያ ቋንቋውን አጥፍቶበታል። ወያኔን ሲታገሉ የነበሩና በመታገል ላይ ያሉ ኃይሎች ይህ ዘረኛ ቡድን ነፃ ላወጣህ ነው እያለ የፖለቲካ ትርፍ ያተረፈበትን ጥቂት የማህበረሰብ ክፍል ላለማስከፋት ባሰሉት የተሳሳተ ስሌት የወሮበላውን ስረ−መሰረታዊ ማንነት ከጫካ ህይወቱ ጀምረው ለሕዝቡ ብትንትን አድርገው አለማሳየታቸው ለስርዐቱ ከዚህ መድረስ ጉልህ ድርሻ አበርክቷል። ሌላው በቀላሉ ሊታይ የማይገባው ምክንያት በቁጥር አናሳ ቢሆኑም በትጋትና በታማኝነት ለወያኔ የጀርባ አጥንት የሆኑት አባላትና ደጋፊዎቹ የሚያደርጉት የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የሀሳብ፣ የታማኝነት፣ የስለላ፣ የማሰር፣ የመግደልና ሲያሻም በውጊያ የመሳተፍ ያላሰለሰ ድጋፍ ነው።

በተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በኩል በተደጋጋሚ የሚስተዋሉ ችግሮች ወያኔ አድጎ ለጉልምስና እንዲበቃ ካስቻሉት ባለውለታዎቹ መካከል ዋነኛ ለመሆናቸው አለመግባባት ይኖራል ብዬ አላስብም። በአገራችን የተካሄዱትንና በመካሄድ ላይ ያሉትን በርካታ ፀረ−ወያኔ ትግሎች ስናጤን የተቃዋሚው ኃይል ለዘረኛው ቡድን ብሔር ተኮር ፖለቲካዊ አደረጃጀት የሚመጥን በአግባቡ የተነደፈ አፀፋዊ ስልት አለማዘጋጀቱን መረዳት አይቸግርም። ለዚህ ዋናው ምስክር ወያኔ የያዘውን ዓይነት ወጥ የሆነና ህይወትን እስከመክፈል የሚያዘጋጅ ፍልስፍና ሳይኖራቸው በብሔር አልያም በአገር አንድነት ስም ለተቃዋሚነት እየተሰባሰቡ ብልጭ ድርግም የሚሉ ድርጅቶች መብዛት ነው። ባለፉት 26 ዓመታት የሕዝብን ሙሉ ድጋፍና ተቀባይነት አግኝተው ጎጠኛውን አገዛዝ ፈትኖ ለመጣል የተንቀሳቀሱ ድርጅቶች ቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ መሆንም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚጠቀስ ነው። ከተቃዋሚው ጎራ ጋር በተገናኘ በዋነኛነት የሚነሳው ሌላ ጉዳይ የፓለቲካ ድርጅቶች መተባበርና አብሮ መስራት አለመቻል ነው። እንደአሸን የበዙት የአገራችን የፓለቲካ ድርጅቶች በጋራ ለመስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ከመምከር ይልቅ የማያግባቧቸውን ነገሮች ማግኘት የሚቀላቸው ይመስላል። ለዚህም ይሆናል ከቅርብ ግዜ ወዲህ ጫፍ ላይ የደረሰው የልዩነትና የብሔረተኝነት ፖለቲካ በሌሎች አገራት እየታየ ያለውን መሰል የእርስ በርስ መተላለቅ ሊያስከትልብን ይችላል በሚል ስጋት የወያኔን በሥልጣን ላይ መቆየት ሳይወዱ በፍርሀት የሚመርጡ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ የመጣ የሚመስለው። የፓለቲካ ድርጅቶች መተባበር ለወያኔ እጅግ ከባድ የራስ ምታት፣ ለተቃዋሚው ጎራ የስኬት መንገድ ቀያሽ እንዲሁም ለሕዝቡ ሀይልና ተስፋ ለመሆኑ ቅንጅት ትልቅ ምሳሌ ነበር − በቅንጅት ውስጥ የተቀናጁት ድርጅቶች ከመሰባሰባቸው በፊት ብዙም ታዋቂ አልያም ተደማጭ አልነበሩምና። ይህ እንዳለ ሆኖ አገራችንን ከገባችበት አረንቋ ለማውጣት ሌት ተቀን የሚታገሉ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች የሚከፍሉት መስዋዕትነትና መላው ሕዝብ እየወረደበት ያለው የመከራ ዶፍ ወያኔ ሕዝብን የመተንፈሻ ቀዳዳ አሳጥቶና በፍርሀትና በኑሮ ውድነት ሸብቦ እየገዛ ያለው ዕድሜ ቀላል አለመሆኑን ይመሰክራሉ።

በዚህ ዘመን እንደኢትዮጵያ በተማሩ ልጆቿ የተከዳች አገር የሌለች እስኪመስል ድረስ የምሁሩ ክፍል በሀገሩ ጉዳይ ባይተዋርነትን መምረጡ አገራችን አሁን ያለችበት አስከፊ ሁኔታ ላይ እንድትወድቅ ትልቅ ድርሻ ያበረከተ አሳዛኝና የሚያስቆጭ ሀቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተደጋጋሚ የተፈጠሩ የፖለቲካ ክፍተቶችን በአግበቡ መጠቀም አለመቻላችን ወያኔን በወንበሩ ተደላድሎ እንዲቆይ ረድተውታል ብዬ አስባለሁ። ለማስታወስ የ91ዱ የወያኔ የውስጥ ክፍፍል (በመለስ አባባል መበስበስ)፣ የ97ቱ የምርጫና የተከተለው ግርግር፣ የመለስ ሞት፣ በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሳውና እስካሁንም ትኩሳቱ ያልበረደው የሕዝብ ተቃውሞ እንዲሁም ሌሎች መሰል ክስተቶች የፈጠሯቸውንና ያልተጠቀምንባቸውን መልካም አጋጣሚዎች መጥቀስ ይቻላል።

ከዚህ ሁሉ የምንገነዘበው በጥቂት ዘረኞች የምንገዛበትን ዘመን ለማብቃትና የነፃነት ነፋስ በአገራችን ለማንፈስ መሰራት ያለባቸው ስራዎች እጅግ በርካታ መሆናቸውን ነው። ይህ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተቃውሞው ጎራ የሚያካሄደውን እንቅስቃሴ የሚመለከት ይሆናል። እዚህ ላይ እስካሁን የተካሄደው የተቃዋሚዎች ትግል ያመጣው ምንም ፋይዳ የለም ለማለት ፈፅሞ እንደማይዳዳኝ አስረግጬ ማለፍ እወዳለሁ። በርካታ አገር ወዳድ ወገኖች የህይወት፣ የእስርና የስደት መስዋዕትነት የከፈሉባቸውንና ወያኔን ቁጭ ብድግ ያደረጉባቸውን ስራዎች አክባሪም አድናቂም ነኝ። ይህ ባይሆን ኖሮ አገራችን እስካሁንም እንደአገር ባልቆመች፣ ወያኔም በሕዝቡ ላይ ካደረሰው በላይ ስንት መዐት ባደረሰ ነበር። ነገር ግን መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች በአግባቡ ሳይሰሩ በቆዩ ቁጥር የሕዝብ ሰቆቃ እየባሰና ስርዐቱንም ማስወገድ ይበልጥ እያስቸገረ ይመጣልና በግልፅ መነጋገሩ መልካም ይሆናል።

ወያኔ ከሥልጣን ተወግዶ እውነተኛ የሆነ ለውጥ በአገራችን ሊሰፍን የሚችለው ሕዝብ የተሳተፈበት ትግል ሲካሄድ ነውና በተቃውሞው ጎራ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሕዝብን ተረድተው ወደሕዝብ የሚደርሱ መሆን አለባቸው። ለዚህም ብሔረተኝነትን ጋብ የሚያደርገና የወያኔን መሰረታዊ የፖለቲካ አሰላለፍ ከስሩ የሚያነቃንቅ እንቅስቃሴ መንደፍና መተግበር የግድ ይላል። ለዚህ ዋነኛውና አዋጪው መንገድ በሕዝቡ ውስጥ ተዳፍኖ ያለውን የኢትዮጵያዊነትና የአገር ወዳድነት ስሜት በአግባቡ መጠቀም ነው እላለሁ። በሕዝቡ ዘንድ የማይበርድ ኢትዮጵያዊነት ታምቆ ለመኖሩ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ቢቻልም በዋነኛነት በቅርቡ ለሕዝብ ጆሮ የበቁት የቴዲ አፍሮ ስራዎችና ቃለመጠይቆች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባለው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ያገኙትን ተቀባይነትና የፈጠሩትን መነሳሳት ከግንዛቤ ማስገባት ያስፈልጋል። በተመሳሳይ በተለያዩ የስፓርት ዝግጅቶችና ሕዝባዊ በዓላት ላይ የሚታዩት አገራዊ መንፈሶችም ትርጉምና መልዕክት አላቸው። እስካሁን የተደረጉ ፀረ−ወያኔ እንቅስቃሴዎች ይህንን ሕዝባዊ የአገር ፍቅርና ተቆርቋሪነት ዋነኛ እሴት ባለማድረጋቸው ውጤታቸው እንደምናየው ሆኗል። የተቃዋሚው እንቅስቃሴ ወያኔያዊውና ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ በተቃዋሚው ጎራ ስር እየሰደደ ያለው ብሔር ተኮር ፓለቲካ ህልውናችንን የሚንድ፣ ያለንን የሚያሳጣ፣ አገርንና ሕዝብን የሚበትን፣ ጠላትነትን የሚያራባ እንዲሁም ማንነትን የሚያጠፋ መሆኑን በአግባቡ ለሕዝብ ማስረዳትና ማሳየት ይኖርበታል። ወያኔ ዘወትር የሚዘምርለት ነገር ግን በገሀድ የማይታየው የኢኮኖሚ እድገት ከአገር ህልውና የሚበልጥ ቦታ እንደሌለው በማስገንዘብ ሕዝቡን ለማነሳሳት መስራት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው።

ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደጎን በመተው በሚያግባቡን ትልልቅ ጉዳዮች ላይ ተባብረን አገርንና ሕዝብን ከባሰ ጥፋት ለማዳን መስራት አማራጭ የለውም። ለዚህም የአንድነት ሀይሉ እስክህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ታግሎ የሚያታግልበትን ግልፅና ወጥ የሆነ መርህና ግብ ይዞ መውጣትና ለተግባራዊነቱም ሕዝብን ለማነሳሳት ያለመሰልቸት መስራት አለበት። ልዩነትና ንትርክ በግዜ ከመቀለድ ውጭ ያተረፉልን ምንም ነገር የለም፣ አይኖርምም። ወያኔን ጥሎ ሥልጣን ላይ ለመቀመጥ ከመተራመስ አገርን አድኖ ለሕዝብ ለማስረከብ መስራት ውጤቱ ያማረ ይሆናል። የትግል አቅጣጫችን ለየቅል እንደሆነ ከቀጠልን ግን ዕድሜ ይስጠን እንጂ የዚህን የከረፋ አገዛዝ 50ኛ ዓመት ማክበራችን አይቀሬ ነው።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!