ሸንቁጥ አየለ

Mamushet Amare
አቶ ማሙሸት አማረ

ግንባሩን አላጠፈ። በመከራ ውስጥ በመራመዱ አልተከፋም። ከግማሽ እድሜው በላይ በትግል ውስጥ በማሳለፉ ቅሬታ የለውም። ከአስራ ሶስት ዓመታት በላይ በስር ቤት በማሳለፉም በምሬት ሲናገር ተደምጦ አያውቅም። ኢትዮጵያን ይወዳታል እንጅ ኢትዮጵያ እንድትወደው አንድም ቀን ጠብቆ አያውቅም። ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሲናገር ታላቅ እና ከፍ ያለ አክብሮት አለው። ቃላቱ ጠንቃቃ ነው። አንደበቱ ልዝብ ነው። ስሜቱን የመግታታ ልምምድ ውስጥ ያለፈ ታላቅ ባለ አዕምሮ ሰው ነው።

በኢትዮጵያዊነት ሲከሱት አልተበሳጨም። በብሔሩ አሳበው ሲያሳድዱት አንድም ቀን አልተሸማቀቀም። በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት አቀንቃኝነት ሲኮንኑትም አንድ ጊዜም ቅር አልተሰኘም። የሆነውን ነገር ሁሉ ይወደዋል። ኢትዮጵያ ያላትንም ሁሉ ይወዳል። ኢትዮጵያ ውስጥ በወያኔ ዘመን ለመፈረጅ ሰው መሆን በቂ እንደሆነ በደንብ ገብቶታል። ሰው ከዚህ ወይ ከዚያ ብሔር ቢሆን ወያኔን እስከተቃወመ ድረስ በብሔሩ ይፈረጃል። ኦርቶዶክስ ወይም ሙስሊም ቢሆንም ወያኔን እስከተቃወመ ድረስ በወያኔ ይፈረጃል። ኢትዮጵያዊነት እምነቱ ከፍ ያለም ቢሆን በኢትዮጵያዊነት እምነቱ ይከሰሳል። እናም ማሙሸት አማረ ስትጠይቀው የሚመልሰው መልስ ያስደምማል። "ወያኔ የሚሰራው ስራውን ነው። መፈረጅ እና የማጥላሊያ ቅጣይ ማውጣትን እንደ ግብ የሚወስደው ታጋዮችን ለማሸማቀቅ መሆኑ መታወቅ አለበት። እናም ትግል ውስጥ የሚገባ ሁሉ ይሄን አውቆ ከተነሳ መፈረጅን በታላቅ ደስታ መቀበል አለበት" ብሎ ይመልሳል። በመሆኑም ዝም ብሎ በአርምሞ ይታገላል።

የሚታግልበትን ድርጅት ስም ነጥቀው ለሌላ ሲሰጡት ትግል ቆመ አላለም። ባንዳዎች ዙሪያውን ሲከቡት ወደኋላ አላፈገፈገም። ደጋፊዎቹ እንደ ቦና ጉም ትን ብለው ሲሸሹት ከኢትዮጵያዊነት ትግሉ ሸብረክ አላለም። ሌላው ቀርቶ በጣም ይታመንባቸው የነበሩት ይትግል አጋሮቹ የከሰሱት ጊዜ እንኳን ትግል እርሜ አላለም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሸፍጥ የተሞላ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል። እናም ሁሉንም ነገር ፈገግ ብሎ ያሳልፈዋል። "ኢትዮጵያዊነት መከራ እና ፈተና ውስጥ ያለፈ ታላቅ መንፈስ ነው!" ይልሃል ማሙሸት አማረ። "በእኛ ዘመን የተለዬ ነገር አልገጠመንም። የቀደሙ አባቶቻችንን የገጠማቸው መከራ እና ፈተና እንጅ የገጠመን" ብሎ ያምናል ማሙሸት አማረ።

በውይይት ወቅት በተመስጦ ያደምጣል። መናገር ከጀመረ የመረጃ ዝናብ ያዘንባል። ንግግሩ በቁም ነገር የተሞላ ነው። ሀሰት እና ሃሰተኛ ይጸዬፋል። ወዳኋላ ወይም ወደፊት በማለት አይዋዥቅም ። ወደፊት ብቻ በትግል መስመሩ ላይ ይራመዳል። ውስብስብ በሆነው እና በባንድነት ስነልቦና በተሞላው የኢትዮጵያ የተቃውሞ ወንዝ ውስጥ ገብቶ መዋኘት ከባድ እንደሆነ ያውቃል። በተለይም ባንዶችን ፊት ለፊት መናገር እና መግጠም ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ባንዶቹ እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ንጹሃኑን ጠልፈው እየጣሉ፣ ከጠላትም ከወገንም በሁለት ቢላዎ እየበሉ፣ እሞቀበት ገብተው እየጨፈሩ፣ ከፓርቲ ፓርቲ እያማረጡ፣ ከባንዳው ወያኔ ጋር እየተርመጠመጡ፣ የቀደመ የኢትዮጵያውያንን መሰረት ሁሉ እያንኳሰሱ፣ ዛሬ ያመኑበትን ነገ እየረገሙ ይመላለሳሉ። ማሙሸት አማረ ግን እንዲህ አይነት ነገር ከቶም አይነካካውም። ጽይፉ ነው። መጸዬፍ ብቻ አይደለም ፊት ለፊት ይገጥመዋል።

ራበኝ አይልም። ለግሌ አይልም። ይሄ ቀረብኝ አይልም። እንደሌሎች ልታወቅ ልታወቅ አይልም። ሀሰት ፈብርኮ አደባባይ ላይ ወጥቶ አይጨፍርም። እቤት ውስጥም፣ እጓዳም፣ አደባባይም ላይ ያው አንድ አቋም አለው። አንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በወያኔ ስርዓት ስለማትመጣ ወያኔን መታገል አለብን ብሎ በፍጹም ያምናል። በአደባባይም ይናገራል። ትግሉንም በትህትና ለሃያ ስድስት ዓመታት ቀጥ ብሎ አራምዶታል። አሁንም በመከራ ወህኒ ውስጥ ስለኢትዮጵያ ይማቅቃል። ማሙሸት አማረ። እሱ ስለ ኢትዮጵያ ሲል በፍቅር እና በደስታ ይሄን ያህል ዓመታት ይማቅ እንጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ስለዚህ ሰው በቂ እውቀት የለውም። ምናልባትም ስለዚህ ሰው ሕዝቡ እንዳያውቅ ያሸመቁ ብዙ ታጋይ መሳዮች እንዳሉም እውነትን የሚያነፈንፈው ብልህ ወገን በቂ መረጃ ላይኖረው ይችላል።

አንድ ቀን እንዲህ ሆነ። ስየ አብርሃ የሚባል ገዳይ የወያኔ ምሰሶ ከመለስ ዜናዊ ጋር ተጣላ ተባለ። እናም ወዲህ እና ወዲያ እንደ ወጭት ውሃ የሚዋልለው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ተሰብስቦ ስየ አብርሃን ጭንቅላታችን ላይ እናስቀምጠውና ይምራን። ወያኔን ስየ ይጥልናል የሚል ውይይት ተጀመረ። ስለሆነም መኢአድንም በአንድ አድርጎ ስየ ይምራልን የሚል ልኩስኩስ ሀሳብ መጣ። ማሙሸት ጥያቄ ጠየቀ። "ስየ ከመለስ በምን ይሻላል? ደግሞስ ስየ ይምራን ስትሉ ምን አይነት ሥርዓት እንዲያመጣላችሁ ፈልጋችሁ ነው?" አንዳንዱ እየተነሳ ዘባረቀ። "ስየን የወያኔ ሰራዊት ስለሚያውቀው ወያኔን ለመጣል ምርጡ አማራጭ ስየ ነው" የሚል ማብራሪያ ሰጠ። አንዳንዱም "ስየ ቆራጡ" እያለ ፈነጨ።

ማሙሸት ይሄን ሁሉ አዳምጦ አንድ መልስ መለሰ። "ስየን ለጊዜው እንደፈለጋችሁ በአንቀልባ አዝላችሁት ዙሩ። አሁን መጽሀፍ እየጻፈ ነው። መጽሀፉ ሲወጣ ምን እንደሚል ታዩታላችሁ። ወያኔ የሚባለው ፓርቲ ምርጡ ፓርቲ ነው። ጥፋተኛው መለስ ብቻ ነው ብሎ ይሰብክሃል። በስየ አይን ወያኔ ማለት የሰማያት ጻድቃን ስብስብ ሲሆን የስየ ጸቡም ከመለስ ጋር ብቻ ነው። እናም ስየ ማለት መለስ ማለት ነው። መለስን አንስተህ ስየን ለማስቀመጥ ምን ትግል ያስፈልጋል? ይሄ ፈጽሞ ከንቱ ትግል ነው። እኛ ስየ ከሚባል ሰው ጋር አንሰራም" ሆኖም በቦታው የነበሩ ጋዜጠኛ ተብዬዎች እና ፖለቲከኞች ወጥተው ማሙሸት ላይ በትችት ወረዱበት።

ይሄን ያስተዋለ አንዱ የማሙሸት ጓደኛም " አንዳንዴ ምን አለበት ዝም ብትል። ይሄ ሁሉ ትችት ባንተ ላይ የሚዘንበው ብልጠት ስለሚጎልህ ነው" ሲል መከረው። ማሙሸት ፈገግ አለ። "አጼ ምኒልክን የሚወቅስ አገር እኔን አንድ ተራ ማሙሸት አማረን ለምን ወቀሰኝ ብዬ እንድከፋ ጠብቀህ ከሆነ አይከፋኝም። ሆንም ባንዳ አዝዬ ትግል እያልኩ እንድዞር አትጠብቅ። እሞቀበት መደለቅ የፈለገ መብቱ ነው። እኔ ግን እውነቱን በመናገር መሳሳታቸውን ከመናገር ከታቀብኩ ሕዝቤን እያታለልኩ ነው ማለት ነው። ስየ ማለት ያው እንደነ መለስ አገር ያፈረሰ ወንጀለኛ ነው።"

ማሙሸት አማረ አሁንም የመኢአድ ሕጋዊ ፕሬዝዳንት ነው። ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች እና ጸሃፊዎች ከውጭ አገር እስከ አገር ቤት ህሊናቸውን ወደ ውስጥ መመርመር የማይችሉ ግልብ ናቸው። ወያኔ ሕጋዊውን መሪ ሲያስረው "የቀድሞው" የመኢአድ መሪ ይሉታል። ተደጋግሞ ቢነገራቸውም አይሰሙም። የወያኔን የስር ውሳኔ ተቀብለው እንደ ገደል ማሚቶ ይጮሃሉ። የቀድሞው የሚባለው ሕዝብ ከሻረው ብቻ ነው። በሕጋዊነት ፓርቲው፣ አመራሪ፣ አባሉ እና ደጋፊው ሕዝብ የመረጠውን ሕጋዊ መሪ ወያኔ "ሕጋዊ አይደለህም"፣ "ወንጀለኛ ነህ” ስላለው ሕጋዊነቱን አያጣም። ስለዚህ አንድ መሪ ስለታሰረ ብቻ እየሮጡ "የቀድሞው" ማለት የወያኔን ውሳኔ ማጽደቅ ነው ተብለው ቢነገሩም አይሰሙም። እናም የቀድሞው የመኢአድ ፕሬዝዳንት ብለው ይጠሩታል።

እናም በርካታ ሚዲያዎች የአንባገነን እና የዘረኛ ቡድንን ውሳኔ እንደ ውሳኔ እየተቀበሉ በርካታ ታጋዮችን ከትግል ማማ ላይ እያወረዱ ይፈጠፍጧቸዋል። እንዲህ አይነት የገደል ማሚቶ ሚዲያ በተሰበሰበበት ማህበረሰብ ውስጥ እውነት እንደ እሳት ውስጥ ቅቤ ዝም ብሎ ሳይታይ ይቀልጣል። ማህበረሰቡ ሆያሆዬ ወዳድ እና እውነትን ከመመርመር የዘገዬ ስለሆነ ስር ያለው እና ስር የሌለውን አጥርቶ አያስተውልም። አጥርቶ የሚያስተውልበት ሚዲያም የለው።

ከወያኔ ጋር ተጣላን ስላሉ ብቻ (መጣላት አለመጣላታቸው በወል አይታወቅም) ወያኔን ያገለገሉ፣ ሕዝብን ሲገሉ እና ሲያስገድሉ የነበሩ፣ እጃቸው በደም የተጨማለቀ ሰዎችን ብሎም አገሪቱን ሲያፈርሱ የነበሩ ብልጣብልጦችን እንደ ምርጥ ታጋይ ሰማዬ ሰማያት ለማውጣት የሚጣደፈው የተቃዋሚ ተብዬዎች ሚዲያ ጽኑአን ታጋዮችን እና የሰበአዊ መብት ተከራካራካሪዎችን እንዲሁም ጋዜጠኞችን በወያኔ ውሳኔ እስር ቤት ሲገቡ ወንጀለኛ ያደርጋቸው እና "የቀድሞ" ጋዜጠኛ፣ "የቀድሞ" መሪ፣ "የቀድሞ" ምንትስ እያለ ይጠራቸዋል። በዚህም የሀቅ ልጆች እና የሀቅ ታጋዮች ወያኔ እንደሚፈልገው ከሕዝቡ ልብ እየተፋቁ ወደ ቀድሞነት እየተለወጡ ወደ ስርቻ ይወረወራሉ። የሚያስባቸው እና የሚያስታውሳቸው የለም።

የኢትዮጵያ ሰው አንዳንዴ ያስቃል። ቆራጥ ታጋይ እና የታመነ መሪ ይፈልጋል። ግን ቆራጦቹን እና የታመኑትን ወያኔ ወደ እስር ቤት ሲጥላቸው እንደ ተጣለ እቃ ይረሳቸዋል። ምርጦቹ ጋዜጠኞች፣ ምርጦቹ ታጋዮች እና ምርጦቹ መሪዎች ሲታሰሩ በቃ "የቀድሞ" ይባሉ እና እንደ ተጣለ እቃ ወደ ስርቻ ተወርውረው ይረሳሉ። ሃሃሃሃ ... ከዚያ ይልቅ የወያኔ አገልጋይ የነበሩትን እና የሕዝብ አራጆቹን ብልጣብልጦች ልክ እንደ ጀግና እያስጨፈረ ድል እንዲያመጡለት ይጠብቃል። ድል? እም ... ቀልድ።

መርህ የሚባለው ነገር ገደል ገብቷል። እውነት እሳት ውስጥ እንደገባ ቅቤ የትም ትቀልጣለች። በዚህ አይነቱ ውስብስብ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ምርጦቹ ስይታዩ ይቀልጣሉ። የሆነ ሆኖ ማሙሸት አማረ በዚህ ሁሉ ሲከፋ አይሰማም። ቅሬታም ፈጽሞ የለውም። የእርሱ አላማ አንድ ነው። ኢትዮጵያን መውደድ፣ ለሚወደውም ነገር በደስታ እና በታላቅ ወኔ መስዋዕት መሆን። እየሆነም ያለው ይሄው ነው።

አሁን ማሙሸት አማረ በወያኔ ወንጀለኛ ትእዛዝ እስር ቤት ነው። በመላ አገሪቱ በተለይም በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን አመጽ የመራው እና ያስተባበረው ማሙሸት አማረ ነው ብሎ ወያኔ ከሶታል። ወያኔ ምንም አይነት ክስ በማሙሸት አማረ ላይ ቢያቀርብም ቅሉ ግን ማሙሸት አማረ አሁንም ሕጋዊው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መሪ ነው። የሩብ ክፍለ ዘመን አሸብራቂ ታጋይ የሆነው ማሙሸት አማረ በትህትና እና በቆራጥነት ስለ ታላቂቱ ኢትዮጵያ አገሩ የከፈለው መስዋዕትነት ሁሉ በታመኑ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ አለው።

ማሙሸት አማረ በእስር ቤት ውስጥ ብትሆንም መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልህ!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!