ገለታው ዘለቀ

Dream of ISIS
የአይሲስ (IS) ሕልም

የተከበሩና የዘወትር የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገር የሚቆጫቸው እንደራሴ ስሚዝ ክሪስ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ትግል ለመደገፍ ሲሉ H.Res 128 ሕግን አርቅቀዋል። ይህ ሕግ በውጭ ጉዳይ በንዑስ ኮሚቴው በሙሉ ድምጽ ጸድቆ ወደ ዋናው ምክር ቤት ለድምጽ ውሳኔ በመሄድ ላይ ነው። ባለፈው ኦክቶበር ሁለት ለሕዝብ ተወካዮች ለድምጽ ይቀርባል ተብሎ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ይሁን እንጂ እንደተራዘመ ተገልጻል።

የተራዘመበት ምክንያት በትክክል ባይገለጽም ነገር ግን በመሃል የኢትዮጵያ መንግሥት በአምባሳደሩ አማካኝነት ለአሜሪካ እንደራሴዎች ይህን ሕግ ካሳለፋችሁ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋራ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት አትተባበርም በማለት የማባበል ይሁን የማስፈራራት ስራ አየሰራ እንደሆነ የተከበሩ እንደራሴ ማይክ ኮፍማን ተናግረዋል።

ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት አባባል ምን ማለት ነው? የዚህ አባባል አንድምታው ምንድን ነው? የሚለውን ማጤን ተገቢ ነው። በቅድሚያ H.Res 128 ምን ይዘት እንዳለው እንመልከት። በክቡር እንደራሴ ክሪስ ስሚዝ የተዘጋጀውና በሌላ በኩል በሰኔት የተዘጋጀው S.Res 168 ሰነድ ተመሳሳይነት አላቸው። H.Res 128 አጠቃላይ ዓላማው በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት እንዲከበርና ሁሉን አቀፍ የሆነ የተሻለ አስተዳደርን ለማጠናከር ነው።

ዝርዝር ይዘቱ የሚጠይቀው በኢትዮጵያ ውስጥ ተጠያቂነት እንዲኖር፣ ነፍጥ ያነሱ ኀይላት ከዚህ ታቅበው መነጋገር እንዲችሉ፣ ከዚህ በፊት ሰው የፈጁና በዘረፋ ላይ የተሰማሩ በሕግ ፊት ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያትት ሲሆን ጠበቅ ያለ ጉዳይም ይዟል።

በተለይ ኢትዮጵያውያንን በግፍ ሥርዓት የያዙት ማእቀብ እንዲደረግባቸው ሚገድሉ፣ የሚያሰቃዩ፣ የሚዘርፍ፣ ሁሉ ንብረታቸው እንዲያዝ ይጠይቃል። ይህን ሕግ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት H.Res 128 ሕግ ካሳለፋችሁ ከናንተ ጋር ሽብርተኛን አልዋጋም ያስባለው። በርግጥ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥልቅ ተሃድሶ ላይ ነኝ ካለ፣ በርግጥ ለሕዝብ የቆመ መንግሥትና ሙስናን ለመዋጋት የተነሳ ከሆነ ይህን ሕግ ሊፈራው አይገባም ነበር።

እንዴውም ይህን ሕግ ለለውጥ እና ሙስናን ለመዋጋት እንደ ደጋፊ ኀይል ሊጠቀምበት ባሰበ ነበር። እንደ ጠቃሚም ድጋፍ አይቶት በነፍጥ ለውጥ እናመጣለን ያሉ ሃይሎችን ወደ ድርድር ለማምጣት በተጠቀመበት ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት አልወደደውም። አልወደደውም ብቻ ሳይሆን ምላሹ አስገራሚ ነው።

ይህ ሕግ ለዋናው ምክር ቤት ቀርቦ ድምጽ እንዳይሰጥበት ወይም ድምጽ ሲሰጥ እንዲወድቅ የሚታገለው ለሽብር ስራ አልተባበርም በሚል ማስፈራሪያ ነው። ለመሆኑ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከአሜሪካ ጋር አልተባበርም ማለት ምን ማለት ነው? በዚህ ካልተባበረ በምን በምን ጉዳይ ላይ ሊተባበር ነው።

ነገ የአውሮፓ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወይም የአፍሪካ ሕብረት ተመሳሳይ ሕግ አውጥተው ቢያቀርቡ ከናንተ ጋር ሽብርተኛነትን አልዋጋም የሚል ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት መርህ መጨረሻው ምንድነው? በንግድ ልውውጥና በመሳሰሉት ጉዳዮች አብሬ አልሰራም ለምን አላለም። ካከሁበት ሁኔታ ተለወጥ፣ ተስተካከል፣ የምትሉኝ ክሆነ ሽብርተኛ አልዋጋም ማለት ሽብረተኝነት የእኔ ስጋት አይደለም እኔና ሽብርተኞች የግል ጸብ የለንም እንደማለት የሚያስቆትርበት አይሆንም ወይ።

እስከዛሬም በጸረ ሽብር ስራው የነበረኝ ተሳትፎ ችግሩን እንደራሴ ችግር አይቼው ሳይሆን ከእናንተ ድጋፍ ለማግኘት ነው እንደማለትም ጭምር ነው። H.Res 128 ካለፈ ከአሜሪካ ጋር አልሸባብን አልዋጋም ማለት አሜሪካ ከእኔ ጋር የጸረ ሽብር ስራ ለመስራት ካሰብሽ መጀመሪያ እሴቶችሽን ሰብረሽ ነይ። የውስጥ አሸባሪ ብሆንም፣ ሙስናና ሕገወጥ ግድያ ባካሂድም ይህንን ስራ ተው የምትይ ከሆነ አልሸባብን አልዋጋም ብሎ ማለት የአሜሪካንን እሴት መስበር ነው።

አሜሪካ እንደ ልዕለ ኀያል ሃገር የነጻነት፣ የዴሞክራሲ እሴቶቿ የውጭ ፖሊሲዋን ይገዛዋል። ለዚያም ነው ይህ ሕግ በውጭ ጉዳይ ኮሚቴው በሙሉ ድምጽ የጸደቀው። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ውትወታ ከአሜሪካ እሴቶች ጋር የሚጋጭ በመሆኑና ሙገታው ራሱ አሳፋሪ በመሆኑ ተቀባይነት ያገኛል ብየ አላምንም። በመሰረቱ አልሸባብን የምን ዋጋው ለአሜሪካ ብለን አይደለም። እንዴውም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለው የሽብር እንቅስቃሴ ከማንም በላይ የሚያሳስበን ሰዎች እንደመሆናችን የዓለም አቀፍ ትብብር መሪዎች አስተባባሪዎች ልንሆን ይገባል። አይሲስ የተባለው ዓለማቀፍ አሸባሪ ቡድን ከረጅም ጊዜ ሕልሙ መሃል ኢትዮጵያን የእስልምና መንግሥት አገር ማድረግ ነው። ዝቅ ሲል የሚታየውን ስዕል መመልከት የበለጠ ገላጭ ነው።

የአይሲስ (IS) ሕልም

አሸባሪነት በአፍሪካ ቀንድም ይሁን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የኛ የራሳችን ችግር ነውና ይህ ጉዳይ ዋና የጸጥታችን ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል። በምንም ዓይነት ለድርድር የምናቀርበው እጀንዳ መሆን የለበትም። ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ብዙህነት ያላት ሃገር ሆና በተለይ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ለረጅም ጊዜ በሰላም የኖረባት አገር መሆኗ ለዓለም ምሳሌ ያደርጋታል። ይህ ሰላም ተጠብቆ የሚቆየው ታዲያ አክራሪነትን ሳንታክት ከተዋጋን ብቻ ነው። በመሆኑም አክራሪነትን በየትኛውም ደረጃ የመከላከላችን ተግባር ለድርድር የሚቀርብ የደህነታችን አጀንዳ መሆን አይጠበቅበትም።

የአሜሪካ እንደራሴዎች ከዚህ ከኢትዮጵያ መንግሥት ውትወታ የሚረዱት ነገር አለ። አንደኛው ይህን ማስፈራሪያ ወይም ማሳመኛ አድርጎ መምጣቱ የሚያሳፍር ሲሆን ሌላው ዋና ጉዳይ ደግሞ ይህ መንግሥት በሃገሩ በዜጎቹ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽም በመሆኑና በውስጥ አለመረጋጋት የተመታ በመሆኑ ዘላቂና ታማኝ የአሜሪካ ጓድ ሊሆን እንደማይችል ነው። የዴሞክራሲ ምህዳሩን አጥብቦ ሕዝቡን በብሔር ከፋፍሎ የሚያፋጅ መንግሥት ጸረ ሽብር የሆነ ኀይል እንደማይሆን ይገመግሙታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የቅቡልነት (legitimacy) ችግርና የመታመን (trust) ችግር እንዳለበት ስለሚረዱ ይህ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ ቀርቶ በራሱ ሃገርም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ያመጣል ብለው አያምኑም።

በቀጣናው ሰላም መረጋጋትን ለማምጣት ቅቡልነት በጣም ዋና ጉዳይ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት በፍጹም የቆረጠና የገባው የጸረ ሽብር ኀይል ሊሆን አይችልም። ፕሬዚደንት ትራምፕም ይህንን አይደግፉም። በሽበርተኞች ላይ የጸና አቋም ያላቸው ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ ሃቀኛ ጓድ ያስፈልጋቸዋል። የጸረ ሽብርን ስራ መነገጃ ካደረገ መንግሥት ጋር ግንኙነት አይሹም። በመሆኑም ይህ ሎቢው ይሳካል ብሎ ማመን ይከብዳል። ለማናቸውም ይህ ሕግ ይጸድቅ ዘንድ የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ የአሜሪካንን እንደራሴዎች ማነጋገር ማስረዳት ያስፈልጋል። አሜሪካም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆሟን ታሳያለች ብለን እናምናለን። ዛፍ ላይ ወጥቶ የተቀመጠበትን ዛፍ ለመቁረጥ እየገዘገዘ ካለ መንግሥት ጋር የሚተባበር የለም።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ