ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሳይከበር የጥላቻ ፖለቲካን እና የመሳሰሉትን ለመዋጋት መሞከር ከንቱ ልፋት ነው

በተስፋዬ ማሩ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.) - ለአቶ አብርሃም ያየህ ጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ

በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱትን የጥላቻ ክስተቶች በተመለከተ ጥቂት ተብሏል። ቀና አመለካከት ያላቸው ሰዎች ጥላቻ ሊያመጣ የሚችለውን ክፉ ውጤት እየጠቀሱ ማስጠንቀቂያ በሞላበት ሁኔታ ለማስተማር ሞክረዋል።

 

(ይህንን ጽሑፍ በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ ከፈለጉ እዚህ ይጫኑ!) ጥላቻ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም የሰው ልጅ አደገኛ እንደሆነ አውቀው ከልባቸው ሊዋጉት የሚንቀሳቀሱ ዜጎች ሊበረታቱና ሊመሰገኑ ይገባል። ነገር ግን የፈለገ ቀና አመለካከት ቢኖራቸው መልዕክታቸው - እንደየመልዕክቱ ያለውን ጉድለት ብንተወው እንኳ - እንደሚገባው ተላልፎ ውጤት ያመጣል ማለት አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ ነፃ ሃሳብ በታፈነበት ሀገር ጥላቻን እና የመሳሰሉትን ለመዋጋት መሞከር ከንቱ ልፋት ከመሆኑም ባሻገር፤ አንዳንዴ፣ ጥላቻን እንደ ፖለቲካ ስልት ለሚያራምዱ ቡድኖች መሣሪያ መሆንን ያመጣል። የጥላቻ ፖለቲካ በማኅበረሰብ ውስጥ መስፋፋት ወይም አለመስፋፋት ጉዳይ በቀጥታ ከዲሞክራሲ - በተለይም ሃሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት - ጉዳይ ጋር መሰረታዊ ግንኙነት አለው።

 

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሥርዓት የተለያዩ አመለካከቶች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ መፍቀድን ይቅርና ጭራሹኑ እንዳይፈልቁ ለማገድ ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ እስከ መገናኛ ብዙኀን ድረስ በዘረጋቸው የተለያዩ አፋኝ ፖሊሲዎች አማካኝነት የሚጥር ነው። ይህ ደግሞ በማኅበረሰባችን ውስጥ እንደ ማንኛውም ማኅበረሰብ ሊከሰቱ የሚችሉትን እንደ ጥላቻ ያሉ ችግሮችን በስኬት እንዳንዋጋ የሚከለክል ዋናው እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር ጭራሹኑ የሚያባብስ ነው። የነፃ ሃሳቦች አፈናው ሳያንስ ደግሞ እራሱ የምንዋጋውን ነገር በግንባር ቀደምትነት የሚያራምድ ገዢ ፓርቲ ሲጨመርበት ችግሩ የባሰ ይሆናል።

 

ጥላቻ

የሰው ልጆች ጎራ እና ቡድን ለይቶ መጠላላትና መሰዳደብ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረ ነገር አይደለም። በማንኛውም ሰዓት ወደ ማንኛውም የዓለም ክፍል ልብን የሚያይ ማይክሮስኮፕ ይዛችሁ ሄዳችሁ ብትፈልጉ ሌላን ዘውጌ ማኅበረሰብ፣ ሌላን ሀገር፣ ወይም ደግሞ ሌላን ዘር የሚጠላ ሰው ማግኘታችሁ አይቀርም። የኢትዮጵያም ጉዳይ ነገሮች ሠላም በሆኑበት ሁኔታ እንኳ ከዛ የተለየ አይሆንም። ልክ እንደዛው ደግሞ በጥላቻ ላይ የተመሰረቱና የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም ሀገር ይኖራሉ። ሌላው ቀርቶ በዲሞክራሲያዊነታቸው እና በብልጽግናቸው በዓለም በታወቁት እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገሮች እንኳ አፋቸውን አውጥተው “እኛ ከነጮች በስተቀር ሌሎችን ሰው አድርገን አናይም” ብለው የሚናገሩ እንደ Ku Klux Klan (KKK) ያሉ ቡድኖች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ግራና ቀኝ ጫፍ ላይ ተቀምጠው እርስ በርስ የሚሰዳደቡ እና የሚጠላሉ ሞልተዋል።

 

ነገር ግን አንድ ህዝብ በሌላው ላይ ያለው ጥላቻ የተለያየ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል እና አንዳንዴም አደገኛ ሊሆን እንደሚችል አይካድም። ከላይ የጠቀስኳቸው እንደ አሜሪካን ሀገር ባሉ ሀገሮች ያሉ በጥላቻ ላይ የተመሰረቱ ቡድኖች የአብዛኛው ህዝብ ወኪሎች ከመሆን እጅግ የራቁ ናቸው። ይህም ሊሆንበት ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ የተለያዩ ሃሳቦች በነፃነት እንዲገለጹ የሚያስችል መብት ስላለ አብዛኛው የሀገሪቱ ህዝብ የተለያዩ አመለካከቶችን አጣቅሶና አገናዝቦ በመማር የመሃሉን ወይም ወደ መሃል የተጠጋውን መንገድ እንዲመርጥ ዕድል ስላገኘ ነው። በተጨማሪም በተለይ ከሞራል አኳያ ተቀባይነት የሌላቸው (ለምሳሌ በጥላቻ ላይ የተመሰረቱ) ሃሳቦች ሲገለጡ ብዙዎች በነፃነት እና በግልጽ ተረባርበው ይወቅሷቸዋል። ስለዚህ ሃሳባቸው ስር ሳይሰድ የመነቀል ዕድሉ ከፍ ያለ ነው።

 

የነፃነት መነፈግንና የጥላቻን መስፋፋት ምን ያገናኛቸዋል?

ሃሳቦችን በነፃነት የመግለጽ መብት መነፈግ በሁለት ቀጥተኛ መንገዶች ጥላቻን ለመሳሰሉ ነገሮች መስፋፋት አስተዋጽዖ ያደርጋል። አንደኛ - የተለያዩ ሃሳቦች በነፃነት እንዳይንሸራሸሩ ሲከለከል የህዝቡ የመማማር ዕድል ይጠባል። በንደዛ ዓይነት ስፍራ/ሀገር የሚገኙት መረጃዎችና ሃሳቦች አፈናውን በሚያካሂዱት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የይለፍ ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ ነው ለህዝቡ የሚደርሱት። ይህም ህዝቡን የነዚህ ሰዎች ወይም ቡድኖች አስተሳሰብ እስረኛ ያደርገዋል። በተለይም ከዚህ በታች ለማሳየት እንደምሞክረው፣ ይህንን አፈና የሚያካሂደው እንደ ህወሓት ያለ ቡድን ሲሆን ደግሞ ሁኔታውን ይበልጡኑ አደገኛ ያደርገዋል። ህወሓት የጥላቻን ፖለቲካ በግልጽ የሚጠቀም ፓርቲ ነው። ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ፓርቲ አንዲትን ሀገር ሲገዛና እንደዚህ ያለ አፈና ሲያካሂድ የሚቃወሙትና “ልክ አይደለህም፤ ተሳስተሃል” የሚሉት ከሌሉ ሁኔታው ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ መገመት ትችላላችሁ።

 

ሁለተኛው - መንገድ ደግሞ፣ ሃሳብን በነፃነት እንዳይገልጹ የተከለከሉ ሰዎች የመታፈን፣ የመገፋትና አማራጭን የመከልከል ስሜት ይሰማቸዋል። በዚህ ሁኔታ ያሉ ሰዎች ደግሞ የሆነ አማራጭ ሲያገኙ መልካም ሆነ ክፉ ብዙም አይገዳቸውም፤ ይልቁንስ አማራጭ ስለሆነ ብቻ ሊቀበሉት ይችላሉ። ይህም ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ይበልጡኑ አሳሳቢ ያደርገዋል። ምክንያቱም ስለ ሠላምና ፍቅር የሚናገሩ ቡድኖች በታፈኑ ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ ስፍራውን የሚረከቡት አሉታዊ መልዕክቶችን ያነገቡ ጽንፈኞች ናቸው። መተንፈሻ መንገድ ሲፈልግ የቆየው ህዝብም፣ በተለይ ደግሞ የመማማር እና የመወቃቀስ ዕድሉ ቀንሶ ባለበት፣ ለእነዚህ ኃይሎች ሊወድቅ ይችላል።

 

አንድን ህዝብ ከጽንፈኞችና ከአስተሳሰባቸው ወጥመድ ለማላቀቅ ብቸኛው መንገድ፣ ነፃነቱን ማክበር፣ በተቻለው መንገድ ሁሉ እንዲማር ማበረታታትና የትምህርት ምንጭ የሆኑትን እንደ መገናኛ ብዙኀንና እንደ ትምህርት ቤት ያሉትን ተቋሞች ነፃነት ማክበር ነው። ባሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በጥላቻ ላይ በመመስረት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች እና ግለሰቦች ሥራ ከህወሓት/ኢህአዲግ እና ከደጋፊዎቹ በስተቀር የጥቂት ጽንፈኞች ቅዠት ከመሆን አልፎ የብዙኀኑ አመለካከት ከመሆን እጅግ የራቀ ነው። ነገር ግን፣ አሁን ሀገሪቱ ውስጥ እየሆነ እንዳለው፣ የአብዛኛው ህዝብ አመለካከት ታፍኖ የጥቂቶች አስተሳሰብ ብቻ ከፍ ከፍ የሚልበት ሁኔታ ከቀጠለ፤ የጽንፈኞች አመለካከት ነግሶ ወደ ፊት የብዙዎች አመለካከት የሚሆንበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል።

 

ነፃነት በኢትዮጵያ

ባሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የመገናኛ ብዙኀን ነፃነት የላቸውም። በሀገሪቱ ውስጥ ትርጉም ያለው ጫና (influence) ያላቸውን መገናኛ ብዙኀን ተቆጣጥሮ ያለው ህወሓት/ኢህአዲግ ነው። እነዚህን በህዝብ ገንዘብ የሚተዳደሩና ብዙ አድማጮች ያሏቸውን የመገናኛ ብዙኀን ተጠቅሞ መቻቻልን በተመለከተ የሀገሪቱን ህዝብ ገንቢ ትምህርት የማስተማር ዕድል አለው። ነገር ግን ሲያሻው በአማሮች እና ተለጣፊዎቻቸው በሚላቸው ቡድኖች ላይ ስድብ ሲያሽጎደጉድ፣ ሲያሻው ደግሞ አንዳንዶች ላይ የሚሰነዘሩትን የጥቂት ጽንፈኛ ቡድኖችና ግለሰቦች የጥላቻ መልዕክቶች እያጋነነና የብዙኀኑ እያስመሰለ መጡባችሁ እያለ ሲያስፈራራ፣ ወይም ራሱ ፈጥሮ ያባዛቸውን የጥላቻ መልዕክት ያካተቱ ጽሑፎች በፖለቲካ ፓርቲዎች ስም እየበተነ በአጥፊ ተግባሮች ሲሰማራ ሰንብቷል።

 

እነዚህን በአንዳንድ ህዝቦች ላይ የተነጣጠሩ የጅምላ ውንጀላዎች የሚፃረር እንዳይኖር ደግሞ ነፃው ፕሬስ ዓለም ላይ በጥቂት ሀገሮች ብቻ ታይቶ በሚታወቅ ሁናቴ ተጠቅቷል። በቅርብ ጊዜ የወጣው መገናኛ ብዙኀንን የሚመለከተው ሕግም “በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ ፕሬስ እንዲኖር አልፈቅድም!” ብሎ እቅጩን ላለመናገር የተፃፈ ሽፋን ነው። ከእስር በኋላ የሥራ ፈቃድ ያገኙት የግል ጋዜጠኞች በየሣምንቱ የተለያየ ክስ እየተደረገባቸው፣ እየታሰሩ እየተፈቱ፣ ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው በገዛ ሀገራቸው በቁም እስር ይኖራሉ። ባጠቃላይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ መረጃ የማስተላለፍ ሥራንና ዋና ዋና የማስተላለፊያ መስመሮቹን ተቆጣጥሮ (monopolize አድርጎ) ያለው በህወሓት/ኢህአዲግ የሚመራው መንግሥት ብቻ ነው።

 

ስለ ሠላምና ፍቅር የሚናገሩ ቡድኖች እና ግለሰቦች ደግሞ በተለያየ አጋጣሚ ታፍነዋል፤ አፈናውም በተጠናከረ መንገድ ቀጥሏል። በ1997 ምርጫ፣ ከዛ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የፍቅርንና ሠላምን ቋንቋ የምረጡኝ ዘመቻቸው ዋና ክፍል ያደረጉት የቅንጅት መሪዎች እስራት አንዱ ምሳሌ ነው። ዛሬም ቢሆን የተፈቱት መናገር የሚችሉባቸው ግድቦች ከተሰጧቸው በኋላ ነው። ከነሱ በተጨማሪም፣ መንግሥት የጀመረውን በተለያዩ ዘውጌ ማኅበረሰባት ላይ የተሰነዘሩ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳዎች የሚፃረር እንዳይኖር ከነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች ጋር የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ታስረዋል፣ ተሰደዋል። ስለ ሠላምና ስለ መቻቻል፣ እንዲሁም ደግሞ ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ ስለማብረድ (conflict resolution) ህዝቡን በማስተማር አኳያ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው። ነገር ግን እነሱም ቢሆኑ በቅርቡ ሊጸድቅ በሚችለው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በሚመለከተው ሕግ ከዚህ በፊቱ በባሰ ሁኔታ ይጠቃሉ።

 

እነዚህ ምሳሌዎች የሚነግሩን ነገር፣ ዓለም በሚያውቃቸው ላይ እንዲህ ለማድረግ የደፈረ መንግሥት በየገጠሩ እና በየትናንሽ ከተሞች ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ ምን እያደረገ እንደሆነ ነው። ለነገሩ የነዚህ ሰዎች መጠቃት ላብዛኛው ህዝብ እንደ ማስጠንቀቂያ ነው። “ተናገርና ወዮልህ!”፣ “ህዝቤን ባስተሳሰብ ወይም በሌላ እመራለሁ ብለህ ተነሳና ወዮልህ!” መሆኑ ነው። ደፍረው ተነስተው መንግሥትን የሚቃወሙ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ያሉ ዜጎችም በመንግሥት የሚደረግባቸውን የግድያና የእስራት ግፍ በየጊዜው እየሰማን ነው።

 

ትምህርት

የኢትዮጵያ ህዝብ በባህሉ የተማሩ የሚላቸውንና መሪዎችን (ተመረጡም አልተመረጡም) ያከብራል፣ ይሰማልም። ይህ ባህል በመሰረቱ ክፋት የለበትም፤ እንዳውም አብዛኞቻችን ትምህርትን እንድንወድ አድርጎናል። ነገር ግን መልካም ነገሮችን ወስዶ ለክፉ ሥራ መሣሪያ ማድረግ ይቻላል። የህዝብን የዋህነት በመጠቀም አንዳንድ “ክፉ” ወይም “ደግ” መሪዎች የራሳቸው ሃሳብ ብቻ የሚንሸራሸርበት ሜዳን ሊያበጁና ህዝቡን የአመለካከታቸው እስረኛ ሊያደርጉት ይችላሉ። ስለዚህም ህዝባችን ለአመለካከቱ በተወሰኑ ልጆቹ እና በመሪዎቹ ላይ ጥገኛ ከመሆኑ ይልቅ በተቻለ መጠን ከተለያዩ ጎራዎች እየተማረ የራሱን አመለካከት በራሱ እንዲገነባ ማበረታታት (to empower) ትክክለኛው መንገድ ነው።

 

ኢህአዲግ ግን ከላይ እንደጠቀስኩት የተለያዩ ሃሳቦች በነፃነት እንዲገለጹ አይፈቅድም። የዚህም ዋነኛ ምክንያት፣ ግለሰቦች በነፃነት ከተለያዩ ምንጮች ተምረው እና አስበው የራሳቸውን አቋም ለመያዝ ከተበረታቱ (ወይም empowerment ካገኙ) ለሱ ህልውና አደገኛ እንደሆነ አድርጎ ያስባል። ምክንያቱም በእውቀቱ የበረታንና በራሳቸው ችሎታ የሚያምኑ ግለሰቦች የሞሉበትን ህዝብ አሁን ባለው ዓይነት ቁጥጥር ስር አውሎ መግዛት አስቸጋሪ ስለሆነ ነው።

 

በነፃነት የማሰብ ባህል ያለመበረታታትና የሃሳቦች በነፃነት ያለመገለጽ ደግሞ የአንድን ሰው ትምህርት ወይም ግላዊ እድገት (personal development) እጅግ አድርጎ ይጎዳል። በነፃነት ማሰብ ስንችልና ያንንም ሃሳብ በነፃነት ስንገልጽ፣ ለሃሳቦቻችን ከተጋለጡት ሰዎች ጋር ውይይትን ይቀሰቅሳል፤ ያም ውይይት በዙሪያችን ያሉት ሰዎች አስተያየት (feedback) እንዲሰጡን ያነሳሳቸዋል። በእንደዚህ አኳኋን እነሱም ይማራሉ፣ የኛም ሃሳብ ቀድሞ ከገለጽነው ይልቅ ይጎለብታል። በዛ ሃሳብ ላይ ደግሞ በመመስረት የተማርነው ትምህርት ወደ ሌላ ሃሳብ ያሻግረናል። በምዕራባውያን ሀገሮች ትንሽም ቢሆን የተማርን ሰዎች፣ መምህራኑ ምን ያህል ተማሪዎች ሃሳባቸውን እንዲገልጹ እና ውይይት እንዲያደርጉ በመገፋፋት ላይ እንደሚያተኩሩ እናውቃለን። ምክንያቱም እነዚህ ሀገሮች ትምህርት የሚባለው ነገር መሰረታዊ እሴቶች እንደሆኑ ስለሚያውቁ ነው።

 

በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በህወሓት/ኢህአዲግ እየተመራች ያለችው የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ግን፤ በነፃ አስተሳሰብ የተካኑ ምሁራንና ተማሪዎች የሚመላለሱባቸው የእውቀት መዳረሻዎች ሳይሆኑ፤ የመንግሥት ሰላዮች እንደ አሸን የፈሉባቸው የተስፋ እስር ቤቶች ሆነዋል። በቅርቡ መንግሥትን የሚፃረር አመለካከት በመግለጿ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተባርራ የወጣችው አሜሪካዊት ፕሮፌሰር አቢጌል ሳልስበሪ ታሪክ የዚህ ምሳሌ ነው። ፕሮፌሰሯ ከኢትዮሚድያ (www.ethiomedia.com) ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ስለዩኒቨርሲቲው የዘረዘረቻቸውን ጉዶች ሳነብ የተረዳኋቸውንና ከዚህ ጽሑፍ ጋር የሚገናኙትን ሦስት ነገሮች እጠቅሳለሁ። አንደኛ - ተማሪዎችና አስተማሪዎች ሃሳባቸውን በነፃ እንዳይገልጹ ከፍተኛ አፈና አለ። ሁለተኛ - የትምህርት ቤቱን የትምህርት አሰጣጥ ስንመለከት፣ ኅብረተሰባቸውን በማንቃት ወደ ቀጣዩ ከፍተኛ ደረጃ ሊመሩ የሚችሉ መሪዎችን ሳይሆን እራሳቸው እንኳ የሚሄዱበትን የማያውቁ በፍርሃት የተሸበቡ ተማሪዎችን እያፈራ እንደሆነ እናያለን። ሦስተኛ ደግሞ፣ ትምህርት ቤቱን ተቆጣጥረው ያሉት የመንግሥት ካድሬዎች በተማሪዎቹ ዘንድ የሚያበረታቷቸው ክፉ ባህሪያት (መምህራንን በማስፈራራት ገንዘብ መጠየቅ፣ ሴት መምህራን ላይ ወሲባዊ ማስፈራራቶችን ማድረግ፣ በመምህራን ላይ በሐሰት መመስከር፣ … ወዘተ) በመልካም ባህሪ የታነጹ የወደፊት መሪዎችን የሚያፈራ ተቋም ሳይሆን የወንጀለኞች ማሠልጠኛ ተቋም እንዳስመሰለው እናያለን።1

 

እነዚህ ምሳሌዎች የሚያሳዩን ህወሓት/ኢህአዲግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ህዝብ ሊማማርባቸው የሚችልባቸውን አውታሮች ሁሉ ተቆጣጥሮ ይዞ እሱ ከፈቀዳቸው ሃሳቦች ውጪ ምንም እንዲተላለፍ እንደማይፈልግ እና ህዝቡም በርትቶ (empowered ሆኖ) ከቁጥጥሩ ውስጥ እንዲወጣ እንደማይፈቅድ ነው። እርሱ የሚፈቅዳቸው ሃሳቦች ደግሞ - ከላይ የጠቀስኳቸውና ከዚህም በኋላ የምጠቅሳቸው ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት - አብዛኛውን ጊዜ አሉታዊ ከመሆናቸውም በላይ ለሀገራችን የወደፊት ዕጣ አደገኛ አዝማምያ ያላቸው ናቸው። ይህ እንዲህ ሆኖ እያለ፣ ሃሳብን በነፃነት ከመግለጽ እና ከመሳሰሉት ፖለቲካዊ መብቶች መከበር ውጪ ስለሌላ ጉዳይ መስበክ በኔ አመለካከት ከንቱ ልፋት ነው።

 

“ግማሽ” እውነቶች

 

ይህንን ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ በቅርቡ በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ (http://ethiopiazare.com) ላይ በአቶ አብርሃም ያየህ የተፃፈ “የጥላቻ - ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ህልውና ጠንቅ ነው” የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ ነው።2 ጥላቻ ምን ያህል አጥፊ እንደሆነ በመናገራችው ሊመሰገኑና ሊበረታቱ ይገባል። እኔም ጥላቻ አጥፊ እንደሆነና በጥላቻ የሠለጠነ ልብ ሁልጊዜም የሚጠላውን እንደሚፈልግ እስማማለሁ። በጥላቻ ሥራ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ነን ባዮች ግለሰቦችንና ቡድኖችን እኔም ከርሳቸው ጋር በመስማማት ልወቅስ እወዳለሁ። ነገር ግን በጽሑፉ ውስጥ ከተጠቀሱት ሁሉም ነጥቦች ጋር አልስማማም፤ የጽሑፉም አጠቃላይ አዝማምያ አሳዛኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሙባቸውን የአንዳንድ ታሪካዊ ክስተቶች የተዛባ አተረጓጎም (በኔ አመለካከት) ጉዳይ ሌላ ጊዜ ስለታሪክ ማውራት ካስፈለገን እጠቅሰዋለሁ። አሁን ከጽሑፉ አርዕስት ጋር በቀጥታ ስለሚገናኙት ጉዳዮች ላውራ።

 

በመጀመሪያ፣ ፀሐፊው ሻዕቢያ በትግራይ እና በአማራው ህዝብ ላይ፤ እንዲሁም ደግሞ ዚያድ ባሬ በአማራው ላይ ያራምዱት ስለነበረው የጥላቻ ፖለቲካ ጠቅሰው፤ ከሁለቱ ቡድኖች እጅግ በበለጠ ሀገራችንን የሚመለከታትን ህወሓት እራሱ በአማራ ህዝብ ላይ ያደርግ የነበረውን፤ በአሁኑ ጊዜም በአማራው እና “ጥገኞቻቸው” ናቸው ብሎ በሚፈርጃቸው እንደ ጉራጌ ባሉ ህዝቦች ላይ የሚያደርገውን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ አለመጥቀሳቸው ሊገባኝ አልቻለም። ምናልባትም ሊደርሱበት ለፈለጉት ድምዳሜ ስለማይረዳ (inconvenient) ይሆናል ብዬ ገመትኩ።

 

ሻዕቢያንና ዚያድ ባሬን የጠቀሱት ምን ያህል የጥላቻ ድርጊት ህዝቦችን እንደሚያጠፋ ለማሳየት ያህል ነው። ያንንም ለማሳየት የሶማሊያን ባሁን ጊዜ እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መዘፈቅ፤ ሻዕቢያም ባድመን ፍለጋ ቀብጦ ኢትዮጵያን ሲወር በህወሓት/ኢህአዲግ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን “እልም ያሉ የወያኔ/ኢህአዲግ ጠላቶች በተለይም አማሮች ጭምር” መሸነፉን ጠቅሰዋል። እዚህ ጋ ሁለቱን በጥላቻ የዘመቱ ቡድኖች ከኢትዮጵያ ጋ አወዳድረው (contrast አድርገው) ኢትዮጵያን እንደ አሸናፊ አድርገው ማሳየታቸው፣ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መሪ ስለሆነውና ከትግሉ ጅማሬ አንስቶ ልክ እንደሌሎቹ ቡድኖች ጥላቻን እንደ ስልት ስለተጠቀመው እና አሁንም በመጠቀም ላይ ስላለው ቡድን እንዳይናገሩ አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል። ምናልባት ይህንን ያልጠቀሱበት ሌላ ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል፤ እኔ ግን ከዚህ ጽሑፋቸው በመነሳት ያደረግሁትን ግምት ለመግለጽ ያህል ነው።

 

ከዚያም በተጨማሪ፣ የጽሑፋቸው አጠቃላይ ድምዳሜ በትግራይ ህዝብ ላይ በአሁኑ ሰዓት ሌሎች ህዝቦችን እንወክላለን ከሚሉ ቡድኖች እና ግለሰቦች የሚሰነዘረው ጥላቻ የሀገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው የሚል እና ያም ሁኔታ ከቀጠለ እሳቸው መገንጠልን ሊመርጡ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ መሰል መልዕክት ያዘለ ነው። እዚህ ጋርም ሥልጣን ላይ ያለው እና የትግራይን ህዝብ እወክላለሁ የሚለው ህወሓት ገና በትግል ሳለ ጀምሮ በአማራው ህዝብ ላይ እና በኢትዮጵያ ላይ፤ ዛሬም ደግሞ እሱና በሱ ቁጥጥር ስር ያለው ኢህአዲግ በተለያዩ ዘውጌ ማኅበረሰቦች ላይ የሚሰነዝሩትን የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ አልጠቀሱም።

 

በመጀመሪያ፣ በተለይ ጥላቻን የመሳሰሉ የሞራል ጉዳዮች ላይ ትምህርት ልስጥ ብሎ ተነስቶ እንደዚህ ግማሽ ወይም የተመረጡ እውነቶችን ብቻ መናገር (being selective) የአንባቢን አመኔታ ሊያስገኝ አይችልም። ሆኖም የሞራሉ ጉዳይ ሌላ እራሱን የቻለ ርዕስ ስለሆነ እንተወው። እኔ ለማተኮር የምፈልገው ጽሑፉ አፈና ባለበት ሀገር ምን ዓይነት ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል በማሳየት ላይ ነው። ይህ ጽሑፍ በምሳሌነት የሚያሳየን፣ እንደዚህ አደገኛ የሆኑ እና የተመረጡ ወይም ግማሽ እውነቶችን ብቻ ያዘሉ ጽሑፎች ኢትዮጵያ ውስጥ ጥላቻን በመዋጋቱ ፊና አዎንታዊ ውጤት ሊያመጡ ይቅርና፤ ይባሱኑ እንዋጋዋለን ብለው ለሚሉት ችግር አጋዥ እንደሚሆኑ ነው። ምክንያቱም የእኒህን ሰው ጽሑፍ ሊቃወሙ ወይም የጎደለውን ሞልተውበት ሙሉውን እውነት ለማሳየት የሚችሉት ግለሰቦችና ቡድኖች ታፍነው ነው ያሉት። በዛ ሁኔታ ደግሞ የዚህ ዓይነት ጽሑፍ ብቸኛው ተጠቃሚ የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ለይቶ ብቸኛው ተጠዪ እንደሆነ ለማሳየት በሚሞክር የፖለቲካ ስልት ተሰማርቶ የከረመው ህወሓት/ኢህአዲግ ነው።

 

ፀሐፊው እራሳቸው ምንም እንኳ ኢህአዲግ ባይወዳቸውም ጽሑፋቸውን ግን ለራሱ ፕሮፖጋንዳ ሲል ሊጠቀምበት እንደሚችል ጠቁመዋል። ደጋግመውም በማስጠንቀቂያ መልክ፣ ጽሑፋቸው “ገበያ ከመውጣቱ በፊት” ትግራይ ውስጥ እንደሚነበብ ተናግረዋል። እውነታቸውን ነው። ግን ውጤቱ ምንድን ነው?

 

ህወሓት እና የጥላቻ ፖለቲካ

ህወሓት፣ የትግራይን ህዝብ በራሱ ጥግ ላይ ለማስቀረት ሲል የተለያዩ የኢትዮጵያ ቡድኖች እንደሚጠሉት እና ሊያጠቁት እንደሚሹ ማስመሰልን ዋነኛ ስልቱ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው። በትግል በነበረበት ወቅት የተጠቀመው - ልክ እንደ ሻዕቢያ - በአማሮች ላይ ያነጣጠረን የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ነበር። አማሮች የሚኖሩት፣ የሚወጡትና የሚገቡት የትግራይን ህዝብ ለማጥፋት፣ ለማዋረድና ለርሱ የሚገባውን ክብር ለመንጠቅ እንደሆነ አድርጎ፤ ለዚህም እንደ ማስረጃ እንዲሆነው አልያም ሐሰተኛ ወሬዎችን በማስፋፋት ወይም ታሪክን በሚፈልገው መንገድ በመተርጎም በህዝቡ ላይ ጠዋት ማታ በራዲዮና በጽሑፍ ፕሮፓጋንዳ ያዘንብ ነበር። የአማራንም ህዝብ ከደርግ ጋር በማቆራኘት፣ የትግራይ ህዝብ ደርግ የሚያወርድበትን ግፍ - አማራውን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ያደርግ እንደነበረው - የአማራው ህዝብ እንዳደረገበት አድርጎ እንዲያይ አድርጎታል። በዛን ጊዜ በህወሓት ይነፉ የነበሩትን ፕሮፓጋንዳዎች ምሳሌ መስጠት ከጀመርኩ ጊዜም ቦታም ስለማይበቃኝ፣ በ1968 ዓ.ም. ካሳተሙት ከዚያ ዝነኛ ማኒፌስቷቸው ላይ አንድ ሁለት ዓረፍተ ነገሮችን ጠቅሼ ልለፍ፦

 

“የትግራይ ህዝብ ለረጅም ዘመን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቱ ተነፍጎ ሲጠላና ሲናቅ እንዲሁም አድልዎ ሲፈጸምበት ቆይቷል። ይህም በደል ጨቋኝዋ የአማራ ብሔር ሆነ ብላ እንደመንግሥት መመሪያዋ አድርጋ ስትሠራበት የቆየች ሲሆን ፋሽስታዊ ደርግም በባሰና በመረረ መንገድ ቀጥሎበታል።”3

 

ይሄና የመሳሰሉት ፕሮፖጋንዳዎችም በትግራይ ህዝብ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ከማድረጋቸው የተነሳ፣ የትግራይ ሰዎች አማራ የሆኑ ግለሰቦችን የሚያይበት አስተያየት አስጊ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎት ነበር። ዓለም ሰገድ ዓባይ የተባለ አንትሮፖሎጂስት ህወሓት/ኢህአዲግ ሥልጣን ላይ እንደወጣ ከሁለት ዓመት በኋላ በትግራይና በኤርትራ ጥናት አድርጎ በሁለቱ ህዝቦች የማንነት ስሜት ላይ በፃፈው መጽሐፍ ላይ እንደሚጠቅሰው ከስልሳ አራት በመቶ በላይ የሚሆኑ የትግራይ ተወላጅ ተጠያቂዎች በአማራ ዶክተሮች ለመታከም እንደማያምኑ መልሰውለታል።4 ለዚህም ፍርሃት ከተሰጡት ምክንያቶች ውስጥ አንድ አዛውንት እንደገለጹት አማራ ዶክተሮች ትግራውያን ምሁሮችን እንደሚገሉ መስማታቸውን ነው። ይህ የሚያሳየን በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ያለው የህዝቡ ፍርሃት የተያያዘው ከታሪካዊ ሽኩቻዎች ጋር ሳይሆን በዘመኑ ሆን ተብለው እንደ ህወሓት ባሉ ቡድኖች ከሚስፋፉ የሐሰት ውንጀላዎች ጋር መሆኑን ነው።

 

ይህ አማራውን ለሁሉም ነገር የመውቀስና የመወንጀል ነገር የህወሓት/ኢህአዲግ ዋነኛ ስልቱ እንደሆነ የምናውቀው ፓርቲው ጭንቅ በደረሰበት ጊዜ ሁሉ የሚያራግበው ስለሆነ ነው። ከቅርብ ግዜ ትዝታችን እንደምናስታውሰው፣ ከምርጫ 97 በኋላ ሀገሪቱ በአደጋ ተወጥራ በነበረችበት ጊዜ ህወሓት/ኢህአዲግ አማራውን እና “ጥገኛው” ብሎ የፈረጀውን የጉራጌን ህዝብ የሚያጠቁ ፕሮፖጋንዳዎችን በሰፊው ይዞ ተነስቶ ነበር። ጦማር ጋዜጣ ነኀሴ 18 ቀን 1997 ዓ.ም. እንደዘገበው፣ የሲዳማ ተወላጆችን በኢህአዲግ ፖሊሲዎች ላይ ሲያወያዩ የነበሩት የጊዜው የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር አቶ ተፈራ ዋልዋ፤ “የኦርቶዶክስ ኃይማኖት የነፍጠኞች መሸሸጊያ ነው። በዚህም ኃይማኖት የሚሸሸጉ አማራዎችና ጉራጌዎች ናቸው” ሲሉ የተናገሩት አንድ ምሳሌ ነው።5 ሚኒስትሩ እዚህ ጋ ምን ለማለት እንደፈለጉ ግልጽ ባይሆንም፣ አማሮችና ጉራጌዎች የሠሩት ሥራ ባይታወቅም መደበቅ የሚያስፈልጋቸው ህዝቦች እንደሆኑ ይጠቁማል። ይህም መልዕክት አዎንታዊ ካለመሆኑም በተጨማሪ አደገኛ ነው። ሪፖርተር ጋዜጣ ከሁለት ሣምንት በኋላ የዘገበው ዘገባ ግን ሚኒስትሩ የተናገሩት ነገር ህወሓት/ኢህአዲግ በጊዜው ይከተል ከነበረው ስልት ጋር እንደሚገናኝ የንግግራቸውን ምንጭ በመጥቀስ ይገልጽልናል። መስከረም 1 ቀን 1998 ዓ.ም. የወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ፣ “ዲሞክራሲና ዲሞክራሲያዊ አንድነት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ኢህአዲግ አሣትሞ ለውይይት ያቀረበው ሌላው መጽሐፍ “የትምክህት ዋነኛው ኃይል ከአማራው ጥገኛ በተጨማሪ ጉራጌው ነው” ሲል ማስፈሩን ይነግረናል።6

 

እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በጃንዋሪ 2006 በባህር ዳር በተደረገ ኮንፈረንስ ላይ በአማሮች ላይ የተደረገው ዘመቻ ቀጠለ። የኢህአዲግ ዜና አውታር በሆነው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ድረ ገጽ ላይ በወጣ መግለጫ ብጤ ጽሑፍ ላይ እንዳየነው የተለያዩ የኢህአዲግ አባል ፓርቲዎች “ትምክህተኛ አማሮች” በህዝቦቻቸው ላይ ያደረሱትን ግፍ ዘርዝረዋል። እነዚህ ትምክህተኛ አማሮች እነማን ናቸው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ በዕለቱ በህወሓት በተሰጠው መግለጫ በመጨረሻው አንቀጽ ላይ አቶ አዲሱ ለገሰ በሰጡት አስተያየት ውስጥ ይገኛል። “It seems that all the Amharas are chauvinists. But most of the Amhara people were oppressed by a few chauvinists.”7 (ትርጉም፦ እንደሚመስለው ከሆነ ሁሉም አማሮች ትምክህተኞች ናቸው። ነገር ግን አብዛኛው የአማራ ህዝብ በጥቂት ትምክህተኞች ተጨቁነው ነበር።) እውነቱን ለመናገር ለማለት የፈለጉትን ነገር እሳቸውም የሚያውቁት አይመስልም፤ በዛም ወጣ በዚህ ግን አዎንታዊ ዘመቻ ላይ እየተሳተፉ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ከሳቸው አባባል በመነሳት ግን ህወሓት/ኢህአዲግ “ትምክህተኛ” አማሮች እያለ በሀገሪቱ ውስጥ ለተፈጸሙ ታሪካዊ በደሎች ሁሉ ሁሌ በጅምላ የሚወቅሰው የአማራውን ህዝብ በሙሉ ነው ማለት ነው።

 

ከነዚህ ምሳሌዎች በተጨማሪም፣ ልክ ከምርጫው በኋላ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ መንግሥት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ስም መልዕክቶችን እያባዛ በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃትን የጠራበት ሁኔታ የሚረሳ አይደለም። በራሪ ወረቀቶቹ ለጋዜጠኞች በፋክስ ሲላኩ የተላከበትን ቁጥር በመከታተል ምንጩ የህወሓት ሰዎች ከሚያስተዳድሩት ንግድ ቤት ውስጥ እንደሆነ የደረሱበት ሰዎች ነበሩ። ከዚያም ባሻገር ግን የወረቀቶቹ ምንጭ ህወሓት/ኢህአዲግ እንደሆነ ከሚያረጋግጡት ማስረጃዎች አንዱ ቅንጅት በዚያን ጊዜ እንደዛ ያሉት ጥሪዎች ከርሱ እንዳልሆኑ ለህዝቡ ለማስታወቅ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኀን የላካቸው መግለጫዎች ሳይተላለፉ መቅረታቸው ነው።

 

ምክንያቶች

ህወሓት እንደዚህ ባሉ አፍራሽ ተግባራት የሚሳተፍበት ብዙ ምክንያቶች አሉት። በየጊዜው እየተነሳ አማሮችን ለይቶ በቃላት የሚያጠቃበት አንደኛው ምክንያት ራሱ ከሚፈጥራቸው ችግሮች የሰዎችን ዓይን/ቀልብ ለማግለል (to deflect attention) ይጠቅመኛል ብሎ ስለሚገምት ነው። ሌላው እና ዋነኛው ምክንያት ግን ከህልውናው ጋር በቀጥታ የተያያዘ እና ከትግራይ ህዝብ ድጋፍ ጋር የተገናኘ ነው። ህወሓት በጫካ የታገለው የትግራይን ህዝብ ከ”ትምክህተኛው አማራ ጭቆና” ነፃ ለማውጣት ነው። ለዚያም እንዲረዳው በአማራው ህዝብ ላይ ብዙ ስድብ አዥጎድጉዶ ታምኖለታል። ለዚያም ነው ትግራይ ነፃ ከወጣች በኋላ ወደ አዲስ አበባ የመቀጠሉን ጉዳይ የትግራይ ህዝብ መጀመሪያ ላይ አጥብቆ የተቃወመው - ህዝቡ የትግሉ ዓላማ ትግራይን ኢትዮጵያ ከሚሏት የአማሮች ሀገር “ነፃ” ማውጣት ስለመሰለውና ያም ሥራ ስለተጠናቀቀ።

 

ዛሬ ሥልጣን ላይ ወጥቶ በሁሉም ዘርፍ - በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካ እና በሰብዓዊ መብቶች፣ ሉዓላዊነትን ባለማስከበር፣ … ወዘተ - ቀድሞ ከወቀሳቸው ያልተሻለ፤ እንዳውም የባሰበት ሆኖ ተገኘ። ህወሓትን ህወሓት ያደረጉት መሰረቶች ሁሉ ተንደው ህልውናውን መከላከል ባለበት (having to defend its very existence) ሁኔታ ላይ ደረሰ። ለራሱ አዲስ ማንነትን (ወይም ሽፋንን) ለመፍጠርም ከአንድ የፖለቲካ ፍልስፍና ወደ ሌላው ሲዘል በየመሃሉ የሚከፈቱት ክፍተቶች መሞላት አለባቸው። ለዚህም መድኃኒቱ በህወሓት ቤት፣ የማይሞተውንና ዘለዓለማዊ የሆነውን፣ ሁልጊዜም የሚሰራውን የጥላቻ ፖለቲካ በመጠቀም እሱ የትግራይ ህዝብ የጥንት የጠዋት ጋሻና ከአማራውም ጠባቂው እንደሆነ ማስታወስ ነው። ይህ “ጅቡ አማራ ሊበላህ መጣ!” ማስፈራሪያ ካለፈው ተሞክሮው ምን ያህል እንደሠራለት ያውቃል።

 

ሌሎች የኢህአዲግ አባል ፓርቲዎችም በየተራው እየተነሱ አማሮችን እንዲሰድቡ የሚያደርገው - በግልጽ ከሚታየው ህዝቡን የመከፋፈል አጀንዳ ባሻገር - በትግራይ ህዝብ ላይ ለሚያደርገው ማስፈራሪያ ምስክር እንዳለው ለማስመሰል ነው።

 

የእኔነት (identity) ጉዳይ

ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ላንዳንድ ሰዎች አጥጋቢ አይሆኑ ይሆናል። እውነት ነው፣ እነዚህ ነገሮች ለኢህአዲግ ባህሪ ብቸኞቹ ምክንያቶች ላይሆኑ ይችላሉ። ብዙ ሰዎች፣ “ኢህአዲግ የፈለገውን ያህል ሥልጣን ቢፈልግ እንኳ፣ የፈለገውን ያህልም ትግራይን የብቻው ለማድረግ ቢፈልግ እንኳ፣ የጥላቻ ፖለቲካ ለሀገራችን የወደፊት ህልውና ምን ያህል አስጊ መሆኑን እያወቀ እንዴት እንደዚህ ያደርጋል? ኢትዮጵያ ሳትኖር የሱስ ሥልጣን የት ሊኖር ይችላል?” … ብለው ይሉ ይሆናል። ይህን የሚሉበት ምክንያት፣ ህወሓት/ኢህአዲግ በታሪካችን ወይም ባሁኑ ጊዜ በሀገራችን ከተፈጠሩና እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች መንስኤነት በምክንያታዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ገለጻ በመስጠት ፈንታ በየጊዜው እየተነሳ የአማራውን ወይም አንድ በጊዜው ያላማረውን ህዝብ በጅምላ ሲወነጅል የሚያደርገው ነገር ቢኖር ልጆቻችንም ነገሮችን ሁሉ እንደዛው በዘር አኳኋን እንዲመለከቱ ማስተማርን ነው። ትናንትና አፄ ምኒልክ (የአማራ ነፃ አውጪ ግንባር የሚል ቡድን መሪ ሳይሆኑ) እና ወታደሮቻቸው በአርሲ ላደረጉት ግድያ የአማራው ህዝብ በጅምላ ከተወነጀለ፣ ዛሬ የትግራይ ህዝብ ወኪል ነኝ በሚል ፓርቲ ቁጥጥር ስር ያለው መንግሥት የሚመራው ጦር በዓባይ ፀሐዬ እቅድ ላይ ተመስርቶ በኦጋዴን ያካሄደውን ጭፍጨፋ ነገ የኦጋዴኑ ወጣት ተነስቶ በትግራይ ህዝብ ላይ መለከኩ የማይቀር ጉዳይ ነው። የኦሮሞውም የአማራውም ልጆች የአሁኑ ሁኔታ ከቀጠለ እና የምክንያታዊነት ድምፆች መደፍጠጣቸው ከቀጠለ እንደዛ ማድረጋቸው የማይቀር ጉዳይ ነው።

 

“ታዲያ ምን ይሁን ብሎ ነው ኢህአዲግ ህዝቤ ብሎ በሚጠራው የትግራይ ህዝብ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የሚያዘጋጀው?” ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። የዚህ ደግሞ መልሱ ትንሽ ትንተናን ይጠይቃል። የአሁኖቹ የህወሓት መሪዎች በደም እና/ወይም በአስተሳሰብ የቀድሞው የትግራይ የገዢ መደብ ርዝራዦች (የልጅ ልጆች) ናቸው። (በአንድ ወቅት በጊዜው የነበረውን የማርክሲዝም መዝሙር መዘመራቸው አይረሳም። አሁንም ቢሆን የአገዛዝ ምሶሷቸውን ያቆምልናል ብለው የሚያስቡትን አንዳንድ የማርክሲስት ባህሪያት አስቀርተው ይዘዋል። ከዛ በተረፈ ግን፣ ህዝብ በየዓመቱ በሚራብበት ሀገር የነዚህ ሰዎች የዲዛይነር ሙሉ ልብስ ብቻ እንኳን ማርክሲስቱን ጭልጥ ያለን ካፒታሊስት ከመፎካከር ያለፈ ነው።) እነዚህ ገዢዎችም ኢትዮጵያን የሚያዩዋት በጥንት ጊዜ በሸዋና በትግራይ የገዢ መደቦች መሃል በነበረው የሽኩቻ መነጽር ውስጥ ነው። ለነሱ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ተቀባይነት ያላት ያ የትግራይ ገዢ መደብ እስከመራት ድረስ ብቻ ነው። ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ እስከመራት አይደለም፤ ይልቁንስ የዛ ገዢ መደብ አባል የሆነ የትግራይ ተወላጅ ብቻ። አጼ ዮሐንስ እንደሞቱ ጀግናው አሉላ አባ ነጋ በአፄ ምኒልክ ንግሥና ላይ ተቃውሞ ለማድረግ በተለያዩ መንገዶች ተንቀሳቅሰው ነበር። ነገር ግን ራስ አሉላ በትውልዳቸው ከገዢው መደብ ሳይሆኑ ከድህነት ተነስተው በአፄ ዮሐንስ አጋዥነትና በጀግንነታቸው ማዕረጋቸውን ያገኙ ስለሆኑ በትውልድ የገዢው መደብ አባላት የሆኑት እንቅፋት ሆነውባቸው የትግራይ ህዝብ በእሳቸው ዓላማ ዙሪያ እንዳይሰበሰብ ከልክለዋል። ልክ እንደዛው ዘመን ደግሞ ዛሬ በህወሓት አማካኝነት ትግራይ ውስጥ በሚነሱ እንደ አረና ትግራይ ባሉ የተቃዋሚ ኃይላት ላይ የሚደረገውን ጥቃት መመልከት ትችላላችሁ። እርግጥ ነው፣ ህወሓት/ኢህአዲግ ተቃዋሚዎችን በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ይቃወማል፤ ነገር ግን ትግራይ ውስጥ የሚካሄደው ዓይነት ጥቃት ከሁሉም ለየት ያለ ነው። ባጭሩ ህወሓት በትግራይ ላይ የይገባኛል ስሜት ይሰማዋል፤ ስለዚህም ሌሎች ተቃዋሚዎች (በትግራውያን የተመሰረቱ ፓርቲዎች እንኳ ቢሆኑ) ያቺን ምድር እንዲረግጡ አይፈቅድም። ከዚህም በተጨማሪ እንደ መለስ ያሉ ሰዎች ፓርቲው ውስጥ የሚያሳዩት ባህሪ ለሚሰማቸው “የይገባናል” ስሜት ምስክር ነው። መለስ ብዙ ጊዜ የፊውዳሎች ልጅ መሆኑን እየጠቀሰ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የበላይነቱን እንደሚያሳውቅ ይነገራል (“እኔ የፊውዳሎች ልጅ ስለሆንኩ ፖለቲካ ይገባኛል”፣ “እኔ የፊውዳሎች ልጅ ስለሆንኩ ሰዎችን ከኋላ መውጋት አልወድም”፣ … ወዘተ)።

 

ነገር ግን ይህ “ኢትዮጵያን እኛ ካልመራናት አንፈልጋትም” አካሄድ ዘላቂነት እንደሌለው ያውቃሉ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የብዙኀን ሀገር ስለሆነች ሌሎችም ተራቸውን መፈለጋቸው እና መቀመጫቸውን መነቅነቃቸው ስለማይቀር። ያኔ ደግሞ ወንበሩን ለመልቀቅ አይፈልጉም፤ ምክንያቱም የነሱ ገዢነት ለድርድር የሚቀርብ ስላልሆነ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ከዓመታት በፊት ትግል ላይ እያሉ ያነሱትን የትግራይን የመገንጠል ጉዳይ ከ1997 ምርጫ በኋላ መልሰው እንደቀሰቀሱት የተዘገበው።

 

እንግዲህ እውነት የትግራይን መገንጠል እንደ መጨረሻ ዕቅድ ይዘው ያሉ ሰካራም ኢኮኖሚስቶች ከሆኑ፤ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የሚያስተሳስረውን ነገር ረስቶ የብቻው የሆነ እኔነት (identity) በውስጡ መፈጠር እንዳለበት ይረዳሉ። ሰዎች ወይም ህዝቦች የእኔነት ስሜት እንዲሰማቸው አጠገባቸው ካሉት ሰዎች ወይም ህዝቦች የሚለያቸው ነገር ሊኖር ይገባዋል። ያንን ልዩነትም ደግሞ የሚያሳይ ግልጽ የሆነ መስመር ያስፈልጋል። እንደዛ የልዩነት መስመር ሆነው ከሚያገለግሉ ነገሮች ውስጥ አንዱ፣ አንዳንድ የሶሲዎሎጂ ወይም የአንትሮፖሎጂ ምሁራን እንደሚሉት፣ ሰዎቹ ወይም ህዝቦቹ የሚሰማቸው በሌሎች የመጠቃት ስሜት ነው። የትግራይ ህዝብ የህወሓትን ወደ አዲስ አበባ መቀጠል በተቃወመበት ጊዜ የራሱ የሆነን እና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የተለየን የማንነት ስሜት ወደ መፍጠር እና ማጎልበት ተጠግቶ ነበር ለማለት ይቻላል። ያ ደግሞ ሊሆን የቻለው፣ ለዓመታት የሚቃወመው በሌለበት በትግራይ ምድር ላይ በራዲዮና በጽሑፍ፣ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ህወሓት ባዥጎደጎዳቸው የጥላቻ ፕሮፖጋንዳዎች እና ደርግም ደግሞ ያንን ፕሮፓጋንዳ በማገዝ በትግራይ ህዝብ ላይ ባደረጋቸው ጥቃቶች አማካኝነት ነው።

 

ስለዚህ፣ ህወሓት የአማራውን ህዝብ በትግራይ ላይ ለተከሰቱት እና ለሚከሰቱት ችግሮች ሁሉ እየወቀሰና እያስወቀሰ፤ በትግራይ ህዝብ ላይም ያለ የሌለን ጥላቻ እየሰበሰበ የሚያጋንነው የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ተለይቶ በሱነቱ የመጠቃት ስሜት እንዲሰማው ነው። በተጨማሪም፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ለሚያደርጋቸው የተለያዩ ግፎች አላዋቂዎች ተነስተው - ልክ እሱ ለታሪካዊ ግፎች አማሮችን በጅምላ ሲወቅስ እንደነበረው - የትግራይን ህዝብ ቢወቅሱና ጥቃትን ቢፈጽሙ ለሱ የበለጠ ስኬት ነው። ምክንያቱም በዛ ምክንያት በህዝቡ ውስጥ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የተለየ የእኔነት ስሜት ሊፈጠር ስለሚችል። ያም ደግሞ ህወሓት ወደፊት ላቀዳቸው እቅዶች ያግዘዋል።

 

ማጠቃለያ

አቶ አብርሃም እንዳሉት ጽሑፋቸው በርግጥም ህወሓትን ይጠቅመዋል። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ግን፣ እውነትንም ሆነ ኢትዮጵያን አይጠቅምም።

 

ውድ አንባቢዎች፣ እዚህ ጋ መልሼ ቀድሞ ወዳነሳሁት ነጥብ ልመልሳችሁ። እንዳገራችን ባለ የተለያዩ ሃሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ በማይፈቀድላቸው ቦታዎች እንደ አቶ አብርሃም ጽሑፍ ያሉ ግማሽ እውነት የያዙ ወይም ደግሞ ጭራሽ እውነት የጎደላቸው ጽሑፎች ለገዢው ፓርቲ ዓላማ ስለሚጠቅሙ ብቻ ትልቅ መድረክ የማግኘት ዕድል ሲኖራቸው፤ እንደ እኔ የሳቸውን ጽሑፍ ለመፈተሽ እና የጎደለውን ሚዛናዊነት ለመስጠት የሚሹት ግን ይረገጣሉ።

 

እሳቸው ጥላቻ እየተሰነዘረ ያለው በትግራይ ህዝብ ላይ ብቻ እንደሆነ አስመስለው፣ የጥቂት ጽንፈኞችን ቅዠታም አመለካከት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሁሉ እንደያዘው አድርገው በማሳየት ከአስርተ ዓመታት በፊት የተጀመረውን የትግራይን ህዝብ አስፈራርቶ ከወገኖቹ የመለየት ሥራ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ያግዛሉ። እኔ ደግሞ፣ “በትግራይ ህዝብ ላይ እንደማንኛውም ህዝብ በጥቂት ጽንፈኞች አማካኝነት ጥላቻ ይሰነዘራል። ያ ማለት ግን የጽንፈኞች አቋም የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሁሉ ወይም የህዝብ አመለካከት ነው ማለት አይደለም። ‘አይደለም ጥላቻው ከጥቂት ጽንፈኞች ያለፈ ነው’ ብለው ቢሉ እንኳ የሠላምና የፍቅር ሰባኪዎች ድምፅ በታፈነበት እና ጥላቻን እንደ ስልት የሚጠቀመው ቡድን በነገሠበት ሀገር የጽንፈኞች አቋም የብዙዎች ሆኖ ቢያገኙት የሚያስደንቅ አይደለም። ልክ በትግራይ ህዝብ ላይ በጥቂት ሰዎችና ቡድኖች አማካኝነት ጥላቻ እንደሚሰነዘረው ሁሉ፣ የትግራይን ህዝብ እወክላለሁ በሚለው በህወሓት አማካኝነት በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ጥላቻ ሲሰነዘር ቆይቷል፤ አሁንም ቀጥሏል። ይህ ደግሞ የበለጠ ሊያሰጋ የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ ይህንን ትውልድም ሆነ ልጆቻችንን በትግራይ ሰው ላይም ሆነ በጉራጌ፣ በአማራ ላይም ሆነ በኦሮሞ ላይ ከሚሰነዘር የጥላቻ ቀንበር ለማዳን፤ የጥላቻን ፖለቲካ ግንባር ቀደም አድርጎ የሚሠራውን መንግሥት እና ለዛም እንዲረዳው የሚያደርገውን አፈና መቃወም አለብን” ባይ ነኝ።

 

አቶ አብርሃም በጽሑፋቸው ውስጥ ይሄ “ወያኔ የትግራይን ህዝብ ለማስፈራራት ሲል የፈጠረው ማስፈራራት” የሚባለው ነገር የትግራይ ልጆች የራሳቸውን አመለካከት መያዝ አይችሉም ብሎ እንደማለት እና አለማክበር እንደሆነ፤ እንዲሁም ደግሞ የትግራይ ልጆች የራሳቸውን አመለካከት መያዝ የሚችሉ እንደሆኑ ይጠቅሳሉ። በርግጥም እንደ እሳቸው ያሉ በምዕራቡ ዓለም ለመኖር የታደሉ ሰዎች የመማር ዕድል ያላቸው ከመሆናቸውም ባሻገር ከተለያዩ ምንጮች መረጃ ስለሚያገኙ እንደ ትግራይ ሰው ብቻ ሳይሆን እንደማንኛውም ሰው የራሳቸውን አቋም ሊይዙ ይችላሉ። ነገር ግን ሀገራችን ውስጥ ከጥቂት ዕድለኞችና ከከበርቴዎች ውጪ ያለው እውነታ የተለየ ነው። አብዛኛው የትግራይ ህዝብ እንደተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ምናልባትም በበለጠ ሁኔታ ለዘመናት በድህነት የቆዘመ፣ አብዛኞቹ ልጆቹ የትምህርት ዕድል ያላገኙ እና በዚህ ዘመን ደግሞ መረጃን ከተለያዩ ምንጮች የማግኘትን ዕድል የተነፈገ ህዝብ ነው። ስለዚህም፣ አዎን እንደማንኛውም የትምህርት ዕድልንና ነፃ መረጃን እንደተነፈገ ህዝብ ሁሉ ይወክሉኛል ብሎ ከሚያምናቸው ቡድኖች የሚመጡ መረጃዎችን የማመንና የመቀበል ሁናቴ ሊታይበት ይችላል (susceptible to manipulation)። ዓለምሰገድ ዓባይ የሠራው ጥናትም የሚያሳየን ይህንን ነው።

 

ይህ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወይም ማንኛቸውም የሰው ልጆች ሊጠመዱበት የሚችሉበት ችግር ነው። መንግሥት እንደዚህ የጥላቻን ንግግር በህዝባቸው ላይ ሲያወርድ ያዩ ሰዎችም በተቃራኒ ለሚመጡ ጽንፈኛና “ጥላቻን በጥላቻ” የመመለስን መርኆ ከሚከተሉ ቡድኖች ወይም ሰዎች ለሚመጡ አሉታዊ መልዕክቶች የተጋለጡ ናቸው።

 

በሀገራችን ያለው አፈና እንዳለ ሆኖ ደግሞ ጥላቻን በመዋጋት ስም “ጥላቻ ያለው አንተ ቡድን ጋር ነው”፣ “አይደለም ያንተ ጋ ነው” እያልን መጣላት ውጤት ካለማምጣቱም ባሻገር አፍራሽ ነው። በተጨማሪም ይህ በህዝቤ ላይ የሚደረግ ጥላቻ ካልቆመ ኢትዮጵያ የሚሏት ሀገር “ባፍንጫዬ ትውጣ” እና የመሳሰሉትን ማስፈራሪያዎች፤ ወይም ደግሞ የጥላቻን ክፋት በመተንተን ላይ ብቻ ያተኮሩ ንግግሮችና ጽሑፎችን መጠቀም ውጤት ሊያመጣ የሚችል አይመስለኝም። አንድ ጓደኛዬ ባንድ ወቅት ለሆነ ችግር ያማከረችው ፓስተሯ የነገራትን ዘዴ ላካፍል። “አንድ ብርጭቆ ንጹኅ ውሃ ውስጥ አፈር ቢገባ አፈሩን ቀጥታ በጣቶቼ ላውጣው ብሎ መሞከር ሞኝነት ነው። አፈሩ አይወጣም፤ ይልቁንስ ውሃው ውስጥ እንዳለ ይዳረሳል እንጂ። ነገር ግን ዝም ብለሽ ንጹኅ ውሃ ብትጨምሪበት ቀስ በቀስ ቆሻሻው እየተሸነፈ ሄዶ በስተመጨረሻ ሙሉ በሙሉ ንጹኅ የሆነ ውሃ መልሰሽ ታገኛለሽ” አላት። ልክ እንደዚሁ፤ ጥላቻን እና የመሳሰሉትን ችግሮች በስኬት መዋጋት የምንችለው ቀጥታ ጦር ይዘን በመግጠም አይደለም። በተቻለን መጠን በተበከለው ማኅበረሰብ ላይ አዎንታዊ መልዕክቶችን በማፍሰስ ነው። ማለትም፣ ለህዝቡ አዎንታዊ አማራጮችን በመስጠት። አዎንታዊ አማራጭ የተሰጠው ህዝብ ለጥላቻ መልዕክተኞች አይገዛም ወይም የመገዛት ዕድሉ እጅግ ዝቅተኛ ነው። በሀገራችን ውስጥ ያለው አፈና ግን እነዚህ አማራጮች ለህዝብ እንዳይደርሱ እየከለከለ ነው።

 

ከዚህ ቀደም እንደጠቀስኩት፤ የፍቅርና የሠላም ድምፆች ሲታፈኑ፣ ጥላቻንና አለመቻቻልን ያነገቡ ኃይሎች ይነሳሉ። ይህ ሀገራችንን ጨምሮ በብዙ ሀገር ታሪኮች የተከሰተ ጉዳይ ነው። ባሁኑ ጊዜ፣ ያታደልን ሆንንና መንግሥት መብታችንን ካላከበረ ከሥልጣን እናወርደዋለን ብለው ጠንካራ መንገድ የወሰዱ እንደ ግንቦት 7 ያሉ ቡድኖች እንኳ የጥላቻን መንገድ ሳይሆን የመቻቻልንና የይቅርታን መንገድ መርጠዋል። ከዚያም ምርጫቸው በመነሳት ነው በየቀኑ ወንጀልን በመፈጸም ላይ ላሉት የኢትዮጵያ መሪዎች አስቀድመው ይቅርታን እየሰጡ ያሉት።

 

ቀሪዎቻችንም፣ ከህዝብ መታፈን የተነሳ የጽንፈኞች አስተሳሰብ ገኖ የሀገራችንን ህልውና አደገኛ ወደ ሆነ ስፍራ ሳይወስደው እና መቻቻልን የማያውቁ ኃይሎች ከመነሳታቸው በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲከበር በተቻለን መጠን ሁሉ መታገል አለብን።

 

የሀገራችን ህዝብ ደግሞ የፍቅርንና የቸርነትን፤ ተቻችሎ የመኖርንና የመረዳዳትን አስፈላጊነት ለመረዳት ከበቂ በላይ የሆነ መሰረት አለው። ከዘጠና በመቶ በላይ የሆነው ህዝባችን ፈጣሪን የሚያመልክ ክርስቲያን ወይም እስላም ነው። በሁለቱም ኃይማኖቶች ያደገ ኢትዮጵያዊ ጎረቤትን ስለማክበርና ስለመርዳት፣ በኀዘን ጊዜያቸውም ስለማጽናናት አልተማረም ማለት ያስቸግራል። በተጨማሪም ከላይ እንደጠቀስኩት፣ ህዝቡ የተማረን የመስማትና ምክርን የማክበር ባህል አለው። ስለዚህ የተለያዩ ሃሳቦች ነፃ ሆነው በሚንሸራሸሩበት ሁኔታ ብዙኀኑ ሊመርጡት የሚችሉትን መንገድ መገመት አያዳግትም - ያም የፍቅርንና የመቻቻልን መንገድ ነው።

 

የነፃነታችን መከበር ጥላቻን ከመዋጋትና ከማሸነፍ ወዲያም የሚወስደን ነገር ነው። ሀገራችንን በተመለከተ አሳዛኝ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። የድህነታችን፣ የሉዓላዊነታችን ብዙ ግዜ መደፈር እና አለመመከት፣ እንዲሁም እነዚህ ነገሮች የፈጠሩት ስለወደፊት ዕድል ፈንታችን ያለን ፍርሃት የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ግን ሊያጠፉን አይችሉም። ሊያጠፋን የሚችለው፣ እነዚህን ችግሮች ለመፋለም እና/ወይም ችግሮችን ከመፋለም አልፈን ስለ ብልጽግናና ስለምጥቀት ለማውራት እና ለመመራመር የሚያስፈልገንን ዕውቀት እንዳንሸምት እና በነፃነትም ተማክረን ዘዴ እንዳንዘይድ የሚከለክለን በመንግሥታችን የተጫነብን አፈና ነው። መጽሐፉም “ህዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቷል” የሚለው ለዛ ነው።

 


 

1 “Ethiomedia Interview with Prof. Abigail Salisbury”, Ethiomedia, 24 April 2008,

http://www.ethiomedia.com/abai/ethiomedia_interviews_abigail_salisbury.html (21 August 2008)

2 አብርሃም ያየህ፣ “የጥላቻ-ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ህልውና ጠንቅ ነው፣” ኢትዮጵያ ዛሬ፣ ሐምሌ 30፣ 2000፣

http://www.ethiopiazare.com/articles/opinion/34-opinion/394-abraham-yayeh (21 August 2008)

3 የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት፣ “መግለጫ” (የካቲት፣ 1968)፣ ገጽ 15።

4 Alemseged Abay, Identity Jilted or Re-Imagined Identity? (The Red Sea Press, 1998), 155.

5 “ “የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የነፍጠኞች መሸሸጊያ ነው” አቶ ተፈራ ዋልዋ፣” ጦማር (ነሐሴ 18፣ 1997)

6 “ኢህአዴግ ቅንጅትን ከሻዕቢያ፣ አማራና ጉራጌን ከትምክህት ሃይሎች ጋር ፈረጀ፣” ሪፖርተር (መስከረም 1፣ 1998)

7 “Nations, nationalities in a new apirit[sic] of unity: Reflections of Bahir Dar Conference,” Walta Information Center, January 2006, http://www.waltainfo.com/Analysis/2006/Jan/9467.htm (21 August 2008)

 


አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ