Ethiopian PM Hailemariam Desalegn

ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ

ያሬድ ኃይለማርያም (ከብራስልስ)

የዛሬ ሦስት ዓመት ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓ›ም “ግፍና አፈና ዐመጽን ይወልዳሉ፤ የዐመጸኛ አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው (መ.ምሳሌ ም.22፣ ቁ.14)” በሚል አርዕስት ለንባብ ባበቃሁትና በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በገመገምኩበት ጽሁፍ ይህን ከትቤ ነበር፤ “አንድ ሕዝብ በላዩ ላይ ገዢዎች እየተፈራረቁበት ረዘም ላለ ጊዜ በአገዛዝ ሥርዓት ሥር ስር ሊቆይ ይችል። ይሁንና ዕድሜ ልክ የገዛ አፋኛ ሥርዓት ግን የለም። ሥርዓቱም እንደ ድርጅት፣ ሹማምንቱም እንደ ሰው የጉብዝና ዕድሜያቸው የተወሰነ ነው። የአፈናን ስልት በመለዋወጥና ሸምቀቆውን በማጥበቅም ዕድሜን ማራዘም የሚቻል ቢመስልም በተቃራኒዉ ውድቀትንም ያፋጥናል። ግፉ እየበረታና የመብት ጥሰቱም መረን እየለቀቀ በሄደ ቁጥር የሕዝብ ትእግስት ይሟጠጣል። ሕዝብ መቆጣት ከጀመረና ቁጣውም ወደ አደባባይ አመጽ በተቀየረ ጊዜ የግፍ አገዛዝ ወደ መቃብር፣ ግፈኞቹም ወደ ዘብጥያ እንደሚወርዱ እርቀን ሳንሄድ ባለፉት አምስትና አሥርት ዓመታት ውስጥ በአለም የታዩ ሕዝባዊ ነውጦችንና ያስከተሉትን መዘዝ ማጤን በቂ ነው።” የዚህ ጽሁፍ አላማም የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግ ቀን ይመጣል እያለ አምቆ የያዘው ብሶትና ክፌት ሊፈነዳ ጥቂት ስለቀረው ሥርዓቱ በጊዜ እራሱን ያርቅ፤ ካልሆነ ግን የማይቀረው አመጽ ይነሳል። የሥርዓቱም ፍጻሜ እንዳያምር ይሆናል። የሚል ማሳሰቢያ ጭምር ነበር። ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነገሮች እያፈጠጡ መጡ። ይህን ጽሁፍ ምሉውን ለማንበብ ከዚህ ገጽ ሥር ያለውን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ።[1]

ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት በማያባራ የሕዝብ ተቃውሞ ስትናጥ ቆይታለች። ከአንድ ዓመት በፊትም መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. “ግፍ በገፍ የሞላባት አገር” በሚል በጻፍኩት አጭር ጽሑፍ ይህን ሃሳብ አቅርቤ ነበር፤ “ከአፋኝና ታፋኝ የፖለቲካ አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልንላቀቅና ጭቆናን ታሪክ አድርገን ወደ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና ልንሸጋገር የምንችለው ግፉአን ብቻ ሳይሆኑ ግፍ ፈጻሚዎቹም አብረው ነጻ ሲወጡ ብቻ ነው። ስለዚህም አገርን የማዳን ትግሉ ለአገዛዝ ሥርዓቱ የመጨቆኛ መሳሪያ በመሆን እያገለገሉ ያሉ አጋር ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን ከወያኔ ጉያ ማውጣትና የሕዝብ ወገንተኛ እንዲሆኑ ማድረግን ዋና ግቡ ማድረግ አለበት። ለዚህም በመሳሪያ አቅም፣ በፖለቲካ አደረጃጀት፣ በገንዘብም አቅም ይሁን ሰፊውን የአገሪቱን ክፍል በማስተዳደር ዕረገድ የማይናቅ ድርሻ ያላቸውን ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ሌሎች አጋር ድርጅቶችን የትግሉ አካል እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ከወዲሁ ማመቻቸት ትግሉን ከማፋጠን ባለፈም ሊደርስ የሚችለውን የጥፋትና እልቂት አደጋም የመቀነስ ኃይል ይኖረዋል።[2]

የአገዛዝ ሥርዓቱ በጠመንጃ ብቻ ሊቆጣጠረው ያልቻለውን የሕዝብ ቁጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግና የፈላጭ ቆራጭነት ስልጣን የተሰጠው ኮማንድ ፖስት በማዋቀር ቁጣውን ለማፈን ያደረገውም ጥረት ከሽፏል። ለዚህም ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በተጠናከረ መልኩ የቀጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጥሩ ማሳያ ነው። ይህ የተቀጣጠለው ተቃውሞ እያደርም ሥርዓቱን ይቦረቡረው ጀምሯል። ትላንት ፊታቸውን ከልለው የተቃውሞ ምልክት በእጆቻቸው እያሳዩ ለሕዝባቸው ድጋፍ ይሰጡ የነበሩ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ዛሬ በይፋ ከሰልፈኛው ጋር ተቀላቅለው ድጋፋቸውን ሲሰጡ በግላጭ እያየን ነው። ከሥርዓቱ ምስረታ አንስተው በከፍተኛ አመራርነት ላይ ያገለገሉ ባለስልጣናትም፤ አባዱላ ገመዳ እና በረከት ስምዖንን ጨምሮ የጊዜውን መጨላለም አይተው ሳይዳፈን በፊት ገለል ማለታቸው ሌላው ሥርዓቱ ክፉኛ መታወኩን ማሳያ ምልክት ነው። ሌሎች በግልጽ ጎልተው የሚታዩ በርካታ ምልክቶችንም መጠቃቀስ ይቻላል።

በጡንቻ የተገኘ የፖለቲካ ሥልጣን ልክ እንደ ሰው ዕድሜ ነው። ልክ እንደ ሰው እጅግ አስጨናቂ በሆነና እንደምጥ ህመም መገለጫ በሌለው ስቃይ ይወለዳል። እንቦቃቅላ፣ ጨቅላ፣ ታዳጊ ልጅ፣ ወጣት፣ ጎልማሳ፣ ሽማግሌ እያለ ዕድሜ ከሰጠውም እስከ መጃጀት ደርሶ ወደ ማይቀረው ሞት ያቀናል። ልዩነቱ የሰው ልጅ ይህን የዕድሜ እርከን ሙሉውን የሚዘልቀው ከ70 ዓመታት በላይ መኖር ሲችል ነው። ከዚያ በታች ሲሆን ሂደቱ እንደተቋረጠ ነው የሚቆጠረው። ከ60ዎቹ በታች ሲሆን ህልፈቱ የዛ ሰው ህይወት በጊዜ እንደተቀጨ ነው የሚቆጠረው። አንድ የአገዛዝ ሥርዓት በሥልጣን ስንት ዓመት ሲቆይ ነው ጎለመሰ፣ አረጀ ወይም ጃጀ የሚባለው?

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰፈነባቸው አገሮች ያለውን አሰራር መነሻ ያደረግን እንደሆን በሥልጣን ላይ የሚቆየው ኃይል ህድሜው የሚወሰነው በሕግና በየወቅቱ በሚካሂዱ ምርጫዎች ላይ በሚገኝ የሕዝብ ድምጽ ነው። በእነዚህ አገሮች ሕግ አንድ ግለሰብ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ለምን ያህል ጊዜ በሥልጣን መቆየት እንደሚችል በግልጽ ስለሚደነገግ የሕዝብን ቅቡልነት ቢያገኝም እንኳን ሥልጣን ይዞ የሚቆይበት ጊዜ ከ8 እስክ 12 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ የተወሰነ ነው። የሕግ ልጓም ያልተበጀለት፣ ሕዝብም የስልጣን ባለቤት ባልሆነበት፣ የሥልጣን ምንጩም ሆነ ዋስትናው ጠመንጃ በሆነበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የአገዛዝ ሥርዓቱ ዕድሜ የእንድ የሽማግሌን ሰው ዕድሜ ግማሽ ወይም እሩቡን ያህል ይዘልቃል። ለዚህም ያለፉትን ሦስት ሥርዓቶች፤ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአረብ አገራት አንባገነኖችን የሥልጣን ዕድሜ ማሰብ በቂ ነው።

የአንባገነን ሥርዓቶች ወደ ሥልጣን አመጣጥም ሆን ከሥልጣን መገለል ልክ እንደ ሰው ልጅ ውልደትና ሞት በስቃይ፣ በህመምና በጭንቅ የተሞሉ ናቸው። የሰው ልጅ ዕድሜው ገፍቶ እርጅና ሲጫጫነው ጉልበቱ ይርዳል፣ አቅሙ ይሳሳል፣ ጉብዝናውም ተንጠፍጥፎ ያልቃል፣ ወኔው ይከዳዋል፣ እግርና እጆቹን እንኳ ማዘዝ ይሳነውል፤ ባናቱ ላይ ዕድሜን ተከትለው በሚመጡ የጤና መታወኮች የተነሳ ስቃይም ይበረታበታል። “ሲያልቅ አያምር” እንደሚባለው በዚህ የዕድሜ እርከን ውስጥ ሲደረስ የሰው ልጅ ከመቼውም ጊዜ በበለጥ የማይቀረውን ሞት ሌት ተቀን ያሰላስላል። እንደ የእምነቱም ፈጣሪው አሟሟቱን ከስቃይና ከመጉላላት የጸዳ እንዲያደርግለት “አሟሟቴን አሳምረው” እያለ በጸሎቱ ይማጸናል። በእርጅና ላይ ስቃይ፣ ህመምና መጉላላት ሲታከልበት ውሎና አዳር ከወደ አልጋ ስለሚሆን እንኳን ለታማሚው ላስታማሚውም አይመችም። በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰው በሕክምና ስቃዩን ያስታግሳል እንጂ ሞትን ጨርሶ ሊያስቀር አይችልም። በተመሳሳይ ሁኔታም በጉልበት የተያዘ ስልጣን እንደፈረጠመና አስፈሪ እንደሆነ አይዘልቅም። በሥልጣን ያፈረጠሙት ጉልበት ይዝላል፤ በእብሪት ያበጠውም ልብ ይሟሽሻል፤ የተማመኑበት ክንድም ይርዳል፤ የጉልበተኝነቱ ስሜት በፍርሃት የዋጣል። ያኔ ተንቀው የነበሩ ትናንሽ ኃይሎች ብርታት ያገኛሉ። የሚተማመንበት ጉልበቱ የከዳው ሥርዓትም ሌሎችን በኃይል የማዘዝና የመጨፍለቅ አቅም ስለሚያጣ ለአጭር ጊዜ ቢውተረተርም ጣሩን ያራዝም ይሆናል እንጂ መፈራረሱ አይቀርም።

ታዋቂው የውጭ ፖሊሲዎች ተንታኝና ጸሐፊ የሆነው Moisés Naim, “The End of Power”, በሚለው ግሩም መጸሐፉ ላይ የአንባገነኖች ሥርልጣን እንዴት እንደሚከስምና መዘዙን በግልጽ ይዘረዝራል። የሕግ ልጓም የማይገዛው፣ ያልተገራና በጥቂት ጉልበተኞች እጅ ብቻ የሚገኝ የተከማቸ የፖለቲካ ሥልጣን መጨረሻው እንደ ድንገተኛ ጎርፍ ነው። በዙሪያው ያለው አሰሱን ግብስብሱን ሁሉ ጠራርጎ ወዴት እንደሚተም አቅጣጫው አይታወቅም። በአንድ ግለሰብ ወይም ጉልበተኛ ቡድን ተሰብስቦ የተያዘም የፖለቲካ ሥልጣን ወይም ኃይል በሌሎች ትናንሽ ኃይሎች ተጠልፎ ሲወድቅ የሕዝቡን መብት፣ ጥቅምና ደህንነት የሚያስጠብቅ ሌላ ጠንካራ ኃይል እስከሚፈጠር ድርስ ባለው ክፍተት ውስጥ አገርና ሕዝብ ለከፋ አደጋም ይጋለጣሉ። እንደ ጸሐፊው አገላለጽ የአንድ ጉለበተኛ ሥርዓት መንኮታኮት (Decay of power) ለተገፋውና በአፈና ውስጥ ለቆየው ሕዝብ ትልግ ደስታና ግልግል የመሆኑን ያህል በአገር ደረጃ ደግሞ ይዟችው የሚመጣቸው አደጋዎች አሉ። ሥርዓት አልበኞች፣ ጽንፈኞችና አክራሪዎች፣ የውጭና የውስጥ ጠላቶች እድሉን ለመጠቀም አመቺ ሁኔታ ሲለሚፈጠርላቸው በዙ ጊዜ ዝርፊያ እና ደም አፋሳሽ ግጭቶች ይከሰታሉ። Moisés ስጋቱን በመጽሐፉ ገጽ 221 ላይ በዚህ መልክ ይገልጸዋል፤

“Celebrating the benefits of the decay of power should not lead us to ignore that a glass that is half-full is also half-empty. The decay of power also entails dangers. … It has facilitated the rise of extremist politics – whether separatist, xenophobic, and sectarian – in established democracies and fledgling political systems.”

ኢትዮጵያም ዛሬ የተንጠለጠለችበት አፋፍ ይህ አስፈሪ ሁኔታ እየተቃረበ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የወያኔ አገዛዝ ሥርዓት እርጅናውን አገባዶ የሞትን ባብር ከሚጠብቅበት ፌርማታ ላይ የደረሰ ይመስላል። ስለሆነም ከወዲሁ ሊከሰቱ የሚችሉትን አደጋዎች አይነትና መጠናቸውን በዝርዝር ማወቅ ሕዝቡና ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ የሚታገሉ ኃይሎች የበኩላቸውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ይረዳል። የአደጋውንም መጠን ለመቀነስና አይቀሬውም ለውጥ ደም አፋሳሽ በሆን መልኩ እንዳይጠናቀቅ ከወዲሁ ሁሉም የበኩልን ድርሻ እንዲወጣ ለማስገንዘብ ይረዳል ብዮ ስለማስብ ለእኔ የሚታዩኝን አድጋዎችና የመፍትሔ ሃሳቦች በመጠቆም ጽሁፌ ልደምድም።

አደጋዎች፤

  • ሰሞኑን የጀመረው ተቃውሞ በዚሁ ከቀጠለ ሥርዓቱ የአስቸኳይ ጊዜውን አዋጅ እረዘም ላለ ጊዜ በድጋሚ ሊያውጅ ይችላል። ምናልባትም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሚመራውን የሲቪል አስተዳደር ሰላምና መረጋጋትን በአገሪቱ ማስፈን ተስኖታል በሚል ሽፋን በኮማንድ ፖስት ስም የተዋቀረው ወታደራዊ ኃይል እንዲተካውና የአገሪቱን አስተዳደር ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠረው ሊደረግ ይችላል።
  • ይህ ከሆነ ደግሞ የመከላከያና የደህንነት ኃይሉ ቁልፍ ቦታዎች በህውሃት ቁጥጥር ስር ሰለሆኑ ለይስሙላ የተቀመጠው የኢህአዴግ ፌዴሬሽ በይፋ ፈርሶ አገሩቱ በአንድ ወታደራዊ ቡድን እጅ እንድትቆይ ሊያደርግ ይችላል።
  • ይህ ደግሞ የክልሎችን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ ስለሚችል ግጨቱ የሚሆነው በወያኔ እና የአጃቢነት ሚና በነበራቸ የክልል መንግሥታት መካከል ይሆናል። ይህ ፍትጊያ አሁንም እየታየ ስለሆን አፍጦና አግጦ ይወጣል። እንደ Moisés Naim አገላለጽ ይህ አይነቱ ፍትጊያ ጉልበተኛ ሆኖ የቆየው ኃይል ሥልጣን መባቻ ላይ መድረሱን ከሚያሳዩት ምልክቶች መካከል አንዱ ነው።
  • የተጀመረው የሕዝብ ተቃውሞ መልኩን ስቶ ወደ ከተማ አመጽ ከተቀየረ ግጭቱን በአስቸኳይ አዋጅም ሆነ በጠመንጃ መቆጣጥር የማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል። ነገሮች ወደዚህ አቅጣጫ እያመሩ ለመሆናቸውም ከወዲሁ በአንዳንድ ሥፍራዎች ባለፉት ሁለትና ሦስት ቀናት ምልክቶች ታይተዋል። በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የሚገኙ የክልሎቹ ታጣቂዎች የተቃውሞው አካል ከሆኑና ሕዝባችን ላይ አንተኩስም የሚል አቋም ከያዙ የሕዝባዊው ተቃውሞ መልኩን ሊቀይር ይችላል።
  • ይህ ከሆነ ግጭቱ በፌዴራል መንግስቱ ሥም ግጭት ወደተነሳባቸው ሥፍራዎች በሚላኩ ልዩ ታጣቂ ኃይሎችና በክልል ታጣቂዎች መካከል ይሆናል። ይህ ሁኔታም ወያኔን ከማዳከም አልፎ አገሪቱንም ወዳልተፈለገ ደም አፋሳሽ ሁኔታ ሊከታት ይችላል።
  • ሥርዓቱን በተመጣጠነ ኃይል ሊፎካከርና ሊታገል የሚችል የተቃዋሚ ኃይል እንዳይፈጠር በመደረጉ በአሁን ሰዓት ያለውን የፖለቲካ ውጥረት በኢህአዴግ እና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል ሳይሆን በአንድ በኩል በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ ባሉ ድርጀቶች መካከል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሥርዓቱና ሆድ በባሰውና ጭቆና ባስመረረው ሕዝብ መካከል የአልገዛም፣ ትገዛለህ ትንቅንቅ እንዲሆን እድርጎታል። በመላ የአገሪቱ ተቀባይነት ያለውና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይል አለመኖሩ ደግሞ ትግሉን አገራዊ ቅርጽ እንዳይዝ ያደርገዋል። እየሆነ ያለውም ይሄው ነው።
  • ይህ የተደራጀና አገራዊ እራዕይ ያለው የፖለቲካ ኃይል ሳይሆን በብሶት በቻ እየተመራ በየመንደሩ ከሥርዓቱ ጋር የሚካሄድ ትንቅንቅ እያደር ኢትዮጵያን ላለመበታተኑና እና ግጭቱም በጎሣ ላይ እያነጣጠረ ላለመሄዱ ምን፣ ዋስትና የለም። በቅርቡ በኦሮሚያና በሱማሌ ክልላዊ መንግሥት መካከል የተስተዋለው መናቆርና መናናቅ፤ ያስከተለውም ደም አፋሳሽ ሁኔታ እንደምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል።

ተስፋዎቻችን፤

  • የመጀመሪያው ተስፋ ሰጪ የሆነው ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔን ጨምሮ ከተለያዩ አክራሪ ጎሰኞች ሲረጭበት የኖረውን የዘረኝነት መርዝ ተቋቁሞ ዛሬም ‘አይንተ ትብስ አንተ ትብስ’ እየተባባለ ዘርና ኃይማኖት ሳይወስኑት እጅ ለእጅ ተያይዞ በአብሮነት መቀጠሉ ነው። ወደፊትም እንዲሁ እንደሚቀጥል ብዙ የተስፋ ምልክቶች እያየን ነው።
  • ሌላው ተስፋ ህውኃት ሕዝብን ለማፈኛ በመሳሪያነት የሚጠቀምባቸውን ግለሰቦች፣ ታጣቂዎች፣ አጋር የፖለቲካ ድርጅቶችና ተቋማትን ጠላት አድርጎ መፈረጅ የሥርዓቱ ጡንቻ እንደፈረጠመ እንዲቆይ ማገዝ መሆኑን ብዙ ሰው እየተረዳው የመጣ ይመስለኛል። ከፍረጃ ፖለቲካ መላቀቅ ከቻልን እነዚህን አካላት እያስደነበርን ሥርዓቱ ከሌለ አብረን እንጠፋለን የሚል የተሳሳትና የብልጣብልጥ ስሌት እንዲያሰሉ በማድረግ የሥርዓቱ መሳሪያ በመሆን ሕዝባቸውና አገራቸውን እየበደሉ እንዲኖሩ እናደርጋቸዋለን። በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት ከሥርዓቱ ጋር ተለጥፈው የሚገኙትን ኃይሎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ የሚደረገው ትግል አካል ማድረግ ለውጡን ማፋጠን ብቻ ሳይሆን ያንጃበቡትንም የመተላለቅ አድጋዎች ይቀንሳቸዋል ብዮ አምናለሁ።

ለማንኛው ኢትዮጵያን ለዘመናት የተጣባትና ከአንድ ግፍኛ ወደ ሌላ ግፈኛ ሥርዓት የመገለባበጥ አዙሪት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያከትምና ሕዝብም የአገሩና የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን የበኩላችንን ድርሻ እየተወጣን “የሥርዓቱንም አሟሟት አሳምርልን” ብሎ መጸለዩ አይከፋም።

ቸር ያሰማን!

ያሬድ ኃይለማርያም

ከብራስልስ

ጥቅምት 19፣ 2017 እ.አ.አ

 

[1] https://humanrightsinethiopia.wordpress.com/2014/12/19/%E1%8C%8D%E1%8D%8D%E1%8A%93-%E1%8A%A0%E1%8D%88%E1%8A%93-%E1%8B%90%E1%88%98%E1%8C%BD%E1%8A%95-%E1%8B%AD%E1%8B%88%E1%88%8D%E1%8B%B3%E1%88%89/

[2] https://humanrightsinethiopia.wordpress.com/2016/03/14/%E1%8C%8D%E1%8D%8D-%E1%89%A0%E1%8C%88%E1%8D%8D-%E1%8B%A8%E1%88%9E%E1%88%8B%E1%89%A0%E1%89%B5-%E1%8A%A0%E1%8C%88%E1%88%AD/

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!