Bekele Gerba

አሳሪያቸው ያልታወቀው አቶ በቀለ ገርባ

ይገረም አለሙ

“አይተዳደርም ሁለት ኮርማ አንድ ቤት

አንዱ ተሸንፎ ካላለ አቤት አቤት” ውርሰ ቃል

በዘመነ መሳፍንትም በሉት በፊውዳሉ፣ በአጼውም ይሁን በወታደራዊው ወይንም በተጋዳላዮቹ በየትኛውም የኢትዮጵያ የመንግሥትነት ዘመን አንድም በሕገ ሥርዓቱ አለያም በጉልበቱ የነገሠ ንጉሠሠ ነገሥት ነበር። በመሆኑም በየአካባቢው ራሱን የሚያነግሠውም ሆነ በንጉሠ ነገሥቱ የሚሾመው ንጉሥ እንዳሻው አይሆንም። ሥልጣኑ ገደብ ኀላፊነቱ ልክ አለው። ጡንቻው ሕሊናውን አደንዝዞት፣ አለያም ከማን አንሼ እብሪት ተጠናውቶት ራሴ ንጉሥ ነኝ የምን ለንጉሥ ማደር ነው ብሎ ያሻውን ለመሥራት ቢሞክር፣ ትዕዛዝ አልቀበል አላከብር ማለት ቢዳዳው በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝና ውሳኔ አንድም በሕግ እንዲያም ካለ በጉልበት አቅሙን እንዲያውቅ ልኩን እንዲረዳ ይደረጋል።

አቶ መለስ ግለሰብም፣ ፓርቲም፣ መንግሥትም በነበረበት ዘመን ለጠቅላይ ገዥነት ለንጉሠ ነገሥትነት የመብቃቱ ምክንያት ለሥልጣን ከነበረው ስስትና፤ ሌባ እናት ልጇን አታምንም እንዲሉ ሆኖበት የፈጸመው በመሆኑ ያደረሰው ጥፋት ጥሎት፣ የሄደው የከፋ ሥርዓት ከኢትዮጵያ እንዲህ በቀላሉ የሚነቀል አይደለም። ሰውየው በሕግ ባልተጻፈ በድርጅታቸውም ውሳኔ ባላገኘ አቆላልፎ የመግዛት ተንኮል ሴራው ከሁሉ በልጦ ሁሉን በርቀት አቁሞ ሲሻው እንደ ባለሥልጣን እያስጠገና እያዘዘ፤ ሲሻው ደግሞ ከደጅ አስቁሞ እንደ አሽከር እያመናጨቀና በአደባባይ ጭምር እያዋረደ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ ለመኖሩ ሲሠራ እንደነበር ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰው ሊክደው የሚችለው አይደለም። ሆድን በጮማ ቢደልሉት፣ መንፈስን በአልኮል ቢያደነዝዙት ሕሊና የሚባለው ነገር እንደ ሙጀሌ መነዝነዙ አይቀርም።

የአቶ መለስን እኩይነት በቁሙ ከምናውቀው ከሞቱ በኋላ የተረዳነው ይበልጣል። እኛ በተቃውሞ ጉራ የተሰለፍነው አይደለንም፤ ከሕወሓት ጀምሮ በየደረጃው አባልም አጋርም የሚል መሸንገያ የተሰጣቸው ሁሉ አደባባይ አውጥተው አይናገሩት እንጂ የመለስ ተንኮልና ሴራ ግልጽ ብሎ የታያቸው ከሞቱ በኋላ ይመስለኛል።

የተነሳሁት ስለ መለስ እኩይነት ለመጻፍ አይደለም፤ ብዙ የተባለበትም ነው። አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ንጉሠ ነገሥት አልባ ንጉሥነት የመለስ ሥራና ሴራ ውጤት መሆኑ ነው ከመለስ እንድነሳ ያስገደደኝ። የመለስን ሥራና ሴራ መለስ ብሎ ላጤነው ሲሻው አገሪቱ በጠቅላላ ሥርዓት የሚባል ነገር የሌለባት ያስመስላታል፤ ሲሻው ንጉሠ ነገሥት የሌላቸው ንጉሦች ያሻቸውን የሚያደርጉበት ፍጹማዊ ሁኔታ ያለ በማስመሰል ይጠቀምባቸዋል ብቻ ሳይሆን፤ እየጠለፈ ለመጣልም ይጠቀምበታል። በምንም ተአምር ግን ንጉሠ ነገሥትነቱን አያስደፍርም። ለመደፋር የሞከሩት እነ ስየና ተወልደ የደረሰባቸው ጊዜው ሩቅ አይደለምና አይረሳም።

ዛሬ የኢትዮጵያ የመንግሥትነት ታሪክ ከመሰረቱ ተለውጦ እነማን መሆናቸው አይደለም፤ ጭራሽ ቁጥራቸው የማይታወቅ የሚታዩም የማይታዩም አንድም እራሳቸውን ያነገሡ ሁለትም ከእነርሱ ፍርፋሪ በሚከጅሉ አጨብጫቢዎች፣ አጋፋሪዎችና አዳናቂዎች እየታጀቡ እኔም በቦታዬ ንጉሥ ነኝ ያሉና ለመሆንም የሚዳዳቸው፣ ያለምንምና ማንም ሀይ ባይነት ኢትዮጵያን እያመሷት ሕዝቡንም ቁም ስቅሉን እያሳጡት ነው።

ሁለት ዝሆኖች ሲራገጡ ሳሩ መጎዳቱ ባይቀርም አንዱ ማሸነፉ ስለማይቀር ከተራራ ላይ ሆነህ ተመልከት ፍልሚያው ሲያበቃ አሸነፊው መድከሙ ስለማይቀር ያኔ በትኩስ ጉለበት አሸናፊው ላይ ጉብ ማለት የሚል አባባል መኖሩ ቢታወቅም የእኛ ንጉሠ ነገሥት አልባ ንጉሦች ማንነታቸውም ሆነ ብዛታቸው ብሎም የትነታቸው ስለማይታወቅ እንደዝሆኖቹ ምሳሌ እስኪለይላቸው ብሎ ለመጠበቅ የሚቻል አይደለም። እንደውም አንዳንዶቹ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ሥራቸውን የሚያከናውኑት በሌሎች በመሆኑ እነርሱ ተለይተው ሳይታወቁ አገርና ሕዝብ ሊያልቁ ይችላሉ።

ለዚህ ቀላሉና የቅርብ ማጣቀሻ የሚሆነን የአቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ ነው። አቶ በቀለ በዋስ እንዲፈቱ የወሰነው ጠቅላይ ፍርድ ቤት እዛ ውሳኔ ላይ የደረሰባቸውን ህጋዊ ምክንያቶች በዝርዝር ገልጹዋል። በመሆኑም እንኳን ተወካይ እየላከ ችሎቱን የሚከታተለውና የውሳኔው ግልባጭ የሚደረድሰው ማረሚያ ቤት ቀርቶ ዜናውን በመገናኛ ብዙሀን የተከታተለው ሁሉ በቀላሉ የሚረዳው ነው። ከሁሉም በላይ ክሱ ከሽብር ወደ መደበኛ ሕግ ተቀይሮ እየተከራከሩ ባሉበት ጉዳይ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ ከታሰሩት ግዜ በላይ የማስያፈርድባቸው በመሆኑ የሚለው አጽኖኦት የሚሰጠው ነው። እንደው የጉዳዩን እንዴትነት ይበልጥ ለማሳየት ይህን አልኩ እንጂ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ካልተስማማው አቃቤ ሕግ ይግባኝ ይጠይቃል እንጂ ማረሚያ ቤት ፍርድ ቤት ያሰናበተውን ታሳሪ አልቅ የሚልበት ወይንም ፍርድ ቤቱን ሽቅብ ተጠራርቶ ማብራሪያ የሚጠይቅበት ምንም የሕግ መሰረት የለም። አለ የሚል ካለ በመጮህ ሳይሆን አንቀጽ ጠቅሶ ያስረዳ።

የዳኝነት ሥልጣን የሚለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 በንዑስ አንቀጽ 1 “ በፌዴራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው” ይልና በቁጥር 2 ላይ ደግሞ “በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማናቸውም የመንግሥት አካል፣ ከማንኛውም ባለሥልጣን ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተጽኖ ነጻ ነው” በማለት በማያሻማ ቃል የሚገልጠው ሕገ መንግሥት ይህን ብሎ ብቻ ሳያበቃ በንዑስ ቁጥር 3 ላይ “ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነጻነት ያከናውናሉ፤ ከሕግ በስተቀር በሌላ አይመሩም” ይላል። የቂሊንጦው ባለሥልጣናት ተግባር እነዚህንና መሰል የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች የሚረጋግጥ ነው። ታዲያ የዚህ ጽሁፍ አብይ ጭብጥ የሆነው ጥያቄ የሚነሳው እዚህ ጋር ነው። ባለሥልጣናቱ የቱንም ያህል በፖለቲካ ቢታበዩ በጥላቻ ቢታወሩ በእብሪት ቢሰክሩ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አቅምም ሞራልም አላቸው ወይ ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ አረ እንዴት ሆኖ የሚል ይሆናል። ምክንያቱም አይደለም ንጉሥ መሆን ለመሆንም የሚመኙ አይደሉምና በምን አቅማቸው። አቅመ ቢስ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ማመዛዘኛ ህሊና የሌላቸው መሆናቸው ሌሎች እንደፈለጉ የሚጠቀሙባቸው እቃዎች (አድራጎታቸው ይህ ስለሆነ ነው፣ ለቃሉይቅርታ) ስላደረጋቸው ከጀርባ ሆነው ለሚሻኮቱት ንጉሦች የመሻኮቻው ሚዳ ሆነው በሜዳው ላይ ያገኙትን ሁሉ ይረግጣሉ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ማንነት፤ እንዴት ብሎ የሚጠይቅ ወኔ የላቸውምና ነገ ለፍርድ ሊያስቀርባቸው የሚችል የሕገ መንግሥት ጥሰት በገሀድ ይፈጽማሉ።

የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመናኛ ካድሬ ሲጣስ ዛሬ የመጀመሪያ ሆኖ አይደለም ይህን ማንሳቴ። በፊት የሚደረጉት ሁሉ በጠቅላይ ገዢው በንጉሠ ነገሥት መለስ ስለነበር ድርጊቱም አድራጊውም አስደራጊውም በግልጥ ይታወቅ ነበር። ለምሳሌ በአጋጣሜ ተገኝቼ የአይን ምስክር ለመሆን የበቃሁበት በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ችሎት በዋስ የተፈታው ስየ የችሎቱ ውሳኔ ተጥሶ ታፍኖ ተመልሶ ወደ እስር ቤት የተላከው ጠባቂዎቹ ከአቶ መለስ በደረሳቸው የራዲዮ ትዕዛዝ ነው። የበቀለ ገርባን ግን ማን ሊሆን ይችላል ብለን ብዙ ንጉሦችን እያነሱ ከመጣል ባለፈ እገሌ ነው ብሎ መናገር የሚቻል አይመስለኝም። ስሙን ካነሳሁ አይቀር ደጋግሜ በጋዜጣ ጠይቄው ያለመለሰልኝን ጥያቄ ለስዬ ላቅርብ። የአፈና መዋቅሩን ከአደራጁት አንዱ ነህና እንዴትና በምን ሁኔታ ለምንስ ዓላማና ግብ ብታዘጋጁት ነው አንተን ከዶሮ ማነቂያ አፍኖ ለመውሰድ የቻለው? አንተን “ጦርነትን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን መሥራትም የምትችለውን” ቀንደኛ ህውሀት ከመንገድ አፍኖ ለመውሰድ የበቃ የአፈና መዋቅር ለሌላው ዜጋ ይበገራል ብሎ ማሰብ እንደማይቻል እየታወቀ ይህን በመጽኃፍም ያለማንሳትህ ለምን ይሆን?

ንጉሠ ነገሥት አልባ ንጉሦች ለመበራከታቸው ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ቢቻልም ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው። ከወራት በፊት በሶማሌ እና በኦሮምያ ክልሎች መካካል የተቀበረውን የመለስ ቦንብ አፈንድተው ሲራኮቱ የሁለት አገር ግጭት እንጂ በአንድ ፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ያሉ ክልሎች፣ በአንድ ንጉሠ ነገሥት የሚመሩ ንጉሦች አይመስሉ እንደነበር ታዝበን አልፈናል። ግን ግን እናንተዬ ስኳር ነጋዴው ንጉሥ የትኛው/የትኞቹ ሆነው ነው እኛ በ60 ብር ኪሎ ስኳር አጥተን በሕገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ስኳር የጫኑ መኪናዎች በቀያችን አያልፉም ባሉ ዜጎች ላይ አምቦ ላይ ጥይት እንዲዘንብባቸው ለማድረግ የቻሉት። እነዚህ ላቅ ያለ ሥልጣን ያላቸው መሆን አለባቸው። እንደው መቼስ ይሆን የአገራችን ታጣቂዎቸ ካነገቱት መሳሪያ የሚሻሉ የሚሆኑት? እኛስ መቼ ይሆን ግፉ ጎፍንኖን በወያኔ መገዛት በቃን አራት ነጥብ የምንለው። (በቃል ሳይሆን በተግባር በስሜት ሳይሆን በእምነት)

እነዚህ እየተደራደርን ነው የሚሉን ምን ብለን እንደምንጠራቸው የቸገሩን የዘመናችን ጉዶችስ ከየትኛው ንጉሥ ወይንም ንጉሦች ጋር ይሆን የሚደራደሩት? ሊነግሩን ይችላሉ፡ ጉዶች ማለቴ ነገር ለማካበድ ብዬ አይደለም፣ አይነት ብዛታቸው የማይታወቁት ንጉሶቻችን በሥልጣናችን አትምጡ እያሉ ከሚፈጽሙት ግድያ አልፈው ምንስ ወዴትስ ብንነግድ ምን አገባችሁ ማን ሆናችሁ ነው የእኛን መኪና መንገድ የምትከለክሉ ብለው ጦር አዝምተው ግድያ ከፈጸሙ ሰዎች ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር ይህንንም እንደ ጀብዱ ማውራት ጉዶች ሊያሰኛቸው የሚችል ሆኖ ስለታየኝ ነው።

ሌላው አስገራሚ የእኛ ነገር ራሳቸውን ካነገሡት ወይንም ለማንገሥ ከሚጣጣሩት መካከል ንጉሥ ምርጫ መያዛችን ነው። አንድ ሰሞን አንዱን የብአዴን ሰው ማሞካሸቱ ጣራ ነክቶ ነበር። ምን ቢያሰማምሩት ብረት ወርቅ አይሆንም እንዲሉ ያ ብዙ የተባለለት ሰው መሆን የሚችለው ራሱን እንጂ የሚባለውን አይደለምና የሆነውን ሆነ። ሰሞነኛው ተሞጋሽ ባለ ሳምንት ደግሞ ከኦሕዴድ ሆኗል። ይህም በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ ወይንም ሰልፋችን ከዚህ ነው ከሚሉት ውስጥ ግልጽ ዓላማና ግብ የሌላቸው መኖራቸውን የሚያሳይ ነው። 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ