ወያኔ

ወያኔም ያታልላል፤ እኛም እንታለላለን

ፊልጶስ

አሁን … አሁን ”'ከልሂቃኑ እስከ ኢ-ልሂቃኑ” ድረስ፤ ቀድም ብሎ ሙሶሎኒያዊያንና ሂትለራዊያን፤ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሻዕቢያዊያንና ወያኔያዊያን፤ እንዲሁም ኦነጋዊያን ከባንዳ አያቶቻቸውና አባቶቻቸው የተቀበሉትን የፈጠራና የጥላቻ ታሪክ ስላወሩትና የሥልጣን ኮርቻውን ስለተፈናጠጡት፤ የሚናገሩትና የሚጽፉት ሁሉ እንደ እውነት ተቆጥሮ፤ “በኢትዮጵያ ሕዝብ መኻል ጥላቻና በደል አለ!” መባሉ ነው።

በኢትዮጵያዊያን መኻል ጥላቻም ሆነ በደልና ቂም በቀል የለም። እኛ ኢትዮጵያኖች እንደ ሸማ ድር ተሸምነን፤ ልዩነታችን አንድነታችን፣ አንድነታችን ልዩነታችን፣ ልዩነታችን ውበታችን፤ ከምንም በላይ ደግሞ በሰውነታችን መከራውንም ደስታውንም አብረን ለዘመናት ያሳለፍን መሆናችንና ወደፊትም በአንድነታችን ጸንተን እንደምንቀጥል፤ በዚች ሰዓት እንኳን ለተጠራጣሪዎችና ለወያኔያዊያን አይደለም፤ ከምድረ-ገጽ መጥፋታችን እንደማለዳ ፀሐይ ለሚናፍቁ ሀሉ እያስተማርናቸው ነው።

ትላንትም ሆነ ዛሬ ያለው እውነታ፤ ጥላቻና ቂም በቀል ያለው፤ ...

1ኛ- ከታሪካዊ የአገሪቱና የሕዝቧ ጠላቶች ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ እውን ለማድረግ ከተሰለፉ ባንዳዎች መንደርተኞች፤

2ኛ- የሥልጣን ኮርቻ ለመፈናጠጥ አቋራጭ መንገድ በሚፈልጉ መሃይማንና ተማርን ባይ ጉልበተኛ ቡድኖችና ግለሰቦች፤

3ኛ- ምንም ዓይነት አገራዊ ሆነ ወገናዊ ስሜት ባልተፈጠረባቸው በግል ጥቅም በታወሩ ግለሰቦችና ቡድኖች መኻል ነው።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፤ ለማ መገርሳ ባህርዳር ሂዶ ደጉን ስለጎበኘ፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚተርክ በቴሌቭዥን ስለታየ፤ እርቅ እንደወረደና ወያኔም ችግር ላይ እንደወደቀ ተደርጎ ይሰበካል። ዕድሜ ልካቸውን ውሸት ሲናገሩ የነበሩ ሰዎች፤ ዛሬ ላይ ለፖለቲካ ፍጆታ በወያኔ ት'ዛዝ፣ የነበረንና ያለን እውነታ ስለተናገሩ እንዴት እንደተዓምር ሊቆጠር ቻለ?

”... በስምንተኛው ሺ በያዝነው ዘመን

ውሸት ገኖ አዘዘው፣ ሰው መስሎ ሰውን። ...” አሉ አሉ ወሎየው።

በመጀመሪያ ደረጃ ማንና ማን ነው የተጣለውና ያስጣለው?

ለማና ገዱስ ማንን ነው የሚወክሉት? ማንስ ነው የወከላቸው?

እነዚህ ሰዎች በወያኔ አዝማችነት በአገርና በሕዝብ ላይ ስንት ጉድ ሠርተዋል?

ግድያውም ሆነ የጥላቻ ሰበካውና ሐውልት ማቆሙ የሚካሄደው ”ቦለቲከኛ” ነን በሚሉት እንጂ፤ በየትኛው የሕዝብ መሃከል ነው?

ለመሆኑ ለማና ደጉ እንዲገናኙ ማን ፈቅዶላቸው ነው? ከወንበሩስ ያስቀመጣቸው ማን ነው?

ወያኔ ማጠፊያ ሲያጥረው አቅጣጫ ለማስለወጥና ለማታለል መሆኑ ለሩብ ዓመታት አሳልፈንም እንዴት ግንዛቤ እናጣለን?

ተደራጅቶ የሚታገለው ያጣው ወያኔ፣ የሕዝብ አመጽ ግን ግራ እያጋባው ትቢያና አቧራ እየላሰ መነሳቱ ከ'ኛ ይልቅ እየገረመው የመጣው ለራሱ ለወያኔ ነው። ታዲያ ወያኔ ወጥመድ ውስጥ እንዳለች አይጥ ሆኖ በሚሠራው ድራማ፤ እኛ ደግሞ ታዳሚዎች በመሆን አብረን እናጭበጭባለን። በወያኔ ቦይ መፍሰሳችንን አቁመን፤ የራሳችን የቤት ሥራ መሥራት ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚል ዜጋ ሁሉ የሚጠበቅ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው። ጊዜው ደግሞ ነገ ወይም ከነገወዲያ አይደለም፤ ዛሬ እንጂ።


ፊልጶስ

ጥቅምት 2010 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!