Former Ethiopian President Girma WoldeGiorgis

፳፻፯ ዓ.ም. የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የመሰረተ ድንጋይ ሲያኖሩ

ሥዩም ወርቅነህ

አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኘው አንባገነን፣ አፓርታይድና ዘረኛው የወያኔ/ሕወሓት-ኢህአዴግ ሥርዓት ሕዝብ የሚፈልገውን ይቅርና የሥርዓቱ ጀሌዎች የለፈፉትን እንደማያስፈጽም እሙን ነው። ይህ ደግሞ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግልፅ የሆነ ጉዳይ ነው። ድፍን ኢትዮጵያዊ በሚባል ደረጃ ወያኔ/ሕወሓት-ኢህአዴግ የሙሰኛ፣ የፀረ-ኢትዮጵያዊና የዘረኞች ሥብሥብ መሆኑን ይሥማማል። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ተሥማምተውና ተፈቃቅደው እንዳይቀጥሉ ሌት-ከቀን እየሠሩ መሆኑ ግልፅ ነው። ሥርዓቱ በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ አገራችንና ሕዝባችን ለችጋር እንደሚጋለጡና ሥርዓቱ ካልተወገደ የመበታተን አደጋም እንደሚገጥመን ሳንወድ በግድ የምንቀበለው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል።

Guragee Zone
የቀድሞው ፕ/ት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ያኖሩት የመሠረት ድንጋይ

ወያኔ/ሕወሓት-ኢህአዴግ ምርጫ በመጣ ቁጥር ሕዝብን ለማጭበርበር በሁሉም የሕብረተሰባችን ክፍል እየዞረ አስቧቸው የማያውቃቸው የልማት ተግባሮችን እሠራለሁ በማለት የመሰረት ድንጋይ እንደሚያስቀመጥ የተለመደ ጉዳይ ነው። ሕዝባችንም ይህን የማጭበርበሪያ ተግባር በአግባቡ ስለሚረዳ ሥርዓቱን እንደማይመርጥ የሚታወቅ ነው። ወያኔ/ሕወሓት-ኢህአዴግ ምርጫን ለማሸነፍ የሚጠቀምበት ምርኩዝ ምርጫ ቦርድ ሲሆን፤ ለተቃውሞ የወጡትን ለመቀልበስ፤ የሚገድልበት፣ የሚያስርበት፣ የሚደበድብበት፣ የሚያስርበትና የሚያስፈራራበት ምርኩዝ ደግሞ የሥርዓቱ መከላከያ ሠራዊት ነው።

Guragee Zone
በ፳፻፲ የፈረሰው የቀድሞው ፕ/ት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ያኖሩት የመሠረት ድንጋይ

የወያኔ/ሕወሓት-ኢህአዴግ ሥርዓትን አንቅረው ከተፉት የአገራችን ማኅበረሰብ ውስጥ የጉራጌ ማኅበረሰብ አንዱ ነው። በተከታታይ በተደረጉ አገራዊ ምርጫዎች ድምፁን በመንፈግ በተግባር አሳይቷል። በዚህም ምክንያት የማኅበረሰቡ ተወላጆች ሠርፈ ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለዋል። ይህን ደግሞ የሚቀለበስ ጉዳይ አይደለም። “ሚሥማር ሲመቱት ነው የሚጠብቀው” እንደሚባለው ሁሉ፤ የጉራጌ ማኅበረሰብም ሥርዓቱን ላይመለስ ለማስወገድ ታጥቆ ተነስቷል። ይህን የተገነዘበው የወያኔ/ሕወሓት-ኢህአዴግ ሥርዓት፤ ከ7 ዓመት በፊት ሕዝቡ ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ሊገነባው ያሰበውን የጤና፣ የትምህርትና የግብርና ማዕከል፤ ብሩን በመዝረፍ በቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የተጣለውን መሰረተ ድንጋይ በማፍረስ፣ ሊሠራ የታሰበው መሰረተ ልማት እንደተሰረዘ ገልጿል። ይህ በጣም አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባር ነው።

በመጀመሪያ ማዕከሉ የሚገነባው የጉራጌ ማኅበረሰብ ባዋጣው ገንዘብ እንጂ፤ ከሥርዓቱ ከሚደጎም በጀት አልነበረም። ሲቀጥል በጉራጌ ዞን የጤና የትምህርትና የግብርና ማዕከል ባለመኖሩ ሥርዓቱ ማኅበረሰቡን እያስገደደ እየገዛና ግብር እያስከፈለ ስለሆነ፤ መሰረታዊ ተቋማትን የመገንባት ግዴታ አለበት። የጉራጌ ማኅበረሰብ ለፍቶ ያመጣውን ገንዘብ ከመመዝበር አልፎ ሕዝብን እያስጨፈሩ የተጣለውን መሰረተ ድንጋይ በአንድ ግንበኛ አፍርሶ "ተቋሙ አይገነባም ወደ ትግራይ ክልል ተቀልብሷል" ማለት ሥርዓቱ ለጉራጌ ማኅበረሰብ ያለውን ከልክ ያለፈ ንቀትና ጥላቻ በግልጽ ያመለክታል። ይህ ደግሞ የጉራጌ ማኅበረሰብ ቢያበረታው እንጂ የሚያሰንፈው ጉዳይ አይደለም።

ይህ ሥርዓት ወደ ሥልጣን ከመጣ 27 ዓመት ቢሞላውም ለጉራጌ ሕዝብ ነቀርሳ ከመሆን ውጪ አንድ ልማት ያመጣው ነገር የለም። የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የተገነባው በማኅብረሰቡ ጉልበትና ሀብት ነው። ለመላው የጉራጌ ማኅበረሰብ ያለው አንድ ሆስፒታል ብቻ ነው። ሕዝብ ሲታመም የሚታከምበት ሆስፒታል ሳይገነቡ፣ በራሱ ተነሳሽነት ሀብትና ንብረቱን አሟጦ ሊገነባው ያሰበውን ማዕከል ጭምር እየቀለበሱ ለሕዝብ የቆምኩ ነኝ ብሎ መለፈፍ ከቀልድም ያለፈ ጅልነት ነው።

ጉራጌ ንቃ!

ትግላችን ይቀጥላል!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!