በኤርትራ በቀር ወደ ኢትዮጵያ ነፃነት የሚወስድ መንገድ የለም

አባኪያና ጓደኞቹ ከካናዳ - ነኀሴ 2000 ዓ.ም.

ኤርትራን እንደ አገር፤ ሻዕቢያን እንደ አጋር

ብዙዎቻችሁ ይሄ ቀጥዬ የምጽፈው ነገር፤ ገና ከርዕሱ ወደላይ ሊላችሁ ይችላል። ለምደነዋል። ሃሳብን በነፃነት በመግለጽ መብት ብናምንም፣ ብዙ ራሳችንን እንደ ዲሞክራት የምንቆጥር ሰዎች በፖለቲካችን ውስጥ የሚሰነዘሩ አንዳንድ ሃሳቦች ሽቅብ ሽቅብ ሲሉን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተመልክቻለሁ። ሃሳብ እንደተመልካቹ ነው። አንዳንድ ሰዎች የኤርትራ ነገር እይይይይይይ … ሊያሰኛቸው ይችላል። አንድ ምልከታ ነውና አልቃወምም።

 

በጣም አንድ አንድ ሰዎች ደግሞ የኤርትራ ነገር፣ በቃ በሆኑ ኃይሎች መካከል በሆነ ምክንያት ሲደረግ እንደነበረ ትንቅነቅና ባንደኛው ኃይል አሸናፊነት እንደተጠናቀቀ ትግል ልናይም ጀምረናል። ደርግ ኢትዮጵያን ሻዕቢያ ደግሞ ኤርትራን ወክለው ሲዋጉ ኖሩ። አንዱ አሸነፈ። ሕይወት ግን በሌላ ምእራፍ መቀጠል አለበት። እንደ ቅንጅት ማለት ነው። ትናንት ቅንጅት ነበር። በመካከል የሆነው ሆነና ዛሬ ደግሞ አንድነት ሆኖ ኢህአዴግን እንደ ገና ድፎ በሁለት በኩል የማንገረገቡ ሂደት ውስጥ ባለፈው ሳምንት ያገኘውን ፈቃድ ይዞ የውስጥ ትግሉን ይቀጥላል። ሌሎች ታጋዮችም፡ እንደ ቅንጅት በአገር ውስጥ መንቀሳቀስ ካልመረጡ፡ እንደ ታጋይ ታጋይ ሆነው መጓዝ ከፈለጉ፡ በሰፊው የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ፈቃድ፡ በጠባቡ ደግሞ የጎረቤት አገሮች ፖለቲካዊና ቁሳዊ ምጽዋት ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ኤርትራ።

 

አንዳንድ ሰዎች፡ ምን አንዳንድ ሰዎች፡ ብዙ ሰዎች ኤርትራን ለትጥቅም ይሁን ለሌላ መሰል የአመጽ ትግል፡ እንደ ትግል አጋር አድርጎ መያዝ ወይም መጠቀም ይቻላል ብለው አያምኑም። ለዚህ ደግሞ ከበቂ በላይ ማስረጃዎችን ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች ዋንኛው፡ ቀደም ሲል ሻዕቢያ እንደ ሽፍታ አሁን ደግሞ ኤርትራ እንደ መንግስት ኢትዮጵያን ለማጥፋት የቆሙ ነበሩ ወይም ናቸው። አሁንም አልተኙልንም አይተኙልንምም የሚል ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ከኤርትራ ጋር መስራት አይቻልም ብለው የሚያምኑት ሰዎች ይሄን አሳበቸውን የሚሰነዝሩት፡ እንደኤርትራዊ ሳይሆን እንደኢትዮጵያዊ እያሰቡ ነውና የሀሳቡን አስኪያጅነት በተገቢው አያሳዩም ብዬ አጠንክሬ እናገራለሁ።

 

የሻዕቢያን የቀደመ ጸረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ መካድ ባንችልም፡ አሁን ባለው የአፍሪካው ቀንድ ሁኔታ፡ እንደሻዕቢያ ወይንም እንደኤርትራዊ ወይንም እንደኤርትራ መንግስት ቢያስቡ ግን ይህ እምነታቸው ይለወጣል ብዬ አምናለሁ። አሁን ባለው የዚያ አካባቢ ጠቅላላ ሁኔታ፡ ለኛ ጸረ-ኢህአዴግ እንቅስቃሴ ለምናደርግ ሀይሎችም ይሁን፡ ለራሳቸው ለኤርትራዊያን መለስን ለመጣል፡ ጥለውም፡ ለኤርትራዊያን እንደልባቸው የሚዋዋሏት ኢትዮጵያ፡ ለኛም እንደ ሀሳባችን ኢትዮጵያን መልሰን ለመገንባት የተሻለው መንገድ ከኤርትራ ጋር መስራት ነው ብዬ እጽፋለሁ። ስለዚህ ባለፈው ሰሞን አቶ ኤልያስ ክፍሌ መሸጥ የያዘውን ይህንን ከኤርትራ ጋር የመስራት ሀሳብ ለማጣጣልና ዋጋ ለማውረድ የተሰነዘሩ ትችቶች ሁሉ፡ እርባና ቢስ ናቸው ብዬ ባላጣጥልም፡ የዚህን ሀሳብ አይቻሌነት ከማብራራት ይልቅ በአቶ ኤልያስ ደምና ትውልድ ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው፡ ጎዶሎ ናቸው። በኔ በቀር ወደአብ የሚደርስ የለም ተበሎ በታላቁ መጽሀፍ እንደተጻፈው፡ በኤርትራ በቀር ኢትዮጵያን በቶሎ ማዳን አይቻልም፡ ቢቻልም በዳዴ ነው ብዬ እተነብያለሁ።

 

አንደኛ፡ ከጭቅጭቅ ያልጸዳ ሀሳብና የተሳሳተ ፍረጃ

አሁን ደግሞ አኛ እያልኩ ልጻፍ፤ ይሄ ሀሳብ የኔ ብቻ አይደለምና። ከኤርትራ ጋር እንስራ የሚለው ሀሳብ ከክርክር የጸዳና የማያጨቃጭቅ አይደለም። በመሰረቱ በሌላ ጽሁፋችን ከዚህ በፊት እንደጻፍነው፡ ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት የምንከተለው መንገድ ሁሉ ከጥያቄና ከንትርክ የጸዳ አይደለም። ኢትዮጵያን ከወያኔ ነጻ ከማውጣት ጋር በተያያዘም ይሁን፡ ወደፊት በሁሉም መስክ የተሻለች ለማድረግ፡ ሁሉም የሚስማሙበትና ከክርክር የጸዳ መፍተሄ አለኝ የሚል ካለ እሱ ቱልቱላ መንፋት እንለዋለን። ስለዚህ ከኢትዮጵያ ትግል ጋር በተያያዘ ዋናው ጥያቄ፡ ከክርክርና ከትችት የነጻ መፍትሄ ማግኘቱ ላይ ሳይሆን የምናስበወ መንገድ በትክክል የምንፈልገው ቦታ ሊያደርሰን ይችላል ወይ ነው። በመሆኑም ሰዎች ወይም ድርጅቶች በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችም እንጂ፡ በሚከተሉት መንገድ ብቻ መጥፎዎች ወይም ጸረ-ኢትዮጵያ ተብለው የመፈረጅ ባህል ስህተት ነው። ወያኔ/ኢህአዴግን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ በጫካ ከተከተለው መንገድ ይልቅ አጠንክረን ያወገዝነው፡ የጠላነውም ስልጣን ከያዘ በኋላ ባደረገውና በፈጸመው ግፍ ነው። የትናንቱ የወያኔ አካሄድ ከጭቅጭቅና ከውዝግብ ያልጸዳ ቢሆንም፡ የበለጠ ያቃጠለን፡ በየትም ብሎ በየት ስልጣኑን ከያዘ በኋላ የሰራው ነው። ወያኔ ከጸረ-ኢትዮጵያ ሀይሎች ጋር ሁሉም ቢሆን ተባብሮ ደርግን መጣሉ ሳይሆን፡ ደርግን ጥሎ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት የሚሰራው ጸረ-ኢትዮጵያ ስራ ነው እንድንጠላው እንድንዋጋውም ያደረገን። ወያኔ እንደ አንድ ቡድን ደርግን አሸንፎ፡ ስልጣን ከያዘ በኋላ በከፈትነው አዲስ የህይወት ምእራፍ የሰራው እየሰራም ያለው ግፍ ነው ያቃጠለን፡ የሚያንገበግበንም እንጂ፡ አስቀድሞ የሰራው የተከተለው ጸረ-ኢትዮጵያ ሀይሎችን ሁሉ የመጠቀም ስልቱ አይደለም።

 

አሁንም ለምሳሌ የሰላማዊ ትግሉን እናደርጋለን ብለው አገር ቤት የተሰለፉትን ድርጅቶች አካሄድ የማይደግፉ ሀይሎች፡ ያ ትግል የማይቻልበትን ምክንያት በመደርደር ያንን መንገድ የሚከተሉትን ቡድኖች ይነቅፋሉ። በተቃራኒው ደግሞ፡ ባለሰላማዊ ትግሎቹም የአመጽ ትግል አራማጆችን ይነቅፋሉ። ዞሮ ዞሮ ሰው የሚያዋጣውን መንገድ የሚያውቀው እሱ ነው። እና ስላላመንበት ብቻ ያ መንገድ አያስኬድም ማለት አንችልም። ሁሉም መንገዶች ደግሞ የራሳቸው መልካምና መጥፎ ጎን አላቸው። የዚህ የኤርትራ በኩል ትግል ደግሞ፡ እንደው አሁን አሁን ትንሽ ትንሽ ቀና እያለ እየተሻለ መጣ እንደሁ እንጂ፡ ከኤርትራ ጋራ በተያያዘ ያልጠገገ ቁስል ስላለንና ኤርትራ ለረጅም ግዜ ለኢትዮጵያ ጠንቅ ሆና ስለቆየች፡ አሁንም ብዙ ሰዎቸ ኤርትራ እንደ ኦብነግ እና ኦነግ ያሉ ተገንጣይ ሀይሎችን አገሯ ላይ በማሰለፏ ምክንያት፡ የዚህ የኤርትራ ጉዞን በከፍተኛ ሁኔታ ይቃወማሉ። እንደማንኛወም ስልት፡ የዚህ በኤርትራ በኩል እንግባ የሚለው ሀሳብ ብዙ መተንተን፡ መበተን፡ መበለት እና መሰለቅ እንዳለበት ይታመናል። በዚህም መሰረት፡ የለም ይሄ ሀሳብ አያስኬድም፡ ወደምንፈልገው አቅጣጫ አያራምድም ብሎ መከራከር አንድ ነገር ነው። ከዚያ ውጪ ግን ሌላ ከክርክር የጸዳ ሰማያዊ ስልት የሰነቁ ይመስል ብድግ ብሎ በህይወታቸው ነገር ግን ባመቻቸው መንገድ በኤርትራም ጭምር የተሰለፉ ኢትዮጵያዊያንን ለማውገዝ መነሳት፡ በተዘዋዋሪ ወያኔን ማገዝ ነው። አሸናፊዎች ሁሉ ያሸነፉበት ስልት ከማሸነፋቸው በፊት ከክርክር የራቀ አልነበረምና ከክርክር የጸዳ ኢህአዴግን ማንበርከኪያ ስልት አለኝ የሚል ካለ ለሱ ስሰግድ ልኖር እምላለሁ። ራሳቸው ሕወሀቶችና ሻዕቢያዎች የተከተሉትን ስልት መጥቀስ እንችላለንና።

 

ሁለተኛ የጥቅም አንድነትና የቁጭት አንድነት፤ እንደሻዕቢያ ሳስብ፡ የሚጠቅመኝን አውቃለሁ

አንዱ ከኤርትራ ጋር እንድንሰራ የሚነሽጠን ምክንያት፡ ኤርትራ በመገንጠሏ አገር ነኝ ወይም ሆንኩኝ ከሚል ባዶ ኩራት በስተቀር ያተረፈችው እምብዛም ቁሳዊና ኢኮኖሚያዊ ነገር አለመኖሩና፡ በነሱም በኩል ያሰቡትና የተመኙት ባለመምጣቱ ከዚህ በኋላ እንደ አገር፡ አገር ሆኖ ለመኖር፡ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ መስራቱን አይጠሉትም የሚል ግምት ነው። ግምት አይደለም ስሌት ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፡ ሻዕቢያ ያቋቋሟቸው ሌሎች ሀይሎች ማለትም ሕወሀትና ኢህአዴግ፡ በኤርትራዊያን ታጋዮች መታወርና አርቆ ማሰብ አለመቻል ምክንያት፡ የነሱ ሊሆን ይችል የነበረውን፡ የትልቋን ኢትዮጵያ ሀብት መቆጣጠርና መመንዘር፡ ኤርትራ ግን ባዶ እጇን መቅረቷ፡ ማስቆጨቱና ማንገብገቡ እንኩዋንስ ለኤርትራ መሪዎች፡ ለማናችንም የተሰወረ አይደለም። የኤርትራ መንግስት ዛሬ የወያኔ ስርአት የያዘው ስልጣን የሱ እንደነበር በማሰብ የቁጭት እድሜ እየገፋ እንደሆነ መመልከት ይቻላል። ዛሬ ኢህአዴግ የሚንደላቀቅበት ሁሉ የነሱ ነበር። ኤርትራዊያን ወይም የኤርትራ መንግስት ከዚህ ስህተታቸው አይማሩም፡ በመጪው ዘመንም በተቀረው ኢትዮጵያ ውስጥ በነጻነት መግባት መውጣት አለመቻሉ አይቆጫቸውም አይናፍቁትም ብሎ ማሰብ ይከብዳል። የዋህነትም ነው።

 

ሦስተኛ፡ በስጋት ውስጥ ላለመኖር፡ የምርጫ ማጣት

ከዚህ በኋላ ኤርትራ እንደ አገር ለመኖር ያላት አማራጭ እሷን አደጋ ላይ የማትጥላት፡ ኢትዮጵያን መፍጠር ወይም መጠፍጠፍ ነው። እኛ ደግሞ ይሄንን እስከተረዳን ድረስ፡ የኤርትራ ኢትዮጵያን እሷ በምትፈልገው ቦታ ለማስቀመጥ መጣር የምንፈልገውን እስክናገኝም ቢሆን የምንቀበለውና የምንችለው ነው። እንደኤርትራዊ ሳስብ፡ ኤርትራ ከተከፋፈለች ኢትዮጵያ ይልቅ፡ ያልተከፋፈለች ነገር ግን ከሷ ያልጠነከረች ወይንም እሷ እንደልቧ እየገባች እየወጣች የምትነግድባት ኢትዮጵያ ትሻላታለች። አንድ ነገር ግን ሀቅ ነው፤ ኤርትራን የሚያስመርጠን ምርጫ ማጣት ነው እንጂ ኤርትራ ምርጥ ምርጫ ሆና አይደለም። በኢህአዴግ ስር ከምንኖር ደግሞ የተሻለውን ክፉ መምረጥ ይሻላል። ይሄንን የኤርትራን ፍላጎት እስከተረዳነው ድረስ፡ በጥንቃቄና በሰለጠነ ተንኮል ከኤርትራ ጋር መስራቱ ምንም ክፋት የለበትም ብለን ባናቃልለውም፡ ፖለቲካ ማለት ባንድ በኩልም ያንድን ነገር ክፋቱን እያወቁም ቢሆን ሌላን ነገር ለማግኘት ሲባል ለክፋቱ መፍትሄ ሰንቆ እዚያ አደጋ ውስጥ መግባት ነውና፡ ከኤርትራ ጋር መስራቱ ምናልባት በደንብ ሊታሰብበት ሊመከርበት ይገባ ይሆን እንደሆን እንጂ፡ የምንሸሸው ወይንም አማትበን ወይም አኡዚብላህ ብለን የመንጠየፈው ሀሳብ አይደለም። በሌላ አነጋገር መጠየቅ ያለብን ጥያቄ፡ ከኤርትራ ጋር እንስራ አንስራ ሳይሆን፡ ከኤርትራ ጋር ስንሰራ አገራችን ላይ ሊመጣ የሚችለውን መጪ ስጋት እንዴት እንቋቋመው ነው። ማናቸውም አይነት ትግልና መንገድ ደግሞ፡ ከዚህ አይነት ጥያቄ የጸዳ አይደለም።

 

የተከፋፈለች ኢትዮጵያ ብትፈጠር፡ ኤርትራ ምን ትጠቀማለች? መቼም ኤርትራ ኢትዮጵያን ከፋፍላ፡ አማራው አንድ አገር፡ ደቡቡ አንድ አገር፡ ኦሮሞው ደግሞ ሌላ አገር ሆኖ፡ ኤርትራ አፋርንና አማራውን አልፋ ከኦሮሞና ከሶማሌ ጋር የሚያስነግድ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምቾት አይኖራትም። ልድገመውና፡ ለኤርትራ፡ እንደኤርትራዊ ካሰብነው፡ እነሱን የማታሰጋ ደከም ያለች ኢትዮጵያ ትሻላቸዋለች፡ ከተከፋፈለች ኢትዮጵያ። ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ኤርትራ ጸረ-ኢትዮጵያ እንደሆነች አድርጎ ማሰቡ አያስኬድም። ጎበዝ ኤርትራ ለኢትዮጵያ የምትጨነቅ ወዳጅ አገር ስለመሆኗ አይደለም የምንናገረው። ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የኢትዮጵያን መኖር ይፈልጉታል እንጂ። በመሰረቱ እኛም የምንጨነቀው ስለራሳችን አገር ጥቅም ነውና። እንጂ ኤርትራ ማዶ ተሻግረን ስንሄድ ለኤርትራ አስበን ሳይሆን ለራሳችን አስበን ነው።

 

አራተኛ፡ ከሁሉም በፊት ግን፡ ኢህአዴግን የጠላት ቁንጮ

መጀመሪያ ስለኢህአዴግ ያለን ግንዛቤ አንድ ወይም ተቀራራቢ መሆን አለበት። ኤርትራን እንደ አጋር ለማየት ከመወሰናችን ወይንም ከኤርትራ ጋር የመስራት ሀሳብ ላይ ከመምከራችን በፊት ስለሕወሀት/ኢህአዴግ ያለን እምነት ተቀራራቢ ካልሆነ፡ ቀድሞውንም በኤርትራ ጉዳይ ላይ መምከር የለብንም። ያው ሁላችንም ባመቸን እንጓዝ። ማለቴ ይሄ ባለፈው ሰሞን ኢህአዴግ ጠላት ነው አይደለም የሚሉት አይነት ክርክር ማለት ነው። ኢህአዴግ በኛ አስተያየት የጠላት ሁሉ ቆንጮ ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ በማናቸውም መልኩ መወገድ አለበት ብለን እናምናለን። ኢህአዴግና ሻዕቢያ ወዳጅ ነበሩ። አሁን ባለው ሁኔታ ግን አይደሉም። ላይታረቁ ተጣልተዋል። ደም ተቃብተዋል። ይሄንን ደም መቃባት መጠቀም አለብን ነው ስሌቱ። ሻዕቢያ ኢህአዴግን ለማጥፋት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። እኛም ኢህአዴግን ለማጥፋት የማንፈነቅለው ድንጋይ ከሌለ፡ እኛንና ሻዕቢያን የሚያገናኘን በጥንቃቄ ልንጠቀምበት የሚገባ የጥቅም ሰንሰለት ተፈጠረ ማለት ነው። ይሄም ሽቅብ ሽቅብ የሚል አሳብ ይሆን ይሆናል። ወያኔ ሽቅብ ሽቅብ በሚል ሀሳብ ነው አራት ኪሎ የደረሰችው።

 

ኤርትራ እንደነበረች ነች ብሎ ማመን ይከብዳል። የማይለወጥ ምንም ነገር የለም። አሁን ክፉውንም ደጉንም አይተውታል። አሁን ነጻነቱንም ባርነቱንም አጣጥመውታል። አሁን ምን ጠንካሮችና አዋቂዎች ብንሆን፡ ነገሮችን ሁልግዜ መቆጣጠር እንደማንችል አውቀነዋል። ለዚህ ደግሞ ከራሳቸው ከሻዕቢያና ከኢህአዴግ ታሪክ መማር እንችላለን። በእውኑ ሻዕቢያና ኢህአዴግ ለብዙ አመታት የተዋጉለት ታሪካዊ ሂደት በዚህ መልኩ ይቋጫል ብሎ የገመተ ነበረን? በእውኑ ዛሬ ወያኔና ሻዕቢያ እንዲህ ካለው ደም መቃባት ውስጥ ገብተው ይኖራሉ ብሎ ያሰበ አለን? የማይገለበጠው የኤርትራና የወያኔ ታሪክ እንዲህ በጭንቅላቱ ከተደፋ፡ ኤርትራዊያን አሁንም የሚያስቡት እንደጥንቱ ነው ብሎ ለማለት ይከብዳል። ሳይወድ በግድ ይለወጣሉ። ዓለምን የሚገዛው የለውጥ ሕግ ኤርትራና ሻዕቢያን ወይንም የነሱን የፖለቲካ ፍልስፍናም የማይጎበኝበት ምክንያት አይታየኝም።

 

የሀገር መነኩሴ፡ የሀገር ባህታዊ

እኛ ፖለቲካዊ እከክ ይዞናል። ኢኮኖሚያዊና ዴሞክራሲያዊ ረሀብ ተጠናውቶናል። ኤርትራም እንደዚያው። ኤርትራ የራሷ ጥቅም የራሷ ረሀብ አላት። እኛም የራሳችን ጥቅም አለን። ማንም አገር ለነፍሱ አይሰራም። የሀገር መነኩሴ የሀገር ባህታዊ የለውም። አሜሪካንም፡ እንግሊዝም አረቦቹም ለጥቅማቸው ነው የቆሙት። ኤርትራም እንደዚያው። በዚህ ሰአት እንደኤርትራዊ ካሰብነው ትክክለኛው የኤርትራ ጥቅም ያለፈ ስህተታቸውን አርመው፡ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንደ ጎረቤትም ይሁን እንደቤተኛ እየተናገዱና እየተስተጋበሩ መኖር ነው። ጠንካራ የኢትዮጵያን መንግስት በመፍጠር በስጋት ውስጥ መኖር አይፈልጉ እንደሆን እንጂ፡ ኢትዮጵያን ከመከፋፈልና ከማፍረስ ምንም ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደማያገኙ ግልጽ ነው። ኤርትራ የኢትዮጵያ አንድነት ያስጨንቃታል አይደለም እያልኩ ያለሁት። የራሷ ጥቅም እንደኔ እንደኔ እምነት ኤርትራ እሷን የማታሰጋት ኢትዮጵያን እንድትፈጥር ያስገድዳታል። ኤርትራ ለነፍሷ የምትኖር በባህታዊያን የምትገዛ የአገር ባህታዊ አይደለችም። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ማግኘት የምትፈልገውን ነገር ማወቅ ከቻልን፡ እኛም የምንፈልገውን ካወቅነው በጥንቃቄና በብልሀት ከተጓዝን፡ የምንፈልገውን ማግኘት እንችላለን። ይሄም ፖለቲካዊ እከካችንን ኢህአዴግን ማስወገድ ነው። ከዚያ በኋላ ያለው ይለያያል። የድሮዋ አይነት ኢትዮጵያ መፍጠር አይቻልም ባልልም፡ አያስኬድም። አሁን ነገሮች ተለዋውጠዋል። በፊት እድሜ ለኤርትራና ለወያኔ፡ አሁን እድሜ ለወያኔ የጥንቱ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት እንደነቃ ብርሌ ነው። ነቅቷል፡ ተሰነጣጥቋል። it is okay. አስፈላጊውን የብሄርተኝነት ማስተካከያና ማሻሻያ ማድረግ ነው። ያ ግን ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ አማርኛ ቋንቋን የትምህርት ቋንቋ መድረግን አይጨምርም። የኤርትራን አገርነትና ሉአላዊነት አምኖ መቀበል የግድ ነው። ኤርትራ በማንፈልገውና በሚዘገንነን መልኩ ሌላ አገር ሆናለች። አክትሟል። መልሳ በፈቃዷና በሂደት ካልመጣች በስተቀር።

 

እነ ኦነግንና ኦብነግን አስጠልላለችና አሁንም ጸረ ኢትዮጵያ አጀንዳዋን አልተወችም የሚል ክስ ይቀርብባታል፡ ኤርትራ። አሁንም ቢሆን እንደኢትዮጵያዊ ሳይሆን እንደኤርትራዊ እናስብ። እኛ ጎብዘን ጠንከር ያለ ድርጅት መፍጠር ካልቻልንና ካልተደራደርን በስተቀር፡ ኤርትራ ከኢህአዴግ ጋር ለገጠመችው ፍልሚያ የሚያግዟት ማናቸውንም ሀይሎች ማሰለፏ አይቀርም። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ወይም የነበራት ጸብ በ1991 አብቅቷል። አሁን ሌላ ምእራፍ ጀምረናል። ዘፍጥረትን አልፈነዋል። አሁን ዘጸአት ላይ ነን። ይሄ ኢሳያስ የመቶ ዓመት የቤት ስራ እንሰጣቸዋለን ብሏል፡ ምናምን የሚለውን ያንድ ወቅት ፉከራ ተዉት። ያው ከኛ እንዳንዱ ስለሆነ የተናገረው ይሆናል። ማለቴ ብሎ ይሆናል። መለስ ራሳችን ላይ ቁጭ ብሎ ስንት ጉድ እየተናገረ ዝም ብለነዋል። ሁለተኛ የሆነ ሰዓት ላይ ሁላችንም አፋችን በትእቢት ብዙ ነገር ይናገራል። በተለይ እኛ ኢትዮጵያዊያን ትእቢተኞች ነንና፡ የኛ የነበረው ኢሳያስ ትናንት ምንም ቢል ምንም አይገርምም። ከዚያ ባሻገር፡ አሁን ከኢህአዴግ ጋር ለገጠሙት ትቅንቅ ነው እነ ኦነግን ያስጠጉት። ጥግ ይዘን ለኤርትራ “እንዲህ አድርጊ ያለበለዚያ አሁንም እንዲህ ነሽና አንቺ ጋር አንጠጋም” አይሰራም። ጠንከር ብለን ሄደን ከተደራደርን ግን ነገሮች የማይለወጡበት ምክንያት የለም።

 

በርግጥ ፈታኝ ነው፡ ቀላልም አይደለም

በመሰረቱ ኤርትራ እንደነኦነግ ባሉ ውጤታማ ያልሆኑ ሀይሎች ደስተኛ እንደሆነች አስበንም መቀመጥ የለብንም። ኤርትራ እንደመጪ ኢትዮጵያዊ ጠንካራ ሀይል ሊደራደራት የሚችል ሀይል ከመጣ፡ በወያኔ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀልና መጪውን ዘመኗን ለማደላደል ስትል ከመደራደር ወደኋላ አትልም። ከወያኔ ጋር የተጋባቸው ፖለቲካዊ እልህ ማናቸውንም ፖለቲካዊ ምላጭ ያስውጣታል። እልህ ሲደመር ፖለቲካ ሲደመር ኢኮኖሚ ሲደመር ነባራዊ ሁኔታ ኤርትራን ከኛ ጎን እንድትሰለፍ ያደርጋታል። ኤርትራ እንደኢኮኖሚ ማህበረሰብ ሰርቫይቭ ለማድረግ የኢትዮጵያን ጉርብትና ትሻለች። በፖለቲካውም አንጻር ኤርትራ እንድትኖር፡ በሰላምና በመግባባት የምትጎራበታት ኢትዮጵያ ታስፈልጋታለች። (ይሄን ሀሳብ፡ ትንሽ ደጋገምኩት መሰል?) ከዚህ አንጻር ወያኔን የምትደቁስ ነገር እሷን የማታሰጋ ኢትዮጵያ ብትኖር ትሻለችች። በተጨማሪም የአንድነት ሀይሎች፡ ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር ለምናደርገው ውህደትና ስምምነት እንዲሁም አብሮ የመስራት ውል፡ ኤርትራ ጥሩ መደራደሪያና ጫና ፈጣሪ ልትሆን ትችላለች። ኤርትራ የምታስታጥቀው ኦነግ፡ ኤርትራ የምትመግበው ኦብነግ፡ ኤርትራ ያስጠጋችው ሲአን ኤርትራን አላደምጥም ሊል አይችልም። ርግጥ በሁለቱም በኩል ሊሰራ ይችላል፡ አሉታዊም አዎንታዊም በሆነ መልኩ።

 

የዚህ ከኤርትራ ጋር የመስራትን አሳብ ከሚቃወሙት ወገኖች የሚያቀርቧቸው ክሶች ወይም መከራከሪያ አሳቦች፡ ኤርትራ ከዚህ ቀደም በተለይ ባለፉት አርባ ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን ጦርነትና ኤርትራውያን የሰሯቸውን ሸፍጦች መሰረት ያደረገ አሁንም ያንን ታደርገዋለች የሚል ፍርሃት ወይም ኤርትራ ጠንካራና ራሱን የቻለ ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ እንዲኖር አትፈልግም የሚሉ ነአቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኤርትራ ጸረ-አንድነት ሀይሎችን አሰልፋለች፡ ኤርትራ የባህር በር ትነፍገናለች ወይንም እንዳይኖረን ታደርጋለች የሚሉ ክሶች ናቸው። አንዳንዶቹ ክሶች መሰረታዊና ጠንካሮች ሲሆኑ፡ አንዳንዶቹ ግን፡ ለምሳሌ መለስ ራሱ ኤርትራዊና ለኤርትራ የሚሰራ ቅጥረኛ ነው የሚለው፤ የሚያስቅና የትግራይን ሕዝብ በልጆቹ ሊመጣበት ከሚችለው መቅሰፍት ለመታደግ ሲባል ብቻ የተዘየደ እነመለስን አሳልፎ የመስጠት ዘመቻ ነው። እነዚህን ሁሉ ክሶች ሙሉ በሙሉ ማስተባበል አይቻልም። አንዳንዶቹን ጊዜ ካልሆነ በስተቀር እኛ አንመልሳቸውም። አብዛኞቹን ግን መዳሰስና በተወሰነ መልኩ መመለስ ይቻላል። በርግጥ ከኤርትራ ጋራ ብቻ ሳይሆን ከማንም መሰል አገር ጋር ብንጠለል የሚሰራ መሰረታዊ መርህ አለ። የቋሚ ወዳጅነት ጉዳይ። እንደይሰሙኝ እንጂ፡ ከኤርትራ ጋር አሁንም እግራችንን ለማሳረፍ ያህልና የምንፈልጋትን እስክናገኝ በብልጠት እንስራ ካላልን፡ እንደው የለት ለተቱ ካልሆነ በስተቀር ቋሚ ወዳጅነትን መመስረት እንችላለን ብሎ በእርግጠኛነት መናገር አይቻልም። የሆነ ቦታ ላይ የኤርትራና የኢትዮጵያ ፍላጎት መጋጨቱ አይቀርም። ይሄ አሁን አይጠቅመንም።

 

ኤርትራ ድልድይም ነች፤

ኤርትራ ከሌሎች ኢህአዴግን ከሚጠሉ አገሮች ጋር የምታገናኘን ድልድይ ነች። ዛሬ በተለያየ ምክንያት ከወያኔ አስተዳደር ጋር ተጣልተው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ያቋረጡ አገራት ብዙ ናቸው። ከነዚህ አገሮች ጋር ግንኙነት ለመፍጠርና መንቀሳቀሻ እርሾ ለማግኘት በአገር ደረጃ ካልቀረብናቸውና ዲፕሎማሲያዊ ሽፋን ካላገኘን በስተቀር፡ ካገር አገር መንቀሳቀሱና መስራቱ ቀላል አይደለም። በሽብርተኝነትና በሽፍትነት መፈረጅ ይመጣል። ዛሬ እነ አረብ ኤሚሬትስን ሌሎች መሰል አገሮችን መጠቀም ከፈለግን ኤርትራ ብቸኛ መንገድ ነች። ማለቴ ልክ ትናንት እነሱ ደርግን ወይም ሀይለስላሴን ያዩ እንደነበረው መለስና ድርጅቱን እንደጠላት የምንመለከት ከሆነ ማለቴ ነው። ልብ አድርጉ፡ ለነ ብርቱካን ሚደቅሳ ለነሀይሉ ሻውል ወይንም መራራ ጊዱና አይደለም የምጽፈው። ማርያምስ መልካሙን መረጠች ይላል መጽሀፍ። ብርቱካንና ሌሎች ታጋዮች መልካሙን መንገድ መርጠዋል። ከነሱ ባሻገር ላለነው ሰዎች ነው የምጽፈው። የነ ብርቱካንን መንገድ ላልመረጥነው።

 

በዚህ ሰዓት ከኤርትራ ውጪ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች ሊያስታጥቅ የሚችል ምንም መንግስት የለም። መለስ፡ በዓለም ፊት ያለው ቦታ፡ በተለይም በአፍሪካ፡ የተከበረ ነው። ወራዳነቱንና ትናንት ማን እንደነበር፡ ልቡንና ሀሳቡን፡ ስስ ብልቱንና መጥፊያውን አጥርተው ሊያውቁ የሚችሉት ከዓለሙ ሁሉ የሚንቁት ኤርትራዊያን ብቻ ናቸው። በዚህ ይመጣ በዚያ፡ ምንስ ያስባል፡ የሚለውን ያውቁታል። ዛሬ የአውሮፓም ይሁን የአሜሪካ መንግስታት እንደስደተኛ ያስጠጉን እንጂ፡ እንደ ሽምቅ ተዋጊ ሊያስጠጉን አይከጅሉም። መለስ በምስራቅም ከቻይና በምእራብም ከአሜሪካ ሽርክ ነው። አንዱ አንዱን ካላጠፉ በስተቀር፡ ሽርክናው በማይጠገንበት መልኩ የተሰበረው በሰሜን ብቻ ነው። በኤርትራ። የመለስ ድህነቱም ሞቱም በሰሜን ነው። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ማለቴ ኢህአዴግ፡ የኤርትራን ተቃዋሚዎች እንደጉድ እየረዳና እያደራጀ ነው። በዚህ ሰዓት ከዓለሙ ሁሉ እኛን ለማስጠጋት የተለየ ጥቅም፡ ምክንያት እና ምኞት ያለው ኤርትራ ብቻ ነው። ሁሉም ነገር ወደኤርትራ።

 

ሌላው ምክንያት፡

ከኤርትራ መስራት አይቻልም ብለው የሚያምኑት ወገኖች የሚያቀርቡት ብቸኛ፡ ምንም ተጨማሪ የሌለው ምክንያት፡ “ኤርትራ ለኢትዮጵያ ጠንቅ ነች፡ ኤርትራ ወይም ሻዕቢያ ኢትዮጵያን ሊያጠፋ ቆርጦ የተነሳ ከወያኔ የባሰ ሀይል ነው” የሚል ነው። ያ ሁሉ እውነት ነበር። አሁን ግን ተቀይሯል። ወደፊት ደግሞ የበለጠ እየተቀየረ ይሄዳል። በመሀከል በተፈጠረው ታሪካዊ ክስተት ምክንያት “ዛሬ ወዳጅ ነች” ብዬ ባምንም ኤርትራ “ወዳጅ ነች፡ ጸረ-ኢትዮጵያ” አይደለችም ብዬ ላሳምናችሁ አልሟገትም። በርግጥም አሁን ባለው ሁኔታ፡ ኤርትራ/ሻዕቢያ ለኢትዮጵያ ጸር እንደነበር የሚያሳየው ወገን ሚዛን ይደፋል። ያንን ሁሉ ማስረጃ ለመናድ በመጣር ጊዜም ጉልበትም አልፈጅም። አንድ ብቸኛ መልስ ግን አለ። ሻዕቢያ አስመራ ወያኔም አራትኪሎ የገቡት፡ የገቡት ብቻም አይደለም፡ ተደላድለውም የተቀመጡት፡ ያም ብቻ አይደለም አፈር ድሜ የሚያስግጡን፡ ጸረ-ኢትዮጵያ ሀይሎችን ተደግፈው ነው። እነ ሱዳን፡ እነ ኢራቅ፡ እነ ግብጽ፡ እነ ሊቢያ የኢትዮጵያ ወዳጆች መሆናቸው ነውን? ሻዕቢያና ወያኔ በጸረ-አትዮጵያ ሀይሎች ተደግፈው ደርግን ድል ማድረግ ከቻሉ፡ እኛስ ባንድ ወቅት ጠላት ከነበረ ሐይል ጋር አሁን ግን “ወዳጅ ከሆነች”፤ እሺ ይሁንላችሁ “አጋር ልትሆን ከምትችል” ኤርትራ ጋር፡ አይደለችም እንጂ ብትሆንስ፡ ጸረ-ኢትዮጵያ ከሆነች ኤርትራ ጋር ተወዳጅተን ጸረ-ኢትዮጵያ የሆነውን ወያኔን ብንወጋ ችግሩ ምንድን ነው? ምንም። ለነገሩ እንዲህ አይነቱ ሀሳብ የግድ በህዝብ መደገፍ የለበትም። በጥቂቶች እንጂ። በሕዝብ የተደገፉ ሀሳቦች ያሸነፉበት ቀን ትዝ አይለኝም ወይም ትቂት ነው። በኛም ባለም ታሪክም።

 

ፀሎቴ፡ ስለቴ፡ ሻዕቢያን ጠብቅልኝ፡ ግንቦት ሰባት ፍጠን

ጸሎቴ ሁሉ አንድ ነው፤ እባክህ አምላኬ የኢሳያስን እድሜ አርዝምልኝ። ወያኔ/መለስ ኢሳያስን ድል አድርጎ ያደረ እለት፡ ያኔ የኛ መለስን በኛ ካላንደር የመጣል ተስፋችን አብሮ ሞተ ማለት ነው። ከዚያ በኋላ መለስ ቢወድቅም/ቢለወጥም እንኳን፡ አድዋን አውርዶ አዲግራትን ወይም አክሱምን ወይም ሌላ የህወሀት ከባድ ጡንቻን መስቀል ይሆናል ነገሩ። ሰዎቹን ከቆነጠጡበት ሊነቅላቸው የሚችለው፡ ጥፍራቸውንና ምሳቸውን ጠንቅቆ የሚያውቅ አጋር፡ ኤርትራና ሻዕቢያ ነው። ሕዝባዊ አመጽ? ምናልባት ሊሰራ ይችላል። በሀያልና ጠንካራ ወዳጅ ያልተደገፈ ሕዝባዊ አመጽ የትም እንደማያደርስ፡ ሀምሳ ሀምሳ እየሰዋን ወደቤት ተመልሰን ገብተን አይተነዋል። ጎበዝ ከኤርትራ ጋር እንስራ። ግንቦት ሰባት፡ ይሄን የኤርትራን ጉዞ በደንብ ግባበት። እስካሁን ያየነው ሁሉ ያው ከዚህ በፊት እንዳየነው ነው። ትንሽ ለየት የሚያደርገውና ከኢትዮጵያ የሚያደርሰን፡ ኤርትራ ነው። ለኢትዮጵያ፡ መዳን በኤርትራ በኩል እንጂ በየትም አይደለም። ግን ሀሳብ ነው። በሀሳቡ ላይ ብቻ ሀሳብ ስጡበት፤ “ከኤርትራ ጋር መስራት ይቻላልን?” መጀመሪያ ግን ተረጋጉ።

 

አባኪያና ጓደኞቹ ነን ከካናዳ - ነኀሴ 2000 ዓ.ም.

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!