TPLF-EPRDF meeting

ወያኔ/ኢሕአዴግ

ሸንቁጥ አየለ

የሲቪል ሕግ ሥርዓት (civil law system) የሚከተሉ አገራት በአብዛኛው የሚካፈሉት የወንጀል ሕግ ጽንሰ ሐሳብ የበላይ አለቃህ ወንጀል እንድትሠራ ቢያዝህ ወንጀሉን እስከሠራኸው ድረስ ወንጀለኛ ነህ። ወንጀል እንድትሠራ አለቃህ ሲያዝህ እንቢ በል። የአለቃህን ትዕዛዝ ተቀብለህ ወንጀሉን የሠራኸው እንደሆነ ወንጀለኛ ነህ። በአለቃህ ማሳበብ አትችልም በማለት ያብራራል።

ኢሕአዴግ የሚባለው ድርጅት ውስጥ የተሰበሰቡ እና ተሰብስበው የነበሩ ወንጀለኞች ትንታኔያቸው ሁሉ ያስገርማል። ወያኔ የሚባለው ርኩስ መንፈስ ያለበት ኃይል ስለሆነ የሚያዘው በአገሪቱ የሚሠራው ወንጀል እና ኃጢአት ሁሉ የወያኔ ነው ይሉሃል። እነሱ በወያኔ መረብ ውስጥ ሆነው እና የወያኔን ዐይነት ወንጀል እየሠሩ ወያኔን ብቻ ከሰው እራሳቸውን ከደሙ ነጻ ያወጣሉ። በርግጥም የሚያሞኙት አላጡም።

ሰሞኑን 60 ሶማሌዎች በኦሮሚያ ክልል ተጨፍጭፈዋል። ለዚህ ወንጀል ተጠያቂው ማን ነው? እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በርካታ የአማራ ማኅበረሰብ ላይ በኦሮሚያ ውስጥ የጭፍጨፋ እርምጃ እየተወሰደባቸው ነው። ተጠያቂው ማን ነው? ወያኔ ብቻ?

ከወራት በፊት በግማሽ ሚሊዮን የሚቆጠር የኦሮሞ ሕዝብ ከሶማሌ ክልል በአንድ ጊዜ እንዲፈናቀል ተደርጓል። የተገደለው ምን ያህል እንደሆነ ከፈጣሪ በቀር የሚያውቅ የለም። ጋምቤላ ክልል ላይ በአኝዋኮች ላይ ምን ተደረገ? ደቡብ ክልል ላይ በአማራ ላይ ምን ተፈጸመ? አሁንም በመላ አገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ምን እየተከናወነ ነው? ተማሪዎቹ የሚጨፈጨፉት በማን ነው?

ለዚህ ሁሉ ወንጀል ማን ነው ተጠያቂው? ሕወሓት ብቻ?

እያንዳንዱ ኢሕአዴግ የሚባል ወንጀለኛ ኃይል ውስጥ የተሰባሰበው ነው። ኦሮሞዎች ሲገደሉ በሶማሌ ክልል መሪዎች ብቻ መለጠፍ አይቻልም። ወይም በሕወሓት ብቻ ማሳበብ አይቻልም። ሁሉም የኢሕአዴግ አካል እና አመራር ሁሉ ተጠያቂ ነው። ኦሮሞን እመራለሁ የሚለው ኦሕዴድ ጭምር ተጠያቂ ነው። ጎሰኝነትን፣ ጥላቻን እና መከፋፈልን ከወያኔ ተምረው እና ከወያኔ ጋር ሆነው ኢትዮጵያን ያመሷት ሁሉ ወንጀለኞች ናቸው።

አማራዎች ሲገደሉ ጣትን ወደ በደቡብ ክልል መሪዎች ወይም በኦሮሚያ ክልል መሪዎች ወይም በሕወሓት መሪዎች ላይ ብቻ መቀሰር አይቻልም። ሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እና አመራሮች ተጠያቂ ናቸው። ብአዴን የሚባለው አማራን እመራለሁ የሚለው ድርጅት ጭምር። ሌላው ቀርቶ ዛሬ በስደት አገር እንደ ተቃዋሚ እንገፍ እንተፍ የሚሉት ቁዝር የወያኔ ድርጅት መሥራች የነበሩ ወይም ወያኔን ለአስራ አምስት ዓመታ እና ለሃያ ዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩ እና ትናንትና በአማራ ሕዝብ ላይ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ሲያሰራጩ የነበሩ ሁሉ ወንጀለኛ ናቸው። በምድር የሚፈርድ አካል ባይኖርም ሕጉ ቀድሞ ፈርዶባቸዋል ከሕጉ ፍርድ በሃልዎት አያመልጡም። የሰው ሠራሹ ሕግ ባይፈርድባቸውም እንኳን የአምላክ ሕግ ይፈርድባቸዋል እና። ንጉሥ ዳዊት ብዙ ሚስቶች እያሉት የሚስኪኑን ሰው አንድ ሚስት በማማገጡ ብሎም ያንኑ ምስኪን በወንጀል በማስገደሉ እግዚአብሔር ቀጥቶታል። አልታይም ብሎ ወንጀሉን ቢሠራውም ሁሉን የሚያይ አምላክ ከፍርድ አልዘገየም።

የኢትዮጵያን ሕዝብ ያጋደላችሁ፣ ያስገደላችሁ፣ ከወያኔ ጋር የተባበራችሁ፣ ወያኔን እያገለገላችሁ ያላችሁ፣ ዘረኝነት በመዝራት ኢትዮጵያ ከምድረ ገጽ ትጠፋ ዘንድ የሠራችሁ ሁሉ ከፍርድ እንደማታመልጡ አትርሱት። በሰው ባይሆን በእግዚአብሔር ትቀጣላችሁ። ሌላው ቀርቶ አንዱን ወንጀለኛ ከሳችሁ አንዱን ወንጀለኛ የምታጀግኑ እውራኖች ሁሉ ከፍርድ አታመልጡም። ወያኔን ኮንኖ ኦሕዴድን ማንገሥ፣ ወያኔን ደግሞ ብአዴን ከፍ ከፍ ማድረግ፣ ወያኔን ኮንኖ ደሕዴንን ማወደስ ሁሉም ወንጀል ነው። ከወንጀለኛ አካላት ትዕዛዝ እየተቀበሉ ሕዝባችንን የሚያሳርዱ ናቸውና። ሕዝባችን በልዩ ልዩ ቦታ ሲታረድ ወንጀልን አልተቃወሙምና።

ዛሬ አንዳንድ ተንታኝ ነን የምትሉ ወይም ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ነን የምትሉ በብልጠት እና በማምታታት አንዱን ወንጀለኛ ከሌላው ወንጀለኛ ለማጋጨት ብለን ነው አንዱን ኮንነን ሌላውን የምናወድሰው ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ወይም አንዳንድ ሰዎች ኦሮሞ ስለሆኑ የኦሮሞ ወንጀለኛ ኦህዴዶችን ለማጀገን ወይም አማራ ስለሆኑ የአማራ ድርጅት ተብሎ የተሰየመውን የብአዴን ወንጀለኞችን ለማጀገን ደፋ ቀና እያሉም ሊሆን ይችላል። ሆኖም ወንጀል እና ወንጀለኝነትን በሕዝባችን ሕሊና ውስጥ እየዘራችሁ፣ ወንጀል እና ወንጀለኝነትን ሕዝቡ እንዳይጸየፍ እያበረታታችሁ ብሎም ኢትዮጵያውያንን እያሳረዱ ያሉትን ወንጀለኛ ኃይሎች እንደ ብሔራዊ ጀግና እየሰበካችሁ ነውና፤ በሰው ባይሆን በሰማይ አምላክ መቀጣታችሁ አይቀርም። እግዚአብሔር ሐሰትና ወንጀለኝነትን መጸየፉን ብታምኑም ባታምኑም እውነታው ግን በሰማይ ሕግ ወይም በምድር ሕግ አለዚያም በሁለቱም መጠየቃችሁ እንደማይቀር አለመረዳታችሁ አሳዛኝ ነው።

ዛሬ 60 የሶማሌ ማኅበረሰብ አባላት ሲታረዱ ለምን ብአዴን አይቃወም? ለምን ኦሕዴድ አይቃወምም? ትናንት ኦሮሞዎች፣ እንዲሁም አማራዎች ሲጨፈጨፉ ሁሉም እያዩ ዝም የሚሉት ምን ስለሆኑ ነው? ወያኔ ብቻ ተጠያቂ ነው ማለት አይቻልም። አንድ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት ወይም አንድ የኢሕአዴግ አባል ግለሰብ ጉልበት ባይኖረው ተሰሚነት ባይኖረው ወይም ጮሆ የሚሰማው ቢያጣ የሚሠራውን ወንጀል አውግዞ እስከዛሬም ከወንጀለኛው ኢሕአዴግ ጋር በመሠራቱ ወንጀለኛ መሆኑን አምኖና ለሠራውም ወንጀል ሕዝብን በይፋ ይቅርታ ጠይቆ ከድርጅቱ ለቆ መጥፋት ይችላል። አንድ ሰው ወንጀል ለማውገዝ ከርሱ ጎሣ ላይ ወንጀል እንዲሠራ መጠበቅ የለበትም። ጎሠኝነት በራሱ ወንጀል ነው። ጎሠኝነት ማለት ሕዝብን መለያየት፣ የኔ ወገን ባቻ ይድላው፣ ሌላው ይጥፋ፣ ወይም ደግሞ የኔ ጎሣ እስካልጠፋ ድረስ የሌላው ጎሣ ቢጠፋ አይመለከተኝም ብሎ ማሰብ ነው።

ስለሆነም እነዚህን ወንጀለኞች ተስፋ አድርጋችሁ ወንጀለኛውን ወያኔን ለመቃወም ወንጀለኞቹን ኦሕዴድን እና ብአዴን ለማንገሥ የምትንጠራወዙም ያው ወንጀለኛ ናችሁ። ኢትዮጵያን የናንተ የተምታታ እና የተሳከረ ትንታኔ አያድናትም። የምትድን ከሆነ እውነትን የሚፈርድ እግዚአብሔር ያድናታል እንጅ። ወያኔን ከነ ሰንኮፉ፣ ከነ ተባባሪ ወንጀለኞቹ እና ከሐሳብ ተጋሪዎቹ ጋር ሁሉ ነቅሎ መጣል እና የኢትዮጵያን ሕዝብ እውነተኛ ሰላም እና ዴሞክራሲ እንዲያገኝ ለማድረግ ቁርጥ እና ጥርት ያለ ትግል ማድረግ ሲገባ፤ አንዱን ወንጀለኛ በሌላው ወንጀለኛ ለመተካት የምታሽቃብጡ ሁሉ የሕዝብ ጠላት እና ወንጀለኛ መሆናችሁን ሕዝብ በአርምሞ እያስተዋለ በልቡ እንደሚያዝን እንዳትዘነጉት።

አሁንም የራሳቸውን ጎሣ ጥቅም እና ፍላጎት ብቻ በማስቀደም የሚራወጡ የወያኔ ተባባሪ ኃይላት፣ በኢሕአዴግ ድርጅት ውስጥ በግንባር አባልነት የተሰገሰጉ ድርጅቶች ሁሉ ወንጀለኛ፣ የኢትዮጵያ የጥፋት ምንጭ ናቸው። በነዚህ ኃይሎች ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተገፍቶ ተገፍቶ አሁን ለደረሰበት የሰቆቃ እና የመከራ ዘመን የበቃው። እነዚህ ወንጀለኞች አንዱን ካንዱ የተሻለ ለማድረግ የምትራወጡ ሁሉ ያው ወንጀለኛ ናችሁ። እናም ታጋይ ከሆናችሁ ትግላችሁ ጥርት ያለ እና ወያኔን ከነ ሰንኮፎቹ እና ተባባሪ ወንጀለኞቹ የሚነቅል ይሁን። የሐሳብ አቀንቃኝም ከሆናችሁ የሐሳባችሁ ፍሰት ጥርት ባለ እውነት፣ ሰብአዊነት እና ዴሞክራሲያዊነት ላይ ይጽና። ኢትዮጵያ እንድትድን ከፈለጋችሁ እውነትን፣ ፍትሕን፣ ዴሞክራሲያዊነትን እና ሰብአዊነትን ብቻ ተስፋ አድርጉ። ለዚህም ሐቅ ብቻ ተዋደቁ። 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!