ፍቅር ወርቁ

የአፍሪካን ታሪክና ፖለቲካ ከምታስተምርበት ከሀገረ አሜሪካ ... ዩኒቨርሲቲ፤ የወቅቱን የሀገራችንን ፖለቲካዊ ትኩሳት መሠረት አድርገህ ያስነበብከውን ድንቅ ጽሑፍ/ታሪካዊ ትንታኔ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ድረ-ገጽ ላይ አነበብኩት። በእውነት ይበል የሚያሰኝ ነውና እባክህ ብዕርህ አይንጠፍብን። እንደው ይኸው ጽሑፍህን መሠረት አድርጌ በታሪካችን ዙሪያ ባሉ ውርክቦች ላይ አስተያየት አዘል የሆኑ ጥቂት ሐሳቦችን ለማንሳት ወደድኹ። ለወጋችን/ለሐሳቤ ማዋዣ ይሆን ዘንድ አንድ የቆየ ክስተት/ገጠመኜን በማስቀደም ልጀምር።

ከዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለን 'የታሪክ ተማሪዎች ማኅበር' ለማቋቋም አንድ እንቅስቃሴ ተደርጎ ነበር። ታዲያ የዚህ እንቅስቃሴ አስተባባሪዎች የማኅበሩን ምሥረታ ለማብሰር በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የምንገኝ የታሪክ ተማሪዎችን በማሰባሰብ በ6 ኪሎ ግቢ ውስጥ አንድ ስብሰባ ተደርጎ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይም ዕውቁ፣ አንጋፋውና ትሑቱ የታሪክ ምሁር፣ ሊቅ ፕ/ር መርዕድ ወ/አረጋይ በክብር እንግድነት በመካከላችን ተገኝተው ነበር። እንደማስታውሰው ከትምህርት ክፍሉ ከተገኙት የታሪክ መምህራን መካከል ብቸኛው፣ ተጋባዥ ሰው እርሳቸው ብቻ ነበሩ።

ታዲያ ስለ ታሪክ ማኅበሩ ምሥረታና ስለ ሕይወት ልምዳቸው እንዲያካፍሉን በአክብሮት በተጋበዙበት በዛ መድረክ ላይ ፕ/ር መርዕድ - ከጥልቅ እውቀታቸው፣ በዕድሜና በእውቀት ካካበቱት በሳል የሕይወት ልምዳቸውና አስተውሎታቸው የተቀዳ ድንቅ ምክራቸውን በተስፋና በቁጭት መካከል በሚዋልል ስሜት ውስጥ ሆነው በዕንባ ጭምር ታጅበው ነበር ያካፈሉን። ከፕ/ር ንግግር ውስጥ የማስታውሰው - በሀገራችን ሥርዓት በተለዋወጠ ቁጥር (በተለይ የደርግን ሥርዓት በማንሳት) የኢትዮጵያን ታሪክ በማስተማር ረገድ በጊዜው ያጋጠማቸውን ብርቱ ፈተና/ተግዳሮት በማስታወስ እንዲህ ነበር ያሉን።

በወቅቱ አሉ ትሑቱ ምሁር ፕ/ር መርዕድ፤ "በወቅቱ ለምን የታሪክ ትምህርትን ለማጥናት መረጥኩ እስክል ድረስ - ክቡር የሰው ልጅን ሰብአዊነቱን፣ የመንፈስ ልእልናውን የሚጋፋና አካዳማዊ ነጻነትን ቅርቃር ውስጥ የሚያስገባ ፈተና ነበር የገጠመኝ ..." ቋንቋ ያለው በሚመስል ጥልቅ ዝምታ ውስጥ ጥቂት ከቆዩ በኋላ ፕ/ር ሳግና ሲቃ በተቀላቀለበት ድምፅ... "በሀገራችን ታሪክ ጥያቄ ውስጥ እየወደቀ ነው ... ተማሪዎች እንግዲህ በርቱ፤ ተስፋ አትቁረጡ፣ ሊገጥማችሁ የሚችለው ማንኛውም ፈተና ከሒደታችሁ እንዳይገታችሁ፤ በሚያስፈልጋችሁ ሁሉ ድጋፌ አይለያችሁም፣ በርቱ እንግዲህ ልጆቼ...።" የዛን ጊዜው የአንጋፋው ምሁር፣ የፕ/ር መርዕድ ንግግር አጭር ግን ደግሞ ነጎድጓድና መብረቅ፣ ውሽንፍር የታከለበት የሚመስል፣ አንዳንች የቁጭት፣ የብሶት ስሜት አብዝቶ የሚንጠውና በመጪው ዘመናችን ታሪካችንና የታሪክ ሙያ እንዴት ያለ ፈተና ውስጥ እየገባ እንዳለ ቀድሞ ያየ፤ ያስተዋለ ነበር።

አዎ ግና ያ ብዙ ተስፋ የተደረገበት የታሪክ ተማሪዎች ማኅበር የአንደኛ ዕድሜ ዓመቱን የልደት ሻማውን እንኳን ለመለኮስ አልታደለም ነበር። እናም በአጭር ተቀጨ። ፕ/ር መርዕድ እንደፈሩት ማኅበሩ በጊዜው ባጋጠመው ፈተና ተሰናክሎ፣ በነበር 'ታሪክ' ሆኖ መቀረት ብቸኛ ዕጣው ፈንታው ኾነ። ከማኅበሩ መፍረስ በኋላም የፕ/ር መርዕድ ያ እንባቸው የታሪክ ማኅበሩ ገና በሽል ላይ እያለ በአእምሮአችን ማኅፀን ውስጥ ሾተላይ የሚያጨናግፈው መሆኑን አስቀድመው አይተው ኖሮ በኀዘኔታና በቁጭት ስሜት መርዶአችንን ቀድመው የገለጹበት ትንቢታዊ ዕንባ አድርገን ነበር የወሰድነው፤ የተረዳነው።

በነገራችን ላይ ሽመልስ ከሁለት ዓመት በፊት ይመስለኛል በዛው በአሜሪካ ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ሱራፌል ወንድሙ እኚህን በአፍሪካና በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ታሪክ ላይ ጥልቅ የሆነ ሰፊ እውቀት ያላቸውን ምሁር - ፕ/ር መርዕድን የሙት ዓመት መታሰቢያ አስታውሶ፣ ታሪካቸውንና ሥራቸውን የሚዘክር አንድ የድንቅ የሆነ ዝግጅት በአዲስ ዜማ የሬዲዮ ሾው ፕሮግራም ላይ አቅርቦልን ነበር። ታዲያ በወቅቱ ስለ መምህራችን ፕ/ር መርዕድ ወ/አረጋይ የተማሪነት ትዝታዬንና ይህን ትውስታዬን በአጭሩ አንዳጋራውት አስታውሳለሁ። በአጭር ቃል እርሳቸው (Prf. Mered, he was really a genius for History, humble & truly a Professional Historian.)

ሽመልስ ይህን ከዓመታት በፊት በግቢያችን በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተማሪዎች ማኅበር በማቋቋም ሰበብ የሆነውን ክስተት ያነሣሁልህ የሀገራችን ታሪክና የታሪክ ባለ ሙያዎች በኢትዮጵያ ምድር እየተጋፈጡት ያለው አበሳና ፈተና ምን ያህል የበረታ እንደሆነ በጥቂቱ ለማስመር ፈልጌ ነው።

ዛሬ ዛሬ እንደምንታዘበው በታወቀ ምክንያት የኢትዮጵያ ታሪክ አወዛጋቢነት ቀጥሏል፡፡ "ታሪክ የሞተ ፖለቲካ ነው፤" የሚለው አባባል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አይሠራም፡፡ ይልቁንስ "ታሪክ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም ሊቀጥል የሚችል ፖለቲካ ነው፤" በዘመናችን በስሜት በሚነዳ የዘውግ (የዘር፣ የጎሣ) ፖለቲካ ውስጥ ታሪክ ትልቅ ማገዶ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እንዲህ ባሉ የታሪክ ውርክቦች ውስጥ ይበልጥ አትራፊው ኃይል ማን መሆኑን ደግሞ እያየን ነው። ታሪክ የአሸናፊዎች ደንገ-ጡር በሆነችባት ኢትዮጵያ ገዥዎች በየዘመናቸው ለአገዛዛቸው በሚያመቸው መልኩ ታሪክን በርዘውና ከልሰው ሲያቀርቡ በሌላ በኩል ደግሞ ታሪክን ሳያላምጡ የሚሰለቅጡ ደቃቅ "ፖለቲከኞች" አስፈሪና አሳፋሪ በሆነ መልኩ እጅጉን በርክተዋል፤ ተበራክተዋል፡፡

የታሪክ ሊቃውንቱ "ታሪክ የትውልዶች መገናኛ ድልድይ ነው፤" ሲሉ ቢደመጥም፤ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ታሪክ የትውልዱ የልዩነት ማስመሪያ ቀይ ቀለም ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ለዘውግ ፖለቲካ ማፋፋሚያ ዓይነተኛ ማገዶ እየሆነ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ በኋላ ታሪክ ለየዘውጉ (በ"ጨቋኝ"፤ "ተጨቋኝ" ትርክት) ዘውጋዊ ንቃት መፍጠሪያነት እንጂ ከዚህ በተሻገረ መልኩ የአገራዊ ውህድ ህላዌ መጋቢና ደጋፊ ሆኖ ሲገለጽ አይስተዋልም፡፡ እናም የኢትዮጵያ ታሪክ አተራረክ በአጥቂነትና በተከላካይነት የሚበየን የውዝግብ መድረክ ሆኗል፡፡ የአንድ ዘውግ ጉዳይን ሁልግዜ በተጠቂ ስሜት፤ ሌላኛውን ዘውግ በአጥቂነት የማየት ዝንባሌም በታሪክ ትንተና ውስጥ ማየት የተለመደና የሚመረጥ አካኼድ ሆኗል፡፡ ከታሪካችን የሚያግባባንን ማግኘትም ተስኖናል፡፡ ጭራሹን ጉልህ የልዩነታችን መስክ ሆኖ ቀርቧል፡፡ የአገራዊ የጋራ ማንነታችንና የብሔራዊ እሴቶቻችን ንጣፍ መሠረት ሊሆን የሚችሉ ነገሥታቶቻችንና የትናንትና የጋራ ታሪካችን በዚህን ያህል መጠን የልዩነታችን ቀይ መስመር አስማሪ መሆናቸው የሰከነ የውይይት ባህል እየራቀን ለመሄዱ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

እናም እንዲህ የትናንትና ታሪካችን እንደ አስፈላጊነቱና አዋጭነቱ እየተመነዘረና እየተጠመዘዘ፣ እየተቀሸበና እየተኳሸ ለዘመናችን የፖለቲካ ቁማርተኞች ዋንኛ መጫወቻ ካርድ በተደረገበት፤ ታሪክና የታሪክ እውቀት የትናንትናውንና የዛሬውን ትውልድ አፋጦ፣ "በላ ልበልሃ - ተጠየቅ" በሚል ስልት ፍርድ ቤት በመሰለበት፣ ታሪካችን ሙግትና እሰጥ-አገባ ያየለበት በሆነባት በሀገራችን ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱ ሚዛናዊ የሆነ አስተውሎት የተሞላበት ሙያዊ የሆነ የታሪክ ትንታኔ - ታሪክን በተመለከተ ውዥንብር ውስጥ ለገባነው ለብዙዎቻችን ጠቃሚ ነው እላለኹ። አበው በታሪክ ዙርያ ዘመን ያልሻረው አንድ ድንቅ የሆነ አባባል አላቸው። እንዲህ ይላል፤ "ታሪክን በሚገባ የመረመረና የተማረ፣ አዋቂ ሰው ላለፉት ትውልዶች ባልንጀራ፣ ለራሱ ትውልድ መምህር ለመጪው ትውልድ ደግሞ ነቢይ ነው።" እንዲሉ፤ እናም ዶ/ር እንዲህ ዓይነቱ አስተማሪና ቆም ብለን ታሪካችንን በቅጡ እንድንመረምር፣ እንድንፈትሽ የሚያተጉ በሳል የሆኑ ታሪካዊ ትንታኔ የታከለባቸው ጽሑፎችህ እንደሚቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ።

ሰላም!!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!